‘ንግግራችሁ ሁልጊዜ በጨው የተቀመመ ይሁን’
1. ‘ንግግራችን በጨው የተቀመመ’ ይሁን ሲባል ምን ማለት ነው?
1 “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ በጨው እንደ ተቀመመ ሁልጊዜ በጸጋ የተሞላ [“ለዛ ያለው፣” NW] ይሁን።” (ቈላ. 4:6) ንግግራችን በጨው የተቀመመ ይሁን ሲባል ትክክለኛ ቃላትን መምረጥና የሚያዳምጠንን ሰው ደስ በሚያሰኝ መንገድ መናገር ማለት ነው። በአገልግሎት ላይ በምንሆንበት ጊዜ ይህን ማድረጋችን እጅግ አስፈላጊ ነው።
2. ኢየሱስ ለሳምራዊቷ ሴት ሊመሠክርላት የቻለው እንዴት ነበር?
2 ኢየሱስ የተወው ምሳሌ:- ኢየሱስ በውኃ ጉድጓድ አጠገብ አረፍ ባለበት ጊዜ ውኃ ልትቀዳ የመጣችን አንዲት ሳምራዊት ሴት ቅድሚያውን በመውሰድ አነጋግሯታል። ሳምራዊቷ ሴት በውይይቱ መሃል በአይሁዶችና በሳምራውያን መካከል ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን ጥላቻ የሚያንጸባርቁ ሐሳቦችን በተደጋጋሚ ጊዜያት አንስታለች። ምንም እንኳ አይሁዶች፣ ሳምራውያን የመጡት አይሁዳዊ ካልሆኑ ዘሮች ነው የሚል ጠንካራ ስሜት ቢኖራቸውም እሷ ግን ሳምራውያን የያዕቆብ ዝርያዎች ናቸው የሚል እምነት እንዳላት ጭምር ገልጻለች። ኢየሱስ፣ ሳምራዊቷ ሴት የምታነሳቸውን ሐሳቦች ከመቃወም ይልቅ አዎንታዊ በሆኑ ነጥቦች ላይ አተኩሯል። በዚህም ምክንያት እሷንም ሆነ የከተማውን ሰዎች የሚጠቅም ምሥክርነት መስጠት ችሏል።—ዮሐ. 4:7-15, 39
3. በአገልግሎት ላይ ስንሆን የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
3 ለሰዎች በምንመሠክርበት ጊዜ ዓላማችን መልካሙን “የምሥራች” ማወጅ መሆኑን መዘንጋት አይገባንም። (ሮሜ 10:15) ፍላጎታችን የቤቱ ባለቤት በግል የሚያምንባቸውን ነገሮች እያጥላላንበት እንደሆነ እንዲሰማው ማድረግ ሳይሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማራኪና የሚያንጹ ሐሳቦችን ማካፈል ነው። የቤቱ ባለቤት የሰጠው አስተያየት የተሳሳተ አመለካከት እንዳለው የሚያንጸባርቅ ከሆነ ስህተቱን ፊት ለፊት መንገር አያስፈልገንም። ከሰጠው ሐሳብ ውስጥ እኛ የምንስማማበት አሊያም ከልብ በመነጨ ስሜት እንድናመሰግነው የሚያደርግ ምን ነጥብ አለ? ምናልባት “ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በዚህ መልኩ አስበውት ያውቃሉ?” በማለት አንድ ጥቅስ ልናነብለት እንችላለን።
4. የቤቱ ባለቤት የዘለፋ ንግግር ቢናገር ምን ማድረግ ይኖርብናል?
4 የቤቱ ባለቤት የዘለፋ ንግግር ቢናገር ወይም ፍላጎቱ መከራከር እንደሆነ ቢገባንስ ምን ማድረግ እንችላለን? በዚህ ጊዜም ቢሆን በጠባያችንም ሆነ በአነጋገራችን ገርነትና የዋህነት ማሳየታችንን መቀጠል ይኖርብናል። (2 ጢሞ. 2:24, 25) ግለሰቡ የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት ፍላጎት ከሌለው በዘዴ ውይይቱን ማቋረጡ የተሻለ ይሆናል።—ማቴ. 7:6፤ 10:11-14
5. አንዲት እህት ለዛ ያለው መልስ በመስጠቷ ምን ጥሩ ውጤት አገኘች?
5 ጥሩ ውጤት:- አንዲት እህት ለጎረቤቷ ለመመሥከር ስትሞክር ሴትየዋ ጸያፍ ቃላቶችን በመናገር በንዴት ትጮኽባታለች። እህታችን ደግነት በተሞላበት መንገድ፣ “እንደዚህ ስለተሰማሽ አዝናለሁ፤ ደህና ዋይ” ትላታለች። ከሁለት ሳምንት በኋላ ሴትየዋ እህት ቤት ድረስ በመሄድ ያን ቀን ስላደረገችው ነገር ይቅርታ የጠየቀቻት ሲሆን እህት የምትነግራትን ለመስማት ፈቃደኛ እንደሆነች ገለጸችላት። በእርግጥም ለዛ ያለው ወይም ትሕትና የተሞላበት መልስ መስጠት ብዙውን ጊዜ ጥሩ ውጤት ያስገኛል!—ምሳሌ 15:1፤ 25:15
6. በአገልግሎት ላይ አነጋገራችን በጨው የተቀመመ እንዲሆን ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
6 ምሥራቹን በምናውጅበት ጊዜ አነጋገራችን በጨው የተቀመመ እንዲሆን ለማድረግ ጥረት እናድርግ። እንዲህ ማድረጋችን የቤቱ ባለቤት ለማዳመጥ ፈቃደኛ ባይሆንም እንኳ በሌላ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቱ ሲመጡ ለመስማት ይበልጥ እንዲነሳሳ ሊያደርገው ይችላል።