የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
ከጥር 3-9
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መሳፍንት 15-16
“ክህደት፣ እንዴት ያለ አሳፋሪ ድርጊት ነው!”
ክህደት—ጊዜያችንን ለይቶ የሚያሳውቅ የምልክቱ ገጽታ!
4 እስቲ በመጀመሪያ አሻጥረኛ የሆነችውን የደሊላን ሁኔታ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ሳምሶን ደሊላን እንደወደዳት ይናገራል። ሳምሶን የአምላክን ሕዝብ በመወከል ፍልስጤማውያንን የመዋጋት ፍላጎት ነበረው። ይሁንና አምስት የፍልስጤማውያን ገዥዎች ሳምሶንን ለመግደል አሴሩ፤ እነዚህ ሰዎች ደሊላ ለሳምሶን ጽኑ ፍቅር እንደሌላት ስለተረዱ ሳይሆን አይቀርም ሳምሶን ማንም የማይቋቋመው ጥንካሬ ሊኖረው የቻለበትን ሚስጥር የምትነግራቸው ከሆነ ከፍተኛ መጠን ያለው ጉቦ እንደሚሰጧት ነገሯት። የገንዘብ ፍቅር ያናወዛት ደሊላ ግብዣውን ተቀበለች፤ ይሁንና ሚስጥሩን ለማወቅ ሦስት ጊዜ ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀረ። በመሆኑም “ዕለት ዕለት በመጨቅጨቅ አሰለቸችው።” በዚህም የተነሳ ‘በሕይወት መኖሩን እስከ መጥላት ደረሰ።’ በመጨረሻም፣ ፀጉሩን ተቆርጦ እንደማያውቅና ቢቆረጥ ግን ኃይሉን እንደሚያጣ ነገራት። ደሊላም፣ ሳምሶን በጭኗ ላይ እንቅልፍ ወስዶት ሳለ ፀጉሩን ከቆረጠችው በኋላ በእሱ ላይ የፈለጉትን እንዲያደርጉበት ለጠላቶቹ አሳልፋ ሰጠችው። (መሳ. 16:4, 5, 15-21) እንዴት ያለ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ነው! ደሊላ ስግብግብ በመሆኗ የሚወዳትን ሰው አሳልፋ ሰጥታለች።
የመሳፍንት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
14:16, 17፤ 16:16፦ በማልቀስና በመነዝነዝ አንድን ሰው ማስጨነቅ መልካም ግንኙነት እንዲበላሽ ሊያደርግ ይችላል።—ምሳሌ 19:13፤ 21:19
ክህደት—ጊዜያችንን ለይቶ የሚያሳውቅ የምልክቱ ገጽታ!
15 ታዲያ ያገቡ ሰዎች ለትዳር ጓደኛቸው ያላቸውን ታማኝነት እንደጠበቁ መኖር የሚችሉት እንዴት ነው? የአምላክ ቃል “በልጅነት ሚስትህም ደስ ይበልህ”፤ እንዲሁም “ከምትወዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ” የሚል ምክር ይሰጣል። ይህ ምክር ለባሎች ብቻ ሳይሆን ለሚስቶችም ይሠራል። (ምሳሌ 5:18፤ መክ. 9:9) በመሆኑም ባለትዳሮች ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ በአካልም ሆነ በስሜት በመቀራረብ ለትዳር አጋራቸው ‘ሙሉ ልባቸውን’ መስጠት ይኖርባቸዋል። ይህም ሲባል አንዳቸው ለሌላው ትኩረት መስጠት፣ አብረው ጊዜ ማሳለፍ እንዲሁም እርስ በርስ መቀራረብ አለባቸው ማለት ነው። ትዳራቸውንም ሆነ ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና ለማጠናከር ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ አብረው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ አብረው ማገልገልና የይሖዋን በረከት ለማግኘት አብረው መጸለይ ይኖርባቸዋል።
ለይሖዋ ምንጊዜም ታማኝ ሁኑ
16 አንዳንድ ክርስቲያኖች ከባድ ኃጢአት በመፈጸማቸው ምክንያት “በእምነት ጤናሞች እንዲሆኑ” ጠንከር ያለ ተግሣጽ ተሰጥቷቸዋል። (ቲቶ 1:13) ሌሎች ደግሞ ባሳዩት ምግባር የተነሳ ከጉባኤ ተወግደዋል። ዞሮ ዞሮ ከተግሣጹ ‘ሥልጠና ያገኙ ሰዎች’ የተሰጣቸው ምክር በመንፈሳዊ እንዲያገግሙ ረድቷቸዋል። (ዕብ. 12:11) ይሁንና የተወገደ የቤተሰብ አባል ወይም ዘመድ አሊያም የቅርብ ጓደኛ ቢኖረንስ? በዚህ ጊዜ ታማኝነታችን ፈተና ላይ ይወድቃል። እርግጥ ነው፣ ታማኝ መሆን ያለብን ለአምላክ እንጂ ለግለሰቡ አይደለም። ይሖዋ ከተወገደ ከማንኛውም ሰው ጋር ግንኙነት እንዳይኖረን የሰጠውን ትእዛዝ እንፈጽም እንደሆነና እንዳልሆነ ከላይ ሆኖ እንደሚመለከተን ማስታወስ ይኖርብናል።—1 ቆሮንቶስ 5:11-13ን አንብብ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ሳምሶን ከይሖዋ ባገኘው ብርታት ድል አደረገ!
ሳምሶን ትኩረቱ ሁሉ ያረፈው ከፍልስጥኤማውያን ጋር በሚያደርገው ውጊያ ላይ ነበር። በጋዛ አንዲት ሴተኛ አዳሪ ቤት ለማረፍ የገባው ከአምላክ ጠላቶች ጋር ለመዋጋት በማሰብ ነበር። በጠላት ከተማ የሚያድርበት ቦታ ያስፈልገው ነበር፤ ማግኘት የሚችለው ደግሞ የሴተኛ አዳሪ ቤት ነው። ሳምሶን የሥነ ምግባር ብልግና የመፈጸም ሐሳብ አልነበረውም። እኩለ ሌሊት ሲሆን ከሴቲቱ ቤት በመውጣት የከተማይቱን ቅጥር በር ከሁለት መቃኖቹ ጋር ነቅሎ 60 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ወደሚገኝ ኬብሮን አጠገብ ያለ ኮረብታ ጫፍ ድረስ ተሸክሞ ተጓዘ። ይህን ያደረገው ከአምላክ ባገኘው ድጋፍና እርሱ በሰጠው ኃይል ነበር።—መሳፍንት 16:1-3
ከጥር 10-16
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መሳፍንት 17-19
“የአምላክን ሕግ አለመታዘዝ ለችግር ይዳርጋል”
it-2 390-391
ሚክያስ
1. የኤፍሬም ሰው ነው። ሚክያስ ከእናቱ 1,100 የብር ሰቅል ሰርቆ በመውሰድ ከአሥርቱ ትእዛዛት መካከል ስምንተኛውን ጥሷል (ዘፀ 20:15)። በኋላ ላይ ጥፋቱን ተናዝዞ ብሩን ለእናቱ ሲመልስላት እንዲህ አለችው፦ “የተቀረጸ ምስልና ከብረት የተሠራ ሐውልት እንዲሠራበት ለልጄ ስል ብሩን ከእጄ ለይሖዋ እቀድሰዋለሁ። ለአንተም መልሼ እሰጥሃለሁ።” ከዚያም 200 የብር ሰቅል ወስዳ ለብር አንጥረኛ ሰጠች፤ አንጥረኛውም የተቀረጸ ምስልና ከብረት የተሠራ ሐውልት ሠራበት፤ ምስሎቹም በሚክያስ ቤት ተቀመጡ። ሚክያስ “የአማልክት ቤት” ነበረው፤ ኤፉድና ተራፊም ከሠራ በኋላ ከወንድ ልጆቹ አንዱን ካህን ሆኖ እንዲያገለግለው ሾመው። ከላይ ከላይ ሲታይ ይህ ድርጊቱ ይሖዋን ለማክበር የተደረገ ቢመስልም ፈጽሞ ተገቢ ያልሆነ ነገር ነበር፤ ምክንያቱም ስለ ጣዖት አምልኮ የተሰጠውን ትእዛዝ የጣሰ ከመሆኑም ሌላ (ዘፀ 20:4-6) ይሖዋ የማደሪያ ድንኳኑንና ክህነቱን በተመለከተ ያቋቋመውን ሥርዓት ተላልፏል። (መሳ 17:1-6፤ ዘዳ 12:1-14) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሚክያስ የሙሴ ልጅ የጌርሳም ልጅ የሆነውን ዮናታንን ወሰደው፤ ካህን ሆኖ እንዲያገለግለውም ይህን ወጣት ሌዋዊ ቀጠረው። (መሳ 18:4, 30) ሚክያስ፣ ያደረግኩት ነገር ትክክል ነው የሚል የተሳሳተ ስሜት ስላደረበት “ይሖዋ መልካም እንደሚያደርግልኝ አሁን ተረድቻለሁ” አለ። (መሳ 17:7-13) ሆኖም ዮናታን የአሮን ዘር ስላልሆነ የክህነት አገልግሎት ለመስጠት ብቃት አልነበረውም፤ ስለዚህ ሚክያስ በስህተት ላይ ስህተት ከመጨመር ውጪ ሌላ ያተረፈው ነገር አልነበረም።—ዘኁ 3:10
it-2 391 አን. 2
ሚክያስ
ብዙም ሳይቆይ ሚክያስና አብረውት ያሉት ሰዎች ዳናውያኑን ይከታተሏቸው ጀመር። በኋላ ላይ ሲደርሱባቸው ዳናውያኑ ሚክያስን “ምን ሆነሃል?” ብለው ጠየቁት፤ ሚክያስም “የሠራኋቸውን አማልክቴን ወሰዳችሁ፤ ካህኑንም ይዛችሁ ሄዳችሁ። እንግዲህ ምን ቀረኝ?” አላቸው። በዚህ ጊዜ ዳናውያኑ፣ ‘እየተከተልኩ እጮሃለሁ’ የሚል ከሆነ ጉዳት እንደሚያደርሱበት በመዛት ሚክያስን አስጠነቀቁት። ሚክያስም፣ ዳናውያኑ ከእሱና አብረውት ካሉት ሰዎች ይልቅ ብርቱዎች እንደሆኑ ስለተረዳ ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ። (መሳ 18:22-26) ዳናውያኑ ከዚያ በኋላ ወደ ላይሽ ሄደው ከተማዋን አቃጠሏት፤ በስፍራውም የዳን ከተማን ገነቡ። ዮናታንና ወንዶች ልጆቹ የዳናውያን ነገድ ካህናት ሆኑ፤ “ሚክያስ የሠራውንም የተቀረጸ ምስል አቆሙት፤ ምስሉም የእውነተኛው አምላክ ቤት [የማደሪያ ድንኳኑ] በሴሎ በነበረበት ጊዜ ሁሉ በዚያ ነበር።”—መሳ 18:27-31
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ሕያው የሆነ የአምላክ ቃል ትርጉም
6 የአምላክ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የሚጠቁሙት ማስረጃዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል እንጂ አልቀነሱም። በ2013 ተሻሽሎ በወጣው የእንግሊዝኛ አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ የአምላክ ስም 7,216 ጊዜ የሚገኝ ሲሆን ይህ ቁጥር በ1984 በተዘጋጀው እትም ላይ ካለው በ6 ይበልጣል። የአምላክ ስም የገባባቸው አምስት ተጨማሪ ቦታዎች 1 ሳሙኤል 2:25፤ 6:3፤ 10:26፤ 23:14, 16 ናቸው። በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የአምላክ ስም ቀድሞ በነበረበት ቦታ እንዲገባ የተደረገበት ዋነኛ ምክንያት፣ ማሶሬቶች ከገለበጡት የዕብራይስጥ ቅጂ 1,000 ዓመት በፊት በተዘጋጁት የሙት ባሕር ጥቅልሎች ላይ ስሙ ስለሚገኝ ነው። ከዚህም ሌላ በጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ላይ በተደረገ ተጨማሪ ጥናት ምክንያት መሳፍንት 19:18 ላይ የአምላክ ስም እንዲገባ ተደርጓል።
ከጥር 17-23
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መሳፍንት 20-21
“የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ጥረት ማድረጋችሁን አታቋርጡ”
አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟችሁ እንደ ፊንሐስ ዓይነት እርምጃ ትወስዳላችሁ?
ከብንያም ነገድ የሆኑት የጊብዓ ሰዎች፣ የአንድን ሌዋዊ ቁባት ደፍረው በመግደል አሳዛኝ ድርጊት ከፈጸሙ በኋላ ሌሎቹ ነገዶች የብንያምን ነገድ ለመውጋት ዘምተው ነበር። (መሳ. 20:1-11) ለውጊያ ከመውጣታቸው በፊት የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ጸልየው የነበረ ቢሆንም ሁለት ጊዜ ትልቅ ሽንፈት ደረሰባቸው። (መሳ. 20:14-25) በዚህ ጊዜ ጸሎታቸው ተቀባይነት እንዳላገኘ ተሰምቷቸው ይሆን? ለተፈጸመው መጥፎ ድርጊት የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ በመነሳታቸው ይሖዋ አልተደሰተም ነበር ማለት ነው?
አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟችሁ እንደ ፊንሐስ ዓይነት እርምጃ ትወስዳላችሁ?
ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ሽማግሌዎች ብርቱ ጥረት ቢያደርጉና አምላክ እንዲረዳቸው ደጋግመው ቢጸልዩም በጉባኤ ውስጥ ያሉት እንዳንድ ችግሮች ቶሎ አይወገዱ ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥም ሽማግሌዎች ኢየሱስ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ማስታወሳቸው ተገቢ ነው፦ “ደጋግማችሁ ለምኑ [ወይም ጸልዩ]፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታሰልሱ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።” (ሉቃስ 11:9) ሽማግሌዎች ያቀረቡት ጸሎት ቶሎ መልስ እንዳላገኘ ቢሰማቸውም እንኳ ይሖዋ በራሱ ጊዜ መልስ እንደሚሰጣቸው ሊተማመኑ ይገባል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ይህን ያውቁ ኖሯል?
ወንጭፍ በጥንት ጊዜ ለጦርነት ጥቅም ላይ የዋለው እንዴት ነበር?
ዳዊት ግዙፉን ጎልያድን የገደለው በወንጭፍ ተጠቅሞ ነበር። ዳዊት በወንጭፍ መጠቀምን የተማረው እረኛ በነበረበት ወቅት እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።—1 ሳሙኤል 17:40-50
ወንጭፍ በጥንቶቹ ግብፃውያንና አሦራውያን ሥነ ጥበብ ላይ ይታያል። ይህ መሣሪያ፣ መሃል ላይ ከቆዳ ወይም ከጨርቅ የተሠራ ማቀፊያ ያለው ሲሆን ማቀፊያው በሁለቱም አቅጣጫ ገመዶች አሉት። ወንጫፊው ከ5 እስከ 7.5 ሳንቲ ሜትር ዳያሜትር ያለውና 250 ግራም ያህል የሚመዝን ለስላሳ ወይም ድቡልቡል ድንጋይ በማቀፊያው ላይ ያስቀምጣል። ከዚያም ወንጭፉን ከአናቱ በላይ አሽከርክሮ አንዱን ገመድ ይለቀዋል፤ በዚህ ጊዜ ድንጋዩ ወደተፈለገበት አቅጣጫ በከፍተኛ ኃይል ይወነጨፋል።
በመካከለኛው ምሥራቅ በተደረጉ ቁፋሮዎች በጥንት ዘመን በርካታ የወንጭፍ ድንጋዮች ተገኝተዋል። የሠለጠኑ ጦረኞች የሚያስወነጭፏቸው ድንጋዮች በሰዓት ከ160 እስከ 240 ኪሎ ሜትር በሆነ ፍጥነት ይጓዙ ነበር። ወንጭፍ አንድን ድንጋይ የሚያስወነጭፍበት ርቀት ቀስት ከሚያስፈነጥርበት ርቀት ጋር ተመሳሳይ ስለመሆኑ ምሁራን ስምምነት ላይ ባይደርሱም ወንጭፍም እንደ ቀስት ሰው ሊገድል ይችላል።—መሳፍንት 20:16
ከጥር 24-30
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሩት 1-2
“ታማኝ ፍቅር አሳዩ”
ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸውን ምሰሉ
5 ወጣት መበለት የሆነችው ሩት፣ በሞዓብ ቤተሰቦቿ ስላሉ እናቷና ሌሎች ዘመዶቿ ሊያስጠጓት ብሎም ሊንከባከቧት እንደሚችሉ ማሰብ ትችል ነበር። ሞዓብ የትውልድ አገሯ ነው። ባሕሉ፣ ቋንቋውም ሆነ ሕዝቡ ለእሷ አዲስ አይደለም። ሩት በቤተልሔም እነዚህን ነገሮች እንደምታገኝ ናኦሚ ቃል ልትገባላት አትችልም። ናኦሚም ብትሆን ሩትን የመከረቻት በሞዓብ እንድትቀር ነው። ናኦሚ፣ ምራቶቿ ትዳርም ሆነ የራሳቸው ኑሮ እንዲኖራቸው ልትረዳቸው ስለመቻሏ ስጋት አድሮባታል። ታዲያ ሩት ምን ታደርግ ይሆን? “ወደ ወገኖቿና ወደ አማልክቷ” በተመለሰችው በዖርፋና በሩት መካከል ያለውን ልዩነት ልብ በል። (ሩት 1:9-15) ሩት ወገኖቿ ወደሚያመልኳቸው የሐሰት አማልክት ለመመለስ ትወስን ይሆን? በፍጹም እንዲህ አላደረገችም።
ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸውን ምሰሉ
6 ሩት ስለ ይሖዋ አምላክ የምታውቀው ነገር አለ፤ ይህን ያወቀችው ከቀድሞ ባሏ ወይም ከናኦሚ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ከሞዓብ አማልክት የተለየ ነው። ሩት፣ ይሖዋ ልትወደውና ልታመልከው የሚገባ አምላክ እንደሆነ ተገንዝባ ነበር። እውቀት ብቻውን ግን በቂ አይደለም። ሩት ውሳኔ ማድረግ ይኖርባታል። ይሖዋ፣ አምላኳ እንዲሆን ትመርጥ ይሆን? ይህች ወጣት ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ አድርጋለች። ለናኦሚ “ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል” ብላታለች። (ሩት 1:16) ሩት ለናኦሚ ስለነበራት ፍቅር ስናስብ ልባችን በጥልቅ የሚነካ ቢሆንም ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለይሖዋ ያላት ፍቅር ነው። ሩት በይሖዋ ክንፎች ሥር ለመጠለል በመፈለጓ ከጊዜ በኋላ ቦዔዝ አድንቋታል። (ሩት 2:12ን አንብብ።) ቦዔዝ የተጠቀመበት አገላለጽ፣ ጥላ ከለላ ለማግኘት በወላጆቿ ክንፎች ሥር የምትሸሸግን ጫጩት እንድናስብ ያደርገን ይሆናል። (መዝ. 36:7፤ 91:1-4) ይሖዋ ለሩት እንደነዚህ ወላጆች ሆኖላታል። ስላሳየችው እምነት ወሮታዋን የከፈላት ሲሆን በውሳኔዋ እንድትቆጭ የሚያደርግ ምንም ነገር አላጋጠማትም።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የሩት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
1:13, 21—ኑኃሚን ሕይወት መራራና በመከራ የተሞላ እንዲሆንባት ያደረገው ይሖዋ ነበር? አይደለም። ኑኃሚንም እንደዚያ ስትል መከራ አምጥቶብኛል ብላ አምላክን መክሰሷ አልነበረም። ሆኖም ከደረሰባት መከራ አንጻር ይሖዋ ፊቱን እንዳዞረባት ተሰምቷት ነበር። በሁኔታው ክፉኛ የተመረረች ሲሆን ግራ ተጋብታም ነበር። ከዚህም በላይ በጊዜው የማሕፀን ፍሬ የአምላክን በረከት እንደ ማግኘት ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን መካን መሆን ደግሞ እንደ እርግማን ተደርጎ ይታይ ነበር። ሁለት ልጆቿን በሞት ያጣችውና የልጅ ልጅ ለማየት ያልታደለችው ኑኃሚንም ይሖዋ እንዳዋረዳት ተሰምቷት ነበር።
ከጥር 31–የካቲት 6
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሩት 3-4
“ጥሩ ስም ማትረፍና ያተረፍነውን ስም ይዞ መቀጠል”
“ምግባረ መልካም ሴት”
ቦዔዝ፣ ሩትን ያናገራት በደግነትና በሚያጽናና መንገድ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። እንዲህ አላት፦ “ልጄ ሆይ፤ እግዚአብሔር ይባርክሽ፤ ከዚህ በፊት ካደረግሽው ይልቅ ያሁኑ በጎነትሽ ይበልጣል፤ ባለጠጋም ሆነ ድኻ፣ ወጣት ወንድ ፈልገሽ አልሄድሽምና።” (ሩት 3:10) ቦዔዝ “ከዚህ በፊት ካደረግሽው” ሲል ሩት፣ ኑኃሚንን ተከትላ ወደ እስራኤል በመምጣትና አማቷን በመንከባከብ ያሳየችውን ታማኝ ፍቅር መግለጹ ነው። “ያሁኑ በጎነትሽ” ያለው ደግሞ በዚያ ምሽት ያደረገችውን ነገር ለመጥቀስ ነው። ቦዔዝ እንደ ሩት ያለች ወጣት ሴት ሀብታምም ይሁን ድሃ የፈለገችውን መርጣ ወጣት የሆነ ባል በቀላሉ ማግባት እንደምትችል ተረድቷል። ሩት ግን ለኑኃሚን ብቻ ሳይሆን ለሟቹ የኑኃሚን ባል ጭምር መልካም ማድረግ ፈልጋለች፤ የኑኃሚን ባል የዘር ሐረጉ እንዲቀጥል ማድረግ ስለምትችልበት መንገድ አስባ ነበር። ቦዔዝ፣ ይህች ወጣት በፈጸመችው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ድርጊት ልቡ የተነካው ለምን እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም።
“ምግባረ መልካም ሴት”
ሩት፣ በሰው ሁሉ ዘንድ “ምግባረ መልካም ሴት” በመሆኗ እንደምትታወቅ ቦዔዝ የነገራትን መለስ ብላ ስታስብ ምን ያህል ተደስታ ይሆን! ይሖዋን ለማወቅና እሱን ለማገልገል ያላት ጉጉት እንዲህ ያለ መልካም ስም እንድታተርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም ለእሷ ፈጽሞ እንግዳ የሆኑ ልማዶችንና ባሕሎችን ለመቀበል ፈቃደኛ በመሆን ለኑኃሚንና ለሕዝቧ ታላቅ ደግነትና አሳቢነት አሳይታለች። እኛም ሩትን በእምነቷ የምንመስላት ከሆነ ለሌሎች እንዲሁም ለባሕላቸው ጥልቅ አክብሮት ለማሳየት እንጥራለን። እንዲህ ካደረግን እኛም እንደ ሩት በመልካም ምግባራችን ጥሩ ስም እናተርፋለን።
“ምግባረ መልካም ሴት”
ቦዔዝ ሩትን አገባት። ዘገባው ከዚያ በኋላ ስለሆነው ነገር ሲገልጽ “እግዚአብሔር እንድትፀንስ አደረጋት፤ ወንድ ልጅም ወለደች” ይላል። የቤተልሔም ሴቶች ኑኃሚንን የመረቋት ሲሆን ሩትንም ከሰባት ወንዶች ልጆች ይልቅ ለኑኃሚን የምትሻል በመሆኗ አሞገሷት። ከጊዜ በኋላም የሩት ልጅ የንጉሥ ዳዊት አያት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሩት 4:11-22) ዳዊት ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት ነው።—ማቴዎስ 1:1
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የሩት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
4:6—አንድ ሰው የቅርብ ዘመዱን በመቤዠት የራሱን ርስት ‘አደጋ ላይ ሊጥል’ የሚችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ለድህነት የተጋለጠው ሰው መሬቱን ሸጦት ከነበረ የሚቤዠው ሰው ቀጣዩ የኢዮቤልዩ በዓል እስከሚከበርበት ጊዜ ድረስ በቀሩት ዓመታት መጠን ተሰልቶ የሚወሰነውን ዋጋ በመክፈል መሬቱን መግዛት ይኖርበታል። (ዘሌዋውያን 25:25-27) ይህም የሀብቱን መጠን ይቀንስበታል። ከዚህም በላይ ሩት ወንድ ልጅ ከወለደች የተገዛውን መሬት የሚወርሰው ርስቱን የተቤዠው ሰው የቅርብ የሥጋ ዘመዶች ሳይሆኑ ይህ ልጅ ነው።
ከየካቲት 7-13
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ሳሙኤል 1-2
“በጸሎት ለይሖዋ ልባችሁን አፍስሱ”
ለአምላክ የልቧን አውጥታ ነገረችው
12 በዚህ መንገድ ሐና ጸሎትን በተመለከተ ለአምላክ አገልጋዮች ሁሉ ምሳሌ ትታለች። አንድ ልጅ አፍቃሪ ለሆነው አባቱ እንደሚያደርገው ሁሉ የይሖዋ ሕዝቦችም የሚያሳስባቸውን ነገር ሁሉ ያላንዳች ገደብ ግልጥልጥ አድርገው ለእሱ በመናገር ልባቸውን በፊቱ እንዲያፈሱ ይሖዋ በደግነት ጋብዟቸዋል። (መዝሙር 62:8ን እና 1 ተሰሎንቄ 5:17ን አንብብ።) ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ለይሖዋ የሚቀርብ ጸሎትን በተመለከተ በመንፈስ መሪነት የሚከተለውን አጽናኝ ሐሳብ ጽፏል፦ “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።”—1 ጴጥሮስ 5:7
ሐና ሰላም ያገኘችው እንዴት ነው?
ከዚህ ምን እንማራለን? ስለሚያስጨንቁን ነገሮች ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ምን እንደሚሰማን ልንነግረው እንዲሁም የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንዲሰጠን ከልብ በመነጨ ስሜት ልንጠይቀው እንችላለን። ችግሩን ለመፍታት ማድረግ የምንችለው ነገር ከሌለ ጉዳዩን ለእርሱ መተው ይኖርብናል። ልንከተለው የሚገባ ከዚህ የተሻለ አካሄድ የለም።—ምሳሌ 3:5, 6
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአንደኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
2:10— ሐና በእስራኤል ሰብዓዊ ንጉሥ ባልነበረበት ወቅት ይሖዋ “ለንጉሡ ኀይልን ይሰጣል” በማለት የጸለየችው ለምንድን ነው? እስራኤላውያን ሰብዓዊ ንጉሥ እንደሚኖራቸው በሙሴ ሕግ ውስጥ አስቀድሞ ተነግሮ ነበር። (ዘዳግም 17:14-18) ያዕቆብም ሊሞት ሲቃረብ “በትረ መንግሥት [የንጉሣዊ ሥልጣን ምልክት] ከይሁዳ እጅ አይወጣም” በማለት ተንብዮ ነበር። (ዘፍጥረት 49:10) ከዚህም በላይ ይሖዋ የእስራኤላውያን ቅድመ አያት ስለሆነችው ስለ ሣራ ሲናገር “የሕዝቦችም ነገሥታት ከእርሷ ይወጣሉ” ብሎ ነበር። (ዘፍጥረት 17:16) ስለዚህ ሐና የጸለየችው ወደፊት ስለሚመጣው ንጉሥ ነበር።
ከየካቲት 14-20
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ሳሙኤል 3-5
“ይሖዋ አሳቢ አምላክ ነው”
ሁሉን ቻይ ሆኖም አሳቢ
3 ሳሙኤል በማደሪያው ድንኳን ውስጥ ‘ይሖዋን ማገልገል’ የጀመረው ገና ትንሽ ልጅ እያለ ነው። (1 ሳሙ. 3:1) አንድ ምሽት ሳሙኤል ተኝቶ እያለ አንድ ያልተለመደ ነገር ተከሰተ። (1 ሳሙኤል 3:2-10ን አንብብ።) ሳሙኤል አንድ ድምፅ ስሙን ሲጠራው ሰማ። ሳሙኤል፣ አረጋዊው ሊቀ ካህናት ኤሊ የጠራው ስለመሰለው ወደ እሱ እየሮጠ ሄዶ “አቤት፣ ጠራኸኝ?” አለው። ኤሊ ግን “አይ፣ አልጠራሁህም” በማለት መለሰለት። ይህ ሁኔታ ሁለት ጊዜ ሲደገም ኤሊ ሳሙኤልን እየጠራው ያለው አምላክ መሆኑን አስተዋለ። ስለዚህ ምን ምላሽ መስጠት እንዳለበት ለሳሙኤል ነገረው፤ ሳሙኤልም እንደታዘዘው አደረገ። ይሁንና ይሖዋ ሳሙኤልን ሲጠራው፣ ገና ከመጀመሪያው ማንነቱን ያልገለጸለት ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ መልሱን በቀጥታ አይናገርም፤ ሆኖም ቀጥሎ የተከናወኑት ነገሮች ይሖዋ ይህን ያደረገው ለብላቴናው ሳሙኤል አስቦለት ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
ሁሉን ቻይ ሆኖም አሳቢ
4 1 ሳሙኤል 3:11-18ን አንብብ። የይሖዋ ሕግ፣ ልጆች በዕድሜ የገፉ ሰዎችን በተለይም የሕዝብ አለቃ የሆኑትን እንዲያከብሩ ያዝዝ ነበር። (ዘፀ. 22:28፤ ዘሌ. 19:32) በመሆኑም ብላቴናው ሳሙኤል በጠዋት ተነስቶ ወደ ኤሊ በመሄድ፣ ይሖዋ የነገረውን አስደንጋጭ የፍርድ መልእክት በድፍረት ለኤሊ ማስተላለፍ ምን ያህል ሊከብደው እንደሚችል መገመት አያዳግትም! እንዲያውም ዘገባው “ሳሙኤል ራእዩን ለኤሊ መንገር ፈርቶ ነበር” ይላል። ሆኖም አምላክ፣ ሳሙኤልን እያነጋገረው ያለው እሱ መሆኑን ኤሊ እንዲያውቅ አደረገ። በዚህም የተነሳ ኤሊ ራሱ ሳሙኤልን ጠርቶ የይሖዋን መልእክት እንዲነግረው አዘዘው። ኤሊ “እሱ ከነገረህ ነገር ውስጥ አንዲት ቃል እንኳ [እንዳትደብቀኝ]” አለው። ሳሙኤልም በታዘዘው መሠረት ይሖዋ ያለውን “በሙሉ ምንም ሳይደብቅ ነገረው።”
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአንደኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
3:3—ሳሙኤል የተኛው በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ነበር? አልነበረም። ሳሙኤል ሌዋዊ ቢሆንም የክህነት መብት የሌለው የቀዓት ዝርያ ነበር። (1 ዜና መዋዕል 6:33-38) በመሆኑም በሕጉ መሠረት “ንዋየ ቅዱሳቱን ለአንድ አፍታ እንኳን ለማየት” አይፈቀድለትም። (ዘኍልቍ 4:17-20) ሳሙኤል መግባት የሚፈቀድለት ወደ መገናኛ ድንኳኑ ቅጥር ግቢ ብቻ ነበር። የተኛውም እዚያ መሆን አለበት። ዔሊም ቢሆን የሚተኛው እዚያው መገናኛ ድንኳኑ ግቢ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። “የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት” የሚለው አገላለጽ የመገናኛ ድንኳኑን አካባቢ የሚያመለክት መሆን አለበት።
ከየካቲት 21-27
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ሳሙኤል 6-8
“ንጉሣችሁ ማን ነው?”
it-2 163 አን. 1
የአምላክ መንግሥት
ሰብዓዊ ንጉሥ እንዲሾምላቸው ጠየቁ። እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ከ400 ዓመት ገደማ በኋላ፣ አምላክ ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን ከገባ ከ800 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ እስራኤላውያን ሰብዓዊ ንጉሥ እንዲሾምላቸው ጥያቄ አቀረቡ፤ እንደ ሌሎቹ ብሔራት ሁሉ የሚመራን ንጉሥ ይሾምልን አሉ። ይህ ጥያቄያቸው፣ ራሱን የይሖዋን ንግሥና ለመቀበል እንዳልፈለጉ የሚያስቆጥር ነው። (1ሳሙ 8:4-8) እርግጥ ነው፣ ሕዝቡ አምላክ መንግሥት እንደሚያቋቁም መጠበቃቸው ተገቢ ነው፤ ይሖዋ ለአብርሃምና ለያዕቆብ ከገባው ቃል ጋርም የሚስማማ ነው። ይህን እንዲጠብቁ የሚያደርጓቸው ሌሎች ምክንያቶችም ነበሯቸው፤ ያዕቆብ ሊሞት ሲል ስለ ይሁዳ ከተናገረው ትንቢት (ዘፍ 49:8-10)፣ እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ ይሖዋ ለእነሱ ከተናገረው ሐሳብ (ዘፀ 19:3-6)፣ በሕጉ ላይ ከተጠቀሰው ሐሳብ (ዘዳ 17:14, 15) እንዲሁም አምላክ ነቢዩን በለዓምን እንዲናገር ካነሳሳው መልእክትም እንኳ በመነሳት (ዘኁ 24:2-7, 17) እዚህ መደምደሚያ ላይ መድረስ ይችላሉ። የሳሙኤል እናት የሆነችው ታማኟ ሐናም፣ በጸሎቷ ላይ ይህን ተስፋ ገልጻ ነበር። (1ሳሙ 2:7-10) ያም ቢሆን ይሖዋ፣ ስለ መንግሥቱ የሚገልጸውን “ቅዱስ ሚስጥር” ገና ሙሉ በሙሉ አልገለጠም ነበር፤ መንግሥቱን የሚያቋቁምበት ጊዜ መቼ እንደሆነ፣ መንግሥቱ ምን ዓይነት መዋቅር እና አደረጃጀት እንደሚኖረው፣ ሌላው ቀርቶ ምድራዊ ይሁን ሰማያዊ እንኳ ገና የገለጸው ነገር አልነበረም። ስለዚህ ሕዝቡ አሁን ንጉሥ እንዲሾምላቸው መጠየቃቸው ቦታቸውን አልፈው እንደሄዱ የሚያሳይ ነበር።
ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ቢኖሩም ጸንቷል
ሳሙኤል ጉዳዩን በጸሎት ለይሖዋ ባቀረበ ጊዜ ይሖዋ ምን እንደተናገረ ልብ በል፦ “ንጉሣቸው እንዳልሆን የናቁት እኔን እንጂ አንተን አይደለምና ሕዝቡ የሚሉህን ሁሉ አድምጥ።” ይህ አባባል ሳሙኤልን ምን ያህል ያጽናናው ይሆን? ይሁንና ሕዝቡ የተናገረው ይህ ሐሳብ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ እንደመሳደብ ይቆጠር ነበር። ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ሰብዓዊ ንጉሥ ማንገሣቸው ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው በመንገር ሕዝቡን እንዲያስጠነቅቅ ለነቢዩ ነገረው። ሳሙኤል የይሖዋን ሐሳብ ሲነግራቸው ሕዝቡ “አይሆንም፤ ንጉሥ እንዲነግሥልን እንፈልጋለን” በማለት አሻፈረኝ አሉ። ምንጊዜም ለአምላኩ ታዛዥ የነበረው ሳሙኤል ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ይሖዋ የመረጠላቸውን ንጉሥ አነገሠላቸው።—1 ሳሙኤል 8:7-19
የይሖዋ አገዛዝ ትክክለኛ መሆኑ ተረጋገጠ!
9 ይሖዋ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ትክክል መሆኑን ታሪክ አሳይቷል። እስራኤላውያን በሰብዓዊ ንጉሥ በተለይ ደግሞ ለይሖዋ ታማኝ ባልሆነ ንጉሥ መገዛታቸው ከባድ ችግሮች አስከትሎባቸዋል። ከእስራኤላውያን ታሪክ አንጻር ይሖዋን በማያውቁ ሰዎች የሚመሩ መንግሥታት በታሪክ ዘመናት ሁሉ ዘላቂ የሆነ ጥቅም ማስገኘት አለመቻላቸው ምንም አያስገርምም። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ፖለቲከኞች አምላክ ሰላምና ደኅንነት ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት እንዲባርክላቸው ይጸልያሉ፤ ይሁን እንጂ አምላክ የእሱን አገዛዝ የማይቀበሉ ሰዎችን እንዴት ሊባርክ ይችላል?—መዝ. 2:10-12
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
መጠመቅ ለምን አስፈለገ?
13 ተጠምቀን የይሖዋ ምሥክር ከመሆናችን በፊት ለውጥ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። መለወጥ ክርስቶስ ኢየሱስን ለመከተል ከሙሉ ልብ የመነጨ ውሳኔ ያደረገ ሰው በፈቃደኝነት የሚወስደው እርምጃ ነው። እንዲህ ያለ እርምጃ የሚወስዱ ግለሰቦች ቀድሞ ይከተሉት የነበረውን የተሳሳተ ጎዳና በመተው በአምላክ ፊት ትክክል የሆነውን ለማድረግ ይወስናሉ። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ መለወጥን ለማመልከት የገቡት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ግሦች ጀርባን መስጠት፣ ዞር ማለት የሚል ትርጉም አላቸው። ይህ እርምጃ ከተሳሳተ ጎዳና ወደ አምላክ መዞርን ያመለክታል። (1 ነገሥት 8:33, 34) መለወጥ “ለንስሐ የሚገባ ነገር” ማድረግን ይጠይቃል። (ሥራ 26:20) በሐሰት አምልኮ መካፈልን መተው፣ ከአምላክ ትእዛዛት ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስና ለይሖዋ ብቻ የተወሰነ አምልኮ ማቅረብን ይጠይቃል። (ዘዳግም 30:2, 8-10፤ 1 ሳሙኤል 7:3) መለወጥ በአስተሳሰባችን፣ በዓላማችን እንዲሁም በባሕርያችን ላይ ለውጥ እንድናሳይ ያደርገናል። (ሕዝቅኤል 18:31) አምላካዊ ያልሆኑ ባሕርያትን በአዲሱ ሰው ስንተካ ‘ተመልሰናል’ ለማለት እንችላለን።—ሥራ 3:19፤ ኤፌሶን 4:20-24፤ ቆላስይስ 3:5-14
ከየካቲት 28–መጋቢት 6
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ሳሙኤል 9-11
“ሳኦል መጀመሪያ ላይ ትሑትና ልኩን የሚያውቅ ሰው ነበር”
በትሕትና እና ልክህን በማወቅ ከአምላክህ ጋር ሂድ
11 ንጉሥ ሳኦል ስላጋጠመው ነገር እናስብ። ሳኦል ወጣት እያለ ልኩን የሚያውቅ ሰው ነበር። ከቦታው አልፎ የሚሄድ ሰው አልነበረም፤ ተጨማሪ ኃላፊነት ሲሰጠው እንኳ ለመቀበል አመንትቶ ነበር። (1 ሳሙ. 9:21፤ 10:20-22) ከጊዜ በኋላ ግን ሳኦል ከቦታው አልፎ መሄድ ጀመረ። ይህ መጥፎ ባሕርይ መታየት የጀመረው ንጉሥ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ነው። በአንድ ወቅት ሳኦል፣ ነቢዩ ሳሙኤልን በትዕግሥት መጠበቅ አቅቶት ነበር። ሳኦል፣ ልኩን የሚያውቅ ሰው ቢሆን ኖሮ ይሖዋ ለሕዝቡ ሲል እርምጃ እንደሚወስድ ይተማመን ነበር፤ እሱ ግን የሚቃጠል መሥዋዕት በማቅረብ ያልተፈቀደለትን ነገር አደረገ። በዚህም ምክንያት የይሖዋን ሞገስ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ንግሥናውን አጣ። (1 ሳሙ. 13:8-14) እኛም ከዚህ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ትምህርት በመውሰድ ከቦታችን አልፈን ላለመሄድ መጠንቀቃችን የጥበብ እርምጃ ነው።
የራስን ጥቅም የመሠዋትን መንፈስ ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?
8 የእስራኤል ንጉሥ የነበረው የሳኦል ታሪክ፣ የራስ ወዳድነት ምኞት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈሳችንን ቀስ በቀስ ሊያጠፋብን የሚችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይሆነናል። ሳኦል፣ ንጉሥ ሆኖ ሲቀባ ቦታውን የሚያውቅና ትሑት ሰው ነበር። (1 ሳሙ. 9:21) ንግሥናውን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑት እስራኤላውያን ከአምላክ የተሰጠውን ሥልጣን ባለማክበራቸው ሊቀጡ እንደሚገባ ሊያስብ ይችል ነበር፤ እሱ ይህን ከማድረግ ተቆጥቧል። (1 ሳሙ. 10:27) እስራኤላውያን ከአሞናውያን ጋር ባደረጉት ጦርነት ንጉሥ ሳኦል የአምላክን መንፈስ አመራር በመቀበሉ ሕዝቡ ድል እንዲቀዳጅ አድርጓል። ከዚያም፣ ድሉ የተገኘው በይሖዋ እርዳታ እንደሆነ በመግለጽ ትሑት መሆኑን አሳይቷል።—1 ሳሙ. 11:6, 11-13
አሞናውያን—ለተደረገላቸው ደግነት ጥላቻ የመለሱ ሰዎች
አሁንም አሞናውያን ይሖዋ ላደረገላቸው ደግነት ጥላቻ መለሱ። ይሖዋ ይህንን ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት እንዳላየ ሆኖ አላለፈውም። “ይህን [የናዖስን] ነገር በሰማው ጊዜ በሳኦል ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ወረደ፣ ቁጣውም እጅግ ነደደ።” ሳኦል በአምላክ መንፈስ መሪነት 330,000 ወታደሮችን የያዘ ሠራዊት አሰባሰበና ‘ከእልቂት የተረፉት ለየብቻቸው በመሮጥ እስኪበታተኑ’ ድረስ አሞናውያንን ድል አደረጋቸው።—1 ሳሙኤል 11:6, 11 የ1980 ትርጉም
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአንደኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
9:9—“ዛሬ ነቢይ የሚባለው በዚያ ጊዜ ባለ ራእይ ይባል ነበር” የሚለው አገላለጽ ምን ትርጉም አለው? ይህ ዓረፍተ ነገር በሳሙኤል ጊዜና በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ነቢያት ይበልጥ እየታወቁ ሲመጡ “ባለ ራእይ” የሚለው አጠራር “ነቢይ” በሚለው መተካቱን ለመግለጽ የገባ ሊሆን ይችላል። ከነቢያት መካከል የመጀመሪያው ሳሙኤል ነው።—የሐዋርያት ሥራ 3:24