የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
ሰኔ 6-12
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 34-37
“በይሖዋ ታመኑ፤ መልካም የሆነውንም አድርጉ”
(መዝሙር 37:1, 2) በክፉዎች አትበሳጭ፤ ወይም በክፉ አድራጊዎች አትቅና። 2 እንደ ሣር በፍጥነት ይደርቃሉ፤ እንደለመለመ ተክልም ይጠወልጋሉ።
‘በይሖዋ ደስ ይበላችሁ’
“አትቅና”
3 የምንኖረው ‘አስጨናቂ በሆነ ዘመን’ ውስጥ ከመሆኑም ሌላ ክፋት በእጅጉ ተስፋፍቶ ይገኛል። “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ” የሚሉት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ሲፈጸሙ ተመልክተናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13) ክፉ ሰዎች የተሳካላቸውና ብልጽግና ያገኙ መስለው መታየታቸው ብቻ እንኳ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል! ይህ መንፈሳዊ እይታችን እንዲዛባ በማድረግ አቅጣጫችንን ሊያስተን ይችላል። የመዝሙር 37 የመክፈቻ ቃላት “በክፉዎች ላይ አትቅና [“አትበሳጭ፣” የ1980 ትርጉም]፣ ዓመፃንም በሚያደርጉ ላይ አትቅና” በማለት ይህን ከባድ አደጋ በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ይሰጡናል።
4 የዓለማችን መገናኛ ብዙኃን የፍትሕ መጓደልን በተመለከተ በየዕለቱ በርካታ ዘገባዎች ያቀርባሉ። አጭበርባሪ ነጋዴዎች ከመያዝ ያመልጣሉ። ወንጀለኞች ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ሰዎችን መጠቀሚያ ያደርጓቸዋል። ነፍሰ ገዳዮች ሳይያዙ ወይም ሳይቀጡ ይቀራሉ። የፍትሕ መዛባት የሚታይባቸው እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሊያበሳጩንና የአእምሮ እረፍት ሊነሱን ይችላሉ። ክፉዎች የተሳካላቸው መስለው መታየታቸው የቅንዓት ስሜት ሊያሳድርብንም ይችላል። ሆኖም የእኛ መናደድ በሁኔታው ላይ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል? ክፉዎች ባገኙት ስኬት መቅናት አካሄዳቸው በሚያስከትልባቸው መዘዝ ላይ የሚያመጣው ለውጥ አለ? ምንም ለውጥ አያመጣም! ደግሞም ‘የምንበሳጭበት’ ምክንያት የለም። ለምን?
5 መዝሙራዊው “እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፣ እንደ ለመለመ ቅጠልም ይረግፋሉና” የሚል መልስ ይሰጣል። (መዝሙር 37:2) ለምለም ሣር ሲያዩት የሚያምር ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ይጠወልግና ይደርቃል። የክፉዎች ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም። ያገኙት ብልጽግና አብሯቸው አይዘልቅም። በሚሞቱበት ጊዜ በሸፍጥ ያገኙት ሀብት ምንም ሊጠቅማቸው አይችልም። በመጨረሻ ከፍትሕ የሚያመልጥ ሰው የለም። ጳውሎስ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 6:23) ክፉዎችና ዓመፀኞች በሙሉ የኋላ ኋላ የሚገባቸውን “ደመወዝ” ስለሚቀበሉ ከዚህ ምድር ላይ ይጠፋሉ። ይህ በእርግጥ እርባና የሌለው የሕይወት ጎዳና ነው!—መዝሙር 37:35, 36፤ 49:16, 17
6 ታዲያ ክፉዎች ባገኙት እርባና የሌለው ብልጽግና መናደድ ይኖርብናል? ከመዝሙር 37 የመጀመሪያ ሁለት ቁጥሮች የምናገኘው ትምህርት አለ፦ እነርሱ ያገኙት ስኬት ይሖዋን ለማገልገል ከመረጥከው ጎዳና እንዲያስወጣህ አትፍቀድ። ከዚህ ይልቅ ትኩረትህን በመንፈሳዊ በረከቶችና ግቦች ላይ አድርግ።—ምሳሌ 23:17
(መዝሙር 37:3-6) በይሖዋ ታመን፤ መልካም የሆነውንም አድርግ፤ በምድር ላይ ኑር፤ ለሰዎችም ታማኝ ሁን። 4 በይሖዋ ሐሴት አድርግ፤ እሱም የልብህን መሻት ይሰጥሃል። 5 መንገድህን ለይሖዋ አደራ ስጥ፤ በእሱ ታመን፤ እሱም ለአንተ ሲል እርምጃ ይወስዳል። 6 ጽድቅህን እንደ ንጋት ብርሃን፣ የአንተንም ፍትሕ እንደ ቀትር ፀሐይ ያበራዋል።
‘በይሖዋ ደስ ይበላችሁ’
‘በይሖዋ ታመን፣ መልካምንም አድርግ’
7 መዝሙራዊው “በእግዚአብሔር ታመን፣ መልካምንም አድርግ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቶናል። (መዝሙር 37:3ሀ) ጭንቀት ላይ ስንወድቅ ወይም ደግሞ ጥርጣሬ ሲያድርብን በይሖዋ ላይ ጽኑ እምነት ማሳደር ይኖርብናል። የተሟላ መንፈሳዊ ጥበቃ ሊያደርግልን የሚችለው ይሖዋ ነው። ሙሴ “በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 91:1) በዚህ ሥርዓት ውስጥ የዓመፅ መብዛት ሲያስጨንቀን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በይሖዋ መታመን ይኖርብናል። እግራችንን ወለም ሲለን ጓደኛችን ደግፎ ቢይዘን ደስ እንደሚለን ሁሉ በታማኝነት ለመጓዝ በምናደርገው ጥረትም የይሖዋ ድጋፍ ያስፈልገናል።—ኢሳይያስ 50:10
8 ዓመፀኞች በሚያገኙት ስኬት ላለመበሳጨት መፍትሔው በግ መሰል ሰዎችን ለመፈለግና የይሖዋን ዓላማ በትክክል እንዲያውቁ ለመርዳት በትጋት መሥራት ነው። ክፋት እየተባባሰ ባለበት በዚህ ዘመን ሌሎችን በመርዳቱ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና” ብሏል። ከሁሉ የላቀው “መልካም” ሥራ የአምላክን መንግሥት ታላቅ ምሥራች ለሌሎች ማካፈል ነው። ለሕዝብ የምንሰጠው ምሥክርነት በእርግጥ ‘የምሥጋና መሥዋዕት’ ነው።—ዕብራውያን 13:15, 16፤ ገላትያ 6:10
9 ዳዊት በመቀጠል “በምድርም ተቀመጥ፣ ታምነህም ተሰማራ” ብሏል። (መዝሙር 37:3ለ) በዳዊት ዘመን የነበረው ‘ምድር’ ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ክልል ማለትም ተስፋይቱን ምድር ያመለክታል። በሰሎሞን የንግሥና ዘመን የተስፋይቱ ምድር ድንበር በሰሜን በኩል ከዳን አንስቶ በደቡብ እስከ ቤርሳቤህ የሚደርስ ሲሆን እስራኤላውያን የሚኖሩት በዚህ ክልል ውስጥ ነበር። (1 ነገሥት 4:25) በዛሬው ጊዜ በየትኛውም የምድር ክፍል ብንኖር ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ መላዋ ፕላኔት ገነት የምትሆንበትን ጊዜ በጉጉት እንጠብቃለን። እስከዚያ ድረስ ግን በመንፈሳዊ ሁኔታ ተረጋግተን እንኖራለን።—ኢሳይያስ 65:13, 14
10 ‘ታምነን መሰማራታችን’ ምን ያስገኝልናል? በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ምሳሌ “የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል” ይላል። (ምሳሌ 28:20) በምንኖርበት ቦታ ሁሉ እንዲሁም ለምናገኘው ሰው በሙሉ ምሥራቹን በመስበክ በታማኝነት መጽናታችን ከይሖዋ በረከት እንደሚያስገኝልን የታወቀ ነው። ለምሳሌ ያህል ፍራንክና ባለቤቱ ሮዝ በሰሜናዊ ስኮትላንድ በምትገኝ በአንዲት ከተማ አቅኚ ሆነው ማገልገል የጀመሩት ከ40 ዓመታት በፊት ነበር። እነርሱ ወደዚያ ከመሄዳቸው በፊት እውነትን ተቀብለው የነበሩ ጥቂት ሰዎች ከእውነት ወጥተዋል። እነዚህ አቅኚ ባልና ሚስት በዚህ ተስፋ ሳይቆርጡ የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ተያያዙት። በአሁኑ ጊዜ በዚያ ከተማ ውስጥ አንድ ትልቅ ጉባኤ ይገኛል። በእርግጥም እነዚህ ባልና ሚስት ያሳዩት ታማኝነት የይሖዋን በረከት አስገኝቶላቸዋል። ፍራንክ “ከሁሉ የላቀው በረከት አሁንም እውነት ውስጥ መሆናችንና ይሖዋ በእኛ መጠቀም መቀጠሉ ነው” ሲል በትሕትና ተናግሯል። አዎን፣ ‘ታምነን ስንሰማራ’ ብዙ በረከት እናገኛለን፤ በዚያም እንደሰታለን።
‘በይሖዋ ደስ ይበልህ’
11 ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ለማጠናከርና በእርሱ ላይ ያለንን እምነት ጠብቀን ለመኖር ‘በይሖዋ ደስ ሊለን’ ይገባል። (መዝሙር 37:4ሀ) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም እንኳ ከልክ በላይ በራሳችን ጉዳይ ከመጠመድ ይልቅ ትኩረታችን በይሖዋ ላይ እንዲያርፍ እናደርጋለን። እንዲህ ማድረግ የምንችልበት አንደኛው መንገድ ቃሉን ለማንበብ ጊዜ በመመደብ ነው። (መዝሙር 1:1, 2) መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ደስታ ያስገኝልሃል? ስለ ይሖዋ ይበልጥ ለመማር ብለህ የምታነብብ ከሆነ ደስታ ሊያስገኝልህ ይችላል። የተወሰነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ካነበብህ በኋላ ቆም ብለህ ‘ያነበብኩት ክፍል ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል?’ ብለህ ለምን ራስህን አትጠይቅም። መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብብ ማስታወሻ ደብተር ወይም ወረቀት መያዝህ ሊጠቅምህ ይችላል። ያነበብከው ክፍል ምን መልእክት እንዳለው ለማሰብ ቆም ባልክ ቁጥር የአምላክን ውድ ባሕርያት ለማስታወስ የሚያስችሉህን ጥቂት ቃላት ጻፍ። ዳዊት በአንድ ሌላ መዝሙር ላይ “አቤቱ፣ ረድኤቴ መድኃኒቴም፣ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 19:14) ለአምላክ ቃል ትኩረት መስጠታችን በይሖዋ ፊት “ያማረ” ሆኖ ይታያል፤ እኛም ደስታ እናገኝበታለን።
12 በማጥናትና በማሰላሰል ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማው የቻልነውን ያህል የመማር ግብ ማውጣት እንችላለን። እስከዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው እና ወደ ይሖዋ ቅረቡ የተባሉት ዓይነት ጽሑፎች በአድናቆት ስሜት ልናሰላስልባቸው የምንችል ብዙ ሐሳቦች ይዘዋል። እንዲህ በማድረግ በጽድቅ የምንመላለስ ከሆነ ይሖዋ ‘የልብህን መሻት ይሰጥሃል’ በማለት ዳዊት ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (መዝሙር 37:4ለ) ሐዋርያው ዮሐንስ የሚከተሉትን ቃላት ለመጻፍ የተነሳሳው እንዲህ ዓይነት ትምክህት ስለነበረው መሆን አለበት፦ “በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን።”—1 ዮሐንስ 5:14, 15
13 ታማኝ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የይሖዋ ሉዓላዊነት ከነቀፋ ጸድቶ ማየት ከፍተኛ ደስታ ያስገኝልናል። (ምሳሌ 27:11) ቀደም ሲል ጨቋኝ ወይም አምባገነን አገዛዝ ሰፍኖባቸው በነበሩ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ወንድሞቻችን ስላከናወኑት ከፍተኛ የስብከት እንቅስቃሴ ስንሰማ ልባችን በደስታ አይሞላም? ይህ ሥርዓት ከማብቃቱ በፊት ምን ዓይነት ተጨማሪ ነፃነት ሊገኝ እንደሚችል አናውቅም። በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ለጊዜው ወደ አገራቸው ለመጡና በነፃነት የማምለክ አጋጣሚ ላገኙ ተማሪዎች፣ ስደተኞችና ሌሎች ሰዎች ምሥራቹን በመስበክ በትጋት ይሳተፋሉ። እነዚህ ሰዎች ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ መንፈሳዊ ጨለማ በዋጠው ማለትም ሥራው በታገደበት አገራቸው ውስጥ የእውነትን ብርሃን ማብራታቸውን እንዲቀጥሉ ከልብ እንመኛለን።—ማቴዎስ 5:14-16
‘መንገድህን ለይሖዋ አደራ ስጥ’
14 የሚያስጨንቁንና ከባድ ሸክም የሆኑብን ነገሮች የሚወገዱ መሆናቸውን ማወቁ ምንኛ ያስደስታል! ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? ዳዊት “መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፣ በእርሱም ታመን” ካለ በኋላ “እርሱም ያደርግልሃል” ሲል ገልጿል። (መዝሙር 37:5) ይሖዋ አስተማማኝ አለኝታ መሆኑን የሚያሳዩ በጉባኤያችን ውስጥ በቂ ምሥክሮች አሉ። (መዝሙር 55:22) በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ማለትም በአቅኚነት፣ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት፣ በሚስዮናዊነት ወይም በቤቴል የሚያገለግሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሁሉ የይሖዋ እንክብካቤ አስተማማኝ መሆኑን ሊመሰክሩ ይችላሉ። የምታውቃቸው የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ካሉ ቀርበህ በማነጋገር ይሖዋ ምን ዓይነት ድጋፍ እንደሰጣቸው ለምን አትጠይቃቸውም? በአስቸጋሪ ጊዜም እንኳ የይሖዋ እጅ አጭር አለመሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ተሞክሮዎች እንደሚነግሩህ የታወቀ ነው። ይሖዋ ለሕይወት የሚያስፈልጉንን ነገሮች ምንጊዜም ያሟላልናል።—መዝሙር 37:25፤ ማቴዎስ 6:25-34
15 ይሖዋን አለኝታችን ስናደርገውና ሙሉ በሙሉ በእርሱ ስንታመን መዝሙራዊው ቀጥሎ የተናገረው ይፈጸምልናል፦ “ጽድቅህን እንደ ብርሃን ፍርድህንም እንደ ቀትር ያመጣል።” (መዝሙር 37:6) የይሖዋ ምሥክር ስለሆንን ብቻ በአብዛኛው ሰዎች ለእኛ የተሳሳተ አመለካከት አላቸው። ሆኖም ምሥራቹን የምንሰብከው ለአምላክና ለሰዎች ባለን ፍቅር ተገፋፍተን መሆኑን ልበ ቅን ሰዎች መገንዘብ እንዲችሉ ይሖዋ ዓይናቸውን ይከፍትላቸዋል። ከዚህም ሌላ ብዙዎች ለመልካም ባሕርያችን የተሳሳተ ትርጉም ቢሰጡም እንኳ ማንነታችን ከሰዎች ዓይን የተሰወረ አይደለም። ይሖዋ ማንኛውንም ዓይነት ተቃውሞና ስደት እንድንቋቋም ይረዳናል። ከዚህም የተነሳ የአምላክ ሕዝቦች ጽድቅ እንደ ቀትር ፀሐይ ደምቆ ይበራል።—1 ጴጥሮስ 2:12
(መዝሙር 37:7-11) በይሖዋ ፊት ዝም በል፤ እሱንም በተስፋ ተጠባበቅ። የጠነሰሰውን ሴራ በተሳካ ሁኔታ እየፈጸመ ባለ ሰው አትበሳጭ። 8 ከቁጣ ተቆጠብ፤ ንዴትንም ተው፤ ተበሳጭተህ ክፉ ነገር አትሥራ። 9 ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ። 10 ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ክፉዎች አይኖሩም፤ በቀድሞ ቦታቸው ትፈልጋቸዋለህ፤ እነሱ ግን በዚያ አይገኙም። 11 የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል።
‘በይሖዋ ደስ ይበላችሁ’
‘ጸጥ በል፤ በትዕግሥትም ተጠባበቅ’
16 መዝሙራዊው በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “በእግዚአብሔር ፊት ጸጥ በል፤ በትዕግሥትም ተጠባበቀው፤ መንገዱ በተቃናለት፣ ክፋትንም በሚሸርብ ሰው ልብህ አይሸበር።” (መዝሙር 37:7 አ.መ.ት) እዚህ ላይ ዳዊት ይሖዋ እርምጃ እስኪወስድ ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ እንዳለብን አበክሮ ገልጿል። የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እስካሁን ድረስ አለመምጣቱ ለማጉረምረም ምክንያት ሊሆነን አይችልም። የይሖዋ ምሕረትና ትዕግሥት መጀመሪያ ካሰብነው እጅግ የላቀ መሆኑን አላስተዋልንም? መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ምሥራቹን በትጋት እየሰበክን በትዕግሥት እንደምንጠብቅ ማሳየት እንችላለን? (ማርቆስ 13:10) በዚህ ጊዜ ደስታችንንና መንፈሳዊ ደኅንነታችንን የሚያሳጣ የችኮላ እርምጃ ላለመውሰድ መጠንቀቅ አለብን። በዚህ ጊዜ የሰይጣን ዓለም የሚያሳድረውን ጎጂ ተጽዕኖ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በኃይል መዋጋት እንዲሁም መንፈሳዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅና በይሖዋ ፊት ያለንን የጽድቅ አቋም ላለማጉደፍ ተጠንቅቀን መኖር አለብን። የብልግና ሐሳቦችን ከአእምሯችን ለማስወገድና ተቃራኒ ፆታ ላላቸውም ሆነ እንደኛው ዓይነት ፆታ ላላቸው ሰዎች ተገቢ ያልሆነ ዝንባሌ ላለማሳየት በአቋማችን ጸንተን እንቀጥል።—ቆላስይስ 3:5
17 ዳዊት “ከቁጣ ራቅ መዓትንም ተው” የሚል ምክር ሰጥቶናል። “እንዳትበድል አትቅና። ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ።” (መዝሙር 37:8, 9) አዎን፣ ይሖዋ ከምድር ላይ ማንኛውንም ክፋትና የክፋት መንስዔ የሆኑትን ሰዎች የሚያስወግድበትን በጣም እየቀረበ ያለውን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠበቅ እንችላለን።
“ገና ጥቂት”
18 “ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም።” (መዝሙር 37:10) ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እንዲሁም ከይሖዋ ርቆ በራስ የመመራት ዝንባሌ ወደሚያከትምበት ጊዜ እየተቃረብን ስንሄድ ይህ ጥቅስ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ሰዎች ያቋቋሙት የትኛውም ዓይነት መንግሥት ወይም አገዛዝ ከንቱ መሆኑ ታይቷል። በመሆኑም የአምላክ አገዛዝ ማለትም እውነተኛ ቲኦክራሲ ዳግመኛ ወደሚቋቋምበት ጊዜ ተቃርበናል። ይህ አገዛዝ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የይሖዋ መንግሥት ነው። ይህ መንግሥት መላውን ዓለም ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠር ከመሆኑም በላይ የሚቃወሙትን ሁሉ ያስወግዳል።—ዳንኤል 2:44
19 የአምላክ መንግሥት በሚያስተዳድረው አዲስ ዓለም ውስጥ ‘ኃጢአተኛ’ ለማግኘት ብትጥርም እንኳ አታገኝም። በእርግጥም በይሖዋ ላይ የሚያምፅ ማንኛውም ሰው ወዲያውኑ ይጠፋል። ሉዓላዊ አገዛዙን የሚቃወም ወይም ለአምላካዊ ሥልጣን ለመገዛት ፈቃደኛ የማይሆን ሰው በዚያ አይገኝም። ጎረቤቶችህ በሙሉ እንደ አንተው ይሖዋን ለማስደሰት ፍላጎት ያላቸው ይሆናሉ። ሰዎች ደኅንነታቸው እንደተጠበቀ ይሰማቸዋል፤ በር መቆለፊያና መቀርቀሪያ አያስፈልግም! ሰዎች በሌሎች ላይ ሙሉ እምነት እንዳይጥሉና ደስተኞች እንዳይሆኑ የሚያግዳቸው ነገር አይኖርም።—ኢሳይያስ 65:20፤ ሚክያስ 4:4፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
20 “ገሮች . . . ምድርን ይወርሳሉ” የሚለው ጥቅስ ፍጻሜውን ያገኛል። (መዝሙር 37:11ሀ) ይሁንና “ገሮች” የተባሉት እነማን ናቸው? “ገር” ተብሎ የተተረጎመው ቃል “ማስጨነቅ፣ ማዋረድ፣ ዝቅ ማድረግ” የሚል ትርጉም ካለው ቃል የተገኘ ነው። አዎን፣ “ገሮች” የተባሉት የደረሰባቸውን የፍትሕ መጓደል በሙሉ ይሖዋ እንዲያስተካክልላቸው ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የሚጠባበቁ ሰዎች ናቸው። “በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” (መዝሙር 37:11ለ) በአሁኑ ጊዜም እንኳ በእውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መንፈሳዊ ገነት በማግኘታችን ብዙ ሰላም አለን።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(መዝሙር 34:18) ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተደቆሰባቸውንም ያድናል።
ወደ አምላክ ቅረብ
ልባቸው ለተሰበረ ሰዎች የሚሆን መጽናኛ
‘ይሖዋ ፈጽሞ ሊወደኝ አይችልም ብዬ አስብ ነበር።’ ይህን ያለችው ለብዙ ዓመታት ከመንፈስ ጭንቀት ጋር ስትታገል የኖረች አንዲት ክርስቲያን ነች። ይህች ሴት ይሖዋ ከእሷ እንደራቀ ሆኖ ይሰማት ነበር። በእርግጥ ይሖዋ በመንፈስ ጭንቀት ከሚሠቃዩ አገልጋዮቹ ይርቃል? መዝሙራዊው ዳዊት በመንፈስ ተመርቶ መዝሙር 34:18 ላይ ያሰፈረው ሐሳብ የሚያጽናና መልስ ይዟል።
ዳዊት፣ ከባድ ጭንቀት በአንድ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ ላይ ምን ስሜት ሊያሳድር እንደሚችል ያውቅ ነበር። ወጣት በነበረበት ጊዜ እሱን ለመግደል ቆርጦ የተነሳ አንድ ቀናተኛ ንጉሥ ቀን ከሌት ያሳድደው ስለነበር ከቦታ ወደ ቦታ እየተንከራተተ ለመኖር ተገዶ ነበር። ዳዊት በፍልስጥኤም ምድር ወደምትገኘው ጌት ወደተባለች የጠላት ከተማ ሄዶ ጥገኝነት ጠየቀ፤ ይህን ያደረገው ሳኦል በማይገምተው ስፍራ ለመደበቅ በማሰብ ሳይሆን አይቀርም። ይሁንና ማንነቱ ሲታወቅ እብድ እንደሆነ በማስመሰል ከሞት መንጋጋ ለጥቂት አመለጠ። ዳዊት ከዚህ አደጋ ስለታደገው አምላክን አመስግኗል፤ መዝሙር 34ንም እንዲጽፍ ያነሳሳው ይህ ሁኔታ ነበር።
ዳዊት፣ አምላክ ባደረባቸው ጭንቀት የተነሳ በሐዘን ከተዋጡ ወይም የእሱን እርዳታ ለማግኘት ብቁ እንዳልሆኑ ከሚሰማቸው ሰዎች የራቀ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር? እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።” (ቁጥር 18) እነዚህ ቃላት የሚያጽናኑትና ተስፋ የሚፈነጥቁት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
ይሖዋ ‘ቅርብ ነው።’ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ይህ ሐረግ “ጌታ በትኩረት የሚከታተልና ንቁ እንዲሁም ሕዝቡን ለመርዳትና ለማዳን ምንጊዜም ዝግጁ እንደሆነ የሚገልጽ ጥሩ አባባል ነው” ብሏል። ይሖዋ የሕዝቡን ሁኔታ በትኩረት እንደሚከታተል ማወቅ የሚያጽናና ነው። በዚህ “በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ሕዝቡ ምን ዓይነት ችግር እንደሚደርስበት ያያል፤ እንዲሁም የሕዝቡን ውስጣዊ ስሜት ይረዳል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ የሐዋርያት ሥራ 17:27
‘ልባቸው የተሰበረ።’ አንዳንድ ማኅበረሰቦች “የተሰበረ ልብ” የሚለውን አባባል አፍቅሮ ምላሽ ያጣ ሰው የሚሰማውን ስሜት ለማመልከት ይጠቀሙበታል። ይሁንና መዝሙራዊው የተናገራቸው ቃላት “በሌላ ምክንያት የሚመጣ ሐዘንንም ጭምር” እንደሚያመለክት አንድ ምሑር ገልጸዋል። አዎን፣ አንዳንድ ጊዜ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችም እንኳ ልባቸውን የሚሰብር ከባድ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል።
‘መንፈሳቸው የተሰበረ።’ ተስፋ የቆረጡ ሰዎች ለራሳቸው ያላቸው ግምት በጣም ስለሚቀንስ ለጊዜው ሁሉም ነገር ጭልምልም ይልባቸዋል። ለመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የተዘጋጀ አንድ መጽሐፍ ይህ አገላለጽ “የወደፊቱ ጊዜ የጨለመባቸው” ተብሎ ሊተረጎም እንደሚችል ይናገራል።
ታዲያ ይሖዋ ‘ልባቸውና መንፈሳቸው ለተሰበረ’ ሰዎች ምን አመለካከት አለው? ፍቅርና አሳቢነት ሊያሳያቸው እንደማይገባ አድርጎ በመቁጠር ከእነሱ ይርቃል? በፍጹም! ችግር የገጠመውን ልጁን አቅፎ እንደሚያጽናና አፍቃሪ ወላጅ ይሖዋም የእሱን እርዳታ ለማግኘት የሚጮኹ አገልጋዮቹን ለመርዳት ዝግጁ ነው። የተሰበረ ልባቸውንና የተደቆሰ መንፈሳቸውን ለመጠገን ልባዊ ፍላጎት አለው። ያጋጠማቸውን ማንኛውንም አስቸጋሪ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስፈልጋቸውን ጥበብና ጥንካሬ ሊሰጣቸው ይችላል።—2 ቆሮንቶስ 4:7፤ ያዕቆብ 1:5
ታዲያ ወደ ይሖዋ መቅረብ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ለምን ጥረት አታደርግም? ሩኅሩኅ የሆነው አምላክ እንዲህ የሚል ቃል ገብቷል፦ “የተዋረዱትን መንፈሳቸውን ለማነሣሣት፣ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ለማነቃቃት . . . የተሰበረ ልብ ካለውና በመንፈሱ ከተዋረደው ጋር እሆናለሁ።”—ኢሳይያስ 57:15
(መዝሙር 34:20) አጥንቶቹን ሁሉ ይጠብቃል፤ አንዳቸውም ቢሆኑ አልተሰበሩም።
‘ይህ ለመታሰቢያ ይሁናችሁ’
19 እስራኤላውያን፣ ፋሲካን ሲያከብሩ በጉን ካረዱ በኋላ አንዱንም አጥንት እንዳይሰብሩ ታዝዘዋል። (ዘፀ. 12:46፤ ዘኍ. 9:11, 12) ታዲያ ቤዛውን ለመክፈል ስለመጣው “የአምላክ በግ” ምን ማለት ይቻላል? (ዮሐ. 1:29) ኢየሱስ የተሰቀለው በሁለት ወንጀለኞች መካከል ነበር። አይሁዳውያን፣ የተሰቀሉት ሰዎች አጥንት እንዲሰበር ጲላጦስን ጠየቁ። አጥንታቸው መሰበሩ ቶሎ እንዲሞቱ ያደርጋል፤ አይሁዳውያን ይህን ያደረጉት ድርብ ሰንበት በሆነው በኒሳን 15 ዕለት ሰዎቹ በእንጨት ላይ ተሰቅለው እንዲውሉ ስላልፈለጉ ነው። በመሆኑም ወታደሮቹ የሁለቱን ወንጀለኞች እግር ሰበሩ፤ “ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን ቀደም ብሎ መሞቱን ስላዩ እግሮቹን አልሰበሩም።” (ዮሐ. 19:31-34) ይህም ከፋሲካ በግ ጋር በተያያዘ ከተሰጠው መመሪያ ጋር ይስማማል፤ ከዚህ አንጻር በጉ፣ ኒሳን 14 ቀን 33 ዓ.ም. ለሆነው ነገር “ጥላ” ሆኗል ሊባል ይችላል። (ዕብ. 10:1) ከዚህም በተጨማሪ በወቅቱ የተከናወኑት ነገሮች መዝሙር 34:20 ፍጻሜውን እንዲያገኝ ማድረጋቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ ያለንን እምነት ሊያጠናክርልን ይገባል።
ሰኔ 13-19
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 38-44
“ይሖዋ የታመሙትን ይደግፋል”
(መዝሙር 41:1, 2) ለተቸገረ ሰው የሚያስብ ደስተኛ ነው፤ በመከራ ቀን ይሖዋ ይታደገዋል። 2 ይሖዋ ይጠብቀዋል፤ በሕይወትም ያኖረዋል። በምድር ላይ ደስተኛ ይባላል፤ ለጠላቶቹ ምኞት አሳልፈህ አትሰጠውም።
ይሖዋ ይደግፍሃል
7 ያም ቢሆን ጥንት የነበሩ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች እንዳደረጉት እኛም በምንታመምበት ጊዜ መጽናኛ፣ ጥበብና ድጋፍ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዞር ማለት እንችላለን። ንጉሥ ዳዊት እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ለተቸገረ ሰው የሚያስብ ደስተኛ ነው፤ በመከራ ቀን ይሖዋ ይታደገዋል። ይሖዋ ይጠብቀዋል፤ በሕይወትም ያኖረዋል።” (መዝ. 41:1, 2) እርግጥ ነው፣ ዳዊት ይህን ሲል በዚያ ዘመን የኖረ ለተቸገረ የሚያስብ አንድ ሰው፣ ሞትን ፈጽሞ አያይም ማለቱ እንዳልነበረ እናውቃለን። በመሆኑም ዳዊት፣ ለተቸገረ የሚያስብ ሰው በተአምራዊ ሁኔታ ሕይወቱ እንደሚቀጥልና ለዘላለም እንደሚኖር መናገሩ አይደለም። በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ሐሳብ አምላክ፣ ታማኝና ለሌሎች አሳቢ የሆኑ ሰዎችን እንደሚረዳ የሚጠቁም ነው። የሚረዳቸው እንዴት ነው? ዳዊት ይህን ሲያብራራ “ታሞ በአልጋ ላይ ተኝቶ ሳለ ይሖዋ ይደግፈዋል፤ በታመመበት ወቅት መኝታውን ሙሉ በሙሉ ትቀይርለታለህ” ብሏል። (መዝ. 41:3) ለተቸገረ አሳቢነት ያሳየ ሰው፣ አምላክ እሱንም ሆነ የታማኝነት አካሄዱን እንደማይረሳ እርግጠኛ መሆን ይችላል። በተጨማሪም አምላክ፣ ሰውነታችን ራሱን በራሱ የመጠገን ችሎታ እንዲኖረው አድርጎ ስለፈጠረን ግለሰቡ ከበሽታው ሊያገግም ይችላል።
ዘላለማዊ የሆኑትን የይሖዋን ክንዶች መደገፊያህ ማድረግ
6 አሳቢ የሆነ ሰው ችግረኞችን ይረዳል። እዚህ ላይ “ክፉ ቀን” የተባለው ክፉ ችግር የሚያጋጥምበት ማንኛውም አጋጣሚ ወይም አንድን ግለሰብ ሊያዳክም የሚችል ረጅም የመከራ ጊዜ ሊሆን ይችላል። ግለሰቡ በበሽታው ጊዜ እንዲጠብቀው በአምላክ ይታመናል፤ ሌሎችም ይሖዋ ለእርሱ ያደረገለትን የምሕረት ድርጊቶች በመናገር ‘በምድር ላይ በደስታ ያመሰግኑታል።’ አምላክ ዳዊትን “በደዌው አልጋ ሳለ” ረድቶታል። ይህም የሆነው የዳዊት ልጅ አቤሴሎም የእስራኤልን ዙፋን ለመቀማት በፈለገበት አስጨናቂ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም።—2 ሳሙኤል 15:1-6
(መዝሙር 41:3) ታሞ በአልጋ ላይ ተኝቶ ሳለ ይሖዋ ይደግፈዋል፤ በታመመበት ወቅት መኝታውን ሙሉ በሙሉ ትቀይርለታለህ።
ይሖዋ በጥንት ዘመናት ሕዝቦቹን ‘ታድጓል’
12 ዳዊት ‘ታዳጊው’ በሆነው አምላክ ላይ ምንጊዜም ቢሆን ይተማመን ነበር። ዳዊት በሕመም ላይ ስላለ አንድ ጻድቅ የአምላክ አገልጋይ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “እግዚአብሔር በክፉ ቀን ይታደገዋል። ታሞ ባለበት ዐልጋ ላይ እግዚአብሔር ይንከባከበዋል፤ በበሽታውም ጊዜ መኝታውን ያነጥፍለታል።” (መዝ. 41:1, 3) እዚህ ላይም ዳዊት “እግዚአብሔር ይንከባከበዋል” በማለት በአምላክ እንደሚተማመን መግለጹን ልብ በል። ዳዊት፣ ይሖዋ እንደሚታደገው እርግጠኛ ነበር። ታዲያ ይሖዋ የታደገው እንዴት ነበር?
13 ዳዊት፣ ይሖዋ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከበሽታ ያድነኛል ብሎ አልጠበቀም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ‘እንደሚንከባከበው’ ማለትም ታምሞ በተኛበት ወቅት የሚያስፈልገውን ድጋፍና ጥንካሬ እንደሚሰጠው ሙሉ በሙሉ ይተማመን ነበር። ደግሞም እንዲህ ዓይነት እርዳታ ያስፈልገው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ንጉሡ፣ በሽታው አቅም ያሳጣው ከመሆኑም በላይ ስለ እሱ መጥፎ ነገር በሚናገሩ ጠላቶቹ ተከብቦ ነበር። (ቁጥር 5, 6) ይሖዋ፣ የሚያጽናኑ ሐሳቦችን እንዲያስታውስ በመርዳት ዳዊትን አጠናክሮት ሊሆን ይችላል። ዳዊት “ስለ ታማኝነቴ ደግፈህ ይዘኸኛል” ብሏል። (ቁጥር 12 NW) ከዚህም በላይ ይህ ንጉሥ፣ የጤንነት ችግሩ አቅም ያሳጣውና ጠላቶቹ ስለ እሱ መጥፎ ነገር መናገራቸው የጎዳው ቢሆንም እንኳ ይሖዋ እንደ ታማኝ ሰው አድርጎ እንደሚመለከተው ማወቁ ብርታት ሰጥቶት ሊሆን ይችላል። ከጊዜ በኋላ ዳዊት ከሕመሙ አገግሟል። ይሖዋ፣ የታመሙ ሰዎችን እንደሚንከባከብ ማወቅ የሚያጽናና አይደለም?—2 ቆሮ. 1:3
(መዝሙር 41:12) እኔ በበኩሌ ንጹሕ አቋሜን በመጠበቄ ትደግፈኛለህ፤ በፊትህም ለዘላለም ታኖረኛለህ።
ይሖዋ ይደግፍሃል
18 የምንኖረው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ከመሆኑም ሌላ ሁላችንም ፍጹማን አይደለንም፤ በመሆኑም ሕመም ማናችንም ልናመልጠው የማንችለው ነገር ነው። በአሁኑ ወቅት ከሕመማችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ እንደምንድን አንጠብቅም። ይሁንና ራእይ 22:1, 2 ፍጹም ጤና የምናገኝበት ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። ሐዋርያው ዮሐንስ “የሕይወት ውኃ ወንዝ” እና “ሕዝቦችን ለመፈወስ የሚያገለግሉ” ቅጠሎች ያሏቸውን “የሕይወት ዛፎች” በራእይ ተመልክቶ ነበር። ይህ በዛሬው ጊዜም ሆነ ወደፊት የሚኖርን ከዕፀዋት የተዘጋጀ መድኃኒት አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ለመስጠት በኢየሱስ በኩል ያደረገውን ዝግጅት ያመለክታል፤ በእርግጥም ይህ በጉጉት የምንጠብቀው ነገር ነው።—ኢሳ. 35:5, 6
19 ይህን ግሩም ተስፋ እየተጠባበቅን ባለንበት በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ ስለ እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብና ስንታመም ስሜታችንን እንደሚረዳልን እናውቃለን። ልክ እንደ ዳዊት ሁሉ እኛም በምንታመምበት ጊዜ አምላካችን እንደሚደግፈን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንዲሁም “እኔ በበኩሌ ንጹሕ አቋሜን በመጠበቄ ትደግፈኛለህ፤ በፊትህም ለዘላለም ታኖረኛለህ” በማለት የተናገረውን የዳዊትን ቃላት ማስተጋባት እንችላለን።—መዝ. 41:12
ንጹሕ አቋምህን መጠበቅህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
3. ለተስፋችን በጣም አስፈላጊ ነው
15 ይሖዋ የሚፈርድልን ንጹሕ አቋማችንን መሠረት አድርጎ ስለሆነ እንዲህ ያለ አቋም መያዛችን ለተስፋችን በጣም አስፈላጊ ነው። ዳዊት ይህን ያውቅ ነበር። (መዝሙር 41:12ን በNW አንብብ።) ይህ የአምላክ አገልጋይ ለዘላለም የአምላክን ሞገስ የማግኘት ተስፋ ነበረው። በዛሬው ጊዜ እንዳሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች ሁሉ ዳዊትም ይሖዋ አምላክን በማገልገልና ከእሱ ጋር ያለውን ዝምድና ይበልጥ እያጠናከረ በመሄድ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ያደርግ ነበር። ዳዊት ይህ ተስፋው ሲፈጸም ለማየት ከፈለገ ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ መኖር እንዳለበት ያውቅ ነበር። በተመሳሳይ እኛም ንጹሕ አቋማችንን ስንጠብቅ ይሖዋ ይደግፈናል፣ ያስተምረናል፣ ይመራናል እንዲሁም ይባርከናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(መዝሙር 39:1, 2) እኔ “በምላሴ ኃጢአት እንዳልፈጽም አካሄዴን እጠብቃለሁ። ክፉ ሰው ከእኔ ጋር እስካለ ድረስ አፌን ለመጠበቅ ልጓም አስገባለሁ” አልኩ። 2 ዱዳ ሆንኩ፤ ደግሞም ዝም አልኩ፤ መልካም ነገር ከመናገር እንኳ ታቀብኩ፤ ይሁንና ሥቃዬ ከባድ ነበር።
“ለዝምታ ጊዜ አለው”
ክፉ ሰዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ አንደበታችንን መጠበቃችን አስተዋይነት ነው። በአገልግሎት ላይ ፌዘኛ ሰዎች ሲያጋጥሙን፣ የተሻለው መልስ ዝም ማለት ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም አብረውን የሚማሩ ልጆች ወይም የሥራ ባልደረቦቻችን መጥፎ ቀልዶችንና የብልግና ቃላትን ሲናገሩ፣ በቀልዳቸው ወይም በንግግራቸው እንዳልተደሰትን ለማሳየት አንዳንድ ጊዜ ዝም ማለታችን አስተዋይነት ነው። (ኤፌ. 5:3) መዝሙራዊው “ክፉዎችም በእኔ ዘንድ እስካሉ ድረስ፣ ልጓም በአፌ አስገባለሁ” በማለት ጽፏል።—መዝ. 39:1
የመዝሙር አንደኛ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
39:1, 2፦ ክፉ ሰዎች፣ የእምነት ወንድሞቻችንን ለመጉዳት በማሰብ ጥያቄ ሲያቀርቡልን ‘ልጓም በአፋችን በማስገባት’ ዝም ማለት ከሁሉ የተሻለ የጥበብ መንገድ ነው።
(መዝሙር 41:9) ሌላው ቀርቶ ከእኔ ጋር ሰላም የነበረው፣ እምነት የጣልኩበትና ከማዕዴ ይበላ የነበረ ሰው ተረከዙን በእኔ ላይ አነሳ።
መሲሑን አገኙት!
መሲሑን ወዳጁ ይከዳዋል፤ ደቀ መዛሙርቱም ትተውት ይሸሻሉ!
5 መሲሑን አታላይ የሆነ ወዳጁ እንደሚከዳው አስቀድሞ ተነግሯል። ዳዊት “እንጀራዬን ተካፍሎኝ የበላ፣ የምተማመንበትም የቅርብ ወዳጄ፣ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ” የሚል ትንቢት ተናግሯል። (መዝ. 41:9) አብረው ማዕድ የሚቋደሱ ሰዎች ወዳጆች ተደርገው ይቆጠሩ ነበር። (ዘፍ. 31:54) ስለሆነም አስቆሮቱ ይሁዳ በኢየሱስ ላይ የፈጸመው ተግባር ከሁሉ የከፋ ክህደት ነው። ኢየሱስ የሚከዳውን ሰው አስመልክቶ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ስል ስለ ሁላችሁም መናገሬ አይደለም፤ የመረጥኳቸውን አውቃለሁ። ይሁንና ‘ከማዕዴ ይበላ የነበረ ተረከዙን በእኔ ላይ አነሳ’ የሚለው የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው”፤ ኢየሱስ ይህን ያለው ዳዊት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንዳገኘ ለመጠቆም ነበር።—ዮሐ. 13:18
ይሖዋ በጥንት ዘመናት ሕዝቦቹን ‘ታድጓል’
11 ለምሳሌ ያህል፣ ዳዊት እንጀራውን ተካፍሎት የበላ የሚተማመንበት ወዳጁ እንደከዳው ገልጿል። (ቁጥር 9) ይህ ሐሳብ ዳዊት በሕይወቱ ውስጥ ያጋጠመውን አንድ ሁኔታ ያስታውሰናል። ታማኝ አማካሪው የነበረው አኪጦፌል፣ አቤሴሎም ባመፀበት ወቅት ከእሱ ጋር በማበር በንጉሡ ላይ ዓምፆ ነበር። (2 ሳሙ. 15:31፤ 16:15) በሕመም ምክንያት አቅም ያጣው ንጉሥ በአልጋው ላይ ሆኖ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ፤ ንጉሡ የክፋት እቅዳቸውን መፈጸም እንዲችሉ የእሱን መሞት በሚመኙ ሴረኞች እንደተከበበ ያውቅ ነበር።—ቁጥር 5
ሰኔ 20-26
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 45-51
“ይሖዋ የተሰበረን ልብ ችላ አይልም”
(መዝሙር 51:1-4) አምላክ ሆይ፣ እንደ ታማኝ ፍቅርህ መጠን ሞገስ አሳየኝ። እንደ ታላቅ ምሕረትህ መተላለፌን ደምስስ። 2 ከበደሌ ሙሉ በሙሉ እጠበኝ፤ ከኃጢአቴም አንጻኝ። 3 መተላለፌን በሚገባ አውቃለሁና፤ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነው። 4 አንተን፣ አዎ ከማንም በላይ አንተን በደልኩ፤ በአንተ ዓይን ክፉ የሆነውን ነገር ፈጸምኩ። ስለዚህ አንተ በምትናገርበት ጊዜ ጻድቅ ነህ፤ በምትፈርድበት ጊዜም ትክክል ነህ።
የይሖዋ ምሕረት ተስፋ ከመቁረጥ ያድነናል
9 ዳዊትና ቤርሳቤህ ስለሠሩት በደል በአምላክ ከመጠየቅ ሊያመልጡ አልቻሉም። ኃጢአታቸው ሊያስገድላቸው የሚችል ቢሆንም አምላክ ምሕረት አድርጎላቸዋል። በተለይ ለዳዊት ምሕረት ያደረገለት ይሖዋ ገብቶለት በነበረው የመንግሥት ቃል ኪዳን ምክንያት ነው። (2 ሳሙኤል 7:11–16) ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር በሠራው ኃጢአት ምን ያህል ተጸጽቶ እንደነበረ ከመዝሙር 51 መረዳት ይቻላል። ልቡ በጸጸት ተመትቶ የነበረው ንጉሥ ይህን ልብ የሚነካ መዝሙር ያጠናቀረው ነቢዩ ናታን በመለኮታዊው ሕግ ላይ የሠራው በደል ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ሕሊናውን አንቅቶ ካስገነዘበው በኋላ ነበር። ነቢዩ ናታን የዳዊትን ኃጢአት ገልጦ ለመናገር ድፍረት አስፈልጎት ነበር። ዛሬም ቢሆን ክርስቲያን ሽማግሌዎች የሌሎችን በደል ሲያስታውቁ ደፋሮች መሆን ያስፈልጋቸዋል። ንጉሡ ኃጢአቱን ከመካድና ናታን እንዲገደል ከማዘዝ ይልቅ ራሱን ዝቅ አድርጎ ኃጢአቱን ተናዘዘ። (2 ሳሙኤል 12:1-14) መዝሙር 51 ዳዊት እንዲህ ባለው ወራዳ ሁኔታ ወድቆ በነበረበት ጊዜ ለአምላክ በጸሎት የተናገረው ቃል ነው። እኛም በተለይ በደል ፈጽመን የይሖዋን ምሕረት ለማግኘት የምንናፍቅ ከሆንን ይህንን መዝሙር በጸሎታችን ብናሰላስለው ጥሩ ይሆናል።
በአምላክ ዘንድ ተጠያቂዎች ነን
10 ዳዊት ኃጢአቱን ለምን እንደሠራ ሰበብ ለመፍጠር አልፈለገም። ከዚህ ይልቅ “አቤቱ እንደ ቸርነትህ [ፍቅራዊ ደግነትህ አዓት ] መጠን ማረኝ። እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ” ሲል ጸለየ። (መዝሙር 51:1) ዳዊት በመተላለፉ የአምላክን ሕግ ድንበር ዘልሎአል። ይሁን እንጂ አምላክ በፍቅራዊ ደግነቱ ወይም በታማኝ ፍቅሩ ተገፋፍቶ ሞገስ ቢያሳየው ወደ ቀድሞው መንፈሳዊ ሁኔታ ሊመለስ ይችላል። አምላክ ከዚህ በፊት የፈጸማቸው ብዙ የምሕረት ድርጊቶች ንሥሐ የገባው ንጉሥ ፈጣሪው መተላለፉን እንደሚሽርለት የጸና እምነት አሳድሮበታል።
11 ይሖዋ በሥርየት ቀን ይቀርቡ የነበሩትን መሥዋዕቶች እንደ ጥላ አድርጎ በመጠቀም ንሥሐ የሚገቡ ሰዎችን ኃጢአት ከበደላቸው የሚያነጻበት መንገድ እንዳለው ፍንጭ ሰጥቶአል። አምላክ ምሕረቱንና ይቅርታውን የሚዘረጋልን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ባለን እምነት መሠረት እንደሆነ አሁን እናውቃለን። ዳዊት በይሖዋ ፍቅራዊ ደግነትና ምሕረት ሊታመን የቻለው ለዚህ መሥዋዕት ጥላና አምሳያ የሆኑትን መሥዋዕቶች በማሰብ ብቻ ከነበረ ዛሬ ያሉት የአምላክ አገልጋዮች አምላክ ለመዳናቸው በሰጣቸው ቤዛ ምን ያህል የበለጠ እምነት ማሳየት ይገባቸዋል!—ሮሜ 5:8፤ ዕብራውያን 10:1
12 ዳዊት እንደሚከተለው በማለት አምላክን ተማጽኖአል:- “ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፣ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤ እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፣ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና።” (መዝሙር 51:2, 3) ኃጢአት መሥራት ማለት የአምላክን የአቋም ደረጃዎች ዒላማ መሳት ማለት ነው። ይህ ሁኔታ በዳዊት ላይ ደርሶ ነበር። ይሁን እንጂ ስለሠራው በደል ግድ የሌለው፣ ቅጣት ስለደረሰበት ብቻ ወይም በሽታ ይይዘኝ ይሆናል ብሎ ያዘነ ነፍሰ ገዳይ ወይም አመንዝራ አልነበረም። ዳዊት ይሖዋን የሚወድ ሰው ስለነበረ ክፉ የሆነውን ነገር ይጠላ ነበር። (መዝሙር 97:10) በሠራው ኃጢአት ይሰቀቅ ስለነበረ አምላክ ሙሉ በሙሉ አጥቦ እንዲያጠፋለት ጸልዮአል። ዳዊት መተላለፉን በሚገባ ይገነዘብ ስለነበረ የኃጢአት ፍላጎቱ እንዲያሸንፈው በመፍቀዱ በጣም አዝኖአል። ኃጢአቱም ሁልጊዜ በፊቱ ይታየው ነበር። ምክንያቱም አንድ አምላክን የሚፈራ ሰው ንሥሐ ገብቶና ተናዝዞ የይሖዋን ይቅርታ እስካላገኘ ድረስ ሕሊናው እረፍት አይሰጠውም።
13 ዳዊት በአምላክ ዘንድ ተጠያቂነት እንዳለበት ማመኑን እንደሚከተለው በማለት አመልክቶአል:- “አንተን ብቻ በደልሁ፣ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፣ በነገርህ ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ።” (መዝሙር 51:4) ዳዊት የአምላክን ሕግ ተላልፎአል። የንግሥና ሥልጣኑንም አቃልሎአል። ከዚህም በላይ “ታላቅ የስድብ ምክንያት” በማድረግ ይሖዋን አሰድቦአል። (2 ሳሙኤል 12:14፤ ዘጸአት 20:13, 14, 17) በተጨማሪም ዳዊት ያደረጋቸው የኃጢአት ሥራዎች በእስራኤላውያን ኅብረተሰብና በራሱ ቤተሰብ ላይ የተሠሩ በደሎች ነበሩ። ልክ በአሁኑ ጊዜ አንድ የተጠመቀ በደለኛ በክርስቲያን ጉባዔና በሚወዱት ሰዎች ላይ ሐዘንና ብስጭት እንደሚያመጣው ማለት ነው። ንሥሐ የገባው ይህ ንጉሥ እንደ ኦርዮን ባሉት ሰዎች ላይ ኃጢአት እንደሠራ ቢገነዘብም በይበልጥ በኃላፊነት የሚጠየቀው በይሖዋ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። (ከዘፍጥረት 39:7-9 ጋር አወዳድር) የይሖዋ ፍርድ ጻድቅ እንደሚሆን ዳዊት ተናግሮአል። (ሮሜ 3:4) ኃጢአት የሠሩ ክርስቲያኖችም ይህን የመሰለ አመለካከት ሊኖራቸው ያስፈልጋል።
(መዝሙር 51:7-9) ንጹሕ እሆን ዘንድ በሂሶጵ ከኃጢአቴ አንጻኝ፤ ከበረዶም የበለጠ እነጣ ዘንድ እጠበኝ። 8 ያደቀቅካቸው አጥንቶች ደስ እንዲላቸው፣ የደስታንና የሐሴትን ድምፅ አሰማኝ። 9 ፊትህን ከኃጢአቴ መልስ፤ የፈጸምኳቸውንም ስህተቶች ሁሉ አስወግድ።
የይሖዋ ምሕረት ተስፋ ከመቁረጥ ያድነናል
ወደ ቀድሞው ጥሩ ሁኔታ ለመመለስ የቀረበ ልመና
18 የሕሊና ወቀሳ ደርሶበት የነበረ ማንኛውም ክርስቲያን “ሐሴትንና ደስታን አሰማኝ፣ የሰበርሃቸውም አጥንቶቼ ደስ ይላቸዋል” ሲል ዳዊት የተናገራቸውን ቃላት መረዳት አያስቸግረውም። (መዝሙር 51:8) ዳዊት ንሥሐ ከመግባቱና ኃጢአቱን ከመናዘዙ በፊት ሕሊናው ይረብሸው ስለነበረ በጣም ያዝንና ይተክዝ ነበር። ጥሩ መዘምራንና ሙዚቀኞች የሚያሰሙአቸው የደስታና የሐሴት ዝማሬዎች እንኳ አያስደስቱትም ነበር። ኃጢአተኛው ዳዊት የአምላክን ሞገስ በማጣቱ ምክንያት በጣም ይጨነቅ ስለነበረ አጥንቶቹ እንደተቀጠቀጡበት ሰው ብርቱ ሕመም ይሰማው ነበር። ይቅርታ ለማግኘት፣ መንፈሱ እንዲታደስለትና ቀድሞ የነበረው ደስታ እንዲመለስለት በብርቱ ናፍቆአል። ዛሬም ቢሆን አንድ ንሥሐ የገባ በደለኛ ከአምላክ ጋር የነበረውን ዝምድና ከማበላሸቱ በፊት የነበረውን ደስታ ለማግኘት ከፈለገ የይሖዋን ይቅርታ ማግኘት ያስፈልገዋል። አንድ ንሥሐ የገባ ሰው የነበረውን “የመንፈስ ቅዱስ ደስታ” መልሶ ካገኘ ይሖዋ ይቅር ብሎታል፣ ይወደዋል ማለት ነው። (1 ተሰሎንቄ 1:6) ይህም እንዴት ያለ መጽናናትን ያስገኛል!
19 በተጨማሪም ዳዊት “ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፣ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ” ሲል ጸልዮአል። (መዝሙር 51:9) ይሖዋ ኃጢአትን በሞገስ ዓይኑ ይመለከታል ብሎ ማሰብ አይቻልም። በዚህም ምክንያት የዳዊትን ኃጢአት እንዳይመለከት ፊቱን እንዲመልስ ተጠይቆአል። በተጨማሪም ንጉሡ አምላክ በደሉንና አመጸኝነቱን በሙሉ እንዲደመስስለት ጸልዮአል። የዳዊት መንፈስ ሊነሳሳ የሚችለው፣ ከተጫነው የሕሊና ወቀሳ ሊገላገል የሚችለውና ንሥሐ የገባው ንጉሥ የሚወደው አምላኩ ይቅርታ እንዳደረገለት ሊያውቅ የሚችለው ይሖዋ ይህን ካደረገለት ብቻ ነው።
አንተም ኃጢአት ሠርተህ ከሆነስ?
20 ማንኛውም ከባድ ኃጢአት የሠራ ራሱን የወሰነ ክርስቲያን አገልጋይ ንሥሐ ከገባ አምላክ ሞገስ እንዲያደርግለትና ከኃጢአቱ እንዲያነጻው በእርግጠኝነት ሊጠይቅ እንደሚችል መዝሙር 51 ያመለክታል። አንተም በዚህ መንገድ ከባድ በደል የሠራህ ክርስቲያን ከሆንክ ለምን የሰማዩ አባታችን ይቅርታ እንዲያደርግልህ በጸሎት አትጠይቅም? በፊቱ ሞገስ አግኝተህ ለመቆም ከፈለግህ የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልግህ ግለጽለት። ቀድሞ የነበረህን ደስታ እንዲመልስልህ ጠይቀው። ንሥሐ የገቡ ክርስቲያኖች ሁሉ ይህን የመሰለ ልመናቸውን ለይሖዋ በጸሎት ሊያቀርቡ ይችላሉ። እርሱም “በብዙ ይምራል።” (ኢሳይያስ 55:7፤ መዝሙር 103:10-14) እርግጥ አስፈላጊውን መንፈሳዊ እርዳታ እንዲሰጡ የጉባኤ ሽማግሌዎችን ቀርቦ ማነጋገር ይገባል።— ያዕቆብ 5:13-15
(መዝሙር 51:10-17) አምላክ ሆይ፣ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ በውስጤም ጽኑ የሆነ አዲስ መንፈስ አኑር። 11 ከፊትህ አትጣለኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ አትውሰድ። 12 የአንተ ማዳን የሚያስገኘውን ደስታ መልስልኝ፤ አንተን የመታዘዝ ፍላጎት በውስጤ እንዲቀሰቀስ አድርግ። 13 ኃጢአተኞች ወደ አንተ እንዲመለሱ፣ ለሕግ ተላላፊዎች መንገድህን አስተምራለሁ። 14 አምላክ ሆይ፣ የመዳኔ አምላክ፣ አንደበቴ ጽድቅህን በደስታ ያስታውቅ ዘንድ የደም ባለዕዳ ከመሆን አድነኝ። 15 ይሖዋ ሆይ፣ አፌ ምስጋናህን እንዲያውጅ ከንፈሮቼን ክፈት። 16 መሥዋዕት እንዲቀርብልህ አትፈልግምና፤ ቢሆንማ ኖሮ ባቀረብኩልህ ነበር፤ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባ አያስደስትህም። 17 አምላክን የሚያስደስተው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ አምላክ ሆይ፣ የተሰበረንና የተደቆሰን ልብ ችላ አትልም።
ንጽሕናችንን ጠብቀን መኖር እንችላለን
6 አስተዳደጋችን ወይም የቀድሞ አኗኗራችን ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች እንድንወድ ተጽዕኖ ያደርግብን ይሆናል። ያም ቢሆን ይሖዋ፣ እሱን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማገልገላችንን እንድንቀጥል የሚያስፈልጉትን ለውጦች ለማድረግ ይረዳናል። ንጉሥ ዳዊት ይህን ተገንዝቦ ነበር። ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ከፈጸመ በኋላ ይሖዋን “ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ በውስጤም ጽኑ የሆነ አዲስ መንፈስ አኑር” በማለት ተማጽኖታል። (መዝ. 51:10, 12) ደካማው ሥጋችን በኃጢአት ድርጊቶች በቀላሉ ሊማረክ ይችላል፤ ይሁንና ይሖዋ የፈቃደኝነት መንፈስ ይኸውም እሱን የመታዘዝ ፍላጎት በውስጣችን እንዲቀሰቀስ ሊረዳን ይችላል። መጥፎ ምኞቶች በውስጣችን ሥር ሰደው ንጹሕ ሐሳቦችን ገፍተው ለማውጣት ቢሞክሩም እንኳ ይሖዋ የእሱን መመሪያዎች በመታዘዝ በዚያ መሠረት መኖር እንድንችል አካሄዳችንን ይመራልናል። ይሖዋ ማንኛውም ጎጂ ነገር በእኛ ላይ እንዳይሠለጥን ሊከላከልልን ይችላል።—መዝ. 119:133
ይሖዋ የተሰበረውን ልብ አይንቅም
ንጹሕ ልብ ያስፈልጋል
4 ራሱን የወሰነ አንድ ክርስቲያን በሠራው ኃጢአት ምክንያት በመጥፎ መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ከሆነ ከይሖዋ ምህረትና ይቅርታ በተጨማሪ ምን ነገር ሊያስፈልገው ይችላል? ዳዊት “አቤቱ፣ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፣ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ” በማለት ተማጽኖአል። (መዝሙር 51:10) ዳዊት ይህን ልመና ያቀረበው ከባድ ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌው ገና ከልቡ እንዳልጠፋ ስለተገነዘበ እንደሆነ ግልጽ ነው። ዳዊት ከቤርሳቤህና ከኦርዮን ጋር በተያያዘ የሠራውን የመሰለ ከባድ ኃጢአት አልሠራን ይሆናል። ቢሆንም ወደ መጥፎ ድርጊት በሚመሩ ፈተናዎች ከመሸነፍ ለመዳንና በማንኛውም ከባድ ኃጢአት ከመካፈል ለመራቅ የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል። እንዲያውም ከሥርቆትና ከነፍስ ግድያ ጋር የሚተካከል ክብደት ካላቸው እንደ መጎምጀትና እንደ ጥላቻ የመሰሉትን ባሕርያት ከልባችን ለማውጣት መለኮታዊ እርዳታ ሊያስፈልገን ይችላል።—ቆላስይስ 3:5, 6፤ 1 ዮሐንስ 3:15
5 ይሖዋ አገልጋዮቹ በሙሉ “ንጹሕ ልብ” ማለትም የሐሳብና የዓላማ ንጽሕና እንዲኖራቸው ይፈልጋል። ዳዊትም እንዲህ ዓይነቱን ንጽሕና እንዳላሳየ ስለተገነዘበ ልቡን እንዲያጠራለትና ከመለኮታዊ የአቋም ደረጃዎች ጋር እንዲስማማ እንዲያደርግለት ጸልዮአል። በተጨማሪም መዝሙራዊው አዲስና ቅን መንፈስ ወይም የአእምሮ ዝንባሌ እንዲኖረው ፈልጎአል። ወደ ኃጢአት የሚገፋፉ ፈተናዎችን ለመቋቋምና የይሖዋን ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲጠብቅ የሚያስችለው መንፈስ አስፈልጎታል።
መንፈስ ቅዱስ በጣም አስፈላጊ ነው
6 በስህተታችንና በሠራነው መጥፎ ድርጊት ምክንያት ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜ አምላክ ሊጥለንና ቅዱስ መንፈሱን ወይም አንቀሳቃሽ ኃይሉን ከእኛ ሊወስድ እንደተቃረበ ሊሰማን ይችላል። ዳዊት እንደዚህ ተሰምቶት ነበር። “ከፊትህ አትጣለኝ፣ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ” የሚል ልመና ያቀረበው በዚህ ምክንያት ነበር። (መዝሙር 51:11) እጅግ አዝኖና ተጸጽቶ የነበረው ዳዊት በኃጢአቱ ምክንያት ይሖዋን ለማገልገል የማይበቃ ሰው እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ከአምላክ ፊት መጣል ማለት የእርሱን በረከት፣ ሞገስና ማጽናኛ ማጣት ማለት ነው። ዳዊት ወደ ቀድሞ መንፈሳዊ ሁኔታው እንዲመለስ ከተፈለገ የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ ማግኘት ይኖርበታል። የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ በንጉሡ ላይ ካረፈ ይሖዋን ለማስደሰት የሚያስችለውን መለኮታዊ መመሪያ እንዲያገኝ በጸሎት ሊጠይቅ፣ ከኃጢአት ሊርቅና በጥበብ ሊያስተዳድር ይችላል። ዳዊት የመንፈስ ቅዱስ ሰጪ በሆነው አምላክ ላይ ኃጢአት መሥራቱን ተገንዝቦ ይሖዋ መንፈሱን እንዳይወሰድበት መማጸኑ ተገቢ ነው።
7 እኛስ? መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠን መጸለይና የመንፈስ ቅዱስን መመሪያ ባለመከተል እርሱን ከማሳዘን መጠበቅ ይገባናል። (ሉቃስ 11:13፤ ኤፌሶን 4:30) ይህን ሳናደርግ ብንቀር መንፈሱን ልናጣና የዚህ መንፈስ ፍሬዎች የሆኑትን ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ትዕግሥትን፣ ደግነትን፣ ጥሩነትን፣ እምነትን፣ የዋህነትንና ራስን መግዛትን ማሳየት ሊያቅተን ይችላል። በተለይ ንሥሐ ባለመግባት ኃጢአት መሥራታችንን ብንቀጥል ይሖዋ አምላክ ቅዱስ መንፈሱን ይወስድብናል።
የማዳን ደስታ
8 መንፈሣዊ ተሐድሶ ያገኘ ንሥሐ የገባ ክርስቲያን ዳግመኛ በይሖዋ የመዳን ዝግጅት ሊደሰት ይችላል። ዳዊትም ይህንን በመናፈቅ “የማዳንህን ደስታ ስጠኝ፣ በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ” ሲል ተማጽኖአል። (መዝሙር 51:12) ይሖዋ አምላክ በሚሰጠው የተረጋገጠ የመዳን ተስፋ ሐሴት ማድረግ ምንኛ ግሩም ነገር ነው! (መዝሙር 3:8) ዳዊት በአምላክ ላይ ኃጢአት ከሠራ በኋላ የመዳን ደስታ እንዲመለስለት በጸሎት ጠይቆአል። ይሖዋ በኋለኞቹ ዘመናት በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት በኩል የመዳን ዝግጅት አድርጓል። እኛም ራሳችንን የወሰንን የአምላክ አገልጋዮች ሆነን እያለ ከባድ ኃጢአት ከሠራን በኋላ የመዳን ደስታ እንዲመለስልን የምንፈልግ ከሆንን ንሥሐ የመግባት ዝንባሌ እንዲኖረንና በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት እስከመሥራት የሚያደርስ ከባድ ኃጢአት እንዳንሠራ መጠንቀቅ ይኖርብናል።—ማቴዎስ 12:31, 32፤ ዕብራውያን 6:4-6
9 ዳዊት ይሖዋ “በእሽታ መንፈስ” እንዲደግፈው ጠይቋል። ይህ የእሽታ ወይም የፈቃደኝነት መንፈስ የሚያመለክተው አምላክ ለመርዳት ፈቃደኛ መሆኑን ወይም ቅዱስ መንፈሱን ሳይሆን ዳዊትን የሚገፋፋውን የአእምሮ ዝንባሌ ነው። ዳዊት አምላክ ትክክል የሆነውን ነገር እንዲያደርግና ዳግመኛ ወደ ኃጢአት እንዳይገባ የሚያስችለውን የፈቃደኝነት መንፈስ በመስጠት እንዲደግፈው ጸልዮአል። ይሖዋ አምላክ አገልጋዮቹን ዘወትር ይደግፋል። በተለያዩ ፈተናዎች የጎበጡትን አገልጋዮቹን ቀና ያደርጋል። (መዝሙር 145:14) ይህን መገንዘባችን፣ በተለይ በደል ሠርተን የተጸጸትንና ከእንግዲህ ወዲህ አምላክን በታማኝነት ለማገልገል የወሰንን ከሆንን በጣም ያጽናናናል።
ሕግ ተላላፊዎች የሚማሩት ምንድን ነው?
10 አምላክ ከፈቀደለት ዳዊት ለይሖዋ ምህረት ያለውን አድናቆት የሚያሳይና ሌሎች ሰዎችን የሚጠቅም ከራስ ወዳድነት የራቀ ሥራ ለመሥራት ፈልጎአል። ንሥሐ የገባው ንጉሥ ለይሖዋ ባቀረበው ጸሎት ቀጥሎ “ለሕግ ተላላፎች መንገድህን አስተምራለሁ፣ ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ” ብሎአል። (መዝሙር 51:13) ኃጢአተኛው ዳዊት የአምላክን ሕግ ተላላፊዎች ሊያስተምር የሚችለው እንዴት ነው? ምን ነገር ሊነግራቸው ይችላል? ይህስ ምን ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?
11 ዳዊት እሥራኤላውያን ሕግ ተላላፊዎችን ከክፉ መንገዳቸው እንዲመለሱ በማሰብ የይሖዋን መንገድ በሚያሳያቸው ጊዜ ኃጢአት ምን ያህል ክፉ እንደሆነ፣ ንሥሐ ምን እንደሆነና የአምላክን ምህረት እንዴት ለማግኘት እንደሚቻል ሊነግራቸው ይችላል። ዳዊት የይሖዋን ሞገስ ማጣትና የሕሊና ጸጸት ምን ያህል እንደሚያሰቃይ ስለቀመሰ ንሥሐ ለገቡና ልባቸው ለተሰበረ ኃጢአተኞች ርህሩህ አስተማሪ ሊሆን ይችላል። እርግጥ፣ የራሱን ምሳሌ በመጥቀስ ሌሎችን ለማስተማር የሚችለው እርሱ ራሱ የይሖዋን የአቋም ደረጃዎች ከተቀበለና የይሖዋን ይቅርታ ካገኘ በኋላ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም በመለኮታዊ ሕግጋት ለመገዛት የማይፈልጉ ሰዎች የአምላክን ሕግጋት ለሌሎች ለማስተማር አይችሉም።—መዝሙር 50:16, 17
12 ዳዊት ፍላጎቱን በሌላ አነጋገር ሲገልጽ “የመድኃኒቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፣ ከደም አድነኝ፣ አንደበቴም በአንተ ጽድቅ ትደሰታለች” ብሎአል። (መዝሙር 51:14) የደም ወንጀል የሞት ቅጣት ያስከትላል። (ዘፍጥረት 9:5, 6) ስለዚህ ዳዊት የመድኃኒቱ አምላክ በኦርዮን ላይ ከፈጸመው የደም ወንጀል እንዳዳነው ማወቁ የልብና የአእምሮ ሰላም ይሰጠዋል። ከዚያ በኋላ አንደበቱ ስለራሱ ሳይሆን ስለአምላክ ጽድቅ በደስታ ሊዘምር ይችላል። (መክብብ 7:20፤ ሮሜ 3:10) ማንኛውም በዘመናችን የሚኖር ሰው በዝሙት ያረከሰውን ሰው ንጽሕና ሊመልስ ወይም የገደለውን ሰው ከሞት ሊያስነሳ እንደማይችል ሁሉ ዳዊትም የሠራውን የምንዝር ኃጢአት ሊፍቅ ወይም ኦርዮንን ከመቃብር ሊያወጣ አይችልም። ኃጢአት ለመሥራት በምንፈተንበት ጊዜ ይህን ማሰብ አይገባንምን? ይሖዋ በጽድቅ ላሳየን ምህረት ምን ያህል አድናቂዎች መሆን ይገባናል! እንዲያውም ለይሖዋ ምህረት ያለን አድናቆት ሌሎች ሰዎችን ወደዚህ የጽድቅና የይቅርታ ምንጭ እንድንመራ ሊገፋፋን ይገባል።
13 አምላክ በምህረት ከንፈሮቹን ካልከፈተለት በስተቀር ማንኛውም ኃጢአተኛ ስለ ይሖዋ እውነቶች በመናገር ይሖዋን ለማወደስ ከንፈሮቹን በትክክለኛው መንገድ ለመክፈት አይችልም። በዚህም ምክንያት ዳዊት “አቤቱ፣ ከንፈሮቼን ክፈት፣ አፌም ምስጋናህን ያወራል” ሲል ጸልዮአል። (መዝሙር 51:15) ዳዊት አምላክ ይቅርታ ስላደረገለት የሕሊና እረፍት ካገኘ በኋላ ሕግ ተላላፊዎችን ስለ ይሖዋ መንገዶች ሊያስተምርና ይሖዋን ከፍ ከፍ ሊያደርግ ይችላል። ልክ እንደ ዳዊት ኃጢአታቸው ይቅር የተባለላቸው ሁሉ ይሖዋ ያሳያቸውን ይገባናል የማይሉትን ደግነት ማድነቅና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የአምላክን እውነት ማወጅና ምስጋናውን መናገር ይኖርባቸዋል።—መዝሙር 43:3
አምላክ የሚቀበላቸው መሥዋዕቶች
14 ዳዊት ጥልቅ የሆነ ማስተዋል አግኝቶ ስለነበረ “መሥዋዕትን ብትወድስ በሰጠሁህ ነበር፣ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ደስ አያሰኝህም” ለማለት ችሎአል። (መዝሙር 51:16) የሕጉ ቃል ኪዳን ለአምላክ የእንስሳት መሥዋዕት እንዲቀርብ ያዝ ነበር። ዳዊት የሠራው የምንዝርና ነፍስ የመግደል ወንጀል ግን በሞት የሚያስቀጣው ስለነበረ በእንስሳት መሥዋዕት የሚሠረይ አልነበረም። ሊሠረይ የሚችል ቢሆን ኖር የፈለገውን ያህል ዋጋ ከፍሎ መሥዋዕት ቢያቀርብ ቅር አይለውም ነበር። ልባዊ የሆነ ንሥሐ ከሌለ መሥዋዕት ምንም ዓይነት ዋጋ የለውም። ስለዚህ መጥፎ ድርጊት መፈጸሙን እየቀጠለ አንድ ዓይነት ጥሩ ነገር በመሥራት ላካክስ እችላለሁ ብሎ ማሰብ ስህተት ነው።
15 ዳዊት በመቀጠል “የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፣ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም” ብሎአል። (መዝሙር 51:17) አንድ ንሥሐ የገባ ሰው ሊያቀርብ የሚችለው ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት “የተሰበረ መንፈስ” ነው። እንዲህ ያለው ሰው የእልከኝነት መንፈስ አይኖረውም። የተሰበረ መንፈስ ያለው ራሱን ለአምላክ የወሰነ ሰው በሠራው ኃጢአት ምክንያት ልቡ በጣም ያዝናል። አምላክ ሞገሱን እንደነሳው ስለሚታወቀው ራሱን ዝቅ ያደርጋል። መለኮታዊ ሞገስ እንደገና ለማግኘት ሲል ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ ነው። ከኃጢአታችን ንሥሐ ከመግባታችንና ሙሉ ልባችንን ሰጥተን ለአምላክ ከማደራችን በፊት ምንም ዓይነት ዋጋ ያለው ነገር ለአምላክ ልናቀርብ አንችልም።—ናሆም 1:2
16 አምላክ እንደ ተሰበረና እንደ ተቀጠቀጠ ልብ ያለውን መሥዋዕት አልቀበልም አይልም። ስለዚህ ሕዝቦቹ ሆነን ስንኖር ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥመን ተስፋ መቁረጥ አይገባንም። በሕይወት መንገድ ላይ በምንጓዝበት ጊዜ ልባችን መለኮታዊ ምሕረት ለማግኘት እንዲጮህ የሚያደርገው እንቅፋት ቢያጋጥመን ተስፋችን ተሟጥጦ አልቋል ማለት አይደለም። ከባድ ኃጢአት ብንሠራ እንኳን ንሥሐ ከገባን ይሖዋ የተሰበረውን ልባችንን አሽቀንጥሮ አይጥልም። የክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት መሠረት በማድረግ ይቅርታ ያደርግልናል፣ ወደ ሞገሱም ይመልሰናል። (ኢሳይያስ 57:15፤ ዕብራውያን 4:16፤ 1 ዮሐንስ 2:1) ይሁን እንጂ ጸሎታችን ልክ እንደ ዳዊት መለኮታዊ ሞገስ እንደገና እንዲሰጠን መሆን ይኖርበታል እንጂ የሚያስፈልገን ተግሣጽና እርማት እንዲቀርልን መሆን አይገባውም። አምላክ ዳዊትን ይቅር ብሎታል፤ ሆኖም ተገቢውን ቅጣት ሰጥቶታል።—2 ሳሙኤል 12:11-14
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(መዝሙር 45:4) በግርማህም ድል ለመቀዳጀት ገስግስ፤ ፈረስህን እየጋለብክ ለእውነት፣ ለትሕትናና ለጽድቅ ተዋጋ፤ ቀኝ እጅህም የሚያስፈሩ ተግባሮችን ያከናውናል።
ክብር የተጎናጸፈውን ንጉሥ ክርስቶስን አወድሱ!
ንጉሡ “ስለ እውነት” ሲል ይገሰግሳል
11 መዝሙር 45:4ን አንብብ። ተዋጊው ንጉሥ ጦርነት የሚያውጀው ግዛቱን ለማስፋትና ሰዎችን ለማስገበር አይደለም። ከዚህ ይልቅ የተቀደሰ ዓላማ ይዞ የጽድቅ ጦርነት ያውጃል። “ስለ እውነት፣ ስለ ትሕትና ስለ ጽድቅ” ይገሰግሳል። ከሁሉ ይበልጥ ጥብቅና ሊቆምለት የሚገባው ታላቅ እውነት የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ነው። ሰይጣን በይሖዋ ላይ ባመፀ ጊዜ የእሱን አገዛዝ ሕጋዊነት ተገዳድሯል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ አጋንንትም ሆኑ ሰዎች ይህን መሠረታዊ እውነት ሲቃረኑ ቆይተዋል። ይሖዋ የቀባው ንጉሥ የይሖዋን ሉዓላዊ አገዛዝ ትክክለኛነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማረጋገጥ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ደርሷል።
(መዝሙር 48:12, 13) በጽዮን ዙሪያ ሂዱ፤ በዙሪያዋም ተጓዙ፤ ማማዎቿን ቁጠሩ። 13 የመከላከያ ግንቦቿን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ። ለመጪዎቹ ትውልዶች መናገር ትችሉ ዘንድ፣ የማይደፈሩ ማማዎቿን በሚገባ አጢኑ።
መንፈሳዊውን ገነት ይበልጥ አስውቡት
13 በእውነት ቤት የቆየንበት ጊዜ ምንም ያህል ቢሆን ለሌሎች ስለ ይሖዋ ድርጅት ማውራት ይኖርብናል። በዚህ ክፉ፣ ምግባረ ብልሹና ፍቅር የጎደለው ዓለም ውስጥ መንፈሳዊ ገነት መኖር መቻሉ በእርግጥም በዘመናችን የተፈጸመ ተአምር ነው! የይሖዋን ድርጅት ወይም ‘የጽዮንን’ አስደናቂ ነገሮች እንዲሁም የመንፈሳዊውን ገነት እውነት “ለመጪዎቹ ትውልዶች” በደስታ ልናስተላልፍ ይገባል።—መዝሙር 48:12-14ን አንብብ።
ሰኔ 27–ሐምሌ 3
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 52-59
“ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል”
(መዝሙር 55:2) ትኩረት ስጠኝ፤ መልስልኝም። ያሳሰበኝ ጉዳይ እረፍት ነስቶኛል፤ ደግሞም በጣም ተጨንቄአለሁ።
(መዝሙር 55:4, 5) ልቤ በውስጤ በጣም ተጨነቀ፤ የሞት ፍርሃትም ዋጠኝ። 5 ፍርሃት አደረብኝ፤ ደግሞም ተንቀጠቀጥኩ፤ ብርክም ያዘኝ።
(መዝሙር 55:16-18) እኔ በበኩሌ አምላክን እጣራለሁ፤ ይሖዋም ያድነኛል። 17 በማታ፣ በጠዋትና በቀትር እጨነቃለሁ፤ ደግሞም እቃትታለሁ፤ እሱም ድምፄን ይሰማል። 18 በእኔ ላይ ጦርነት ከከፈቱ ሰዎች ይታደገኛል፤ ሰላም እንዳገኝም ያደርጋል፤ እጅግ ብዙ ሰዎች በእኔ ላይ ተነስተዋልና።
የመዝሙር ሁለተኛ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
55:4, 5, 12-14, 16-18፦ ዳዊት የገዛ ልጁ አቤሴሎም የጠነሰሰበት ሴራና የቅርብ አማካሪው አኪጦፌል የፈጸመበት ክህደት ከፍተኛ የስሜት ቀውስ አስከትሎበታል። ይሁንና እነዚህ ችግሮች በይሖዋ ላይ ያለውን የመተማመን ስሜት አልቀነሱበትም። ስሜታችንን የሚጎዳ ነገር ቢደርስብን በይሖዋ ላይ ያለንን የመተማመን መንፈስ እንዲያዳክምብን መፍቀድ አይኖርብንም።
ሸክማችሁን ምን ጊዜም በይሖዋ ላይ ጣሉ
በአንድ ወቅት ንጉሥ ዳዊት የደረሰበት ችግር ከአቅሙ በላይ እንደሆነ ያህል ተሰምቶት ነበር። በመዝሙር 55 ላይ እንደምናነበው ጠላቶቹ ባደረሱበት ችግርና ለእርሱ በነበራቸው ከፍተኛ ጥላቻ ምክንያት በጭንቀት እንደተዋጠ ይነግረናል። እጅግ ተጨንቆና በፍርሃት ተውጦ ነበር። በደረሰበት ሐዘን ምክንያት ይቃትት ነበር። (መዝሙር 5:12-14) የሚዘልፈኝ ጠላት አይደለምና፤ ቢሆንማ ኖሮ በቻልኩት ነበር። በእኔ ላይ የተነሳው ባላጋራ አይደለም፤ ቢሆንማ ኖሮ ከእሱ በተሸሸግኩ ነበር። 135:2, 5, 17) ሆኖም ይህ ሁሉ መከራ ቢደርስበትም ይህን መከራ መቋቋም የሚችልበት መንገድ አግኝቷል። እንዴት? አምላኩ እንዲረዳው በመጠየቅ ነው። እርሱ የተሰማው ዓይነት ስሜት ለሚሰማቸው ሰዎች የሰጠው ምክር ‘ሸክምህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል’ የሚል ነው።—መዝሙር 55:22
(መዝሙር 55 ነገር ግን ይህን ያደረግከው እንደ እኔው ሰው የሆንከው አንተ ነህ፤ በሚገባ የማውቅህ የገዛ ጓደኛዬ ነህ። 14 በመካከላችን የጠበቀ ወዳጅነት ነበር፤ ከብዙ ሕዝብ ጋር ወደ አምላክ ቤት አብረን እንሄድ ነበር።
ሸክማችሁን ምን ጊዜም በይሖዋ ላይ ጣሉ
የቅርብ ወዳጅ ሲከዳ የሚፈጠረውን ችግር መቋቋም
ይህም ዳዊት መዝሙር 55ን እንዲጽፍ ወደገፋፋው ድርጊት ይወስደናል። በዚህ ወቅት በከፍተኛ የስሜት ውጥረት ውስጥ ነበር። “ልቤ በላዬ ተናወጠብኝ፣ የሞት ድንጋጤም ወደቀብኝ” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 55:4) ይህን ሥቃይ ያስከተለበት ምንድን ነው? የዳዊት ልጅ አቤሴሎም ንግሥናውን ከዳዊት ለመንጠቅ አሢሮ ነበር። (2 ሳሙኤል 15:1-6) ይህ የልጁ ክህደት ሳያንስ ይባስ ብሎ የዳዊት ታማኝ አማካሪ የነበረው አኪጦፌል በዳዊት ላይ በተጠነሰሰው ሤራ ተባባሪ ሆነ። ዳዊት በመዝሙር 55:12-14 ላይ የተናገረው ስለ አኪጦፌል ነው። ዳዊት በዚህ ሤራና ክህደት ምክንያት ከኢየሩሳሌም ለመሸሽ ተገደደ። (2 ሳሙኤል 15:13, 14) ይህ ሁኔታ እንዴት ያለ ጭንቀት አስከትሎበት መሆን አለበት!
(መዝሙር 55:22) ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል። ጻድቁ እንዲወድቅ ፈጽሞ አይፈቅድም።
የመዝሙር ሁለተኛ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
55:22፦ ሸክማችንን በይሖዋ ላይ የምንጥለው እንዴት ነው? (1) ስላሳሰበን ነገር ለይሖዋ በጸሎት በመንገር፣ (2) ቃሉና ድርጅቱ የሚሰጡንን መመሪያና ድጋፍ በመቀበል እንዲሁም (3) ችግሩን ለማቅለል የተቻለንን ያህል በመጣር ሸክማችንን በይሖዋ ላይ መጣል እንችላለን።—ምሳሌ 3:5, 6፤ 11:14፤ 15:22፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7
ራስህን ከልክ በላይ አታስጨንቅ
ሙሴ በርካታ አሳሳቢ ጥያቄዎች ወደ አእምሮው መጥተው እንደነበር ግልጽ ነው። “እነሆ፣ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ:- የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ ባልሁም ጊዜ:- ስሙስ ማን ነው? ባሉኝ ጊዜ፣ ምን እላቸዋለሁ?” በማለት ይሖዋን ጠይቋል። (ዘጸአት 3:13, 14) በተጨማሪም ሙሴ፣ ፈርዖን ባያምነው ምን እንደሚያደርግ አሳስቦት ነበር። አሁንም ይሖዋ ለነቢዩ ምላሽ ሰጥቶታል። ሌላው የመጨረሻው የሙሴ ችግር “አፈ ትብ” አለመሆኑ ነበር። ይህ ችግር ምን መፍትሄ ሊኖረው ይችላል? እንደ ሙሴ ሆኖ እንዲናገር ይሖዋ አሮንን ሰጠው።—ዘጸአት 4:1-5, 10-16
ሙሴ ለጥያቄዎቹ በተሰጠው መልስ መሠረት በመዘጋጀትና በአምላክ ላይ በመታመን ይሖዋ እንዳዘዘው ማድረግ ጀመረ። በፈርዖን ፊት በሚቀርብበት ጊዜ ምን ነገር ሊፈጠር እንደሚችል በማሰብ አእምሮውን ከማስጨነቅ ይልቅ ሙሴ እንደተባለው ‘እንዲሁ አደረገ።’ (ዘጸአት 7:6) ሙሴ ራሱን ከልክ በላይ አስጨንቆ ቢሆን ኖሮ እምነቱ ሊዳከምና የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ድፍረት ሊያጣ ይችል ነበር።
ሙሴ የተሰጠውን ኃላፊነት አጥጋቢ በሆነ መንገድ ለመወጣት እንዲችል የተጠቀመበት ሚዛኑን የጠበቀ አካሄድ ሐዋርያው ጳውሎስ “ጤናማ አእምሮ” ብሎ ለጠቀሰው ነገር ምሳሌ የሚሆን ነው። (2 ጢሞቴዎስ 1:7፤ ቲቶ 2:2-6 NW) ሙሴ ጤናማ አእምሮ ባይኖረው ኖሮ በተሰጠው ከባድ ኃላፊነት የተነሳ ከልክ በላይ ሊጨነቅና እስከ ጭራሹም ኃላፊነቱን አልቀበልም እስከማለት ሊደርስ ይችል ነበር።
ሐሳብህን ተቆጣጠር
በዕለታዊ ሕይወትህ ውስጥ የእምነት ፈተና ወይም መከራ ሲደርስብህ ምን ታደርጋለህ? ከፊትህ የተደቀኑትን እንቅፋቶች ወይም ተፈታታኝ ሁኔታዎች በማሰብ ብቻ በፍርሃት ትዋጣለህ? ወይስ ሚዛናዊ አመለካከት ትይዛለህ? አንዳንዶች እንደሚሉት ‘ገና ድልድዩ ጋ ሳትደርስ አትሻገር።’ ምናባዊውንም ድልድይ መሻገር አስፈላጊ ላይሆን ይችላል! ታዲያ ገና ይሆናል በሚል ፍራቻ ለምን በጭንቀት ትሠቃያለህ? መጽሐፍ ቅዱስ “ሰውን የልቡ ኃዘን [“ጭንቀት፣” NW] ያዋርደዋል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 12:25) ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው ውሳኔ ከማድረግ ይልቅ ዛሬ ነገ እያለ አንድን ጉዳይ ማጓተቱ ወደ ባሰ ችግር ውስጥ እንዲገባ ሊያደርገው ይችላል።
ከሁሉ የሚከፋው ደግሞ አላስፈላጊ ጭንቀት መንፈሳዊ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑ ነው። ሀብት ያለው የማታለል ኃይልና “የዚህ ዓለም አሳብ [“ጭንቀት፣” NW] ‘ለመንግሥቱ ቃል’ ያለንን አድናቆት ሙሉ በሙሉ ሊያንቀው እንደሚችል ኢየሱስ ክርስቶስ አመልክቷል። (ማቴዎስ 13:19, 22) እሾኽ ቡቃያው አድጎ እንዳያፈራ እንደሚያደርግ ሁሉ ከልክ በላይ መጨነቅም መንፈሳዊ እድገት እንዳናደርግና ለአምላክ ክብር በሚያመጣ መንገድ ፍሬ እንዳናፈራ ሊያግደን ይችላል። እንዲያውም አንዳንዶች ራሳቸው የፈጠሩት አፍራሽ የሆነ ጭንቀት ራሳቸውን ለይሖዋ እንዳይወስኑ አድርጓቸዋል። ‘ራሴን ስወስን ከገባሁበት ቃል ጋር ተስማምቶ መኖር ቢያቅተኝስ?’ ብለው ይፈራሉ።
ሐዋርያው ጳውሎስ በምናደርገው መንፈሳዊ ውጊያ ‘አእምሮን ሁሉ ማርከን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እንድናደርግ’ ነግሮናል። (2 ቆሮንቶስ 10:5) ቀንደኛ ጠላታችን የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ በሚያስጨንቁን ነገሮች ተጠቅሞ እኛን ተስፋ ለማስቆረጥና በአካላዊ፣ በስሜታዊና በመንፈሳዊ እኛን ለማዳከም ከፍተኛ ፍላጎት አለው። ሰይጣን የመወላወል ዝንባሌ ያላቸውን ዝንጉ ሰዎች እንዴት ወጥመድ ውስጥ ማስገባት እንደሚችል በሚገባ ያውቃል። ጳውሎስ “ለዲያብሎስ ፈንታ አትስጡ” በማለት ክርስቲያኖችን ያስጠነቀቀውም ለዚህ ነው። (ኤፌሶን 4:27) ሰይጣን “የዚህ ዓለም አምላክ” እንደመሆኑ መጠን ‘የማያምኑትን ሰዎች አሳብ በማሳወር’ በኩል ተሳክቶለታል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) የእኛንም አሳብ እንዲቆጣጠር ፈጽሞ መፍቀድ አይኖርብንም!
እርዳታ ማግኘት ይቻላል
አንድ ልጅ ችግር ሲያጋጥመው ወደሚያፈቅረው አባቱ ዘንድ በመሄድ መመሪያና ማጽናኛ ሊያገኝ ይችላል። በተመሳሳይም እኛ ችግሮቻችንን ይዘን ወደ ሰማያዊው አባታችን ወደ ይሖዋ ልንሄድ እንችላለን። እንዲያውም ይሖዋ ሸክማችንንና ጭንቀታችንን በእርሱ ላይ እንድንጥል ግብዣ አቅርቦልናል። (መዝሙር 55:22) አንድ ልጅ አባቱ አንድ ጊዜ ዋስትና ከሰጠው በኋላ በገጠመው ችግር ዳግመኛ እንደማይጨነቅ ሁሉ እኛም ሸክማችንን ሁሉ በይሖዋ ላይ እርግፍ አድርገን እንጥላለን።—ያዕቆብ 1:6
ጭንቀታችንን በይሖዋ ላይ ልንጥል የምንችለው እንዴት ነው? ፊልጵስዩስ 4:6, 7 መልሱን ይሰጠናል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” አዎን፣ ይሖዋ የምናቀርበውን ያልተቋረጠ ጸሎትና ምልጃ ሰምቶ አእምሯችን አስፈላጊ ባልሆኑ ጭንቀቶች እንዳይረበሽ ሊከላከል የሚችል ውስጣዊ ሰላም ሊሰጠን ይችላል።—ኤርምያስ 17:7, 8፤ ማቴዎስ 6:25-34
ሆኖም ከጸሎታችን ጋር ተስማሚ የሆነ ሥራ ለማከናወን እንድንችል በአካልም ሆነ በአእምሮ ራሳችንን ማግለል አይኖርብንም። (ምሳሌ 18:1) ከዚያ ይልቅ ከችግሮቻችን ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና መመሪያዎች መመርመራችን የተገባ ይሆናል። እንዲህ በማድረግ በራሳችን ማስተዋል ከመደገፍ እንርቃለን። (ምሳሌ 3:5, 6) ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁ ጉዳዮችንና የተለያዩ ችግሮችን በተመለከተ በቂ መረጃዎችን ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስንና የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎችን መመልከት ይችላሉ። በተጨማሪም ሁልጊዜ እኛን ለማነጋገር ደከመን ሰለቸን የማይሉ ጥበብና ተሞክሮ ያላቸው ሽማግሌዎችና የጎለመሱ ክርስቲያኖች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ስላሉልን ተባርከናል። (ምሳሌ 11:14፤ 15:22) እንደ እኛ ስሜታዊ ውጥረት ውስጥ ያልገቡና ስለ ጉዳዩ አምላካዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ችግራችንን በሌላ አቅጣጫ እንድንመለከተው ሊረዱን ይችላሉ። ምንም እንኳ ውሳኔ ማድረጉን ለእኛ ቢተዉልንም ከፍተኛ የማበረታቻና የድጋፍ ምንጭ ሊሆኑልን ይችላሉ።
“አምላክን መጠባበቅ”
በሐሳባችን የምንፈጥራቸው ችግሮች የሚያስከትሉት ጭንቀት ሳይጨመር እንኳ በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመወጣት የምናደርገው ትግል የሚፈጥርብን ውጥረት ራሱ ቀላል እንዳልሆነ ማንም አይክድም። ገና ለገና ሊከሰት ይችል ይሆናል በሚል ሐሳብ የምንጨነቅና በፍርሃት የምንዋጥ ከሆነ በጸሎትና በምልጃ ወደ ይሖዋ እንቅረብ። መመሪያና ጥበብ ለማግኘትና ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዲኖርህ ወደ ይሖዋ ቃልና ድርጅት ዞር በል። ምንም ዓይነት ሁኔታ ያጋጥመን ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ እናገኛለን።
መዝሙራዊው ከፍተኛ የልብ ሐዘንና የመረበሽ ስሜት ባደረበት ጊዜ “ነፍሴ ሆይ፣ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? [“አምላክን ተጠባበቂ፣” NW] የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 42:11) ይህ የእኛንም ስሜት የሚያንጸባርቅ ይሁን።
አዎን፣ በእርግጥ ሊከሰት ይችላል ብለህ ለምትጠብቀው ነገር እቅድ አውጣ፤ ገና ለገና ሊከሰት ይችላል በሚል የሚያሳስብህን ጉዳይ ደግሞ ለይሖዋ ተውለት። “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።”—1 ጴጥሮስ 5:7
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(መዝሙር 56:8) ከቦታ ቦታ ስንከራተት አንድ በአንድ ትከታተላለህ። እንባዬን በአቁማዳህ አጠራቅም። ደግሞስ በመጽሐፍህ ውስጥ ሰፍሮ የለም?
ስለ እኔ በእርግጥ የሚያስብ አለ?
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የመዝሙር መጽሐፍ፣ ንጉሥ ዳዊትን የመሰሉ በጥንት ዘመን የነበሩ ዕብራውያን የዘመሯቸውን በርካታ ማራኪ መዝሙሮች የያዙ ሲሆን እነዚህ መዝሙሮች ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ፍቅራዊ አሳቢነት እንደሚያሳይ ይገልጻሉ። በመዝሙር 56:8 ላይ ንጉሥ ዳዊት “እንባዬን በዕቃህ አጠራቅም፤ ሁሉስ በመዝገብህ የተያዘ አይደለምን?” በማለት አምላክን እንደተማጸነ እናነባለን። ከዚህ ንጽጽር ማየት እንደሚቻለው ይሖዋ፣ መዝሙራዊው እየደረሰበት ያለውን መከራ ብቻ ሳይሆን መከራው በስሜቱ ላይ ያስከተለውን ሥቃይ ጭምር እንደሚያውቅ ዳዊት ተረድቶ ነበር። ይሖዋ የዳዊትን ሥቃይ ያውቅ የነበረ ከመሆኑም ሌላ እንባውን እንዲያፈስ ያደረገውን ውስጣዊ ስሜት ተመልክቶ ነበር። እውነት ነው፣ ፈጣሪያችን ፈቃዱን ለማድረግ የሚጥሩትንና “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን” ሰዎች ሁሉ ይመለከታል።
በአቍማዳ ውስጥ ያለ እንባ
ዳዊት አቍማዳን አስመልክቶ ከተናገረው ልብ የሚነካ ሐሳብ ትልቅ ትምህርት እናገኛለን። እንዴት? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ዓለም የሚቆጣጠረው ሰይጣን እንደሆነና በዛሬው ጊዜም “በታላቅ ቍጣ” እንደተሞላ ይናገራል። በመሆኑም በምድራችን ላይ አስጨናቂ ሁኔታዎች ይታያሉ። (ራእይ 12:12) በዚህም የተነሳ ብዙዎች በተለይም አምላክን ለማስደሰት የሚጥሩ ሰዎች ልክ እንደ ዳዊት ስሜታዊ፣ አእምሯዊና አካላዊ ሥቃይ ይደርስባቸዋል። አንተስ ያለህበት ሁኔታ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው? እነዚህ ታማኝ ሰዎች ‘እያለቀሱም’ ቢሆን ድፍረት በተሞላበት ሁኔታ አቋማቸውን ሳያጎድፉ ለመኖር ጥረት ከማድረግ ፈጽሞ ወደኋላ አይሉም። (መዝሙር 126:6) እነዚህ ሰዎች፣ በሰማይ የሚኖረው አባታቸው እየደረሰባቸው ያለውን ችግር እንደሚያይ ብቻ ሳይሆን ችግሩ የሚያስከትልባቸውን የስሜት መረበሽም በሚገባ እንደሚረዳላቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። ርኅሩኅ የሆነው አምላክ የአገልጋዮቹን ሥቃይ በሚገባ የሚረዳ ከመሆኑም በላይ ያፈሰሱትን እንባና ያሳለፉትን ችግር ፈጽሞ አይረሳም። በመሆኑም በምሳሌያዊ አነጋገር እንባቸውን በአቍማዳ ያጠራቅማል።
(መዝሙር 59:1, 2) አምላኬ ሆይ፣ ከጠላቶቼ ታደገኝ፤ በእኔ ላይ ከተነሱት ሰዎች ጠብቀኝ። 2 ከክፉ አድራጊዎች ታደገኝ፤ ከጨካኝ ሰዎችም አድነኝ።
ይሖዋ ለእርዳታ የምናሰማውን ጩኸት ይሰማል
13 ታዲያ ችግራችንን ለይሖዋ በጸሎት መንገራችን ብቻ በቂ ነው? አይደለም። ከዚህ የበለጠ ነገር ማድረግም ይጠበቅብናል። ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። ንጉሥ ሳኦል ዳዊትን እንዲገድሉ ሰዎችን ወደ ቤቱ በላከ ጊዜ ዳዊት እንዲህ ሲል ጸልዮአል:- “አምላክ ሆይ፤ ከጠላቶቼ እጅ አድነኝ፤ ሊያጠቁኝ ከሚነሡብኝም ጠብቀኝ። ከክፉ አድራጊዎች ታደገኝ፤ ደም ከተጠሙ ሰዎችም አድነኝ።” (መዝ. 59:1, 2) ዳዊት ጸሎት ከማቅረቡም በተጨማሪ የሚስቱን ምክር በመስማት ሸሽቶ አምልጧል። (1 ሳሙ. 19:11, 12) እኛም በተመሳሳይ፣ የገጠመንን አስጨናቂ ችግር ለመቋቋም አሊያም ያለንበትን ሁኔታ ለማሻሻል የሚረዳንን ጥበብ እንዲሰጠን ወደ ይሖዋ መጸለይ እንችላለን።—ያዕ. 1:5