ክርስቲያናዊ ሕይወት
ንጹሕ ምግባርና ጥልቅ አክብሮት ማሳየት የሰዎችን ልብ ይነካል
አማኝ የሆኑ ሚስቶች የክርስቶስ ዓይነት ምግባር በማሳየት ባሎቻቸው እውነትን እንዲቀበሉ መርዳት ይችላሉ። ሆኖም እንዲህ ለማድረግ በችግር ውስጥ ለበርካታ ዓመታት መጽናት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። (1ጴጥ 2:21-23፤ 3:1, 2) ኢፍትሐዊ የሆነ ነገር እየደረሰባችሁ ከሆነ ክፉውን በመልካም ማሸነፋችሁን ቀጥሉ። (ሮም 12:21) መልካም ምሳሌነታችሁ ከቃላት የበለጠ ኃይል ሊኖረው እንደሚችል አትዘንጉ።
ራሳችሁን በትዳር ጓደኛችሁ ቦታ ላይ ለማስቀመጥ ሞክሩ። (ፊልጵ 2:3, 4) የትዳር ጓደኛችሁን ስሜት ለመረዳትና ርኅራኄ ለማሳየት ጥረት አድርጉ፤ እንዲሁም ኃላፊነታችሁን ለትዳር ጓደኛችሁ አክብሮት እንዳላችሁ በሚያሳይ መንገድ ተወጡ። ጥሩ አድማጭ ሁኑ። (ያዕ 1:19) ታጋሽ ሁኑ፤ እንዲሁም የትዳር ጓደኛችሁን እንደምትወዱት አረጋግጡለት። የትዳር ጓደኛችሁ በምላሹ ደግነትና አክብሮት ባያሳያችሁ እንኳ ይሖዋ ታማኝነታችሁን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ።—1ጴጥ 2:19, 20
ይሖዋ ኃላፊነታችንን እንድንወጣ ብርታት ይሰጠናል የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት፤ ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦
ግሬስ ሊ ትዳር እንደመሠረተች የነበራት ሕይወት ምን ይመስል ነበር?
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንድትቀበል ያነሳሳት ምንድን ነው?
እህት ግሬስ ከተጠመቀች በኋላ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጽናት የተወጣችው እንዴት ነው?
እህት ግሬስ ባለቤቷን በተመለከተ ምን በማለት ጸልያለች?
እህት ግሬስ ንጹሕ ምግባርና ጥልቅ አክብሮት በማሳየቷ ምን በረከት አግኝታለች?
ንጹሕ ምግባርና ጥልቅ አክብሮት ማሳየት ትልቅ ለውጥ ያመጣል!