የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2024 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከኅዳር 4-10
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 105
“ቃል ኪዳኑን ለዘላለም . . . ያስታውሳል”
ይሖዋ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ በሰጠን ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር
11 ይሖዋ በጥንት ዘመን ለሕዝቦቹ ቃል የገባቸውን የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አብርሃምና ሣራ በስተ እርጅናቸው ወንድ ልጅ እንደሚወልዱ ቃል ገብቶላቸዋል። (ዘፍ. 17:15-17) በተጨማሪም ዘሮቹ የከነአንን ምድር እንደሚወርሱ ለአብርሃም ነግሮታል። የአብርሃም ዘሮች የሆኑት እስራኤላውያን በግብፅ ባሪያዎች በነበሩባቸው በርካታ ዓመታት ይህ ቃል ሊፈጸም የሚችል አይመስልም ነበር። ሆኖም ቃሉ ተፈጽሟል። በኋላም ይሖዋ፣ ኤልሳቤጥ በስተ እርጅናዋ ልጅ እንደምትወልድ ተናግሮ ነበር። በተጨማሪም ድንግል ለነበረችው ለማርያም የአምላክን ልጅ እንደምትወልድ ቃል ገብቶላታል፤ ይህም ይሖዋ በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በኤደን ገነት የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ያደርጋል።—ዘፍ. 3:15
12 ይሖዋ የገባቸውን ቃሎች በመፈጸም ረገድ ባስመዘገበው ታሪክ ላይ ማሰላሰላችን አዲስ ዓለም ለማምጣት ኃይል እንዳለው ያለንን እምነት ያጠናክረዋል። (ኢያሱ 23:14፤ ኢሳይያስ 55:10, 11ን አንብብ።) ይህ ደግሞ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ የተሰጠን ተስፋ በእርግጥ እውን እንደሚሆን ለሌሎች ለማስረዳት ያስችለናል። ይሖዋ ራሱ ስለ አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር ሲናገር “እነዚህ ቃላት አስተማማኝና እውነት [ናቸው]” ብሏል።—ራእይ 21:1, 5
it-2 1201 አን. 2
ቃል
ማሰብ የሚችሉም ሆነ ግዑዛን ፍጥረታት ለአምላክ ቃል ይታዘዛሉ፤ እሱም ዓላማውን ለመፈጸም ሊጠቀምባቸው ይችላል። (መዝ 103:20፤ 148:8) የአምላክ ቃል እምነት የሚጣልበት ነው፤ በተጨማሪም አምላክ ቃል የገባውን ነገር መፈጸም አይረሳም። (ዘዳ 9:5፤ መዝ 105:42-45) እሱ ራሱ ስለ ቃሉ ሲናገር “ለዘላለም ጸንቶ [እንደሚኖር]” እንዲሁም ዓላማውን ሳይፈጽም እንደማይመለስ ገልጿል።—ኢሳ 40:8፤ 55:10,11፤ 1ጴጥ 1:25
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
w86 11/1 19 አን. 15
ወጣቶች—ደስታና አንድነት ላለው ቤተሰብ የምታበረክቱት ድርሻ
15 የዮሴፍ እግሮች “በእግር ብረት ደከሙ፣ እርሱም በብረት ውስጥ ገባ። ቃሉ እስኪመጣለት ድረስ (የይሖዋ) ቃል ፈተነው” ወይም አነጠረው። (መዝሙር 105:17-19) የይሖዋ ተስፋ እስኪፈጸምለት ድረስ ዮሴፍ ለ13 ዓመታት ባሪያና እሥረኛ በመሆን ብዙ መከራ ደረሰበት። በደረሱበት ሁኔታዎች ተፈተነ ወይም ጥራት ያለው ሆነ። ይሖዋ ችግሮቹን ራሱ ባያመጣቸውም ለአንድ ዓላማ ሲል እንዲመጡ ፈቀደ። ዮሴፍ በመከራ ማጥ ውስጥ ቢገባም በይሖዋ ቃል ላይ የነበረውን ተስፋ ጠብቆ ይኖር ይሆን? መልካም ባሕርዮቹን ወደ ብስለት ያደርሳቸው ይሆን? አስፈላጊውን ትዕግስት፣ ትሕትና፣ መንፈሳዊ ብርታትና አስቸጋሪ ሥራን ለመቀበል ያለውን ቆራጥነት ያዳብር ይሆን? ዮሴፍ በእሳት ነጥሮ እንደወጣ ወርቅ ሆነ። ከበፊቱ የበለጠ ጥራት ያለውና ከዚያ በኋላ በሚያስደንቅ መንገድ በተጠቀመበት አምላክ ፊት የበለጠ ክቡር ሆነ።—ዘፍጥረት 41:14, 38-41, 46፣ 42:6, 9
ከኅዳር 11-17
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 106
“አዳኛቸው የሆነውን አምላክ ረሱ”
“ከይሖዋ ጎን የሚቆም ማን ነው?”
13 እስራኤላውያን ጥቁር ደመናውንና መብረቁን ጨምሮ አምላክ የፈጸማቸውን ሌሎች አስገራሚ ምልክቶች ሲያዩ በጣም ፈሩ። በመሆኑም ሙሴ እስራኤላውያን ባቀረቡለት ጥያቄ መሠረት እነሱን ወክሎ ከይሖዋ ጋር ለመነጋገር ወደ ሲና ተራራ ወጣ። (ዘፀ. 20:18-21) ሆኖም ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እዚያ ብዙ ቆየ። እስራኤላውያን እምነት የሚጥሉበት መሪያቸው ሄዶ በመቅረቱ በምድረ በዳ ያለረዳት የተተዉ ይመስል ነበር። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው እስራኤላውያን ሙሉ እምነታቸውን የጣሉት በዓይን በሚያዩት በሙሴ ላይ ነበር። በተፈጠረው ነገር ስለተጨነቁ አሮንን እንዲህ አሉት፦ “እንግዲህ ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ ምን እንደደረሰበት ስለማናውቅ . . . ከፊት ከፊታችን የሚሄድ አምላክ ሥራልን።”—ዘፀ. 32:1, 2
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የመዝሙር ሦስተኛና አራተኛ መጻሕፍት ጎላ ያሉ ነጥቦች
106:36, 37፦ ይህ ጥቅስ የጣዖት አምልኮን ለአጋንንት ከመሠዋት ጋር አያይዞታል። ይህም ጣዖትን የሚያመልክ ሰው በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ሊሆን እንደሚችል ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ “ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ” በማለት ያሳስበናል።—1 ዮሐንስ 5:21
ከኅዳር 18-24
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 107-108
“ይሖዋ ጥሩ ስለሆነ ምስጋና አቅርቡለት”
ጉባኤው ይሖዋን ያወድሰው
2 የክርስቲያን ጉባኤ ሰዎች ተሰባስበው ከሚመሠርቱት ማኅበራዊ ቡድን የተለየ ነው። ጉባኤው አንድ ዓይነት አስተዳደግና የኑሮ ሁኔታ አሊያም በስፖርት ወይም በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች ረገድ ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የሚሰባሰቡበት ማኅበር ወይም ክበብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የጉባኤ ዝግጅት የተደረገበት ዋነኛ ዓላማ ይሖዋ አምላክን ለማወደስ ነው። የመዝሙር መጽሐፍ ጎላ አድርጎ እንደሚያሳየው ከጥንት ጀምሮም የጉባኤ ዓላማ ይህ ነበር። መዝሙር 35:18 “በታላቅ ጉባኤ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበትም አወድስሃለሁ” ይላል። በተመሳሳይም በመዝሙር 107:31, 32 ላይ “እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤ በሕዝብ ጉባኤ መካከል ከፍ ከፍ ያድርጉት” የሚል ማበረታቻ ቀርቦልናል።
ለይሖዋ ምስጋና አቅርቡለት፤ ትባረካላችሁ
4 የአመስጋኝነት መንፈስ እንድናዳብርና ምንጊዜም አመስጋኝ ልብ እንዲኖረን ከፈለግን ከይሖዋ ያገኘናቸውን በረከቶች ማስተዋልና በእነዚህ ላይ በአድናቆት ማሰላሰል እንዲሁም ይሖዋ በታማኝ ፍቅሩ ስላከናወናቸው ነገሮች በጥሞና ማሰብ አለብን። መዝሙራዊው ይህን በማድረጉ፣ ይሖዋ ባከናወናቸው በርካታ ድንቅ ነገሮች ተደምሟል።—መዝሙር 40:5፤ 107:43ን አንብብ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 420 አን. 4
ሞዓብ
ዳዊት ንጉሥ ከሆነ በኋላም በእስራኤልና በሞዓብ መካከል ጦርነት ነበር። ሞዓባውያኑ ሙሉ በሙሉ ድል ተደርገው ለዳዊት ግብር ገበሩለት። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ጦርነቱ ሲደመደም ከሞዓብ ተዋጊዎች መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ተገድለው ነበር። ዳዊት የሚገደሉትን ሁለት ሦስተኛና የሚተርፉትን አንድ ሦስተኛ ወታደሮች ለመወሰን መሬት ላይ አጋድሞ በገመድ ለካቸው። (2ሳሙ 8:2, 11, 12፤ 1ዜና 18:2, 11) የዮዳሄ ልጅ በናያህ “የሞዓቡን የአርዔልን ሁለት ወንዶች ልጆች [የገደለው]” በዚህ ውጊያ ላይ ሳይሆን አይቀርም። (2ሳሙ 23:20፤ 1ዜና 11:22) ዳዊት በሞዓባውያን ላይ ያገኘው ወሳኝ ድል ከ400 ዓመታት በፊት በለዓም የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ ነው፦ “ኮከብ ከያዕቆብ ይወጣል፤ በትረ መንግሥትም ከእስራኤል ይነሳል። የሞዓብን ግንባር፣ የሁከት ልጆችንም ሁሉ ራስ ቅል ይፈረካክሳል።” (ዘኁ 24:17) በተጨማሪም መዝሙራዊው፣ አምላክ ሞዓብን “መታጠቢያ ገንዳዬ” ብሎ እንደጠራው የገለጸው ስለዚህ ድል ሲናገር ሳይሆን አይቀርም።—መዝ 60:8፤ 108:9
ከኅዳር 25–ታኅሣሥ 1
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 109-112
ንጉሡን ኢየሱስን ደግፉ!
የመዝሙር አምስተኛ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
110:1, 2—ዳዊት “ጌታዬ” ብሎ የጠራው ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠበት ወቅት ምን ይሠራ ነበር? ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በ1914 ንጉሥ ሆኖ እስከ ተሾመበት ጊዜ ድረስ በአምላክ ቀኝ ተቀምጦ ነበር። በእነዚያ ጊዜያት በመንፈስ በተቀቡት ተከታዮቹ ላይ ይገዛ ነበር። ይህን ያደረገው በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ አመራር በመስጠትና በመንግሥቱ ከእርሱ ጋር ገዥ ለሚሆኑበት ጊዜ በማዘጋጀት ነበር።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:18-20፤ ሉቃስ 22:28-30
ከአምላክ ጋር የሚዋጉ አያሸንፉም!
3 ከ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አንስቶ የይሖዋ ሕዝቦች ጥቃት ሲደርስባቸው ቆይቷል። በብዙ አገሮች በክፋት የተነሳሱ ሰዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች እወጃ ለማስተጓጎል ብሎም ለማስቆም ሞክረዋል። እንዲህ ለማድረግ ያነሳሳቸው ደግሞ “የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ [የሚዞረው]” ቀንደኛው ባላጋራችን ዲያብሎስ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:8) ‘የተቀጠሩት የአሕዛብ ዘመናት’ በ1914 ካበቁ በኋላ አምላክ ልጁን ‘በጠላቶቹ መካከል የመግዛት’ ተልዕኮ ሰጥቶ የምድር አዲስ ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። (ሉቃስ 21:24 NW፤ መዝሙር 110:2) ክርስቶስ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ሰይጣንን ከሰማይ በማባረር በምድር አካባቢ ብቻ እንዲወሰን አድርጎታል። ዲያብሎስ የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን ስለሚያውቅ በቅቡዓኑና በተባባሪዎቻቸው ላይ ንዴቱን ሊወጣባቸው ይሞክራል። (ራእይ 12:9, 17) እነዚህ ከአምላክ ጋር የሚዋጉ ሰዎች በተደጋጋሚ የሰነዘሩት ጥቃት ውጤት ምንድን ነው?
እድገት አድርግ
ተሰጥዎህን እንድትጠቀምበት የቀረበልህን ማበረታቻ ተግባራዊ ማድረግ ቀዳሚ ሆኖ መገኘት ይጠይቅብሃል። ሌሎች አብረውህ እንዲያገለግሉ ትጠይቃለህ? ጉባኤህ ውስጥ ያሉትን አዲሶች፣ ወጣቶች እንዲሁም አቅመ ደካማ የሆኑትን ወንድሞችና እህቶች ለመርዳት ጥረት ታደርጋለህ? የመንግሥት አዳራሹን በማጽዳት ወይም በአውራጃ ስብሰባና በሌሎች ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ በተለያየ ሥራ ትሳተፋለህ? አልፎ አልፎ ረዳት አቅኚ ሆነህ ማገልገል ትችላለህ? የዘወትር አቅኚ ሆነህ ማገልገል ወይም ይበልጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ጉባኤ ተዛውረህ መርዳት ትችላለህ? የተጠመቅህ ወንድ ከሆንክ የጉባኤ አገልጋይና ሽማግሌ ለመሆን የሚያስፈልጉትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ለማሟላት እየተጣጣርህ ነው? በሥራ ለማገዝና ኃላፊነት ለመቀበል ፈቃደኛ ሆኖ መገኘት የእድገት ምልክት ነው።—መዝ. 110:3 አ.መ.ት
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
በመንግሥቱ ላይ የማይናወጥ እምነት ይኑራችሁ
15 የአብርሃም ቃል ኪዳንና የዳዊት ቃል ኪዳን የሴቲቱ ዘር ንጉሥ እንደሚሆን በግልጽ የሚያሳዩ ቢሆንም ይህ ብቻ ለሰው ዘሮች በሙሉ በረከት ለማምጣት በቂ አይሆንም። የሰው ዘሮች የተሟላ በረከት እንዲያገኙ ከኃጢአታቸው ነፃ ወጥተው ከይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ቤተሰብ ጋር አንድነት ሊኖራቸው ይገባል። ይህ እንዲሆን ደግሞ ዘሩ የክህነት አገልግሎትም መስጠት አለበት። ጠቢብ የሆነው ፈጣሪ ይህን ለማስፈጸም ሲል እንደ መልከጼዴቅ ያለ የክህነት ቃል ኪዳን በመግባት ሌላ ሕጋዊ ዝግጅት አድርጓል።
16 ይሖዋ፣ ሁለት ዓላማዎች ያሉት ቃል ኪዳን ከኢየሱስ ጋር እንደሚገባ በንጉሥ ዳዊት በኩል ተናግሯል፦ አንደኛው ዓላማ ኢየሱስ በጠላቶቹ መካከል እስኪገዛ ድረስ በአምላክ ‘ቀኝ መቀመጡ’ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዐት . . . ለዘላለም ካህን” መሆኑ ነው። (መዝሙር 110:1, 2, 4ን አንብብ።) “እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዐት” የተባለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የአብርሃም ዘሮች ተስፋይቱን ምድር ከመውረሳቸው ከረጅም ጊዜ በፊት የሳሌም ንጉሥ የሆነው መልከጼዴቅ “የልዑሉ አምላክ ካህን” ሆኖ ያገለግል ነበር። (ዕብ. 7:1-3) መልከጼዴቅ እንዲህ እንዲያደርግ በቀጥታ የሾመው ይሖዋ ነው። ንጉሥና ካህን ሆኖ እንዳገለገለ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሰው ሰው እሱ ብቻ ነው። በተጨማሪም ከእሱ በፊትም ሆነ ከእሱ በኋላ እንዲህ ያለ ቦታ የነበረው ሰው መኖሩ ስላልተገለጸ “ለዘላለም ካህን” ሊባል ይችላል።
17 ኢየሱስ ካህን ሆኖ የተሾመው ከይሖዋ ጋር በገባው በዚህ ቃል ኪዳን አማካኝነት ነው፤ እንዲሁም “በመልከጼዴቅ ሥርዓት መሠረት . . . ለዘላለም ካህን” ይሆናል። (ዕብ. 5:4-6) ይህ በግልጽ እንደሚያሳየው ይሖዋ፣ ለምድርና ለሰው ልጆች የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ለማድረግ ሲል በመሲሐዊው መንግሥት እንደሚጠቀም ሕጋዊ ማረጋገጫ ሰጥቷል።
ከታኅሣሥ 2-8
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 113-118
ለይሖዋ ምን እንመልስለታለን?
በፍቅር ታነጹ
13 ከምንም ከማንም በላይ ይሖዋን መውደድ እንዳለብን ከኢየሱስ አነጋገር በግልጽ ለመረዳት ይቻላል። ሆኖም ለይሖዋ የተሟላ ፍቅር ይዘን አንወለድም። ይህ ልናዳብረው የሚገባ ነገር ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ እሱ ስንሰማ የሰማነው ነገር ወደ እሱ እንድንሳብ አድርጎናል። ምድርን ለሰው ልጆች እንዴት እንዳዘጋጃት ደረጃ በደረጃ አወቅን። (ዘፍጥረት 2:5-23) ኃጢአት ለመጀመሪያ ጊዜ ሰብአዊውን ቤተሰብ ሲበክል የራሳቸው ጉዳይ ብሎ ከመተው ይልቅ እኛን ለመዋጀት እርምጃ በመውሰድ ለሰው ዘር ምን ዓይነት አያያዝ እንዳደረገ ተማርን። (ዘፍጥረት 3:1-5, 15) የታመኑ ሆነው የተገኙትን በደግነት የያዘ ሲሆን በመጨረሻም ኃጢአታችን ይቅር እንዲባልልን አንድያ ልጁን ሰጠ። (ዮሐንስ 3:16, 36) ይህ እየጨመረ የሚሄድ እውቀት ለይሖዋ ያለን አድናቆት እያደገ እንዲሄድ አድርጓል። (ኢሳይያስ 25:1) ንጉሥ ዳዊት ከፍቅራዊ እንክብካቤው የተነሳ ይሖዋን እንደ ወደደው ተናግሯል። (መዝሙር 116:1-9) ዛሬ ይሖዋ ይንከባከበናል፣ ይመራናል፣ ያጠነክረናል እንዲሁም ያበረታታናል። ስለ እሱ ይበልጥ ባወቅን መጠን ፍቅራችን ጥልቅ እየሆነ ይሄዳል።—መዝሙር 31:23፤ ሶፎንያስ 3:17፤ ሮሜ 8:28
በአመስጋኝነት ተቀበሉ—በሙሉ ልባችሁ ስጡ
መዝሙራዊው “ስለ ዋለልኝ ውለታ ሁሉ፣ . . . [“ለይሖዋ፣” NW] ምን ልክፈለው?” በማለት ጠይቋል። (መዝ. 116:12) ይሖዋ ለመዝሙራዊው የዋለለት ውለታ ምንድን ነው? ይህ የአምላክ አገልጋይ “ጭንቅና ሐዘን” ባጋጠመው ወቅት ይሖዋ ደግፎ አቁሞታል። እንዲሁም ‘ነፍሱን ከሞት አድኖለታል።’ በመሆኑም መዝሙራዊው፣ አንድ ነገር በማድረግ የይሖዋን ውለታ ‘መክፈል’ ፈልጓል። ታዲያ ምን ማድረግ ይችላል? ‘ስእለቴን ለይሖዋ እፈጽማለሁ’ በማለት ተናግሯል። (መዝ. 116:3, 4, 8, 10-14) ለይሖዋ የገባውን ቃል ለማክበርና አምላክ የሚጠብቅበትን ነገር ሁሉ ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር።
አንተም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ። እንዴት? ይህን የምታደርገው ምንጊዜም ከአምላክ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወትህን በመምራት ነው። ስለዚህ የይሖዋ አምልኮ በሕይወትህ ውስጥ ምንጊዜም ትልቁን ቦታ እንዲይዝ እንዲሁም በምታደርገው ነገር ሁሉ የአምላክ መንፈስ እንዲመራህ መፍቀድ ይኖርብሃል። (መክ. 12:13፤ ገላ. 5:16-18) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ላደረገልህ ነገር ሁሉ መቼም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ልትከፍለው አትችልም። ይሁንና ይሖዋን በሙሉ ልብ ለማገልገል የምትችለውን ሁሉ ማድረግህ የይሖዋን ‘ልብ ደስ ያሰኘዋል።’ (ምሳሌ 27:11) በዚህ መንገድ ይሖዋን ማስደሰት መቻል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!
ከዘሌዋውያን መጽሐፍ የምናገኛቸው ትምህርቶች
9 ሁለተኛው ትምህርት፦ ይሖዋን የምናገለግለው አመስጋኝነታችንን መግለጽ ስለምንፈልግ ነው። በጥንት ዘመን በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበራቸው የኅብረት መባዎች ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚያስተምሩን ነገር አለ። የዘሌዋውያን መጽሐፍ እንደሚያሳየው አንድ እስራኤላዊ “አመስጋኝነቱን ለመግለጽ” የኅብረት መሥዋዕት ማቅረብ ይችል ነበር። (ዘሌ. 7:11-13, 16-18) ግለሰቡ ይህን መባ የሚያቀርበው ስለሚጠበቅበት ሳይሆን በራሱ ፍላጎት ተነሳስቶ ነው። ስለዚህ የኅብረት መሥዋዕት፣ አንድ ሰው ለአምላኩ ለይሖዋ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ በፈቃደኝነት የሚያቀርበው መባ ነው። መባውን የሚያቀርበው ሰው፣ ቤተሰቡ እንዲሁም ካህናቱ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውን እንስሳ ሥጋ ይበሉ ነበር። ሆኖም የእንስሳው የተወሰኑ ክፍሎች ለይሖዋ ብቻ መቅረብ ነበረባቸው። እነዚህ የትኞቹ ክፍሎች ናቸው?
10 ሦስተኛው ትምህርት፦ ይሖዋን ስለምንወደው ምርጣችንን እንሰጠዋለን። ይሖዋ ስቡን ከእንስሳው የሰውነት ክፍሎች ሁሉ ምርጡ እንደሆነ አድርጎ ይቆጥረው ነበር። በተጨማሪም ኩላሊቶቹን ጨምሮ አንዳንድ የሰውነቱ ክፍሎች ልዩ ቦታ እንደሚሰጣቸው ገልጾ ነበር። (ዘሌዋውያን 3:6, 12, 14-16ን አንብብ።) በመሆኑም አንድ እስራኤላዊ እነዚህን የእንስሳው ክፍሎችና ስቡን መሥዋዕት አድርጎ ሲያቀርብ ይሖዋ በጣም ይደሰት ነበር። እንዲህ ያለውን መባ የሚያቀርብ እስራኤላዊ ለአምላክ ምርጡን የመስጠት ልባዊ ፍላጎት እንዳለው ያሳያል። በተመሳሳይም ኢየሱስ ለይሖዋ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ እሱን በሙሉ ነፍሱ በማገልገል በፈቃደኝነት ለይሖዋ ምርጡን ሰጥቷል። (ዮሐ. 14:31) ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ያስደስተው ነበር፤ ለአምላክ ሕጎችም ጥልቅ ፍቅር ነበረው። (መዝ. 40:8) ይሖዋ፣ ኢየሱስ በፈቃደኝነት እንደሚያገለግለው ሲመለከት ምንኛ ተደስቶ ይሆን!
11 በጥንት ዘመን ይቀርቡ እንደነበሩት የኅብረት መሥዋዕቶች ሁሉ እኛም በፈቃደኝነት ለይሖዋ የምናቀርበው አገልግሎት ለእሱ ያለንን ፍቅር የሚያሳይ ነው። ለይሖዋ የምንሰጠው ምርጣችንን ሲሆን ይህን የምናደርገውም ከልባችን ስለምንወደው ነው። ይሖዋ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አገልጋዮቹ ለእሱና ለመሥፈርቶቹ ባላቸው ጥልቅ ፍቅር ተነሳስተው እንደሚያገለግሉት ሲመለከት ምንኛ ይደሰት ይሆን! ይሖዋ የምናደርገውን ነገር ብቻ ሳይሆን አንድን ነገር ለማድረግ የተነሳሳንበትን ምክንያት ጭምር እንደሚመለከትና ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ማወቃችን ያጽናናናል። ለምሳሌ ያህል፣ በዕድሜ የገፋህ ክርስቲያን ከሆንክ እንደ ቀድሞህ የምትፈልገውን ያህል ማገልገል አትችል ይሆናል፤ ሆኖም ይሖዋ የሚመለከተው እያደረግክ ያለኸውን ነገር ብቻ እንዳልሆነ አስታውስ። በይሖዋ አገልግሎት የምታደርገው ተሳትፎ ከቁጥር የማይገባ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል፤ ይሁንና ይሖዋ እሱን አቅምህ በፈቀደ መጠን ለማገልገል ያነሳሳህ ለእሱ ያለህ ፍቅር መሆኑን ይመለከታል። ይሖዋ ለእሱ ምርጥህን በመስጠትህ ይደሰታል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
አንድ መዝሙራዊ በመንፈስ ተመርቶ “የታማኞቹ ሞት በይሖዋ ፊት ውድ ነው” ሲል ዘምሯል። (መዝ. 116:15 NW) ይሖዋ የእያንዳንዱን እውነተኛ አገልጋይ ሕይወት እጅግ ክቡር እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል። ይሁን እንጂ ይህ ጥቅስ የሚናገረው ስለ አንድ ግለሰብ ሞት ብቻ አይደለም።
የአንድን ክርስቲያን ሞት አስመልክቶ የቀብር ንግግር በሚቀርብበት ጊዜ ግለሰቡ ለይሖዋ ታማኝነቱን ጠብቆ የሞተ ቢሆንም እንኳ መዝሙር 116:15 በሟቹ ላይ እንደሚሠራ መናገር ተገቢ አይሆንም። ለምን? ምክንያቱም መዝሙራዊው የተናገረው ሐሳብ ሰፋ ያለ ትርጉም ስላለው ነው። ይህ ጥቅስ የሚያመለክተው አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹ በቡድን ደረጃ እንዲጠፉ የማይፈቅድ መሆኑን ነው፤ ምክንያቱም እጅግ ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው አድርጎ ይመለከታቸዋል።—መዝሙር 72:14ን እና 116:8ን ተመልከት።
ከታኅሣሥ 9-15
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 119:1-56
“ወጣቶች በንጽሕና መመላለስ የሚችሉት እንዴት ነው?”
w87 11/1 18 አን. 10
በሁሉም ነገር ንጹሕ ናችሁ?
10 ጳውሎስ በኤፌሶን 5:5 ላይ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፦ “እንደምታውቁትና በሚገባ እንደምትገነዘቡት ሴሰኛ ወይም ርኩስ ወይም ስግብግብ ማለትም ጣዖት አምላኪ የሆነ ማንኛውም ሰው በክርስቶስና በአምላክ መንግሥት ምንም ውርሻ የለውም።” ያም ቢሆን በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች የፆታ ብልግና በመፈጸም ይኸውም ‘በራሳቸው አካል ላይ ኃጢአት በመሥራት’ ወቀሳ ይሰጣቸዋል ወይም ይወገዳሉ። (1 ቆሮንቶስ 6:18) ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለ ሁኔታ የሚያጋጥማቸው ‘በአምላክ ቃል መሠረት ራሳቸውን ባለመጠበቃቸው’ ነው። (መዝሙር 119:9) ለምሳሌ ብዙ ወንድሞች ለመዝናናት ወጣ ሲሉ ከሥነ ምግባር አንጻር ራሳቸውን አይጠብቁም። ከእምነት አጋሮቻቸው ይልቅ ከዓለማዊ ሰዎች ጋር ወዳጅነት ይመሠርታሉ። አንዳንድ ክርስቲያኖች እነዚህ ዓለማውያን ‘በጣም ጥሩ ሰዎች ናቸው’ የሚል ሰበብ ለራሳቸው በመስጠት አብረዋቸው አጠያያቂ ድርጊቶችን ፈጽመዋል። ሌሎች ደግሞ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ከልክ በላይ ተቀራርበዋል። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ከአንዲት የሥራ ባልደረባው ጋር በጣም ከመቀራረቡ የተነሳ ቤተሰቡን ትቶ ከእሷ ጋር መኖር ጀምሯል! በውጤቱም ከጉባኤ ተወገደ። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” ማለቱ ተገቢ ነው።—1 ቆሮንቶስ 15:33
“ማሳሰቢያህ ለእኔ ደስታዬ ነው”
ይሖዋ፣ ይህ አስቸጋሪ ጊዜ የሚፈጥረውን ጫና መቋቋም እንዲችሉ የሚረዷቸውን ማሳሰቢያዎች ለአገልጋዮቹ ይሰጣል። ከእነዚህ ማሳሰቢያዎች መካከል አንዳንዶቹን የምናገኛቸው በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ወቅት ሲሆን ሌሎቹን ደግሞ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በሚቀርቡት ትምህርቶች ወይም ወንድሞች በሚሰጧቸው ሐሳቦች አማካኝነት ነው። በእነዚህ መንገዶች ከምናገኘው ትምህርት ውስጥ አብዛኛው ለእኛ አዲስ አይደለም። ቀደም ሲል ተመሳሳይ ሐሳብ አጋጥሞን ሊሆን ይችላል። ሆኖም የመርሳት ባሕርይ ስላለን የይሖዋን ዓላማ፣ ሕግጋትና መመሪያዎች በተመለከተ በየጊዜው ማሳሰቢያ ማግኘት ያስፈልገናል። የአምላክን ማሳሰቢያዎች ማድነቅ ይገባናል። እነዚህ ማሳሰቢያዎች ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ሕይወት እንድንመራ ባደረጉን ምክንያቶች ላይ እንድናተኩር በመርዳት መንፈሳችንን ያድሱልናል። መዝሙራዊው “ምስክርነትህ [“ማሳሰቢያህ፣” NW] ለእኔ ደስታዬ ነው” ሲል ለይሖዋ የዘመረው በዚህ ምክንያት ነው።—መዝሙር 119:24
ከንቱ ነገር ከማየት ዓይናችሁን መልሱ!
2 ይሁንና የምናየው ነገር ጉዳት ሊያስከትልብንም ይችላል። የምናየው ነገር በአእምሯችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር በዓይናችን የሚገባው ነገር በልባችን ውስጥ አንድ ዓይነት ፍላጎት ወይም ምኞት እንዲጠነሰስ ሊያደርግ ወይም ቀድሞውኑም የነበረውን ምኞት ሊያባብሰው ይችላል። ሰይጣን ዲያብሎስ በሚገዛው እንዲሁም በሥነ ምግባር ባዘቀጠና የራሱን ፍላጎት ብቻ ለማርካት በሚሮጥ ዓለም ውስጥ ስለምንኖር ከትክክለኛው ጎዳና ስተን እንድንሄድ ሊያደርጉን የሚችሉ ምስሎችና ፕሮፖጋንዳዎች ይዥጎደጎዱብናል፤ እነዚህን ነገሮች የተመለከትናቸው ለቅጽበት ያህል ብቻ እንኳ ቢሆን ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድሩብናል። (1 ዮሐ. 5:19) በመሆኑም መዝሙራዊው “ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ፤ በራስህ መንገድ እንደ ገና ሕያው አድርገኝ” በማለት አምላክን መማጸኑ ምንም አያስገርምም።—መዝ. 119:37
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
በይሖዋ ቃል ታመኑ
2 በመዝሙር 119 ላይ የጎላው ነጥብ የአምላክ ቃል ወይም መልእክት ያለው ጠቀሜታ ነው። ጸሐፊው መዝሙሩን ያሠፈረው በፊደል ቅደም ተከተል ሲሆን ይህም ለማስታወስ እንዲረዳው ብሎ ያደረገው ይሆናል። አንድ መቶ ሰባ ስድስት ጥቅሶችን የያዘው ይህ መዝሙር በዕብራይስጥ ሆሄ ቅደም ተከተል መሠረት የተጻፈ ነው። መጀመሪያ በተጻፈበት በዕብራይስጥ ቋንቋ በመዝሙሩ ውስጥ የሚገኙት 22 አንቀጾች በተመሳሳይ ፊደል የሚጀምሩ 8 መስመሮች ነበሯቸው። መዝሙሩ ስለ አምላክ ቃል፣ ሕግ፣ ምስክርነት (ማሳሰቢያዎች)፣ መንገዶች፣ ደንቦች፣ ሥርዓቶች፣ ትእዛዛት፣ ፍርዶች፣ ቃሎችና ድንጋጌዎች ይናገራል። በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ መዝሙር 119 በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ትርጉም መሠረት ይብራራል። ጥንት የነበሩና በዘመናችን ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ባሳለፉት ሕይወት ላይ ማሰላሰላችን በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት ለተጻፈው ለዚህ መዝሙር ያለንን ግንዛቤ የሚያሰፋልን ከመሆኑም ሌላ በጽሑፍ ለሰፈረው የአምላክ ቃል ማለትም ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለንን አመስጋኝነት ያሳድግልናል።
ከታኅሣሥ 16-22
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 119:57-120
መከራን በጽናት መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
“ሕግህን ምንኛ ወደድሁ!”
2 “የአምላክ ሕግ ለመዝሙራዊው የብርታትና የመጽናናት ምንጭ የሆነለት እንዴት ነው?” ብለን እንጠይቅ ይሆናል። እንዲጽናና የረዳው ይሖዋ እንደሚያስብለት እርግጠኛ መሆኑ ነው። መዝሙራዊው ጠላቶቹ ችግር ቢያደርሱበትም እንኳን የአምላክን ፍቅራዊ ሕግ መታዘዝ የሚያስገኘውን ጥቅም ማወቁ ደስተኛ እንዲሆን አስችሎታል። ይሖዋም በደግነት እንደያዘው ተገንዝቦ ነበር። ከሁሉም በላይ በአምላክ ሕግ ውስጥ የሚገኘውን መመሪያ በሥራ ላይ ማዋሉ ከጠላቶቹ ይልቅ አስተዋይና ሕያው አድርጎታል። በተጨማሪም ሕጉን መታዘዙ ሰላምና ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረው አድርጓል።—መዝሙር 119:1, 9, 65, 93, 98, 165
ለይሖዋ ማሳሰቢያዎች ልባዊ ፍቅር አላችሁን?
3 የአምላክ ማሳሰቢያዎች “ትእዛዝህን ለመጠበቅ ጨከንሁ አልዘገየሁምም። የኀጥአን ገመዶች ተተበተቡብኝ፤ ሕግህን ግን አልረሳሁም” በማለት ለዘመረው መዝሙራዊ እጅግ የተወደዱ ነበሩ። (መዝሙር 119:60, 61) ሰማያዊ አባታችን ጠላቶቻችን የሚተበትቡብንን ገመድ እንደሚበጣጥስልን እርግጠኞች ስለሆንን የይሖዋ ማሳሰቢያዎች ስደትን በጽናት እንድንቋቋም ይረዱናል። የመንግሥቱን የስብከት ሥራችንን ለመፈጸም እንችል ዘንድ በጊዜው እንዲህ ያሉትን መሰናክሎች ያስወግድልናል።—ማርቆስ 13:10
የመዝሙር አምስተኛ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
119:71—በመከራ ውስጥ ማለፍ መልካም የሚሆነው እንዴት ነው? መከራ በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ እንድንታመን፣ ከልብ ወደ እርሱ እንድንጸልይ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት እንድናጠናና ያገኘነውን እውቀት ተግባራዊ እንድናደርግ ያስተምረናል። ከዚህም በላይ መከራ ሲደርስብን የምንወስደው እርምጃ ያለን ጉድለት ጎልቶ እንዲታይ ያደርጋል። መከራ እንዲያስተካክለን ወይም እንዲያጠራን የምንፈቅድ ከሆነ እንድንማረር አያደርገንም።
“ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ”
3 ከሐዘናችን እንድንጽናና ከማንም በላይ ሊረዳን የሚችለው ሩኅሩኅ የሆነው የሰማዩ አባታችን ይሖዋ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4ን አንብብ።) የሌሎችን ስሜት በመረዳት ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ የሚሆነው ይሖዋ፣ “የማጽናናችሁ እኔ ራሴ ነኝ” የሚል ማረጋገጫ ለሕዝቡ ሰጥቷቸዋል።—ኢሳ. 51:12፤ መዝ. 119:50, 52, 76
5 ይሖዋ እንደሚያጽናናን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በመሆኑም ከደረሰብን ሐዘን ጋር በተያያዘ የልባችንን አውጥተን ለእሱ ከመናገር ወደኋላ ልንል አይገባም። ይሖዋ ሥቃያችንን እንደሚረዳልንና በጣም የሚያስፈልገንን መጽናኛ እንደሚሰጠን ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ይሁን እንጂ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው?
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የመዝሙር አምስተኛ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
119:96—‘ለፍጹምነት ሁሉ ዳርቻ አለው’ ሲባል ምን ማለት ነው? ‘ለፍጹምነት ሁሉ ዳርቻ አለው’ ሲባል ምን ማለት ነው? መዝሙራዊው ስለ ፍጽምና የተናገረው ከሰው አመለካከት አንጻር ነው። እንዲሁም ሰው ስለ ፍጽምና ያለው እውቀት ውስን መሆኑን በአእምሮው ይዞ መሆን አለበት። በአንጻሩ ደግሞ የአምላክ ትእዛዝ እንዲህ ያለ ወሰን የለውም። የእርሱ መመሪያ በሁሉም የሕይወት ዘርፎች የሚሠሩ ናቸው።
ከታኅሣሥ 23-29
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 119:121-176
ከአላስፈላጊ የስሜት ሥቃይ ራሳችንን መጠበቅ
የአምላክን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በመጠቀም ሕሊናችሁን አሠልጥኑ
5 የአምላክ ሕጎች ሕሊናችንን እንዲያሠለጥኑት፣ እነዚህን ሕጎች ከማንበብ ወይም ከማወቅ ያለፈ ነገር ማድረግ ያስፈልገናል። ለሕጎቹ ፍቅርና አክብሮት ማዳበር ይኖርብናል። የአምላክ ቃል “ክፉ የሆነውን ጥሉ፤ መልካም የሆነውንም ውደዱ” ይላል። (አሞጽ 5:15) ይሁንና እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ቁልፉ፣ ይሖዋ ለነገሮች ያለው ዓይነት አመለካከት ማዳበር ነው። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፦ እንቅልፍ አልወስድ ብሎህ ተቸግረሃል እንበል። ሐኪምህ ጤናማ የአመጋገብ ልማድ እንዲኖርህ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንድታደርግና በሕይወትህ ውስጥ ሌሎች አስፈላጊ ለውጦችን እንድታደርግ የሚረዳህ ጠቃሚ ምክር ሰጠህ። ምክሩን በተግባር ስታውል ጥሩ እንቅልፍ መተኛት ቻልክ! ሐኪሙ ላደረገልህ እርዳታ በጣም አመስጋኝ እንደምትሆን ጥርጥር የለውም።
6 በተመሳሳይም ፈጣሪያችን የሰጠን ሕጎች ኃጢአት መሥራት ከሚያስከትለው መዘዝ ይጠብቁናል፤ እንዲሁም የተሻለ ሕይወት እንድንመራ ይረዱናል። ለምሳሌ ከውሸት፣ ከማጭበርበር፣ ከስርቆት፣ ከፆታ ብልግና፣ ከዓመፅ እንዲሁም ከመናፍስታዊ ድርጊቶች እንድንርቅ የሚመክሩንን የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎች መታዘዛችን ምን ያህል እንደሚጠቅመን እናስብ። (ምሳሌ 6:16-19ን አንብብ፤ ራእይ 21:8) የይሖዋን መመሪያዎች መከተል የሚያስገኘውን ታላቅ ጥቅም በሕይወታችን ውስጥ ስንመለከት ለይሖዋም ሆነ ለሕጎቹ ያለን ፍቅርና አድናቆት እየጨመረ እንደሚሄድ ጥርጥር የለውም።
ወጣቶች ሆይ፤ ምን ነገር እየተከታተላችሁ ነው?
12 ከሁሉ በላይ ደግሞ መጥፎ የሆነውን ነገር መጥላትን ወይም መጸየፍ መማር ያስፈልግሃል። (መዝሙር 97:10) በመጀመሪያ ላይ ሊያስደስት የሚችልን ነገር መጥላት የሚቻለው እንዴት ነው? ስለሚያስከትላቸው ውጤቶች በማሰብ ነው። “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳል።” (ገላትያ 6:7, 8) በስሜትህ ለመሸነፍ በምትፈተንበት ጊዜ ከሁሉ በላይ ይህ ድርጊት ይሖዋን እንዴት እንደሚያሳዝነው አስብ። (ከመዝሙር 78:41 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም የማይፈለግ እርግዝና ሊመጣ ወይም እንደ ኤድስ ያለ መጥፎ በሽታ ሊይዝህ እንደሚችል አስብ። በዚህ ምክንያት የሚደርስብህን የስሜት ቀውስና ውርደት አመዛዝን። ከዚህም በተጨማሪ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ጠባሳ ሊያስከትል ይችላል። አንዲት ክርስቲያን ሴት እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ባለቤቴ ከመገናኘታችን በፊት ከሌሎች ሰዎች ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመናል። ዛሬ ሁለታችንም ክርስቲያኖች ብንሆንም ይህ የቀድሞ ተግባራችን በጋብቻችን ውስጥ ጥልና መቀናናት እንዲኖር ምክንያት ሆኖአል።” ቲኦክራቲካዊ መብቶችን የሚያሳጣህና ከክርስቲያን ጉባኤ ሊያስወግድህ የሚችል መሆኑም መዘንጋት የለበትም። (1 ቆሮንቶስ 5:9-13) ለጊዜያዊ ደስታ ይህን ሲባል ያህል ውድ ዋጋ መክፈል ተገቢ ነውን?
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአምላክ ቃል “እውነት” እንደሆነ ተማመኑ
2 እኛ የይሖዋ አገልጋዮች፣ እሱ “የእውነት አምላክ” እንደሆነና ምንጊዜም ለእኛ ጥቅም እንደሚያስብ እርግጠኞች ነን። (መዝ. 31:5፤ ኢሳ. 48:17) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ልንተማመንበት እንደምንችል እንዲሁም “[የቃሉ] ፍሬ ነገር እውነት” እንደሆነ እናውቃለን። (መዝሙር 119:160ን አንብብ።) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር በጻፉት ሐሳብ እንስማማለን፤ እንዲህ ብለዋል፦ “አምላክ የተናገረው ማንኛውም ነገር ውሸት ሊሆን ወይም ሊከሽፍ የሚችልበት ምንም መንገድ የለም። የአምላክ ሕዝቦች አምላክን ስለሚያምኑት እሱ በተናገረው ነገር መተማመን ይችላሉ።”
ከታኅሣሥ 30–ጥር 5
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 120-126
በእንባ ዘርተው በእልልታ አጨዱ
ለአምላክ ክብር የሚሰጡ የተባረኩ ናቸው
10 የደቀ መዝሙርነትን ቀንበር በምንሸከምበት ጊዜ ሰይጣንን እንደተቃወምነው ይቆጠራል። ያዕቆብ 4:7 “ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል” የሚል ተስፋ ይሰጣል። እንዲህ ሲባል ግን ዲያብሎስን መቃወም ቀላል ነው ማለት አይደለም። አምላክን ማገልገል ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል። (ሉቃስ 13:24) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ መዝሙር 126:5 ላይ “በእንባ የሚዘሩ፣ በእልልታ ያጭዳሉ” የሚል ተስፋ ይዟል። አዎን፣ የምናመልከው አምላክ አመስጋኝ ነው። ‘ከልብ ለሚሹት ዋጋ የሚሰጥ’ ሲሆን ክብር የሚሰጡትን ደግሞ ይባርካቸዋል።—ዕብራውያን 11:6
ጠንካራ እምነት ይዛችሁ ትገኙ ይሆን?
17 የምትወዱትን ሰው በሞት በማጣታችሁ ምክንያት በሐዘን ተውጣችኋል? ከሞት ስለተነሱ ሰዎች የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን በማንበብ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያላችሁን እምነት አጠናክሩ። የቤተሰባችሁ አባል ከጉባኤ በመወገዱ ምክንያት ልባችሁ በሐዘን ተሰብሯል? አምላክ የሚሰጠው ተግሣጽ ምንጊዜም ጠቃሚ እንደሆነ ያላችሁን እምነት ለማጠናከር የግል ጥናት አድርጉ። ያጋጠማችሁ ችግር ምንም ይሁን ምን አጋጣሚውን እምነታችሁን ለመገንባት ተጠቀሙበት። ልባችሁን በይሖዋ ፊት አፍስሱ። ራሳችሁን አታግልሉ፤ ከዚህ ይልቅ ከወንድሞቻችሁና ከእህቶቻችሁ ጋር ተቀራረቡ። (ምሳሌ 18:1) ለመጽናት በሚረዷችሁ እንቅስቃሴዎች ተካፈሉ፤ በእነዚህ እንቅስቃሴዎች የምትካፈሉት እያለቀሳችሁ ቢሆንም እንኳ እንዲህ ማድረጋችሁን አታቁሙ። (መዝ. 126:5, 6) አዘውትራችሁ በስብሰባዎች ላይ ተገኙ፤ በአገልግሎት ተካፈሉ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን አንብቡ። በተጨማሪም ይሖዋ ባዘጋጀላችሁ በረከቶች ላይ ምንጊዜም ትኩረት አድርጉ። ይሖዋ የሚረዳችሁ እንዴት እንደሆነ ስታስተውሉ በእሱ ላይ ያላችሁ እምነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ይጠናከራል።
በመከሩ ሥራ ወደፊት ግፉ!
13 በመዝሙር 126:5, 6 ላይ የሚገኙት “በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ [“ያጭዳሉ፣” NW]። በሄዱ ጊዜ፣ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ” የሚሉት ቃላት ለአምላክ የመከር ሠራተኞች በተለይም ስደት እየደረሰባቸው ላሉት ትልቅ ማጽናኛ ይሆናሉ። ስለ መዝራትና ማጨድ የሚናገሩት የመዝሙራዊው ቃላት ከጥንቷ ባቢሎን ከምርኮ የተመለሱትን ቀሪዎች ይሖዋ እንደተንከባከባቸውና እንደባረካቸው የሚያሳዩ ናቸው። ነፃ በወጡበት ወቅት እጅግ ተደስተው የነበረ ቢሆንም በግዞት በቆዩባቸው 70 ዓመታት ምንም ባልተሠራበት ጠፍ መሬት ላይ ዘራቸውን በመዝራታቸው አልቅሰው ሊሆን ይችላል። ሆኖም መዝራታቸውንና የግንባታ እንቅስቃሴያቸውን የገፉበት የድካማቸውን ፍሬ እንዲሁም እርካታ አግኝተዋል።
14 እኛ ራሳችን ፈተና ሲያጋጥመን ወይም እኛም ሆንን የእምነት ባልንጀሮቻችን ለጽድቅ ስንል መከራ ሲደርስብን ልናለቅስ እንችላለን። (1 ጴጥሮስ 3:14) መጀመሪያ ላይ በአገልግሎቱ ምንም ያህል ብንደክም ፍሬ አናገኝ ይሆናል፤ ይህም የመከሩ ሥራችንን አስቸጋሪ እንዲሆን ሊያደርግብን ይችላል። ይሁን እንጂ መዝራታችንንና ማጠጣታችንን ከቀጠልን አምላክ ብዙውን ጊዜ እኛ ከጠበቅነው በላይ እንዲያድግ ያደርገዋል። (1 ቆሮንቶስ 3:6) መጽሐፍ ቅዱስንና ቅዱስ ጽሑፋዊ ጽሑፎችን በማሰራጨት ያገኘነው ውጤት ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
‘መጠጊያችን የሆነው አምላክ’—ለመጠበቅ የሚጠቀምበት ኃይል
15 በመጀመሪያ ደረጃ አምላክ የሚያደርግልንን አካላዊ ጥበቃ እንመልከት። የይሖዋ አምላኪዎች እንደመሆናችን መጠን አምላክ በቡድን ደረጃ እንዲህ ዓይነቱን ጥበቃ ያደርግልናል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን። አለዚያ ለሰይጣን ጥቃት በእጅጉ የተጋለጥን እንሆናለን። “የዚህ ዓለም ገዢ” የሆነው ሰይጣን እውነተኛውን አምልኮ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ቢችል በጣም ደስ እንደሚለው መገመት አያዳግትም። (ዮሐንስ 12:31፤ ራእይ 12:17) አንዳንድ ኃያላን መንግሥታት የስብከት ሥራችንን ከማገዳቸውም በላይ እኛን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ሞክረዋል። ይሁን እንጂ የይሖዋ አገልጋዮች በአቋማቸው በመጽናት ያለማሰለስ መስበካቸውን ቀጥለዋል! ኃያላን ብሔራት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውንና ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ መስለው የሚታዩትን የእነዚህን ክርስቲያኖች ሥራ ማስቆም ያልቻሉት ለምንድን ነው? ይሖዋ ኃያል በሆኑት ክንፎቹ ጥላ ስለጋረዳቸው ነው!—መዝሙር 17:7, 8