የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ሰኔ 2020
ከሰኔ 1-7
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 44–45
“ዮሴፍ ወንድሞቹን ይቅር አላቸው”
(ዘፍጥረት 44:1, 2) ከዚህ በኋላ ዮሴፍ የቤቱ ኃላፊ የሆነውን ሰው እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “የቻሉትን ያህል እህል በየከረጢቶቻቸው ሙላላቸው፤ የእያንዳንዳቸውንም ገንዘብ በየከረጢቶቻቸው አፍ ላይ አድርገው። 2 ሆኖም የእኔን ጽዋ ይኸውም የብር ጽዋዬን ውሰድና እህል ለመግዛት ካመጣው ገንዘብ ጋር አድርገህ በትንሹ ወንድማቸው ከረጢት አፍ ላይ አድርገው።” እሱም ልክ ዮሴፍ እንዳዘዘው አደረገ።
“እኔን በአምላክ ቦታ ያስቀመጠኝ ማን ነው?”
በዚህ መንገድ ዮሴፍ ወጥመዱን ዘረጋ። ከዚያም ወንድሞቹን ተከታትሎ እንዲደርስባቸው፣ እንዲይዛቸውና ጽዋውን ሰርቃችኋል ብሎ እንዲወነጅላቸው የቤቱን ኃላፊ አዘዘው። ጽዋው በቢንያም ከረጢት ውስጥ ሲገኝ ሁሉም ወደ ዮሴፍ ተመለሱ። አሁን ዮሴፍ ወንድሞቹ ምን ያህል እንደተለወጡ ለማየት የሚያስችል አጋጣሚ አገኘ። ይሁዳ ወንድሞቹን ወክሎ መናገርና የዮሴፍን ምሕረት መለመን ጀመረ። እንዲያውም “[ሁላችንም] ባሪያዎች እንሆናለን” በማለት ተናገረ። ዮሴፍ ግን ግብፅ ውስጥ ባሪያ ሆኖ የሚቀረው ቢንያም ብቻ እንደሆነና ሌሎቹ መሄድ እንደሚችሉ ተናገረ።—ዘፍጥረት 44:2-17
በዚህ ጊዜ ይሁዳ ከልብ በመነጨ ስሜት “ከአንድ እናት ከተወለዱት መካከል የቀረው እሱ ብቻ ነው፤ አባቱም በጣም ይወደዋል” በማለት ተናገረ። እነዚህ ቃላት የዮሴፍን ልብ በጥልቅ ነክተውት መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ያዕቆብ ከሚወዳት ሚስቱ ከራሔል የወለደው የመጀመሪያ ልጅ እሱ ነው። ራሔል የሞተችው ቢንያምን ስትወልድ ነበር። እንደ አባቱ ሁሉ ዮሴፍም ስለ ራሔል ብዙ ትዝታዎች እንዳሉት ግልጽ ነው። ምናልባትም ዮሴፍ ቢንያምን ከሌሎቹ ወንድሞቹ አስበልጦ የሚወደው በመካከላቸው ባለው በዚህ ዝምድና የተነሳ ሳይሆን አይቀርም።—ዘፍጥረት 35:18-20፤ 44:20
ይሁዳ፣ ዮሴፍ ቢንያምን ባሪያ አድርጎ እንዳያስቀረው ይማጸን ጀመር። አልፎ ተርፎም በቢንያም ምትክ ባሪያ ለመሆን ሐሳብ አቀረበ። ከዚያም የሚከተለውን ስሜት የሚነካ ሐሳብ በመናገር ደመደመ፦ “ልጁን ሳልይዝ እንዴት ወደ አባቴ እመለሳለሁ? በአባቴ ላይ እንዲህ ያለ መከራ ሲደርስ ማየት አልችልም!” (ዘፍጥረት 44:18-34) ይሁዳ ምን ያህል እንደተለወጠ ከተናገረው ነገር መረዳት ይቻላል። ይሁዳ ከልቡ ንስሐ እንደገባ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ስሜት እንደሚያስብ፣ ሩኅሩኅ እንደሆነና ለራሱ ጥቅም እንደማይጨነቅ አሳይቷል።
ዮሴፍ ከዚህ በላይ ስሜቱን መቆጣጠር አልቻለም። በውስጡ ያመቀውን ስሜት ለማውጣት ተገደደ። አገልጋዮቹን ሁሉ ካስወጣ በኋላ ድምፁ በፈርዖን ቤተ መንግሥት እስኪሰማ ድረስ ጮኾ አለቀሰ። በመጨረሻም “እኔ . . . ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ” በማለት ማንነቱን ገለጠላቸው። ዮሴፍ በድንጋጤ ክው ብለው የቀሩትን ወንድሞቹን ያቀፋቸው ሲሆን የበደሉትን በደል ሁሉ በደግነት ይቅር አላቸው። (ዘፍጥረት 45:1-15) በዚህ መንገድ ዮሴፍ በልግስና የሚምረውን የይሖዋን ባሕርይ አንጸባርቋል። (መዝሙር 86:5) እኛስ እንዲህ እናደርጋለን?
(ዘፍጥረት 44:33, 34) ስለዚህ እባክህ ልጁ ከወንድሞቹ ጋር እንዲሄድ እኔ ባሪያህ በልጁ ፋንታ እዚሁ ቀርቼ ለጌታዬ ባሪያ ልሁን። 34 ልጁን ሳልይዝ እንዴት ወደ አባቴ እመለሳለሁ? በአባቴ ላይ እንዲህ ያለ መከራ ሲደርስ ማየት አልችልም!”
(ዘፍጥረት 45:4, 5) ስለሆነም ዮሴፍ ወንድሞቹን “እባካችሁ ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው። እነሱም ወደ እሱ ቀረቡ። ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። 5 አሁን ግን እኔን ወደዚህ በመሸጣችሁ አትዘኑ፤ እርስ በርሳችሁም አትወቃቀሱ፤ ምክንያቱም አምላክ ከእናንተ አስቀድሞ የላከኝ ሕይወት ለማዳን ሲል ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 44:13) በዚህ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ እያንዳንዳቸውም ጓዛቸውን መልሰው በአህዮቻቸው ላይ በመጫን ወደ ከተማዋ ተመለሱ።
it-2 813
ልብስ መቅደድ
በአይሁዳውያን እና በሌሎች የምሥራቅ ሰዎች ዘንድ በተለይ የቅርብ ዘመድ ሲሞት ሐዘንን ለመግለጽ ልብስን መቅደድ የተለመደ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ልብሳቸውን የሚቀድዱት ደረታቸው እስኪገለጥ ድረስ ብቻ እንጂ ልብሱ ሙሉ በሙሉ ተቀድዶ መለበስ እስከማይችል ድረስ አልነበረም።
ይህ ልማድ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው የያዕቆብ የመጀመሪያ ልጅ ከሆነው ከሮቤል ጋር ተያይዞ ነው፤ ሮቤል ወደ ውኃ ጉድጓዱ ተመልሶ ዮሴፍን በዚያ ሲያጣው ልብሱን በመቅደድ “ልጁ የለም! እንግዲህ ምንድን ነው የማደርገው?” አለ። ሮቤል የመጀመሪያ ልጅ እንደመሆኑ መጠን ታናሽ ወንድሙን የመጠበቅ ኃላፊነት በዋነኝነት የወደቀው በእሱ ላይ ነበር። አባቱ ያዕቆብም ልጁ እንደሞተ ሲነገረው ልብሱን የቀደደ ከመሆኑም ሌላ በሐዘን ማቅ ለብሷል (ዘፍ 37:29, 30, 34)፤ በኋላም ግብፅ ውስጥ የዮሴፍ ወንድሞች ቢንያም እንደ ሌባ መቆጠሩን ሲመለከቱ ልብሳቸውን በመቅደድ ሐዘናቸውን ገልጸዋል።—ዘፍ 44:13
(ዘፍጥረት 45:5-8) አሁን ግን እኔን ወደዚህ በመሸጣችሁ አትዘኑ፤ እርስ በርሳችሁም አትወቃቀሱ፤ ምክንያቱም አምላክ ከእናንተ አስቀድሞ የላከኝ ሕይወት ለማዳን ሲል ነው። 6 ረሃቡ በምድር ላይ ከጀመረ ይህ ሁለተኛ ዓመቱ ነው፤ ምንም የማይታረስባቸውና አዝመራ የማይሰበሰብባቸው አምስት ዓመታት ገና ይቀራሉ። 7 አምላክ ግን በምድር ላይ ዘራችሁን ሊያስቀርና በታላቅ ማዳን ሕይወታችሁን ሊታደግ ከእናንተ አስቀድሞ ላከኝ። 8 ስለዚህ ለፈርዖን ዋና አማካሪ፣ በቤቱም ሁሉ ላይ ጌታ እንዲሁም በመላው የግብፅ ምድር ላይ ገዢ ሊያደርገኝ ወደዚህ የላከኝ እውነተኛው አምላክ እንጂ እናንተ አይደላችሁም።
ያለ ምክንያት መጠላት
15 ያለ ምክንያት በሚጠሉን ሰዎች እንዳንመረር ምን ሊረዳን ይችላል? ቀንደኞቹ ጠላቶቻችን ሰይጣንና አጋንንቱ መሆናቸውን አትዘንጉ። (ኤፌሶን 6:12) አንዳንድ ሰዎች አውቀውና ሆነ ብለው የሚያሳድዱን ቢሆንም የአምላክን ሕዝቦች ከሚቃወሙት መካከል ብዙዎቹ ይህን የሚያደርጉት ካለማወቅ ወይም በሌሎች ግፊት ነው። (ዳንኤል 6:4-16፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:12, 13) ይሖዋ ‘ሰዎች ሁሉ የሚድኑበትና እውነትን የሚሰሙበት’ አጋጣሚ እንዲያገኙ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) እንዲያውም ቀድሞ ተቃዋሚዎች የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንከን የማይወጣለትን ምግባራችንን ተመልክተው የእምነት ወንድሞቻችን ሆነዋል። (1 ጴጥሮስ 2:12) በተጨማሪም ከያዕቆብ ልጅ ከዮሴፍ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን። ዮሴፍ በወንድሞቹ ምክንያት ብዙ መከራ ቢደርስበትም ለእነርሱ የጥላቻ ስሜት አላደረበትም። ለምን? ምክንያቱም በጉዳዩ ውስጥ የይሖዋ እጅ እንዳለበትና ዓላማውን በዚህ መንገድ ሊያስፈጽም እንዳሰበ ተገንዝቦ ስለነበር ነው። (ዘፍጥረት 45:4-8) በተመሳሳይ ይሖዋ የሚደርስብንን ማንኛውንም ተገቢ ያልሆነ ሥቃይ ለስሙ ክብር የሚያመጣ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል።—1 ጴጥሮስ 4:16
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፍጥረት 45:1-15) በዚህ ጊዜ ዮሴፍ አጠገቡ በነበሩት አገልጋዮቹ ፊት ስሜቱን መቆጣጠር አልቻለም። በመሆኑም “ሁሉንም ሰው አስወጡልኝ!” በማለት ጮኸ። ዮሴፍ ራሱን ለወንድሞቹ በገለጠበት ወቅት ከእሱ ጋር ማንም ሰው አልነበረም። 2 ከዚያም ጮክ ብሎ ማልቀስ ጀመረ፤ ግብፃውያንም ሰሙት፤ በፈርዖንም ቤት ተሰማ። 3 በመጨረሻም ዮሴፍ ወንድሞቹን “እኔ ዮሴፍ ነኝ። አባቴ እስካሁን በሕይወት አለ?” አላቸው። ወንድሞቹ ግን በሁኔታው በጣም ስለደነገጡ ምንም ሊመልሱለት አልቻሉም። 4 ስለሆነም ዮሴፍ ወንድሞቹን “እባካችሁ ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው። እነሱም ወደ እሱ ቀረቡ። ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። 5 አሁን ግን እኔን ወደዚህ በመሸጣችሁ አትዘኑ፤ እርስ በርሳችሁም አትወቃቀሱ፤ ምክንያቱም አምላክ ከእናንተ አስቀድሞ የላከኝ ሕይወት ለማዳን ሲል ነው። 6 ረሃቡ በምድር ላይ ከጀመረ ይህ ሁለተኛ ዓመቱ ነው፤ ምንም የማይታረስባቸውና አዝመራ የማይሰበሰብባቸው አምስት ዓመታት ገና ይቀራሉ። 7 አምላክ ግን በምድር ላይ ዘራችሁን ሊያስቀርና በታላቅ ማዳን ሕይወታችሁን ሊታደግ ከእናንተ አስቀድሞ ላከኝ። 8 ስለዚህ ለፈርዖን ዋና አማካሪ፣ በቤቱም ሁሉ ላይ ጌታ እንዲሁም በመላው የግብፅ ምድር ላይ ገዢ ሊያደርገኝ ወደዚህ የላከኝ እውነተኛው አምላክ እንጂ እናንተ አይደላችሁም። 9 “ቶሎ ብላችሁ ወደ አባቴ ሂዱና እንዲህ በሉት፦ ‘ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ በመላው ግብፅ ላይ ጌታ አድርጎኛል። ሳትዘገይ ወደ እኔ ና። 10 ወንዶች ልጆችህን፣ የልጅ ልጆችህን፣ መንጎችህን፣ ከብቶችህንና ያለህን ነገር በሙሉ ይዘህ በመምጣት በአቅራቢያዬ በጎሸን ምድር ትኖራለህ። 11 ረሃቡ ገና ለአምስት ዓመታት ስለሚቀጥል እኔ የሚያስፈልግህን ምግብ እሰጥሃለሁ። አለዚያ አንተም ሆንክ ቤትህ እንዲሁም የአንተ የሆነው ሁሉ ችግር ላይ ትወድቃላችሁ።”’ 12 እንግዲህ አሁን እያናገርኳችሁ ያለሁት እኔው ራሴ መሆኔን እናንተም ሆናችሁ ወንድሜ ቢንያም በገዛ ዓይናችሁ አይታችኋል። 13 በመሆኑም በግብፅ ስላለኝ ክብር ሁሉ እንዲሁም ስላያችሁት ስለ ማንኛውም ነገር ለአባቴ ንገሩት። አሁንም በፍጥነት ሄዳችሁ አባቴን ወደዚህ ይዛችሁት ኑ።” 14 ከዚያም በወንድሙ በቢንያም አንገት ላይ ተጠምጥሞ አለቀሰ፤ ቢንያምም አንገቱን አቅፎት አለቀሰ። 15 የቀሩትን ወንድሞቹንም አንድ በአንድ እየሳመ አለቀሰ፤ ከዚህ በኋላም ወንድሞቹ ከእሱ ጋር ማውራት ጀመሩ።
ከሰኔ 8-14
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 46–47
“በረሃብ ወቅት ምግብ ማግኘት”
(ዘፍጥረት 47:13) በዚህ ወቅት ረሃቡ እጅግ በርትቶ ስለነበር በመላው ምድር እህል አልነበረም፤ የግብፅም ምድር ሆነ የከነአን ምድር በረሃቡ የተነሳ በጣም ተጎድተው ነበር።
w87 5/1 15 አን. 2
በረሐብ ጊዜ ሕይወት ማዳን
2 ሰባቱ የጥጋብ ዓመታት ተፈጸሙ፤ ይሖዋም አስቀድሞ እንደተናገረው በግብጽ ላይ ብቻ ሳይሆን “በምድር ሁሉ ላይ ራብ ሆነ።” የተራበው የግብጽ ሕዝብ ወደ ፈርዖን እየመጣ እንጀራ ስጠን እያለ መጮኽ ጀመረ። ፈርዖንም “ወደ ዮሴፍ ሂዱ፣ እርሱ ያላችሁንም ሁሉ አድርጉ አላቸው።” ግብጻውያን ገንዘባቸው ሁሉ ተሟጦ እስኪያልቅ ድረስ ዮሴፍ እህል ይሸጥላቸው ነበር። በኋላም በእህሉ ልዋጭ ከብቶቻቸውን መቀበል ጀመረ። በመጨረሻውም ሕዝቡ ወደ ዮሴፍ መጥተው “እኛንም ምድራችንንም በእህል ግዛን፣ እኛም ለፈርዖን ባሪያዎች እንሁን” አሉት። ስለዚህ ዮሴፍ የግብጻውያንን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛው።—ዘፍጥረት 41:53-57፤ 47:13-20
(ዘፍጥረት 47:16) ዮሴፍም “ገንዘባችሁ ካለቀ ከብቶቻችሁን አምጡ፤ እኔም በከብቶቻችሁ ምትክ እህል እሰጣችኋለሁ” አላቸው።
(ዘፍጥረት 47:19, 20) ዓይንህ እያየ ለምን እንለቅ? መሬታችንስ ለምን ጠፍ ሆኖ ይቅር? እኛንም ሆነ መሬታችንን በእህል ግዛን፤ እኛ ለፈርዖን ባሪያዎች እንሁን፤ መሬታችንም የእሱ ይሁን። በሕይወት እንድንኖርና እንዳንሞት እንዲሁም መሬታችን ጠፍ ሆኖ እንዳይቀር የምንዘራው እህል ስጠን።” 20 በመሆኑም ዮሴፍ የግብፃውያንን መሬት በሙሉ ለፈርዖን ገዛለት፤ ምክንያቱም ረሃቡ እጅግ ስለበረታባቸው ሁሉም ግብፃውያን መሬታቸውን ሸጠው ነበር፤ ስለዚህ ምድሪቱ የፈርዖን ሆነች።
(ዘፍጥረት 47:23-25) ከዚያም ዮሴፍ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “ይኸው ዛሬ እናንተንም ሆነ መሬታችሁን ለፈርዖን ገዝቻለሁ። ዘር ይኸውላችሁ፤ እናንተም በመሬቱ ላይ ዝሩ። 24 ባፈራም ጊዜ አንድ አምስተኛውን ለፈርዖን ስጡ፤ አራቱ እጅ ግን ለመሬታችሁ ዘር እንዲሁም ለራሳችሁ፣ በቤታችሁ ላሉትና ለልጆቻችሁ ምግብ እንዲሆናችሁ የእናንተ ይሆናል።” 25 እነሱም “አንተ ሕይወታችንን አትርፈህልናል፤ በጌታዬ ፊት ሞገስ እናግኝ እንጂ እኛ ለፈርዖን ባሪያዎች እንሆናለን” አሉት።
መንግሥቱ የአምላክ ፈቃድ በምድር እንዲፈጸም ያደርጋል
11 ሁሉ ነገር ይትረፈረፋል። ዓለም በመንፈሳዊ ረሃብ እየተሠቃየ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፦ “‘እነሆ፣ በምድሪቱ ላይ ረሃብ የምሰድበት ጊዜ ይመጣል’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፤ ‘ረሃቡ የይሖዋን ቃል የመስማት ረሃብ እንጂ ምግብን የመራብ ወይም ውኃን የመጠማት አይደለም።’” (አሞጽ 8:11) የአምላክ መንግሥት ዜጎችስ ተመሳሳይ ረሃብ አጋጥሟቸው ይሆን? ይሖዋ፣ በሕዝቡና በጠላቶቹ መካከል የሚኖረውን ልዩነት ለመግለጽ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል፦ “እነሆ፣ አገልጋዮቼ ይበላሉ፤ እናንተ ግን ትራባላችሁ። እነሆ፣ አገልጋዮቼ ይጠጣሉ፤ እናንተ ግን ትጠማላችሁ። እነሆ፣ አገልጋዮቼ ሐሴት ያደርጋሉ፤ እናንተ ግን ኀፍረት ትከናነባላችሁ።” (ኢሳ. 65:13) አንተስ እነዚህ ቃላት ሲፈጸሙ ተመልክተሃል?
12 መንፈሳዊ ምግብ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና ጥልቀቱ እየጨመረ እንደሚሄድ ወንዝ በተትረፈረፈ ሁኔታ እየቀረበልን ነው። በመንፈሳዊ ረሃብ በተጠቃው በዚህ ዓለም ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱት ጽሑፎቻችን እንዲሁም በቪዲዮዎችና በድምፅ በተቀረጹ ነገሮች፣ በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎቻችን ብሎም በድረ ገጻችን አማካኝነት መንፈሳዊ ምግብ ምንጊዜም እንደማይቋረጥ ኃይለኛ ጅረት እየጎረፈልን ነው። (ሕዝ. 47:1-12፤ ኢዩ. 3:18) ይሖዋ የተትረፈረፈ ነገር እንደሚሰጠን የገባው ቃል በሕይወትህ ውስጥ በየዕለቱ ሲፈጸም በማየትህ አትደሰትም? ታዲያ በየዕለቱ ከይሖዋ ማዕድ ትመገባለህ?
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 46:4) እኔ ራሴ ከአንተ ጋር ወደ ግብፅ እወርዳለሁ፤ ደግሞም እኔ ራሴ ከዚያ አወጣሃለሁ፤ ዮሴፍም ዓይኖችህን በእጁ ይከድናል።”
it-1 220 አን. 1
ባሕርያት እና አካላዊ መግለጫዎች
የሟችን ዓይን በእጅ መክደን። ይሖዋ ለያዕቆብ “ዮሴፍም ዓይኖችህን በእጁ ይከድናል” ሲለው (ዘፍ 46:4) ያዕቆብ ከሞተ በኋላ ዮሴፍ ዓይኑን እንደሚከድነው መግለጹ ነበር፤ ይህ ድርጊት ደግሞ በአብዛኛው የበኩር ልጅ ኃላፊነት ነበር። በመሆኑም እዚህ ላይ ይሖዋ የብኩርና መብት ለዮሴፍ መሰጠት እንዳለበት ለያዕቆብ እያመላከተው ይመስላል።—1ዜና 5:2
(ዘፍጥረት 46:26, 27) የያዕቆብ ዝርያዎች የሆኑትና ከእሱ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት ሰዎች፣ የልጆቹን ሚስቶች ሳይጨምር በአጠቃላይ 66 ነበሩ። 27 ዮሴፍ በግብፅ የወለዳቸው ወንዶች ልጆች ሁለት ነበሩ። ወደ ግብፅ የገቡት የያዕቆብ ቤተሰቦች በአጠቃላይ 70 ነበሩ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሥራ 7:14
በአጠቃላይ 75 ሰዎች፦ እስጢፋኖስ በግብፅ የነበሩት የያዕቆብ ቤተሰቦች በአጠቃላይ 75 እንደነበሩ የተናገረው በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያለን አንድ ጥቅስ ጠቅሶ ላይሆን ይችላል። ይህ አኃዝ ማሶሬቶች ባዘጋጁት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ አይገኝም። ዘፍ 46:26 “የያዕቆብ ዝርያዎች የሆኑትና ከእሱ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት ሰዎች፣ የልጆቹን ሚስቶች ሳይጨምር በአጠቃላይ 66 ነበሩ” ይላል። ቁጥር 27 ደግሞ “ወደ ግብፅ የገቡት የያዕቆብ ቤተሰቦች በአጠቃላይ 70 ነበሩ” ይላል። እዚህ ላይ ሰዎቹ የተቆጠሩት በሁለት መንገድ ነው፤ በመጀመሪያው አኃዝ ላይ የተቆጠሩት በሥጋ የያዕቆብ ዘር የሆኑ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም፤ ሁለተኛው አኃዝ ደግሞ ወደ ግብፅ የገቡትን ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር ይገልጻል። የያዕቆብ ዘሮች ቁጥር በዘፀ 1:5 እና በዘዳ 10:22 ላይም የተጠቀሰ ሲሆን በሁለቱም ጥቅሶች ላይ የሚገኘው አኃዝ “70” ነው። እስጢፋኖስ የጠቀሰው ሦስተኛ አኃዝ ግን የያዕቆብን ሌሎች ዘመዶችም የሚያካትት ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች ይህ አኃዝ የዮሴፍ ልጆች የሆኑትን የምናሴንና የኤፍሬምን ልጆችና የልጅ ልጆች እንደሚያካትት ይናገራሉ፤ የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ዘፍ 46:20 ላይ እነዚህን ሰዎች ይጠቅሳል። ሌሎች ደግሞ በዘፍ 46:26 ላይ በሚገኘው አኃዝ ውስጥ ያልተካተቱትን የያዕቆብ ልጆች ሚስቶች እንደሚጨምር ይገልጻሉ። ስለዚህ “75” የሚለው አኃዝ ጠቅላላ ድምር ሊሆን ይችላል። ይሁንና ይህ አኃዝ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ጥቅም ላይ ይውሉ በነበሩ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ላይ የተመሠረተ ሊሆንም ይችላል። ምሁራን ለበርካታ ዓመታት “75” የሚለው አኃዝ በግሪክኛው ሰብዓ ሊቃናት ዘፍ 46:27 እና ዘፀ 1:5 ላይ እንደሚገኝ ያውቁ ነበር። በተጨማሪም በ20ኛው መቶ ዘመን ዘፀ 1:5ን በዕብራይስጥ የያዙ የሙት ባሕር ጥቅልል ሁለት ቁራጮች የተገኙ ሲሆን እነሱም “75” የሚለውን አኃዝ ይዘዋል። እስጢፋኖስ የጠቀሰው አኃዝ እንደነዚህ ባሉ ጥንታዊ ቅጂዎች ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ እስጢፋኖስ የጠቀሰው አኃዝ የያዕቆብን ዘሮች አጠቃላይ ብዛት በሌላ አቆጣጠር የሚያስቀምጥ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፍጥረት 47:1-17) ስለዚህ ዮሴፍ ወደ ፈርዖን ሄዶ “አባቴና ወንድሞቼ እንዲሁም መንጎቻቸው፣ ከብቶቻቸውና የእነሱ የሆነው ሁሉ ከከነአን ምድር መጥተዋል፤ በጎሸን ምድር ይገኛሉ” አለው። 2 እሱም ከወንድሞቹ መካከል አምስቱን ወስዶ ፈርዖን ፊት አቀረባቸው። 3 ፈርዖንም የዮሴፍን ወንድሞች “ሥራችሁ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነሱም “እኛ አገልጋዮችህም ሆን የቀድሞ አባቶቻችን በግ አርቢዎች ነን” በማለት መለሱለት። 4 ከዚያም ፈርዖንን እንዲህ አሉት፦ “ወደዚህ የመጣነው በምድሪቱ ላይ እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆነን ለመኖር ነው፤ ምክንያቱም በከነአን ምድር ረሃቡ በጣም ስለበረታ ለአገልጋዮችህ መንጋ የሚሆን የግጦሽ ቦታ የለም። ስለሆነም እባክህ አገልጋዮችህ በጎሸን ምድር እንዲኖሩ ፍቀድላቸው።” 5 በዚህ ጊዜ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “አባትህና ወንድሞችህ ወደ አንተ መጥተዋል። 6 የግብፅ ምድር እንደሆነ በእጅህ ነው። አባትህና ወንድሞችህ ምርጥ በሆነው የምድሪቱ ክፍል እንዲኖሩ አድርግ። በጎሸን ምድር ይኑሩ፤ ከእነሱ መካከል ጥሩ ችሎታ እንዳላቸው የምታውቃቸው ሰዎች ካሉ በከብቶቼ ላይ ኃላፊ አድርገህ ሹማቸው።” 7 ከዚያም ዮሴፍ አባቱን ያዕቆብን አስገብቶ ፈርዖን ፊት አቀረበው፤ ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው። 8 ፈርዖንም ያዕቆብን “ለመሆኑ ዕድሜህ ስንት ነው?” ሲል ጠየቀው። 9 ያዕቆብም ፈርዖንን እንዲህ አለው፦ “ከቦታ ወደ ቦታ በመንከራተት ያሳለፍኩት ዘመን 130 ዓመት ነው። የሕይወት ዘመኔ አጭርና ጭንቀት የበዛበት ነበር፤ ደግሞም አባቶቼ ከቦታ ወደ ቦታ በመንከራተት ያሳለፉትን ዘመን አያክልም።” 10 ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ፈርዖንን መረቀው፤ ከፊቱም ወጥቶ ሄደ። 11 በመሆኑም ዮሴፍ፣ አባቱና ወንድሞቹ እንዲሰፍሩ አደረገ፤ ፈርዖንም ባዘዘው መሠረት ምርጥ ከሆነው የግብፅ ምድር፣ የራምሴስን ምድር ርስት አድርጎ ሰጣቸው። 12 ዮሴፍም ለአባቱ፣ ለወንድሞቹና ለመላው የአባቱ ቤተሰብ በትናንሽ ልጆቻቸው ቁጥር ልክ ቀለብ ይሰፍርላቸው ነበር። 13 በዚህ ወቅት ረሃቡ እጅግ በርትቶ ስለነበር በመላው ምድር እህል አልነበረም፤ የግብፅም ምድር ሆነ የከነአን ምድር በረሃቡ የተነሳ በጣም ተጎድተው ነበር። 14 ዮሴፍም ሰዎች እህል ሲገዙ የከፈሉትን በግብፅ ምድርና በከነአን ምድር የሚገኘውን ገንዘብ በሙሉ እየሰበሰበ ወደ ፈርዖን ቤት ያስገባ ነበር። 15 ከጊዜ በኋላ በግብፅ ምድርና በከነአን ምድር ያለው ገንዘብ አለቀ፤ ግብፃውያንም በሙሉ ወደ ዮሴፍ በመምጣት “እህል ስጠን! ገንዘብ ስለጨረስን ብቻ እንዴት ዓይንህ እያየ እንለቅ?” ይሉት ጀመር። 16 ዮሴፍም “ገንዘባችሁ ካለቀ ከብቶቻችሁን አምጡ፤ እኔም በከብቶቻችሁ ምትክ እህል እሰጣችኋለሁ” አላቸው። 17 በመሆኑም ከብቶቻቸውን ወደ ዮሴፍ ያመጡ ጀመር፤ ዮሴፍም በፈረሶቻቸው፣ በመንጎቻቸው፣ በከብቶቻቸውና በአህዮቻቸው ምትክ እህል ይሰጣቸው ነበር፤ በዚያም ዓመት በከብቶቻቸው ሁሉ ምትክ እህል ሲሰጣቸው ከረመ።
ከሰኔ 15-21
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 48–50
“ከአረጋውያን ብዙ ነገር መማር ይቻላል”
(ዘፍጥረት 48:21, 22) ከዚያም እስራኤል ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ እኔ የምሞትበት ጊዜ ቀርቧል። አምላክ ግን ከእናንተ እንደማይለይ እንዲሁም ወደ አባቶቻችሁ ምድር እንደሚመልሳችሁ የተረጋገጠ ነው። 22 በእኔ በኩል ከአሞራውያን እጅ በሰይፌና በቀስቴ የወሰድኩትን መሬት ከወንድሞችህ አንድ ድርሻ መሬት አስበልጬ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ።”
it-1 1246 አን. 8
ያዕቆብ
ያዕቆብ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ የልጅ ልጆቹን ይኸውም የዮሴፍን ልጆች ባርኳቸው የነበረ ሲሆን በመለኮታዊ አመራር ታናሽየውን ኤፍሬምን ከታላቅየው ከምናሴ አስቀድሞታል። ከዚያም ለበኩር ልጅ የሚገባውን ሁለት እጅ ለሚወርሰው ለዮሴፍ እንዲህ ብሎት ነበር፦ “ከአሞራውያን እጅ በሰይፌና በቀስቴ የወሰድኩትን መሬት ከወንድሞችህ አንድ ድርሻ መሬት አስበልጬ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ።” (ዘፍ 48:1-22፤ 1ዜና 5:1) ያዕቆብ በሴኬም አቅራቢያ የሚገኘውን መሬት ከኤሞር ወንዶች ልጆች በሰላማዊ መንገድ የገዛው ከመሆኑ አንጻር (ዘፍ 33:19, 20) ለዮሴፍ የገባው ቃል ዘሮቹ ወደፊት ከነአንን ድል አድርገው እንደሚይዙ የሚያመለክት ትንቢት ሳይሆን አይቀርም፤ ወደፊት የሚፈጸመውን ነገር በራሱ ሰይፍና ቀስት እንዳከናወነው አድርጎ መናገሩ እምነቱን የሚያሳይ ነው። (አሞራዊ የሚለውን ተመልከት።) ዮሴፍ ከዚህ መሬት ሁለት እጅ ተሰጥቶታል የተባለው ለኤፍሬምና ለምናሴ ነገድ ሁለት ድርሻ መሬት ስለተሰጠ ነው።
(ዘፍጥረት 49:1) ያዕቆብም ወንዶች ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “በኋለኞቹ ቀናት ምን እንደሚያጋጥማችሁ እንድነግራችሁ ተሰብሰቡ።
it-2 206 አን. 1
የመጨረሻዎቹ ቀናት
ያዕቆብ ሊሞት በተቃረበበት ጊዜ የተናገረው ትንቢት። ያዕቆብ ልጆቹን “በኋለኞቹ ቀናት ምን እንደሚያጋጥማችሁ እንድነግራችሁ ተሰብሰቡ” ብሏቸው ነበር፤ ያዕቆብ “በኋለኞቹ ቀናት” ሲል እሱ የሚናገረው ትንቢት ወደፊት የሚፈጸምበትን ጊዜ ማመልከቱ ነበር። (ዘፍ 49:1) ከ200 የሚበልጡ ዓመታት አስቀድሞ ይሖዋ የያዕቆብ አያት ለሆነው ለአብራም (ለአብርሃም) ዘሮቹ ለ400 ዓመት እንደሚጎሳቆሉ ነግሮት ነበር። (ዘፍ 15:13) በመሆኑም ያዕቆብ “በኋለኞቹ ቀናት” ያለው ጊዜ 400ዎቹ የጉስቁልና ዓመታት ከማለቃቸው በፊት ሊጀምር አይችልም። (ስለ ዘፍጥረት 49 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በያዕቆብ ልጆች ስም የቀረቡትን ርዕሶች ተመልከት።) ትንቢቱ ከጊዜ በኋላ ከመንፈሳዊው ‘የአምላክ እስራኤል’ ጋር በተያያዘ ኋለኛ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ መጠበቁ ምክንያታዊ ነው።—ገላ 6:16፤ ሮም 9:6
(ዘፍጥረት 50:24, 25) ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፦ “እንግዲህ እኔ የምሞትበት ጊዜ ቀርቧል፤ ይሁንና አምላክ ፊቱን ወደ እናንተ እንደሚመልስ የተረጋገጠ ነው፤ ደግሞም ያለጥርጥር ከዚህ ምድር አውጥቶ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ወደማለላቸው ምድር ያስገባችኋል።” 25 በመሆኑም ዮሴፍ የእስራኤልን ወንዶች ልጆች “አምላክ ፊቱን ወደ እናንተ እንደሚመልስ ጥርጥር የለውም። አደራ፣ በዚያን ጊዜ አፅሜን ከዚህ ይዛችሁ እንድትወጡ” በማለት አስማላቸው።
አረጋውያን ለወጣቶች በረከት ናቸው
10 አረጋውያን በእምነት አጋሮቻቸው ላይም በጎ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ። የያዕቆብ ልጅ የሆነው ዮሴፍ በስተርጅናው የሰጠው እምነቱን የሚያሳይ ቀላል ትእዛዝ ከእርሱ በኋላ በኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እውነተኛ አምላኪዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ዮሴፍ ‘ስለ ዐጽሙ ትእዛዝ በሰጠበት’ ጊዜ ይኸውም እስራኤላውያን ግብጽን ለቅቀው ሲወጡ ዐጽሙን ይዘው እንዲሄዱ በተናገረበት ወቅት የ110 ዓመት ሰው ነበር። (ዕብራውያን 11:22፤ ዘፍጥረት 50:25) ይህ ትእዛዝ እስራኤላውያን ነጻ እንደሚወጡ ማረጋገጫ ይሰጥ ስለነበር ሕዝቡ ዮሴፍ ከሞተ በኋላ በባርነት ባሳለፏቸው በርካታ ዓመታት ውስጥ ተስፋ እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 49:19) “ጋድ ደግሞ የወራሪዎች ቡድን አደጋ ይጥልበታል፤ እሱ ግን ዱካውን ተከታትሎ ይመታዋል።
ለአምላክ ክብር የሚሰጡ የተባረኩ ናቸው
4 ከእስራኤል ነገዶች መካከል የሆኑት የጋድ ሰዎች ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የሚገኘው ለከብት ርቢ ምቹ የሆነው መሬት እንዲሰጣቸው ጠየቁ። (ዘኍልቁ 32:1-5) ይሁን እንጂ በዚያ አካባቢ መኖር ከባድ ችግሮችን መጋፈጥ ይጠይቃል። በስተ ምዕራብ በኩል ለሚሰፍሩት ነገዶች የዮርዳኖስ ወንዝ ተገን በመሆን ወታደራዊ ወረራን የሚመክት የተፈጥሮ አጥር ይሆናቸዋል። (ኢያሱ 3:13-17) ይሁን እንጂ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን አገር በተመለከተ በጆርጅ አዳም ስሚዝ የተዘጋጀው ዘ ሂስቶሪካል ጂኦግራፊ ኦቭ ዘ ሆሊ ላንድ እንዲህ ይላል፦ “ታላቁ የአረብ ምድር አምባ ምንም መሰናክል የሌለው የተንጣለለ ሜዳ ነው። ከዚህም የተነሳ ባለፉት ዘመናት በሙሉ ቦታውን ረሃብተኛ የሆኑ ዘላኖች ይወርሩት የነበረ ሲሆን አንዳንዶቹም ግጦሽ ፍለጋ በየዓመቱ አምባው ላይ ይሰፍራሉ።”
5 የጋድ ነገድ በየጊዜው የሚካሄድበትን ወረራ መቋቋም የሚችለው እንዴት ነው? ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ቅድመ አያታቸው ያዕቆብ መሞቻው ተቃርቦ በነበረበት ጊዜ “ጋድን ወራሪዎች አደጋ ይጥሉበታል፤ እርሱ ግን ዱካቸውን ተከታትሎ ብድሩን ይመልሳል” የሚል ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ዘፍጥረት 49:19) ላይ ላዩን ሲታይ ያዕቆብ መጥፎ ትንቢት የተናገረ ሊመስል ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የጋድ ነገድ በአጸፋው ጥቃት እንዲሰነዝር የተሰጠ መመሪያ መሆኑ ነው። የጋድ ነገድ እንዲህ ካደረገ የጠላቶቹን ዱካ ተከታትሎ እንደሚያሳድዳቸውና ወራሪዎቹ እፍረት ተከናንበው እንደሚሸሹ ያዕቆብ አረጋግጦለታል።
(ዘፍጥረት 49:27) “ቢንያም እንደ ተኩላ ይቦጫጭቃል። ያደነውን ጠዋት ላይ ይበላል፤ ምሽት ላይ ደግሞ ምርኮ ያከፋፍላል።”
ia 142 ሣጥን
አንድ ትንቢት ፍጻሜውን አገኘ
አስቴርና መርዶክዮስ ለአምላክ ሕዝብ በመታገል በጥንት ዘመን የተነገረ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም አድርገዋል። በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ይሖዋ፣ ያዕቆብን ከልጆቹ ስለ አንዱ የሚከተለውን ትንቢት እንዲናገር በመንፈሱ መርቶት ነበር፦ “ብንያም፣ ነጣቂ ተኵላ ነው፤ ያደነውን ማለዳ ይበላል፤ የማረከውን ማታ ይከፋፈላል።” (ዘፍ. 49:27) በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጀመሪያ ላይ፣ በሌላ አባባል “ማለዳ” ላይ ከነበሩት የቢንያም ዝርያዎች መካከል ንጉሥ ሳኦልና ለይሖዋ ሕዝቦች የተዋጉ ሌሎች ኃያላን ጦረኞች ይገኙበታል። በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ “ማታ” ላይ ማለትም በእስራኤል የነገሥታት መስመር ጀምበር ከጠለቀች በኋላ የቢንያም ነገድ አባላት የሆኑት አስቴርና መርዶክዮስ የይሖዋን ጠላቶች ተዋግተው ድል አድርገዋል። ብዛት ያለውን የሐማን ንብረት ስለወረሱም የማረኩትን ተከፋፍለዋል ሊባል ይችላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፍጥረት 49:8-26) “ይሁዳ ሆይ፣ ወንድሞችህ ያወድሱሃል። እጅህ የጠላቶችህን አንገት ያንቃል። የአባትህ ወንዶች ልጆች በፊትህ ይሰግዳሉ። 9 ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው። ልጄ፣ በእርግጥም ያደንከውን በልተህ ትነሳለህ። እንደ አንበሳ ያደፍጣል፤ እንደ አንበሳ ይንጠራራል፤ ማንስ ሊያስነሳው ይደፍራል? 10 ሴሎ እስኪመጣ ድረስ በትረ መንግሥት ከይሁዳ፣ የአዛዥም በትር ከእግሮቹ መካከል አይወጣም፤ ለእሱም ሕዝቦች ይታዘዙለታል። 11 አህያውን በወይን ተክል ላይ፣ ውርንጭላውንም ምርጥ በሆነ የወይን ተክል ላይ ያስራል፤ ልብሱን በወይን ጠጅ፣ መጎናጸፊያውንም በወይን ፍሬ ጭማቂ ያጥባል። 12 ዓይኖቹ ከወይን ጠጅ የተነሳ የቀሉ፣ ጥርሶቹም ከወተት የተነሳ የነጡ ናቸው። 13 “የዛብሎን መኖሪያ በባሕር ዳርቻ፣ መርከቦች መልሕቅ ጥለው በሚቆሙበት ዳርቻ ይሆናል፤ የወሰኑም ጫፍ በሲዶና አቅጣጫ ይሆናል። 14 “ይሳኮር በመንታ ጭነት መካከል የሚተኛ አጥንተ ብርቱ አህያ ነው። 15 ማረፊያ ቦታው መልካም፣ ምድሩም አስደሳች መሆኑን ያያል። ሸክሙን ለመሸከም ትከሻውን ዝቅ ያደርጋል፤ ለግዳጅ ሥራ ይንበረከካል። 16 “ከእስራኤል ነገዶች አንዱ የሆነው ዳን በሕዝቡ ላይ ይፈርዳል። 17 ዳን፣ ጋላቢው ወደ ኋላ እንዲወድቅ የፈረሱን ሰኮና የሚነክስ በመንገድ ዳር ያለ እባብ፣ በመተላለፊያ ላይ ያለ ቀንዳም እባብ ይሁን። 18 ይሖዋ ሆይ፣ የአንተን ማዳን እጠባበቃለሁ። 19 “ጋድ ደግሞ የወራሪዎች ቡድን አደጋ ይጥልበታል፤ እሱ ግን ዱካውን ተከታትሎ ይመታዋል። 20 “የአሴር ምግብ የተትረፈረፈ ይሆናል፤ በንጉሥ ፊት የሚቀርብ ምግብ ያዘጋጃል። 21 “ንፍታሌም ሸንቃጣ የሜዳ ፍየል ነው። ከአፉም ያማሩ ቃላት ይወጣሉ። 22 “ዮሴፍ ፍሬያማ የሆነ ዛፍ ቀንበጥ ነው፤ ቅርንጫፎቹን በግንብ ላይ የሚሰድ በምንጭ ዳር ያለ ፍሬያማ የሆነ ዛፍ ቀንበጥ ነው። 23 ቀስተኞች ግን እረፍት ነሱት፤ ቀስታቸውንም ወረወሩበት፤ ለእሱም ጥላቻ አደረባቸው። 24 ሆኖም ቀስቱ ከቦታው ንቅንቅ አላለም፤ እጆቹም ብርቱና ቀልጣፋ ናቸው። ይህም ከያዕቆብ ኃያል አምላክ እጆች፣ ከእረኛው፣ ከእስራኤል ዓለት የተገኘ ነው። 25 እሱ ከአባትህ አምላክ የተገኘ ነው፤ አምላክም ይረዳሃል፤ እሱም ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር ይሆናል። አምላክም ከላይ ከሰማያት በሚገኙ በረከቶች፣ ከታች ከጥልቁ በሚገኙ በረከቶች እንዲሁም ከጡትና ከማህፀን በሚገኙ በረከቶች ይባርክሃል። 26 የአባትህ በረከቶች ከዘላለማዊ ተራሮች ከሚመጡት በረከቶችና ጸንተው ከሚኖሩት ኮረብቶች ከሚገኙት መልካም ነገሮች የላቁ ይሆናሉ። በረከቶቹም በዮሴፍ ራስ ላይ፣ ከወንድሞቹ መካከል ተነጥሎ በወጣው በእሱ አናት ላይ ይሆናሉ።
ከሰኔ 22-28
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 1–3
“መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ”
(ዘፀአት 3:13) ሆኖም ሙሴ እውነተኛውን አምላክ “ወደ እስራኤላውያን ሄጄ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ ስላቸው እነሱ ደግሞ ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን ልበላቸው?” አለው።
የይሖዋን ታላቅ ስም አክብሩ
4 ዘፀአት 3:10-15ን አንብብ። ሙሴ 80 ዓመት በሆነው ጊዜ አምላክ ‘ሕዝቡን የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር እንዲያወጣቸው’ ከባድ ኃላፊነት ሰጠው። ሙሴም በምላሹ አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ ልዩ ትርጉም ያዘለ ጥያቄ አቅርቧል። ሙሴ ‘ስምህ ማን ነው?’ ብሎ የጠየቀ ያህል ነበር። የአምላክ ስም ለረጅም ጊዜ ይታወቅ የነበረ ከመሆኑ አንጻር ሙሴ ይህን ጥያቄ የጠየቀው ለምን ነበር? ሙሴ ስሙ የሚወክለውን አካል በተመለከተ ይበልጥ ማወቅ ፈልጎ እንደነበር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል፤ በሌላ አነጋገር ሕዝቡ አምላክ ነፃ እንደሚያወጣቸው አምነው እንዲቀበሉ የሚያደርግ መረጃ ማቅረብ ፈልጎ ነበር። እስራኤላውያን በባርነት መገዛት ከጀመሩ በርካታ ዓመታት ተቆጥረው ስለነበር ሙሴ ይህን ያህል መጨነቁ ምንም አያስገርምም። እስራኤላውያን የአባቶቻቸው አምላክ ሊያድናቸው ይችል እንደሆነ ጥርጣሬ ሊያድርባቸው እንደሚችል መገመት አያዳግትም። እንዲያውም አንዳንድ እስራኤላውያን የግብፃውያንን አማልክት እስከ ማምለክ ደርሰው ነበር!—ሕዝ. 20:7, 8
(ዘፀአት 3:14) በዚህ ጊዜ አምላክ ሙሴን “መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ” አለው። በመቀጠልም “እስራኤላውያንን ‘“እሆናለሁ” ወደ እናንተ ልኮኛል’ በላቸው” አለው።
kr 43 ሣጥን
የአምላክ ስም ትርጉም
ይሖዋ የሚለው ስም “መሆን” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ግስ የተገኘ ነው። አንዳንድ ምሁራን ይህ ግስ ከአምላክ ስም ጋር በተያያዘ የገባበት መንገድ አስደራጊ መሆንን የሚያመለክት እንደሆነ ይገልጻሉ። በመሆኑም ብዙዎች የአምላክ ስም “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም እንዳለው ያስባሉ። ይህ ፍቺ፣ ይሖዋ ፈጣሪ በመሆን ያከናወነውን ተግባር ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል። ይሖዋ፣ ጽንፈ ዓለምና የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ወደ ሕልውና እንዲመጡ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ ፈቃዱና ዓላማው ፍጻሜውን እንዲያገኝ ማድረጉን ቀጥሏል።
ታዲያ በዘፀአት 3:13, 14 ላይ ለሚገኘው ሙሴ ላነሳው ጥያቄ ይሖዋ የሰጠውን መልስ መረዳት የሚኖርብን እንዴት ነው? ሙሴ፣ ይሖዋን እንዲህ በማለት ጠይቆት ነበር፦ “ወደ እስራኤላውያን ሄጄ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ ስላቸው እነሱ ደግሞ ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን ልበላቸው?” ይሖዋም ሙሴን “መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ” አለው።
ሙሴ፣ አምላክን የጠየቀው ስሙን እንዲነግረው እንዳልሆነ ልብ በል። ሙሴም ሆነ እስራኤላውያን የአምላክን ስም በደንብ ያውቁ ነበር። ሙሴ የፈለገው፣ ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ የሚያሳይና እምነቱን የሚያጠናክርለት እንዲሁም የስሙ ትርጉም ምን እንደሆነ የሚጠቁም ነገር እንዲነግረው ነው። በመሆኑም ይሖዋ “መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ” በማለት ሲመልስ ስለ ማንነቱ አስገራሚ የሆነ ነገር እየገለጸ ነበር፦ በእያንዳንዱ ሁኔታ ዓላማውን ለመፈጸም መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ለሙሴና ለእስራኤላውያን አዳኝና ሕግ ሰጪ ከመሆኑም ሌላ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ የሚያሟላ አምላክ ሆኖላቸዋል። በመሆኑም ይሖዋ ለሕዝቡ የገባውን ቃል ለመፈጸም ሲል መሆን የሚፈልገውን ሁሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ የሚለው ስም ይህን ሐሳብ የሚያጠቃልል ቢሆንም የስሙ ትርጉም፣ መሆን የሚፈልገውን እንደሚሆን የሚገልጽ ብቻ አይደለም። የስሙ ትርጉም፣ ዓላማውን ለመፈጸም ሲል ፍጥረታቱ እሱ የሚፈልገውን እንዲሆኑ እንደሚያደርግም ያመለክታል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 2:10) ልጁም ባደገ ጊዜ አምጥታ ለፈርዖን ልጅ ሰጠቻት፤ እሱም ልጇ ሆነ። እሷም “ከውኃ ውስጥ አውጥቼዋለሁ” በማለት ስሙን ሙሴ አለችው።
g04 4/8 6 አን. 5
ሙሴ—እውነተኛ ታሪክ ወይስ ተረት?
ይሁን እንጂ አንዲት ግብፃዊት ልዕልት እንዲህ ያለውን ሕፃን ወስዳ አሳደገች ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው? አዎ፣ ምክንያቱም በግብፃውያን ሃይማኖት መሠረት አንድ ሰው ሰማይ ለመሄድ የደግነት ድርጊት መፈጸም ይጠበቅበታል። የማደጎ ልጅ የማሳደግ ልማድን አስመልክቶ ደግሞ የአርኪኦሎጂ ባለሙያ የሆኑት ጆይስ ቲልዴስሊ እንዲህ ብለዋል፦ “ግብፃውያን ሴቶች ከወንዶች ጋር በእኩልነት ይኖሩ ነበር። ቢያንስ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ከሕግ እና ከኢኮኖሚ አንጻር እኩል መብት ነበራቸው፤ በመሆኑም . . . ሴቶች የማደጎ ልጅ የማሳደግ ይችሉ ነበር።” እንዲያውም አዳፕሽን ፓፒረስ የተባለው ጥንታዊ ሰነድ አንዲት ግብፃዊት ሴት ባሪያዎቿን እንደ ልጆቿ አድርጋ በማደጎ እንዳሳደገቻቸው ይገልጻል። የሙሴ እናት ልጁን እያጠባች እንደ ሞግዚት እንድታሳድገው መቀጠሯን በተመለከተ ደግሞ ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ እንዲህ ይላል፦ “የሙሴ ወላጅ እናት ገንዘብ እየተከፈላት ልጁን እንድታሳድግ መደረጉን የሚገልጸው ታሪክ . . . በሜሶጶጣሚያ ይደረጉ ከነበሩ የማደጎ ስምምነቶች ጋር ይመሳሰላል።”
(ዘፀአት 3:1) ሙሴ የምድያም ካህን የሆነው የአማቱ የዮቶር መንጋ እረኛ ሆነ። እሱም መንጋውን እየመራ ወደ ምድረ በዳው ምዕራባዊ ክፍል ከተጓዘ በኋላ በመጨረሻ ወደ እውነተኛው አምላክ ተራራ ወደ ኮሬብ ደረሰ።
የዘፀአት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
3:1—ዮቶር ካህን የተባለው ከምን አንጻር ነው? በዕብራውያን አባቶች ዘመን አንድ የቤተሰብ ራስ ለቤተሰቡ ካህን ሆኖ ያገለግል ነበር። ዮቶር የምድያማውያን ነገድ መንፈሳዊ መሪ ነበር። ምድያማውያን ኬጡራ ከተባለችው ሚስቱ የተወለዱ የአብርሃም ዝርያዎች በመሆናቸው ስለ ይሖዋ አምልኮ ሳያውቁ አይቀሩም።—ዘፍጥረት 25:1, 2
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፀአት 2:11-25) ሙሴ በጎለመሰ ጊዜ ወንድሞቹ የተጫነባቸውን ሸክም ለማየት ወደ እነሱ ወጣ፤ ከዚያም ከወንድሞቹ አንዱ የሆነውን ዕብራዊ አንድ ግብፃዊ ሲደበድበው አየ። 12 በመሆኑም ወዲያና ወዲህ ተመልክቶ ማንም አለመኖሩን ካረጋገጠ በኋላ ግብፃዊውን ገድሎ አሸዋ ውስጥ ደበቀው። 13 ሆኖም በማግስቱ ሲወጣ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ ተመለከተ። እሱም ጥፋተኛውን “የገዛ ወገንህን የምትመታው ለምንድን ነው?” አለው። 14 በዚህ ጊዜ “አንተን በእኛ ላይ አለቃና ፈራጅ ማን አደረገህ? ግብፃዊውን እንደገደልከው እኔንም ልትገድለኝ ታስባለህ?” አለው። ሙሴም “ይህ ነገር ታውቋል ማለት ነው!” ብሎ በማሰብ ፈራ። 15 ከዚያም ፈርዖን ይህን ነገር ሰማ፤ ሙሴንም ሊገድለው ሞከረ፤ ይሁን እንጂ ሙሴ ከፈርዖን ሸሽቶ በምድያም ምድር ለመኖር ሄደ፤ እዚያም በአንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ። 16 በምድያም የነበረው ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነሱም ውኃ ቀድተው ገንዳውን በመሙላት የአባታቸውን መንጋ ውኃ ለማጠጣት መጡ። 17 ሆኖም እንደወትሮው እረኞቹ መጥተው ሴቶቹን አባረሯቸው። በዚህ ጊዜ ሙሴ ተነስቶ ለሴቶቹ አገዘላቸው፤ መንጋቸውንም አጠጣላቸው። 18 ሴቶቹም ወደ ቤት፣ ወደ አባታቸው ወደ ረኡዔል በተመለሱ ጊዜ አባታቸው “ዛሬ እንዴት ቶሎ መጣችሁ?” ሲል በመገረም ጠየቃቸው። 19 እነሱም “አንድ ግብፃዊ ከእረኞቹ እጅ አዳነን፤ እንዲያውም ውኃ ቀድቶ መንጋችንን አጠጣልን” አሉት። 20 እሱም ልጆቹን “ታዲያ ሰውየው የት አለ? ለምን ትታችሁት መጣችሁ? አብሮን ይበላ ዘንድ ጥሩት” አላቸው። 21 ከዚያ በኋላ ሙሴ ከሰውየው ጋር ለመኖር ተስማማ፤ ሰውየውም ልጁን ሲፓራን ለሙሴ ዳረለት። 22 እሷም ከጊዜ በኋላ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ሙሴም “በባዕድ አገር የምኖር የባዕድ አገር ሰው ሆንኩ” በማለት ስሙን ጌርሳም አለው። 23 ከረጅም ጊዜ በኋላ የግብፁ ንጉሥ ሞተ፤ እስራኤላውያን ግን ካሉበት የባርነት ሕይወት የተነሳ መቃተታቸውንና እሮሮ ማሰማታቸውን አላቆሙም ነበር፤ ከባርነት ሕይወታቸው የተነሳ እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙት ጩኸት ወደ እውነተኛው አምላክ ወጣ። 24 ከጊዜ በኋላም አምላክ በመቃተት የሚያሰሙትን ጩኸት አዳመጠ፤ እንዲሁም ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር የገባውን ቃል ኪዳኑን አሰበ። 25 በመሆኑም አምላክ እስራኤላውያንን አየ፤ ያሉበትንም ሁኔታ ተመለከተ።
ከሰኔ 29–ሐምሌ 5
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 4–5
“በምትናገርበት ጊዜ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ”
(ዘፀአት 4:10) ሙሴም ይሖዋን “ይሖዋ ሆይ፣ ይቅርታ አድርግልኝ፤ እኔ ከዚህ በፊትም ሆነ አንተ አገልጋይህን ካነጋገርክበት ጊዜ ጀምሮ ፈጽሞ አንደበተ ርቱዕ አይደለሁም፤ ንግግር የማልችልና ተብታባ ሰው ነኝ” አለው።
(ዘፀአት 4:13) እሱ ግን “ይሖዋ ሆይ፣ ይቅርታ አድርግልኝ፤ እባክህ መላክ የፈለግከውን ሌላ ማንኛውንም ሰው ላክ” አለው።
ሰበብ ማቅረብ—ይሖዋ እንዴት ይመለከተዋል?
“ጥሩ ችሎታ የለኝም።” የምሥራቹ አገልጋይ ለመሆን ብቃት እንደሌለህ ይሰማህ ይሆናል። በጥንት ጊዜ የኖሩ አንዳንድ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮችም ይሖዋ የሰጣቸውን ሥራ ለመፈጸም ችሎታ እንደሌላቸው ተሰምቷቸው ነበር። ሙሴን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሙሴ ይሖዋ ግልጽ የሆነ ተልእኮ በሰጠው ጊዜ “ጌታ ሆይ፣ ቀድሞም ሆነ፣ አንተ ከባሪያህ ጋር ከተነጋገርህ ወዲህ፣ ከቶ አንደበተ ርቱዕ ሰው አይደለሁም። እኔ ኮልታፋና ንግግር የማልችል ሰው ነኝ” ብሎ ነበር። ይሖዋ ቢያበረታታውም እንኳ ሙሴ “ጌታ ሆይ ፤ እባክህ ሌላ ሰው ላክ” በማለት ተናግሯል። (ዘፀ. 4:10-13) በዚህ ጊዜ ይሖዋ ምን አደረገ?
(ዘፀአት 4:11, 12) ይሖዋም እንዲህ አለው፦ “ለሰው አፍ የፈጠረለት ማን ነው? ሰዎችን ዱዳ፣ ደንቆሮ ወይም ዕውር የሚያደርግ አሊያም ለሰዎች የዓይን ብርሃን የሚሰጥ ማን ነው? እኔ ይሖዋ አይደለሁም? 12 በል አሁን ሂድ፤ በምትናገርበት ጊዜ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ የምትናገረውንም ነገር አስተምርሃለሁ።”
“የማይታየው” አምላክ ይታይሃል?
5 ሙሴ ወደ ግብፅ ከመመለሱ በፊት አምላክ አንድ ጠቃሚ የሆነ እውነታ አስተምሮት ነበር፤ ይህ እውነታ “እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው” የሚለው ሲሆን ሙሴም ከጊዜ በኋላ ይህን ሐሳብ በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ መዝግቦታል። (ኢዮብ 28:28) ሙሴ እንዲህ ዓይነት ፍርሃት በማዳበር ነገሮችን በጥበብ እንዲይዝ ለመርዳት ሲል ይሖዋ በሰዎችና ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ መካከል ያለውን ጉልህ ልዩነት ግልጽ አደረገለት። ይሖዋ ሙሴን እንዲህ በማለት ጠየቀው፦ “ለሰው አንደበቱን የሰጠው ማነው? ሰውን ደንቆሮ ወይም ዲዳ የሚያደርገው ማነው? ዓይን የሚሰጥ ወይም ዕውር የሚያደርገውስ ማነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን?”—ዘፀ. 4:11
6 አምላክ ሙሴን ሊያስተምረው የፈለገው ምንድን ነው? ሙሴ መፍራት አያስፈልገውም። የላከው ይሖዋ ነው፤ ስለዚህ ለፈርዖን የአምላክን መልእክት እንዲያደርስ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ሊሰጠው ይችላል። በተጨማሪም ፈርዖን ከይሖዋ ጋር ጨርሶ ሊወዳደር አይችልም። ደግሞም የአምላክ አገልጋዮች በግብፃውያን ገዢዎች እጅ ለአደጋ ሲጋለጡ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አልነበረም። ሙሴ ከዚያ በፊት በነበሩት ፈርዖኖች አገዛዝ ወቅት ይሖዋ አብርሃምን፣ ዮሴፍንና እሱን ራሱን እንዴት ከአደጋ እንደጠበቃቸው አሰላስሎ ሊሆን ይችላል። (ዘፍ. 12:17-19፤ 41:14, 39-41፤ ዘፀ. 1:22–2:10) ሙሴ ‘በማይታየው’ አምላክ በይሖዋ ላይ እምነት በማሳደር በድፍረት ፈርዖን ፊት የቀረበ ሲሆን አምላክ ያዘዘውን መልእክት አንድም ሳያስቀር ተናግሯል።
(ዘፀአት 4:14, 15) በዚህ ጊዜ የይሖዋ ቁጣ በሙሴ ላይ ነደደ፤ እንዲህም አለው፦ “እሺ ሌዋዊው ወንድምህ አሮንስ? እሱ በደንብ መናገር እንደሚችል አውቃለሁ። ደግሞም አንተን ለማግኘት አሁን ወደዚህ እየመጣ ነው። በሚያይህም ጊዜ ልቡ በደስታ ይሞላል። 15 ስለሆነም እሱን አነጋግረው፤ ቃላቱንም በአንደበቱ አኑር፤ በምትናገሩበትም ጊዜ ከአንተና ከእሱ ጋር እሆናለሁ፤ ምን ማድረግ እንዳለባችሁም አስተምራችኋለሁ።
ሰበብ ማቅረብ—ይሖዋ እንዴት ይመለከተዋል?
ይሖዋ፣ ሙሴን የተሰጠውን ተልእኮ ከመፈጸም ነጻ እንዲሆን አላደረገውም። ከዚህ ይልቅ ሥራውን ማከናወን እንዲችል አሮንን መደበለት። (ዘፀ. 4:14-17) ከዚህም በላይ በቀጣዮቹ ዓመታት ይሖዋ ከሙሴ ጎን በመቆም የሰጠውን ማንኛውንም ሥራ በተሳካ ሁኔታ እንዲፈጽም የሚያስፈልገውን ድጋፍ ሁሉ አድርጎለታል። በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ተሞክሮ ያላቸውን የእምነት አጋሮችህን በማነሳሳት አገልግሎትህን እንድትፈጽም እንዲረዱህ ሊያደርግ እንደሚችል እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ከሁሉ በላይ ይሖዋ እንድንፈጽመው ለሰጠን ሥራ ብቁ እንደሚያደርገን የአምላክ ቃል ያረጋግጥልናል።—2 ቆሮ. 3:5፤ “በሕይወቴ በጣም የተደሰትኩባቸው ዓመታት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 4:24-26) ይሖዋም በመንገድ ላይ ባለው የእንግዳ ማረፊያ ስፍራ አገኘው፤ እሱንም ሊገድለው ፈልጎ ነበር። 25 በመጨረሻም ሲፓራ ባልጩት ወስዳ ልጇን ገረዘችው፤ ሸለፈቱን እግሩን ካስነካች በኋላም “ይህ የሆነው አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ስለሆንክ ነው” አለች። 26 ስለሆነም እንዲሄድ ፈቀደለት። እሷም በዚህ ጊዜ በግርዛቱ የተነሳ “የደም ሙሽራ” አለች።
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ሲፓራ “አንተ የደም ሙሽራ ነህ” በማለት የተናገረችው ሐሳብ ያልተለመደ አባባል ነው። ይህ አባባሏ ምን ያመለክታል? ሲፖራ የግርዘት ቃል ኪዳን የሚጠይቀውን ግዴታ ማሟላቷ ይሖዋ ያቋቋመውን ቃል ኪዳን እንደተቀበለች ያሳያል። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር በገባው በሕጉ ቃል ኪዳን አማካኝነት በመካከላቸው በተመሠረተው ዝምድና እርሱ እንደ ባል እነርሱ ደግሞ እንደ ሚስት ተደርገው ተቆጥረዋል። (ኤርምያስ 31:32) በመሆኑም ሲፓራ ይሖዋ (እርሱን ወክሎ የመጣው መልአክ) “የደም ሙሽራ” እንደሆነ ስትናገር ከቃል ኪዳኑ ጋር ተያይዞ ለሚመጣው ግዴታ ተገዢ መሆኗን መግለጿ ሊሆን ይችላል። ከግርዘት ቃል ኪዳኑ ጋር በተያያዘ ይሖዋ አምላክ የባልነት ቦታውን ሲይዝ እርሷ ደግሞ የሚስትነት ቦታውን የተቀበለች ያህል ነው። ያም ሆነ ይህ አምላክ ያወጣውን ሕግ ለማክበር ፈጣን እርምጃ በመውሰዷ የልጅዋ ሕይወት ከሞት ሊተርፍ ችሏል።
(ዘፀአት 5:2) ፈርዖን ግን እንዲህ አለ፦ “የእሱን ቃል ሰምቼ እስራኤልን የምለቀው ለመሆኑ ይሖዋ ማነው? እኔ ይሖዋ የምትሉትን ፈጽሞ አላውቅም፤ እስራኤልንም አለቅም።”
it-2 12 አን. 5
ይሖዋ
“ማወቅ” ሲባል አንድ ነገር ወይም አንድ አካል መኖሩን መገንዘብን ወይም ላይ ላዩን መተዋወቅን ብቻ አያመለክትም። ሞኝ ሰው የሆነው ናባል የዳዊትን ስም ያውቅ የነበረ ቢሆንም “ለመሆኑ ዳዊት ማን ነው?” በማለት ጠይቋል፤ ይህን ሲል “እሱ ማን ስለሆነ ነው?” ማለቱ ነው። (1ሳሙ 25:9-11፤ ከ2ሳሙ 8:13 ጋር አወዳድር።) ፈርዖንም ለሙሴ “የእሱን ቃል ሰምቼ እስራኤልን የምለቀው ለመሆኑ ይሖዋ ማነው? እኔ ይሖዋ የምትሉትን ፈጽሞ አላውቅም፤ እስራኤልንም አለቅም” ብሎት ነበር። (ዘፀ 5:1, 2) ፈርዖን ይህን ሲል ይሖዋ እውነተኛ አምላክ መሆኑን እንደማያውቅ በተጨማሪም በግብፅ ንጉሥና በእሱ አገዛዝ ላይ ሥልጣን ያለው መሆኑን እንዲሁም ሙሴና አሮን በተናገሩት መሠረት ፈቃዱን ለማስፈጸም የሚያስችል ኃይል ያለው መሆኑን እንደማያውቅ ወይም እንደማይቀበል መግለጹ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ሆኖም ፈርዖንና ሁሉም ግብፃውያን እንዲሁም እስራኤላውያን የዚህን ስም እውነተኛ ትርጉም፣ ማለትም ስሙ የሚወክለውን አካል ማወቃቸው አይቀርም። ይህ የሚሆነው ይሖዋ ለሙሴ በገለጸለት መሠረት ከእስራኤላውያን ጋር በተያያዘ ያለውን ዓላማ ሲፈጽም ይኸውም ነፃ ሲያወጣቸው፣ ተስፋይቱን ምድር ሲሰጣቸው ብሎም በዚህ መልኩ ለአባቶቻቸው የገባውን ቃል ኪዳን ሲፈጽም ነው። በዚህ ጊዜ አምላክ “እኔ አምላካችሁ ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ታውቃላችሁ” በማለት የተናገረው ቃል ይፈጸማል።—ዘፀ 6:4-8፤ ሁሉን ቻይ የሚለውን ተመልከት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፀአት 4:1-17) ሆኖም ሙሴ “‘ይሖዋ አልተገለጠልህም’ ቢሉኝና ባያምኑኝስ? ቃሌንስ ባይሰሙ?” አለው። 2 ይሖዋም “በእጅህ የያዝከው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። እሱም መልሶ “በትር ነው” አለ። 3 እሱም “መሬት ላይ ጣለው” አለው። እሱም መሬት ላይ ጣለው፤ በትሩም እባብ ሆነ፤ ሙሴም ከእባቡ ሸሸ። 4 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን “እጅህን ዘርግተህ ጅራቱን ያዘው” አለው። እሱም እጁን ዘርግቶ ያዘው፤ እባቡም በእጁ ላይ እንደገና በትር ሆነ። 5 ከዚያም አምላክ “ይህ የሆነው የአባቶቻቸው አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ይሖዋ እንደተገለጠልህ እንዲያምኑ ነው” አለው። 6 ይሖዋም በድጋሚ “እባክህ እጅህን ወዳጣፋኸው ልብስ ውስጥ አስገባ” አለው። እሱም እጁን ወዳጣፋው ልብስ ውስጥ አስገባ። ባወጣውም ጊዜ እጁ በለምጽ ተመቶ ልክ እንደ በረዶ ነጭ ሆኖ ነበር! 7 ከዚያም “እጅህን ወዳጣፋኸው ልብስ ውስጥ መልሰህ አስገባው” አለው። እሱም እጁን መልሶ ልብሱ ውስጥ አስገባው። እጁንም ከልብሱ ውስጥ ባወጣው ጊዜ እጁ ተመልሶ እንደ ሌላው የሰውነቱ ክፍል ሆነ! 8 እሱም እንዲህ አለው፦ “ባያምኑህ ወይም የመጀመሪያውን ተአምራዊ ምልክት ችላ ቢሉ እንኳ የኋለኛውን ተአምራዊ ምልክት በእርግጥ አምነው ይቀበላሉ። 9 እንደዛም ሆኖ እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑና ቃልህን ለመስማት ፈቃደኛ ባይሆኑ ከአባይ ወንዝ ውኃ ቀድተህ በደረቁ መሬት ላይ አፍስሰው፤ ከአባይ የቀዳኸው ውኃ በደረቁ መሬት ላይ ደም ይሆናል።” 10 ሙሴም ይሖዋን “ይሖዋ ሆይ፣ ይቅርታ አድርግልኝ፤ እኔ ከዚህ በፊትም ሆነ አንተ አገልጋይህን ካነጋገርክበት ጊዜ ጀምሮ ፈጽሞ አንደበተ ርቱዕ አይደለሁም፤ ንግግር የማልችልና ተብታባ ሰው ነኝ” አለው። 11 ይሖዋም እንዲህ አለው፦ “ለሰው አፍ የፈጠረለት ማን ነው? ሰዎችን ዱዳ፣ ደንቆሮ ወይም ዕውር የሚያደርግ አሊያም ለሰዎች የዓይን ብርሃን የሚሰጥ ማን ነው? እኔ ይሖዋ አይደለሁም? 12 በል አሁን ሂድ፤ በምትናገርበት ጊዜ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ የምትናገረውንም ነገር አስተምርሃለሁ።” 13 እሱ ግን “ይሖዋ ሆይ፣ ይቅርታ አድርግልኝ፤ እባክህ መላክ የፈለግከውን ሌላ ማንኛውንም ሰው ላክ” አለው። 14 በዚህ ጊዜ የይሖዋ ቁጣ በሙሴ ላይ ነደደ፤ እንዲህም አለው፦ “እሺ ሌዋዊው ወንድምህ አሮንስ? እሱ በደንብ መናገር እንደሚችል አውቃለሁ። ደግሞም አንተን ለማግኘት አሁን ወደዚህ እየመጣ ነው። በሚያይህም ጊዜ ልቡ በደስታ ይሞላል። 15 ስለሆነም እሱን አነጋግረው፤ ቃላቱንም በአንደበቱ አኑር፤ በምትናገሩበትም ጊዜ ከአንተና ከእሱ ጋር እሆናለሁ፤ ምን ማድረግ እንዳለባችሁም አስተምራችኋለሁ። 16 እሱም አንተን ወክሎ ለሕዝቡ ይናገራል፤ እንደ ቃል አቀባይም ይሆንልሃል፤ አንተም ለእሱ እንደ አምላክ ትሆናለህ። 17 ይህን በትር በእጅህ ይዘህ ትሄዳለህ፤ በእሱም ተአምራዊ ምልክቶቹን ትፈጽማለህ።”