‘የአምላክን ቃል ያለ ፍርሃት ተናገር’
1 በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ ስለ እምነትህ ለመናገር የሚያስችል አጋጣሚ አግኝተህ ፈርተህ ወደኋላ ያልክበት ጊዜ አለ? ለዘመዶችህና ለጎረቤቶችህ ወይም ለማታውቃቸው ሰዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር ይከብድሃል? ሁላችንም የምናገኛቸውን ግሩም አጋጣሚዎች በመጠቀም ‘የአምላክን ቃል ያለ ፍርሃት ለመናገር’ እንድንችል ምን ሊረዳን ይችላል?—ፊልጵ. 1:14
2 ወደኋላ አትበል:- አንድ የቅርብ ወዳጅህ ወይም ዘመድህ በሐሰት ቢወነጀል ለእርሱ ጥብቅና ከመቆም ወደኋላ ትላለህ? ከማንም በላይ የቅርብ ወዳጃችን የሆነው ይሖዋ ለዘመናት ትክክል ያልሆነ ነገር ሲነገርበት ቆይቷል። ሁላችንም ለታላቁ አምላካችን የመመሥከር ልዩ መብት አለን! (ኢሳ. 43:10-12) ለይሖዋ ያለን ጥልቅ ፍቅር ሰዎች ምን ይሉኛል የሚለውን ስሜት ወይም የሚሰማንን ፍርሃት እንድናሸንፍ ከመርዳቱም በላይ ስለ እውነት በድፍረት ከመናገር ወደኋላ እንዳንል ያነሳሳናል።—ሥራ 4:26, 29, 31
3 ለሰዎች የምንናገረው መልእክት ምሥራች መሆኑን አስታውስ። ይህን መልእክት ሰምተው እርምጃ የሚወስዱ ሰዎች ዘላለማዊ በረከቶችን ያገኛሉ። በራሳችን ወይም በተቃዋሚዎቻችን ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ የስብከቱ ሥራችን ባለው ጠቀሜታ ላይ ማተኮራችን በድፍረት እንድንሰብክ ይረዳናል።
4 ሌሎች የተዉልን ምሳሌ:- የአምላክን ቃል ያለ ፍርሃት በመናገር ረገድ ሌሎች የተዉልን የታማኝነት ምሳሌ የብርታት ምንጭ ይሆንልናል። ለምሳሌ ሔኖክ ይሖዋ በዓመጸኞች ላይ የሚያመጣውን ፍርድ በድፍረት አውጇል። (ይሁዳ 14, 15) ኖኅ ግድ የለሽ ለነበሩ ሰዎች በታማኝነት ሰብኳል። (ማቴ. 24:37-39) “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” የነበሩት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ከፍተኛ ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም መስበካቸውን ቀጥለዋል። (ሥራ 4:13, 18-20) መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች በይሖዋ ላይ እምነት በማሳደር የሰውን ፍርሃት ያሸነፉና ቀናተኛ ወንጌላውያን የሆኑ በዘመናችን የሚገኙ ሰዎችን የሕይወት ታሪክ ይዘው ይወጣሉ።
5 በጥንት ጊዜ ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋር የተጋፈጡ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የተከተሉትን የሕይወት አቅጣጫ በመመርመር ድፍረት ማግኘት እንችላለን። (1 ነገ. 19:2, 3፤ ማር. 14:66-71) እነዚህ ሰዎች ‘ከአምላካችን ድፍረት በማግኘታቸው’ ያለ ፍርሃት መስበክ ችለዋል። እኛም እንዲሁ ማድረግ እንችላለን!—1 ተሰ. 2:2