የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ሚያዝያ 2019
ከሚያዝያ 1-7
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ቆሮንቶስ 7-9
“ነጠላነት ስጦታ ነው”
(1 ቆሮንቶስ 7:32) በመሆኑም ከጭንቀት ነፃ እንድትሆኑ እፈልጋለሁ። ያላገባ ሰው ጌታን እንዴት ደስ ማሰኘት እንደሚችል በማሰብ ስለ ጌታ ነገር ይጨነቃል።
ነጠላነታችሁን በጥበብ ተጠቀሙበት
3 ነጠላ የሆነ አንድ ግለሰብ በአብዛኛው ካገባ ሰው ይልቅ የበለጠ ጊዜና የተሻለ ነፃነት አለው። (1 ቆሮ. 7:32-35) ይህ ደግሞ አገልግሎቱን ለማስፋት፣ ለሌሎች ፍቅር በማሳየት ረገድ ልቡን ወለል አድርጎ ለመክፈትና ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ልዩ አጋጣሚ ይፈጥርለታል። በመሆኑም በርካታ ክርስቲያኖች የነጠላነትን ጥቅም እየተገነዘቡ ከመሆኑም ሌላ ለጊዜውም ቢሆን ይህን ስጦታ ‘ለመቀበል’ ወስነዋል። ሌሎች ደግሞ ነጠላ ለመሆን አቅደው አልተነሱ ይሆናል፤ ሆኖም ያሉበት ሁኔታ ሲለወጥ በጉዳዩ ላይ በጸሎት ካሰቡበት በኋላ በይሖዋ እርዳታ የነጠላነትን ሕይወት ሊቀበሉት እንደሚችሉ ተሰምቷቸዋል። በመሆኑም ከአዲሱ ሁኔታቸው ጋር ተስማምተው በመኖር የነጠላነትን ሕይወት ለመቀበል መርጠዋል።—1 ቆሮ. 7:37, 38
(1 ቆሮንቶስ 7:33, 34) ያገባ ሰው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ ማሰኘት እንደሚችል በማሰብ ስለ ዓለም ነገር ይጨነቃል፤ 34 በመሆኑም ሐሳቡ ተከፋፍሏል። በተጨማሪም ያላገባች ሴትም ሆነች ድንግል በአካሏም ሆነ በመንፈሷ ቅዱስ መሆን ትችል ዘንድ ስለ ጌታ ነገር ትጨነቃለች። ይሁን እንጂ ያገባች ሴት ባሏን እንዴት ደስ ማሰኘት እንደምትችል በማሰብ ስለ ዓለም ነገር ትጨነቃለች።
ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፉት ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች
7:33, 34—አንድ ያገባ ሰው እንደሚያሳስበው የተገለጸው ‘የዚህ ዓለም ነገር’ ምንድን ነው? እዚህ ላይ ጳውሎስ፣ ያገቡ ክርስቲያኖች ሊያሳስቧቸው የሚገቡ ከዕለት ተዕለት ኑሯቸው ጋር የተያያዙ ነገሮችን መጥቀሱ ነበር። እነዚህም ምግብን፣ ልብስንና መጠለያን የሚያካትቱ ቢሆንም ክርስቲያኖች የሚጸየፏቸውን በዚህ ዓለም ላይ ያሉ መጥፎ ነገሮች አያጠቃልሉም።—1 ዮሐ. 2:15-17
(1 ቆሮንቶስ 7:37, 38) ሆኖም አንድ ሰው ልቡ ከቆረጠና ይህን ማድረግ እንደማያስፈልገው ከተሰማው፣ ደግሞም ራሱን መግዛት የሚችል ከሆነና ሳያገባ ለመኖር በልቡ ከወሰነ መልካም ያደርጋል። 38 ስለዚህ የሚያገባ ሁሉ መልካም ያደርጋል፤ ሳያገባ የሚኖር ሁሉ ደግሞ የተሻለ ያደርጋል።
ነጠላነት—አሳብ ሳይከፋፈል ለማገልገል የሚያስችል አጋጣሚ
14 ትዳር ሳይዝ የሚያሳልፈውን ጊዜ የራስ ወዳድነት ግቦችን ለማሳደድ የሚጠቀምበት ነጠላ ክርስቲያን ካገቡ ክርስቲያኖች “የተሻለ” አላደረገም። በነጠላነት የሚኖረው “ስለ መንግሥተ ሰማያት” ሳይሆን ለራሱ ሲል ነው። (ማቴዎስ 19:12) ያላገባ ወንድ ወይም ያላገባች ሴት “የጌታን ነገር” እና ‘ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኙ’ ማሰብ ያለባቸው ከመሆናቸውም በላይ ‘ሳይባክኑ [“አሳባቸው ሳይከፋፈል፣” አዓት] በጌታ ይጸናሉ።’ ይህ ማለት አሳባቸው ሳይከፋፈል ይሖዋንና ክርስቶስ ኢየሱስን ያገለግላሉ ማለት ነው። ያላገቡ ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ካገቡ ክርስቲያኖች “የተሻለ” የሚያደርጉት በዚህ መንገድ ብቻ ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(1 ቆሮንቶስ 7:11) ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባሏ ጋር ትታረቅ፤ ባልም ሚስቱን መተው የለበትም።
lvs 251
ተጨማሪ ሐሳብ
በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ የትዳር ጓደኛቸው ምንዝር ባይፈጽምም እንኳ ተለያይተው ለመኖር ወስነዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:11) አንድ ክርስቲያን ከትዳር ጓደኛው ጋር ለመለያየት እንዲወስን ሊያደርጉት የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው፦
• መሠረታዊ ነገሮችን ለማቅረብ ፈቃደኛ አለመሆን፦ አንድ ባል ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር ለማቅረብ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ቤተሰቡ ለከፍተኛ ችግር ቢዳረግ።—1 ጢሞቴዎስ 5:8
• ከባድ አካላዊ ጥቃት፦ አንደኛው የትዳር ጓደኛ፣ ጤንነቱን ይባስ ብሎም ሕይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል የኃይል ጥቃት እንደተሰነዘረበት ቢሰማው።—ገላትያ 5:19-21
• አንድ ሰው ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ሙሉ በሙሉ አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ፦ አንድ ሰው የትዳር ጓደኛው ፈጽሞ ይሖዋን ማገልገል እንዳይችል ጥረት ቢያደርግ።—የሐዋርያት ሥራ 5:29
(1 ቆሮንቶስ 7:36) አንድ ሰው ሳያገባ ቀርቶ ራሱን መቆጣጠር እንደተሳነው ከተሰማው፣ በተለይ ደግሞ አፍላ የጉርምስና ዕድሜን ያለፈ ከሆነና ማግባቱ የሚመረጥ ከሆነ የፈለገውን ያድርግ፤ ኃጢአት አይሆንበትም። እንዲህ ያሉ ሰዎች ያግቡ።
በሥነ ምግባር በረከሰ ዓለም ውስጥ ንጽህናህን ጠብቀህ መኖር ትችላለህ
እንግዲያው ወጣቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የጾታ ስሜት ስለተሰማቸው ብቻ ቸኩለው ማግባት አይገባቸውም። ጋብቻ ቃል ኪዳን ውስጥ ያስገባል፤ የገቡትን ቃል ጠብቆ መኖር ደግሞ ብስለትን ይጠይቃል። (ዘፍጥረት 2:24) አንድ ሰው “ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ” እስኪደርስ ማለትም የጾታ ስሜቱ አይሎ የማመዛዘን ችሎታውን ሊያዛባ የሚችልበት ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ ቢጠብቅ የተሻለ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:36) ለአካለ መጠን ደርሶ ማግባት የሚፈልግ አንድ ሰው የትዳር ጓደኛ ስላላገኘ ብቻ የሥነ ምግባር ብልግና ቢፈጽም እንዴት ያለ ሞኝነትና ኃጢአት ነው!
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(1 ቆሮንቶስ 8:1-13) ለጣዖቶች የቀረበን ምግብ በተመለከተ፣ ሁላችንም እውቀት እንዳለን እናውቃለን። እውቀት ያስታብያል፤ ፍቅር ግን ያንጻል። 2 አንድ ሰው ስለ አንድ ነገር አውቃለሁ ብሎ የሚያስብ ከሆነ ስለዚያ ነገር ማወቅ የሚገባውን ያህል ገና አያውቅም። 3 ሆኖም አንድ ሰው አምላክን የሚወድ ከሆነ በእሱ ዘንድ የታወቀ ነው። 4 ለጣዖቶች የቀረበ ምግብ መብላትን በተመለከተ፣ በዓለም ላይ ጣዖት ከንቱ እንደሆነና ከአንዱ በቀር አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። 5 ብዙ “አማልክት” እና ብዙ “ጌቶች” እንደመኖራቸው መጠን በሰማይም ሆነ በምድር አማልክት ተብለው የሚጠሩ ቢኖሩም እንኳ 6 እኛ ግን ሁሉም ነገር ከእሱ የሆነ እኛም ለእሱ የሆን አንድ አምላክ አብ አለን፤ እንዲሁም ሁሉም ነገር በእሱ በኩል የሆነና እኛም በእሱ በኩል የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለ። 7 ይሁንና ይህ እውቀት ያላቸው ሁሉም ሰዎች አይደሉም። አንዳንዶች ግን ቀደም ሲል ጣዖት ያመልኩ ስለነበር የሚበሉት ምግብ ለጣዖት የተሠዋ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ፤ ሕሊናቸው ደካማ ስለሆነም ይረክሳል። 8 ይሁን እንጂ ምግብ ከአምላክ ጋር አያቀራርበንም፤ ባንበላ የሚጎድልብን ነገር የለም፤ ብንበላም የምናተርፈው ነገር የለም። 9 ነገር ግን የመምረጥ መብታችሁ፣ ደካማ የሆኑትን በሆነ መንገድ እንዳያሰናክላቸው ተጠንቀቁ። 10 አንተ እውቀት ያለህ በጣዖት ቤተ መቅደስ ውስጥ ስትበላ አንድ ሰው ቢያይህ ደካማ የሆነው ይህ ሰው ሕሊናው ለጣዖት የቀረበውን ምግብ እንዲበላ አያደፋፍረውም? 11 እንግዲህ ክርስቶስ የሞተለት ይህ ደካማ የሆነው ወንድምህ በአንተ እውቀት ሳቢያ ጠፋ ማለት ነው። 12 በዚህ መንገድ ወንድሞቻችሁን ስትበድሉና ደካማ የሆነውን ሕሊናቸውን ስታቆስሉ በክርስቶስ ላይ ኃጢአት እየሠራችሁ ነው። 13 ስለዚህ ምግብ ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ ወንድሜን ላለማሰናከል ስል ከእንግዲህ ፈጽሞ ሥጋ አልበላም።
ከሚያዝያ 8-14
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ቆሮንቶስ 10-13
“ይሖዋ ታማኝ ነው”
(1 ቆሮንቶስ 10:13) በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም። ይሁንና አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ፈተና ሲደርስባችሁ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ይሖዋ “ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 10:13) ይህ ሲባል፣ ይሖዋ ልንሸከም የምንችለው ፈተና ምን ያህል እንደሆነ አስቀድሞ በመገምገም ምን ዓይነት ፈተናዎች እንደሚደርሱብን ይወስናል ማለት ነው?
▪ እንዲህ ያለው አመለካከት ምን መልእክት እንደሚያስተላልፍ እንመልከት። አንድ ወንድም፣ ልጁ ራሱን ባጠፋበት ወቅት እንዲህ በማለት ጠይቋል፦ ‘እኔና ባለቤቴ የልጃችን ሞት ያስከተለብንን ሐዘን መቋቋም እንችል እንደሆነ ይሖዋ አስቀድሞ አስቦበታል ማለት ነው? ይህ መከራ የደረሰብን አምላክ ልንቋቋመው እንደምንችል ስላሰበ ነው?’ ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥመንን እያንዳንዱን ነገር ይቆጣጠራል ብለን ለማሰብ የሚያበቃ ምክንያት አለ?
በ1 ቆሮንቶስ 10:13 ላይ የተጠቀሰውን የጳውሎስን ሐሳብ ጠለቅ ብለን ስንመረምር የሚከተለው መደምደሚያ ላይ እንደርሳለን፦ ይሖዋ ልንሸከም የምንችለው ፈተና ምን ያህል እንደሆነ አስቀድሞ ከገመገመ በኋላ በዚህ ላይ ተመሥርቶ ምን ዓይነት ፈተናዎች እንደሚደርሱብን ይወስናል ብለን እንድናምን የሚያደርገን ምንም ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት የለም። እዚህ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ የሚያደርጉንን አራት ምክንያቶች እስቲ እንመልከት።
አንደኛ፣ ይሖዋ ለሰው ልጆች የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷል። በሕይወታችን ውስጥ የምንከተለውን ጎዳና በተመለከተ የራሳችንን ውሳኔ እንድናደርግ ይፈልጋል። (ዘዳ. 30:19, 20፤ ኢያሱ 24:15) ትክክለኛውን መንገድ ከመረጥን፣ ይሖዋ አካሄዳችንን እንደሚመራልን መተማመን እንችላለን። (ምሳሌ 16:9) የተሳሳተ አካሄድ ከመረጥን ግን ውሳኔያችን ከሚያስከትለው መዘዝ ማምለጥ አንችልም። (ገላ. 6:7) ይሖዋ ምን ዓይነት ፈተናዎች እንደሚደርሱብን የሚወስን ቢሆን ኖሮ ይህ የመምረጥ ነፃነታችንን መጋፋት አይሆንበትም?
ሁለተኛ፣ ይሖዋ “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” እንዳያጋጥሙን አይከላከልልንም። (መክ. 9:11) በመጥፎ ጊዜ አጉል ቦታ ላይ በመገኘታችን ምክንያት አደጋ ሊያጋጥመን ምናልባትም የከፋ ጉዳት ሊደርስብን ይችላል። ኢየሱስ፣ ግንብ ተንዶባቸው ስለሞቱ 18 ሰዎች በተናገረበት ወቅት፣ ሰዎቹ እንዲህ ዓይነት አደጋ የደረሰባቸው አምላክ ይህ እንዲሆን ስለወሰነ አለመሆኑን ገልጿል። (ሉቃስ 13:1-5) እንዲህ ያሉ ያልተጠበቁ ክስተቶች ሲደርሱ፣ ማን እንደሚተርፍና ማን እንደሚሞት አምላክ አስቀድሞ ይወስናል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊነት የጎደለው አይሆንም?
ሦስተኛ፣ ንጹሕ አቋምን ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ የተነሳው ጉዳይ እያንዳንዳችንን ይመለከታል። ሰይጣን፣ የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቃቸው አጠያያቂ እንደሆነ ገልጿል፤ ማናቸውም ቢሆኑ ፈተና ሲደርስባቸው ለይሖዋ ታማኝ እንደማይሆኑ ተናግሯል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4፤ ራእይ 12:10) ይሖዋ አንዳንድ ፈተናዎችን ልንሸከማቸው እንደማንችል በማሰብ እነዚህ ፈተናዎች እንዳይደርሱብን የሚከላከልልን ከሆነ፣ አምላክን የምናገለግለው ለራሳችን ጥቅም እንደሆነ በመግለጽ ሰይጣን የሰነዘረው ክስ ትክክል ሊሆን ነው ማለት ነው።
አራተኛ፣ ይሖዋ በእኛ ላይ የሚደርሰውን ነገር በሙሉ አስቀድሞ ማወቅ አያስፈልገውም። አምላክ ምን ዓይነት ፈተናዎች እንደሚደርሱብን አስቀድሞ ይወስናል የሚለው አመለካከት፣ ስለ ወደፊቱ ሕይወታችን ሁሉንም ነገር ያውቃል የሚል መልእክት ያስተላልፋል። ሆኖም ይህ አመለካከት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አይደለም። እርግጥ ነው፣ አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የማወቅ ችሎታ አለው። (ኢሳ. 46:10) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ወደፊት ስለሚከናወኑት ነገሮች የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀምበት ሁልጊዜ እንዳልሆነ ይናገራል። (ዘፍ. 18:20, 21፤ 22:12) ስለሆነም ስለ ወደፊቱ ጊዜ የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀምበት የመምረጥ ነፃነታችንን እንደሚያከብርልን በሚያሳይ መንገድ ነው። ደግሞስ ነፃነታችንን የሚያከብር እንዲሁም አፍቃሪና ጻድቅ የሆነ አምላክ እንዲህ ማድረጉ የሚጠበቅ ነገር አይደለም?—ዘዳ. 32:4፤ 2 ቆሮ. 3:17
ታዲያ፣ “አምላክ . . . ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም” የሚለውን የጳውሎስ ሐሳብ ልንረዳው የሚገባው እንዴት ነው? ጳውሎስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው ይሖዋ ፈተናዎች ከመድረሳቸው በፊት ስለሚያደርገው ነገር ሳይሆን ፈተና ወይም መከራ በሚደርስብን ወቅት ስለሚያደርገው ነገር ነው። ሐዋርያው የተናገራቸው ቃላት፣ በሕይወታችን ውስጥ የትኛውም ፈተና ቢደርስብን በይሖዋ እስከተማመንን ድረስ እሱ እንደሚደግፈን ማረጋገጫ ይሰጡናል። (መዝ. 55:22) ጳውሎስ የተናገረው የሚያጽናና ሐሳብ በሁለት መሠረታዊ እውነቶች ላይ የተመሠረተ ነው።
አንደኛ፣ የሚደርስብን ፈተና “በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ” አይደለም። በእኛ ላይ የሚደርሱት መከራዎች ከዚህ በፊት በሌሎች ላይ የደረሱ ናቸው። በአምላክ ላይ እስከታመንን ድረስ፣ የሚደርስብን ፈተና ልንሸከመው ከምንችለው በላይ አይደለም። (1 ጴጥ. 5:8, 9) በ1 ቆሮንቶስ 10:13 ዙሪያ ካለው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው፣ ጳውሎስ እየተናገረ ያለው እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ ስለደረሱባቸው ፈተናዎች ነው። (1 ቆሮ. 10:6-11) ከእነዚህ ፈተናዎች መካከል የትኛውም ቢሆን በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ ወይም ታማኝ እስራኤላውያን ሊሸከሙት የማይችሉት አልነበረም። እዚህ ጥቅስ ላይ ጳውሎስ ‘ከእነሱ አንዳንዶቹ’ እንዳልታዘዙ አራት ጊዜ ጠቅሷል። አንዳንድ እስራኤላውያን በአምላክ ባለመታመናቸው ምክንያት በመጥፎ ምኞቶች መሸነፋቸው የሚያሳዝን ነው።
ሁለተኛ፣ “አምላክ ታማኝ ነው።” አምላክ ከሕዝቦቹ ጋር ስለነበረው ግንኙነት ከሚናገሩት ዘገባዎች መረዳት እንደሚቻለው እሱ “ለሚወዱትና ትእዛዛቱን ለሚጠብቁ ሁሉ . . . ታማኝ ፍቅር” ያሳያቸዋል። (ዘዳ. 7:9) በተጨማሪም እነዚህ ዘገባዎች አምላክ ምንጊዜም ቃሉን እንደሚፈጽም ያሳያሉ። (ኢያሱ 23:14) ባለፉት የታሪክ ዘመናት እንደታየው አምላክ ሁልጊዜ ታማኝ ነው፤ ከዚህ አንጻር፣ እሱን የሚወዱና የሚታዘዙ ሰዎች ከሚያጋጥማቸው ሁኔታ ጋር በተያያዘ (1) የትኛውም ፈተና መሸከም ከሚችሉት በላይ እንዲከብድባቸው እንደማይፈቅድ እንዲሁም (2) “መውጫ መንገዱን” እንደሚያዘጋጅላቸው መተማመን ይችላሉ።
ይሖዋ፣ በእሱ የሚታመኑ ሰዎች ፈተና ሲደርስባቸው መውጫ መንገድ የሚያዘጋጅላቸው እንዴት ነው? እርግጥ ነው፣ ፈቃዱ ከሆነ ፈተናውን ሊያስወግደው ይችላል። ሆኖም ጳውሎስ “ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ፈተና ሲደርስባችሁ [ይሖዋ] መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል” እንዳለ አስታውስ። በመሆኑም አብዛኛውን ጊዜ “መውጫ መንገዱን” የሚያዘጋጀው ፈተናዎችን በጽናት መቋቋም እንድንችል የሚያስፈልገንን ድጋፍ በመስጠት ነው። ይሖዋ፣ መውጫ መንገድ ሊያዘጋጅልን የሚችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት፦
▪ “በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል።” (2 ቆሮ. 1:3, 4) ይሖዋ በቃሉ፣ በቅዱስ መንፈሱና ታማኙ ባሪያ በሚያቀርበው መንፈሳዊ ምግብ አማካኝነት አእምሯችንን፣ ልባችንንና ስሜታችንን ያረጋጋልናል።—ማቴ. 24:45፤ ዮሐ. 14:16 ግርጌ፤ ሮም 15:4
▪ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ሊመራን ይችላል። (ዮሐ. 14:26) ፈተናዎች ሲያጋጥሙን፣ መንፈስ ቅዱስ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችንና መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንድናስታውስ እንዲሁም መውሰድ የሚገባንን የጥበብ እርምጃ እንድናስተውል ይረዳናል።
▪ በመላእክቱ ተጠቅሞ ይረዳናል።—ዕብ. 1:14
▪ በንግግራቸውና በድርጊታቸው “የብርታት ምንጭ” ሊሆኑልን የሚችሉ የእምነት አጋሮቻችንን በመጠቀም ይረዳናል።—ቆላ. 4:11
እንግዲያው በ1 ቆሮንቶስ 10:13 ላይ የሚገኙት የጳውሎስ ቃላት ያላቸውን ትርጉም በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? ይሖዋ፣ ምን ዓይነት ፈተናዎች እንደሚደርሱብን አስቀድሞ አይወስንም። ሆኖም በሕይወታችን ውስጥ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን እርግጠኛ መሆን የምንችልበት ነገር አለ፦ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ ከታመንን፣ ፈተናዎቹ ሰው መሸከም ከሚችለው በላይ እንዲከብዱብን አይፈቅድም፤ እንዲሁም ፈተናዎቹን በጽናት መቋቋም እንድንችል ምንጊዜም መውጫ መንገዱን ያዘጋጅልናል። ይህን ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው!
(1 ቆሮንቶስ 10:13) በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም። ይሁንና አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ፈተና ሲደርስባችሁ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።
(1 ቆሮንቶስ 10:13) በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም። ይሁንና አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ፈተና ሲደርስባችሁ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(1 ቆሮንቶስ 10:8) ከእነሱ አንዳንዶቹ የፆታ ብልግና ፈጽመው ከመካከላቸው 23,000 የሚሆኑት በአንድ ቀን እንደረገፉ እኛም የፆታ ብልግና አንፈጽም።
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ዘኁልቁ 25:9 ዝሙት በመፈጸማቸው ምክንያት በአንድ ቀን የተገደሉት እስራኤላውያን 24,000 እንደሆኑ ሲናገር 1 ቆሮንቶስ 10:8 ግን 23,000 መሆናቸውን የሚገልጸው ለምንድን ነው?
በሁለቱ ጥቅሶች ላይ የቁጥር ልዩነት የተፈጠረበትን ምክንያት ከተለያየ አቅጣጫ መግለጽ ይቻላል። ትክክለኛው አኃዝ በ23,000 እና በ24,000 መካከል ሊሆንና ቁጥሩን ሙሉ ለማድረግ ተጨምሮበት ወይም ከቁጥሩ ላይ ተቀንሶ ይሆናል ብለን በቀላሉ መግለጽ እንችላለን።
ሌላውን አማራጭ ደግሞ ተመልከት። ሐዋርያው ጳውሎስ በሰጢም የነበሩትን እስራኤላውያን ታሪክ ጠቅሶ የተናገረው ልቅ በሆነው የሕዝቡ አኗኗር በምትታወቀው በጥንቷ ቆሮንቶስ ለነበሩት ክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ እንዲሆናቸው ነው። “ከእነርሱ አንዳንዶቹ ዝሙት ፈጽመው በአንድ ቀን ሀያ ሦስት ሺህ ሰው እንደ ረገፈ፣ እኛም ዝሙት አንፈጽም” ሲል ጽፏል። ጳውሎስ ዝሙት በመፈጸማቸው ምክንያት በቀጥታ ይሖዋ የገደላቸውን ብቻ ለይቶ ሲጠቅስ ቁጥራቸው 23,000 መሆኑን ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 10:8
ይሁን እንጂ ዘኁልቁ ምዕራፍ 25 “እስራኤል የፌጎርን በኣል በማምለክ ተባበረ፤ የእግዚአብሔርም ቁጣ በላዩ ነደደ” በማለት ይገልጻል። ከዚያም ይሖዋ “የሕዝቡን አለቆች ሁሉ” እንዲገድላቸው ሙሴን አዘዘው። ሙሴም ይሖዋ የሰጠውን ትእዛዝ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ለእስራኤል ዳኞች መመሪያ ሰጣቸው። በመጨረሻ ፊንሐስ አንዲት ምድያማዊት ሴት ወደ ሠፈሩ ይዞ የመጣን እስራኤላዊ ለመግደል ፈጣን እርምጃ በመውሰዱ ‘መቅሠፍቱ ተከለከለ።’ ዘገባው “በመቅሠፍቱ የሞተው ሰው ቁጥር ሃያ አራት ሺህ ደርሶ ነበር” በማለት ይደመደማል።—ዘኁልቁ 25:1-9
ዘኁልቁ ላይ የተጠቀሰው ቁጥር በዳኞቹ የተገደሉትን “የሕዝቡን አለቆች” እና በቀጥታ በይሖዋ የተቀሠፉትን ሰዎች እንደሚያጠቃልል ግልጽ ነው። በዳኞቹ እጅ የተገደሉት የሕዝቡ አለቆች አንድ ሺህ ሊደርሱ ይችላሉ፤ ይህም ቁጥሩን ወደ 24,000 ከፍ ያደርገዋል። እነዚህ አለቆች ወይም የዓመፁ ቆስቋሾች ዝሙት የፈጸሙ፣ በበዓሉ ላይ የተገኙ አሊያም በእነዚህ ድርጊቶች ለተካፈሉት ድጋፍ የሰጡ ሆኑም አልሆኑ ‘የፌጎርን በኣል በማምለክ ተባባሪ’ በመሆናቸው ጥፋተኞች ሆነው ተገኝተዋል።
‘መተባበር’ የሚለውን ቃል በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ላይ ማብራሪያ የሚሰጥ አንድ ጽሑፍ “ከአንድ ሰው ጋር ቁርኝት መፍጠር” የሚል ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል ገልጿል። እስራኤላውያን ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሕዝቦች ቢሆኑም ‘የፌጎርን በኣል በማምለክ ተባባሪ’ ሆነው በመገኘታቸው ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ዝምድና አበላሽተዋል። ከ700 ዓመታት ገደማ በኋላ ይሖዋ በነቢዩ ሆሴዕ አማካኝነት እስራኤላውያንን በተመለከተ እንዲህ ብሏል:- “ወደ ብዔልፌጎር በመጡ ጊዜ . . . ለዚያ አሳፋሪ ጣዖት ራሳቸውን ለዩ፤ እንደ ወደዱትም ጣዖት የረከሱ ሆኑ።” (ሆሴዕ 9:10) እንደዚህ ያደረጉ ሁሉ መለኮታዊ ቅጣት ይገባቸው ነበር። በመሆኑም ሙሴ እስራኤላውያንን “እግዚአብሔር በብዔልፌጎር ላይ ምን እንዳደረገ በዐይናችሁ አይታችኋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከመካከላችሁ ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሁሉ አጥፍቶአቸዋል” በማለት አስታውሷቸዋል።—ዘዳግም 4:3
(1 ቆሮንቶስ 11:5, 6) ራሷን ሳትሸፍን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ሴት ሁሉ ደግሞ የእሷን ራስ ታዋርዳለች፤ እንዲህ የምታደርግ ሴት ራሷን እንደተላጨች ሴት ትቆጠራለች። 6 አንዲት ሴት ራሷን የማትሸፍን ከሆነ ፀጉሯን ትቆረጥ፤ ፀጉሯን መቆረጧ ወይም መላጨቷ የሚያሳፍራት ከሆነ ግን ትሸፈን።
(1 ቆሮንቶስ 11:10) ከዚህ የተነሳም ሆነ ለመላእክት ሲባል ሴት በሥልጣን ሥር መሆኗን የሚያሳይ ምልክት በራሷ ላይ ታድርግ።
የአንባቢያን ጥያቄዎች
አንዲት እህት፣ ወንድ አስፋፊ ባለበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምትመራ ከሆነ ራሷን መሸፈን ያስፈልጋታል?
▪ ሐምሌ 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ላይ በወጣ “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ላይ አንዲት እህት፣ የተጠመቀም ሆነ ያልተጠመቀ ወንድ አስፋፊ ባለበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምትመራ ከሆነ ራሷን መሸፈን እንደሚኖርባት ተገልጾ ነበር። ይሁንና በዚህ ርዕስ ላይ የተደረገ ተጨማሪ ምርምር ቀደም ሲል በወጣው መመሪያ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ አመላክቷል።
አንዲት እህት፣ በቋሚነት የሚካሄድ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትመራ አንድ የተጠመቀ አስፋፊ ቢገኝ የራስ መሸፈኛ ማድረግ እንደሚያስፈልጋት ጥርጥር የለውም። እንዲህ ማድረጓ ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ላቋቋመው የራስነት ዝግጅት አክብሮት እንዳላት ያሳያል፤ ምክንያቱም ጥናቱን ስትመራ ወንድሞች ሊያከናውኑት የሚገባውን ኃላፊነት እየተወጣች ነው። (1 ቆሮ. 11:5, 6, 10) ሌላው አማራጭ ደግሞ አብሯት ያለው ወንድም ጥናቱን ለመምራት ብቁ ከሆነና አቅሙ ከፈቀደለት ጥናቱን እሱ እንዲመራ ማድረግ ነው።
በሌላ በኩል ግን እህት በቋሚነት የሚካሄድ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትመራ አብሯት ያለው ያልተጠመቀ አስፋፊ ከሆነ የራስ መሸፈኛ የማድረግ ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ የለባትም፤ በጥናቱ ላይ አብሯት ያለው ባሏ ከሆነ ግን ራሷን ትሸፍናለች። ይሁን እንጂ አንዳንድ እህቶች አብሯቸው ያለው ያልተጠመቀ አስፋፊ ቢሆንም የራስ መሸፈኛ እንዲያደርጉ ሕሊናቸው ይገፋፋቸው ይሆናል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(1 ቆሮንቶስ 10:1-17) እንግዲህ ወንድሞች፣ አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች እንደነበሩና ሁሉም በባሕር መካከል እንዳለፉ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፤ 2 ሁሉም ከሙሴ ጋር በመተባበር በደመናውና በባሕሩ ተጠመቁ፤ 3 ደግሞም ሁሉም አንድ ዓይነት መንፈሳዊ ምግብ ተመገቡ፤ 4 በተጨማሪም ሁሉም አንድ ዓይነት መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ። ይከተላቸው ከነበረው መንፈሳዊ ዓለት ይጠጡ ነበርና፤ ይህም ዓለት ክርስቶስን ያመለክታል። 5 ይሁንና አምላክ በአብዛኞቹ ስላልተደሰተ በምድረ በዳ ወድቀው ቀርተዋል። 6 እነሱ ጎጂ የሆኑ ነገሮችን እንደተመኙ እኛም እንዳንመኝ እነዚህ ነገሮች ለእኛ ምሳሌ ሆነውልናል። 7 “ሕዝቡ ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ። ከዚያም ሊጨፍሩ ተነሱ” ተብሎ እንደተጻፈው ከእነሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖት አምላኪዎች አትሁኑ። 8 ከእነሱ አንዳንዶቹ የፆታ ብልግና ፈጽመው ከመካከላቸው 23,000 የሚሆኑት በአንድ ቀን እንደረገፉ እኛም የፆታ ብልግና አንፈጽም። 9 ከእነሱ አንዳንዶቹ ይሖዋን ተፈታትነው በእባቦች እንደጠፉ እኛም አንፈታተነው። 10 በተጨማሪም ከእነሱ አንዳንዶቹ በማጉረምረማቸው በአጥፊው እንደጠፉ አጉረምራሚዎች አትሁኑ። 11 እነዚህ ነገሮች ምሳሌ ይሆኑ ዘንድ በእነሱ ላይ ደረሱ፤ የተጻፉትም የሥርዓቶቹ ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅ ነው። 12 በመሆኑም የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። 13 በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም። ይሁንና አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ፈተና ሲደርስባችሁ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል። 14 ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ከጣዖት አምልኮ ሽሹ። 15 ይህን የምናገረው ማስተዋል ላላቸው ሰዎች ነው፤ የምናገረው ነገር ትክክል ይሁን አይሁን እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ። 16 የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም መቋደስ አይደለም? የምንቆርሰውስ ቂጣ ከክርስቶስ አካል መቋደስ አይደለም? 17 ምክንያቱም እኛ ብዙ ብንሆንም ቂጣው አንድ ስለሆነ አንድ አካል ነን፤ ሁላችንም የምንካፈለው ከዚሁ አንድ ቂጣ ነውና።
ከሚያዝያ 22-28
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ቆሮንቶስ 14-16
“አምላክ ‘ለሁሉም ሁሉንም ነገር’ ይሆናል”
(1 ቆሮንቶስ 15:24, 25) ከዚያም ማንኛውንም መስተዳድር እንዲሁም ሥልጣንን ሁሉና ኃይልን አጥፍቶ መንግሥቱን ለአምላኩና ለአባቱ በሚያስረክብበት ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል። 25 አምላክ ጠላቶችን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግለት ድረስ ንጉሥ ሆኖ ሊገዛ ይገባዋልና።
“ሞት ይሻራል”
10 “ፍጻሜ” የተባለው የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ፍጻሜ ሲሆን በዚያን ጊዜም ኢየሱስ በትሕትናና በታማኝነት መንግሥቱን ለአምላኩና ለአባቱ ያስረክባል። (ራእይ 20:4) በዚያን ጊዜ አምላክ የነበረው ‘ሁሉን በክርስቶስ የመጠቅለል’ ዓላማ ፍጻሜውን ያገኛል። (ኤፌሶን 1:9, 10) አስቀድሞ ግን ክርስቶስ የአምላክን ሉዓላዊ ፈቃድ የሚቃወመውን ‘አለቅነት ሁሉ፣ ሥልጣን ሁሉና ኃይል’ ያጠፋል። ይህ በአርማጌዶን ከሚመጣው ጥፋት የበለጠ ነገርን ያካትታል። (ራእይ 16:16፤ 19:11-21) ጳውሎስ “[ክርስቶስ] ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 15:25, 26) አዎን፣ የአዳማዊ ኃጢአትና ሞት ርዝራዥ ተጠራርጎ ይጠፋል። ከዚያም አምላክ ሙታንን ወደ ሕይወት መልሶ በማምጣት ‘የመታሰቢያ መቃብሮችን’ ባዶ ያደርጋል።—ዮሐንስ 5:28 NW
(1 ቆሮንቶስ 15:26) የመጨረሻው ጠላት፣ ሞት ይደመሰሳል።
መንግሥቱ የአምላክ ፈቃድ በምድር እንዲፈጸም ያደርጋል
21 ይሁንና ብዙውን ጊዜ በሽታን ተከትሎ የሚመጣውና የኃጢአት ውጤት የሆነው ሞትስ? ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች በሙሉ ይዋል ይደር እንጂ ኃያል ባላጋራ ለሆነው ለዚህ “የመጨረሻው ጠላት” መሸነፋቸው አይቀርም። (1 ቆሮ. 15:26) ሆኖም ሞት ከይሖዋ አቅም በላይ የሆነ ጠላት ነው? “ሞትን ለዘላለም ይውጣል፤ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል” የሚለውን የኢሳይያስ ትንቢት ተመልከት። (ኢሳ. 25:8) ያንን ጊዜ በአእምሮህ መሳል ትችላለህ? የቀብር ሥነ ሥርዓት፣ የመቃብር ቦታ ወይም በሐዘን ምክንያት የሚፈስ እንባ አይኖርም! ከዚህ በተቃራኒ፣ ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን እንደሚያስነሳ የገባው አስደሳች ቃል ሲፈጸም ሰዎች የደስታ እንባ ያነባሉ! (ኢሳይያስ 26:19ን አንብብ።) በመጨረሻም ሞት ያስከተላቸው ጠባሳዎች ሁሉ ይሽራሉ።
(1 ቆሮንቶስ 15:27, 28) አምላክ “ሁሉንም ነገር ከእግሩ በታች አስገዝቶለታልና።” ሆኖም ‘ሁሉም ነገር ተገዝቷል’ ሲል ሁሉንም ነገር ያስገዛለትን እንደማይጨምር ግልጽ ነው። 28 ይሁንና ሁሉም ነገር ከተገዛለት በኋላ ወልድ ራሱ ሁሉን ነገር ላስገዛለት ራሱን ያስገዛል፤ ይህም አምላክ ለሁሉም ሁሉንም ነገር እንዲሆን ነው።
ለሺህ ዓመትና ከዚያም በኋላ የሚዘልቅ ሰላም!
17 በሺህ ዓመቱ ፍጻሜ ላይ “አምላክ ለሁሉም ሁሉንም ነገር [ይሆናል]”፤ በዚያ ጊዜ የሚኖረውን ሕይወት ለመግለጽ ከዚህ የተሻለ አባባል የለም። ይሁንና ይህ አባባል ምን ትርጉም አለው? እስቲ አዳምና ሔዋን ፍጹም እያሉ የነበረውን ሁኔታ መለስ ብላችሁ አስቡ፤ በዚያን ወቅት አዳምና ሔዋን የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ቤተሰብ አባላት ነበሩ። የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ የሆነው ይሖዋ ሰዎችንና መላእክትን ጨምሮ ፍጥረታቱን ሁሉ በቀጥታ ይገዛ ነበር። ፍጥረታቱም ቢሆን ከይሖዋ ጋር በቀጥታ መነጋገር ይችሉ የነበረ ከመሆኑም ሌላ እሱን ያመልኩ እንዲሁም በረከቱን ያገኙ ነበር። ያን ጊዜ ይሖዋ “ለሁሉም ሁሉንም ነገር” ይሆን ነበር።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(1 ቆሮንቶስ 14:34, 35) ሴቶች በጉባኤ ውስጥ እንዲናገሩ ስላልተፈቀደላቸው ዝም ይበሉ። ከዚህ ይልቅ ሕጉም እንደሚለው ይገዙ። 35 ያልገባቸው ነገር ካለ በቤታቸው ባሎቻቸውን ይጠይቁ፤ ምክንያቱም ሴት በጉባኤ መካከል ብትናገር የሚያሳፍር ነው።
w12 9/1 9 ሣጥን
ሐዋርያው ጳውሎስ ሴቶች ሐሳባቸውን እንዳይገልጹ ከልክሏል?
ሐዋርያው ጳውሎስ “ሴቶች . . . በጉባኤ ውስጥ ዝም ይበሉ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 14:34) ጳውሎስ ምን ማለቱ ነበር? የሴቶችን የማመዛዘን ችሎታ ማጣጣሉ ነበር? በፍጹም። እንዲያውም ሴቶች ጠቃሚ ትምህርት እንደሚያስተምሩ ብዙ ጊዜ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ ቲቶ 2:3-5) ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ የልሳንና የትንቢት ስጦታ የነበራቸው ሌሎች ግለሰቦችም ሌላው የእምነት አጋራቸው በሚናገርበት ጊዜ ‘ዝም እንዲሉ’ መክሯል። (1 ቆሮንቶስ 14:26-30, 33) በዚያ ዘመን በግሪክ በነበረው ልማድ መሠረት፣ አንዳንድ ክርስቲያን ሴቶች አዲስ ስላገኙት እምነት የበለጠ ለማወቅ በመጓጓት ተናጋሪውን እያቋረጡ ጥያቄ ይጠይቁ የነበረ ይመስላል። ጳውሎስ ነገሮች በሥርዓት እንዲከናወኑ ሲል ሴቶቹ ‘የገዛ ባሎቻቸውን ቤት እንዲጠይቁ’ አበረታቷቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 14:35
(1 ቆሮንቶስ 15:53) ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይገባዋልና፤ ይህ ሟች የሆነው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋል።
‘ምንጊዜም በጉን ይከተሉታል’
6 ይሖዋ ለታማኙ ባሪያ አባላት የገባውን ቃል ማጤናችን በዚህ ባሪያ ላይ ምን ያህል እንደሚተማመንበት ለመገንዘብ ያስችለናል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና።” (1 ቆሮ. 15:52, 53) አምላክን በታማኝነት ሲያገለግሉ የቆዩት የክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች ትንሣኤ በሚያገኙበት ጊዜ የሚሰጣቸው መንፈሳዊ አካልና የዘላለም ሕይወት ብቻ አይደለም። የሚበሰብስ አካል የነበራቸው እነዚህ ሰዎች፣ ከሞት ሲነሱ ያለመሞት ባሕርይ ማለትም ዘላለማዊ ሕይወትና ሊጠፋ የማይችል አካል ይሰጣቸዋል። ከዚህም በላይ የማይበሰብስ በሌላ አባባል የማይፈርስ አካል ይኖራቸዋል። ምናልባትም ራሱን ችሎ መኖር የሚችል አካል ይኖራቸዋል፤ በሌላ አባባል ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ አካል ካላቸው ሌሎች ፍጥረታት በተለየ መልኩ 144,000ዎቹ ሕልውናቸው የተመካው ከሌላ ምንጭ በሚገኝ ኃይል ላይ አይደለም። ከሞት የተነሱት እነዚህ ቅቡዓን በራሳቸው ላይ የወርቅ አክሊል ደፍተው በዙፋን ላይ እንደተቀመጡ በራእይ 4:4 ላይ ተገልጿል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ንጉሥ የመሆን ክብር ያገኛሉ። ይሁንና አምላክ በእነሱ እንደሚተማመን የሚያሳዩ ሌሎች ማስረጃዎችም አሉ።
“ሞት ይሻራል”
7 ከዚህ በመቀጠል ጳውሎስ “የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው። በመበስበስ ይዘራል፣ ባለመበስበስ ይነሣል” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 15:42) ሰብዓዊ አካል፣ ፍጹም ሆኖም እንኳ ሊበሰብስ ይችላል። ፍጹም ሰብዓዊ አካልን መግደል ይቻላል። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ‘እንደ ገና ወደ መበስበስ እንደማይመለስ’ ተናግሮ ነበር። (ሥራ 13:34) ኢየሱስ ፍጹም ቢሆንም እንኳ ሊበሰብስ የሚችለውን ሰብዓዊ አካል ለብሶ ወደ ሕይወት በጭራሽ አይመለስም። አምላክ ከሞት ለሚነሱት ቅቡዓን የሚሰጠው አካል የማይጠፋ ማለትም የማይሞትና የማይበሰብስ ነው። ጳውሎስ በመቀጠል “በውርደት ይዘራል፣ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፣ በኃይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፣ መንፈሳዊ አካል ይነሣል” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 15:43, 44) በተጨማሪም ጳውሎስ “ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና” በማለት ተናግሯል። የማይሞት ማለት ፍጻሜ የሌለው፣ የማይጠፋ ሕይወት ማለት ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:53፤ ዕብራውያን 7:16) በዚህ ዓይነት ከሞት የሚነሱት ቅቡዓን “የሰማያዊውን መልክ” ማለትም ትንሣኤ እንዲያገኙ ያስቻላቸውን የኢየሱስን መልክ ይይዛሉ።—1 ቆሮንቶስ 15:45-49
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(1 ቆሮንቶስ 14:20-40) ወንድሞች፣ በማስተዋል ችሎታችሁ እንደ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፋት ግን ሕፃናት ሁኑ፤ በማስተዋል ችሎታችሁም የጎለመሳችሁ ሁኑ። 21 በሕጉ ላይ “‘በባዕዳን አንደበትና እንግዳ በሆኑ ሰዎች ቋንቋዎች ለዚህ ሕዝብ እናገራለሁ፤ እነሱ ግን በዚያን ጊዜም እንኳ አይሰሙኝም’ ይላል ይሖዋ” ተብሎ ተጽፏል። 22 በመሆኑም ልሳን ለአማኞች ሳይሆን አማኝ ላልሆኑት ምልክት ነው፤ ትንቢት ግን አማኝ ላልሆኑት ሳይሆን ለአማኞች ነው። 23 ስለዚህ ጉባኤው በሙሉ አንድ ላይ ተሰብስቦ ባለበት ወቅት ሁሉም በልሳኖች ቢናገሩና በዚህ መሃል ምንም የማያውቁ ሰዎች ወይም አማኞች ያልሆኑ ቢገቡ እነዚህ ሰዎች ‘አእምሯችሁን ስታችኋል’ አይሏችሁም? 24 ሆኖም ሁላችሁም ትንቢት እየተናገራችሁ ሳለ አማኝ ያልሆነ ወይም ምንም የማያውቅ ሰው ቢገባ ሁላችሁም የምትናገሩት ቃል እንደ ወቀሳ የሚያገለግለው ከመሆኑም በላይ ራሱን በሚገባ እንዲመረምር ያነሳሳዋል። 25 በዚህ ጊዜ በልቡ የተሰወረው ነገር ይገለጣል፤ በመሆኑም “አምላክ በእርግጥ በመካከላችሁ ነው” እያለ በግንባሩ ተደፍቶ ለአምላክ ይሰግዳል። 26 እንግዲህ ወንድሞች፣ ምን ማድረግ ይሻላል? አንድ ላይ በምትሰበሰቡበት ጊዜ አንዱ ይዘምራል፣ ሌላው ያስተምራል፣ ሌላው ራእይን ይገልጣል፣ ሌላው በልሳን ይናገራል፣ ሌላው ደግሞ ይተረጉማል። ሁሉም ነገር ለማነጽ ይሁን። 27 በልሳን የሚናገሩ ካሉ ከሁለት ወይም ከሦስት አይብለጡ፤ በየተራም ይናገሩ፤ የሚናገሩትንም ሌላ ሰው ይተርጉም። 28 የሚተረጉም ሰው ከሌለ ግን በጉባኤ መካከል ዝም ይበሉና ለራሳቸውና ለአምላክ ይናገሩ። 29 ሁለት ወይም ሦስት ነቢያት ይናገሩ፤ ሌሎቹ ደግሞ ትርጉሙን ለመረዳት ይጣሩ። 30 ሆኖም አንድ ሰው እዚያ ተቀምጦ ሳለ ራእይ ቢገለጥለት የመጀመሪያው ተናጋሪ ዝም ይበል። 31 ሁሉም እንዲማሩና ሁሉም እንዲበረታቱ ሁላችሁም በየተራ ትንቢት መናገር ትችላላችሁ። 32 ነቢያት የመንፈስ ስጦታዎችን በአግባቡ ሊጠቀሙባቸው ይገባል። 33 አምላክ የሰላም እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና። በቅዱሳን ጉባኤዎች ሁሉ እንደሚደረገው 34 ሴቶች በጉባኤ ውስጥ እንዲናገሩ ስላልተፈቀደላቸው ዝም ይበሉ። ከዚህ ይልቅ ሕጉም እንደሚለው ይገዙ። 35 ያልገባቸው ነገር ካለ በቤታቸው ባሎቻቸውን ይጠይቁ፤ ምክንያቱም ሴት በጉባኤ መካከል ብትናገር የሚያሳፍር ነው። 36 የአምላክ ቃል የመጣው ከእናንተ ነው? ወይስ የአምላክ ቃል የደረሰው ወደ እናንተ ብቻ ነው? 37 ነቢይ እንደሆነ ወይም የመንፈስ ስጦታ እንዳለው የሚያስብ ሰው ካለ እነዚህ የጻፍኩላችሁ ነገሮች የጌታ ትእዛዛት መሆናቸውን አምኖ ይቀበል። 38 ሆኖም ይህን ችላ የሚል ካለ እሱም ችላ ይባላል። 39 ስለዚህ ወንድሞቼ፣ ትንቢት ለመናገር ጥረት አድርጉ፤ ይሁንና በልሳኖች መናገርንም አትከልክሉ። 40 ሆኖም ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት ይሁን።
ከሚያዝያ 29–ግንቦት 5
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ቆሮንቶስ 1-3
“ይሖዋ—‘የመጽናናት ሁሉ አምላክ’”
(2 ቆሮንቶስ 1:3) የምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይወደስ፤
“ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ”
4 የምሕረት አባት የሆነው ይሖዋ እንደ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ፣ ሙሴና ንጉሥ ዳዊት ያሉ ወዳጆቹ በሞቱበት ወቅት፣ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ምን ያህል ከባድ ሐዘን እንደሚያስከትል ተመልክቷል። (ዘኁ. 12:6-8፤ ማቴ. 22:31, 32፤ ሥራ 13:22) ይሖዋ እነዚህን ሰዎች ከሞት የሚያስነሳበትን ጊዜ እንደሚናፍቅና በጉጉት እንደሚጠብቅ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢዮብ 14:14, 15) በዚያ ወቅት እነዚህ ሰዎች ደስተኞችና ፍጹም ጤናማ ይሆናሉ። አምላክ፣ ልጁን በጣም የሚወደው ከመሆኑም ሌላ “በየዕለቱ [በእሱ] የተነሳ ልዩ ደስታ ይሰማው” እንደነበር የአምላክ ቃል ይናገራል፤ በመሆኑም ይህ ልጁ ተሠቃይቶ ሲሞት ይሖዋ ምን ተሰምቶት እንደሚሆን ማሰብ እንችላለን። (ምሳሌ 8:22, 30) በዚያ ወቅት ይሖዋ የተሰማውን ሐዘን በቃላት መግለጽ ያዳግታል።—ዮሐ. 5:20፤ 10:17
(2 ቆሮንቶስ 1:4) እኛ ከአምላክ በምናገኘው መጽናኛ በማንኛውም ዓይነት መከራ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ማጽናናት እንድንችል እሱ በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል።
“ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ”
14 በሐዘን የተዋጠን ሰው ለማጽናናት ምን ማለት እንዳለብን ማወቅ ከባድ ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው። ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ “የጥበበኞች ምላስ . . . ፈውስ ነው” ይላል። (ምሳሌ 12:18) ብዙዎች ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ለማጽናናት የሚያስችሉ ሐሳቦችን የምትወዱት ሰው ሲሞት ከተባለው ብሮሹር ላይ አግኝተዋል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ፣ ያዘኑ ሰዎችን ማጽናናት የምትችሉበት ዋነኛው መንገድ “ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ነው። (ሮም 12:15) ጋቢ የተባለች ባሏን በሞት ያጣች እህት፣ አንዳንድ ጊዜ ሐዘኗን መግለጽ የምትችለው በማልቀስ ብቻ እንደሆነ ተናግራለች። አክላም “ወዳጆቼ አብረውኝ ማልቀሳቸው የሚያጽናናኝ ለዚህ ነው። እንዲህ ሲያደርጉ ሐዘኔን የሚጋራኝ ሰው እንዳለ ይሰማኛል” ብላለች።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(2 ቆሮንቶስ 1:22) በተጨማሪም በማኅተሙ ያተመን ሲሆን ወደፊት ለሚመጣውም ነገር ማረጋገጫ ሰጥቶናል፤ ይህም በልባችን ውስጥ ያለው መንፈስ ነው።
የአንባቢያን ጥያቄዎች
እያንዳንዱ ቅቡዕ ክርስቲያን ከአምላክ የሚቀበለው “ማረጋገጫ” እና ‘ማኅተም’ ምንድን ነው?—2 ቆሮ. 1:21, 22 ግርጌ
▪ ማረጋገጫ፦ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው በ2 ቆሮንቶስ 1:22 ላይ “ማረጋገጫ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ከሕግና ከንግድ ጋር በተያያዘ የሚሠራበት” ነው፤ ትርጉሙም “የመጀመሪያ ክፍያ፣ መያዣ፣ ቀብድ ማለት ሲሆን አንድ ነገር የተገዛበትን ዋጋ በተወሰነ መጠን በቅድሚያ በመክፈል የዕቃውን ሕጋዊ ባለቤትነት ለማረጋገጥ ወይም አንድን ውል ሕጋዊ ለማድረግ ያስችላል።” ይሖዋ ለቅቡዓን ሽልማት እንደሚያገኙ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል፤ በ2 ቆሮንቶስ 5:1-5 ላይ እንደተገለጸው ቅቡዓኑ፣ ሙሉውን ክፍያ ወይም ሽልማት ሲያገኙ የማይበሰብስ ሰማያዊ አካል ይለብሳሉ። ሽልማቱ ያለመሞት ባሕርይ ማግኘትንም ይጨምራል።—1 ቆሮ. 15:48-54
በዘመናዊው ግሪክኛ፣ አንድ ሰው ሲታጭ የሚያደርገውን ቀለበት ለማመልከት የሚሠራበት ቃል “ማረጋገጫ” ተብሎ ከተተረጎመው ቃል ጋር ተዛማጅነት አለው። ይህ መሆኑም ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ቅቡዓን፣ የክርስቶስ ምሳሌያዊ ሚስት እንደሆኑ ተደርገው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጸዋል።—2 ቆሮ. 11:2፤ ራእይ 21:2, 9
▪ ማኅተም፦ በጥንት ዘመን ማኅተም የአንድን ነገር ባለቤትነትና ትክክለኛነት ለማመልከት ወይም ስምምነትን ለማረጋገጥ እንደ ፊርማ ሆኖ ያገለግል ነበር። ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ የአምላክ ንብረት መሆናቸውን ለማሳየት በምሳሌያዊ ሁኔታ በመንፈስ ቅዱስ ‘ታትመዋል’ ወይም ምልክት ተደርጎባቸዋል። (ኤፌ. 1:13, 14) ይሁንና ይህ የመጨረሻው ማኅተም አይደለም፤ አንድ ግለሰብ የመጨረሻው ማኅተም የሚደረግበት በታማኝነት ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ አሊያም ታላቁ መከራ ከመምጣቱ ከተወሰነ ጊዜ በፊት ነው።—ኤፌ. 4:30፤ ራእይ 7:2-4
(2 ቆሮንቶስ 2:14-16) በድል ሰልፍ ከክርስቶስ ጋር አብረን እንድንጓዝ በማድረግ ዘወትር ለሚመራንና የእውቀቱ መዓዛ በእኛ አማካኝነት በሁሉም ቦታ እንዲናኝ ለሚያደርገው አምላክ ምስጋና ይድረሰው! 15 እኛ ወደ መዳን በሚወስደው ጎዳና ላይ ባሉት መካከልና ወደ ጥፋት እያመሩ ባሉት መካከል ለአምላክ የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤ 16 ወደ ጥፋት እያመሩ ላሉት ለሞት የሚዳርግ የሞት ሽታ፣ ወደ መዳን በሚወስደው ጎዳና ላይ ላሉት ደግሞ ወደ ሕይወት የሚመራ የሕይወት መዓዛ ነን። እንዲህ ላለው አገልግሎት ብቃት ያለው ማን ነው?
ይህን ያውቁ ኖሯል?
ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ “ድል ሰልፍ” ሲናገር በአእምሮው ምን ይዞ ሊሆን ይችላል?
▪ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[አምላክ] በድል ሰልፍ ከክርስቶስ ጋር አብረን እንድንጓዝ በማድረግ [ይመራናል]፤ የእውቀቱ ሽታ በእኛ አማካኝነት በሁሉም ቦታ እንዲናኝ [ያደርጋል]። ምክንያቱም እኛ ወደ መዳን በሚወስደው ጎዳና ላይ ባሉት መካከልና ወደ ጥፋት እያመሩ ባሉት መካከል ለአምላክ የክርስቶስ መዓዛ ነን፤ ወደ ጥፋት እያመሩ ላሉት ሞት የሚያስከትል የሞት ሽታ፣ ወደ መዳን በሚወስደው ጎዳና ላይ ላሉት ደግሞ ሕይወት የሚያስገኝ የሕይወት ሽታ ነን።”—2 ቆሮንቶስ 2:14-16
ሐዋርያው፣ በሮማውያን ልማድ መሠረት አንድ ጄኔራል በአገሩ ጠላቶች ላይ ድል ሲቀዳጅ ለጄኔራሉ ክብር ለመስጠት ሲባል የሚደረገውን የድል ሰልፍ እየጠቀሰ ነበር። በዚህ ጊዜ ምርኮውም ሆነ የጦር እስረኞቹ ለሕዝብ እይታ የሚቀርቡ ሲሆን በሬዎች መሥዋዕት ወደሚደረጉበት ስፍራ ይነዳሉ፤ ድል አድራጊው ጄኔራልና ሠራዊቱ ደግሞ ከሕዝቡ አድናቆትና ውዳሴ ይጎርፍላቸዋል። በሰልፉ መገባደጃ ላይ በሬዎቹ መሥዋዕት ይደረጋሉ፤ እንዲሁም አብዛኞቹ እስረኞች ይገደላሉ።
ለአንዳንዶች ሕይወትን ለሌሎች ደግሞ ሞትን የሚያመለክተው “የክርስቶስ መዓዛ” የሚለው ተለዋጭ ዘይቤ “ምናልባት ሮማውያን የድል ሰልፉ በሚካሄድበት ጊዜ ያከናውኑት ከነበረው ዕጣን የማጨስ ልማድ የመጣ ሊሆን ይችላል” በማለት ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ ይገልጻል። “ላሸነፉት ሰዎች ድልን የሚያመለክተው መዓዛ ለምርኮኞቹ ደግሞ የሚጠብቃቸውን የሞት ቅጣት ያስታውሳቸዋል።”
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(2 ቆሮንቶስ 3:1-18) ብቁ መሆናችንን ለማሳየት ራሳችንን ለእናንተ እንደ አዲስ ማስተዋወቅ ያስፈልገናል? ወይስ እንደ አንዳንድ ሰዎች ለእናንተ ወይም ከእናንተ የምሥክር ወረቀት ያስፈልገን ይሆን? 2 ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነብቡት በልባችን ላይ የተጻፈ ማስረጃችን እናንተ ራሳችሁ ናችሁ። 3 ምክንያቱም እናንተ በቀለም ሳይሆን በሕያው አምላክ መንፈስ፣ በድንጋይ ጽላቶች ላይ ሳይሆን በሥጋ ጽላቶች ይኸውም በልብ ላይ፣ አገልጋዮች በሆንነው በእኛ አማካኝነት የተጻፋችሁ የክርስቶስ ደብዳቤ እንደሆናችሁ በግልጽ ታይቷል። 4 በክርስቶስ በኩል በአምላክ ፊት እንዲህ ያለ እምነት አለን። 5 ብቃታችንን በገዛ ራሳችን ያገኘነው እንደሆነ አድርገን አናስብም፤ ከዚህ ይልቅ አስፈላጊውን ብቃት ያገኘነው ከአምላክ ነው፤ 6 እሱም የአዲስ ቃል ኪዳን አገልጋዮች ይኸውም የተጻፈ ሕግ ሳይሆን የመንፈስ አገልጋዮች እንድንሆን ብቁዎች አድርጎናል፤ የተጻፈው ሕግ ለሞት ፍርድ ይዳርጋልና፤ መንፈስ ግን ሕያው ያደርጋል። 7 የእስራኤል ልጆች፣ ከፊቱ ክብር የተነሳ የሙሴን ፊት ትኩር ብለው ማየት እስኪሳናቸው ድረስ የሞት ፍርድ የሚያስከትለውና በድንጋይ ላይ በፊደል የተቀረጸው ሕግ በክብር ይኸውም በሚጠፋ ክብር ከመጣ 8 የመንፈስ አገልግሎት እንዴት የላቀ ክብር አይኖረውም? 9 ኩነኔ የሚያስከትለው የሕግ አገልግሎት ክብራማ ከሆነ ጽድቅ የሚያስገኘው አገልግሎትማ እንዴት እጅግ የላቀ ክብር አይኖረውም! 10 እንዲያውም በአንድ ወቅት ክብራማ የነበረው፣ ከእሱ የላቀ ክብር ያለው በመምጣቱ ምክንያት ክብሩ ተገፏል። 11 የሚጠፋው በክብር ከመጣ ጸንቶ የሚኖረውማ እንዴት የላቀ ክብር አይኖረውም! 12 እንዲህ ዓይነት ተስፋ ስላለን ታላቅ የመናገር ነፃነት አለን፤ 13 ደግሞም የእስራኤል ልጆች የዚያን የሚሻረውን ነገር መጨረሻ እንዳይመለከቱ ሙሴ ፊቱን በመሸፈኛ ይሸፍን በነበረበት ጊዜ ያደርግ እንደነበረው አናደርግም። 14 ሆኖም እነሱ አእምሯቸው ደንዝዟል። እስከ ዛሬ ድረስ፣ አሮጌው ቃል ኪዳን ሲነበብ ያው መሸፈኛ እንደጋረዳቸው ነውና፤ ምክንያቱም መሸፈኛው የሚወገደው በክርስቶስ አማካኝነት ብቻ ነው። 15 እንዲያውም እስከ ዛሬ ድረስ የሙሴ መጻሕፍት በተነበቡ ቁጥር ልባቸው በመሸፈኛ እንደተሸፈነ ነው። 16 ሆኖም አንድ ሰው ወደ ይሖዋ ሲመለስ መሸፈኛው ይወገዳል። 17 ይሖዋ መንፈስ ነው፤ የይሖዋ መንፈስ ባለበት ደግሞ ነፃነት አለ። 18 እኛ ሁላችንም ባልተሸፈነ ፊት የይሖዋን ክብር እንደ መስተዋት ስናንጸባርቅ ያንኑ መልክ ለመምሰል ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን፤ በዚህ መንገድ መንፈስ የሆነው ይሖዋ ራሱ እንደሚያደርገን እንሆናለን።