የጥያቄ ሣጥን–2
◼ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ የሚቀርቡትን ክፍሎች ከተለያዩ ጽሑፎች በማሰባሰብ ለሌሎች ማሰራጨት ተገቢ ነው?
ለራሳችን፣ ለቤተሰባችን አባላትና ለተወሰኑ የቅርብ ወዳጆቻችን ይህን ማድረግ ይቻላል። ይሁን እንጂ እነዚህን ጽሑፎች እያተሙ ለሰዎች ማሰራጨት ወይም በሽያጭ መልክ ማቅረብ አይገባም። ምክንያቱም ይህ የባለቤትነት መብትን አስመልክቶ ከወጣው ሕግ ጋር ይጋጫል።—ሮሜ 13:1
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የሚቀርቡ አንዳንድ ክፍሎች ጭብጣቸው ብቻ ስለሚሰጥ ትምህርቱ ከየትኞቹ ጽሑፎች ላይ እንደተወሰደ የሚጠቁም መግለጫ የላቸውም። አንድ ሰው ትምህርቶቹ የተብራሩባቸውን ጽሑፎች ዝርዝር በማዘጋጀት ወይም ጽሑፎቹን በማሰባሰብ እንዲህ ያለውን ክፍል ለሚያቀርቡ ወንድሞችና እህቶች መስጠቱ ተገቢ ነው? በፍጹም! ከዚህም በተጨማሪ የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክለሳ መልሶችን ማሰራጨትም ተገቢ አይደለም፤ እንዲህ ማድረግ አስፋፊዎቹ አስፈላጊውን ነጥብ በአእምሯቸው እንዳይዙ ያደርጋል። ከዚህ ይልቅ ተማሪዎቹ ራሳቸው ምርምር ሊያደርጉ ይገባል። ይህ ደግሞ ይሖዋ “የተባ አንደበት” እንዲኖረን ለማስቻል ሲል በትምህርት ቤቱ አማካኝነት የሚሰጠን አስፈላጊ ሥልጠና አንዱ ገጽታ ነው።—ኢሳ. 50:4