የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ታኅሣሥ 2017
ከታኅሣሥ 25-31
jd-E 125-126 አን. 4-5
ቤተሰባችሁ አምላክን የሚያስደስት እንዲሆን ለማድረግ ጥረት አድርጉ
4 ሚልክያስ በኖረበት በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በአይሁዳውያን ዘንድ ፍቺ ተስፋፍቶ ነበር። ሚልክያስ እንዲህ ያለ ድርጊት ለሚፈጽሙት ሰዎች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ይሖዋ በአንተ ላይ [መሥክሮብሃል]፤ ምክንያቱም እሷ አጋርህና የቃል ኪዳን ሚስትህ ሆና ሳለ በወጣትነት ሚስትህ ላይ ክህደት ፈጽመሃል።” ባሎች በሚፈጽሙት ክህደት ምክንያት የይሖዋ መሠዊያ ክህደት በተፈጸመባቸው ሚስቶች ‘እንባ፣ ለቅሶና ሐዘን’ ተሞልቶ ነበር። ምግባረ ብልሹ የሆኑት ካህናት ደግሞ እንዲህ ያለውን የጭካኔ ድርጊት በቸልታ አልፈውታል።—ሚልክያስ 2:13, 14
5 ይሖዋ በሚልክያስ ዘመን የነበሩ ሰዎች ስለ ትዳር የነበራቸውን ተገቢ ያልሆነ አመለካከት በተመለከተ ምን ተሰማው? ሚልክያስ “‘እኔ ፍቺን እጠላለሁና’ ይላል የእስራኤል አምላክ ይሖዋ” በማለት ጽፏል። በተጨማሪም ይሖዋ ‘እንዳልተለወጠ’ ተናግሯል። (ሚልክያስ 2:16፤ 3:6) ሚልክያስ እንዲህ ያለው ለምንድን ነው? አምላክ ፍቺን እንደማይፈልግ ቀደም ብሎ ገልጿል። (ዘፍጥረት 2:18, 24) በሚልክያስ ዘመንም ይህን ሐሳብ በድጋሚ ተናግሯል። አሁንም ቢሆን ለፍቺ ያለው አመለካከት አልተለወጠም። አንዳንድ ሰዎች በትዳር ጓደኛቸው ስላልተደሰቱ ብቻ ትዳራቸውን ለማፍረስ ይወስኑ ይሆናል። ይሖዋ ግን የእነዚህን ሰዎች ከሃዲ ልብ ይመረምራል። (ኤርምያስ 17:9, 10) እነዚህ ሰዎች ፍቺ ለመፈጸም የወሰኑበት በቂ ምክንያት እንዳላቸው ለማስመሰል ቢሞክሩም እንኳ የትዳር ጓደኛቸውን ለመፍታት ሲሉ የሠሩትን ሸፍጥም ሆነ የጠነሰሱትን ሴራ ይሖዋ ይመለከታል። በእርግጥም “ተጠያቂዎች በሆንበት በእሱ ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ ነው።”—ዕብራውያን 4:13