አገልግሎታችን ርኅራኄ የሚንጸባረቅበት ሥራ ነው
1 ኢየሱስ መልእክቱን ለማዳመጥ የተሰበሰቡት ብዙ ሰዎች “እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ” ሆነው እንደነበር አስተውሏል። (ማቴ. 9:36) በዚህም ምክንያት የይሖዋን መንገድ በአዘኔታና በፍቅር ያስተማራቸው ከመሆኑም በላይ አጽናንቷቸዋል። በተጨማሪም በርኅራኄ መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን የሚያረካ ተግባር አከናውኗል። እርሱ ባስተማረበት መንገድ ላይ የምናሰላስል ከሆነ እኛም የኢየሱስ ዓይነት አስተሳሰብና ስሜት ሊኖረን ይችላል። እንዲሁም እርሱ የነበረውን የርኅራኄ ባሕርይ በአገልግሎታችን ላይ እናሳያለን።
2 እስቲ ጥቂት ጊዜ ወስደህ ኢየሱስ እርዳታውን በእጅጉ ይፈልጉ የነበሩ ሰዎች ወደ እርሱ በቀረቡበት ወቅት ምን ዓይነት ምላሽ እንደሰጠ አስብ። (ሉቃስ 5:12, 13፤ 8:43-48) ለየት ያለ ችግር ላለባቸው ሰዎች ያስብ ነበር። (ማር. 7:31-35) እንዲሁም የሌሎችን ስሜት የሚረዳ ከመሆኑም በላይ አሳቢነት አሳይቷል። በተጨማሪም ላይ ላዩን የሚያየው ነገር ተጽዕኖ አላሳደረበትም። (ሉቃስ 7:36-40) በእርግጥም ኢየሱስ ርኅሩኅ የሆነውን አምላካችንን ባሕርይ አንጸባርቋል።
3 “አዘነላቸው”:- ኢየሱስ አገልግሎቱን ያከናወነው ግዴታው እንደሆነ ተሰምቶት ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ለሰዎች ‘ያዝን’ ስለነበር ነው። (ማር. 6:34) እኛም በተመሳሳይ መልእክቱን ለማድረስ ብቻ ሳይሆን የሰዎችን ውድ ሕይወት ለማዳን እንጥራለን። ሰዎች ስናነጋግራቸው የዚህ ዓይነት ምላሽ የሰጡበትን ምክንያት ለማወቅ መጣር ይኖርብናል። ስጋታቸውና ጭንቀታቸው ምንድን ነው? በሐሰት ሃይማኖት አስተማሪዎች ችላ ተብለውና ተታልለው ይሆን? እንደዚህ ያሉ ሰዎች ከልብ እንደምናስብላቸው ሲገነዘቡ ምሥራቹን ለመስማት ይነሳሱ ይሆናል።—2 ቆሮ. 6:4, 6
4 ርኅራኄ ማሳየት የሰዎችን ልብ ይነካል። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- አንዲት ሴት የሦስት ወር ልጅዋ ስለሞተችባት በጣም አዝናለች። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለች ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በሯን ያንኳኳሉ። ከዚያም አምላክ መከራ እንዲኖር ስለፈቀደበት ምክንያት ያላቸው አመለካከት ትክክል እንዳልሆነ አሳምናቸዋለሁ በሚል መንፈስ ወደ ቤት እንዲገቡ ጋበዘቻቸው። ይሁን እንጂ ይህች ሴት ከጊዜ በኋላ እንዲህ ብላለች:- “ስለደረሰብኝ ሁኔታ ስነግራቸው በርኅራኄ ስሜት ያዳመጡኝ ሲሆን በመጨረሻ ሲሄዱ በጣም ተጽናንቼ ስለነበር ሌላም ጊዜ እንዲመጡ ተስማማሁ።” በአገልግሎት ላይ ለምታገኟቸው ሰዎች የርኅራኄ መንፈስ ለማሳየት ትጥራላችሁ?
5 የርኅራኄ ባሕርይ መኮትኮታችን ለሌሎች እውነተኛ መጽናኛ መስጠት እንድንችል ይረዳናል። እንዲህ በማድረግ “የርኅራኄ አባት” የሆነውን ይሖዋን እናስከብራለን።—2 ቆሮ. 1:3