የጥያቄ ሣጥን
◼ የጉባኤ ስብሰባዎችን በስልክ ከማስተላለፍ ጋር በተያያዘ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
በርካታ ጉባኤዎች በሕመም ወይም ከአቅም በላይ በሆኑ ሁኔታዎች ሳቢያ አንዳንድ ጊዜ በመንግሥት አዳራሽ የሚደረጉ ስብሰባዎችን መካፈል ላልቻሉ ግለሰቦች ስብሰባውን ቤታቸው ሆነው በስልክ እንዲያዳምጡ ዝግጅት አድርገዋል። በዚህ ፍቅራዊ ዝግጅት፣ የሚገባቸው ሰዎች ብቻ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታና በሚገባ መደራጀት ይጠይቃል። በመሆኑም ይህን ዝግጅት እንዲከታተሉ የተመደቡ ሽማግሌዎች “ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት” መከናወን እንዲችል ዝግጅቱን በተደራጀ ሁኔታ ማካሄድና ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ ይኖርባቸዋል።—1 ቆሮ. 14:40
ሽማግሌዎች በጉባኤያቸው ውስጥ የሚገኙ ከባድ ሕመም ያለባቸው ወይም አቅመ ደካማ አሊያም የአልጋ ቁራኛ የሆኑ አስፋፊዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንደሆነ መከታተል አለባቸው። ጊዜያዊ ሕመም ወይም የአካል ጉዳት ያጋጠማቸው አስፋፊዎች አሊያም የአልጋ ቁራኛ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በዚህ ዝግጅት እንዲጠቀሙ ሊፈቀድላቸው የሚችል ሲሆን በተሰብሳቢዎች ቁጥር ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ። በዚህ ዝግጅት ለሚጠቀሙ ሰዎች በሙሉ የሚበቃ የስልክ መስመር ከሌለ የጉባኤ ስብሰባ ፕሮግራሞችን ቀድቶ እንደመስጠት ያሉ ሌሎች ዝግጅቶችን ማድረግ ይቻላል።
እርግጥ ነው፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በአካል መገኘት ከሚያስገኘው ጥቅም ጋር ሊወዳደር የሚችል ነገር የለም። በወንድሞቻችን መካከል በአካል መገኘታችን “እርስ በርሳችን እንድንበረታታ” የሚያስችለን ከመሆኑም በላይ አዲሶች ስብሰባ ላይ የመገኘትን አስፈላጊነት ይበልጥ እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። በስብሰባዎቻችን ላይ ስንገኝ ከሠርቶ ማሳያዎች የበለጠ ጥቅም እናገኛለን፣ ሽማግሌዎች በግለሰብ ደረጃ ማበረታቻ እንዲሰጡን ያስችላቸዋል እንዲሁም በወንድማማች ኅብረት ውስጥ ያለውን ከልብ የመነጨ ፍቅር በአካል ተገኝተን እንድናጣጥም ያስችለናል። አንዲት አረጋዊት እህት ወደ መንግሥት አዳራሽ ሲገቡ አንዲት እህት እቅፍ አድርጋ ስትስማቸው “ይህን በስልክ ማግኘት አትችሉም!” በማለት በአድናቆት የተናገሩት ሐሳብ በእርግጥም ትክክል ነው።—ሮም 1:11, 12
‘ከቤተ መቅደስ ፈጽሞ እንደማትጠፋው’ እንደ ሐና ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ አረጋውያንም ጤንነታቸውና ሁኔታቸው በፈቀደላቸው መጠን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው ይገኛሉ። (ሉቃስ 2:36, 37) እነዚህ አረጋውያን አስገዳጅ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው የጉባኤ ስብሰባዎችን በስልክ የሚከታተሉ ቢሆንም ይህን ዝግጅት በመንግሥት አዳራሽ ከመገኘት የተሻለ አማራጭ እንደሆነ አድርገው አይመለከቱትም። የእነሱን ግሩም ምሳሌ በመከተል ታላቁን አምላካችንን ይሖዋን ለማምለክ በሚያስችሉን ስብሰባዎች ላይ በአካል ለመገኘት በደስታ ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥል።—መዝ. 95:1-3, 6፤ 122:1