የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2023 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከመስከረም 4-10
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | አስቴር 1–2
“እንደ አስቴር ልካችሁን የምታውቁ ሁኑ”
ተፈታታኝ ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜም ልካችንን ማወቅ
11 ከልክ ያለፈ አድናቆት በሚቸረን ወይም ምስጋና በሚቀርብልን ጊዜም ልካችንን ማወቅ ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። አስቴር፣ የነበረችበት ሁኔታ በአንድ ጊዜ ሲቀየር የሰጠችውን ግሩም ምላሽ እንመልከት። አስቴር በጣም ውብ ሴት ነበረች፤ ለአንድ ዓመት ያህል ደግሞ ለየት ያለ የውበት እንክብካቤ አግኝታለች። ከመላው የፋርስ ግዛት ከመጡና የንጉሡን ትኩረት ለማግኘት ከሚፎካከሩ በርካታ ወጣት ሴቶች ጋር በየዕለቱ ትገናኝ ነበር። ያም ቢሆን አስቴር ምንጊዜም ሥርዓታማና ጭምት ሴት ነበረች። አርጤክስስ ንግሥት አድርጎ ከመረጣት በኋላም እንኳ ኩሩ ወይም ትዕቢተኛ አልሆነችም።—አስ. 2:9, 12, 15, 17
ለአምላክ ሕዝብ ጥብቅና ቆማለች
15 አስቴር ንጉሡ ፊት የምትቀርብበት ጊዜ ሲደርስ ራሷን ይበልጥ ለማስዋብ ያስፈልገኛል ብላ የምታስበውን ማንኛውንም ነገር የመጠየቅ ነፃነት ተሰጥቷት ነበር። እሷ ግን ሄጌ ከነገራት ውጭ ምንም ባለመጠየቅ ጭምት መሆኗን አሳይታለች። (አስ. 2:15) የንጉሡን ልብ ለመማረክ ውበት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ተገንዝባ ይሆናል፤ ልክን ማወቅና ትሕትና በዚያ ቤተ መንግሥት ውስጥ እምብዛም የማይታዩ ባሕርያት እንደሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ እንዲህ ዓይነት አመለካከት መያዟ ትክክል ነበር?
ተፈታታኝ ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜም ልካችንን ማወቅ
12 ልካችንን ማወቃችን ምንጊዜም ሥርዓታማ የሆነ አለባበስና አጋጌጥ እንዲኖረን እንዲሁም ተገቢ ምግባር እንድናሳይ ይረዳናል። የሰዎችን ልብ መማረክ የምንችለው ጉራ በመንዛት ወይም አላስፈላጊ ትኩረት ወደ ራሳችን በመሳብ ሳይሆን “የሰከነና ገር መንፈስ” በማሳየት እንደሆነ እንገነዘባለን። (1 ጴጥሮስ 3:3, 4ን አንብብ፤ ኤር. 9:23, 24) በልባችን ውስጥ የኩራት ስሜት ካለ ውሎ አድሮ በድርጊታችን መታየቱ አይቀርም። ለምሳሌ ያህል፣ ልዩ መብት እንዳለን፣ አንዳንድ ሚስጥሮችን እንደምናውቅ ወይም ኃላፊነት ካላቸው ወንድሞች ጋር የተለየ ቅርርብ እንዳለን ጠቆም እናደርግ ይሆናል። አሊያም ደግሞ የሌሎች አስተዋጽኦ ያለበት አንድ ሐሳብ ወይም ድርጊት የእኛ ብቻ እንደሆነ በሚያስመስል መልኩ ልናወራ እንችላለን። በዚህ ረገድም ቢሆን ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ኢየሱስ የተናገረው አብዛኛው ነገር በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተወሰደ ነበር። ኢየሱስ በንግግሩ ልኩን እንደሚያውቅ አሳይቷል፤ ይህን ያደረገው አድማጮቹ የሚናገረው ነገር በራሱ እውቀትና ጥበብ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን ከይሖዋ የመጣ እንደሆነ እንዲያውቁ ይፈልግ ስለነበር ነው።—ዮሐ. 8:28
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ይህን ያውቁ ኖሯል?
ተመራማሪዎች ማርዱካ (በአማርኛ መርዶክዮስ) የተባለ ሰው ስም የተጻፈበት የፋርስ የኪዩኒፎርም ጽሑፍ አገኙ። ይህ ሰው በሹሻን የሚሠራ ባለሥልጣን ምናልባትም የሒሳብ ባለሙያ ነበር። የምሥራቃውያን ታሪክ ሊቅ የሆኑት አርተር ኡንግናድ በወቅቱ የነበረው “ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ መርዶክዮስን የሚጠቅሰው ማመሣከሪያ” ይህ ኪዩኒፎርም ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።
እኚህ ምሁር ሪፖርታቸውን ከጻፉ ወዲህ ምሁራን በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች የፋርስ ኪዩኒፎርሞችን ተርጉመዋል። ከእነዚህ መካከል የፐርሰፖሊስ ጽላቶች ይገኙበታል፤ እነዚህ ጽላቶች የተገኙት በፐርሰፖሊስ ቅጥሮች አቅራቢያ በሚገኘው ግምጃ ቤት ፍርስራሾች ውስጥ ነው። ጽላቶቹ የተቀረጹት በቀዳማዊ ጠረክሲስ የግዛት ዘመን እንደሆነ ተደርሶበታል። ጽላቶቹ የተጻፉት በኤላም ቋንቋ ሲሆን በአስቴር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ስሞችን ይዘዋል።
በርካታ የፐርሰፖሊስ ጽላቶች በቀዳማዊ ጠረክሲስ የግዛት ዘመን በሹሻን የቤተ መንግሥት ጸሐፊ ሆኖ ይሠራ የነበረውን ማርዱካ የተባለውን ሰው ስም ይጠቅሳሉ። አንዱ ጽላት ማርዱካ ተርጓሚ እንደነበር ይናገራል። ይህ መረጃ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መርዶክዮስ ከሚሰጠው መግለጫ ጋር ይስማማል። መርዶክዮስ በንጉሥ አሐሽዌሮስ (ቀዳማዊ ጠረክሲስ) ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚሠራ ቢያንስ ሁለት ቋንቋዎችን የሚናገር ባለሥልጣን ነበር። መርዶክዮስ በሹሻን በሚገኘው ቤተ መንግሥት በንጉሡ በር አዘውትሮ ይቀመጥ ነበር። (አስ. 2:19, 21፤ 3:3) የንጉሡ በር የተባለው የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት የሚሠሩበት ትልቅ ሕንፃ ነው።
በጽላቶቹ ላይ በተጠቀሰው ማርዱካ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሰው መርዶክዮስ መካከል አስደናቂ ተመሳሳይነት አለ። የኖሩት በተመሳሳይ ዘመንና በተመሳሳይ ቦታ ሲሆን በተመሳሳይ የሥራ ቦታ ባለሥልጣን ሆነው አገልግለዋል። ይህ ሁሉ ተመሳሳይነት መኖሩ፣ ማርዱካ እና መርዶክዮስ አንድን ሰው ያመለክታል የሚል መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ሊያደርገን ይችላል።
ከመስከረም 11-17
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | አስቴር 3–5
“ሌሎች እምቅ ችሎታቸውን እንዲጠቀሙበት እርዷቸው”
it-2 431 አን. 7
መርዶክዮስ
ለሃማ ለመስገድ ፈቃደኛ አልሆነም። ከዚህ በኋላ አሐሽዌሮስ አጋጋዊውን ሃማን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሾመው፤ እንዲሁም ይህ አዲስ ሥልጣን ስለተሰጠው በንጉሡ በር ያሉ ሁሉ እንዲሰግዱለት አዘዘ። መርዶክዮስ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም፤ ይህንንም ያደረገው አይሁዳዊ በመሆኑ እንደሆነ ገልጿል። (አስ 3:1-4) መርዶክዮስ ይህን ያደረገው በዚህ ምክንያት መሆኑን መግለጹ ለአምላክ የተወሰነ አይሁዳዊ እንደመሆኑ መጠን ውሳኔው ከአምላኩ ከይሖዋ ጋር ካለው ዝምድና ጋር ተያያዥነት እንዳለው ያሳያል። ለሃማ መስገድ እስራኤላውያን ቀደም ሲል ያደርጉ እንደነበረው ለአንድ ሰው ሥልጣን እውቅና ለመስጠት መሬት ላይ ከመስገድ የተለየ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። (2ሳሙ 14:4፤ 18:28፤ 1ነገ 1:16) መርዶክዮስ ለሃማ ያልሰገደበት በቂ ምክንያት ነበረው። ሃማ አማሌቃዊ ሳይሆን አይቀርም፤ ይሖዋ ደግሞ ከአማሌቅ ጋር “ከትውልድ እስከ ትውልድ” እንደሚዋጋ ገልጿል። (ዘፀ 17:16፤ ሃማ የሚለውን ተመልከት) መርዶክዮስ ለሃማ ያልሰገደው በፖለቲካዊ ምክንያት ሳይሆን በአምላክ ዘንድ ያለውን ንጹሕ አቋም ለመጠበቅ ሲል ነው።
it-2 431 አን. 9
መርዶክዮስ
አምላክ እስራኤልን ለማዳን ተጠቅሞበታል። መርዶክዮስ በፋርስ ግዛት ውስጥ ያሉ አይሁዳውያን በሙሉ እንዲጠፉ አዋጅ በወጣበት ወቅት አስቴር በዚህ ጊዜ ንግሥት የሆነችው አይሁዳውያንን ለማዳን እንደሆነ እምነት እንዳለው ገልጿል። አስቴር ከባድ ኃላፊነት እንደተጣለባት የነገራት ከመሆኑም ሌላ የንጉሡን ሞገስና እርዳታ እንድትለምን ጠየቃት። እንዲህ ማድረጓ ሕይወቷን አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆንም እንኳ አስቴር የተጠየቀችውን አድርጋለች።—አስ 4:7–5:2
ለአምላክ ሕዝብ ጥብቅና ቆማለች
22 አስቴር መልእክቱ ሲደርሳት በድንጋጤ ክው ብላ መሆን አለበት። ይህ አጋጣሚ እምነቷን በእጅጉ የሚፈትን ነበር። ለመርዶክዮስ ከላከችው ምላሽ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው አስቴር በጣም ፈርታ ነበር። የንጉሡ ሕግ ምን እንደሚል አስታወሰችው። አንድ ሰው ሳይጠራ ንጉሡ ፊት ቀረበ ማለት ሕይወቱን አጣ ማለት ነው። እንዲህ ዓይነት ጥፋት የፈጸመ ሰው በሕይወት መትረፍ የሚችለው ንጉሡ የወርቅ ዘንጉን ከዘረጋለት ብቻ ነው። አስጢን ንጉሡ ፊት እንድትቀርብ ስትጠራ አሻፈረኝ በማለቷ ከደረሰባት ዕጣ አንጻር አስቴር ንጉሡ ርኅራኄ ያሳየኛል ብላ የምትጠብቅበት ምን ምክንያት ይኖራል? አስቴር ላለፉት 30 ቀናት ንጉሡ ወደ እሱ እንድትገባ እንዳልጠራት ለመርዶክዮስ ነገረችው! አመሉ የማይጨበጠው ይህ ንጉሥ ለረጅም ጊዜ ያልጠራት ከመሆኑ አንጻር በእሱ ዘንድ ያላትን ተወዳጅነት እንዳጣች አድርጋ ብታስብ የሚያስገርም አይሆንም።—አስ. 4:9-11
23 መርዶክዮስ፣ አስቴር ያላትን እምነት ይበልጥ ለማጎልበት ጠንከር ያለ ምላሽ ሰጣት። እርምጃ ሳትወስድ ብትቀር አይሁዳውያን ከሌላ ምንጭ መዳን እንደሚያገኙ በእርግጠኝነት ነገራት። ሆኖም በአይሁዳውያን ላይ የተነሳው ስደት ገፍቶ ከመጣ አስቴርስ ብትሆን እንዴት በሕይወት እተርፋለሁ ብላ ልትጠብቅ ትችላለች? በዚህ ጊዜ መርዶክዮስ፣ ሕዝቡ ተጠራርጎ እንዲጠፋም ሆነ የገባው ቃል ሳይፈጸም እንዲቀር ፈጽሞ በማይፈቅደው በይሖዋ ላይ ከፍተኛ እምነት እንዳለው አሳይቷል። (ኢያሱ 23:14) ከዚያም መርዶክዮስ ለአስቴር “አንቺ ንግሥት ለመሆን የበቃሽው ለዚህ ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?” የሚል ጥያቄ አቀረበላት። (አስ. 4:12-14) መርዶክዮስ የተወው ምሳሌ ሊኮረጅ የሚገባው አይደለም? መርዶክዮስ በአምላኩ በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ ተማምኖ ነበር። እኛስ?—ምሳሌ 3:5, 6
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአምልኮ ነፃነት ለማግኘት መታገል
14 በጥንት ዘመን እንደነበሩት እንደ አስቴርና መርዶክዮስ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦችም ይሖዋን እሱ ባዘዛቸው መሠረት የማምለክ ነፃነታቸውን ለማስከበር ትግል ያደርጋሉ። (አስ. 4:13-16) አንተስ በዚህ ረገድ አስተዋጽኦ ማድረግ ትችል ይሆን? አዎን። በአሁኑ ጊዜ የፍትሕ መጓደል እየደረሰባቸው ላሉ መንፈሳዊ ወንድሞችህና እህቶችህ አዘውትረህ መጸለይ ትችላለህ። እንዲህ ያለው ጸሎት፣ መከራና ስደት የሚያጋጥማቸው ወንድሞችንና እህቶችን በእጅጉ ሊረዳቸው ይችላል። (ያዕቆብ 5:16ን አንብብ።) ይሁንና ይሖዋ እነዚህን ጸሎቶች ሰምቶ እርምጃ ይወስዳል? በፍርድ ቤት ያገኘናቸው ድሎች ይህን እንደሚያደርግ ያረጋግጣሉ!—ዕብ. 13:18, 19
ከመስከረም 18-24
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | አስቴር 6–8
“ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ በማድረግ ረገድ ግሩም ምሳሌ”
ለሕዝቧ ስትል ሕይወቷን ለአደጋ ያጋለጠች ጠቢብና ደፋር ሴት
15 አስቴር ልመናዋን ለንጉሡ ለማቅረብ አንድ ተጨማሪ ቀን ታግሣ መቆየቷ ሐማ ለራሱ ውድቀት ሁኔታዎችን እንዲያመቻች አጋጣሚ ፈጠረ። ምናልባት በዚያ ሌሊት ንጉሡ እንቅልፍ እንዲያጣ ያደረገው ይሖዋ አምላክ ይሆን? (ምሳሌ 21:1) የአምላክ ቃል በትዕግሥት ‘የመጠበቅ’ ዝንባሌ እንድናዳብር የሚያበረታታን ያለ ምክንያት አይደለም! (ሚክያስ 7:7ን አንብብ።) አምላክን በትዕግሥት የምንጠብቅ ከሆነ እሱ ለችግሮቻችን የሚሰጠው መፍትሔ እኛ ከምንፈጥረው ብልሃት እጅግ የላቀ መሆኑን ማስተዋል እንችላለን።
በድፍረት ተናገረች
16 አስቴር ከዚህ በላይ የንጉሡን ትዕግሥት መፈታተን አልፈለገችም፤ በመሆኑም በሁለተኛው ግብዣ ላይ ሁሉንም ነገር ልትነግረው ወሰነች። ግን እንዴት አድርጋ ትንገረው? ደግነቱ ንጉሡ ራሱ ምን እንዲደረግላት እንደምትፈልግ በድጋሚ ስለጠየቃት ጉዳይዋን የምትናገርበት አጋጣሚ አገኘች። (አስ. 7:2) በመጨረሻ አስቴር ‘የምትናገርበት ጊዜ’ ደረሰ።
ለሕዝቧ ስትል ሕይወቷን ለአደጋ ያጋለጠች ጠቢብና ደፋር ሴት
17 አስቴር የሚከተለውን ሐሳብ ከመናገሯ በፊት በልቧ ወደ አምላኳ ጸልያ እንደሚሆን መገመት እንችላለን፦ “ንጉሥ ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼና ግርማዊነትህን ደስ የሚያሰኝ ከሆነ፣ ሕይወቴን ታደጋት፤ ልመናዬ ይህ ነው፤ ሕዝቤን አትርፍ፤ ጥያቄዬም ይኸው ነው።” (አስ. 7:3) አስቴር፣ ንጉሡ ደስ የሚያሰኘውን ውሳኔ ቢያስተላልፍ ውሳኔውን ለማክበር ዝግጁ መሆኗን እንደገለጸች ልብ በል። አስቴር፣ ንጉሡን ሆን ብላ ካዋረደችው ከቀድሞዋ ሚስቱ ከአስጢን ምንኛ የተለየች ነበረች! (አስ. 1:10-12) ከዚህም በላይ አስቴር፣ ንጉሡ በሐማ ላይ እምነት መጣሉ ሞኝነት እንደሆነ በመናገር አልነቀፈችውም። ከዚህ ይልቅ በሕይወቷ ላይ ከተጋረጠው አደጋ እንዲጠብቃት ንጉሡን ለመነችው።
ለሕዝቧ ስትል ሕይወቷን ለአደጋ ያጋለጠች ጠቢብና ደፋር ሴት
18 ይህ ልመና ንጉሡን እንዳስደነገጠውና እንዳስገረመው ጥርጥር የለውም። ለመሆኑ ማን ነው እንዲህ ደፍሮ ንግሥቲቱን ለመጉዳት የቃጣው? አስቴር በመቀጠል እንዲህ አለች፦ “እኔና ሕዝቤ ለጥፋት፣ ለመገደልና ለመደምሰስ ተሸጠናል። የተሸጥነው ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች እንድንሆን ብቻ ቢሆን ኖሮ ዝም ባልኩ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ጥፋት በንጉሡም ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል በቸልታ መታለፍ የለበትም።” (አስ. 7:4 NW) አስቴር የገጠማትን ችግር በግልጽ እንደተናገረች ልብ በል፤ ሆኖም ችግሩ ለባርነት የመዳረግ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ በዝምታ ታልፈው እንደነበር አክላ ገልጻለች። ይሁንና ይህ የዘር ማጥፋት ሴራ በንጉሡ ላይ ከባድ ኪሣራ ስለሚያስከትል በዝምታ ሊታለፍ አይገባም።
19 አስቴር የተወችው ምሳሌ የማሳመን ችሎታን በተመለከተ ብዙ ነገር ያስተምረናል። ለምትወደው ሰው ወይም ለአንድ ባለሥልጣን ስላሳሰበህ ጉዳይ መናገር ቢያስፈልግህ ሐሳብህን በትዕግሥት፣ በአክብሮትና በግልጽነት ለማስረዳት መሞከርህ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል።—ምሳሌ 16:21, 23
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአስቴር መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
7:4 የግርጌ ማስታወሻ—አይሁዳውያን በመደምሰሳቸው ‘ንጉሡ የሚያጣው’ እንዴት ነው? አስቴር፣ አይሁዳውያን በባርነት ሊሸጡ ይችሉ እንደነበር በብልሃት በመግለጽ መጥፋታቸው ንጉሡን እንደሚጎዳው ተናግራለች። ሐማ ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ለማስገባት ቃል የገባው 10,000 መክሊት ብር አይሁዳውያንን በባርነት ለመሸጥ አቅዶ ቢሆን ኖሮ ሊገኝ ከሚችለው ትርፍ ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። ሐማ ያቀደው ተሳክቶለት ቢሆን ኖሮ ንጉሡ ንግሥቲቱንም ያጣ ነበር።
ከመስከረም 25–ጥቅምት 1
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | አስቴር 9–10
“ሥልጣኑን ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ተጠቅሞበታል”
it-2 432 አን. 2
መርዶክዮስ
መርዶክዮስ በሃማ ምትክ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነ ከመሆኑም ሌላ የመንግሥት ሰነዶችን ለማጽደቅ የሚያስችለውን የንጉሡን የማኅተም ቀለበት ተቀበለ። ንጉሡ ለአስቴር የሃማን ቤት ከሰጣት በኋላ አስቴር መርዶክዮስን በሃማ ቤት ላይ ሾመችው። ከዚያም መርዶክዮስ በንጉሡ ፈቃድ መሠረት አይሁዳውያን ራሳቸውን እንዲከላከሉ ሕጋዊ መብት የሚሰጥ አዋጅ አወጣ። ይህም ለአይሁዳውያን የመዳንና የደስታ ምንጭ ሆኖላቸዋል። በፋርስ ግዛት ሥር ያሉ ብዙዎች ከአይሁዳውያን ጎን ቆሙ፤ ከዚያም ሕጉ የሚፈጸምበት ቀን ማለትም አዳር 13 ሲደርስ አይሁዳውያን ዝግጁ ነበሩ። መርዶክዮስ ከፍተኛ ሥልጣን ስለነበረው ባለሥልጣናቱ ከጎናቸው ነበሩ። በሹሻን ውጊያው ለአንድ ተጨማሪ ቀን ቀጠለ። የሃማን አሥር ልጆች ጨምሮ በፋርስ ግዛት የነበሩ ከ75,000 በላይ የአይሁዳውያን ጠላቶች ተደመሰሱ። (አስ 8:1–9:18) መርዶክዮስ ከአስቴር ጋር በመተባበር በአዳር ወር 14ኛና 15ኛ ቀን ማለትም ‘በፑሪም ቀናት’ ዓመታዊ በዓል እንዲከበር አዘዘ፤ እነዚህ ቀናት የግብዣና የደስታ እንዲሁም አንዳቸው ለሌላውና ለድሆች ስጦታ የሚሰጡባቸው ቀናት እንዲሆኑ አዘዘ። አይሁዳውያን ይህን ትእዛዝ ተቀበሉ፤ እንዲሁም በዓሉን ለዘሮቻቸውና ከእነሱ ጋር ለሚተባበሩ ሰዎች አስተላለፉ። በግዛቱ ውስጥ ሁለተኛውን ሥልጣን የያዘው መርዶክዮስ የአምላክ ሕዝቦች በሆኑት በአይሁዳውያን ዘንድ የተከበረ እንዲሁም ለእነሱ ጥቅም የቆመ ሰው ነበር።—አስ 9:19-22, 27-32፤ 10:2, 3
it-2 716 አን. 5
ፑሪም
ዓላማ። አንዳንድ ምሁራን በዘመናችን ያሉ አይሁዳውያን የሚያከብሩት የፑሪም በዓል ከሃይማኖታዊ ይልቅ ብሔራዊ አንድምታ እንዳለውና አንዳንድ ጊዜም በፈንጠዝያ ላይ ያተኮረ እንደሆነ የሚናገሩ ቢሆንም በዓሉ በተቋቋመበትም ሆነ ጥንት በተከበረበት ወቅት ሁኔታው እንደዚያ አልነበረም። መርዶክዮስም ሆነ አስቴር የእውነተኛው አምላክ የይሖዋ አገልጋዮች ነበሩ፤ በዓሉም የተቋቋመው እሱን ለማስከበር ነው። በዚያ ወቅት አይሁዳውያንን ያዳናቸው ይሖዋ አምላክ ነው ሊባል ይችላል፤ ምክንያቱም ጉዳዩ የተነሳው መርዶክዮስ ይሖዋን ብቻ ለማምለክ ቁርጥ ውሳኔ በማድረጉ የተነሳ ነው። ሃማ አማሌቃዊ ሳይሆን አይቀርም፤ ይሖዋ ደግሞ አማሌቃውያንን የረገማቸው ከመሆኑም ሌላ እንዲጠፉ ወስኖባቸዋል። መርዶክዮስ አምላክን በመታዘዝ ለሃማ ለመስገድ ፈቃደኛ አልሆነም። (አስ 3:2, 5፤ ዘፀ 17:14-16) ከዚህም ሌላ፣ መርዶክዮስ ለአስቴር የተናገራቸው ቃላት (አስ 4:14) ለአይሁዳውያን መዳን የሚያመጣላቸው የላቀ ኃይል ያለው አካል እንደሆነ እንደሚያምን ይጠቁማል፤ በተጨማሪም አስቴር ንጉሡን ለመጋበዝ ለመጀመሪያ ጊዜ እሱ ዘንድ ከመቅረቧ በፊት መጾሟ የአምላክን እርዳታ እንደለመነች ያሳያል።—አስ 4:16
በኃይል አጠቃቀም ረገድ አምላክን ኮርጅ
12 ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው የሚመሩ የበላይ ተመልካቾችን ሾሟል። (ዕብራውያን 13:17) ለዚህ ኃላፊነት የበቁ ወንዶች አምላክ የሰጣቸውን ሥልጣን ለመንጋው አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግና መንጋውን በመንፈሳዊ ለመንከባከብ ሊጠቀሙበት ይገባል። ሽማግሌዎች ሥልጣናቸውን የጉባኤውን አባላት ለመጫን ሊጠቀሙበት ይገባልን? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ በጉባኤው ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖራቸው የሚገባ ከመሆኑም በላይ ራሳቸውን ከፍ አድርገው ማየት የለባቸውም። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) መጽሐፍ ቅዱስ ለበላይ ተመልካቾች “በገዛ ልጁ ደም የዋጀውን የአምላክን ጉባኤ ጠብቁ” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጣል። (የሐዋርያት ሥራ 20:28 NW) ይህ ማሳሰቢያ ሽማግሌዎች እያንዳንዱን የመንጋው አባል በርኅራኄ እንዲይዙ ሊገፋፋቸው ይገባል።
13 ይህን ሁኔታ በሚከተለው መንገድ በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል። የቅርብ ጓደኛህ አንድ ውድ ዕቃ እንድትይዝለት በአደራ ሰጠህ እንበል። ይህን ዕቃ በውድ ዋጋ እንደገዛው ታውቃለህ። በመሆኑም ዕቃውን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደምትይዘው የታወቀ ነው። በተመሳሳይም አምላክ ለሽማግሌዎች ውድ ዋጋ ያለው ንብረት ማለትም በበጎች የተመሰሉ አባላትን ያቀፈ ጉባኤ በአደራ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 21:16, 17) ይሖዋ በጎቹን በጣም ስለሚወዳቸው በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ውድ ደም ገዝቷቸዋል። ይሖዋ ለበጎቹ ከሁሉ የላቀውን ውድ ዋጋ ከፍሏል። ትሑት የሆኑ ሽማግሌዎች ይህን ስለሚገነዘቡ የይሖዋን በጎች በእንክብካቤ ይይዛሉ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአስቴር መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
9:10, 15, 16—አዋጁ ምርኮ መውሰድን ቢፈቅድላቸውም እንኳ አይሁዳውያን ይህን ማድረግ ያልፈለጉት ለምን ነበር? ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ዓላማቸው ራሳቸውን መከላከል እንጂ መበልጸግ እንዳልሆነ በማያሻማ ሁኔታ አሳይተዋል።
ከጥቅምት 2-8
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 1–3
“ይሖዋን ምን ያህል እንደምትወዱት ምንጊዜም አሳዩ”
ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ የተዉትን የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ ተከተሉ
16 ኢዮብ ያጋጠሙት ተፈታታኝ ሁኔታዎች። ኢዮብ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ለውጥ አጋጥሞታል። ከፈተናው በፊት “በምሥራቅ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ሰው” ነበር። (ኢዮብ 1:3) እንዲሁም ባለጸጋ፣ የታወቀና እጅግ የተከበረ ሰው ነበር። (ኢዮብ 29:7-16) ኢዮብ ከፍ ያለ ቦታ የነበረው ቢሆንም ለራሱ የተጋነነ አመለካከት አልነበረውም፤ እንዲሁም አምላክ እንደማያስፈልገው አልተሰማውም። እንዲያውም ይሖዋ “አገልጋዬ” ብሎ የጠራው ሲሆን “በንጹሕ አቋም የሚመላለስ ቅን ሰው እንዲሁም አምላክን የሚፈራና ከክፋት የራቀ” በማለት መሥክሮለታል።—ኢዮብ 1:8
17 ይሁንና የኢዮብ ሕይወት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ። በከባድ ድህነት ውስጥ የተዘፈቀ ከመሆኑም ሌላ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተዋጠ። እንደምናውቀው የዚህ ሁሉ መከራ መንስኤ ስም አጥፊ የሆነው ሰይጣን ነው፤ ሰይጣን፣ ኢዮብ አምላክን የሚያመልከው ለግል ጥቅሙ ሲል እንደሆነ በመናገር የሐሰት ክስ ሰንዝሮበታል። (ኢዮብ 1:9, 10ን አንብብ።) ይሖዋ ይህን ተንኮል ያዘለ ክስ በቸልታ አላለፈውም። ከዚህ ይልቅ ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቅ እሱን የሚያመልከው በንጹሕና ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ልብ ተነሳስቶ እንደሆነ ማረጋገጥ የሚችልበት አጋጣሚ ሰጥቶታል።
ንጹሕ አቋማችሁን ጠብቁ!
10 ሰይጣን በእያንዳንዳችን ላይ ተመሳሳይ ክስ ሰንዝሯል። ይህ ክስ አንተን በግለሰብ ደረጃ የሚነካህ እንዴት ነው? በተዘዋዋሪ መንገድ ሰይጣን ይሖዋ አምላክን ከልብ እንደማትወደው፣ ራስህን ለማዳን ስትል እሱን ማገልገልህን እንደምታቆምና በፈተናዎች ሥር ንጹሕ አቋምህን እንደማትጠብቅ ተናግሯል! (ኢዮብ 2:4, 5፤ ራእይ 12:10) ይህን ማወቅህ ምን ስሜት ያሳድርብሃል? ስሜትህ በጣም እንደሚጎዳ ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም እስቲ የሚከተለውን ለማሰብ ሞክር፦ ይሖዋ፣ ንጹሕ አቋምህን እንዲፈትነው ለሰይጣን ፈቅዶለታል። ይህን ግሩም አጋጣሚ የሰጠህ በአንተ ላይ ሙሉ እምነት ስላለው ነው። ይሖዋ ንጹሕ አቋምህን እንደምትጠብቅና ሰይጣን ውሸታም መሆኑ እንዲረጋገጥ እንደምታደርግ ይተማመንብሃል። ደግሞም በዚህ ረገድ እንደሚረዳህ ቃል ገብቷል። (ዕብ. 13:6) የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ የሚተማመንብህ መሆኑ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ታዲያ ንጹሕ አቋምህን መጠበቅህ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገነዘብክ? ንጹሕ አቋማችንን መጠበቃችን የሰይጣንን ውሸት ውድቅ ለማድረግ፣ ለአባታችን መልካም ስም ጥብቅና ለመቆም እንዲሁም የእሱን አገዛዝ ለመደገፍ ያስችለናል። ለመሆኑ ይህን አስፈላጊ ባሕርይ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ከኢየሱስ የመጨረሻ ቃላት ተማሩ
9 ኢየሱስ ምን ብሏል? ኢየሱስ ልክ ከመሞቱ በፊት “አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” በማለት ጮዃል። (ማቴ. 27:46) መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ እንዲህ ያለው ለምን እንደሆነ አይገልጽልንም። ሆኖም እነዚህ ቃላት ምን እንደሚያስገነዝቡን እንመልከት። አንደኛ ነገር፣ ኢየሱስ እነዚህን ቃላት መናገሩ በመዝሙር 22:1 ላይ ያለው ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል። ከዚህም ሌላ እነዚህ ቃላት ይሖዋ በልጁ ዙሪያ ‘የአጥር ከለላ’ እንዳላደረገ ያሳዩናል። (ኢዮብ 1:10) ኢየሱስ ጠላቶቹ እስከ መጨረሻው ድረስ እንዲፈትኑት አባቱ መፍቀዱን ያውቅ ነበር፤ ማንም ሰው የዚህን ያህል ተፈትኖ አያውቅም። ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ቃላት ኢየሱስ ለሞት የሚያበቃ ምንም ዓይነት ወንጀል እንዳልፈጸመ ያረጋግጣሉ።
ከጥቅምት 9-15
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 4–5
“ከተሳሳተ መረጃ ራሳችሁን ጠብቁ”
it-1 713 አን. 11
ኤሊፋዝ
2. ከኢዮብ ሦስት ጓደኞች አንዱ። (ኢዮብ 2:11) ቴማናዊ የሆነው ይህ ሰው የኤሳው የበኩር ልጅ የሆነው የኤሊፋዝ ዘር ሳይሆን አይቀርም፤ በመሆኑም የአብርሃም ዘርና የኢዮብ የሩቅ ዘመድ ነበር። እሱም ሆነ ዘሮቹ በጥበባቸው ይኩራሩ ነበር። (ኤር 49:7) ከሦስቱ “አጽናኞች” መካከል ኤሊፋዝ የተከበረና ተሰሚነት ያተረፈ ይመስላል፤ ይህም ከእነሱ መካከል በዕድሜ ትልቁ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል። ሙግታቸውን ባቀረቡባቸው በሦስቱም ጊዜያት መጀመሪያ የተናገረው እሱ ከመሆኑም ሌላ ንግግሮቹም ከሌሎቹ ይረዝማሉ።
መጥፎ አስተሳሰብን ተዋጉ!
ኤልፋዝ በአንድ ወቅት ያጋጠመውን ተአምራዊ የሆነ ክስተት በማስታወስ እንዲህ አለ፦ “መንፈስ ሽው ብሎ በፊቴ አለፈ፤ የገላዬም ጠጒር ቆመ። እርሱም ቆመ፣ ምን እንደሆነ ግን መለየት አልቻልሁም፤ አንድ ቅርጽ በዐይኔ ፊት ነበረ፤ በእርጭታ ውስጥ እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማሁ።” (ኢዮብ 4:15, 16) በኤልፋዝ አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ አድርጎ የነበረው ምን ዓይነት መንፈስ ነው? ቀጥሎ የተናገረው ነቀፋ አዘል ንግግር፣ መንፈሱ ከአንድ ታማኝ የይሖዋ መልአክ የመነጨ እንዳልሆነ በግልጽ ያሳያል። (ኢዮብ 4:17, 18) ተጽዕኖ ያሳደረበት ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር ነበር። ይህ ባይሆን ኖሮ ይሖዋ ውሸት በመናገራቸው ኤልፋዝንና ሁለቱን ጓደኞቹን ይገስጻቸው ነበር? (ኢዮብ 42:7) በእርግጥም፣ ኤልፋዝ ይናገር የነበረው በአጋንንት ተጽዕኖ ነው። የተናገራቸው ሐሳቦች አምላካዊ አስተሳሰብን አያንጸባርቁም።
በሰይጣን ፕሮፓጋንዳ አትሸነፍ
ሰይጣን፣ ሰዎች ለአምላክ ታማኝነታቸውን ጠብቀው መቀጠል የማይችሉ ደካማ ፍጥረታት እንደሆኑ ኢዮብን ሊያጽናኑት ከመጡት ወዳጆቹ አንዱ በሆነው በኤልፋዝ አማካኝነት ገልጿል። ኤልፋዝ፣ ሰዎችን “በጭቃ ቤት የሚኖሩ” ብሎ የጠራቸው ሲሆን ኢዮብን እንዲህ ብሎታል፦ “መሠረታቸው ከዐፈር [ነው]፣ ከብልም ይልቅ በቀላሉ [ይጨፈለቃሉ] . . . በንጋትና በምሽት መካከል ይደቃሉ፤ ሳይታሰብም ለዘላለም ይጠፋሉ።”—ኢዮብ 4:19, 20
በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በሌላ ጥቅስ ላይ በቀላሉ ከሚሰበር ‘የሸክላ ዕቃ’ ጋር ተመሳስለናል። (2 ቆሮ. 4:7) በወረስነው ኃጢአትና አለፍጽምና የተነሳ ደካሞች ነን። (ሮም 5:12) በራሳችን ኃይል የሰይጣንን ጥቃት ልንቋቋም አንችልም። ሆኖም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ያለ እርዳታ አልተተውንም። ድክመት ቢኖርብንም በአምላክ ዓይን ብርቅ ወይም ውድ ነን። (ኢሳ. 43:4) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ለሚጠይቁት ቅዱስ መንፈሱን ይሰጣል። (ሉቃስ 11:13) መንፈሱ ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነውን ኃይል’ የሚሰጠን ሲሆን ይህም ሰይጣን የሚያመጣብንን ማንኛውንም ዓይነት መከራ ለመቋቋም ያስችለናል። (2 ቆሮ. 4:7፤ ፊልጵ. 4:13) ‘በእምነት ጸንተን በመቆም’ ዲያብሎስን ከተቃወምነው አምላክ ጽኑና ጠንካሮች እንድንሆን ያደርገናል። (1 ጴጥ. 5:8-10) ስለዚህ ሰይጣን ዲያብሎስን የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለንም።
ከተሳሳተ መረጃ ራስህን ጠብቅ
● የመረጃውን ምንጭ እና ይዘት ገምግም
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሁሉንም ነገር መርምሩ።”—1 ተሰሎንቄ 5:21
አንድን ዘገባ ከማመንህ ወይም ለሌሎች ከማስተላለፍህ በፊት እውነት መሆኑን አረጋግጥ፤ ዘገባው በስፋት የተሰራጨ ወይም ዜና ላይ በተደጋጋሚ የተነገረ ቢሆንም እንኳ እንዲህ ማድረግህ አስፈላጊ ነው። ታዲያ መረጃው እውነት መሆኑን ማረጋገጥ የምትችለው እንዴት ነው?
የመረጃው ምንጭ አስተማማኝ መሆኑን ገምግም። የዜና ተቋማትና ሌሎች ድርጅቶች ትርፍ ለማግኘት ወይም ፖለቲካዊ አቋማቸውን ለማራመድ ሲሉ አንድን ዘገባ አዛብተው ሊያቀርቡ ይችላሉ። ከአንድ ምንጭ የሰማኸውን ዜና ሌሎች ምንጮች ካወጡት ዜና ጋር አወዳድር። አንዳንድ ጊዜ ጓደኞችህ ባለማወቅ አንድን የተሳሳተ መረጃ በኢሜይል ሊልኩልህ ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ሊለጥፉ ይችላሉ። ስለዚህ አንድን መረጃ ምንጩን አግኝተህ እስካላረጋገጥክ ድረስ መረጃውን አትመን።
የመረጃው ይዘት ጊዜ ያላለፈበትና ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጥ። እየተነገረ ያለው ነገር ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ቀኖችን፣ ሊታወቁ የሚችሉ እውነታዎችንና ጠንካራ ማስረጃዎችን ለማግኘት ሞክር። ውስብስብ የሆነ ዘገባ በጣም ቀላል ተደርጎ ከቀረበ ወይም ዘገባው የሰዎችን ስሜት ለመቀስቀስ ታስቦ የተዘጋጀ ከሆነ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልግሃል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ጸንታችሁ ቁሙ፣ የሕይወትንም ሩጫ አሸንፉ
በእውነተኛ አምላኪዎች የተገነባው ዓለም አቀፋዊ ድርጅት አካል መሆን ጸንቶ ለመቆም በእጅጉ ይረዳናል። የዚህ እርስ በእርስ የሚፋቀር ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር አባል መሆን ምንኛ መታደል ነው! (1 ጴጥሮስ 2:17) ሌሎች ወንድሞቻችንም በእምነት ጸንተው እንዲቆሙ መርዳት እንችላለን።
ቅን የነበረው ኢዮብ ለሌሎች ያበረከተውን እርዳታ ተመልከት። አጽናኝ ተብዬው ኤልፋዝ እንኳን “ቃልህ የሚሰናከለውን ያስነሣ ነበር፣ አንተም የሚብረከረከውን ጉልበት ታጸና ነበር” ብሎ ለማመን ተገድዷል። (ኢዮብ 4:4) እኛስ በዚህ ረገድ ምን እያደረግን ነው? በግለሰብ ደረጃ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አምላክን በማገልገል እንዲጸኑ የመርዳት ኃላፊነት አለብን። ከእነርሱ ጋር በአንድ ላይ በምንሆንበት ጊዜ “የደከሙትን እጆች አበርቱ፣ የላሉትንም ጉልበቶች አጽኑ” የሚሉትን ቃላት በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ማድረግ እንችላለን። (ኢሳይያስ 35:3) እንግዲያው ከክርስቲያን ወንድሞችህ ጋር ስትገናኝ አጋጣሚውን ተጠቅመህ እነርሱን ለማበረታታትና ለማጠናከር ለምን ጥረት አታደርግም? (ዕብራውያን 10:24, 25) ይሖዋን ለማስደሰት ሲሉ ለሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት ያለህን አድናቆት ለመግለጽ ጣል የምታደርጋቸው የምስጋና ቃላት የጀመሩትን የሕይወት ሩጫ በድል ለመወጣት በጽናት እንዲቀጥሉ ሊረዳቸው ይችላል።
ከጥቅምት 16-22
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 6–7
“ሕይወት መራራ ሲሆን”
የኢዮብ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
7:1፤ 14:14—ኢዮብ “ብርቱ ተጋድሎ [“የግዳጅ ሥራ፣” NW]” ወይም “ተጋድሎ [“የግዳጅ አገልግሎት፣” NW]” ሲል ምን ማለቱ ነበር? ኢዮብ ሥቃዩ በጣም የበዛበት ከመሆኑ የተነሳ ሕይወት ከባድና አድካሚ የግዳጅ ሥራ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። (ኢዮብ 10:17 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ትንሣኤ እስከሚያገኝበት ጊዜ ድረስ በሲኦል የሚቆየው ወዶ ሳይሆን ግድ ሆኖበት ስለሆነ ኢዮብ ይህን ወቅት ከግዳጅ አገልግሎት ጋር አመሳስሎታል።
‘ይሖዋ ተስፋ የቆረጡትን ያድናል’
ሕይወት “አጭርና በመከራ የተሞላ” መሆኑን ስናስብ እንጨነቅ ይሆናል። (ኢዮብ 14:1) ከዚህ አንጻር አንዳንድ ጊዜ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ቢሰማን የሚያስገርም አይደለም። በጥንት ዘመን የኖሩ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮችም እንደዚህ ተሰምቷቸው ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹ ሞትን እስከ መመኘት ደርሰዋል። (1 ነገ. 19:2-4፤ ኢዮብ 3:1-3, 11፤ 7:15, 16) ሆኖም የሚታመኑበት አምላካቸው ይሖዋ በተደጋጋሚ አጽናንቷቸዋል እንዲሁም አጠንክሯቸዋል። የእነሱ ታሪክ የተመዘገበልን እኛን ለማጽናናት እና ለማስተማር ነው።—ሮም 15:4
በሕይወት መኖር ሲታክትህ
ያለህበት ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ ሊመስል ቢችልም እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ያለኸው አንተ ብቻ እንዳልሆንክ አስታውስ፤ የሚያሳዝነው በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል ከአንድ ዓይነት ችግር ጋር እየታገለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ በአንድነት ሆኖ በመቃተትና አብሮ በመሠቃየት ላይ እንደሚገኝ” ይናገራል። (ሮም 8:22) ያለብህ ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ የሚያገኝ ባይመስልም ብዙውን ጊዜ ነገሮች በጊዜ ሂደት መሻሻላቸው አይቀርም። ታዲያ እስከዚያው ድረስ ምን ሊረዳህ ይችላል?
የሚሰማህን ነገር ለጎለመሰና እምነት ለምትጥልበት ወዳጅህ አዋየው። መጽሐፍ ቅዱስ “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፣ ደግሞም ለመከራ ቀን እንደተወለደ ወንድም ነው” ይላል። (ምሳሌ 17:17 NW) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ኢዮብ የተባለ ጻድቅ ሰው ከባድ መከራ በደረሰበት ወቅት ስለተሰማው ነገር ለሌሎች ተናግሮ ነበር። ኢዮብ በወቅቱ የተሰማውን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሕይወቴን እጅግ ጠላሁ፤ ስለዚህም ማጕረምረሜን ያለ ገደብ እለቃለሁ፤ በነፍሴም ምሬት እናገራለሁ።” (ኢዮብ 10:1) የሚሰማህን ነገር ለሌሎች ማካፈልህ ያጋጠመህን የስሜት ውጥረት ሊቀንስልህ የሚችል ሲሆን ስለ ሁኔታው ያለህ አመለካከትም እንዲለወጥ ሊያደርግ ይችላል።
ለአምላክ የልብህን ግልጥልጥ አድርገህ ንገረው። አንዳንዶች ጸሎት ውጥረትን ከማስታገስ ያለፈ ፋይዳ የለውም የሚል አመለካከት አላቸው፤ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ግን ከዚህ የተለየ ነው። መዝሙር 65:2 ይሖዋ አምላክን ‘ጸሎት ሰሚ’ በማለት የሚጠራው ሲሆን 1 ጴጥሮስ 5:7 ደግሞ “እሱ ስለ እናንተ ያስባል” በማለት ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ የመተማመንን አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፦
“በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።”—ምሳሌ 3:5, 6
“[ይሖዋ] ለሚፈሩት ፍላጎታቸውን ይፈጽማል፤ ጩኸታቸውን ይሰማል፤ ያድናቸዋልም።”—መዝሙር 145:19
“በእሱ ላይ ያለን ትምክህት ይህ ነው፤ የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል።”—1 ዮሐንስ 5:14
“እግዚአብሔር ከክፉዎች ሩቅ ነው፤ የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል።”—ምሳሌ 15:29
እየደረሱብህ ያሉትን ችግሮች ለአምላክ የምትነግረው ከሆነ ይረዳሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁልጊዜ በእርሱ ታመኑ፤ ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ” በማለት የሚያበረታታበት በቂ ምክንያት አለው።—መዝሙር 62:8
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
አዳምጧቸው፣ እወቋቸው እንዲሁም ርኅራኄ አሳዩአቸው
10 እኛም አንዳችን ሌላውን ለመረዳት ጥረት በማድረግ የይሖዋን ምሳሌ መከተል እንችላለን። እንግዲያው ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን በደንብ እወቋቸው። ከስብሰባ በፊትና በኋላ ከእነሱ ጋር ተጨዋወቱ፤ አብራችሁ አገልግሉ፤ እንዲሁም የሚቻል ከሆነ ቤታችሁ ጋብዟቸው። እንዲህ ስታደርጉ፣ የማትቀረብ የምትመስላችሁ እህት ዓይን አፋር እንደሆነች፣ ቁሳዊ ነገር እንደሚወድ የሚሰማችሁ ወንድም ለጋስ እንደሆነ ወይም ደግሞ ብዙ ጊዜ ስብሰባ ላይ አርፍዶ የሚገኝ አንድ ቤተሰብ ተቃውሞን እየተቋቋመ እንደሆነ ልትገነዘቡ ትችላላችሁ። (ኢዮብ 6:29) እርግጥ ነው፣ ‘በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ መግባት’ የለብንም። (1 ጢሞ. 5:13) ያም ቢሆን ስለ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም በባሕርያቸው ላይ ተጽዕኖ ስላሳደሩት ነገሮች በተወሰነ መጠንም ቢሆን ማወቃችን ጠቃሚ ነው።
ከጥቅምት 23-29
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 8–10
“የአምላክ ታማኝ ፍቅር ከሰይጣን ውሸቶች ይጠብቀናል”
አምላክን ማስደሰት እንችላለን?
ኢዮብ በሕይወቱ ላይ ብዙ መከራ ተፈራርቆበታል፤ የደረሰበት መከራ ፍትሕ የጎደለው እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ኢዮብ ለአምላክ ታማኝ መሆን አለመሆኑ በአምላክ ዘንድ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ አስቦ ነበር። (ኢዮብ 9:20-22) ኢዮብ ስለ ራሱ ጽድቅ በጣም እርግጠኛ ከመሆኑ የተነሳ ‘እኔ ከአምላክ ይበልጥ ጻድቅ ነኝ’ ብሎ የተናገረ ያህል ነበር።—ኢዮብ 32:1, 2፤ 35:1, 2
የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?
14 የአምላክ ታማኝ ፍቅር መንፈሳዊ ጥበቃ ያስገኝልናል። ዳዊት ወደ ይሖዋ ሲጸልይ እንዲህ ብሏል፦ “አንተ መሸሸጊያዬ ነህ፤ ከጭንቀት ትሰውረኛለህ። በድል እልልታ ትከበኛለህ። . . . በይሖዋ የሚታመን ሰው . . . ታማኝ ፍቅሩ ይከበዋል።” (መዝ. 32:7, 10) ጥንታዊ ከተሞች በቅጥር መከበባቸው ለነዋሪዎቹ ጥበቃ ያስገኝ ነበር። በተመሳሳይም የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ዙሪያችንን በመክበብ፣ ታማኝነታችንን አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ነገሮች መንፈሳዊ ጥበቃ ያስገኝልናል። በተጨማሪም የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ወደ ራሱ እንዲስበን ያነሳሳዋል።—ኤር. 31:3
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
“የይሖዋን አስተሳሰብ ያወቀ ማን ነው?”
19 “የይሖዋን አስተሳሰብ” በተመለከተ ምን ትምህርት አግኝተናል? በዚህ ረገድ ትክክለኛውን ግንዛቤ ለማግኘት የአምላክን ቃል መጠቀም ይኖርብናል። ነገሮችን ሙሉ በሙሉ መረዳት ስለማንችል በእኛ አመለካከት፣ መሥፈርትና አስተሳሰብ ላይ ተመርኩዘን በይሖዋ ላይ ፈጽሞ መፍረድ አይኖርብንም። ኢዮብ “መልስ እሰጠው ዘንድ፣ እሟገተውም ዘንድ፣ [አምላክ] እንደ እኔ ሰው አይደለም” ብሏል። (ኢዮብ 9:32) ልክ እንደ ኢዮብ እኛም የይሖዋን አስተሳሰብ ስንረዳ እንደሚከተለው ለማለት እንነሳሳለን፦ “እነዚህ የሥራው ዳር ዳር ናቸው፤ ስለ እርሱ የሰማነው ምንኛ አነስተኛ ነው! የኀይሉንስ ነጐድጓድ ማን ሊያስተውል ይችላል?”—ኢዮብ 26:14
20 ቅዱሳን መጻሕፍትን ስናነብ በተለይ ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር በተያያዘ ለመረዳት የሚከብደን ሐሳብ ብናገኝ ምን ማድረግ ይኖርብናል? በጉዳዩ ላይ ምርምር አድርገንም እንኳ ግልጽ መልስ ማግኘት ባንችል ይህ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት የሚፈትን አጋጣሚ እንደሆነ አድርገን ልንመለከተው እንችላለን። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች፣ በይሖዋ ባሕርያት ላይ ያለንን እምነት ለመግለጽ አጋጣሚ እንደሚሰጡን አስታውስ። ይሖዋ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ሙሉ በሙሉ መረዳት እንደማንችል በትሕትና አምነን እንቀበል። (መክ. 11:5) እንዲህ ማድረጋችን ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ የተናገረውን ሐሳብ እንድናስተጋባ ያነሳሳናል፦ “የአምላክ ብልጽግናና ጥበብ እንዲሁም እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው! ምክንያቱም ‘የይሖዋን ሐሳብ ማወቅ የቻለ ማን ነው? አማካሪውስ የሆነ ማን ነው?’ ወይስ ‘መልሶ ይከፍለው ዘንድ ለእሱ ያበደረ ማን ነው?’ ምክንያቱም ሁሉም ነገር የተገኘው ከእሱ፣ በእሱና ለእሱ ነው። ለዘላለም ክብር ለእሱ ይሁን። አሜን።”—ሮም 11:33-36
ከጥቅምት 30–ኅዳር 5
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 11–12
“ጥበብን አግኝቶ መጠቀም የሚቻልባቸው ሦስት መንገዶች”
ኢዮብ የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ አድርጓል
17 ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ እንዲኖር የረዳው ምንድን ነው? ኢዮብ ችግሮቹ ከመከሰታቸው በፊት ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና እንደነበረው ግልጽ ነው። ሰይጣን በይሖዋ ላይ ስለሰነዘረው ክስ ኢዮብ ያውቅ እንደነበርና እንዳልነበር በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ታማኝ ለመሆን ቆርጦ ነበር። “እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 27:5 NW) ኢዮብ ከይሖዋ ጋር እንዲህ ያለ የቅርብ ዝምድና ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው? የሩቅ ዘመዶቹ የሆኑት አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ከአምላክ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት የሰማው ነገር በጎ ተጽዕኖ አሳድሮበት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም የፍጥረት ሥራዎችን በመመልከት አብዛኞቹን የይሖዋን ባሕርያት አስተውሎ መሆን አለበት።—ኢዮብ 12:7-9, 13, 16ን አንብብ።
ይሖዋ ከአንተ ጋር ስለሆነ ፈጽሞ ብቻህን አይደለህም
10 ከታማኝ ክርስቲያኖች ጋር ወዳጅነት መሥርት። በጉባኤ ውስጥ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑልህ የሚችሉ ወዳጆች ፈልግ፤ እነዚህ ወንድሞች ከአንተ የተለየ ዕድሜና አስተዳደግ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “በዕድሜ በገፉት መካከል ጥበብ” እንደሚገኝ ይናገራል። (ኢዮብ 12:12) በዕድሜ ተለቅ ያሉ ክርስቲያኖችም ከታማኝ ወጣቶች ብዙ የሚማሩት ነገር አለ። ዳዊት ከዮናታን ዕድሜው በጣም ያንስ ነበር፤ ይህ መሆኑ ግን የቅርብ ወዳጅነት ከመመሥረት አላገዳቸውም። (1 ሳሙ. 18:1) ዳዊትና ዮናታን እርስ በርስ መረዳዳታቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ይሖዋን ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ረድቷቸዋል። (1 ሳሙ. 23:16-18) በቤተሰቧ ውስጥ ብቸኛ የይሖዋ ምሥክር የሆነችው አይሪና እንዲህ ብላለች፦ “የእምነት ባልንጀሮቻችን መንፈሳዊ ወላጆቻችን፣ ወንድሞቻችን ወይም እህቶቻችን ሊሆኑልን ይችላሉ። ይሖዋ የሚያስፈልገንን እርዳታ ለመስጠት በእነሱ ሊጠቀም ይችላል።”
11 በተለይ ዓይናፋር ከሆንክ አዲስ ጓደኛ ማፍራት ሊከብድህ ይችላል። ዓይናፋር የሆነችውን ራትና የተባለች እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ራትና እውነትን ስትማር ተቃውሞ አጋጥሟት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “የመንፈሳዊ ቤተሰቤ እርዳታና ድጋፍ እንደሚያስፈልገኝ አምኜ መቀበል ነበረብኝ።” ስሜትህን አውጥተህ ለሌላ ሰው ማካፈል ከባድ ሊሆንብህ ይችላል፤ ግን የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት የሚቻለው የልብን አውጥቶ በመነጋገር ነው። ወዳጆችህ ሊያበረታቱህና ሊደግፉህ ይፈልጋሉ፤ ሆኖም ምን ዓይነት እርዳታ እንደሚያስፈልግህ ልትነግራቸው ይገባል።
12 ወዳጅነት መመሥረት ከሚቻልባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ ከእምነት አጋሮችህ ጋር በአገልግሎት መካፈል ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኬሮል እንዲህ ብላለች፦ “ከእህቶች ጋር በአገልግሎትና በሌሎች ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች በመካፈል በርካታ ጥሩ ጓደኞች አግኝቻለሁ። ባለፉት ዓመታት ይሖዋ በእነዚህ ወዳጆቼ አማካኝነት ደግፎኛል።” በእርግጥም ከታማኝ ክርስቲያኖች ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት የምታደርገው ጥረት የሚክስ ነው። ይሖዋ እንዲህ ባሉ ወዳጆች ተጠቅሞ እንደ ብቸኝነት ያሉ አሉታዊ ስሜቶችን እንድትቋቋም ይረዳሃል።—ምሳሌ 17:17
it-2 1190 አን. 2
ጥበብ
መለኮታዊ ጥበብ። ፍጹም ጥበብ የሚገኘው “እሱ ብቻ ጥበበኛ” ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ነው። (ሮም 16:27፤ ራእይ 7:12) እውቀት ማለት እውነታውን መረዳት ማለት ነው፤ ይሖዋ ደግሞ “ከዘላለም እስከ ዘላለም” (መዝ 90:1, 2) የሚኖር ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ስለ ጽንፈ ዓለም፣ ስለ አወቃቀሩ፣ ስለ ይዘቱና ስለ ታሪኩ ሁሉንም ነገር ያውቃል። ሰዎች ምርምር ለማድረግና የተለያዩ ነገሮችን ለመፈልሰፍ የሚጠቀሙባቸውን የተፈጥሮ ሕጎች፣ ዑደቶችና መሥፈርቶች የደነገገው እሱ ነው፤ እነዚህ ነገሮች ባይኖሩ ኖሮ እነዚህ ምሁራን ለሥራቸው መሠረት የሚሆናቸው አስተማማኝ ነገር አይኖራቸውም ነበር። (ኢዮብ 38:34-38፤ መዝ 104:24፤ ምሳሌ 3:19፤ ኤር 10:12, 13) ከዚህ በመነሳት የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹ የተረጋጋ ሕይወት ለመምራት፣ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግና ስኬታማ ለመሆን ይበልጥ ወሳኝ ናቸው ቢባል ምክንያታዊ ነው። (ዘዳ 32:4-6፤ ይሖዋ [የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን የሚያወጣ አምላክ] የሚለውን ተመልከት።) ከእሱ የመረዳት ችሎታ በላይ የሆነ ምንም ነገር የለም። (ኢሳ 40:13, 14) ከጽድቅ መሥፈርቶቹ ጋር የሚጻረሩ ነገሮች ለተወሰነ ጊዜ እንዲኖሩ አልፎ ተርፎም እንዲስፋፉ ሊፈቅድ ቢችልም የወደፊቱ ጊዜ ምንጊዜም በእጁ ነው፤ እንዲሁም ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ መከናወኑ አይቀርም፤ የተናገረው ነገር ሁሉ ‘በእርግጥ ይፈጸማል።’—ኢሳ 55:8-11፤ 46:9-11
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆች ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ
▪ ‘ልጄ ከሚናገረው ሐሳብ በስተጀርባ ያለውን ነገር ለማስተዋል እሞክራለሁ?’ ኢዮብ 12:11 “ምላስ የምግብን ጣዕም እንደሚለይ፣ ጆሮ ቃላትን አይለይምን?” ይላል። ልጅህ የሚናገረውን ነገር ‘ለመለየት’ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች አብዛኛውን ጊዜ እነሱ ብቻ ትክክል እንደሆኑ አድርገው ማውራት ይቀናቸዋል። ለአብነት ያህል፣ ልጅህ “ሁልጊዜ እንደ ሕፃን ትመለከተኛለህ!” ወይም “አንድም ቀን እኔ የምለውን ሰምተኸኝ አታውቅም!” ይል ይሆናል። “ሁልጊዜ” እና “አንድም ቀን” የሚሉትን ቃላት አንስተህ ከልጅህ ጋር ክርክር ከመግጠም ይልቅ ለማለት የፈለገውን ነገር ለመረዳት መጣር ይኖርብሃል። ለምሳሌ ያህል፣ ልጅህ “ሁልጊዜ እንደ ሕፃን ትመለከተኛለህ” ሲል “እንደማትተማመንብኝ ይሰማኛል” እንዲሁም “አንድም ቀን እኔ የምለውን ሰምተኸኝ አታውቅም” ሲል ደግሞ “ምን እንደሚሰማኝ ልነግርህ እፈልጋለሁ” ማለቱ ሊሆን ይችላል። ልጅህ ከሚናገረው ሐሳብ በስተጀርባ ያለውን ነገር ለማስተዋል ሞክር።