“መዳናችን ቀርቧል!” የተባለውን የአውራጃ ስብሰባ
ለማስተዋወቅ የሚደረግ ዓለም አቀፍ ዘመቻ በሁሉም ጉባኤዎች የሚገኙ አስፋፊዎች ልዩ የመጋበዣ ወረቀት ያሰራጫሉ
1 በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ በ2006 የጸደይ ወራት የሚጀምረው የአውራጃ ስብሰባ በመላው ዓለም በተከታታይ ይካሄዳል። አንድ መቶ ሃምሳ አምስት በሚያህሉ አገሮች የሚካሄደውን ይህን የአውራጃ ስብሰባ ለማስተዋወቅ ዓለም አቀፍ ዘመቻ ይደረጋል። ዘመቻው፣ ከሐምሌ አንስቶ እስከ ነሐሴ 2006 የመጀመሪያ ሳምንት ድረስ በጀርመን፣ በቼክ ሪፑብሊክና በፖላንድ የሚደረጉ ልዩ የአውራጃ ስብሰባዎችን ማስተዋወቅንም ይጨምራል።
2 የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ማብቂያ ላይ እንደመሆኑ መጠን አምላክ ሰዎችን ከዚህ ክፉ ዓለም ለማዳን የሰጠውን ተስፋ ጎላ አድርገው የሚገልጹት እነዚህ ስብሰባዎች ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ ሰዎችን በእጅጉ እንደሚማርኳቸው እሙን ነው። የስብሰባው መልእክት ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል። ይህን አጽናኝና ተስፋ ሰጪ መልእክት ብዙ ሰዎች እንዲሰሙ ለማድረግ ሲባል ከ98,000 በላይ በሆኑ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባውን በማስተዋወቁ ዘመቻ ላይ በቅንዓት ይካፈላሉ።
3 እያንዳንዱ አስፋፊ 50 የመጋበዣ ወረቀቶችን ማሰራጨት ይችል ዘንድ በቂ መጠን ያለው መጋበዣ ወረቀት ለየጉባኤው ይላካል። የተቀረውን መጋበዣ ወረቀት አቅኚዎች እንዲያሰራጩ ይደረጋል። እያንዳንዱ ጉባኤ የተመደበበት የአውራጃ ስብሰባ ከመደረጉ ከሦስት ሳምንት ቀደም ብሎ ዘመቻውን ይጀምራል። ይህም ሙሉ በሙሉ ባይሆንም እንኳ የጉባኤውን አብዛኛውን ክልል ለማዳረስ የሚያስችል በቂ ጊዜ እንዲኖር ያደርጋል።
4 የሚቻል ከሆነ የመጋበዣውን ወረቀት ለእያንዳንዱ የቤት ባለቤት መስጠት ጥሩ ነው። ሆኖም ሰዎቹ ቤታቸው የማይገኙ ከሆነ ጥበብ በተሞላበት መንገድ የመጋበዣውን ወረቀት በራቸው ላይ ትተንላቸው መሄድ እንችላለን። ሁሉንም መጋበዣ ወረቀቶች በሦስት ሳምንት ውስጥ አሰራጭቶ ለመጨረስ ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።
5 ቀደም ሲል እንደተገለጸው፣ “መዳናችን ቀርቧል!” የተሰኘውን የአውራጃ ስብሰባ ለማስተዋወቅ በዓለም ዙሪያ የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ምሥክርነት ለመስጠት እንደሚያስችል እንተማመናለን። በመላው ዓለም በሚደረገው በዚህ ዘመቻ ላይ ለመካፈል የምታደርጉትን ጥረት ይሖዋ አብዝቶ እንዲባርከው ጸሎታችን ነው።