ሌሎች እናንተን በመመልከት ምን ሊማሩ ይችላሉ?
1. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እሱን በመመልከት ምን ተምረዋል?
1 ኢየሱስ “ቀንበሬን ተሸከሙ፣ ከእኔም ተማሩ” ብሏል። (ማቴ. 11:29) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ በቃል ብቻ ሳይሆን ጥሩ ምሳሌ በመሆን ጭምር ሌሎችን አስተምሯል። ደቀ መዛሙርቱ እሱን በመመልከት ምን ሊማሩ እንደሚችሉ አስቡ። ኢየሱስ ርኅሩኅ፣ ደግና አፍቃሪ ነበር። (ማቴ. 8:1-3፤ ማር. 6:30-34) እንዲሁም እውነተኛ ትሕትና ነበረው። (ዮሐ. 13:2-5) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለአገልግሎት ከእሱ ጋር ሲሄዱ እውነትን ለሰዎች በማስተማር ረገድ ውጤታማ የሆነ ደከመኝን የማያውቅ ጠንካራ ሠራተኛ መሆኑን አስተውለው ነበር። (ሉቃስ 8:1፤ 21:37, 38) ታዲያ ሌሎች አገልግሎት ላይ እኛን በመመልከት ምን ሊማሩ ይችላሉ?
2. ጥሩ አለባበስና ምግባር በምናነጋግራቸው ሰዎች ላይ ምን ጥሩ ስሜት ያሳድራል?
2 የቤት ባለቤቶች፦ ልከኛ የሆነው አለባበሳችን፣ መልካም ምግባራችንና ለሰዎች ያለን ከልብ የመነጨ አሳቢነት በቤት ባለቤቶች ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። (2 ቆሮ. 6:3፤ ፊልጵ. 1:27) እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በተደጋጋሚ እንደምንጠቅስ ያስተውላሉ። ሌሎች ደግሞ በሚናገሩበት ወቅት በአክብሮት ስለምናዳምጣቸው ይገረማሉ። በእነዚህ ነገሮች ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆን ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት እንዲያድርባቸው እንደሚያደርግ አትዘንጉ።
3. በወንድሞቻችን ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ማሳደር እንችላለን?
3 ወንድሞቻችን፦ በወንድሞቻችን ላይ ልናሳድር የምንችለውን በጎ ተጽዕኖም አስቡ። በአገልግሎት ላይ የምናሳየው ቅንዓት ወደ ሌሎች ይጋባል። ብረት ብረትን እንደሚስለው ሁሉ እኛም ጥሩ ዝግጅት የተደረገባቸውን አቀራረቦች መጠቀማችን ሌሎች የስብከት ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ያበረታታቸዋል። (ምሳሌ 27:17) ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በትክክል በመመዝገብና ቶሎ ሄዶ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ ትጉዎች መሆናችን ሌሎች ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል። አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ በመፈጸም በወንድሞቻችን ላይ በጎ ተጽዕኖ ማሳደር እንችላለን።—2 ጢሞ. 4:5
4. ምሳሌ በመሆን ረገድ በየጊዜው ራሳችንን መገምገም ያለብን ለምንድን ነው?
4 የምታደርጉትንና የምትናገሩትን ነገር እንዲሁም ጥሩ ምሳሌ በመሆን በሌሎች ላይ የምታሳድሩትን ተጽዕኖ በተመለከተ ራሳችሁን በየጊዜው ለምን አትገመግሙም? ጥሩ ምሳሌ መሆናችን ይሖዋን የሚያስደስተው ከመሆኑም በላይ ሐዋርያው ጳውሎስ “እኔ የክርስቶስን አርዓያ እንደምከተል እናንተም የእኔን አርዓያ ተከተሉ” በማለት የተናገረውን ሐሳብ ለማስተጋባት ያስችለናል።—1 ቆሮ. 11:1