የመስክ አገልግሎት ጎላ ያሉ ገጽታዎች
የልዩ አደባባይ ምሥክርነት ሥራ ከተጀመረበት ከሚያዝያ 10, 2014 ጀምሮ በአዲስ አበባ በአራት ቦታዎች፣ በሞጆ ደረቅ ወደብና በአዳማ ሰፊ ምሥክርነት ሲሰጥ ቆይቷል። በዚህም መሠረት 10,097 መጻሕፍት፣ 8,196 መጽሔቶች፣ 4,824 ብሮሹሮችና 1,191 ትራክቶች በሰዎች እጅ ሊገቡ ችለዋል። በቅርቡ በሌሎች አካባቢዎችም ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንገኛለን። ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች 160 አቅኚዎች እያገለገሉ ነው። አቅኚዎች በዚህ ሥራ ለመካፈል ያላቸው ስሜት የሚደነቅና የሚያበረታታ ነው። በግል ሥራቸውና በሌሎች ኃላፊነቶቻቸው ላይ ማስተካከያ በማድረግ የመንግሥቱን ጉዳይ ለማስቀደም ጥረት አድርገዋል። አቅኚዎቹ ለአገልግሎታቸው ትልቅ ድጋፍ እንዳገኙ እንዲሁም ይሖዋና ድርጅቱን ወክለው በአደባባይ መቆማቸው ልዩ የደስታ ስሜት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። ጽሑፎቻችን የደረሷቸው ሰዎችም ቢሆኑ አድናቆታቸውንና አመስጋኝነታቸውን እየገለጹ ከመሆናቸውም ባሻገር በቀጣይነት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፍላጎት እያሳዩ ነው። በዚህ የስብከት ዘዴ ለመካፈል ሲሉ የአቅኚነት አገልግሎት የጀመሩ አስፋፊዎችም አሉ። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ይሖዋ ሥራውን እየባረከውና ውጤትም እየተገኘ ነው።