የመስክ አገልግሎት ጎላ ያሉ ገጽታዎች
ልዩ የአገልግሎት ዘመቻው በመጋቢት ወር የተጠናቀቀ ሲሆን በአጠቃላይ 365 ወንድሞችና እህቶች ተካፍለዋል፤ እነዚህ ወንድሞች ከዚህ ቀደም ፈጽሞ ወይም እምብዛም ባልተሠራባቸው 140 አካባቢዎች ላይ አገልግለዋል። የመታሰቢያው በዓል የመጋበዣ ወረቀት የሚሰራጩባቸው ሳምንታት የዋሉት በመጋቢት ወር ላይ በመሆኑ በልዩ ዘመቻው ወቅት ግሩም ምሥክርነት ለመስጠት አስችሏል። በዚህም የተነሳ ከ25,000 የሚበልጡ ሰዎች በበዓሉ ላይ ተገኝተዋል። ቢያንስ በሰባት አካባቢዎች የመታሰቢያው በዓል የተከበረው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ከእነዚህ መካከል በአንዳንዶቹ 122 የደረሰ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ተመዝግቧል። በተጨማሪም በመጋቢት ወር 3,239 ረዳት አቅኚዎች ነበሩ። ይህ ማለት በመጋቢት ወር በአጠቃላይ 5,424 አቅኚዎች ነበሩ ማለት ነው! ይህ ትጋት የተሞላበት እንቅስቃሴ 9,607 የደረሰ አዲስ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር እንዲመዘገብ ምክንያት ሆኗል፤ ከዚህም ሌላ በተመላልሶ መጠየቅና መጽሔት በማበርከት ረገድም አዲስ ከፍተኛ ቁጥር ተመዝግቧል። ይህ ይበል የሚያሰኝ ነው! እንግዲያው ሁላችንም ፍላጎት ያሳዩትን እነዚህን ሰዎች ተከታትለን በመርዳት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ እንጋብዛቸው።