የመስክ አገልግሎት ጎላ ያሉ ገጽታዎች
በዚህ ዓመት በተካሄዱት 24 የክልል ስብሰባዎች ላይ የነበረው አጠቃላይ የተሰብሳቢ ብዛት 16,609 ሲሆን 293 ሰዎች ተጠምቀዋል። በጠቅላላው 2,026 የሚሆኑ የዘወትር አቅኚዎች ነበሩን። ከ200,000 የሚበልጡ ትራክቶች ተበርክተዋል፤ በሚገባ ታስቦባቸው የተዘጋጁት እነዚህ ትራክቶቻችን ፍላጎት ላላቸው በርካታ ሰዎች ምሥክርነት ለመስጠት አስችለዋል። በተጨማሪም በክልላችን የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በየቀኑ jw.org የተባለውን ድረ ገጻችንን ይመለከታሉ። በእርግጥም አስደናቂ የሆነ ምሥክርነት እየተሰጠ ነው!
በክልላችን የነበረው ሌላው ጎላ ያለ ክንውን ታኅሣሥ 13, 2014 የበላይ አካል አባል የሆነው ጄፍሪ ጃክሰን መጽሐፍ ቅዱስ—አዲስ ዓለም ትርጉም በአማርኛ ታትሞ መውጣቱን መግለጹ ነው። በቀጥታ ስርጭት አማካኝነት በ59 ቦታዎች የሚገኙ 10,180 ሰዎች ይህን ልዩ ፕሮግራም መከታተል ችለው ነበር! ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በአማርኛ ታትሞ መውጣቱ መጽሐፉን ላስጻፈው ለይሖዋ ክብርና ውዳሴ እንደሚያመጣ የታወቀ ነው! ከዚህም በተጨማሪ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ወንድሞቻችንም ሆኑ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ይበልጥ ቀላልና የሚያረካ እንዲሆንላቸው እንደሚያደርግ እንተማመናለን!