◼ የስብሰባው ሰዓት፦ በመሰብሰቢያ ቦታው ወንበር መያዝ የሚቻለው ከጠዋቱ 2:00 ጀምሮ ነው። በሦስቱም ቀናት የመክፈቻው ሙዚቃ የሚጀምረው ከጠዋቱ 3:20 ላይ ነው። በዚህ ጊዜ ሁላችንም ቦታ ቦታችንን መያዝ ይኖርብናል፤ ይህም ፕሮግራሙን ክብር ባለው መንገድ ለማስጀመር ያስችላል። ስብሰባው በመዝሙርና በጸሎት የሚደመደመው ዓርብና ቅዳሜ 10:55 እንዲሁም እሁድ 9:50 ላይ ይሆናል።
◼ ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች፦ በአንዳንድ አካባቢዎች ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ይደረጋሉ። ቅርንጫፍ ቢሮው የተወሰኑ ጉባኤዎችን እንዲሁም ከውጭ አገር የሚመጡ ልዑካንን በስብሰባው ላይ እንዲገኙ የጋበዘው የስብሰባ ቦታውን የወንበር ብዛት፣ የመኪና ማቆሚያ ቦታ እንዲሁም የሆቴል ክፍሎችን ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ አትዘንጉ። አስፋፊዎች ሳይጋበዙ በብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ከሆነ መጨናነቅ ሊፈጠር ይችላል። እርግጥ ነው፣ በሁኔታዎች አስገዳጅነት በራሳችሁ የአውራጃ ስብሰባ ላይ መገኘት አትችሉ ይሆናል፤ በዚህ ጊዜ በሌላ የአውራጃ ስብሰባ ላይ መካፈል የምትችሉ ቢሆንም በብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ መሆን ግን የለበትም።
◼ መኪና ማቆሚያ፦ አውራጃ ስብሰባ በሚደረግባቸው በሁሉም ቦታዎች ላይ የመኪና ማቆሚያው ስፍራ በእኛ ቁጥጥር ሥር ከሆነ ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ እንደ አመጣጣቸው ያለምንም ክፍያ ይስተናገዳሉ። ያለው የመኪና ማቆሚያ አብዛኛውን ጊዜ ውስን ስለሚሆን በተቻለ መጠን መኪናችሁን በመተው ከሌላው ጋር ተዳብላችሁ የምትሄዱ ከሆነ የመኪናዎችን ቁጥር መቀነስ ይቻላል።
◼ ወንበር መያዝ፦ እባካችሁ፣ ጠዋት ላይ የስብሰባው ቦታ በሮች ሲከፈቱ የምትፈልጉትን ቦታ ለመያዝ ስትሉ አትሽቀዳደሙ። የሌሎችን ፍላጎት በማስቀደም የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየታችን እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችንን ለይቶ የሚያሳውቅ ከመሆኑም ሌላ የሚመለከቱን ሰዎች አምላክን እንዲያከብሩ ያነሳሳቸዋል። (ዮሐ. 13:34, 35፤ 1 ቆሮ. 13:4, 5፤ 1 ጴጥ. 2:12) ወንበር መያዝ የሚቻለው ከእናንተ ጋር በመኪና ለሚመጡ፣ በአንድ ቤት አብረዋችሁ ለሚኖሩ እንዲሁም ከእናንተ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ላይ ለሚገኙ ሰዎች ብቻ መሆኑን አስታውሱ። ስብሰባው በሚደርግባቸው አንዳንድ አካባቢዎች፣ ለአረጋውያንና የአቅም ገደብ ላለባቸው የሚመደቡ ወንበሮች ይኖራሉ። እነዚህ ወንበሮች ውስን በመሆናቸው ከአረጋውያኑ ወይም የአቅም ገደብ ካላቸው ጋር እንዲቀመጡ የሚፈቀድላቸው እነሱን የሚንከባከቡ አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው።
◼ ምሳ፦ በእረፍት ሰዓት ምግብ ፍለጋ ከስብሰባው ቦታ ወጥታችሁ ከመሄድ ይልቅ እባካችሁ ምሳ ይዛችሁ ኑ። ወንበር ሥር ሊቀመጥ የሚችል የምግብ መያዣ ዕቃ መጠቀም ይቻላል። ትላልቅ የምግብ መያዣ ዕቃዎችንና ጠርሙስ ነክ ዕቃዎችን ወደ ስብሰባው ቦታ ማምጣት አይፈቀድም።
◼ መዋጮ፦ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለዓለም አቀፉ ሥራ በፈቃደኝነት መዋጮ በማድረግ ለዝግጅቱ ያለንን አድናቆት መግለጽ እንችላለን። በአውራጃ ስብሰባው ላይ መዋጮ የሚደረጉ ቼኮች ሁሉ ለ“የይሖዋ ምሥክሮች” የሚከፈሉ መሆናቸው መገለጽ አለበት። በተጨማሪም በዴቢት ወይም በክሬዲት ካርድ ተጠቅሞ መዋጮ ማድረግ ይቻላል።
◼ መድኃኒቶች፦ በሐኪም ትእዛዝ የምትወስዱት መድኃኒት ካለ እንዲህ ዓይነት መድኃኒቶች በስብሰባው ቦታ ስለማይኖሩ እባካችሁ የምትወስዷቸውን መድኃኒቶች በበቂ መጠን መያዛችሁን አረጋግጡ። የስኳር ሕመምተኞች የሚጠቀሙባቸው ሲሪንጆችና መርፌዎች፣ አደጋ የሚያስከትሉ ቆሻሻዎች በመሆናቸው በተገቢው ሁኔታ መወገድ ይኖርባቸዋል እንጂ በስብሰባው ቦታና በሆቴሎች ውስጥ በሚገኝ የቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ውስጥ መጣል አይኖርባቸውም።
◼ የደኅንነት ጥንቃቄ፦ እባካችሁ በተለይ በመንሸራተትና በመደናቀፍ የተነሳ ጉዳት እንዳይደርስባችሁ አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጉ። በየዓመቱ ከጫማ በተለይም ከታኮ ጫማ ጋር በተያያዘ ጉዳት ይደርሳል። በመሆኑም ሊያንሸራትቱ በሚችሉ ስፍራዎች፣ በደረጃዎች፣ የሚያሾልኩ ቀዳዳዎች ባሉት ወለል ላይና እነዚህን በመሳሰሉ ቦታዎች ስትራመዱ ጉዳት እንዳይደርስባችሁ ልከኛና ምቹ የሆነ ጫማ እንድታደርጉ እናበረታታችኋለን።
◼ የመስማት ችግር ያለባቸው፦ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ስብሰባው በኤፍኤም የሬዲዮ ሞገድ ይተላለፋል። በዚህ ዝግጅት መጠቀም የምትፈልጉ ከሆነ በባትሪ የሚሠራ የኤፍኤም መቀበያና የጆሮ ማዳመጫ ይዛችሁ መምጣት ያስፈልጋችኋል።
◼ የሕፃናት ጋሪዎችና የመናፈሻ ወንበሮች፦ የሕፃናት ጋሪዎችንና የመናፈሻ ወንበሮችን ወደ ስብሰባው ቦታ ይዞ መምጣት ተገቢ አይደለም። ይሁን እንጂ ከወላጆች አጠገብ ባለ ወንበር ላይ ሊታሰሩ የሚችሉ ለልጆች ደኅንነት ተብለው የሚዘጋጁ ወንበሮችን (ቻይልድ ሴፍቲ ሲትስ) ይዞ መምጣት ይቻላል።
◼ የአትክልት ቦታዎች፦ በስብሰባ ቦታው ላይ ያሉ አበባዎችንና ሌሎች ተክሎችን ማሳደግ እንዲሁም መንከባከብ ጉልበትና ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ እባካችሁ ልጆቻችሁ አበቦችንም ሆነ ተክሎችን እንዳይቀጥፉ ወይም እንዳይነቅሉ አሠልጥኗቸው።
◼ እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት (S-43) የተባለው ቅጽ፦ እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት የሚለው ቅጽ በስብሰባው ላይ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሥክረንለት ፍላጎት ያሳየን ሰው በሚመለከት መረጃ ለመስጠት ያገለግላል። ቅጹን ከሞላችሁ በኋላ ለአውራጃ ስብሰባው የጽሑፍ ክፍል አሊያም ወደ ጉባኤያችሁ ስትመለሱ ለጉባኤው ጸሐፊ ልትሰጡት ትችላላችሁ።
◼ ምግብ ቤቶች፦ ምግብ ቤት በምትመገቡበት ጊዜ መልካም ምግባር በማሳየት የይሖዋን ስም አስከብሩ። ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ አለባበስ ይኑራችሁ። በአካባቢው የተለመደ ከሆነ ለአስተናጋጆች ጉርሻ ወይም ቲፕ ስጡ።
◼ የመንግሥት አዳራሾችን መጠቀም፦ የመንግሥት አዳራሾችን የማደሪያ ስፍራ አድርገን ባንጠቀምባቸው እንመርጣለን። ይሁን እንጂ በሁኔታዎች አስገዳጅነት አንድን የመንግሥት አዳራሽ ለዚህ ዓላማ መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በዚያ የሚያርፉት በሙሉ አዳራሹ በማንኛውም ሰዓት ንጹሕና የተስተካከለ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። አንሶላና ብርድ ልብሳቸውን አጣጥፈው ማስቀመጥ፣ የተደፋ ነገር ካለ ወዲያውኑ ማጽዳት እንዲሁም ወረቀቶችንና ሌሎች ቆሻሻዎችን ለዚህ ዓላማ በተዘጋጁ ቅርጫቶች ወይም ዕቃዎች ውስጥ መጣል ይኖርባቸዋል።
◼ ሆቴሎች፦
የሚቻል ከሆነ በሆቴል ውስጥ ብታርፉ ይመረጣል። እባካችሁ ከሚያስፈልጋችሁ ቁጥር በላይ ክፍል አትያዙ፤ እንዲሁም ሆቴሉ ከሚፈቅደው በላይ ሰዎችን በክፍላችሁ አታሳድሩ።
ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ካላጋጠማችሁ በስተቀር የያዛችሁትን ሆቴል አትሰርዙ፤ ይሁንና መሰረዝ ካስፈለጋችሁ በአፋጣኝ ለሆቴሉ አሳውቁ፤ እንዲህ ማድረጋችሁ ሌሎች ክፍል ማግኘት እንዲችሉ ይረዳል።—ማቴ. 5:37
በአገራችሁ የተለመደ ከሆነ የሆቴሉ ሠራተኞች ሻንጣ ሲሸከሙላችሁ ጉርሻ ስጧቸው፤ የሆቴል ክፍላችሁን ለሚያጸዳው ግለሰብም እንዲህ ማድረጋችሁን አትርሱ።
ምግብ ማብሰል የሚኖርባችሁ ማብሰል በሚፈቀድባቸው ክፍሎች ውስጥ ብቻ ነው።
ከሆቴሉ ሠራተኞች ጋር ባላችሁ ግንኙነት ምንጊዜም የመንፈስ ፍሬን አንጸባርቁ። ሠራተኞቹ ብዙ ሰዎችን ስለሚያስተናግዱ ደግነትና ትዕግሥት ብናሳያቸው እንዲሁም ምክንያታዊ ብንሆን ደስ ይላቸዋል።
ወላጆች ልጆቻቸው በሆቴሉ ውስጥ የሚያደርጉትን ነገር ምንጊዜም መቆጣጠር ይገባቸዋል፤ ይህ ደግሞ ልጆቻቸው በአሳንሰር አጠቃቀም እንዲሁም በመዋኛ ቦታ፣ በእንግዳ መቀበያው አካባቢ፣ በጂምናዝየምና በሌሎች አካባቢዎች የሚያሳዩትን ባሕርይ መከታተልን ይጨምራል።
◼ ንጽሕና፦ የንጽሕና ክፍሉ የስብሰባ ቦታው በፕሮግራም እንዲጸዳ ዝግጅት የሚያደርግ ቢሆንም ሁላችንም ይሖዋ ከሕዝቡ የሚጠብቀውን ላቅ ያለ የንጽሕና ደረጃ ለማሟላት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን። በመሆኑም በአዳራሹ ወለል ላይም ሆነ በግቢው ውስጥ የተጣሉ ወረቀቶች ወይም ሌሎች ቆሻሻዎች ሊታዩ አይገባም። እነዚህን ቆሻሻዎች ወዲያውኑ በቆሻሻ መጣያ ውስጥ መጣል ተገቢ ነው፤ ይህም የስብሰባው ቦታ ፕሮግራሙ በሚከናወንበት ወቅትም ሆነ በምሳ እረፍት ሰዓት ውበቱን የጠበቀ ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጋል። በተጨማሪም ከወንበራችን ተነስተን ለመሄድ ስናስብ በአካባቢያችን የተጣሉ ነገሮች መኖራቸውን ብናጣራ እንዲሁም ብናነሳቸው ጥሩ ነው።
◼ የፈቃደኛ አገልግሎት፦ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው ማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ በስብሰባው ቦታ ለሚገኘው የፈቃደኛ አገልግሎት ክፍል ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች በወላጃቸው ወይም በአሳዳጊያቸው አሊያም ወላጃቸው ወይም አሳዳጊያቸው ኃላፊነት በሰጠው ሌላ ትልቅ ሰው ሥር በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ።