የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—የካቲት 2020
ከየካቲት 3-9
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 12-14
“ሁላችንንም የሚመለከት ቃል ኪዳን”
(ዘፍጥረት 12:1, 2) ይሖዋም አብራምን እንዲህ አለው፦ “ከአገርህ፣ ከዘመዶችህና ከአባትህ ቤት ወጥተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ። 2 አንተን ታላቅ ብሔር አደርግሃለሁ፤ እንዲሁም እባርክሃለሁ፤ ስምህንም ታላቅ አደርገዋለሁ፤ አንተም በረከት ትሆናለህ።
it-1 522 አን. 4
ቃል ኪዳን
ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን። አምላክ ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን ሥራ ላይ መዋል የጀመረው አብራም (አብርሃም) ወደ ከነአን ሲጓዝ የኤፍራጥስን ወንዝ በተሻገረበት ጊዜ ነው። የሕጉ ቃል ኪዳን የተገባው ይህ ከሆነ ከ430 ዓመታት በኋላ ነው። (ገላ 3:17) አብርሃም በከለዳውያን ዑር በምትገኘው በሜሶጶጣሚያ ይኖር በነበረበት ጊዜ ይሖዋ ያነጋገረው ሲሆን እሱ ወደሚያሳየው አገር እንዲጓዝ ነግሮታል። (ሥራ 7:2, 3፤ ዘፍ 11:31፤ 12:1-3) ዘፀአት 12:40, 41 (ሰብዓ ሊቃናት) እስራኤላውያን በግብፅና በከነአን ምድር ያሳለፉት 430 ዓመት “በተፈጸመበት በዚያው ዕለት” ከግብፅ ባርነት ነፃ እንደወጡ ይገልጽልናል። ከግብፅ ነፃ የወጡት ፋሲካ በሚከበርበት ቀን ይኸውም ኒሳን 14, 1513 ዓ.ዓ. ነው። (ዘፀ 12:2, 6, 7) ይህም አብርሃም ወደ ከነአን ሲሄድ የኤፍራጥስን ወንዝ የተሻገረው ኒሳን 14, 1943 ዓ.ዓ. ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል፤ የአብርሃም ቃል ኪዳን ሥራ ላይ መዋል የጀመረውም በዚህ ጊዜ እንደነበር መረዳት ይቻላል። አብርሃም ወደ ከነአን ምድር ገብቶ እስከ ሴኬም ድረስ ከተጓዘ በኋላ አምላክ በድጋሚ የተገለጠለት ሲሆን “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” በማለት የተስፋውን ቃል ተጨማሪ ገጽታ ነገረው፤ ይህም የአብርሃም ቃል ኪዳን በኤደን ከተሰጠው ተስፋ ጋር ተዛማጅነት እንዳለውና ‘ዘሩ’ ሰው ሆኖ እንደሚወለድ ማለትም ሰብዓዊ የዘር ሐረግ እንደሚኖረው ግልጽ አድርጓል። (ዘፍ 12:4-7) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ይሖዋ በዘፍጥረት 13:14-17፤ 15:18፤ 17:2-8, 19 እና 22:15-18 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን የዚህን ቃል ኪዳን ተጨማሪ ገጽታዎች አሳውቋል።
(ዘፍጥረት 12:3) የሚባርኩህን እባርካለሁ፤ የሚረግምህንም እረግማለሁ፤ የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በአንተ አማካኝነት ይባረካሉ።”
w89 7/1 3 አን. 4
ስለ አብርሃም እውነቱን ማወቅ የሚገባህ ለምንድን ነው?
ይህ የሚያስገርም ተስፋ ነው፤ አብርሃም ይህን የተስፋ ቃል ቢያንስ ሁለት ጊዜ ሰምቶታል። (ዘፍጥረት 18:18፤ 22:18) ይህንን ለመፈጸም አምላክ ከሞቱት ሰዎች ውስጥ የተለያዩ ወገኖችን የሚወክሉ ሰዎች ያስነሣል። ከሞት ለሚነሡት ለእነዚህ ሰዎች ሕይወት በእርግጥ በረከት ይሆንላቸዋል፤ ምክንያቱም አብዛኞቹ ሰዎች በመጀመሪያ ከጠፋችው ገነት ጋር ወደሚመሳሰል ምድራዊ ሁኔታ ይመለሳሉ። ከዚያ በኋላ የዘላለም ሕይወት በረከት እንዴት ለማግኘት እንደሚችሉ ይማራሉ።—ዘፍጥረት 2:8, 9, 15-17፤ 3:17-23
(ዘፍጥረት 13:14-17) ሎጥ ከአብራም ከተለየ በኋላ ይሖዋ አብራምን እንዲህ አለው፦ “እባክህ ካለህበት ቦታ ሆነህ ዓይንህን አቅንተህ ወደ ሰሜን፣ ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ተመልከት፤ 15 ምክንያቱም የምታየውን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘለቄታው ርስት አድርጌ እሰጣለሁ። 16 ዘርህን እንደ ምድር አፈር አበዛዋለሁ፤ ማንም ሰው የምድርን አፈር መቁጠር ከቻለ የአንተም ዘር ሊቆጠር ይችላል። 17 ተነሳ፣ ይህችን ምድር ልሰጥህ ስለሆነ በምድሪቱ ስፋትና ርዝመት ሂድ።”
it-2 213 አን. 3
ሕግ
አንዳንድ ምሑራን ከዚህ ጉዳይ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን የታሪክ መረጃዎች በማገናዘብ መሬት በሽያጭ በሚተላለፍበት ጊዜ ገዢው ከፍ ካለ ቦታ ላይ ሆኖ የመሬቱን ድንበር እንዲያይ ይደረግ እንደነበር ያምናሉ። ገዢው “አይቻለሁ” ካለ መሬቱን በሕጋዊ መንገድ እንደተቀበለ ይቆጠራል። ይሖዋ የከነአንን ምድር እንደሚወርስ ለአብርሃም ቃል በገባለት ጊዜ አብርሃምን በአራቱም አቅጣጫዎች እንዲመለከት አዞታል። አብርሃም “አይቻለሁ” ያላለው አምላክ የተስፋይቱን ምድር እንደሚሰጥ የተናገረው ለአብርሃም ዘር ስለሆነ ሊሆን ይችላል። (ዘፍ 13:14, 15) የእስራኤል ሕጋዊ ወኪል የነበረው ሙሴ ምድሪቱን ‘እንዲመለከት’ ተነግሮት ነበር፤ ከላይ ያነሳነው ሐሳብ ትክክል ከሆነ ሙሴ ምድሪቱን መመልከቱ ምድሪቱ በኢያሱ መሪነት ወደ ተስፋይቱ ምድር ለሚገባው የእስራኤል ሕዝብ ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንደተሰጠች ያመለክታል። (ዘዳ 3:27, 28፤ 34:4፤ በተጨማሪም ማቴ 4:8 ላይ ሰይጣን ለኢየሱስ ያቀረበውን ግብዣ ተመልከት።) ሌላው ሕጋዊ ይዘት ያለው ድርጊት ደግሞ አንድን ርስት የመረከብ ዓላማ ይዞ በርስቱ ላይ መዘዋወር ወይም ወደ ርስቱ መግባት ነው። (ዘፍ 13:17፤ 28:13) መሬት በሚሸጥበት ጊዜ መሬቱ ላይ ያሉት ዛፎች ተቆጥረው ይመዘገቡ እንደነበር አንዳንድ የጥንት ሰነዶች ይጠቁማሉ።—ከዘፍ 23:17, 18 ጋር አወዳድር።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 13:8, 9) ስለዚህ አብራም ሎጥን እንዲህ አለው፦ “እባክህ በእኔና በአንተ እንዲሁም በእኔ እረኞችና በአንተ እረኞች መካከል ምንም ዓይነት ጠብ አይኑር፤ እኛ እኮ ወንድማማቾች ነን። 9 ምድሪቱ ሁሉ በእጅህ አይደለችም? እባክህ ከእኔ ተለይ። አንተ ወደ ግራ ብትሄድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተ ወደ ቀኝ ብትሄድ ደግሞ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ።”
አለመግባባቶችን በፍቅር መፍታት
12 በመግቢያችን ላይ፣ በአብርሃምና የወንድሙ ልጅ በሆነው በሎጥ መካከል ክፍፍል ሊፈጥር የሚችል ጉዳይ ተከስቶ እንደነበር የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ተመልክተናል፤ ይሁንና እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ችግሩን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ፈተውታል። ሁለቱም ሰዎች ከብቶች ነበሯቸው፤ በግጦሽ መሬት ምክንያት ሳይሆን አይቀርም በእረኞቻቸው መካከል ጠብ ተነሳ። ሆኖም አብርሃም የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ሲል፣ ሎጥ ለእሱና ለቤተሰቡ መኖሪያ የሚሆነውን ቦታ መርጦ እንዲወስድ ቅድሚያውን ሰጠው። (ዘፍ. 13:1, 2, 5-9) እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! አብርሃም የራሱን ፍላጎት ወደ ጎን በመተው ሰላም የሚሰፍንበትን መንገድ ፈልጓል። እንዲህ ያለ ደግነት በማሳየቱ ተጎድቷል? በፍጹም። ይህ ሁኔታ ከተፈጠረ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ታላቅ በረከት እንደሚያፈስለት ቃል ገብቶለታል። (ዘፍ. 13:14-17) አምላክ፣ አገልጋዮቹ ከመለኮታዊ መመሪያዎች ጋር የሚስማማ እርምጃ ለመውሰድና አለመግባባቶችን በፍቅር ለመፍታት ጥረት በማድረጋቸው ምክንያት ዘላቂ ጉዳት እንዲደርስባቸው ፈጽሞ አይፈቅድም።
(ዘፍጥረት 14:18-20) የሳሌም ንጉሥ መልከጼዴቅም ምግብና የወይን ጠጅ ይዞ ወጣ፤ እሱም የልዑሉ አምላክ ካህን ነበር። 19 አብራምንም ባረከው፤ እንዲህም አለው፦ “ሰማይንና ምድርን የሠራው ልዑሉ አምላክ አብራምን ይባርክ፤ 20 የሚጨቁኑህን በእጅህ አሳልፎ የሰጠህ፣ ልዑሉ አምላክ ይወደስ!” አብራምም ከሁሉም ነገር ላይ አንድ አሥረኛውን ሰጠው።
(ዕብራውያን 7:4-10) እንግዲህ የቤተሰብ ራስ የሆነው አብርሃም ምርጥ ከሆነው ምርኮ ላይ አንድ አሥረኛውን የሰጠው ይህ ሰው ምን ያህል ታላቅ እንደነበረ ተመልከቱ። 5 እርግጥ የክህነት ኃላፊነት የሚቀበሉ ከሌዊ ልጆች ወገን የሆኑት ሰዎች ምንም እንኳ ወንድሞቻቸው የአብርሃም ዘሮች ቢሆኑም ከሕዝቡ ማለትም ከገዛ ወንድሞቻቸው አሥራት እንዲሰበስቡ ሕጉ ያዛል። 6 ሆኖም ከእነሱ የትውልድ ሐረግ ያልመጣው ይህ ሰው ከአብርሃም አሥራት የተቀበለ ሲሆን የተስፋ ቃል የተሰጠውን ሰው ባርኮታል። 7 እንግዲህ አነስተኛ የሆነው ከእሱ በሚበልጠው እንደተባረከ ምንም ጥርጥር የለውም። 8 በአንድ በኩል አሥራት የሚቀበሉት ሟች የሆኑ ሰዎች ሲሆኑ በሌላ በኩል ግን አሥራት የሚቀበለው ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሠከረለት ሰው ነው። 9 እንግዲህ አሥራት የሚቀበለው ሌዊ እንኳ በአብርሃም በኩል አሥራት ከፍሏል ማለት ይቻላል፤ 10 መልከጼዴቅ አብርሃምን ባገኘው ጊዜ ሌዊ ገና በአባቱ በአብርሃም አብራክ ውስጥ ነበርና።
it-2 683 አን. 1
ካህን
የሳሌም ንጉሥ መልከጼዴቅ ለየት ያለ ካህን (ኮኸን) ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ሰው የዘር ሐረግ እንዲሁም ስለ ሕይወቱ መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ ምንም የሚናገረው ነገር የለም። ክህነቱን ያገኘው በውርስ አይደለም፤ በተጨማሪም በክህነት አገልግሎቱ ከእሱ በፊት የነበረም ሆነ እሱን የተካ ሌላ ሰው የለም። መልከጼዴቅ ንጉሥም ካህንም ነበር። ክህነቱ ከሌዋውያን ክህነት የላቀ ነበር፤ ምክንያቱም አብርሃም ለመልከጼዴቅ አሥራት በከፈለበትና በተባረከበት ጊዜ ሌዊ በአብርሃም አብራክ ውስጥ ስለነበር ሌዊ ለመልከጼዴቅ አሥራት ከፍሏል ሊባል ይችላል። (ዘፍ 14:18-20፤ ዕብ 7:4-10) ከዚህ ሁሉ አንጻር መልከጼዴቅ “እንደ መልከጼዴቅ፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ለተባለለት ለኢየሱስ ክርስቶስ ጥላ ሆኗል።—ዕብ 7:17
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፍጥረት 12:1-20) ይሖዋም አብራምን እንዲህ አለው፦ “ከአገርህ፣ ከዘመዶችህና ከአባትህ ቤት ወጥተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ። 2 አንተን ታላቅ ብሔር አደርግሃለሁ፤ እንዲሁም እባርክሃለሁ፤ ስምህንም ታላቅ አደርገዋለሁ፤ አንተም በረከት ትሆናለህ። 3 የሚባርኩህን እባርካለሁ፤ የሚረግምህንም እረግማለሁ፤ የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በአንተ አማካኝነት ይባረካሉ።” 4 ስለዚህ አብራም ልክ ይሖዋ በነገረው መሠረት ወጣ፤ ሎጥም አብሮት ሄደ። አብራም ከካራን በወጣበት ጊዜ ዕድሜው 75 ዓመት ነበር። 5 አብራም ሚስቱን ሦራን፣ የወንድሙን ልጅ ሎጥን እንዲሁም ያፈሩትን ንብረት ሁሉና በካራን አብረዋቸው የነበሩትን ሰዎች በሙሉ ይዞ ተነሳ፤ እነሱም ወደ ከነአን ምድር አቀኑ። ከነአን ምድር በደረሱም ጊዜ 6 አብራም በሞሬ ትላልቅ ዛፎች አቅራቢያ እስከሚገኘው ሴኬም እስከሚባለው አካባቢ ድረስ ወደ ምድሪቱ ዘልቆ ገባ። በዚያን ጊዜ ከነአናውያን በምድሪቱ ይኖሩ ነበር። 7 ይሖዋም ለአብራም ተገለጠለትና “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” አለው። ስለዚህ አብራም ተገልጦለት ለነበረው ለይሖዋ በዚያ መሠዊያ ሠራ። 8 በኋላም ከዚያ ተነስቶ ከቤቴል በስተ ምሥራቅ ወደሚገኘው ተራራማ አካባቢ ተጓዘ፤ እሱም ቤቴልን በስተ ምዕራብ፣ ጋይን ደግሞ በስተ ምሥራቅ አድርጎ ድንኳኑን ተከለ። በዚያም ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ፤ የይሖዋንም ስም ጠራ። 9 ከዚያ በኋላ አብራም ድንኳኑን ነቅሎ በየቦታው እየሰፈረ ወደ ኔጌብ ተጓዘ። 10 በምድሪቱም ላይ ረሃብ ተከሰተ፤ ረሃቡ በጣም አስከፊ ስለነበር አብራም ለተወሰነ ጊዜ በግብፅ ለመኖር ወደዚያ ወረደ። 11 ወደ ግብፅ ለመግባት ሲቃረብም ሚስቱን ሦራን እንዲህ አላት፦ “እባክሽ ስሚኝ፤ አንቺ በጣም ውብ ሴት ነሽ። 12 ስለሆነም ግብፃውያን አንቺን ሲያዩ ‘ይህች ሚስቱ ናት’ ማለታቸው አይቀርም። ከዚያም እኔን ይገድሉኛል፤ አንቺን ግን ይተዉሻል። 13 በአንቺ የተነሳ መልካም እንዲሆንልኝ እባክሽ፣ እህቴ እንደሆንሽ አድርገሽ ተናገሪ፤ እንዲህ ካደረግሽ ሕይወቴ ይተርፋል።” 14 አብራምም ግብፅ እንደደረሰ ግብፃውያኑ ሴቲቱ እጅግ ውብ እንደሆነች ተመለከቱ። 15 የፈርዖንም መኳንንት ሴቲቱን አዩአት፤ ስለ እሷም ለፈርዖን በአድናቆት ነገሩት። በመሆኑም ሴቲቱ ወደ ፈርዖን ቤት ተወሰደች። 16 ፈርዖንም በእሷ ምክንያት አብራምን ተንከባከበው፤ በጎችን፣ ከብቶችን፣ ተባዕትና እንስት አህዮችን፣ ግመሎችን እንዲሁም ወንድና ሴት አገልጋዮችን ሰጠው። 17 ከዚያም ይሖዋ በአብራም ሚስት በሦራ የተነሳ ፈርዖንንና ቤተሰቡን በታላቅ መቅሰፍት መታ። 18 በመሆኑም ፈርዖን አብራምን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ይህ ያደረግክብኝ ነገር ምንድን ነው? ሚስትህ እንደሆነች ያልነገርከኝ ለምንድን ነው? 19 ‘እህቴ ናት’ ያልከውስ ለምንድን ነው? እኔ እኮ ወስጄ ሚስቴ ላደርጋት ነበር። በል፣ ሚስትህ ይችውልህ፤ ይዘሃት ሂድ!” 20 ስለዚህ ፈርዖን አብራምን በተመለከተ ለአገልጋዮቹ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ እነሱም አብራምን ከሚስቱና ከንብረቱ ሁሉ ጋር አሰናበቱት።
ከየካቲት 10-16
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 15-17
“ይሖዋ የአብራምንና የሦራን ስም የቀየረው ለምንድን ነው?”
(ዘፍጥረት 17:1) አብራም ዕድሜው 99 ዓመት ሲሆን ይሖዋ ተገለጠለትና እንዲህ አለው፦ “እኔ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ። በፊቴ ተመላለስ፤ እንከን የሌለብህ መሆንህንም አስመሥክር።
it-1 817
እንከን፣ እንከን መፈላለግ
በሌላ በኩል ደግሞ የሰው መንገድና ሥራዎቹ ሁሉ በአብዛኛው እንከን ያለባቸው ናቸው። የሰው ልጆች በሙሉ የአዳም ዘሮች ስለሆኑ ሁሉም ኃጢአተኞችና በደለኞች ሆነዋል። (ሮም 5:12፤ መዝ 51:5) ይሖዋ ግን እንከን የለሽ አምላክ ነው፤ ያም ሆኖ ‘እንዴት እንደተሠራን በሚገባ ስለሚያውቅና አፈር መሆናችንን ስለሚያስታውስ’ ምሕረት ያደርግልናል። (መዝ 103:13, 14) ታማኝና ታዛዥ የነበረውን ኖኅን “በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች መካከል . . . እንከን የሌለበት” አድርጎ ቆጥሮታል። (ዘፍ 6:9) አብርሃምን “በፊቴ ተመላለስ፤ እንከን የሌለብህ መሆንህንም አስመሥክር” በማለት አዞታል። (ዘፍ 17:1) ሁለቱም ሰዎች ፍጽምና የጎደላቸው ከመሆኑም ሌላ ከጊዜ በኋላ ሞተዋል፤ ‘ልብን የሚያየው’ ይሖዋ ግን እንከን የለሽ እንደሆኑ አድርጎ ቆጥሯቸዋል። (1ሳሙ 16:7፤ ከ2ነገ 20:3 እና 2ዜና 16:9 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ እስራኤላውያንን “በአምላክህ በይሖዋ ፊት እንከን የለሽ ሆነህ መገኘት አለብህ” ሲል አዟቸዋል። (ዘዳ 18:13፤ 2ሳሙ 22:24) አምላክ እንከን የሌለበት ልጁን (ዕብ 7:26) ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል፤ ይህም የጽድቅ መሥፈርቱን ሳያላላና እንከን የለሽ ዳኝነቱን ጥያቄ ላይ ሳይጥል እምነት ያላቸውንና ታዛዥ የሆኑ ሰዎችን “ጻድቅ” ወይም እንከን የለሽ አድርጎ እንዲቆጥር አስችሎታል—ሮም 3:25, 26፤ ንጹሕ አቋም፤ ፍጽምና የሚለውን ተመልከት።
(ዘፍጥረት 17:3-5) በዚህ ጊዜ አብራም በግንባሩ ተደፋ፤ አምላክም እንዲህ በማለት እሱን ማነጋገሩን ቀጠለ፦ 4 “በእኔ በኩል ከአንተ ጋር የገባሁት ቃል ኪዳኔ እንደጸና ነው፤ አንተም በእርግጥ የብዙ ብሔር አባት ትሆናለህ። 5 ከእንግዲህ ስምህ አብራም አይባልም፤ የብዙ ብሔር አባት ስለማደርግህ ስምህ አብርሃም ይሆናል።
it-1 31 አን. 1
አብርሃም
ዓመታት አለፉ። አብርሃምና ሣራ በከነአን መኖር ከጀመሩ አሥር ዓመት ገደማ ሆኗቸዋል፤ ሣራ ግን አሁንም ልጅ አልወለደችም። በመሆኑም በእሷ ምትክ ልጅ እንድትወልድላት ግብፃዊት አገልጋይዋን አጋርን ለአብርሃም ለመስጠት ሐሳብ አቀረበች። አብርሃምም በሐሳቧ ተስማማ። በዚህ መንገድ በ1932 ዓ.ዓ. አብርሃም የ86 ዓመት ሰው እያለ እስማኤል ተወለደ። (ዘፍ 16:3, 15, 16) ይህ ከሆነ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ማለትም በ1919 ዓ.ዓ. አብርሃም የ99 ዓመት ሰው እያለ ይሖዋ በአብርሃም ቤት ያሉ ወንዶች ሁሉ እንዲገረዙ አዘዘ፤ ይህም በይሖዋና በአብርሃም መካከል ለተገባው ልዩ ቃል ኪዳን እንደ ምልክት ወይም ማኅተም ሆኖ የሚያገለግል ነበር። ይሖዋ አብርሃምን “የብዙ ብሔር አባት [አደርግሃለሁ]” በማለት ስሙን ከአብራም ወደ አብርሃም የቀየረውም በዚሁ ጊዜ ነው። (ዘፍ 17:5, 9-27፤ ሮም 4:11) ከዚህ ብዙም ሳይቆይ አብርሃም በእንግድነት የተቀበላቸው ሥጋ የለበሱ ሦስት መላእክት ሣራ ራሷ ፀንሳ በቀጣዩ ዓመት ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ቃል ገቡ!—ዘፍ 18:1-15
(ዘፍጥረት 17:15, 16) ከዚያም አምላክ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ “ሚስትህን ሦራን በተመለከተ ሦራ ብለህ አትጥራት፤ ምክንያቱም ከእንግዲህ ስሟ ሣራ ይሆናል። 16 እኔም እባርካታለሁ፤ ከእሷም ወንድ ልጅ እሰጥሃለሁ። እባርካታለሁ፤ እሷም ብዙ ብሔር ትሆናለች፤ የሕዝቦች ነገሥታትም ከእሷ ይወጣሉ።”
ስሞች ያላቸው ትርጉም
አምላክ ራሱ ትንቢታዊ መልእክት እንዲኖረው ሲል የአንዳንድ አገልጋዮቹን ስም ቀይሯል። ለአብነት ያህል፣ “አባት ተከበረ” የሚል ትርጉም ያለው የአብራም ስም ተቀይሮ አብርሃም (“የብዙ ሕዝቦች አባት” ማለት ነው) ተብሎ እንዲጠራ አድርጓል። አብርሃም ከስሙ ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ የብዙ ሕዝቦች አባት ሆኗል። (ዘፍጥረት 17:5, 6) የአብርሃም ሚስት የሆነችውን የሦራንም ስም እንመልከት። የስሟ ትርጉም “ተፎካካሪ” ማለት እንደሆነ ይገመታል። አምላክ፣ የነገሥታት ቅድመ አያት እንደምትሆን በማመልከት “ልዕልት” የሚል ትርጉም ያለው “ሣራ” የሚል ስም ሲሰጣት ምንኛ ተደስታ ይሆን።—ዘፍጥረት 17:15, 16
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 15:13, 14) አምላክም አብራምን እንዲህ አለው፦ “ዘሮችህ በባዕድ አገር ባዕዳን ሆነው እንደሚኖሩ እንዲሁም በዚያ ያሉት ሰዎች ለ400 ዓመት በባርነት እንደሚገዟቸውና እንደሚያጎሳቁሏቸው በእርግጥ እወቅ። 14 ይሁንና በባርነት በሚገዛቸው ብሔር ላይ እፈርዳለሁ፤ እነሱም ብዙ ንብረት ይዘው ይወጣሉ።
it-1 460-461
የዘመናት ስሌት
ይሖዋ አብራምን (አብርሃምን) እንዲህ ብሎታል፦ “ዘሮችህ በባዕድ አገር ባዕዳን ሆነው እንደሚኖሩ እንዲሁም በዚያ ያሉት ሰዎች ለ400 ዓመት በባርነት እንደሚገዟቸውና እንደሚያጎሳቁሏቸው በእርግጥ እወቅ።” (ዘፍ 15:13፤ በተጨማሪም ሥራ 7:6, 7ን ተመልከት።) ይሖዋ ይህን ሐሳብ የተናገረው ተስፋ የተሰጠበት ወራሽ ወይም “ዘር” ይኸውም ይስሐቅ ከመወለዱ በፊት ነው። በ1932 ዓ.ዓ. ግብፃዊቷ አገልጋይ አጋር ለአብራም እስማኤልን ወለደችለት፤ በ1918 ዓ.ዓ. ደግሞ ይስሐቅ ተወለደ። (ዘፍ 16:16፤ 21:5) ‘ጉስቁልናው’ ካበቃበት (ዘፍ 15:14) ማለትም እስራኤላውያን ከግብፅ ነፃ ከወጡበት ጊዜ 400 ዓመት ወደ ኋላ ስንቆጥር 1913 ዓ.ዓ. ላይ እንደርሳለን፤ በወቅቱ ይስሐቅ አምስት ዓመት ገደማ የሚሆነው ልጅ ነበር። በባዕድ አገር ‘ባዕድ ሆኖ’ ይኖር የነበረው ይስሐቅ ጡት የጣለው በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም፤ አስቀድሞ የተነገረው ጉስቁልና የጀመረው 19 ዓመት ገደማ የሆነው እስማኤል በይስሐቅ ላይ ‘ባፌዘበት’ በዚህ ወቅት ነው። (ዘፍ 21:8, 9) በዘመናችን እስማኤል በአብርሃም ወራሽ ላይ ማሾፉ ያን ያህል የሚያስገርም ነገር ላይመስል ቢችልም በዚያ ዘመን የነበረው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ሣራ የተሰማት ስሜት እንዲሁም አጋርና ልጇ እስማኤል ከቤት መባረር አለባቸው በማለት የያዘችውን አቋም አምላክ መደገፉ ይህ ጉዳይ በቀላሉ የሚታይ እንዳልነበር ይጠቁማል። (ዘፍ 21:10-13) ይህ ክንውን በአምላክ ቃል ውስጥ በዝርዝር ተመዝግቦ እንዲቆይ መደረጉ በራሱ እስራኤላውያን ከግብፅ ነፃ እስከሚወጡበት ጊዜ ድረስ የሚዘልቀው በትንቢት የተነገረው የ400 ዓመት የጉስቁልና ዘመን እንደጀመረ የሚጠቁም ምልክት መሆኑን ያሳያል።—ገላ 4:29
(ዘፍጥረት 15:16) ሆኖም በአራተኛው ትውልድ ወደዚህ ይመለሳሉ፤ ምክንያቱም የአሞራውያን በደል ጽዋው ገና አልሞላም።”
it-1 778 አን. 4
ከግብፅ ነፃ መውጣት
“በአራተኛው ትውልድ።” ይሖዋ ለአብርሃም፣ ዘሮቹ በአራተኛው ትውልድ ላይ ወደ ከነአን እንደሚመለሱ እንደነገረው ማስታወስ ይኖርብናል። (ዘፍ 15:16) የአብርሃም ቃል ኪዳን ሥራ ላይ መዋል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስራኤላውያን ከግብፅ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ ባሉት 430 ዓመታት ውስጥ (በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መሠረት በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች የሚኖሩትን ረጅም ዕድሜ ግምት ውስጥ ብናስገባ እንኳ) ከአራት በላይ ትውልዶች ኖረዋል። ሆኖም እስራኤላውያን ግብፅ ውስጥ የቆዩት ለ215 ዓመታት ብቻ ነው። ግብፅ ውስጥ ከገቡ በኋላ ያለፉትን ‘አራት ትውልዶች’ ለማስላት አንዱን የእስራኤል ነገድ ብቻ ማለትም የሌዊን ነገድ እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን፦ (1) ሌዊ፣ (2) ቀአት፣ (3) አምራም እና (4) ሙሴ።—ዘፀ 6:16, 18, 20
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፍጥረት 15:1-21) ከዚህ በኋላ የይሖዋ ቃል በራእይ ወደ አብራም መጥቶ “አብራም አትፍራ። እኔ ጋሻ እሆንሃለሁ። የምታገኘውም ሽልማት እጅግ ታላቅ ይሆናል” አለው። 2 አብራምም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ያለልጅ እንደቀረሁና ቤቴን የሚወርሰው የደማስቆ ሰው የሆነው ኤሊዔዘር እንደሆነ ታያለህ፤ ታዲያ ምን ትሰጠኛለህ?” 3 በተጨማሪም አብራም “እንግዲህ ዘር አልሰጠኸኝም፤ ደግሞም ወራሼ የሚሆነው በቤቴ ያለው አገልጋይ ነው” አለ። 4 ሆኖም እንዲህ የሚል የይሖዋ ቃል ወደ እሱ መጣ፦ “ይህ ሰው ወራሽህ አይሆንም፤ ከዚህ ይልቅ የገዛ ልጅህ ወራሽህ ይሆናል።” 5 ወደ ውጭም ካወጣው በኋላ “እባክህ ቀና ብለህ ወደ ሰማይ ተመልከት፤ እስቲ መቁጠር ከቻልክ ከዋክብቱን ቁጠራቸው” አለው። ከዚያም “የአንተም ዘር እንዲሁ ይሆናል” አለው። 6 አብራምም በይሖዋ አመነ፤ አምላክም ይህን ጽድቅ አድርጎ ቆጠረለት። 7 ደግሞም እንዲህ አለው፦ “ይህችን ምድር ርስት አድርጌ ልሰጥህ ከከለዳውያን ዑር ያወጣሁህ እኔ ይሖዋ ነኝ።” 8 አብራምም “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ይህችን ምድር ርስት አድርጌ እንደምወርስ እንዴት አውቃለሁ?” አለ። 9 እሱም መልሶ “አንዲት የሦስት ዓመት ጊደር፣ አንዲት የሦስት ዓመት ፍየል፣ አንድ የሦስት ዓመት አውራ በግ እንዲሁም አንድ ዋኖስና አንድ የርግብ ጫጩት ውሰድ” አለው። 10 እሱም እነዚህን እንስሳት ሁሉ ወስዶ ለሁለት ሰነጠቃቸው፤ ከዚያም አንዱን ግማሽ ከሌላኛው ግማሽ ትይዩ አድርጎ አስቀመጠ። ወፎቹን ግን አልሰነጠቃቸውም። 11 አሞሮችም በበድኖቹ ላይ መውረድ ጀመሩ፤ አብራም ግን ያባርራቸው ነበር። 12 ፀሐይ ልትጠልቅ ስትቃረብም አብራም ከባድ እንቅልፍ ወሰደው፤ ታላቅና የሚያስፈራ ጨለማም ወረደበት። 13 አምላክም አብራምን እንዲህ አለው፦ “ዘሮችህ በባዕድ አገር ባዕዳን ሆነው እንደሚኖሩ እንዲሁም በዚያ ያሉት ሰዎች ለ400 ዓመት በባርነት እንደሚገዟቸውና እንደሚያጎሳቁሏቸው በእርግጥ እወቅ። 14 ይሁንና በባርነት በሚገዛቸው ብሔር ላይ እፈርዳለሁ፤ እነሱም ብዙ ንብረት ይዘው ይወጣሉ። 15 አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ ዕድሜ ጠግበህም ወደ መቃብር ትወርዳለህ። 16 ሆኖም በአራተኛው ትውልድ ወደዚህ ይመለሳሉ፤ ምክንያቱም የአሞራውያን በደል ጽዋው ገና አልሞላም።” 17 ፀሐይዋ ከጠለቀችና ድቅድቅ ጨለማ አካባቢውን ከዋጠው በኋላ የሚጨስ ምድጃ ታየ፤ ለሁለት በተከፈለውም ሥጋ መካከል የሚንቦገቦግ ችቦ አለፈ። 18 በዚያ ቀን ይሖዋ እንዲህ ሲል ከአብራም ጋር ቃል ኪዳን ገባ፦ “ከግብፅ ወንዝ አንስቶ እስከ ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለውን ይህን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ፤ 19 የቄናውያንን፣ የቀኒዛውያንን፣ የቃድሞናውያንን፣ 20 የሂታውያንን፣ የፈሪዛውያንን፣ የረፋይምን፣ 21 የአሞራውያንን፣ የከነአናውያንን፣ የገርጌሻውያንንና የኢያቡሳውያንን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ።”
ከየካቲት 17-23
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 18-19
“‘የምድር ሁሉ ዳኛ’ በሰዶምና በገሞራ ላይ የጥፋት ፍርድ በየነ”
(ዘፍጥረት 18:23-25) ከዚያም አብርሃም ቀረብ ብሎ እንዲህ አለ፦ “በእርግጥ ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አብረህ ታጠፋለህ? 24 እስቲ በከተማዋ ውስጥ 50 ጻድቅ ሰዎች አሉ እንበል። ታዲያ ሁሉንም ዝም ብለህ ታጠፋቸዋለህ? በውስጧ ስለሚኖሩት 50 ጻድቃን ስትል ስፍራውን አትምርም? 25 በጻድቁም ሆነ በኃጢአተኛው ላይ ተመሳሳይ ነገር እንዲደርስ የሚያደርግ እንዲህ ዓይነት እርምጃ በመውሰድ ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አንድ ላይ ትገድላለህ ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው! ይህ በአንተ ዘንድ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። የምድር ሁሉ ዳኛ ትክክል የሆነውን ነገር አያደርግም?”
“የምድር ሁሉ ዳኛ” ምንጊዜም ትክክል የሆነውን ነገር ያደርጋል
“የምድር ሁሉ ዳኛ ትክክል የሆነውን ነገር አያደርግም?” (ዘፍ. 18:25) አብርሃም ይህን ጥያቄ ሲያነሳ፣ ይሖዋ ከሰዶምና ከገሞራ ጋር በተያያዘ ፍጹም ፍትሐዊ የሆነ ፍርድ እንደሚያስተላልፍ ያለውን እምነት መግለጹ ነበር። ይሖዋ “ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አንድ ላይ [በመግደል]” ፍትሕ እንደማያዛባ አብርሃም እርግጠኛ ነበር። አብርሃም እንዲህ ያለው ድርጊት “ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር” እንደሆነ ገልጿል። አብርሃም ይህን ካለ ከ400 ዓመታት ገደማ በኋላ ይሖዋ ስለ ራሱ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እሱ ዓለት፣ የሚያደርገውም ነገር ሁሉ ፍጹም ነው፤ መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸውና። እሱ ፈጽሞ ፍትሕን የማያጓድል ታማኝ አምላክ ነው፤ ጻድቅና ትክክለኛ ነው።”—ዘዳ. 31:19፤ 32:4
(ዘፍጥረት 18:32) በመጨረሻም አብርሃም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ እባክህ፣ አትቆጣና አንድ ጊዜ ብቻ ልናገር፤ በዚያ አሥር ብቻ ቢገኙስ?” እሱም መልሶ “ስለ አሥሩ ስል አላጠፋትም” አለ።
ትዕግሥት—በተስፋ መጽናት
ትዕግሥት በማሳየት ረገድ ሁላችንም ልንከተለው የሚገባን ከሁሉ የላቀው ምሳሌ ይሖዋ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። (2 ጴጥ. 3:15) ይሖዋ ከፍተኛ ትዕግሥት ስላሳየባቸው ወቅቶች የሚናገሩ ብዙ ታሪኮችን በአምላክ ቃል ውስጥ እናገኛለን። (ነህ. 9:30፤ ኢሳ. 30:18) ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ሰዶምን ለማጥፋት ያደረገውን ውሳኔ በተመለከተ አብርሃም በተደጋጋሚ ጥያቄ ባነሳበት ወቅት ይሖዋ ምን እንዳደረገ እንመልከት። በመጀመሪያ ደረጃ፣ አብርሃም ሲናገር ይሖዋ በመሃል ጣልቃ ገብቶ አላቋረጠውም። ከዚህ ይልቅ አብርሃም ጥያቄ ሲጠይቅና ያሳሰቡትን ነገሮች ሲገልጽ ይሖዋ በትዕግሥት አዳምጦታል። ከዚያም ይሖዋ አብርሃም የተናገረውን ነገር በድጋሚ በመናገር እያዳመጠው እንደሆነ አሳይቷል፤ በተጨማሪም ሰዶም ውስጥ አሥር ጻድቃን እንኳ ቢገኙ ከተማዋን እንደማያጠፋት አረጋግጦለታል። (ዘፍ. 18:22-33) ይሖዋ በትዕግሥት በማዳመጥና ቶሎ ባለመቆጣት ረገድ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል!
(ዘፍጥረት 19:24, 25) ከዚያም ይሖዋ በሰዶምና በገሞራ ላይ እሳትና ድኝ አዘነበ፤ ይህም የመጣው ከሰማይ ከይሖዋ ዘንድ ነው። 25 እሱም እነዚህን ከተሞች ገለባበጠ፤ አዎ፣ የከተሞቹን ነዋሪዎችና የምድሪቱን ተክል ሁሉ ጨምሮ መላውን አውራጃ ገለባበጠ።
ይሖዋ ሉዓላዊ ጌታችን ነው!
12 ይሖዋ በቅርቡ ሉዓላዊነቱን እንደሚያረጋግጥ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ ክፋትን ለዘላለም አይታገሥም፤ በአሁኑ ጊዜ የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀኖች ውስጥ እንደሆነ እናውቃለን። ይሖዋ በኖኅ ዘመን በክፉዎች ላይ እርምጃ ወስዷል። ሰዶምና ገሞራን እንዲሁም ፈርዖንንና ሠራዊቱን አጥፍቷል። ሲሣራና ሠራዊቱ እንዲሁም የአሦር ንጉሥ ሰናክሬምና ሠራዊቱ ከሁሉ በላይ የሆነውን አምላክ ሊቋቋሙት አልቻሉም። (ዘፍ. 7:1, 23፤ 19:24, 25፤ ዘፀ. 14:30, 31፤ መሳ. 4:15, 16፤ 2 ነገ. 19:35, 36) በመሆኑም ይሖዋ አምላክ ስሙን የሚንቁትንና ምሥክሮቹን የሚጨቁኑትን ለዘላለም እንደማይታገሥ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ የኢየሱስን መገኘትና የዚህን ክፉ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክቶች እያየን ነው።—ማቴ. 24:3
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 18:1) ከዚያም አብርሃም በጣም ሞቃታማ በሆነው የቀኑ ክፍለ ጊዜ ድንኳኑ ደጃፍ ላይ ተቀምጦ ሳለ ይሖዋ በማምሬ ትላልቅ ዛፎች አጠገብ ተገለጠለት።
(ዘፍጥረት 18:22) ሰዎቹም ከዚያ ተነስተው ወደ ሰዶም አቀኑ፤ ይሖዋ ግን እዚያው ከአብርሃም ጋር ቀረ።
w88-E 5/15 23 አን. 4-5
አምላክን አይቶት የሚያውቅ አለ?
ከዚህ አንጻር አብርሃም የአምላክ ቃል አቀባይ ሆኖ የመጣውን ሥጋ የለበሰ መልአክ ይሖዋ ብሎ እየጠራ ያነጋገረው ለምን እንደሆነ መረዳት እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ይሖዋ ለአብርሃም ተገለጠለት’ ያለው ይህ መልአክ ይሖዋ ለአብርሃም ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልእክት በቀጥታ ስለተናገረ እንዲሁም ይሖዋን ወክሎ ስለመጣ ነው።—ዘፍ 18:1
ስልክ ወይም ሬዲዮ እኛ የምንናገራቸውን ቃላት በቀጥታ ለሌላ ሰው ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ ሁሉ የአምላክ ቃል አቀባይ ሆኖ የመጣ መልአክም የአምላክን መልእክት በቀጥታ ሊያስተላልፍ እንደሚችል ማስታወስ ይኖርብናል። አብርሃም፣ ሙሴ፣ ማኑሄና ሌሎች ሰዎች ሥጋ የለበሰን መልአክ ሲያነጋግሩ ልክ አምላክን እንዳነጋገሩ ሆኖ የተገለጸው በዚህ ምክንያት ነው። እነዚህ ሰዎች መላእክቱንና በመላእክቱ ላይ የተንጸባረቀውን የይሖዋን ክብር ማየት ቢችሉም አምላክን አላዩትም። በመሆኑም እንዲህ ያሉት ዘገባዎች “አምላክን ያየው አንድም ሰው የለም” ከሚለው ሐዋርያው ዮሐንስ ከተናገረው ሐሳብ ጋር ፈጽሞ አይጋጩም። (ዮሐንስ 1:18) እነዚህ ሰዎች ያዩት የአምላክ ወኪል የሆኑ መላእክትን እንጂ አምላክን ራሱን አይደለም።
(ዘፍጥረት 19:26) ሆኖም ከሎጥ በስተ ኋላ የነበረችው የሎጥ ሚስት ወደ ኋላ ዞራ መመልከት ጀመረች፤ እሷም የጨው ዓምድ ሆነች።
የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ያጋጠሟቸውን እርዷቸው
3 ሎጥ፣ አስጸያፊ ሥነ ምግባር ባላቸው የሰዶም ሰዎች መካከል ለመኖር ሲመርጥ የተሳሳተ ውሳኔ አድርጓል። (2 ጴጥሮስ 2:7, 8ን አንብብ።) አካባቢው ለም ቢሆንም ሎጥ ወደዚያ መሄዱ ከባድ መዘዝ አስከትሎበታል። (ዘፍ. 13:8-13፤ 14:12) ሚስቱ ከተማዋን ስለወደደቻት አሊያም በዚያ ከሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች ጋር በጣም ስለተቀራረበች ሳይሆን አይቀርም ይሖዋን መታዘዝ ከባድ ሆነባት። አምላክ በዚያ አካባቢ ላይ ከሰማይ እሳትና ድኝ ባዘነበበት ወቅት ሕይወቷን አጥታለች። ሁለቱ የሎጥ ሴቶች ልጆችስ? ሊያገቧቸው የነበሩት ወንዶች ከሰዶም ጋር አብረው ጠፉ። ሎጥ ቤቱን፣ ንብረቱን ከሁሉ የከፋው ደግሞ ሚስቱን አጥቷል። (ዘፍ. 19:12-14, 17, 26) ሎጥ አስጨናቂ ሁኔታ በገጠመው በዚህ ወቅት ይሖዋ በትዕግሥት ይዞታል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፍጥረት 18:1-19) ከዚያም አብርሃም በጣም ሞቃታማ በሆነው የቀኑ ክፍለ ጊዜ ድንኳኑ ደጃፍ ላይ ተቀምጦ ሳለ ይሖዋ በማምሬ ትላልቅ ዛፎች አጠገብ ተገለጠለት። 2 ቀና ብሎም ሲመለከት እሱ ካለበት ትንሽ ራቅ ብሎ ሦስት ሰዎች ቆመው አየ። ሰዎቹን ባያቸው ጊዜም ከድንኳኑ ደጃፍ ተነስቶ ወደ እነሱ እየሮጠ ሄደ፤ ወደ መሬት ዝቅ ብሎም ሰገደ። 3 ከዚያም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ፣ እንግዲህ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ እባክህ አገልጋይህን አልፈኸው አትሂድ። 4 እባካችሁ ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁና እግራችሁን ታጠቡ፤ ከዚያም ከዛፉ ሥር አረፍ በሉ። 5 ወደ አገልጋያችሁ ከመጣችሁ አይቀር፣ ብርታት እንድታገኙ ትንሽ እህል ላምጣላችሁና ቅመሱ፤ ከዚያም ጉዟችሁን ትቀጥላላችሁ።” በዚህ ጊዜ እነሱ “እሺ፣ እንዳልከው አድርግ” አሉት። 6 በመሆኑም አብርሃም ሣራ ወዳለችበት ወደ ድንኳኑ በፍጥነት ሄዶ “ቶሎ በይ! ሦስት መስፈሪያ የላመ ዱቄት ወስደሽ አቡኪና ቂጣ ጋግሪ” አላት። 7 በመቀጠልም አብርሃም ወደ መንጋው ሮጦ በመሄድ ሥጋው ገር የሆነ ፍርጥም ያለ ወይፈን መረጠ። ለአገልጋዩም ሰጠው፤ እሱም ለማዘጋጀት ተጣደፈ። 8 ከዚያም ቅቤና ወተት እንዲሁም ያዘጋጀውን ወይፈን ወስዶ ምግቡን አቀረበላቸው። እየበሉ ሳሉም ዛፉ ሥር አጠገባቸው ቆሞ ነበር። 9 እነሱም “ሚስትህ ሣራ የት አለች?” አሉት። እሱም “እዚህ ድንኳኑ ውስጥ ናት” አላቸው። 10 ከመካከላቸውም አንዱ ንግግሩን በመቀጠል “የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ በእርግጥ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች” አለ። በዚህ ጊዜ ሣራ ከሰውየው በስተ ጀርባ ባለው በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ሆና ታዳምጥ ነበር። 11 አብርሃምና ሣራ አርጅተው፣ ዕድሜያቸውም ገፍቶ ነበር። ሣራ ልጅ የመውለጃዋ ዕድሜ አልፎ ነበር። 12 በመሆኑም ሣራ “አሁን እንዲህ አርጅቼ ጌታዬም ዕድሜው ገፍቶ እያለ በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ደስታ ላገኝ እችላለሁ?” ብላ በማሰብ በልቧ ሳቀች። 13 ከዚያም ይሖዋ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ “ሣራ ‘እንዲህ ካረጀሁ በኋላም እንኳ ልወልድ ነው ማለት ነው?’ በማለት የሳቀችው ለምንድን ነው? 14 ለይሖዋ የሚሳነው ነገር አለ? የዛሬ ዓመት በዚሁ በተወሰነው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች።” 15 ሣራ ግን ስለፈራች “ኧረ አልሳቅኩም!” ስትል ካደች። በዚህ ጊዜ “እንዴ! ሳቅሽ እንጂ” አላት። 16 ሰዎቹም ለመሄድ በተነሱና ቁልቁል ወደ ሰዶም በተመለከቱ ጊዜ አብርሃም ሊሸኛቸው አብሯቸው ሄደ። 17 ይሖዋ እንዲህ አለ፦ “እኔ ላደርገው ያሰብኩትን ነገር ከአብርሃም ደብቄ አውቃለሁ? 18 አብርሃም በእርግጥ ታላቅና ኃያል ብሔር ይሆናል፤ የምድር ብሔራትም ሁሉ በእሱ አማካኝነት ይባረካሉ። 19 እኔ ከአብርሃም ጋር የተዋወቅኩት ትክክለኛና ተገቢ የሆነውን ነገር በማድረግ የይሖዋን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእሱ በኋላ የሚመጣውን ቤተሰቡን እንዲያዝዝ ነው፤ እንዲህ ካደረገ ይሖዋ አብርሃምን አስመልክቶ ቃል የገባውን ነገር ይፈጽምለታል።”
ከየካቲት 24–መጋቢት 1
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 20-21
“ይሖዋ ምንጊዜም የገባውን ቃል ይፈጽማል”
(ዘፍጥረት 21:1-3) ይሖዋ ልክ በተናገረው መሠረት ሣራን አሰባት፤ ይሖዋም ለሣራ ቃል የገባላትን አደረገላት። 2 በመሆኑም ሣራ ፀነሰች፤ ለአብርሃምም አምላክ ቃል በገባለት በተወሰነው ጊዜ ላይ በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወለደችለት። 3 አብርሃም ሣራ የወለደችለትን ልጅ ይስሐቅ ብሎ ጠራው።
አምላክ “ልዕልት” ብሎ ጠርቷታል
ሣራ መሳቋ እምነት እንደጎደላት የሚያሳይ ነበር? በጭራሽ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሣራም የተስፋን ቃል የሰጠው እሱ ታማኝ እንደሆነ አድርጋ ስላሰበች ዕድሜዋ ካለፈ በኋላም እንኳ ዘር ለመፀነስ በእምነት ኃይል አገኘች” ይላል። (ዕብራውያን 11:11) ሣራ ይሖዋን በደንብ ታውቀዋለች፤ የሰጠውን ማንኛውም ተስፋ መፈጸም እንደሚችልም እርግጠኛ ነች። ከእኛ መካከል እንዲህ ዓይነት እምነት የማያስፈልገው ማን አለ? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን አምላክ በደንብ ለማወቅ ልንጥር ይገባል። እንዲህ ካደረግን ሣራ በአምላክ ላይ እንደዚያ ዓይነት እምነት ማሳደሯ ተገቢ እንደነበር እንገነዘባለን። በእርግጥም ይሖዋ ታማኝ ስለሆነ የገባውን ቃል ሁሉ ይፈጽማል፤ አንዳንድ ጊዜ፣ የሰጠውን ተስፋ የሚፈጽምበት መንገድ በአግራሞት እንድንስቅ ሊያደርገን ይችላል!
“የምትልህን ስማ”
ሣራ ዕድሜዋን ሙሉ ስትመኘው የኖረችውን አስደሳች ነገር በ90 ዓመቷ አገኘች። በወቅቱ መቶ ዓመት ለሞላው ውድ ባለቤቷ ወንድ ልጅ ወለደችለት! አብርሃም፣ አምላክ በነገረው መሠረት ሕፃኑን ይስሐቅ ወይም “ሳቅ” ብሎ ጠራው። ሣራ በዕድሜ ምክንያት የተሸበሸበው ፊቷ በፈገግታ ተሞልቶ “አምላክ በደስታ እንድስቅ አድርጎኛል፤ ይህን የሰማም ሁሉ ከእኔ ጋር አብሮ ይስቃል” ብላ ስትናገር በዓይነ ሕሊናችን መሳል እንችላለን። (ዘፍጥረት 21:6) ሣራ ከይሖዋ ያገኘችው ይህ ተአምራዊ ስጦታ ቀሪ ሕይወቷን በደስታ እንድታሳልፍ እንዳደረጋት ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ስጦታው ትልቅ ኃላፊነትም አስከትሎባታል።
ይስሐቅ አምስት ዓመት ሲሆነው አብርሃም፣ ልጁ ጡት የጣለበትን ቀን ምክንያት በማድረግ ድግስ አዘጋጀ። ይሁን እንጂ ስጋት የሚፈጥር ነገር ነበር። ሣራ ‘በተደጋጋሚ ያስተዋለችው’ አንድ የሚያሳስብ ነገር ነበር። የአጋር ልጅ የሆነው የ19 ዓመቱ እስማኤል በትንሹ ይስሐቅ ላይ በተደጋጋሚ ያፌዝበት ነበር። እስማኤል ይህን ያደረገው እንዲሁ ለቀልድ ብሎ አልነበረም። ሐዋርያው ጳውሎስ ከጊዜ በኋላ በመንፈስ መሪነት እንደጻፈው እስማኤል በይስሐቅ ላይ ስደት አድርሶበታል። ሣራ ይህ አድራጎት ለልጇ ደህንነት ከባድ ስጋት የሚፈጥር እንደሆነ ገባት። ሣራ፣ ይስሐቅ ልጇ ከመሆኑም ባሻገር በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ታውቅ ነበር። ስለዚህ እንደምንም ራሷን አደፋፍራ አብርሃምን በግልጽ አነጋገረችው። አጋርንና እስማኤልን እንዲያባርራቸው ጠየቀችው።—ዘፍጥረት 21:8-10፤ ገላትያ 4:22, 23, 29
ታዲያ አብርሃም ምን ተሰማው? መጽሐፍ ቅዱስ “ሣራ ስለ ልጁ የተናገረችው ነገር በጣም ቅር አሰኘው” ይላል። አብርሃም እስማኤልን ይወደው ነበር፤ ለእስማኤል ያለው ፍቅር የተፈጠረውን ሁኔታ እንዳያስተውል አድርጎታል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ጉዳዩን በሚገባ ስለሚያውቅ ጣልቃ ገባ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ ‘ሣራ ስለ ልጁና ስለ ባሪያህ እየነገረችህ ያለው ነገር ምንም ቅር አያሰኝህ። ዘርህ የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ስለሆነ የምትልህን ስማ።’” ይሖዋ ለአጋርና ለልጁ አስፈላጊው እንክብካቤ እንደሚያደርግላቸው ለአብርሃም አረጋገጠለት። ታማኙ አብርሃምም የታዘዘውን አደረገ።—ዘፍጥረት 21:11-14
(ዘፍጥረት 21:5-7) አብርሃም ልጁ ይስሐቅ ሲወለድ ዕድሜው 100 ዓመት ነበር። 6 ከዚያም ሣራ “አምላክ በደስታ እንድስቅ አድርጎኛል፤ ይህን የሰማም ሁሉ ከእኔ ጋር አብሮ ይስቃል” አለች። 7 አክላም “ለመሆኑ ለአብርሃም ‘ሣራ ልጆች ታጠባለች’ ማን ብሎት ያውቃል? እኔ ግን ይኸው በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወለድኩለት” አለች።
(ዘፍጥረት 21:10-12) ስለዚህ አብርሃምን “ይህችን ባሪያና ልጇን ከዚህ አባር፤ ምክንያቱም የዚህች ባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር ወራሽ አይሆንም!” አለችው። 11 አብርሃም ግን ሣራ ስለ ልጁ የተናገረችው ነገር በጣም ቅር አሰኘው። 12 ከዚያም አምላክ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ “ሣራ ስለ ልጁና ስለ ባሪያህ እየነገረችህ ያለው ነገር ምንም ቅር አያሰኝህ። ዘርህ የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ስለሆነ የምትልህን ስማ።
(ዘፍጥረት 21:14) ስለዚህ አብርሃም በማለዳ ተነሳ፤ ለአጋርም ምግብና የውኃ አቁማዳ ሰጣት። እነዚህንም በትከሻዋ አሸከማት፤ ከዚያም ከልጁ ጋር አሰናበታት። እሷም ሄደች፤ በቤርሳቤህ ምድረ በዳም ትንከራተት ጀመር።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 20:12) ደግሞም እኮ በእርግጥ እህቴ ናት፤ የእናቴ ልጅ ባትሆንም የአባቴ ልጅ ናት፤ እሷም ሚስቴ ሆነች።
wp17.3 12 ግርጌ
“አንቺ በጣም ውብ ሴት ነሽ”
ሣራ ለአብርሃም ግማሽ እህቱ ነበረች። ሁለቱም የታራ ልጆች ነበሩ፤ ሆኖም የአንድ እናት ልጆች አልነበሩም። (ዘፍጥረት 20:12) በዛሬው ጊዜ እንዲህ ያሉ የቅርብ ዘመዳሞች መጋባታቸው ተገቢ አይደለም፤ ነገር ግን በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ከአሁኑ ይለይ እንደነበር ማስታወስ ያስፈልጋል። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ እነሱም ሆኑ ዘሮቻቸው ፍጽምናን ያጡ ቢሆንም በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ከአሁኑ በተሻለ ለፍጽምና የቀረቡ ነበሩ። ሰዎች ጠንካራና ጤናማ ስለነበሩ የቅርብ ዘመዳሞች ቢጋቡም እንኳ ልጆቹ በዚህ ምክንያት የሚመጣ የጤና ችግር አይገጥማቸውም ነበር። ከ400 ዓመታት ገደማ በኋላ ግን የሰዎች የዕድሜ ርዝማኔ በእኛ ዘመን ካሉ ሰዎች ዕድሜ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ነበር። በዚያ ጊዜ የሙሴ ሕግ የቅርብ ዘመዳሞች የፆታ ግንኙነት መፈጸም እንደሌለባቸው ደነገገ።—ዘሌዋውያን 18:6
(ዘፍጥረት 21:33) ከዚያም በኋላ አብርሃም በቤርሳቤህ የታማሪስክ ዛፍ ተከለ፤ በዚያም የዘላለማዊውን አምላክ የይሖዋን ስም ጠራ።
w89 7/1 12 አን. 9
አብርሃም—ከአምላክ ጋር ወዳጅነት ለሚፈልጉት ሁሉ ምሳሌ የሚሆነው ሰው
9 አብራም ለዚህ ምላሽ ሌላ የእምነት መግለጫ የሆነ ድርጊት ፈጽሟል። ታሪኩ እንደሚገልጸው፦ “[ለይሖዋ] በዚያ ስፍራ መሠዊያን ሠራ።” (ዘፍጥረት 12:7) “መሠዊያ” ለሚለው የገባው የዕብራይስጥ ቃል “የመሥዋዕት ማቅረቢያ ቦታ” ማለት ስለሆነ ድርጊቱ የእንስሳት መሥዋዕት ማቅረብን ሳይጨምር አይቀርም። ከዚያ ቆየት ብሎም አብራም እነዚህን የእምነት መግለጫ የሆኑ ሥራዎች በሌሎች የምድሪቱ ክፍሎች ውስጥ ደግሞአቸዋል። በተጨማሪም ‘የይሖዋን ስም ጠርቷል።’ (ዘፍጥረት 12:8፤ 13:18፤ 21:33) “ስም መጥራት” የሚለው የዕብራይስጥ ዐረፍተ ነገር “ስምን ማወጅ (መስበክ)” ማለትም ነው። የአብራም ቤተሰብ እንደዚሁም ከነዓናውያን የአምላኩን የይሖዋን ስም በድፍረት ሲያውጅ ሰምተውት መሆን ይኖርበታል። (ዘፍጥረት 14:22-24) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የአምላክ ወዳጅ ለመሆን የሚፈልጉት ሁሉ ስሙን በእምነት መጥራት ያስፈልጋቸዋል። ይህም “ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ማለትም ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ” በማቅረብ ለሕዝብ በሚደረገው ስብከት መሳተፍን ይጨምራል።—ዕብራውያን 13:15፤ ሮም 10:10
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፍጥረት 20:1-18) አብርሃም ድንኳኑን ከዚያ ነቅሎ ወደ ኔጌብ ምድር ሄደ፤ በቃዴስና በሹር መካከልም መኖር ጀመረ። በጌራራ እየኖረ ሳለ 2 በድጋሚ ሚስቱን ሣራን “እህቴ ናት” አለ። በመሆኑም የጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክ ሰዎችን ልኮ ሣራን አስመጣት፤ ከዚያም ወሰዳት። 3 ከዚያም አምላክ ለአቢሜሌክ ሌሊት በሕልም ተገልጦለት “በወሰድካት ሴት የተነሳ ትሞታለህ፤ ምክንያቱም እሷ ያገባችና ባለቤት ያላት ሴት ናት” አለው። 4 ሆኖም አቢሜሌክ ወደ እሷ አልቀረበም ነበር። በመሆኑም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ፣ ምንም በደል ያልፈጸመን ብሔር ታጠፋለህ? 5 እሱ ‘እህቴ ናት’ አላለኝም? እሷስ ብትሆን ‘ወንድሜ ነው’ አላለችም? ይህን ያደረግኩት በቅን ልቦናና በንጹሕ እጅ ነው።” 6 ከዚያም እውነተኛው አምላክ በሕልም ተገልጦለት እንዲህ አለው፦ “ይህን ያደረግከው በቅን ልቦና ተነሳስተህ እንደሆነ አውቃለሁ፤ በእኔም ላይ ኃጢአት እንዳትሠራ ጠብቄሃለሁ። እንድትነካት ያልፈቀድኩልህም ለዚህ ነው። 7 በል አሁን የሰውየውን ሚስት መልስ፤ እሱ ነቢይ ነውና፤ ስለ አንተም ልመና ያቀርባል፤ አንተም በሕይወት ትኖራለህ። እሷን ባትመልስ ግን በእርግጥ እንደምትሞት እወቅ፤ አንተም ሆንክ የአንተ የሆነው ሁሉ ትሞታላችሁ።” 8 አቢሜሌክ በማለዳ ተነሳ፤ አገልጋዮቹንም በሙሉ ጠርቶ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፤ እነሱም በጣም ፈሩ። 9 ከዚያም አቢሜሌክ አብርሃምን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ይህ ያደረግክብን ነገር ምንድን ነው? በእኔም ሆነ በግዛቴ ላይ እንዲህ ያለውን ታላቅ ኃጢአት ያመጣህብን ለመሆኑ ምን በድዬህ ነው? ያደረግክብኝ ነገር ትክክል አይደለም።” 10 በመቀጠልም አቢሜሌክ አብርሃምን “ለመሆኑ ይህን ያደረግከው ምን አስበህ ነው?” አለው። 11 አብርሃምም እንዲህ አለው፦ “ይህን ያደረግኩት ‘በዚህ ስፍራ እንደሆነ ፈሪሃ አምላክ የሚባል ነገር የለም፤ ሰዎቹ ለሚስቴ ሲሉ ሊገድሉኝ ይችላሉ’ ብዬ ስለሰጋሁ ነው። 12 ደግሞም እኮ በእርግጥ እህቴ ናት፤ የእናቴ ልጅ ባትሆንም የአባቴ ልጅ ናት፤ እሷም ሚስቴ ሆነች። 13 በመሆኑም አምላክ ከአባቴ ቤት ወጥቼ ከአገር አገር እየዞርኩ እንድኖር በነገረኝ ጊዜ ‘በምንሄድበት ስፍራ ሁሉ “ወንድሜ ነው” ብለሽ በመናገር ታማኝ ፍቅር አሳዪኝ’ ብያት ነበር።” 14 ከዚያም አቢሜሌክ በጎችን፣ ከብቶችን እንዲሁም ወንድና ሴት አገልጋዮችን ለአብርሃም ሰጠው፤ ሚስቱን ሣራንም መለሰለት። 15 በተጨማሪም አቢሜሌክ “አገሬ አገርህ ናት፤ ደስ ባለህ ቦታ መኖር ትችላለህ” አለው። 16 ሣራንም እንዲህ አላት፦ “ይኸው ለወንድምሽ 1,000 የብር ሰቅል እሰጠዋለሁ። ይህም አንቺ ንጹሕ ሰው መሆንሽን ከአንቺ ጋር ባሉት ሰዎች ሁሉ ፊትም ሆነ በሌሎች ሰዎች ፊት የሚያሳውቅ ምልክት ነው፤ አንቺም ከማንኛውም ነቀፋ ነፃ ነሽ።” 17 አብርሃምም ወደ እውነተኛው አምላክ ልመና አቀረበ፤ አምላክም አቢሜሌክን፣ ሚስቱንና ሴት ባሪያዎቹን ፈወሳቸው፤ እነሱም ልጆች መውለድ ጀመሩ፤ 18 ምክንያቱም ይሖዋ በአብርሃም ሚስት በሣራ የተነሳ በአቢሜሌክ ቤት ያሉትን ሴቶች ሁሉ መሃን አድርጎ ነበር።