የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 3/09 ገጽ 5-6
  • ከበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—2009
የመንግሥት አገልግሎታችን—2009
km 3/09 ገጽ 5-6

የተወደዳችሁ የይሖዋ አገልጋዮች፦

ከበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ

ውድ ወንድሞች፣ ይህን ደብዳቤ ስንጽፍላችሁ በጣም ደስ ይለናል! እኛም የእምነት ባልንጀሮቹን ‘ከልብ እንደሚወዳቸውና’ “በእውነት እየተመላለሱ መሆናቸውን” ሲያውቅ መደሰቱን እንደተናገረው እንደ ሐዋርያው ዮሐንስ ይሰማናል። (2 ዮሐ. 1, 4) ሁላችንም እውነትን ማወቃችን እንዴት ያለ በረከት ነው! እውነት ከታላቂቱ ባቢሎንም ሆነ ለአምላክ ክብር ከማያመጡት ትምህርቶቿና ልማዶቿ ነፃ አውጥቶናል። ለእውነት መታዘዛችን አፍቃሪ፣ ደግና መሐሪ እንድንሆን ረድቶናል። በተጨማሪም እውነት በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም እንዲኖረን አልፎ ተርፎም የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንድናገኝ አስችሎናል።

ከዚህም በላይ ይሖዋ በየዕለቱ የሚመራንንና የሚያበረታንን መንፈሱን ስለሚሰጠን በጣም አመስጋኞች ነን! “በአምላክ መንፈስ መመራት” በሚል ጭብጥ በቅርቡ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ይሖዋ ሕዝቡን ለመምራትና ለማበርታት መንፈሱን በምን በምን መንገዶች እንደሚጠቀምበት በማወቃችሁ እንደተደሰታችሁ እርግጠኞች ነን። የዓለም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ በሄደ መጠን ከፊት ለፊታችን በሚጠብቀን ወሳኝ ወቅት እንዲመራን ኃያል በሆነው የይሖዋ መንፈስ መመካታችን በጣም አስፈላጊ ነው።

ለእምነታቸው ሲሉ የደረሰባቸውን ብዙ መከራ በጽናት ስለተቋቋሙ ወንድሞቻችን የሚናገሩ አስደናቂ ታሪኮችን ከዓመት መጽሐፍ ላይ ስታነቡ ልባችሁ እንደተነካ እርግጠኞች ነን። የሚገርመው ነገር ከእነዚህ ታማኝ ወንድሞቻችን መካከል ብዙዎቹ እንዲህ ያለው መከራ የደረሰባቸው ከተጠመቁ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ነበር፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ገና አልተጠመቁም ነበር። ታማኝነታቸውና ለጽድቅ ያላቸው አቋም እንድንወዳቸው ያደርገናል! በእርግጥም ግሩም ምሳሌነታቸው በሕይወታችን ውስጥ ምንም ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ቢያጋጥመን ለመንግሥቱ ታማኝ ሆነን ለመቀጠል ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል።—1 ተሰ. 1:6-8

ውድ ወንድሞችና እህቶች፣ ቤተሰባችሁ በፍቅር እንደተሳሰረ እንዲቀጥል ለማድረግ ስትሉ ኢኮኖሚው የሚያሳድረውን ጫናም ሆነ ሌሎች በርካታ ችግሮችን መቋቋም እንደሚያስፈልጋችሁ እናውቃለን። እንዲያውም አንዳንዶቻችሁ መንግሥቱን የመስበኩን ሥራና አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች የጉባኤ እንቅስቃሴዎችን ያለማሰለስ በታማኝነት መደገፍም እንኳ ተፈታታኝ እንደሚሆንባችሁ አይካድም። በጉዳዩ ላይ ብዙ ከተወያየንና ከጸለይንበት በኋላ ከጥር 1, 2009 ጀምሮ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ያደረግነው በዚህ ምክንያት ነው። በግልና በቤተሰብ ጥናታችሁ ሰፋ ያለ ጊዜ በማሳለፍ እነዚህን ዝግጅቶች በሚገባ እንደምትጠቀሙባቸው እንተማመናለን።

በዚህ ዓመት በተደረጉ የልዩ፣ የወረዳና የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በርካታ ተጠማቂዎችን ማየታችን በጣም አስደስቶናል። ከእነዚህ መካከል በዕድሜ ትንሽ የሆኑ ልጆችም ይገኙበታል። እናንተ ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ለእውነት አድናቆት እንዲኖራቸው አድርጋችሁ ስላሳደጋችኋቸውና ገና በለጋ ዕድሜያቸው ይሖዋን ለማገልገል ራሳቸውን እንዲወስኑ ስላበረታታችኋቸው ልትመሰገኑ ይገባል። እነዚህ ልጆች በትምህርት ቤት በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እያጋጠሟቸውም እንኳ ለመጠመቅ ብቁ መሆናቸው ቤተሰቦቻቸው ጥሩ ሥልጠና እንደሰጧቸው የሚመሠክር ነው።—መዝ. 128:1-6

መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማሩ ሥራ የታየው አስደሳች ጭማሪም ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም። ጠንክረው የሚሠሩት ሚስዮናውያንና ልዩ አቅኚዎች ለዚህ ጭማሪ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። እኛ የበላይ አካል አባላት በዓለም ዙሪያ የሚገኙት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች “ና!” የሚለውን ጥሪ በማሰማትና የተጠሙ ሁሉ ‘የሕይወትን ውኃ በነፃ እንዲወስዱ’ በመጋበዝ ላከናወኑት ተግባር ከፍተኛ አድናቆት አለን። (ራእይ 22:17) ባሳለፍነው ዓመት ራሳቸውን መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት ያሳዩት 289,678 የሚያህሉ ሰዎች ከዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ጋር በመቀላቀላቸው በጣም መደሰታችንን ልንገልጽላቸው እንወዳለን!

ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለምም ሆነ ምኞቱ በማለፍ ላይ ናቸው፤ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” በማለት የተናገራቸውን ቃላት ዘወትር ማስታወሳችን አስፈላጊ ነው። (1 ዮሐ. 2:17) እንዲሁም ይህ ዓለም ‘የሚያልፍበት’ ጊዜ በጣም በቀረበበት ወቅት ላይ እንደምንኖር መዘንጋት አይኖርብንም! በመሆኑም ሕይወታችን የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ ያተኮረ እንዲሆን መጣራችንና ‘ምንጊዜም ነቅተን መጠበቃችን’ የጥበብ እርምጃ ነው። (ማቴ. 24:42) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ፈጽሞ የምንቆጭበት ነገር የማይኖር ከመሆኑም በላይ የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት የሚያስገኝልንን በረከት እናጭዳለን።—ኢሳ. 63:7

በ2009 የዓመት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ከበርካታ አገሮች የተሰባሰቡ ስሜት ቀስቃሽ ታሪኮች ማንበባችሁ ሁላችሁም በሕይወታችሁ ውስጥ የአምላክን መንግሥት እንድታስቀድሙ ያበረታታችኋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ምንጊዜም ከአእምሯችን እንደማትጠፉ እንዲሁም በጣም እንደምንወዳችሁና ዘወትር ስለ እናንተ እንደምንጸልይ ልናረጋግጥላችሁ እንፈልጋለን። ይሖዋ አትረፍርፎ እንዲባርካችሁ እንመኛለን።

ወንድሞቻችሁ፣

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ