ልዩ ግብዣ
1. በ2014 ለሚደረገው የአውራጃ ወይም ብሔራት አቀፍ ስብሰባ የመጋበዣ ወረቀት ማሰራጨት የምንጀምረው መቼ ነው?
1 ለጓደኞቻችሁ ወይም ለቤተሰቦቻችሁ ልዩ የምግብ ግብዣ ለማድረግ አስባችኋል እንበል፤ እንዲህ ያለውን ግብዣ ማዘጋጀት ብዙ ጉልበትና ገንዘብ እንደሚጠይቅ የታወቀ ነው፤ በግብዣው ላይ እንዲገኙ የምትጠሯቸው በደስታ ስሜት እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም። በተመሳሳይም በ2014 በሚካሄዱት የአውራጃና ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርበውን መንፈሳዊ ድግስ ለማዘጋጀት ብዙ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ስብሰባው ከመጀመሩ ከሦስት ሳምንታት በፊት አንስቶ ሰዎች በዚህ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ የመጋበዝ መብት አለን። ታዲያ መጋበዣ ወረቀቱን በደስታ ስሜት መስጠት እንድንችል ምን ይረዳናል?
2. በዘመቻው ላይ ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?
2 ይሖዋ በአውራጃ ወይም ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ከሚያቀርብልን መንፈሳዊ ድግስ መካፈላችን በግለሰብ ደረጃ ስለሚያስገኝልን ጥቅም የምናስብ ከሆነ በዘመቻው ላይ ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ እንነሳሳለን። (ኢሳ. 65:13, 14) በተጨማሪም በየዓመቱ የምናደርገው ይህ ዘመቻ ውጤት እንዳለው ማስታወስ ይኖርብናል። ከምንጋብዛቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ስብሰባው ላይ ይገኛሉ። ግብዣውን ተቀብለው የሚመጡት ሰዎች ቁጥር ብዙም ይሁን ጥቂት የመጋበዣ ወረቀቱን ለማሰራጨት ከልብ ጥረት ማድረጋችን ለይሖዋ ክብር የሚያመጣ ከመሆኑም ሌላ የእሱን ልግስና ያሳያል።—መዝ. 145:3, 7፤ ራእይ 22:17
3. የመጋበዣ ወረቀቱ የሚሰራጨው እንዴት ነው?
3 የእያንዳንዱ ጉባኤ የሽማግሌዎች አካል፣ የመጋበዣ ወረቀቱን በጉባኤው ክልል ውስጥ ለብዙ ሰዎች ማዳረስ ስለሚቻልበት መንገድ ተነጋግሮ መወሰን አለበት፤ ይህም ቤታቸው ላልተገኙ ሰዎች የመጋበዣ ወረቀቱን ትቶ መሄድ ወይም የመጋበዣ ወረቀቱን በአደባባይ ምሥክርነት ማሰራጨት ያስፈልግ እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰንን ይጨምራል። ቅዳሜና እሁድ፣ ሁኔታው አመቺ እንደሆነ ከተሰማን መጽሔቶችንም ማበርከት እንችላለን። የወሩ የመጀመሪያ ቅዳሜ ዘመቻውን በምናደርግበት ወቅት ላይ ካረፈ ትኩረት የምናደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጀመር ላይ ሳይሆን የመጋበዣ ወረቀቱን በማሰራጨት ላይ ይሆናል። በዚህ ሥራ በደስታ ስሜት የምንካፈልና ይሖዋ በሚያቀርበው መንፈሳዊ ድግስ ላይ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች እንዲገኙ የምንጋብዝ ከሆነ ዘመቻው ከተጠናቀቀ በኋላ ከፍተኛ እርካታ እንደሚያስገኝልን የታወቀ ነው!