የመስክ አገልግሎት ጎላ ያሉ ገጽታዎች
ልዩ የስብከት ዘመቻ የተካሄደበት የመጨረሻው ወር ማለትም መጋቢት፣ በስድስት ነገሮች አዲስ ከፍተኛ ቁጥር የተገኘበት በመሆኑ ከዚህ በፊት ከነበሩት ወሮች ሁሉ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረግንበት ወር ሊሆን ችሏል! በዚህ ወር 3,390 ረዳት አቅኚዎች ነበሩ፤ የዘወትር አቅኚዎች ቁጥርም 1,654 የደረሰ ሲሆን ይህም አዲስ ከፍተኛ ቁጥር ነው። በአጠቃላይ በመጋቢት ወር 57 በመቶ የሚሆኑት አስፋፊዎች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተካፍለው የነበረ ሲሆን የአስፋፊዎች ቁጥርም 9,406 ደርሷል። በመስክ አገልግሎት ያሳለፍነው ጠቅላላ ሰዓት ባለፈው ዓመት በሚያዝያ ወር ከነበረው 3 በመቶ ጭማሪ አለው። በአገልግሎቱ ላሳያችሁት ቅንዓትና ትጋት ልናመሰግናችሁ እንወዳለን። መጽሔቶችን በማበርከት ረገድም ጥሩ ውጤት ተገኝቷል። እንዲያውም በየካቲት ወር ከተመዘገበው ከፍተኛ ቁጥር 11 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በአሁኑ ጊዜ መንገድ ላይ አስቁመው መጽሔት የሚጠይቁ ሰዎች እየበዙ መምጣታቸውን በርካታ አስፋፊዎች ተናግረዋል። ይህ ሁኔታና በዚህ ወር ያደረግነው ከ130,000 የሚበልጡ ተመላልሶ መጠየቆች እንዲሁም ከ7,800 የሚበልጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ‘ለምሥራቹ’ ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች እንዳሉ ይጠቁማሉ፤ ይህ ደግሞ በግ መሰል የሆኑ ሰዎችን የመርዳት መብታችንን ከፍ አድርገን እንድንመለከተው ያበረታታናል።