የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ኅዳር 2019
ከኅዳር 4-10
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ዮሐንስ 1-5
“ዓለምንም ሆነ በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች አትውደዱ”
(1 ዮሐንስ 2:15, 16) ዓለምንም ሆነ በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች አትውደዱ። ማንም ዓለምን የሚወድ ከሆነ የአብ ፍቅር በውስጡ የለም፤ 16 ምክንያቱም በዓለም ያለው ነገር ሁሉ ይኸውም የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና ኑሮዬ ይታይልኝ ማለት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመነጭ አይደለም።
ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በጥብቅ ተከተል
13 አንዳንዶች በዓለም ላይ ያሉ ነገሮች ሁሉ መጥፎ ናቸው ማለት አይቻልም ብለው ያስቡ ይሆናል። ይህ እውነት ቢሆንም እንኳ ዓለምም ሆነ ዓለም ማራኪ አስመስሎ የሚያቀርባቸው ነገሮች ከይሖዋ አገልግሎት ትኩረታችንን በቀላሉ ሊሰርቁብን ይችላሉ። ዓለም ወደ አምላክ እንድንቀርብ እኛን ለመርዳት ብሎ የሚያዘጋጀው ነገር የለም። በመሆኑም በራሳቸው ምንም ስሕተት የሌለባቸው ነገሮች ቢሆኑም እንኳ በዓለም ያሉ ነገሮችን መውደድ ከጀመርን አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ገብተናል ማለት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ከዚህም በላይ በዓለም ያለው አብዛኛው ነገር መጥፎ ከመሆኑም ሌላ አቋማችንን ሊያበላሽብን ይችላል። ዓመጽ፣ ፍቅረ ነዋይ ወይም የጾታ ብልግና የሚንጸባረቅባቸውን ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች የምንመለከት ከሆነ እነዚህን ነገሮች ልንቀበላቸው ብሎም ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ ልንፈተን እንችላለን። የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል ወይም የንግድ እንቅስቃሴያቸውን ለማስፋት ከሚሯሯጡ ሰዎች ጋር የምንወዳጅ ከሆነ እኛም ለእነዚህ ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ልንጀምር እንችላለን።—ማቴዎስ 6:24፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33
(1 ዮሐንስ 2:17) ከዚህም በተጨማሪ ዓለምም ሆነ ምኞቱ ያልፋሉ፤ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።
ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ አስቡ
18 ሰይጣን “በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች” በመጠቀም የሚያቀርባቸውን ፈተናዎች ለመቋቋም የሚረዳን ሌላው ነገር ዮሐንስ በመንፈስ መሪነት የጻፈውን የሚከተለውን ሐሳብ ማስታወስ ነው፦ “ዓለምም ሆነ ምኞቱ በማለፍ ላይ ናቸው፤ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።” (1 ዮሐ. 2:17) የሰይጣን ሥርዓት እንዲሁ ለዘላለም የሚቀጥል ይመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ ቀን መጥፋቱ አይቀርም። የሰይጣን ዓለም የሚያቀርበው ማንኛውም ነገር ዘላቂ አይደለም። ይህን እውነታ ማስታወሳችን በዲያብሎስ ማታለያዎች እንዳንታለል ይረዳናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(1 ዮሐንስ 2:7, 8) የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ የምጽፍላችሁ ከመጀመሪያ ጀምሮ የነበራችሁን የቆየውን ትእዛዝ እንጂ አዲስ ትእዛዝ አይደለም። ይህ የቆየው ትእዛዝ የሰማችሁት ቃል ነው። 8 ይሁንና በእሱም ሆነ በእናንተ ዘንድ እውነት የሆነውን አዲስ ትእዛዝ እጽፍላችኋለሁ፤ ምክንያቱም ጨለማው እያለፈና እውነተኛው ብርሃን አሁንም እንኳ እያበራ ነው።
የይሖዋ ማሳሰቢያዎች እምነት የሚጣልባቸው ናቸው
14 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አንዳችን ለሌላው ፍቅር እንድናሳይ በሚያበረታቱ ማሳሰቢያዎች የተሞሉ ናቸው። ኢየሱስ ሁለተኛው ታላቅ ትእዛዝ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴ. 22:39) የኢየሱስ ወንድም የሆነው ያዕቆብም ፍቅርን “ንጉሣዊ ሕግ” በማለት ጠርቶታል። (ያዕ. 2:8) ሐዋርያው ዮሐንስ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ የምጽፍላችሁ ከመጀመሪያ ጀምሮ የነበራችሁን የቆየውን ትእዛዝ እንጂ አዲስ ትእዛዝ አይደለም” ብሏል። (1 ዮሐ. 2:7, 8) ዮሐንስ ‘የቆየ ትእዛዝ’ በማለት የተናገረው አገላለጽ ምን ያመለክታል? ዮሐንስ እየተናገረ ያለው የፍቅርን ትእዛዝ አስመልክቶ ነው። “የቆየ” የተባለው ኢየሱስ ትእዛዙን የሰጠው “ከመጀመሪያ ጀምሮ” ማለትም ከአሥርተ ዓመታት በፊት ስለነበረ ነው። “አዲስ” የተባለው ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ አዳዲስ ተፈታታኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥሟቸው ጊዜ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቀውን ይህን ፍቅር ማሳየት ስለሚያስፈልጋቸው ነው። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን፣ ይህን ዓለም ለይቶ የሚያሳውቀውንና ለሰዎች ያለን ፍቅር እንዲጠፋ የሚያደርገውን የራስ ወዳድነት መንፈስ ከማዳበር እንድንጠበቅ የሚረዳ ማስጠንቀቂያ በማግኘታችን አድናቂዎች ልንሆን አይገባም?
(1 ዮሐንስ 5:16, 17) ማንም ሰው ወንድሙ ለሞት የማያበቃ ኃጢአት ሲሠራ ቢያየው ስለ እሱ ይለምናል፤ አምላክም ሕይወት ይሰጠዋል። ይህ የሚሆነው ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት ላልሠሩ ሰዎች ነው። ይሁን እንጂ ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት አለ። እንዲህ ዓይነት ኃጢአት ለሠራ ግለሰብ ማንም ሰው ይጸልይ አልልም። 17 ጽድቅ ያልሆነ ነገር ሁሉ ኃጢአት ነው፤ ይሁንና ለሞት የማያበቃ ኃጢአት አለ።
it-1 862 አን. 5
ይቅርታ
ሌሎችን አልፎ ተርፎም አንድን ጉባኤ ወክሎ የአምላክን ይቅርታ ለማግኘት መጸለይ ስህተት አይደለም። ሙሴ እስራኤላውያን በብሔር ደረጃ የሠሩትን ኃጢአት በመናዘዝ የአምላክን ይቅርታ ለማግኘት ለምኗል፤ ይሖዋም ጸሎቱን ሰምቶታል። (ዘኁ 14:19, 20) ሰለሞንም ቢሆን ቤተ መቅደሱ ለአምላክ በተወሰነ ጊዜ ባቀረበው ጸሎት ላይ፣ ሕዝቡ ኃጢአት ቢሠሩና ከኃጢአት ጎዳናቸው ቢመለሱ ይሖዋ ይቅርታ እንዲያደርግላቸው ለምኗል። (1ነገ 8:30, 33-40, 46-52) ዕዝራ ከስደት የተመለሱትን አይሁዳውያን ወክሎ ኃጢአታቸውን በይፋ ተናዟል። ሕዝቡ ዕዝራ ያቀረበውን ከልብ የመነጨ ጸሎት እንዲሁም የሰጣቸውን ምክር ሲሰሙ የይሖዋን ይቅርታ የሚያስገኝ እርምጃ ለመውሰድ ተነሳስተዋል። (ዕዝራ 9:13–10:4, 10-19, 44) ያዕቆብ በመንፈሳዊ የታመመ ሰው ካለ የጉባኤውን ሽማግሌዎች እንዲጠራና እንዲጸልዩለት አበረታቷል፤ ይህም ግለሰቡ “ኃጢአት ሠርቶ ከሆነ ይቅር [እንዲባል]” ያስችላል። (ያዕ 5:14-16) ሆኖም “ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት አለ”፤ ይህ ኃጢአት በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚፈጸም ኃጢአት ሲሆን እንዲህ ላለው ሆን ተብሎ የሚሠራ ኃጢአት ይቅርታ ማግኘት አይቻልም። አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ኃጢአት ለፈጸሙ ሰዎች መጸለይ የለበትም።—1ዮሐ 5:16፤ ማቴ 12:31፤ ዕብ 10:26, 27፤ ኃጢአት 1 እና መንፈስ የሚለውን ተመልከት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(1 ዮሐንስ 1:1–2:6) ከመጀመሪያ የነበረውን፣ የሰማነውን፣ በዓይናችን ያየነውን፣ በትኩረት የተመለከትነውንና በእጃችን የዳሰስነውን የሕይወትን ቃል በተመለከተ እንጽፍላችኋለን፤ 2 (አዎ፣ ይህ ሕይወት ተገልጧል፤ እኛም አይተናል፤ ደግሞም እየመሠከርን ነው፤ እንዲሁም በአብ ዘንድ የነበረውንና ለእኛ የተገለጠውን የዘላለም ሕይወት ለእናንተ እየነገርናችሁ ነው፤) 3 እናንተም ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተም እየነገርናችሁ ነው። ደግሞም ይህ ኅብረታችን ከአብና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው። 4 እነዚህን ነገሮች የምንጽፍላችሁ ደስታችን የተሟላ እንዲሆን ነው። 5 ከእሱ የሰማነውና ለእናንተ የምናሳውቀው መልእክት ይህ ነው፦ አምላክ ብርሃን ነው፤ በእሱም ዘንድ ጨለማ ፈጽሞ የለም። 6 “ከእሱ ጋር ኅብረት አለን” ብለን እየተናገርን በጨለማ የምንመላለስ ከሆነ እየዋሸን ነው፤ እውነትንም ሥራ ላይ እያዋልን አይደለም። 7 ይሁን እንጂ እሱ ራሱ በብርሃን እንዳለ ሁሉ እኛም በብርሃን የምንመላለስ ከሆነ እርስ በርሳችን ኅብረት ይኖረናል፤ እንዲሁም የልጁ የኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። 8 “ኃጢአት የለብንም” ብለን የምንናገር ከሆነ ራሳችንን እያታለልን ነው፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። 9 ኃጢአታችንን የምንናዘዝ ከሆነ እሱ ታማኝና ጻድቅ ስለሆነ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል፤ እንዲሁም ከክፋት ሁሉ ያነጻናል። 10 “ኃጢአት አልሠራንም” ብለን የምንናገር ከሆነ እሱን ውሸታም እያደረግነው ነው፤ ቃሉም በውስጣችን የለም።
2 የተወደዳችሁ ልጆቼ፣ እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ ኃጢአት እንዳትሠሩ ነው። ማንም ኃጢአት ቢሠራ ግን በአብ ዘንድ ረዳት አለን፤ እሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 2 እሱ ለእኛ ኃጢአት የቀረበ የማስተሰረያ መሥዋዕት ነው፤ ሆኖም ለእኛ ኃጢአት ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ ኃጢአት ጭምር ነው። 3 ደግሞም ትእዛዛቱን መፈጸማችንን ከቀጠልን እሱን የምናውቅ መሆናችንን በዚህ እንረዳለን። 4 “እሱን አውቀዋለሁ” እያለ ትእዛዛቱን የማይፈጽም ሰው ቢኖር ውሸታም ነው፤ እውነትም በዚህ ሰው ውስጥ የለም። 5 ሆኖም የእሱን ቃል የሚጠብቅ ማንም ቢኖር የአምላክ ፍቅር በእርግጥ በዚህ ሰው ላይ ፍጹም በሆነ መንገድ ይታያል። ከእሱ ጋር አንድነት እንዳለንም በዚህ እናውቃለን። 6 ከእሱ ጋር ያለኝን አንድነት ጠብቄ እኖራለሁ የሚል፣ እሱ በተመላለሰበት መንገድ የመመላለስ ግዴታ አለበት።
ከኅዳር 11-17
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ዮሐንስ 1–ይሁዳ
“እውነት ውስጥ ለመቆየት ብርቱ ተጋድሎ ማድረግ አለብን”
(ይሁዳ 3) የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ሁላችንም ስለምናገኘው መዳን ልጽፍላችሁ እጅግ ጓጉቼ የነበረ ቢሆንም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለቅዱሳን ስለተሰጠው እምነት ብርቱ ተጋድሎ እንድታደርጉ ለማሳሰብ ልጽፍላችሁ ተገደድኩ።
‘በጌታ ጠንክሩ’
8 መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን የሚጠቀምባቸውን ዋና ዋና ዘዴዎች ስለሚገልጽልን ዕቅዱ ምን እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን። (2 ቆሮንቶስ 2:11) ዲያብሎስ በጻድቁ ኢዮብ ላይ ከባድ የኢኮኖሚ ኪሳራ አድርሶበታል፣ የሚወዳቸውን ሰዎች በሞት ነጥቆታል፣ ከቤተሰቡ ተቃውሞ ቆስቁሶበታል፣ አካላዊ ሥቃይ አምጥቶበታል እንዲሁም ወዳጅ ተብዬዎቹ በሐሰት እንዲወነጅሉት አድርጓል። ኢዮብ ተጨንቆ የነበረ ከመሆኑም በላይ አምላክ እንደተወው ተሰምቶታል። (ኢዮብ 10:1, 2) ሰይጣን በዛሬው ጊዜ እነዚህን ችግሮች በቀጥታ ባያመጣም በርካታ ክርስቲያኖች በእነዚህ ችግሮች የሚነኩ ሲሆን ዲያብሎስ ችግሮቹን የራሱን ዓላማ ለማስፈጸም ይጠቀምባቸዋል።
9 በዚህ የመጨረሻ ዘመን መንፈሳዊ አደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል። የምንኖረው ከመንፈሳዊ ግቦች ይልቅ ለቁሳዊ ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት በሚሰጥበት ዓለም ውስጥ ነው። መገናኛ ብዙኃን ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ የጾታ ግንኙነቶች የሐዘን ሳይሆን የደስታ ምንጭ እንደሆኑ አድርገው በተደጋጋሚ ያቀርባሉ። እንዲሁም ብዙዎች “ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ” ሆነዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ‘ለእምነት ካልተጋደልን’ በስተቀር እንዲህ ያለው አስተሳሰብ መንፈሳዊ ሚዛናችንን እንድንስት ሊያደርገን ይችላል።—ይሁዳ 3
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ይሁዳ 4) ይህን ያደረግኩት ፍርድ እንደሚጠብቃቸው በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አስቀድሞ የተነገረላቸው አንዳንድ ሰዎች ሾልከው ስለገቡ ነው፤ እነዚህ ሰዎች ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው፣ በአምላካችን ጸጋ እያሳበቡ ዓይን ያወጣ ምግባር የሚፈጽሙ እንዲሁም የዋጀንንና እሱ ብቻ ጌታችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው።
(ይሁዳ 12) እነዚህ ሰዎች ፍቅራችሁን ለመግለጽ በምታዘጋጁት ግብዣ ላይ ተገኝተው አብረዋችሁ ሲመገቡ ልክ በባሕር ውስጥ እንደተደበቀ ዓለት ከመሆናቸውም ሌላ ያላንዳች ኀፍረት ለሆዳቸው ብቻ የሚያስቡ እረኞች ናቸው፤ በነፋስ ወዲያና ወዲህ የሚነዱ ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች እንዲሁም በመከር ጊዜ ፍሬ የማይገኝባቸው፣ ሁለት ጊዜ የሞቱና ከሥራቸው የተነቀሉ ዛፎች ናቸው፤
it-2 279
ፍቅር ለመግለጽ የሚዘጋጁ ግብዣዎች
መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ግብዣዎች ምን ዓይነት እንደሆኑ እንዲሁም በየስንት ጊዜው እንደሚዘጋጁ አይናገርም። (ይሁዳ 12) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያቱ እንዲህ ያለ ግብዣ እንዲዘጋጅ አላዘዙም፤ ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ክርስቲያኖች እነዚህን ግብዣዎች የግዴታ ወይም በቋሚነት ማዘጋጀትም አይጠበቅባቸውም ነበር። አንዳንዶች እንደሚናገሩት፣ እንዲህ ያሉት ግብዣዎች ባለጸጋ ክርስቲያኖች ድሃ የሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለመጋበዝ የሚያዘጋጇቸው ድግሶች ነበሩ። አባት የሌላቸው፣ መበለቶች፣ ሀብታሞችና ድሆች ከተትረፈረፈው ማዕድ የወንድማማችነት መንፈስ በሚንጸባረቅበት ሁኔታ በአንድነት ይመገቡ ነበር።
it-2 816
ዓለት
ስፒላስ የተባለው ሌላ የግሪክኛ ቃል በባሕር ውስጥ የተደበቀ ዓለትን ለማመልከት እንደሚሠራበት ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ይሁዳ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ሾልከው የገቡ መጥፎ ዓላማ ያነገቡ ሰዎችን ለመግለጽ ይህን ቃል ተጠቅሞበታል። የተደበቀ ዓለት መርከቦችን ለከባድ አደጋ ሊዳርግ እንደሚችል ሁሉ እነዚህ ሰዎችም በሌሎቹ የጉባኤ አባላት ላይ ትልቅ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ። ይሁዳ ስለ እነዚህ ሰዎች ሲናገር “ፍቅራችሁን ለመግለጽ በምታዘጋጁት ግብዣ ላይ ተገኝተው አብረዋችሁ ሲመገቡ ልክ በባሕር ውስጥ እንደተደበቀ ዓለት [ናቸው]” ብሏል።—ይሁዳ 12
(ይሁዳ 14, 15) ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ ትውልድ የሆነው ሄኖክ ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ሲል ተንብዮአል፦ “እነሆ! ይሖዋ ከአእላፋት ቅዱሳን መላእክቱ ጋር መጥቷል፤ 15 የመጣውም በሁሉ ላይ ለመፍረድ፣ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለአምላክ አክብሮት በጎደለው መንገድ የፈጸሙትን ክፉ ድርጊትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ኃጢአተኞች በእሱ ላይ የተናገሩትን ክፉ ቃል ለማጋለጥ ነው።”
‘አምላክን በሚገባ ደስ አሰኝቷል’
ሄኖክ የተናገረው ትንቢት ምን ነበር? ትንቢቱ እንዲህ የሚል ነበር፦ “እነሆ! ይሖዋ ከአእላፋት ቅዱሳን መላእክቱ ጋር መጥቷል፤ የመጣውም በሁሉ ላይ ለመፍረድ፣ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለአምላክ አክብሮት በጎደለው መንገድ የፈጸሙትን ክፉ ድርጊትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ኃጢአተኞች በእሱ ላይ የተናገሩትን ክፉ ቃል ለማጋለጥ ነው።” (ይሁዳ 14, 15) እዚህ ላይ ሄኖክ ትንቢቱን የተናገረው ልክ እንደተፈጸመ ማለትም አምላክ በትንቢቱ ላይ የተገለጸውን ነገር እንደፈጸመ አድርጎ እንደሆነ አስተውለህ ይሆናል። ሌሎች በርካታ ትንቢቶችም የተጻፉት በዚህ መንገድ ነው። ነቢዩ፣ ገና ያልተፈጸመን ነገር እንደተፈጸመ አድርጎ የተናገረው ትንቢቱ መፈጸሙ እንደማይቀር ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ስለሆነ ነው።—ኢሳይያስ 46:10
‘አምላክን በሚገባ ደስ አሰኝቷል’
ሄኖክ ስላሳየው እምነት መመርመራችን እኛም ለምንኖርበት ዓለም ያለን አመለካከት አምላክ ካለው አመለካከት ጋር ተመሳሳይ መሆን አለመሆኑን ቆም ብለን እንድናስብ ያነሳሳን ይሆናል። ሄኖክ በድፍረት ያወጀው የፍርድ መልእክት በዚያ ዘመን ለነበረው ዓለም ያስፈልግ እንደነበረ ሁሉ አሁን ላለንበት ዓለምም አስፈላጊ ነው። ሄኖክ በተናገረው ማስጠንቀቂያ መሠረት ይሖዋ በኖኅ ዘመን የነበረውን ፈሪሃ አምላክ የሌለው ዓለም በውኃ አጥፍቶታል። በዚያን ወቅት የተከሰተው ጥፋት ወደፊት ለሚመጣው ይበልጥ ታላቅ የሆነ ጥፋት ምሳሌ ሆኗል። (ማቴዎስ 24:38, 39፤ 2 ጴጥሮስ 2:4-6) አምላክ በዚያ ወቅት እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ፈሪሃ አምላክ በሌለው በዚህ ዓለም ላይ የጽድቅ ፍርዱን ለማስፈጸም ከአእላፋት ቅዱሳን መላእክቱ ጋር በተጠንቀቅ እየተጠባበቀ ነው። እያንዳንዳችን ሄኖክ ያወጀውን ማስጠንቀቂያ ልብ ማለት እንዲሁም ይህን ማስጠንቀቂያ ለሌሎች መናገር ያስፈልገናል። እርግጥ ቤተሰቦቻችንና ጓደኞቻችን ከእኛ የተለየ አቋም ይይዙ ይሆናል። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ብቻችንን እንደሆንን ሊሰማን ይችላል። ሆኖም ይሖዋ ሄኖክን እንዳልተወው ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ታማኝ አገልጋዮቹንም አይተዋቸውም!
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(2 ዮሐንስ 1-13) ከሽማግሌው፣ ለተመረጠችው እመቤትና ለልጆቿ፦ ከልብ እወዳችኋለሁ፤ እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን ያወቁ ሁሉ ይወዷችኋል፤ 2 የምንወዳችሁ በውስጣችን በሚኖረው እውነት የተነሳ ነው፤ ይህም እውነት አብሮን ለዘላለም ይኖራል። 3 አባት ከሆነው አምላክና የአብ ልጅ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ እውነትንና ፍቅርን ጨምሮ ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም እናገኛለን። 4 ከልጆችሽ መካከል አንዳንዶቹ ከአብ በተቀበልነው ትእዛዝ መሠረት በእውነት እየተመላለሱ መሆናቸውን ስላወቅኩ እጅግ ደስ ብሎኛል። 5 ስለሆነም እመቤት ሆይ፣ እርስ በርስ እንዋደድ ዘንድ እለምንሻለሁ። (እየጻፍኩልሽ ያለሁት አዲስ ትእዛዝ ሳይሆን ከመጀመሪያ ጀምሮ የተቀበልነው ነው።) 6 ፍቅር ሲባል ደግሞ በትእዛዛቱ መሠረት መመላለስ ማለት ነው። እናንተ ከመጀመሪያ እንደሰማችሁት ትእዛዙ በፍቅር መመላለሳችሁን እንድትቀጥሉ ነው። 7 ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መምጣቱን አምነው የማይቀበሉ ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ወጥተዋልና። እንዲህ ያለ ሰው አሳችና ፀረ ክርስቶስ ነው። 8 ሙሉ ሽልማት እንድታገኙ እንጂ የደከምንባቸውን ነገሮች እንዳታጡ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። 9 ከክርስቶስ ትምህርት አልፎ የሚሄድና በትምህርቱ ጸንቶ የማይኖር ሁሉ አምላክ የለውም። በዚህ ትምህርት ጸንቶ የሚኖር ሰው ግን አብና ወልድ አሉት። 10 ማንም ሰው ወደ እናንተ ቢመጣና ይህን ትምህርት ይዞ ባይመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ወይም ሰላም አትበሉት። 11 ሰላም የሚለው ሰው የክፉ ሥራው ተባባሪ ይሆናልና። 12 የምነግራችሁ ብዙ ነገር ቢኖረኝም በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልፈልግም፤ ከዚህ ይልቅ ደስታችሁ የተሟላ እንዲሆን ወደ እናንተ መጥቼ ፊት ለፊት እንደማነጋግራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። 13 የተመረጠችው የእህትሽ ልጆች ሰላምታ ያቀርቡልሻል።
ከኅዳር 18-24
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ራእይ 1-3
“ሥራህን አውቃለሁ”
(ራእይ 1:20) በቀኝ እጄ ላይ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብት እንዲሁም የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ቅዱስ ሚስጥር ይህ ነው፦ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱን ጉባኤዎች መላእክት ያመለክታሉ፤ ሰባቱ መቅረዞች ደግሞ ሰባቱን ጉባኤዎች ያመለክታሉ።
የምታሳዩት መንፈስ ምን ዓይነት ነው?
8 እንዲህ የመሰለውን መንፈስ ለማስወገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ ‘በቀኝ እጁ ሰባት ከዋክብት እንደያዘ’ ተደርጎ መገለጹን ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። እነዚህ “ከዋክብት” በዋነኝነት ቅቡዓን የበላይ ተመልካቾችን የሚያመለክቱ ሲሆን በጉባኤ ያሉትን ሁሉንም የበላይ ተመልካቾች ሊያመለክቱም ይችላሉ። ኢየሱስ በእጁ ውስጥ ያሉትን “ከዋክብት” ተገቢ ሆኖ ባገኘው መንገድ ሁሉ መምራት ይችላል። (ራእይ 1:16, 20) ስለዚህ ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ እንደመሆኑ መጠን የሽማግሌዎችን አካል ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራል። በሽማግሌዎች አካል ውስጥ የሚያገለግል አንድ ወንድም በእርግጥ እርማት ካስፈለገው ‘እንደ እሳት ነበልባል ያሉ ዓይኖች’ ያሉት ኢየሱስ በራሱ ጊዜና መንገድ ይህ ወንድም እርማት እንዲሰጠው ያደርጋል። (ራእይ 1:14) እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን በመንፈስ ቅዱስ ለተሾሙት ወንድሞች ተገቢውን አክብሮት ማሳየታችንን መቀጠል ይኖርብናል፤ ምክንያቱም ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ነፍሳችሁን ተግተው ስለሚጠብቁና ይህን በተመለከተ ስሌት ስለሚያቀርቡ በመካከላችሁ ግንባር ቀደም ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ፤ ይህንም የምታደርጉት ሥራቸውን በደስታ እንዲያከናውኑ ነው፤ አለበለዚያ ሥራቸውን በሐዘን ያከናውናሉ፤ ይህ ደግሞ እናንተን ይጎዳችኋል።”—ዕብ. 13:17
(ራእይ 2:1, 2) በኤፌሶን ላለው ጉባኤ መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ ሰባቱን ከዋክብት በቀኝ እጁ የያዘውና በሰባቱ የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚመላለሰው እንዲህ ይላል፦ 2 ‘ሥራህን፣ ድካምህንና ጽናትህን አውቃለሁ፤ ደግሞም መጥፎ ሰዎችን መታገሥ እንደማትችል እንዲሁም ሐዋርያት ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉትን ፈትነህ ውሸታሞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ።
ይሖዋ መዳን እንድናገኝ ይጠብቀናል
11 በራእይ ምዕራፍ 2 እና 3 ላይ የሚገኘው ዘገባ ክብር የተላበሰው ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሿ እስያ የሚገኙ ሰባት ጉባኤዎችን እንደመረመረ ይናገራል። ይህ ራእይ ክርስቶስ የጉባኤዎቹን ሁኔታ በጥቅሉ ብቻ ሳይሆን በዝርዝርም እንደተመለከተ ይገልጻል። እንዲያውም ኢየሱስ የጉባኤውን አባላት በግለሰብ ደረጃ የጠቀሰበት ጊዜ ነበር፤ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ጉባኤ ተገቢውን ምስጋናና ምክር ሰጥቷል። ታዲያ ይህ ምን ይጠቁማል? በራእዩ ፍጻሜ መሠረት ሰባቱ ጉባኤዎች የሚያመለክቱት ከ1914 ወዲህ ያሉትን ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ሲሆን ለሰባቱ ጉባኤዎች የተሰጠው ምክር ደግሞ በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ ለሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች በሙሉ ይሠራል። በመሆኑም ይሖዋ ዛሬም ቢሆን በልጁ አማካኝነት ሕዝቦቹን እየመራ ነው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። ታዲያ ከዚህ አመራር ተጠቃሚ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል ተራመዱ
20 ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል መራመድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአምላክ ያገኘውን ‘የጉባኤ ራስ’ የመሆን ሥልጣን አምኖ መቀበልን ይጠይቃል። (ኤፌሶን 5:22, 23) በኢሳይያስ 55:4 ላይ ያሉት “እነሆ፣ [እኔ ይሖዋ] ለአሕዛብ ምስክር፣ ለወገኖችም አለቃና አዛዥ እንዲሆን ሰጥቼዋለሁ” የሚሉትም ቃላት ልብ ሊባሉ ይገባል። ኢየሱስ መንጋውን እንዴት እንደሚመራ አሳምሮ ያውቃል። በጎቹንና ሥራቸውን ሁሉ ያውቃል። እንዲያውም በትንሿ እስያ የነበሩትን ሰባት ጉባኤዎች በመረመረ ጊዜ ‘ሥራህን አውቃለሁ’ እያለ አምስት ጊዜ ተናግሯል። (ራእይ 2:2, 19፤ 3:1, 8, 15) በተጨማሪም ኢየሱስ ልክ እንደ አባቱ እንደ ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ያውቃል። ኢየሱስ የናሙና ጸሎቱን ይዘት ከመዘርዘሩ በፊት “ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃል” ብሏል።—ማቴዎስ 6:8-13
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ራእይ 1:7) እነሆ፣ ከደመናት ጋር ይመጣል፤ ዓይኖች ሁሉ፣ የወጉትም ያዩታል፤ በእሱም የተነሳ የምድር ነገዶች ሁሉ በሐዘን ደረታቸውን ይደቃሉ። አዎ፣ ይህ በእርግጥ ይሆናል። አሜን።
የአምላክ መንግሥት ጠላቶቹን ያጠፋል
10 ፍርድ መስጠት። ከዚህ በኋላ የአምላክ መንግሥት ጠላቶች በሙሉ ጭንቀታቸውን የሚያባብስ ነገር ለመመልከት ይገደዳሉ። ኢየሱስ “የሰው ልጅ በታላቅ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል” በማለት ተናግሯል። (ማር. 13:26) ኢየሱስ ኃይሉን በሚያሳይ እንዲህ ባለ እንግዳ የሆነ መንገድ መገለጡ ፍርድ ለመስጠት መምጣቱን የሚጠቁም ነው። ኢየሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት የተናገረው የዚሁ ትንቢት ሌላ ክፍል በዚህ ወቅት የሚሰጠውን ፍርድ በተመለከተ ዝርዝር ሐሳቦችን ይዟል። ይህን ሐሳብ ኢየሱስ ስለ በጎችና ፍየሎች በተናገረው ምሳሌ ላይ እናገኘዋለን። (ማቴዎስ 25:31-33, 46ን አንብብ።) የአምላክ መንግሥት ታማኝ ደጋፊዎች ‘በጎች’ እንደሆኑ ይፈረድላቸዋል፤ እነሱም ‘መዳናቸው እየቀረበ እንደሆነ’ ስለሚገነዘቡ ‘ራሳቸውን ቀና ያደርጋሉ።’ (ሉቃስ 21:28) የአምላክ መንግሥት ተቃዋሚዎች ግን ‘ፍየሎች’ እንደሆኑ ይፈረድባቸዋል፤ ፍየሎቹም ‘የዘላለም ጥፋት’ እንደሚጠብቃቸው ስለሚገነዘቡ “በሐዘን ደረታቸውን ይደቃሉ።”—ማቴ. 24:30፤ ራእይ 1:7
(ራእይ 2:7) መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ፦ ድል ለሚነሳ በአምላክ ገነት ውስጥ ካለው የሕይወት ዛፍ እንዲበላ እፈቅድለታለሁ።
የራእይ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1
2:7—‘የአምላክ ገነት’ የተባለው ምንድን ነው? ክርስቶስ ይህን የተናገረው ለቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደመሆኑ መጠን እዚህ ላይ የተገለጸው ገነት የሚያመለክተው በሰማይ ያለውን ገነት መሰል ሁኔታ ማለትም አምላክ ራሱ የሚገኝበትን ስፍራ መሆን ይኖርበታል። ታማኝ የሆኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘የሕይወትን ዛፍ’ የመብላት ግሩም አጋጣሚ ያገኛሉ። የማይሞት ሕይወት ይሰጣቸዋል።—1 ቆሮ. 15:53
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ራእይ 1:1-11) በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ አምላክ ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውና እሱ የገለጠው ራእይ ይህ ነው። ኢየሱስም መልአኩን ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ በምልክቶች ገለጠለት፤ 2 ዮሐንስም አምላክ ስለሰጠው ቃልና ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰጠው ምሥክርነት ይኸውም ስላያቸው ነገሮች ሁሉ መሥክሯል። 3 የዚህን ትንቢት ቃል ጮክ ብሎ የሚያነብ ደስተኛ ነው፤ እንዲሁም ቃሉን የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፉትን ነገሮች የሚጠብቁት ደስተኞች ናቸው፤ የተወሰነው ጊዜ ቀርቧልና። 4 ከዮሐንስ፣ በእስያ አውራጃ ለሚገኙ ለሰባቱ ጉባኤዎች፦ “ካለው፣ ከነበረውና ከሚመጣው” እንዲሁም በዙፋኑ ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ 5 በተጨማሪም “ታማኝ ምሥክር፣” “ከሙታን በኩር” እና “የምድር ነገሥታት ገዢ” ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ለወደደንና በገዛ ደሙ አማካኝነት ከኃጢአታችን ነፃ ላወጣን፣ 6 ነገሥታት እንዲሁም ለአምላኩና ለአባቱ ካህናት ላደረገን ለእሱ ክብርና ኃይል ለዘላለም ይሁን። አሜን። 7 እነሆ፣ ከደመናት ጋር ይመጣል፤ ዓይኖች ሁሉ፣ የወጉትም ያዩታል፤ በእሱም የተነሳ የምድር ነገዶች ሁሉ በሐዘን ደረታቸውን ይደቃሉ። አዎ፣ ይህ በእርግጥ ይሆናል። አሜን። 8 “እኔ አልፋና ኦሜጋ፣ ያለው፣ የነበረውና የሚመጣው፣ ሁሉን ቻይ ነኝ” ይላል ይሖዋ አምላክ። 9 የኢየሱስ ተከታይ በመሆኔ ከእናንተ ጋር የመከራው፣ የመንግሥቱና የጽናቱ ተካፋይ የሆንኩ እኔ ወንድማችሁ ዮሐንስ፣ ስለ አምላክ በመናገሬና ስለ ኢየሱስ በመመሥከሬ ጳጥሞስ በምትባል ደሴት ነበርኩ። 10 በመንፈስ ወደ ጌታ ቀን ተወሰድኩ፤ ከኋላዬም እንደ መለከት ያለ ኃይለኛ ድምፅ ሰማሁ፤ 11 እንዲህም አለኝ፦ “የምታየውን በመጽሐፍ ጥቅልል ላይ ጽፈህ በኤፌሶን፣ በሰምርኔስ፣ በጴርጋሞን፣ በትያጥሮን፣ በሰርዴስ፣ በፊላደልፊያና በሎዶቅያ ለሚገኙት ለሰባቱ ጉባኤዎች ላከው።”
ከኅዳር 25–ታኅሣሥ 1
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ራእይ 4-6
“የአራቱ ፈረሰኞች ግልቢያ”
(ራእይ 6:2) እኔም አየሁ፣ እነሆ ነጭ ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፤ አክሊልም ተሰጠው፤ እሱም ድል እያደረገ ወጣ፤ ድሉንም ለማጠናቀቅ ወደ ፊት ገሰገሰ።
አራቱ ፈረሰኞች—እነማን ናቸው?
የነጩ ፈረስ ጋላቢ ማን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ከዚሁ ከራእይ መጽሐፍ ላይ ማግኘት እንችላለን፤ የራእይ መጽሐፍ በሌላ ጥቅስ ላይ ይህ ጋላቢ “የአምላክ ቃል” እንደሆነ ይናገራል። (ራእይ 19:11-13) ቃል የሚለው ማዕረግ የተሰጠው የአምላክ ቃል አቀባይ ሆኖ ለሚያገለግለው ለኢየሱስ ነው። (ዮሐንስ 1:1, 14) በተጨማሪም “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ” እንዲሁም “ታማኝና እውነተኛ” ተብሎ ተጠርቷል። (ራእይ 19:11, 16) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ ተዋጊ ንጉሥ ነው፤ የተሰጠውን ሥልጣን ደግሞ ተገቢ ባልሆነ ወይም ጨቋኝ በሆነ መንገድ አይጠቀምበትም። ሆኖም ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ጥያቄዎች ይነሳሉ።
wp17.3 4 አን. 5
አራቱ ፈረሰኞች—እነማን ናቸው?
ፈረሰኞቹ መጋለብ የጀመሩት መቼ ነው? የመጀመሪያው ጋላቢ ማለትም ኢየሱስ መጋለብ የጀመረው አክሊል ሲሰጠው መሆኑን ልብ በል። (ራእይ 6:2) ታዲያ ኢየሱስ በሰማይ ላይ ንጉሥ ሆኖ አክሊሉን የተቀበለው መቼ ነው? ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ ባረገበት ወቅት ነው? አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ ሥልጣን እስኪሰጠው ድረስ የተወሰነ ጊዜ መጠበቅ አስፈልጎታል። (ዕብራውያን 10:12, 13) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ይህ ጊዜ ተጠናቆ በሰማይ ላይ መግዛት የሚጀምረው መቼ እንደሆነ የሚጠቁም ምልክት ሰጥቷቸዋል። መግዛት በሚጀምርበት ጊዜ በዓለም ላይ ያሉ ሁኔታዎች መባባስ እንደሚጀምሩ ይኸውም ጦርነት፣ የምግብ እጥረት እንዲሁም ቸነፈር እንደሚከሰት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:3, 7፤ ሉቃስ 21:10, 11) በ1914 አንደኛው የዓለም ጦርነት ከፈነዳ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ በማለት የሚጠራው በመከራ የተሞላ ጊዜ እንደጀመረ ግልጽ ሆነ።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
(ራእይ 6:4-6) ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ሌላ ፈረስ ወጣ፤ በእሱም ላይ ለተቀመጠው ሰዎች እርስ በርሳቸው ይተራረዱ ዘንድ ሰላምን ከምድር እንዲወስድ ተፈቀደለት፤ እንዲሁም ትልቅ ሰይፍ ተሰጠው። 5 ሦስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ ሦስተኛው ሕያው ፍጡር “ና!” ሲል ሰማሁ። እኔም አየሁ፣ እነሆ ጥቁር ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ይዞ ነበር። 6 ከአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት መካከል እንደ ድምፅ ያለ ነገር “አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር፣ ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፤ ደግሞም የወይራ ዘይቱንና የወይን ጠጁን አትጉዳ” ሲል ሰማሁ።
አራቱ ፈረሰኞች—እነማን ናቸው?
ይህ ጋላቢ ጦርነትን ይወክላል። ጋላቢው ሰላምን የሚወስደው ከጥቂት አገሮች ላይ ብቻ ሳይሆን ከመላው ምድር እንደሆነ ልብ በል። በ1914 በታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፋዊ ጦርነት ተከሰተ። ከዚያ በኋላ ደግሞ የከፋ ጥፋት ያስከተለ ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ተቀሰቀሰ። ከ1914 አንስቶ በተከሰቱ ጦርነቶችና ግጭቶች የተነሳ ከ100 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች እንደሞቱ ይገመታል! ሌሎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
wp17.3 5 አን. 4-5
አራቱ ፈረሰኞች—እነማን ናቸው?
“እኔም አየሁ፣ እነሆ ጥቁር ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ይዞ ነበር። ከአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት መካከል እንደ ድምፅ ያለ ነገር ‘አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር፣ ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፤ ደግሞም የወይራ ዘይቱንና የወይን ጠጁን አትጉዳ’ ሲል ሰማሁ።”—ራእይ 6:5, 6
ይህ ጋላቢ ረሃብን ይወክላል። እዚህ ጥቅስ ላይ፣ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ከመከሰቱ የተነሳ አንድ እርቦ (0.7 ኪሎ) ስንዴ በአንድ ዲናር እንደሚሸጥ የተገለጸ ሲሆን በዚያ ዘመን ደግሞ አንድ ዲናር የአንድ ሰው የሙሉ ቀን ደሞዝ ነበር። (ማቴዎስ 20:2) ጥቅሱ ሦስት እርቦ (2.1 ኪሎ) ገብስም በአንድ ዲናር እንደሚሸጥ ይናገራል፤ በወቅቱ ገብስ ከስንዴ ዝቅ ተደርጎ ይታይ ነበር። ትልቅ ቤተሰብ ያለው ሰው በዚህ እህል ቤተሰቡን እንዴት መመገብ ይችላል? በመሆኑም ሰዎች የወይራ ዘይትና የወይን ጠጅን ጭምር መቆጠብ እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል፤ በወቅቱ በነበረው ባህል የወይራ ዘይትና የወይን ጠጅ ለዕለታዊ ቀለብነት የሚያገለግሉ መሠረታዊ ነገሮች ነበሩ።
(ራእይ 6:8) እኔም አየሁ፣ እነሆ ግራጫ ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበር። መቃብርም በቅርብ ይከተለው ነበር። ሞትና መቃብርም በረጅም ሰይፍ፣ በምግብ እጥረት፣ በገዳይ መቅሰፍትና በምድር አራዊት እንዲገድሉ በምድር አንድ አራተኛ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።
wp17.3 5 አን. 8-10
አራቱ ፈረሰኞች—እነማን ናቸው?
አራተኛው ጋላቢ በወረርሽኝና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ የሚከሰት ሞትን ይወክላል። ከ1914 በኋላ ብዙም ሳይቆይ የኅዳር በሽታ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድሏል። በወቅቱ በዓለም ላይ ከሚኖሩት ሰዎች አንድ ሦስተኛው ማለትም ወደ 500 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በኅዳር በሽታ ተይዘው እንደነበር ይገመታል።
ሆኖም ወረርሽኙ በኅዳር በሽታ ብቻ አላበቃም። አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት በ20ኛው መቶ ዘመን ከ300 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በፈንጣጣ ምክንያት ሞተዋል። በሕክምናው መስክ ሰፊ ምርምር ቢደረግም እንኳ አሁንም ድረስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በኤድስ፣ በሳንባ ነቀርሳና በወባ በሽታ ምክንያት ሕይወታቸው በአጭሩ ይቀጫል።
ጦርነት፣ ረሃብም ሆነ ወረርሽኝ መጨረሻ ላይ ለሞት መዳረጋቸው አይቀርም። በቃኝን የማያውቀው መቃብር የሞቱ ሰዎችን ያለማቋረጥ እየሰበሰበ ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ራእይ 4:4) በዙፋኑ ዙሪያ 24 ዙፋኖች ነበሩ፤ በእነዚህም ዙፋኖች ላይ ነጭ ልብስ የለበሱና በራሳቸው ላይ የወርቅ አክሊል የደፉ 24 ሽማግሌዎች ተቀምጠው አየሁ።
(ራእይ 4:6) በዙፋኑ ፊት የክሪስታል መልክ ያለው እንደ ብርጭቆ ያለ ባሕር የሚመስል ነገር ነበር። በዙፋኑ መካከል እና በዙፋኑ ዙሪያ ከፊትም ሆነ ከኋላ በዓይኖች የተሞሉ አራት ሕያዋን ፍጥረታት ነበሩ።
የይሖዋ ሰማያዊ ዙፋን ክብርና ግርማ
8 ዮሐንስ በጥንቱ የመገናኛ ድንኳን ውስጥ ካህናት ተሹመው ያገለግሉ እንደነበር ያውቃል። በዚህም ምክንያት ቀጥሎ የሚገልጸውን ነገር በመመልከቱ ሳይደነቅ አይቀርም። “በዙፋኑ ዙሪያም ሀያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፣ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሀያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር።” (ራእይ 4:4) አዎን እዚህ ላይ ዮሐንስ በካህናት ምትክ እንደ ነገሥታት በዙፋን ላይ የተቀመጡና አክሊል የደፉ 24 ሽማግሌዎች ተመለከተ። እነዚህ ሽማግሌዎች እነማን ናቸው?
የይሖዋ ሰማያዊ ዙፋን ክብርና ግርማ
19 እነዚህ እንስሶች ወይም ሕያዋን ፍጥረታት የምን ምሳሌ ናቸው? ሕዝቅኤል የተባለው ሌላ ነቢይ የገለጸው ነገር የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ይረዳናል። ሕዝቅኤል ይሖዋን በሕያዋን ፍጥረታት በታጀበ ሰማያዊ ሰረገላ ላይ ተቀምጦ ተመልክቶ ነበር። (ሕዝቅኤል 1:5-11, 22-28) ሕዝቅኤል በሌላም ጊዜ ይህን በሕያዋን ፍጥረታት የታጀበውን የሠረገላ ዙፋን በድጋሚ ተመልክቶ ነበር። በዚህ ጊዜ ግን ሕያዋን ፍጥረቶቹ ኪሩቤሎች እንደሆኑ ተናግሮአል። (ሕዝቅኤል 10:9-15) ዮሐንስ የተመለከታቸው አራት እንስሳት ወይም ሕያዋን ፍጥረታት በይሖዋ መንፈሳዊ ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ ማዕረግ ያላቸውን የአምላክ ብዙ ኪሩቤሎች የሚያመለክቱ መሆን ይኖርባቸዋል። በጥንቱ የመገናኛ ድንኳን ውስጥ የይሖዋ ዙፋን ምሳሌ በሆነው በቃል ኪዳኑ ታቦት መክደኛ ላይ ሁለት የወርቅ ኪሩቤሎች ይታዩ ስለነበር ዮሐንስ ኪሩቤሎች ከይሖዋ ጋር በጣም ተቀራርበው መመልከቱ እንግዳ ነገር አልሆነበትም። የይሖዋ ቃል የእሥራኤልን ሕዝብ ለማዘዝ የሚወጣው ከእነዚህ ኪሩቤሎች መሃል ነበር።—ዘፀአት 25:22፤ መዝሙር 80:1
(ራእይ 5:5) ሆኖም ከሽማግሌዎቹ አንዱ “አታልቅስ። እነሆ፣ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፣ የዳዊት ሥር ድል ስላደረገ ሰባቱን ማኅተሞችና ጥቅልሉን ሊከፍት ይችላል” አለኝ።
“እነሆ፣ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ”
5 ብዙውን ጊዜ አንበሳ የድፍረት ምሳሌ ተደርጎ ይጠቀሳል። ከአንበሳ ጋር ፊት ለፊት ተፋጠህ ታውቃለህ? የምታውቅ ከሆነ አንበሳውን ያየኸው ለደህንነትህ በማያሰጋ ሁኔታ በታጠረ የአራዊት መጠበቂያ ውስጥ ሆኖ ሊሆን ይችላል። እንደዚያም ሆኖ እንኳ እንዲህ ያለው አጋጣሚ በውስጥህ ትንሽም ቢሆን የፍርሃት ስሜት ማሳደሩ አይቀርም። የዚህን ግዙፍና ኃይለኛ እንስሳ ፊት ትኩር ብለህ ስትመለከትና እሱም ፍጥጥ ብሎ ሲያይህ ‘መቼም አንበሳ ምንም ነገር ፈርቶ ሊሸሽ አይችልም’ ብለህ ማሰብህ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ አንበሳን “ከአራዊት መካከል ኀይለኛ የሆነው፣ ከምንም ነገር ፊት ግንባሩን የማያጥፈው” በማለት ይገልጸዋል። (ምሳሌ 30:30) ክርስቶስ ያሳየውም ድፍረት ልክ እንዲህ ዓይነት ነው።
6 ኢየሱስ እንደ አንበሳ ዓይነት ድፍረት ያሳየባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት፤ እነዚህም ለእውነት ጥብቅና መቆም፣ ለፍትሕ መቆርቆርና ተቃውሞን መጋፈጥ ናቸው። ከዚያም በተፈጥሯችን ደፋሮች ሆንም አልሆን ሁላችንም ድፍረት በማሳየት ረገድ ኢየሱስን መምሰል እንደምንችል እንመለከታለን።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ራእይ 4:1-11) ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆም፣ በሰማይ የተከፈተ በር ነበር፤ በመጀመሪያ ሲያናግረኝ የሰማሁት ድምፅ እንደ መለከት ድምፅ ያለ ነበር፤ እንዲህም አለኝ፦ “ና ወደዚህ ውጣ፤ መፈጸም ያለባቸውን ነገሮች አሳይሃለሁ።” 2 ከዚያም ወዲያውኑ የአምላክ መንፈስ ወረደብኝ፦ እነሆም፣ በሰማይ አንድ ዙፋን ተቀምጦ ነበር፤ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠ ነበር። 3 በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው የኢያስጲድ ድንጋይና የሰርድዮን ድንጋይ ዓይነት መልክ ነበረው፤ በዙፋኑም ዙሪያ መረግድ የሚመስል ቀስተ ደመና ነበር። 4 በዙፋኑ ዙሪያ 24 ዙፋኖች ነበሩ፤ በእነዚህም ዙፋኖች ላይ ነጭ ልብስ የለበሱና በራሳቸው ላይ የወርቅ አክሊል የደፉ 24 ሽማግሌዎች ተቀምጠው አየሁ። 5 ከዙፋኑ መብረቅ፣ ድምፅና ነጎድጓድ ይወጣ ነበር፤ በዙፋኑም ፊት የሚነድዱ ሰባት የእሳት መብራቶች ነበሩ፤ እነዚህም ሰባቱን የአምላክ መናፍስት ያመለክታሉ። 6 በዙፋኑ ፊት የክሪስታል መልክ ያለው እንደ ብርጭቆ ያለ ባሕር የሚመስል ነገር ነበር። በዙፋኑ መካከል እና በዙፋኑ ዙሪያ ከፊትም ሆነ ከኋላ በዓይኖች የተሞሉ አራት ሕያዋን ፍጥረታት ነበሩ። 7 የመጀመሪያው ሕያው ፍጡር አንበሳ ይመስላል፤ ሁለተኛው ሕያው ፍጡር ወይፈን ይመስላል፤ ሦስተኛው ሕያው ፍጡር የሰው ፊት የሚመስል ፊት ነበረው፤ አራተኛው ሕያው ፍጡር ደግሞ የሚበር ንስር ይመስላል። 8 እነዚህ አራቱ ሕያዋን ፍጥረታት እያንዳንዳቸው ስድስት ስድስት ክንፎች አሏቸው፤ ክንፎቹ በዙሪያቸውና በውስጥ በኩል በዓይኖች የተሞሉ ናቸው። ያለማቋረጥም ቀንና ሌሊት “የነበረው፣ ያለውና የሚመጣው፣ ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ አምላክ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው” ይላሉ። 9 ሕያዋን ፍጥረታቱ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውንና ለዘላለም የሚኖረውን ከፍ ከፍ ባደረጉ ቁጥር እንዲሁም እሱን ባከበሩና ባመሰገኑ ቁጥር 10 ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ፊት ተደፍተው ለዘላለም ለሚኖረው አምልኮ ያቀርባሉ፤ እንዲሁም አክሊላቸውን በዙፋኑ ፊት ጥለው እንዲህ ይላሉ፦ 11 “ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ እንዲሁም ወደ ሕልውና የመጡትም ሆነ የተፈጠሩት በአንተ ፈቃድ ስለሆነ ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።”