የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2022 Christian Congregation of Jehovah’s Witnesses
ከጥር 2-8
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ነገሥት 22–23
“ትሑት መሆን ያለብን ለምንድን ነው?”
ትሑት የነበረው ኢዮስያስ የይሖዋን ሞገስ አግኝቷል
መቅደሱን የሚያድሱት ሠራተኞቹ ከማለዳ አንስተው በትጋት ሥራቸውን አከናወኑ። ኢዮስያስ ክፉ የነበሩት አንዳንድ የቀድሞ አባቶቹ በአምላክ ቤት ላይ ያደረሱትን ጥፋት ሠራተኞቹ መልሰው በማደሳቸው ይሖዋን ባለ ውለታው አድርጎ እንደተመለከተው ጥርጥር የለውም። ሥራው በመፋጠን ላይ ሳለ ሳፋን ሪፖርት ሊያደርግ መጣ። በእጁ የያዘው ምንድን ነው? አንድ የሆነ ጥቅልል ይዟል! ሳፋን ሊቀ ካህኑ ኬልቅያስ “በሙሴ እጅ የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ” እንዳገኘ ነገረው። (2 ዜና መዋዕል 34:12-18) የሚያስደንቅ ነው፤ የተገኘው የሕጉ የመጀመሪያ ቅጂ መሆኑ ጥርጥር የለውም!
ኢዮስያስ መጽሐፉ ምን እንደሚል የመስማት ጉጉት አደረበት። ሳፋን ሲያነብብለት ንጉሡ እሱም ሆነ ሕዝቡ እያንዳንዱን ትእዛዝ እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ያወጣ ያወርድ ነበር። በተለይ ደግሞ መጽሐፉ ስለ እውነተኛው አምልኮ በአጽንዖት ስለሚናገር እንዲሁም ሕዝቡ የሐሰት አምልኮን ከተከተለ መቅሰፍት እንደሚደርስበትና በግዞት እንደሚወሰድ ትንቢት እንደሚናገር ሲገነዘብ በጣም ተገረመ። ኢዮስያስ የአምላክን ትእዛዛት በጥብቅ እንዳልተከተሉ ሲገነዘብ ልብሱን ቀደደና ለኬልቅያስ፣ ለሳፋን እንዲሁም ለሌሎቹ ‘አባቶቻችን በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ቃል ሁሉ ስላልጠበቁ የይሖዋ ቁጣ በላያችን በጣም ስለነደደ ሄዳችሁ ስለተገኘው የመጽሐፍ ቃል ይሖዋን ጠይቁ’ የሚል ትእዛዝ ሰጣቸው።—2 ነገሥት 22:11-13፤ 2 ዜና መዋዕል 34:19-21
ትሑት የነበረው ኢዮስያስ የይሖዋን ሞገስ አግኝቷል
የኢዮስያስ መልእክተኞች በኢየሩሳሌም ወደምትኖረው ወደ ነቢይቱ ሕልዳና ሄደው መልስ ይዘው መጡ። ሕልዳና አዲስ በተገኘው መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው መቅሰፍት በከሃዲው ብሔር ላይ እንደሚደርስ በመጠቆም የይሖዋን ቃል አስተላለፈች። ይሁን እንጂ ኢዮስያስ በይሖዋ ፊት ትሑት ሆኖ ስለተገኘ መቅሰፍቱ አያገኘውም። በሰላም ወደ አባቶቹ ይሰበሰባል።—2 ነገሥት 22:14-20፤ 2 ዜና መዋዕል 34:22-28
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ምንም ዓይነት አስተዳደግ ይኑርህ ስኬታማ መሆን ትችላለህ
ኢዮስያስ በመጥፎ ሁኔታዎች ሥር ቢያድግም በይሖዋ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር ማድረጉን ቀጠለ። የንግሥናው ዘመን እጅግ ስኬታማ ከመሆኑ የተነሣ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይናገርለታል፦ “እንደ ሙሴም ሕግ ሁሉ በፍጹም ልቡ በፍጹምም ነፍሱ በፍጹምም ኃይሉ ወደ እግዚአብሔር የተመለሰ እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ ከእርሱ አስቀድሞ አልነበረም፤ እንደ እርሱም ያለ ንጉሥ ከእርሱ በኋላ አልተነሣም።”—2 ነገሥት 23:19-25
በልጅነታቸው አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ላደጉ ግለሰቦች የኢዮስያስ ምሳሌ ምንኛ አበረታች ነው! ከእርሱ ምሳሌ ምን ልንማር እንችላለን? ኢዮስያስ ትክክለኛውን ጎዳና እንዲመርጥና በዚያው ጎዳና መጓዙን እንዲቀጥል የረዳው ምንድን ነው?
ከጥር 9-15
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ነገሥት 24–25
“የጥድፊያ ስሜታችሁ እንዳይጠፋ ተጠንቀቁ”
የይሖዋ የፍርድ ቀን ቀርቧል!
2 ሶፎንያስ በድፍረት የተናገረው ትንቢት ወጣቱ ኢዮስያስ የይሁዳን ምድር ከርኩስ አምልኮ ማጽዳቱ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይበልጥ ሳያስገነዝበው አልቀረም። ይሁን እንጂ ንጉሡ ምድሪቱን ከሐሰት ሃይማኖት ለማጥራት የወሰደው እርምጃ ከሕዝቡ መካከል ክፋትን ጨርሶ ለማስወገድም ሆነ ‘ኢየሩሳሌምን በንጹሕ ደም የሞላው’ አያቱ ንጉሥ ምናሴ ለሠራው ኃጢአት ሥርየት ሊያስገኝ አልቻለም። (2 ነገሥት 24:3, 4፤ 2 ዜና መዋዕል 34:3) ስለዚህ የይሖዋ የፍርድ ቀን መምጣቱ የማይቀር ነበር።
የኤርምያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
ወቅቱ 607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሆን ሴዴቅያስ ንግሥናውን ከያዘ 11ኛ ዓመቱ ነው። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ለአንድ ዓመት ተኩል ከብቧታል። ናቡከደነፆር በነገሠ በ19ኛው ዓመት፣ በአምስተኛው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የክብር ዘብ ሰራዊት አዛዥ የሆነው ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም “መጣ።” (2 ነገሥት 25:8) ምናልባትም ናቡዘረዳን ከከተማዋ ቅጥር ውጪ ባለው የጦር ሰፈሩ ሆኖ ሁኔታውን ሳያጠናና ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት እቅድ ሳያወጣ አልቀረም። ከሦስት ቀን በኋላም ማለትም ወሩ በገባ በአሥረኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም “መጣ [“ገባ፣” የ1980 ትርጉም]።” ከዚያም ከተማይቱን በእሳት አጋያት።—ኤርምያስ 52:12, 13
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የሁለተኛ ነገሥት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
24:3, 4፦ ምናሴ ደም በማፍሰሱ የተነሳ ይሖዋ ለይሁዳ “ይቅርታ ለማድረግ አልፈለገም።” አምላክ ለንጹሐን ደም አክብሮት አለው። ይሖዋ ለደም መፍሰሱ ተጠያቂ የሆኑትን በማጥፋት የንጹሐንን ደም እንደሚበቀል እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—መዝሙር 37:9-11፤ 145:20
ከጥር 16-22
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ዜና መዋዕል 1–3
“መጽሐፍ ቅዱስ—ልብወለድ ወይስ እውነተኛ ታሪክ?”
አዳም እና ሔዋን በሕይወት የኖሩ ሰዎች ነበሩ?
የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሆኑት በአንደኛ ዜና መዋዕል ከምዕራፍ 1 እስከ 9 እንዲሁም በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ላይ የሚገኙትን የአይሁዳውያንን የዘር ሐረግ ዝርዝሮች እንደ ምሳሌ እንመልከት። በአንደኛ ዜና መዋዕል ላይ 48 ትውልዶች በሉቃስ ዘገባ ላይ ደግሞ 75 ትውልዶች ምንም ሳይጎድል በዝርዝር ተቀምጠዋል። የሉቃስ ዘገባ ያተኮረው በኢየሱስ ክርስቶስ የዘር ሐረግ ላይ ሲሆን በዜና መዋዕል ላይ የሰፈረው ዘገባ ያተኮረው ደግሞ በእስራኤል ብሔር ውስጥ ነገሥታትና ካህናት ሆነው ባገለገሉ ሰዎች የዘር ሐረግ ላይ ነው። በሁለቱም የዘር ሐረግ ዝርዝሮች ውስጥ አዳምን ጨምሮ እንደ ሰለሞን፣ ዳዊት፣ ያዕቆብ፣ ይስሐቅ፣ አብርሃምና ኖኅ ያሉ ታዋቂ ሰዎች ተጠቅሰዋል። በሁለቱም የዘር ሐረግ ዝርዝሮች ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች በሕይወት የነበሩ ናቸው፤ የእነዚህ ሰዎች መገኛ እንደሆነ የተጠቀሰው አዳምም በሕይወት የኖረ ሰው ነው።
ኖኅ እና የጥፋት ውኃ አፈ ታሪክ ነው ወይስ እውነተኛ ታሪክ?
ስለ ትውልድ ሐረግ የሚዘረዝሩ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች፣ ኖኅ በእርግጥ በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑን ያረጋግጣሉ። (1 ዜና መዋዕል 1:4፤ ሉቃስ 3:36) እነዚህን ዘገባዎች ያጠናቀሩት ዕዝራና ሉቃስ ደግሞ ጠንቃቃ ጸሐፊዎች ነበሩ። ሉቃስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው በኖኅ የዘር ሐረግ በኩል እንደሆነ ጽፏል።
አዳም እና ሔዋን በሕይወት የኖሩ ሰዎች ነበሩ?
ቤተ ክርስቲያን የሚያዘወትሩ በርካታ ሰዎች በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማቸውን ስለ ቤዛው የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንደ ምሳሌ እንመልከት። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ከኃጢአት ለማንጻት ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ እንደሰጠ ይናገራል። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16) ሁላችንም እንደምናውቀው ቤዛ የሚያመለክተው አንድ ሰው የጠፋበትን ወይም ያጣውን ነገር ለማስመለስ ወይም እንደገና ለመግዛት የሚከፍለውን ተመጣጣኝ ዋጋ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “ተመጣጣኝ ቤዛ” እንደሆነ አድርጎ የሚገልጸው ለዚህ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:6) ኢየሱስ የሚመጣጠነው ከምን ነገር ጋር ነው ብለን እንጠይቅ ይሆናል? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት መልስ ይሰጣል፦ “ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ ልክ እንደዚሁም ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉ።” (1 ቆሮንቶስ 15:22) ኢየሱስ ታዛዥ የሆኑትን የሰው ዘሮች ለመቤዠት የከፈለው ፍጹም ሕይወት አዳም በኤደን ገነት ኃጢአት በሠራ ጊዜ ካጣው ፍጹም ሕይወት ጋር ተመጣጣኝ ነው። (ሮም 5:12) አዳም በሕይወት የኖረ ሰው ካልነበረ የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ምንም ትርጉም እንደማይኖረው በግልጽ መመልከት ይቻላል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 911 አን. 3-4
የዘር ሐረግ ዝርዝር
የሴቶች ስም። ከታሪክ ጋር የተያያዘ ምክንያት በሚኖርበት ጊዜ የሴቶች ስም አልፎ አልፎ በዘር ሐረግ ዝርዝር ውስጥ ይካተት ነበር። በዘፍጥረት 11:29, 30 ላይ ሦራ (ሣራ) ተጠቅሳለች፤ ይህ የሆነው ተስፋ የተሰጠበት ዘር የሚመጣው በሌላ የአብርሃም ሚስት በኩል ሳይሆን በእሷ በኩል እንደሆነ ለማመልከት መሆን አለበት። በዚያው ዘገባ ላይ ሚልካ የተጠቀሰችው የይስሐቅ ሚስት የሆነችው የርብቃ አያት ስለሆነች ሊሆን ይችላል፤ ይህም ርብቃ ከአብርሃም ዘመዶች መስመር እንደመጣች ያሳያል፤ ምክንያቱም ይስሐቅ ከሌሎች ብሔራት ሚስት ማግባት አልነበረበትም። (ዘፍ 22:20-23፤ 24:2-4) በዘፍጥረት 25:1 ላይ አብርሃም በኋላ ያገባት ሚስቱ ኬጡራ ተጠቅሳለች። ይህም አብርሃም፣ ሣራ ከሞተች በኋላ ትዳር እንደመሠረተና ይሖዋ በተአምራዊ መንገድ ልጅ እንዲወልድ ካስቻለው ከ40 ዓመት በኋላም ሌሎች ልጆች ማፍራት እንደቻለ ያሳያል። (ሮም 4:19፤ ዘፍ 24:67፤ 25:20) በተጨማሪም ምድያምና ሌሎች የአረብ ጎሳዎች ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ዝምድና ያሳያል።
ሊያ፣ ራሔልና የያዕቆብ ቁባቶች ከልጆቻቸው ጋር ተጠቅሰዋል። (ዘፍ 35:21-26) ይህም አምላክ ከጊዜ በኋላ እነዚህን ልጆች የያዘበትን መንገድ ለመረዳት ያስችለናል። የሌሎች ሴቶችም ስም በዘር ሐረግ ዝርዝር ውስጥ የተካተተው በተመሳሳይ ምክንያቶች የተነሳ ነው። ውርስ የሚተላለፈው በእነሱ በኩል ከሆነ ስማቸው ሊካተት ይችላል። (ዘኁ 26:33) እርግጥ የትዕማር፣ የረዓብና የሩት ሁኔታ ለየት ያለ ነው። እነዚህ ሴቶች የመሲሑ የኢየሱስ ክርስቶስ የዘር ሐረግ ውስጥ የተካተቱበት መንገድ አስደናቂ ነው። (ዘፍ 38፤ ሩት 1:3-5፤ 4:13-15፤ ማቴ 1:1-5) በዘር ሐረግ ዝርዝር ውስጥ የተጠቀሱ ሌሎች ሴቶችን በ1 ዜና መዋዕል 2:35, 48, 49፤ 3:1-3, 5 ላይ ማግኘት ይቻላል።
ከጥር 23-29
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ዜና መዋዕል 4–6
“ጸሎቴ ስለ እኔ ምን ይናገራል?”
‘ጸሎትን የሚሰማ’
ያቤጽ የጸሎት ሰው ነበር። ያቤጽ ጸሎቱን የጀመረው የአምላክን በረከት ለማግኘት በመለመን ነው። ከዚያም በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት እንዳለው የሚያሳዩ ሦስት ልመናዎችን አቀረበ።
በመጀመሪያ “ግዛቴንም እንድታሰፋ እለምንሃለሁ” ሲል አምላክን ተማጽኗል። (ቁጥር 10) ይህ የተከበረ ሰው የባልንጀራውን መሬት የሚመኝ ስግብግብ አልነበረም። ከልቡ ያቀረበው ይህ ልመና ይዞታን ሳይሆን ሰዎችን የሚመለከት ሊሆን ይችላል። ምናልባት እውነተኛውን አምላክ የሚያመልኩ በርካታ ሰዎችን መያዝ የሚችል ይዞታ እንዲኖረው ግዛቱ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲሰፋለት መጠየቁ ሊሆን ይችላል።
ቀጥሎም ያቤጽ የአምላክ “እጅ” ከእሱ ጋር እንዲሆን ልመና አቅርቧል። የአምላክ እጅ ሲባል በሥራ ላይ የዋለውን ኃይሉን ያመለክታል፤ ይሖዋ አገልጋዮቹን ለመርዳት በዚህ ኃይል ይጠቀማል። (1 ዜና መዋዕል 29:12) ያቤጽ የለመነውን ነገር ለማግኘት ዘወር ያለው ወደ አምላክ ሲሆን ይሖዋም በእሱ ላይ እምነት ያላቸውን ሰዎች ፍላጎት ለማሟላት እጁ አጭር አይደለም።—ኢሳይያስ 59:1
በሦስተኛ ደረጃ ያቤጽ “እንዳያሳዝነኝም ከክፋት ጠብቀኝ” (የ1954 ትርጉም) በማለት ጸልዮአል። “እንዳያሳዝነኝ” የሚለው አገላለጽ ያቤጽ የጸለየው መከራ እንዳይደርስበት ሳይሆን ክፋት በሚያስከትለው ነገር እንዳያዝን ወይም እንዳይሸነፍ መሆኑን ሊያመለክት ይችላል።
ያቤጽ ያቀረበው ጸሎት ከእውነተኛው አምልኮ ጋር የተያያዙ ነገሮች እንደሚያሳስቡት እንዲሁም ጸሎት ሰሚ በሆነው አምላክ ላይ እምነት እንዳለው በግልጽ ያሳያል። ታዲያ ይሖዋ ምን መልስ ሰጠው? ይህ አጭር ዘገባ ታሪኩን የሚቋጨው “እግዚአብሔርም የለመነውን ሰጠው” በማለት ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአንደኛ ዜና መዋዕል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
5:10, 18-22፦ በሳኦል ዘመነ መንግሥት ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የነበሩት ነገዶች ቁጥር በጊዜው ከነበሩት አጋራውያን በግማሽ የሚያንስ ቢሆንም እንኳ ድል ነስተዋል። ይህ የሆነበት ምክንያት በእነዚያ ነገዶች ውስጥ ያሉ ደፋር ሰዎች በይሖዋ ላይ ይተማመኑና የእርሱንም እርዳታ ለማግኘት ይጠባበቁ ስለነበር ነው። እኛም በቁጥር እጅግ ከሚበልጡን ጠላቶቻችን ጋር መንፈሳዊ ውጊያ የምናደርግ እንደ መሆናችን መጠን በይሖዋ ላይ ሙሉ ትምክህት ይኑረን።—ኤፌሶን 6:10-17
ከጥር 30–የካቲት 5
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ዜና መዋዕል 7–9
“በይሖዋ እርዳታ ተፈታታኝ ኃላፊነቶችን መወጣት ትችላላችሁ”
የአንደኛ ዜና መዋዕል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
9:26, 27፦ ሌዋውያን በር ጠባቂዎች ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር። ቅዱስ ወደሆኑት የቤተ መቅደሱ ሥፍራዎች የሚያስገባው በር ቁልፍ ተሰጥቷቸው ነበር። በራፎቹን በየዕለቱ በመክፈት ታማኝ መሆናቸውን አስመስክረዋል። እኛም በክልላችን ለሚገኙ ሰዎች የመስበክና ይሖዋን ወደ ማምለክ እንዲደርሱ የመርዳት ኃላፊነት በአደራ ተሰጥቶናል። ታዲያ እኛስ እንደ ሌዋውያኑ በር ጠባቂዎች እምነት የሚጣልብን መሆን አይገባንም?
አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟችሁ እንደ ፊንሐስ ዓይነት እርምጃ ትወስዳላችሁ?
ፊንሐስ በጥንቷ እስራኤል ከባድ ኃላፊነት የነበረበት ሰው ቢሆንም በድፍረት፣ በማስተዋልና በአምላክ ላይ በመታመን የገጠሙትን አስቸጋሪ ሁኔታዎች በብቃት መወጣት ችሏል። ፊንሐስ የአምላክን ጉባኤ ለመንከባከብ ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረጉ የአምላክን ሞገስ አስገኝቶለታል። ከ1,000 ዓመታት ገደማ በኋላ ዕዝራ በመንፈስ መሪነት “በቀድሞ ጊዜ የበር ጠባቂዎቹ አለቃ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ” በማለት ጽፏል። (1 ዜና 9:20) አምላክ፣ በዛሬው ጊዜ ሕዝቦቹን ግንባር ቀደም ሆነው ከሚመሩት ወንድሞችም ሆነ እሱን በታማኝነት ከሚያገለግሉት ክርስቲያኖች ሁሉ ጋር እንዲሆን ምኞታችን ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ለይሖዋ ዘምሩ!
6 አዎ፣ ይሖዋ አገልጋዮቹ በመዝሙር እንዲያወድሱት በነቢያቱ በኩል ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። እንዲያውም መዘምራኑ ሙዚቃ ለማቀናበር በተለይ ደግሞ ልምምድ ለማድረግ በቂ ጊዜ እንዲያገኙ ሲባል ሌሎች ሌዋውያን ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች ነፃ እንዲሆኑ ተደርገው ነበር።—1 ዜና 9:33
ከየካቲት 6-12
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ዜና መዋዕል 10–12
“የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ያላችሁን ፍላጎት አጠናክሩ”
“ፈቃድህን እንድፈጽም አስተምረኝ”
12 ዳዊት በሕጉ ውስጥ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በመረዳትና ከዚህ ጋር በሚስማማ መልኩ በመመላለስ ረገድ ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ዳዊት ‘ከቤተልሔም በር አቅራቢያ ከሚገኘው ጕድጓድ የሚጠጣ ውኃ’ ማግኘት እንደሚፈልግ በተናገረ ወቅት የተከናወነውን ነገር እንመልከት። ከዳዊት ሰዎች መካከል ሦስቱ በፍልስጤማውያን ሠራዊት ወደተያዘችው ከተማ ሰንጥቀው በመግባት ውኃውን ቀድተው ተመለሱ። “እርሱ ግን ሊጠጣው ስላልፈለገ በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሰው።” ለምን? ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ከማድረግ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ፤ ይህ በሕይወታቸው ቈርጠው የሄዱትን የእነዚህን ሰዎች ደም እንደ መጠጣት አይደለምን?”—1 ዜና 11:15-19
13 ዳዊት ደም በይሖዋ ፊት መፍሰስ እንጂ መበላት እንደሌለበት ከሕጉ ተረድቶ ነበር። ይህ የሚደረገውም ለምን እንደሆነ እንደሚያውቅ ጥርጥር የለውም። ዳዊት “የፍጡር ሕይወት በደሙ ውስጥ” መሆኑን ያውቃል። ይሁንና ያመጡለት ውኃ እንጂ ደም አይደለም። ታዲያ ዳዊት ለመጠጣት ያልፈለገው ለምንድን ነው? እንዲህ ያደረገው ከሕጉ በስተጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት ተረድቶ ስለነበር ነው። ዳዊት ውኃውን የተመለከተው ክቡር እንደሆነው እንደ ሦስቱ ሰዎች ደም አድርጎ ነው። በመሆኑም ዳዊት ውኃውን መጠጣት ፈጽሞ የማያስበው ነገር ነበር። ውኃውን ከመጠጣት ይልቅ መሬት ላይ ማፍሰስ እንዳለበት ተሰምቶታል።—ዘሌ. 17:11፤ ዘዳ. 12:23, 24
የአምላክን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በመጠቀም ሕሊናችሁን አሠልጥኑ
5 የአምላክ ሕጎች ሕሊናችንን እንዲያሠለጥኑት፣ እነዚህን ሕጎች ከማንበብ ወይም ከማወቅ ያለፈ ነገር ማድረግ ያስፈልገናል። ለሕጎቹ ፍቅርና አክብሮት ማዳበር ይኖርብናል። የአምላክ ቃል “ክፉ የሆነውን ጥሉ፤ መልካም የሆነውንም ውደዱ” ይላል። (አሞጽ 5:15) ይሁንና እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ቁልፉ፣ ይሖዋ ለነገሮች ያለው ዓይነት አመለካከት ማዳበር ነው። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፦ እንቅልፍ አልወስድ ብሎህ ተቸግረሃል እንበል። ሐኪምህ ጤናማ የአመጋገብ ልማድ እንዲኖርህ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንድታደርግና በሕይወትህ ውስጥ ሌሎች አስፈላጊ ለውጦችን እንድታደርግ የሚረዳህ ጠቃሚ ምክር ሰጠህ። ምክሩን በተግባር ስታውል ጥሩ እንቅልፍ መተኛት ቻልክ! ሐኪሙ ላደረገልህ እርዳታ በጣም አመስጋኝ እንደምትሆን ጥርጥር የለውም።
6 በተመሳሳይም ፈጣሪያችን የሰጠን ሕጎች ኃጢአት መሥራት ከሚያስከትለው መዘዝ ይጠብቁናል፤ እንዲሁም የተሻለ ሕይወት እንድንመራ ይረዱናል። ለምሳሌ ከውሸት፣ ከማጭበርበር፣ ከስርቆት፣ ከፆታ ብልግና፣ ከዓመፅ እንዲሁም ከመናፍስታዊ ድርጊቶች እንድንርቅ የሚመክሩንን የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎች መታዘዛችን ምን ያህል እንደሚጠቅመን እናስብ። (ምሳሌ 6:16-19ን አንብብ፤ ራእይ 21:8) የይሖዋን መመሪያዎች መከተል የሚያስገኘውን ታላቅ ጥቅም በሕይወታችን ውስጥ ስንመለከት ለይሖዋም ሆነ ለሕጎቹ ያለን ፍቅርና አድናቆት እየጨመረ እንደሚሄድ ጥርጥር የለውም።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 1058 አን. 5-6
ልብ
“በሙሉ ልብ” ማገልገል። ሥጋዊው ልብ ሥራውን በትክክል እንዲያከናውን ሙሉ መሆን አለበት፤ ምሳሌያዊው ልብ ግን ሊከፋፈል ይችላል። ዳዊት “ስምህን እፈራ ዘንድ ልቤን አንድ አድርግልኝ” በማለት መጸለዩ የአንድ ሰው ልብ ከሚወዳቸውና ከሚፈራቸው ነገሮች ጋር በተያያዘ ሊከፋፈል እንደሚችል ይጠቁማል። (መዝ 86:11) እንዲህ ያለው ሰው “ግማሽ ልብ” ሊኖረው ማለትም በይሖዋ አምልኮ ረገድ ለብ ያለ ሊሆን ይችላል። (መዝ 119:113፤ ራእይ 3:16) አንድ ሰው “መንታ ልብ” (ቃል በቃል ልብና ልብ) ሊኖረውም ይችላል፤ እንዲህ ያለው ሰው ሁለት ጌቶችን ለማገልገል ሊሞክር ወይም አንድ ነገር እያሰበ ሌላ ነገር በመናገር ሊያጭበረብር ይችላል። (1ዜና 12:33 ግርጌ፤ መዝ 12:2 ግርጌ) ኢየሱስ እንዲህ ያለውን ግብዝነት አጥብቆ አውግዟል።—ማቴ 15:7, 8
አምላክን ማስደሰት የሚፈልግ ሰው በግማሽ ልብ ወይም በመንታ ልብ ሳይሆን በሙሉ ልብ ሊያገለግለው ይገባል። (1ዜና 28:9) ልብ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ የማይመለስና ወደ ክፋት ያዘነበለ ከመሆኑ አንጻር እንዲህ ማድረግ ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል። (ኤር 17:9, 10፤ ዘፍ 8:21) ልባዊ ጸሎት ማቅረብ (መዝ 119:145፤ ሰቆ 3:41)፣ አዘውትሮ የአምላክን ቃል ማጥናት (ዕዝራ 7:10፤ ምሳሌ 15:28)፣ ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ በቅንዓት መካፈል (ከኤር 20:9 ጋር አወዳድር) እንዲሁም በይሖዋ ፊት ሙሉ ልብ ካላቸው ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ሙሉ ልብ ለመያዝ ይረዳል።—ከ2ነገ 10:15, 16 ጋር አወዳድር።
ከየካቲት 13-19
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ዜና መዋዕል 13–16
“መመሪያ መከተል ለስኬት ያበቃል”
“ይሖዋ ወዴት አለ?” ብለህ ትጠይቃለህን?
12 የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ እስራኤል ተመልሶ ለበርካታ ዓመታት በቂርያትይዓሪም ከተቀመጠ በኋላ ንጉሥ ዳዊት ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት ፈለገ። ከሕዝቡ አለቆች ጋር ከተማከረ በኋላ ‘ነገሩ መልካም መስሎ ከታያቸውና የይሖዋም ፈቃድ ከሆነ’ ታቦቱን እንደሚያመጣው ተናገረ። ሆኖም በዚህ ጉዳይ ላይ የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማወቅ በቂ ምርምር አላደረገም። እንደዚያ አድርጎ ቢሆን ኖሮ ታቦቱ በሰረገላ ላይ ባልተጫነ ነበር። ከዚህ ይልቅ አምላክ በግልጽ በሰጠው መመሪያ መሠረት ከቀዓት ወገን የሆኑ ሌዋውያን ይሸከሙት ነበር። ዳዊት በተደጋጋሚ ይሖዋን ይጠይቅ የነበረ ቢሆንም በዚህ ወቅት ግን በተገቢው መንገድ አልፈለገውም። ውጤቱም አሳዛኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ዳዊት “እንደ ሥርዓቱም አልፈለግነውምና አምላካችን እግዚአብሔር በመካከላችን ስብራት አደረገ” በማለት ተናግሯል።—1 ዜና መዋዕል 13:1-3፤ 15:11-13፤ ዘኍልቍ 4:4-6, 15፤ 7:1-9
“ይሖዋ ወዴት አለ?” ብለህ ትጠይቃለህን?
13 ሌዋውያን ታቦቱን ተሸክመው ከአቢዳራ ቤት ወደ ኢየሩሳሌም ባመጡት ጊዜ ዳዊት ያቀናበረው መዝሙር ተዘመረ። በመዝሙሩ ውስጥ “እግዚአብሔርን ፈልጉት፣ . . . ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። . . . የሠራትን ድንቅ አስቡ፣ ተአምራቱንም የአፉንም ፍርድ” የሚለው ከልብ የመነጨ ማሳሰቢያ ይገኝበታል።—1 ዜና መዋዕል 16:11-13
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የዘላለሙን ንጉሥ ይሖዋን አምልኩ
14 ዳዊት ቅዱስ የሆነውን የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው። በዚህ አስደሳች ወቅት ሌዋውያኑ አንድ ትኩረት የሚስብ የውዳሴ መዝሙር ዘምረው ነበር፤ በ1 ዜና መዋዕል 16:31 ላይ ‘በአሕዛብ መካከል “ይሖዋ ነገሠ!” ብላችሁ አስታውቁ’ ብለው እንደዘመሩ ተጠቅሷል። ይሁንና አንድ ሰው ‘ይሖዋ የዘላለም ንጉሥ ነው፤ ታዲያ በዚያ ወቅት ነገሠ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። ይሖዋ ነገሠ ሊባል የሚችለው ገዢነቱን ሲያሳይ ወይም በሆነ ጊዜ ላይ እሱን የሚወክል ወይም አንድን ሁኔታ የሚያከናውን ወኪል ሲሾም ነው። ይህ የይሖዋ ንግሥና መገለጫ ትልቅ ትርጉም አለው። ዳዊት ከመሞቱ በፊት ይሖዋ “በእግርህ እንዲተካ ከአብራክህ የተከፈለ ዘር አስነሣልሃለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ” በማለት ንግሥናው ለዘላለም እንደሚቀጥል ቃል ገብቶለት ነበር። (2 ሳሙ. 7:12, 13) የኋላ ኋላ፣ ይህ የዳዊት “ዘር” ከ1,000 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ተገለጠ። ዘሩ ማን ሆኖ ተገኘ? የነገሠውስ መቼ ነው?
ከየካቲት 20-26
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ዜና መዋዕል 17–19
“ቅር የሚያሰኝ ሁኔታ ቢያጋጥማችሁም ደስታችሁን ጠብቁ”
በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ባለው መልካም ነገር ላይ አተኩሩ
በጥንቷ እስራኤል ይኖር የነበረው ዳዊት በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከተጠቀሱት ግሩም ሰዎች መካከል አንዱ ነው። እረኛ፣ ሙዚቀኛ፣ ነቢይና ንጉሥ የነበረው ይህ ሰው በይሖዋ አምላክ ላይ ሙሉ በሙሉ ይታመን ነበር። ዳዊት ከይሖዋ ጋር የነበረው የቅርብ ወዳጅነት ለአምላክ ቤት የመሥራት ፍላጎት አሳድሮበታል። እንዲህ ያለው ቤት ወይም ቤተ መቅደስ በእስራኤል የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል ሆኖ ያገለግላል። ዳዊት ቤተ መቅደሱም ሆነ በውስጡ የሚከናወኑት ተግባሮች ለአምላክ ሕዝብ ደስታና በረከት እንደሚያመጡ ያውቅ ነበር። በመሆኑም እንዲህ ሲል ዘምሯል፦ “አንተ [ይሖዋ] የመረጥሃቸውና በተቀደሰ አደባባይህ እንዲኖሩ ወደ ራስህ ያቀረብሃቸው፥ ደስ ይበላቸው፤ እኛም ከቤትህ በሚገኘው መልካም ነገርና ከመቅደስህ በሚገኘው በረከት እንረካለን።”—መዝሙር 65:4 የ1980 ትርጉም
ባገኛችኋቸው መብቶች ተደሰቱ
11 እኛም በተመሳሳይ በይሖዋ አገልግሎት በተሰጠን በማንኛውም ሥራ ላይ ትኩረታችንን ሙሉ በሙሉ በማሳረፍ ደስታችንን መጨመር እንችላለን። በስብከቱ ሥራ ‘በእጅጉ ተጠመድ’፤ እንዲሁም በጉባኤ እንቅስቃሴዎች ሙሉ ተሳትፎ አድርግ። (ሥራ 18:5፤ ዕብ. 10:24, 25) በስብሰባዎች ላይ የሚያንጹ ሐሳቦች መስጠት እንድትችል በሚገባ ተዘጋጅ። በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ የተሰጠህን ማንኛውንም የተማሪ ክፍል በቁም ነገር ተመልከተው። በጉባኤ ውስጥ አንድ ሥራ ከተሰጠህ ሥራህን በጊዜው አከናውን፤ እንዲሁም እምነት የሚጣልብህ ሁን። በጉባኤ ውስጥ የተሰጠህን የትኛውንም ሥራ ሳትንቅ ጊዜ ሰጥተህ አከናውን። በተመደብክበት ሥራ ችሎታህን ለማሻሻል ጥረት አድርግ። (ምሳሌ 22:29) በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እና በተሰጡህ ኃላፊነቶች ላይ ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ እንዲያርፍ ካደረግህ እድገትህ ይፋጠናል፤ ደስታህም ይጨምራል። (ገላ. 6:4) በተጨማሪም አንተ ለማግኘት የምትመኘውን መብት ሌሎች ሰዎች ቢያገኙ ከእነሱ ጋር አብረህ መደሰት ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል።—ሮም 12:15፤ ገላ. 5:26
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
w20.02 12 ሣጥን
አባታችንን ይሖዋን በጣም እንወደዋለን
ይሖዋ እኔን ትኩረት ሰጥቶ ይመለከተኛል?
‘በምድር ላይ ካሉት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ይሖዋ እኔን ትኩረት ሰጥቶ የሚመለከትበት ምን ምክንያት አለ?’ ብለህ ራስህን ጠይቀህ ታውቃለህ? ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ንጉሥ ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ታስተውለው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ቦታ ትሰጠውስ ዘንድ ሟች የሆነው የሰው ልጅ ምንድን ነው?” (መዝ. 144:3) ዳዊት፣ ይሖዋ በደንብ እንደሚያውቀው እርግጠኛ ነበር። (1 ዜና 17:16-18) ዛሬም ይሖዋ ለእሱ ያለህን ፍቅር እንደሚያስተውል በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት ያረጋግጥልሃል። በዚህ እንድትተማመን የሚያደርጉ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ሐሳቦችን እስቲ እንመልከት፦
• ይሖዋ ከመወለድህ በፊት እንኳ አውቆሃል።—መዝ. 139:16
• ይሖዋ ስሜትህንና ሐሳብህን ያውቃል።—1 ዜና 28:9
• ይሖዋ የምታቀርበውን ጸሎት በሙሉ እሱ ራሱ ያዳምጣል።—መዝ. 65:2
• የምታደርገው ነገር ይሖዋን ሊያስደስተው ወይም ሊያሳዝነው ይችላል።—ምሳሌ 27:11
• ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ወደ ራሱ ስቦሃል።—ዮሐ. 6:44
• ይሖዋ በደንብ ስለሚያውቅህ ከሞት ሊያስነሳህ ይችላል። የቀድሞህን የሚመስል አካል ይሰጥሃል፤ እንዲሁም ከሞት የምትነሳው ትዝታዎችህንና የማንነትህ መለያ የሆኑ ባሕርያትህን ጨምሮ በአእምሮህ ያከማቸኸውን መረጃ በሙሉ ይዘህ ነው።—ዮሐ. 11:21-26, 39-44፤ ሥራ 24:15
ከየካቲት 27–መጋቢት 5
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ዜና መዋዕል 20–22
“ወጣቶች እንዲሳካላቸው እርዷቸው”
እነዚህን ነገሮች “ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ”
8 አንደኛ ዜና መዋዕል 22:5ን አንብብ። ዳዊት ልጁ ሰለሞን እንዲህ ያለውን ከባድ ሥራ ለመምራት ብቁ እንዳልሆነ ሊያስብ ይችል ነበር። ምክንያቱም ቤተ መቅደሱ “እጅግ የሚያምር” መሆን ይኖርበታል፤ ሰለሞን ደግሞ በዚያ ወቅት ‘ገና ወጣትና ተሞክሮ የሌለው’ ነበር። ሆኖም ዳዊት፣ ሰለሞን የተሰጠውን ሥራ መወጣት እንዲችል ይሖዋ እንደሚረዳው ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም ግንባታውን ለመደገፍ ማከናወን በሚችለው ነገር ላይ ትኩረት በማድረግ ለግንባታው የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ በብዛት ማሰባሰብ ጀመረ።
እነዚህን ነገሮች “ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ”
7 ዳዊት ለቤተ መቅደሱ ግንባታ የሚመሰገነው እሱ እንደማይሆን ቢያውቅም ለግንባታው ድጋፍ ከመስጠት ወደኋላ አላለም። ደግሞም ሕንፃው የተጠራው የዳዊት ሳይሆን የሰለሞን ቤተ መቅደስ ተብሎ ነው። ዳዊት የልቡን ፍላጎት ማሳካት ባለመቻሉ አዝኖ ሊሆን ቢችልም የግንባታ ሥራውን ሙሉ በሙሉ ደግፏል። በራሱ ተነሳሽነት ግንባታውን የሚያከናውኑ ሠራተኞችን ያደራጀ ሲሆን ለግንባታው የሚሆን ብረት፣ መዳብ፣ ብር፣ ወርቅ እንዲሁም የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎችን አከማችቷል። በተጨማሪም ሰለሞንን እንዲህ በማለት አበረታቶታል፦ “አሁንም ልጄ ሆይ፣ ይሖዋ ከአንተ ጋር ይሁን፤ ስለ አንተም በተናገረው መሠረት ተሳክቶልህ የአምላክህን የይሖዋን ቤት ለመሥራት ያብቃህ።”—1 ዜና 22:11, 14-16
ወላጆች፣ ልጆቻችሁን እድገት አድርገው እንዲጠመቁ እየረዳችኋቸው ነው?
14 የጉባኤው መንፈሳዊ እረኞች የሆኑት ሽማግሌዎች፣ መንፈሳዊ ግቦች ማውጣት ያለውን ጥቅም ጎላ አድርገው በመግለጽ ወላጆችን ማገዝ ይችላሉ። ከ70 ለሚበልጡ ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለች አንዲት እህት የስድስት ዓመት ልጅ እያለች ወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስል የነገራት ነገር በሕይወቷ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ታስታውሳለች። ይህች እህት “ለ15 ደቂቃ ያህል ስለ መንፈሳዊ ግቦቼ አዋራኝ” ብላለች። በእርግጥም የሚያበረታታ ሐሳብ መናገር በሌሎች ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። (ምሳሌ 25:11) በተጨማሪም ሽማግሌዎች፣ በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ እንዲካፈሉ ወላጆችንና ልጆችን ሊጋብዟቸው እንዲሁም የልጆቹን ዕድሜና ችሎታ ያገናዘቡ ሥራዎችን ሊሰጧቸው ይችላሉ።
15 ሌሎች የጉባኤው አባላትም ለልጆች ተገቢ በሆነ መንገድ ትኩረት በመስጠት ወላጆችን ማገዝ ይችላሉ። ይህም ልጆቹ የሚያደርጉትን መንፈሳዊ እድገት ለማስተዋል ንቁ መሆንን ይጨምራል። አንድ ልጅ በሳምንቱ መካከል በሚደረገው ስብሰባ ላይ ክፍል አቅርቦ ወይም ከልብ የመነጨና ጥሩ ዝግጅት የተደረገበት ሐሳብ ሰጥቶ ይሆናል። አሊያም ደግሞ ያጋጠመውን ፈተና በታማኝነት ተወጥቶ ወይም በትምህርት ቤት ስለ እምነቱ መሥክሮ ሊሆን ይችላል። በእነዚህ ጊዜያት ለልጁ አድናቆታችሁን ከመግለጽ ወደኋላ አትበሉ። ከዚህም ሌላ ከስብሰባ በፊት ወይም በኋላ አንድን ወጣት ትኩረት ሰጥታችሁ ለማነጋገር ጥረት ማድረግ ትችላላችሁ። እነዚህንና ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም ልጆች ‘በታላቁ ጉባኤ’ ውስጥ ቦታ እንዳላቸው እንዲሰማቸው ማድረግ እንችላለን።—መዝ. 35:18
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአንደኛ ዜና መዋዕል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
21:13-15፦ ይሖዋ መቅሰፍቱ እንዲቆም ለመልአኩ ትእዛዝ የሰጠበት ምክንያት የሕዝቦቹ ስቃይ ስለተሰማው ነው። በእርግጥም የይሖዋ ‘ምህረት ታላቅ ነው።’