የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከኅዳር 3-9
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መኃልየ መኃልይ 1–2
እውነተኛ ፍቅር የታየበት ታሪክ
የማይከስም ፍቅር ሊኖር ይችላል?
9 ጋብቻ፣ ፍቅር የሌለበት ውል ወይም ስምምነት አይደለም። እንዲያውም ፍቅር የክርስቲያኖች ጋብቻ መለያ ነው። ይሁንና ይህ ምን ዓይነት ፍቅር ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመራ ፍቅር ነው? (1 ዮሐ. 4:8) በቤተሰብ አባላት መካከል የሚኖረው ዓይነት ተፈጥሯዊ ፍቅር ነው? በእውነተኛ ጓደኛሞች መካከል የሚኖረውን ዓይነት መቀራረብና የጠበቀ ወዳጅነት ያመለክታል? (ዮሐ. 11:3) ወይስ በተቃራኒ ፆታዎች መካከል የሚኖረው ዓይነት ፍቅር ነው? (ምሳሌ 5:15-20) በትዳር ጓደኛሞች መካከል የሚኖረው እውነተኛና ጊዜ የማይለውጠው ፍቅር ከላይ የተጠቀሱትን ሁሉ ያካትታል። ፍቅር ይበልጥ የሚታየው በቃላትም ሆነ በተግባር ሲገለጽ ነው። ባለትዳሮች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ቢጠመዱም አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር መግለጻቸው በጣም አስፈላጊ ነው! እንዲህ ያሉት የፍቅር መግለጫዎች በጋብቻ ውስጥ መተማመን እንዲኖርና ደስታ እንዲሰፍን ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ ሙሽሮች የሚያገቡት ሌሎች የመረጡላቸውን ሰው ሲሆን ተጋቢዎቹ ከሠርጉ ቀን በፊት ብዙም ላይተዋወቁ ይችላሉ፤ እንዲህ ያለ ትዳር ያላቸው ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር በቃላት መግለጻቸው ፍቅራቸው እንዲያድግና ጋብቻቸው እየጠነከረ እንዲሄድ ያደርጋል።
10 ባለትዳሮች አንዳቸው ለሌላው ፍቅራቸውን መግለጻቸው ሌላም ጥቅም አለው። ንጉሥ ሰለሞን ለሱላማዊቷ ልጃገረድ “ባለ ብር ፈርጥ፣ የወርቅ ጕትቻ” እንደሚሰጣት ነግሯት ነበር። እንዲሁም “እንደ ጨረቃ የደመቀች፣ እንደ ፀሓይ ያበራች” መሆኗን በመግለጽ የውዳሴ ቃላት አዥጎድጉዶላታል። (ማሕ. 1:9-11፤ 6:10) ወጣቷ ግን ለምትወደው እረኛ ታማኝ ነበረች። ከፍቅረኛዋ ርቃ በቆየችበት ወቅት በአቋሟ እንድትጸና የረዳትና ያጽናናት ምን ነበር? በመዝሙሩ ላይ መልሱን ነግራናለች። (ማሕልየ መሓልይ 1:2, 3ን አንብብ።) የእረኛውን “የፍቅር መግለጫዎች” ማስታወሷ ነው። ፍቅረኛዋ የተናገረው ነገር ልብን ደስ ከሚያሰኘው “ከወይን ጠጅ” የላቀ እንደሆነ ተሰምቷታል፤ ስሙም በራስ ላይ ‘እንደሚፈስ ሽቱ’ ሆኖላታል። (መዝ. 23:5፤ 104:15) በእርግጥም የትዳር ጓደኛሞች የሚጠቀሙባቸው የፍቅር መግለጫዎች የሚፈጥሩት አስደሳች ትዝታ ፍቅራቸው ዘላቂ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል። እንግዲያው ባልና ሚስት፣ አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር አዘውትረው መግለጻቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው!
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የማይከስም ፍቅር ሊኖር ይችላል?
11 የማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ ላላገቡ በተለይ ደግሞ ማግባት ለሚፈልጉ ክርስቲያኖችም ጠቃሚ ምክር ይዟል። ሱላማዊቷ ወጣት ለሰለሞን ፍቅር አልነበራትም። በመሆኑም የኢየሩሳሌምን ሴቶች “ራሱ እስኪፈልግ ድረስ፣ ፍቅርን እንዳታስነሡት ወይም እንዳትቀሰቅሱት” በማለት አምላቸዋለች። (ማሕ. 2:7፤ 3:5) ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ፍቅር ሊኖረን የሚገባው ለሁሉም ሰው አይደለም። እንግዲያው የማግባት ፍላጎት ያለው አንድ ክርስቲያን ከልቡ የሚወዳት ሴት እስኪያገኝ ድረስ በትዕግሥት መጠበቁ ጥበብ ነው።
ከኅዳር 10-16
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መኃልየ መኃልይ 3-5
ውስጣዊ ውበት ያለው ዋጋ
የማይከስም ፍቅር ሊኖር ይችላል?
8 በመዝሙሩ ውስጥ ካሉት የፍቅር መግለጫዎች መካከል በውጫዊ ውበት ላይ ያተኮሩት ሁሉም አይደሉም። እረኛው ስለ ወጣቷ አንደበት ምን እንዳለ እንመልከት። (ማሕልየ መሓልይ 4:7, 11ን አንብብ።) “ከንፈሮችሽ የማር እንጀራ ወለላ ያንጠባጥባሉ” [NW] ብሏታል። ይህን ያለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የማር እንጀራ ወለላ፣ ተቆርጦ ከቆየ ማር ይልቅ ጣፋጭ ከመሆኑም ሌላ ግሩም ጣዕም አለው። ከአንደበቷ “ወተትና ማር ይፈልቃል”፤ በሌላ አባባል ንግግሯ መልካምና ለዛ ያለው ነው። በእርግጥም እረኛው፣ “ሁለንተናሽ ውብ ነው፤ እንከንም አይወጣልሽም” ሲላት ከአካላዊ ውበቷ ባሻገር እንደተመለከተ ግልጽ ነው።
ለሥነ ምግባር ንጽሕና ሊኖረን የሚገባው አምላካዊ አመለካከት
17 የአቋም ጽናቷን የጠበቀችው ሦስተኛዋ ምሳሌ ሱነማዊቷ ልጃገረድ ነች። በለጋ ወጣትነቷና ውበቷ የተማረከው እረኛው ልጅ ብቻ ሳይሆን ባለጠጋ የነበረው ንጉሥ ሰሎሞንም ጭምር ነበር። በመኃልየ መኃልይ መጽሐፍ ውስጥ በተገለጸው ውብ ታሪክ ውስጥ ሱነማዊቷ ንጽሕናዋን ጠብቃ በመመላለሷ በዙሪያዋ ከነበሩት ሁሉ አድናቆትን አትርፋለች። ሰሎሞንን ፊት ብትነሳውም በመንፈስ አነሳሽነት ታሪኳን ጽፏል። እርሷ ያፈቀረችው እረኛም ንጹሕ አቋሟን አድንቆላታል። እንዲያውም በአንድ ወቅት ቆም ብሎ ካሰላሰለ በኋላ ሱነማዊቷን ‘ከተቆለፈ ገነት’ ጋር አመሳስሏታል። (መኃልየ መኃልይ 4:12) በጥንቷ እስራኤል ውስጥ የነበሩት ውብ የአትክልት ስፍራዎች ግሩም መዓዛ ያላቸውን አበቦችና ግርማ ያላቸውን ዛፎች ጨምሮ የተለያየ ዓይነት ያላቸው ውብ ዕጽዋትን የያዙ ነበሩ። እንዲህ ያሉት የአትክልት ቦታዎች በአጥር ወይም በግድግዳ ዙሪያቸውን የታጠሩ ሲሆን መግባት የሚቻለው በሚቆለፈው በር በኩል ብቻ ነው። (ኢሳይያስ 5:5) ሱነማዊቷ የነበራት የሥነ ምግባር ንጽሕናና ተወዳጅ ባሕርይ ለእረኛው የተለየ ውበት እንዳለው የአትክልት ስፍራ ነበር። ንጽሕናዋን የጠበቀች ነበረች። ፍቅሯን የምትለግሰው ወደፊት ባሏ ለሚሆነው ሰው ብቻ ይሆናል።
g 2/05 9 አን. 2-5
ውስጣዊ ውበት ይማርካል
ውስጣዊ ውበት ሌሎችን ሊማርክ ይችላል? ካገባች አሥር ዓመት ገደማ የሆናት ኪዮርኪና “በእነዚህ ዓመታት በሙሉ ባሌን የምወደው በሚያሳየኝ ሐቀኝነትና እውነተኝነት ምክንያት ነው። በሕይወቱ ውስጥ አምላክን ከማስደሰት የሚያስበልጠው ነገር የለም። ይህም አሳቢና አፍቃሪ እንዲሆን ረድቶታል። በሚያደርጋቸው ውሳኔዎች በሙሉ ስለ እኔ ስሜት ያስባል። በእውነት እንደሚወደኝ አውቃለሁ” ብላለች።
በ1987 ያገባው ዳንኤል “ለእኔ ሚስቴ በጣም ቆንጆ ነች። መልኳንና ቁመናዋን እወደዋለሁ። ይበልጥ የምወዳት ግን በጠባይዋ ምክንያት ነው። ሁልጊዜ ስለ ሌሎች ሰዎች ታስባለች፣ ልታስደስታቸውም ትጥራለች። በጣም ጥሩ ክርስቲያናዊ ባሕርያት አሏት። አብሬያት መኖር የሚያስደስተኝ በዚህ ምክንያት ነው” ብሏል።
በዚህ ውጪያዊ ለሆነ ነገር ብቻ ትኩረት በሚሰጥ ዓለም ውስጥ ስንኖር ጠለቅ ብለን የውስጡን ማየት ያስፈልገናል። “ተፈላጊ” የሚባለውን መልክና ቁመና ማግኘት ፈጽሞ የማይቻል ነው ባይባልም እንኳን አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ የሚያስገኘው ጥቅም በጣም ውስን ነው። እውነተኛ ውስጣዊ ውበት የሚያስገኙ ባሕርያትን ማዳበር ግን ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ቁንጅና አታላይ ነው፤ ውበትም ይረግፋል፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን የተመሰገነች ናት” ይላል። በአንጻሩ ደግሞ “በእርያ አፍንጫ ላይ እንደ ተሰካ የወርቅ ቀለበት፣ ማስተዋል የጎደላት ቆንጆ ሴት እንዲሁ ናት” ሲል ያስጠነቅቃል።—ምሳሌ 11:22፤ 31:30
የአምላክ ቃል ‘ዋጋው እጅግ ለከበረ፣ ገርና ጭምት መንፈስ ላለበት፣ ምንጊዜም ለማይጠፋ የውስጥ ሰውነት ውበት’ ትልቅ ዋጋ እንድንሰጥ ይረዳናል። (1 ጴጥሮስ 3:4) በእርግጥም ከአካላዊ ውበት በጣም የሚበልጠው ይህ ውስጣዊ ውበት ነው። በተጨማሪም ይህን ውበት ሁሉም ሰው ሊያገኘው ይችላል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
2:7፤ 3:5—ልጃገረዲቱ የቤተ መንግሥቱን ወይዛዝርት “በሚዳቋና በሜዳ ዋልያ” ያስማለቻቸው ለምንድን ነው? ሚዳቋና ዋልያ ግርማ ሞገስ የተላበሱና በውበታቸው የሚታወቁ ናቸው። በመሆኑም ሱላማጢሷ ልጃገረድ፣ የቤተ መንግሥቱ ወይዛዝርት ፍቅርን እንዳይቀሰቅሱባት ውብና ማራኪ በሆነው ነገር ሁሉ ማስማሏ ነበር።
ከኅዳር 17-23
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መኃልየ መኃልይ 6–8
በር ሳይሆን ቅጥር ሁኑ
የማይከስም ፍቅር ሊኖር ይችላል?
15 ማሕልየ መሓልይ 4:12ን አንብብ። እረኛው፣ ውዱን “የታጠረ የአትክልት ቦታ” እንደሆነች አድርጎ የገለጻት ለምንድን ነው? ወደታጠረ የአትክልት ቦታ መግባት የሚችለው ሁሉም ሰው አይደለም። መግባት የሚችለው የበሩ ቁልፍ ያለው ሰው ብቻ ነው። ሱላማዊቷ እንዲህ ባለ የአትክልት ስፍራ የተመሰለችው ፍቅሯን የምትሰጠው ልታገባው ላሰበችው ሰው ይኸውም ለእረኛው ብቻ በመሆኑ ነው። ወጣቷ ለንጉሡ ማባበያዎች አልተሸነፈችም፤ በመሆኑም ወለል ብሎ እንደሚከፈት “በር” ሳይሆን እንደ “ቅጥር” መሆኗን አሳይታለች። (ማሕ. 8:8-10) በተመሳሳይም አምላካዊ ፍርሃት ያላቸው ያላገቡ ወንዶችና ሴቶች ለሚያገቡት ሰው ካልሆነ በቀር ለሌላ ሰው ፍቅር ከማሳየት ይቆጠባሉ።
16 እረኛው በአንድ የጸደይ ዕለት አብረው በእግራቸው እንዲንሸራሸሩ ሱላማዊቷን ወጣት ጠይቋት ነበር፤ ወንድሞቿ ግን አልፈቀዱላትም። ከዚህ ይልቅ የወይን እርሻዎች ጠባቂ አደረጓት። ይህን ያደረጉት ለምንድን ነው? ሳያምኗት ቀርተው ነው? ወይስ ሥነ ምግባር የጎደለው ነገር ትፈጽማለች ብለው ስለፈሩ? ይህን ያደረጉት እህታቸው ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንዳትገባ ጥንቃቄ ለማድረግ ብለው ነው። (ማሕ. 1:6፤ 2:10-15) ያላገባችሁ ክርስቲያኖች ከዚህ ግሩም ትምህርት ታገኛላችሁ፦ በምትጠናኑበት ወቅት ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችሁን ለመጠበቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጉ። ማንም ሰው በሌለበት ቦታ ጊዜ ከማሳለፍ ተቆጠቡ። ንጹሕ የሆኑ የፍቅር መግለጫዎችን ማሳየት ተገቢ ሊሆን ቢችልም ወደ ፈተና ሊመሯችሁ ከሚችሉ ሁኔታዎች ራቁ።
ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ቢፈጸም ምናለበት?
ይሁን እንጂ ድንግልና የከፋ መዘዝ እንዳያጋጥም ከመርዳት የበለጠ ጥቅም አለው። መጽሐፍ ቅዱስ ለወንድ ጓደኛዋ የጋለ ፍቅር ቢኖራትም ንጹሕ ሆና ስለቆየች አንዲት ወጣት ልጃገረድ ይናገራል። በዚህም ምክንያት “እኔ ቅጥር ነኝ ጡቶቼም እንደ ግንብ ናቸው” በማለት በኩራት ለመናገር ችላለች። የጾታ ግፊት ሲደርስባት በቀላሉ ‘እንደሚከፈትና ማንም ዘው ብሎ እንደሚገባበት በር’ አልነበረችም። በሥነ ምግባር ረገድ ሰው ሊደርስበት የማይችል ግንብ እንዳለው ትልቅ የቅጥር ምሽግ በመሆን ጽኑ ሆና ቆማለች! “ንጽሕት” ተብላ መጠራት የተገባት ስለነበረች ስለወደፊቱ ባሏ ስትናገር “በዚያን ጊዜም በፊቱ ሰላምን እንደምታገኝ ሆንሁ” በማለት ልትናገር ችላለች። የነበራት የአእምሮ ሰላም በሁለቱ መካከል ለነበረው እርካታ ምክንያት ሆኖአል።— መኃልየ መኃልይ 6:9, 10፤ 8:9, 10
yp2 33
አርዓያ የሚሆኑ ሰዎች—ሱላማጢሷ ወጣት
ሱላማጢሷ ወጣት ከፍቅር ጋር በተያያዘ ስሜቷ እንዳያሸንፋት መጠንቀቅ እንዳለባት ታውቅ ነበር። ጓደኞቿን “ራሱ እስኪፈልግ ድረስ፣ ፍቅርን እንዳታስነሡት ወይም እንዳትቀሰቅሱት አማጥናችኋለሁ” ብላቸዋለች። ሱላማጢሷ ወጣት ስሜቷ የማመዛዘን ችሎታዋን በቀላሉ ሊያዛባው እንደሚችል አስተውላ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ለእሷ የማይሆናት ሰው የሚያቀርብላትን የፍቅር ጥያቄ እንድትቀበል ሌሎች ሊገፋፏት እንደሚችሉ ተገንዝባ ነበር። የራሷ ስሜትም እንኳ የማስተዋል ችሎታዋን ሊያዛባው ይችላል። በመሆኑም ሱላማጢሷ ወጣት እንደ “ቅጥር” ወይም ግንብ ለመሆን ቆርጣ ነበር።—ማሕልየ መሓልይ 8:4, 10
አንቺስ የፍቅር ግንኙነትን በተመለከተ እንደ ሱላማጢሷ በሳል የሆነ አስተሳሰብ አለሽ? በስሜትሽ ብቻ ከመመራት ይልቅ በማሰብ ችሎታሽ መጠቀም ትችያለሽ? (ምሳሌ 2:10, 11) አንቺ የፍቅር ጓደኝነት ለመጀመር ዝግጁ እንደሆንሽ ባይሰማሽም አንዳንድ ጊዜ ሰዎች እንዲህ እንድታደርጊ ይገፋፉሽ ይሆናል። በውስጥሽ የምታብሰለስይው ነገርም እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዲያድርብሽ ሊያደርግሽ ይችላል። ለምሳሌ፣ አንድ ወንድና አንዲት ሴት እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲሄዱ ስትመለከቺ አንቺም የፍቅር ጓደኛ እንዲኖርሽ በጣም ትጓጊያለሽ? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነትሽን ከማይጋራ ሰው ጋር እንኳ የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ፈቃደኛ ትሆኛለሽ? ሱላማጢሷ ወጣት ከፍቅር ግንኙነት ጋር በተያያዘ ብስለት እንዳላት አሳይታለች። አንቺም እንደ እሷ መሆን ትችያለሽ!
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የማይከስም ፍቅር ሊኖር ይችላል?
3 ማሕልየ መሓልይ 8:6ን አንብብ። ፍቅርን ለመግለጽ የተሠራበት ‘የያህ ነበልባል’ የሚለው ሐረግ ትልቅ ትርጉም አለው። እውነተኛ ፍቅር ‘የያህ ነበልባል’ የተባለው እንዲህ ያለው ፍቅር ምንጭ ይሖዋ ስለሆነ ነው። ሰው የተፈጠረው በአምላክ አምሳል በመሆኑ ፍቅር የማንጸባረቅ ችሎታ አለው። (ዘፍ. 1:26, 27) አምላክ የመጀመሪያዋን ሴት ማለትም ሔዋንን ወደ አዳም ሲያመጣት አዳም ደስታውን የገለጸው በግጥም ነው ሊባል ይችላል። ሔዋን ‘የተገኘችው’ ከአዳም በመሆኑ በጣም ትቀርበው እንደነበር ጥርጥር የለውም። (ዘፍ. 2:21-23) ይሖዋ፣ ሰዎችን ሲፈጥር ፍቅር ማሳየት እንዲችሉ አድርጎ በመሆኑ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ጊዜ የማይለውጠውና የማይከስም ፍቅር ሊኖር ይችላል።
ከኅዳር 24-30
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 1–2
‘ከባድ በደል ለተጫናቸው’ የሚሆን ማጽናኛ
አባትና ዓመፀኛ ልጆቹ
8 ኢሳይያስ ጠንከር ያሉ ቃላት በመጠቀም ስለ ይሁዳ ብሔር የሚናገረውን መልእክት ቀጠለ፦ “ኃጢአተኛ ወገንና በደል የተሞላበት ሕዝብ [“የበደል ብዛት የተጫናችሁ፣” 1980 ትርጉም ]፣ ክፉዎች ዘር፣ ርኩሰትን የምታደርጉ ልጆች ሆይ፣ ወዮላችሁ! እግዚአብሔርን ትተዋል የእስራኤልንም ቅዱስ አቃልለዋል ወደ ኋላቸውም እየሄዱ ተለይተዋል።” (ኢሳይያስ 1:4) የክፋት ድርጊቶች ተጠራቅመው ከባድ ሸክም ሊሆኑ ይችላሉ። በአብርሃም ዘመን ይሖዋ የሰዶምና ገሞራ ኃጢአት “እጅግ ከብዳለች” ሲል ተናግሯል። (ዘፍጥረት 18:20) በወቅቱ በይሁዳ ሕዝብ ላይ የሚታየውም ሁኔታ ተመሳሳይ ነበር። ኢሳይያስ ‘የበደል ብዛት የተጫናቸው’ መሆኑን ገልጿል። በተጨማሪም “ክፉዎች ዘር፣ ርኩሰትን የምታደርጉ ልጆች ሆይ” በማለት ጠርቷቸዋል። አዎን፣ የይሁዳ ሰዎች እንደ አጥፊ ልጅ ሆነው ነበር። “ወደ ኋላቸው እየሄዱ ተለይተዋል” ወይም ኒው ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርሽን እንዳስቀመጠው ከሰማያዊ አባታቸው “ፈጽሞ ርቀዋል።”
“እርቅ እንፍጠር”
15 አሁን ደግሞ ይሖዋ ይበልጥ ፍቅራዊ በሆነና ርኅራኄ በተንጸባረቀበት ስሜት ተናግሯቸዋል። “ኑና እንዋቀስ [“እርቅ እንፍጠር፣” NW ] ይላል እግዚአብሔር፤ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች።” (ኢሳይያስ 1:18 ) በዚህ ግሩም ጥቅስ መክፈቻ ላይ የሚገኘው ጥሪ ብዙውን ጊዜ የተሳሳተ ትርጉም ይሰጠዋል። ለምሳሌ ያህል ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል ሁለቱም ወገኖች አንድ ስምምነት ላይ ለመድረስ ሲሉ ይዘውት የነበረውን አቋም ማላላት ያለባቸው ይመስል ይህን ቃል “እንደራደር” በማለት ተርጉሞታል። ግን እንደዚያ አይደለም! ይሖዋ ዓመፀኛና ግብዝ ከነበረው ከዚህ ሕዝብ ጋር ይቅርና ከማንም ጋር ባለው ግንኙነት ቢሆን የሚነቀፍበት ነገር የለም። (ዘዳግም 32:4, 5) ጥቅሱ የሚናገረው እኩል ሁኔታ ባላቸው ወገኖች መካከል ስለሚደረግ ውይይት ሳይሆን ፍትሕ ለማስጠበቅ ሲባል ስለተሰየመ ችሎት ነው። ይሖዋ እስራኤላውያንን ችሎት ፊት ያቀረባቸው ያህል ነው።
16 ይህ የሚያስፈራ ነገር መስሎ ሊታይ ቢችልም ይሖዋ በጣም መሐሪና ርኅሩኅ ዳኛ ነው። ይቅር የማለት ችሎታው አቻ የለውም። (መዝሙር 86:5 NW ) እንደ “አለላ” የሆነችውን የእስራኤል ኃጢአት እንደ “አመዳይ” ሊያነጣው የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። የትኛውም ሰብዓዊ ጥረት፣ ዘዴ፣ ሥራ፣ መሥዋዕት ወይም ጸሎት የኃጢአትን እድፍ ሊያስወግድ አይችልም። ኃጢአትን አጥቦ ማስወገድ የሚችለው የይሖዋ ይቅርታ ብቻ ነው። ይሖዋ ይህን ይቅር ባይነት የሚያሳየው እርሱ ያወጣው መስፈርት ሲሟላ ማለትም እውነተኛና ልባዊ ንስሐ ሲያሳዩ ብቻ ነው።
17 ይህ እውነት በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሣ ይሖዋ በሌላ ምሳሌያዊ መግለጫ በመጠቀም ‘እንደ ደም የቀላችው’ ኃጢአት ቀለም እንዳልተነከረ ‘አዲስ ባዘቶ ጥጥ እንደምትነጣ’ ተናግሯል። ይሖዋ እውነተኛ ንስሐ ገብተን እስካገኘን ድረስ ከባድ የሆኑ ኃጢአቶችን ሳይቀር ይቅር የሚል መሆኑን እንድናውቅ ይፈልጋል። ይሖዋ የእነርሱን ኃጢአት ይቅር እንደማይላቸው የሚሰማቸው ሰዎች ካሉ እንደ ምናሴ ያሉትን ሰዎች ምሳሌ መመርመራቸው የተገባ ይሆናል። ለዓመታት ከባድ ኃጢአት ሲፈጽም ቢቆይም ንስሐ በመግባቱ ይቅርታ አግኝቷል። (2 ዜና መዋዕል 33:9-16) ይሖዋ ከባድ ኃጢአቶች የፈጸሙትን ጨምሮ ሁላችንም ከእርሱ ጋር ‘እርቅ ለመፍጠር’ አሁንም ጊዜ እንዳለን እንድናውቅ ይፈልጋል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የይሖዋ ቤት ከፍ ከፍ ብሏል
9 እርግጥ ዛሬ የአምላክ ሕዝቦች ቃል በቃል በድንጋይ የተሠራ ቤተ መቅደስ ወዳለበት አንድ ተራራ አይሰበሰቡም። በኢየሩሳሌም የነበረው የይሖዋ ቤተ መቅደስ በ70 እዘአ በሮማውያን ሠራዊት ተደምስሷል። ከዚህም በላይ ሐዋርያው ጳውሎስ በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስም ሆነ ከዚያ በፊት ሲያገለግል የቆየው የመገናኛው ድንኳን ምሳሌያዊ ጥላ ብቻ እንደነበሩ ግልጽ አድርጓል። ሁለቱም የሚወክሉት አንድን ታላቅ መንፈሳዊ እውነታ ይኸውም ‘በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለችውን እውነተኛይቱን ድንኳን’ ነው። (ዕብራውያን 8:2) ይህ መንፈሳዊ ድንኳን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ለአምልኮ ወደ ይሖዋ ለመቅረብ የሚያስችል ዝግጅት ነው። (ዕብራውያን 9:2-10, 23) ከዚሁ ጋር በሚስማማ መንገድ በኢሳይያስ 2:2 ላይ የተገለጸው ‘የይሖዋ ቤት ተራራ’ የሚያመለክተው በጊዜያችን ያለውን ከፍ ያለ ክብር የተጎናጸፈውን የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ነው። ንጹሑን አምልኮ የሚቀበሉ ሰዎች በአምልኮ አንድነት ይሰባሰባሉ እንጂ በአንድ የተወሰነ ስፍራ መሰብሰብ አያስፈልጋቸውም።
ከታኅሣሥ 1-7
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 3–5
ይሖዋ ተጨማሪ ነገር የመጠበቅ መብት ነበረው
ከዳተኛ ለሆነው የወይን ቦታ ወዮ!
3 ኢሳይያስ ይህን ምሳሌ ቃል በቃል የተቀኘው ያዳምጡት ለነበሩት ሰዎች ሆነም አልሆነ ትኩረታቸውን ስቦ እንደነበር ምንም አያጠራጥርም። አብዛኛዎቹ ከወይን እርሻ ጋር ትውውቅ ስለሚኖራቸው ኢሳይያስ የሰጠው መግለጫ ሕያውና ተጨባጭ ነበር። ዛሬ ያሉት የወይን አትክልተኞች እንደሚያደርጉት ሁሉ የወይን ቦታው ባለቤት የሚተክለው የወይኑን ዘር ሳይሆን “ምርጥ የሆነውን” ወይም ጥራት ያለውን “የቀይ ወይን” ቅጥፍ ወይም ግርንጫፍ ነው። ለወይን ተክል የሚስማማ ዓይነት ቦታ በመሆኑ የወይን ቦታውን “በፍሬያማው ኮረብታ ላይ” ማድረጉ ተገቢ ነው።
4 አንድ የወይን ቦታ ፍሬ እንዲሰጥ ማድረግ ጥረት ይጠይቃል። ኢሳይያስ የወይኑ ቦታ ባለቤት ‘መሬቱን መቆፈሩንና ድንጋዮችንም ለቅሞ ማውጣቱን’ ተናግሯል። ይህ አሰልቺና አድካሚ ሥራ ነው! ‘ግንብ ለመሥራት’ የተጠቀመባቸው ትላልቆቹን ድንጋዮች ሳይሆን አይቀርም። በጥንት ዘመን እንዲህ ዓይነት ግንቦች ማሳውን ከሌቦችና ከእንስሳት ለሚጠብቁት ሰዎች እንደ ማማ ያገለግሉ ነበር። ከዚህም ሌላ የወይን ቦታውን ለመከለል የድንጋይ ቅጥር ሠርቷል። (ኢሳይያስ 5:5) አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ የሚደረገው በጣም አስፈላጊ የሆነው የላይኛው አፈር ተሸርሽሮ እንዳይወሰድ ለመከላከል ነበር።
5 የወይኑ ቦታ ባለቤት ለዚህ የወይን ቦታ ይህን ያህል በመድከሙ ፍሬ ያፈራል ብሎ መጠበቁ ተገቢ ነው። ይህንንም በማሰብ የመጥመቂያ ጉድጓድ ምሷል። ይሁን እንጂ ፍሬ ለመሰብሰብ የነበረው ተስፋ እውን ሆኖለታል? አልሆነለትም። እንዲያውም የወይን ቦታው ያፈራው ሆምጣጣ ፍሬ ነበር።
ከዳተኛ ለሆነው የወይን ቦታ ወዮ!
8 ኢሳይያስ የወይኑ ቦታ ባለቤት የሆነውን ይሖዋን “ወዳጄ” በማለት ጠርቶታል። (ኢሳይያስ 5:1) ኢሳይያስ ቅርበትን በሚያሳይ እንዲህ ዓይነት መግለጫ አምላክን ሊጠራው የቻለው ከእርሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና ስለነበረው ብቻ ነው። (ከኢዮብ 29:4 NW፤ መዝሙር 25:14 የ1980 ትርጉም ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ ነቢዩ ለአምላክ የነበረው ፍቅር፣ አምላክ ‘ለወይን ቦታው’ ማለትም ራሱ ‘ለተከለው’ ብሔር ካሳየው ፍቅር ጋር ሲወዳደር ከቁጥር አይገባም።—ከዘጸአት 15:17፤ መዝሙር 80:8, 9 ጋር አወዳድር።
9 ይሖዋ ሕዝቡን በከነዓን ምድር ‘በመትከል’ ሕጉንና መመሪያውን ሰጥቷቸዋል። ይህም በሌሎች ብሔራት እንዳይበከሉ እንደ አጥር ሆኖ አገልግሏል። (ዘጸአት 19:5, 6፤ መዝሙር 147:19, 20፤ ኤፌሶን 2:14) ከዚህም በላይ ይሖዋ የሚያስተምሯቸውንና መመሪያ የሚሰጡአቸውን መሳፍንት፣ ካህናትና ነቢያት ሰጥቷቸዋል። (2 ነገሥት 17:13፤ ሚልክያስ 2:7፤ ሥራ 13:20) እስራኤላውያን ወታደራዊ ዛቻ በደረሰባቸው ጊዜ የሚታደጓቸውን ሰዎች አስነስቶላቸዋል። (ዕብራውያን 11:32, 33) ይሖዋ “ለወይኔ ያላደረግሁለት፣ ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድር ነው?” ብሎ መጠየቁ ያለ ምክንያት አልነበረም።
“ይህችን የወይን ተክል ተንከባከባት”!
ኢሳይያስ ‘የእስራኤልን ቤት’ ውሎ አድሮ “ኮምጣጣ ፍሬ [“የዱር ወይን፣” NW]” ካፈራ የወይን ተክል ጋር አመሳስሎታል። (ኢሳይያስ 5:2, 7) ጫካ ውስጥ የሚበቅል ወይን የሚያፈራው ፍሬ መጠኑ አነስተኛ ከመሆኑም በላይ በፍሬው ውስጥ ያለው ዘር ትልቅ ነው። በመሆኑም የወይን ጠጅ ለመሥራትም ይሁን ለምግብነት የማይውለው ይህ የጫካ ወይን ከጽድቅ ይልቅ ዓመጸኝነትን ላፈራው ከሃዲ ብሔር ተስማሚ ምሳሌ ሆኖ አገልግሏል። ፍሬው እርባና ቢስ የሆነው በወይን አምራቹ ስህተት አይደለም። ይሖዋ ብሔሩ ፍሬያማ እንዲሆን የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። በመሆኑም “ከዚህ ካደረግሁለት በላይ ለወይኔ ቦታ ምን ሊደረግለት ይገባ ነበር?” ሲል ጠይቋል።—ኢሳይያስ 5:4
“ይህችን የወይን ተክል ተንከባከባት”!
የእስራኤል ወይን ፍሬ ቢስ መሆኑ በግልጽ በመታየቱ፣ ይሖዋ በሕዝቡ ዙሪያ የገነባውን የመከላከያ አጥር እንደሚያፈርስ አስጠነቀቃቸው። ይሖዋ ምሳሌያዊ ወይኑን መግረዝም ሆነ መኮትኮት አቁሞ ነበር። ለወይኑ ሕልውና አስፈላጊ የሆነው የበልግ ዝናብ ካለመዝነቡም በላይ እርሻውን አረም ወርሶት ነበር።—ኢሳይያስ 5:5, 6
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ከዳተኛ ለሆነው የወይን ቦታ ወዮ!
18 በጥንቷ እስራኤል መሬት ሁሉ የይሖዋ ነበር። እያንዳንዱ ቤተሰብ ከአምላክ ያገኘው ርስት የነበረው ሲሆን ይህን ማከራየት ወይም በብድር መስጠት ካልሆነ በስተቀር ምድሪቱን ‘ለዘለቄታው’ መሸጥ አይቻልም ነበር። (ዘሌዋውያን 25:23) ይህ ሕግ ርስትን በሞኖፖል መያዝን የመሳሰሉትን የግፍ ድርጊቶች የሚከላከል ነበር። እንዲሁም ቤተሰቦች ወደ ድህነት አራንቋ እንዳይገቡ ጠብቋቸዋል። ይሁን አንጂ በይሁዳ የነበሩ አንዳንዶች በስግብግብነት አምላክ ስለ ርስት ያወጣውን ሕግ ይጥሱ ነበር። ሚክያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በእርሻው ላይ ይመኛሉ፣ በግዴታም ይይዙታል፤ በቤቶችም ላይ ይመኛሉ፣ ይወስዱአቸውማል፤ ሰውንና ቤቱን፣ ሰውንና ርስቱንም ይነጥቃሉ።” (ሚክያስ 2:2) ሆኖም ምሳሌ 20:21 “በመጀመሪያ ፈጥኖ [“በስግብግብነት፣” NW] የተከማቸ ርስት ፍጻሜው አይባረክም” በማለት ያስጠነቅቃል።
19 ይሖዋ እነዚህ ስግብግብ ሰዎች አላግባብ ያጋበሱትን ሃብት እንደሚገፍፋቸው ተናግሯል። አላግባብ የነጠቁት ቤት ‘የሚቀመጥበት አይኖርም።’ የቋመጡለትም ምድር የሚያፈራው ፍሬ እጅግ አነስተኛ ብቻ ይሆናል። ይህ እርግማን እንዴትና መቼ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ተለይቶ የተጠቀሰ ነገር የለም። ቢያንስ ግን በከፊል ወደፊት በባቢሎን ምርኮ ወቅት የሚመጣባቸውን ነገር የሚጠቅስ ይመስላል።—ኢሳይያስ 27:10
ከታኅሣሥ 8-14
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 6–8
“እነሆኝ! እኔን ላከኝ!”
ይሖዋ አምላክ ቅዱስ በሆነው መቅደሱ ተቀምጧል
13 እስቲ አሁን ደግሞ ከኢሳይያስ ጋር ሆነን እናዳምጥ። “የጌታንም ድምፅ፦ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም፦ እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ አልሁ።” (ኢሳይያስ 6:8) በራእይው ውስጥ የተካፈለ ሌላ ሰው ስለሌለ ይሖዋ ያቀረበው ጥያቄ ኢሳይያስ ራሱ ምላሽ እንዲሰጥ የሚጠይቅ እንደነበር ግልጽ ነው። ኢሳይያስ የይሖዋ መልእክተኛ እንዲሆን የቀረበ ግብዣ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ይሖዋ “ማንስ ይሄድልናል?” ሲል የጠየቀው ለምንድን ነው? ይሖዋ ‘እኔ’ ከሚለው ነጠላ ተውላጠ ስም ‘እኛ’ ወደሚለው የብዙ ቁጥር ተውላጠ ስም በመሻገር ከራሱ ጋር ቢያንስ ሌላ አንድ አካል እንዳለ አመልክቷል። ይህ ማን ነው? ከጊዜ በኋላ ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ማለትም የእርሱ አንድያ ልጅ አይደለምን? አምላክ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” በማለት የተናገረውም ለዚሁ ልጁ ነበር። (ዘፍጥረት 1:26፤ ምሳሌ 8:30, 31) አዎን፣ በሰማያዊው መቅደስ ከይሖዋ ጋር ያለው አንድያ ልጁ ነው።—ዮሐንስ 1:14
14 ኢሳይያስ ምላሽ ለመስጠት አላመነታም! መልእክቱ ምንም ይሁን ምን ኢሳይያስ “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” በማለት ፈጣን ምላሽ ሰጥቷል። ይህንን ሥራ ብቀበል ምን አገኛለሁ ብሎም አልጠየቀም። የእርሱ የፈቃደኛነት መንፈስ በዛሬው ጊዜ ‘በዓለም ዙሪያ የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ’ ተልእኮ ለተሰጣቸው የአምላክ አገልጋዮች ግሩም ምሳሌ ነው። (ማቴዎስ 24:14) ለመልእክቱ ምላሽ የማይሰጡ ብዙ ሰዎች ቢኖሩም ‘ለአሕዛብ ሁሉ ምሥክርነት’ የመስጠት ሥራቸውን ልክ እንደ ኢሳይያስ በታማኝነት ያከናውናሉ። ተልእኳቸውን የተቀበሉት ከታላቁ ባለሥልጣን መሆኑን ስለሚገነዘቡ ልክ እንደ ኢሳይያስ በትምክህት ወደፊት ይገፋሉ።
ይሖዋ አምላክ ቅዱስ በሆነው መቅደሱ ተቀምጧል
15 ቀጥሎ ደግሞ ይሖዋ ኢሳይያስ ምን እንደሚናገርና የሰዎቹ ምላሽ ምን እንደሚሆን ይጠቅሳል፦ “ሂድ፣ ይህን ሕዝብ፦ መስማትን [“ደጋግማችሁ” NW] ትሰማላችሁ አታስተውሉምም፤ ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም በላቸው። በዓይናቸው እንዳያዩ፣ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፣ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፣ ተመልሰውም እንዳይፈወሱ፣ የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፣ ጆሮአቸውንም አደንቁር፣ ዓይናቸውንም ጨፍን አለኝ።” (ኢሳይያስ 6:9, 10) ይህ ማለት ግን ኢሳይያስ አሳቢነትና ጥበብ በጎደለው መንገድ ሊናገራቸውና አይሁዳውያኑን ከአምላክ ሊያቃቅራቸው ነው ማለት ነውን? በፍጹም እንደዚያ ማለት አይደለም! እነዚህ እንደወገኑ የሚያያቸው የገዛ አገሩ ሰዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ኢሳይያስ የቱንም ያህል ተግባሩን በታማኝነት ቢያከናውን ሕዝቡ የሚሰጡትን ምላሽ ይሖዋ ከተናገራቸው ቃላት መረዳት እንችላለን።
16 ችግሩ ከሕዝቡ ነው! ኢሳይያስ ‘ደግሞ ደጋግሞ’ ቢነግራቸውም መልእክቱን አይቀበሉም ወይም አያስተውሉም። አብዛኛዎቹ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ማየትና መስማት የተሳናቸው ያህል እልከኛና ልበ ደንዳኖች ይሆናሉ። ኢሳይያስ ደጋግሞ ‘ወደዚህ ሕዝብ’ በመሄድ ማስተዋል እንዳልፈለጉ ያረጋግጥላቸዋል። ኢሳይያስ የሚናገረውን የአምላክ መልእክት ላለመቀበል አእምሮና ልባቸውን እንደዘጉ ያሳያሉ። ይህ አባባል ዛሬ ላሉት ሰዎች ምንኛ ተስማሚ ነው! ብዙዎቹ ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ መጪው የአምላክ መንግሥት የሚሰብኩትን ምሥራች ለመስማት ፈቃደኛ አይደሉም።
ይሖዋ አምላክ ቅዱስ በሆነው መቅደሱ ተቀምጧል
23 ኢየሱስ ከኢሳይያስ ትንቢት መጥቀሱ ትንቢቱ በእርሱም ዘመን ተፈጻሚነት እንዳለው ማመልከቱ ነው። በጥቅሉ ሲታይ ሕዝቡ የነበረው የልብ ዝንባሌ በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን ካሳዩት የተለየ አልነበረም። መልእክቱን ላለመቀበል ዓይናቸውን ጨፍነውና ጆሮአቸውን ደፍነው ስለነበር ተመሳሳይ ጥፋት ገጥሟቸዋል። (ማቴዎስ 23:35-38፤ 24:1, 2) ይህ የሆነው በጄኔራል ቲቶ የሚመራው የሮማውያን ሠራዊት በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ በዘመተና ከተማዋንና ቤተ መቅደሷን ባጠፋ ጊዜ ነው። ይሁንና አንዳንዶች ኢየሱስን በመስማት የእርሱ ደቀ መዛሙርት ሆነው ነበር። ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች “ደስተኞች” [NW] ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 13:16-23, 51) “ኢየሩሳሌም በጭፍራ ተከባ” ሲያዩ ‘ወደ ተራሮች መሸሽ እንዲጀምሩ’ ነግሯቸው ነበር። (ሉቃስ 21:20-22) እምነት እንዳለው ያሳየውና መንፈሳዊ ብሔር ሆኖ የተቋቋመው ‘የተቀደሰ ዘር’ ማለትም ‘የእግዚአብሔር እስራኤል’ በዚህ መንገድ ሊድን ችሏል።—ገላትያ 6:16
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የኢሳይያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1
7:3, 4—ይሖዋ ክፉ የሆነውን ንጉሥ አካዝን ከወራሪዎቹ ያዳነው ለምንድን ነው? የሶርያና የእስራኤል ነገሥታት ግንባር ፈጥረው ንጉሥ አካዝን ከሥልጣን ካስወገዱ በኋላ በምትኩ፣ የዳዊት ዘር ያልሆነውን የጣብኤልን ልጅ በዙፋን ላይ በማስቀመጥ የአሻንጉሊት መንግሥት ለመመሥረት አስበው ነበር። ይህ ሰይጣናዊ የሆነ እቅድ፣ ይሖዋ ከዳዊት ጋር የገባው የመንግሥት ቃል ኪዳን እንዳይፈጸም እንቅፋት የሚፈጥር ነው። ይሖዋ ለአካዝ ምሕረት ያሳየው፣ ተስፋ የተሰጠበት “የሰላም ልዑል” የሚመጣበትን የዘር ሐረግ ጠብቆ ለማቆየት ነው።—ኢሳይያስ 9:6
ከታኅሣሥ 15-21
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 9–10
በትንቢት የተነገረ “ታላቅ ብርሃን”
የሰላም መስፍን እንደሚነሳ የተሰጠ ተስፋ
16 አዎን በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ የተጠቀሰው ‘የኋለኛ ዘመን’ ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎቱን ያከናወነበት ዘመን ነው። ኢየሱስ አብዛኛውን ምድራዊ ሕይወቱን ያሳለፈው በገሊላ ነበር። “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ በመስበክ አገልግሎቱን የጀመረው በገሊላ አውራጃ ነበር። (ማቴዎስ 4:17) ታዋቂ የሆነውን የተራራ ስብከቱን የሰጠው፣ ሐዋርያቱን የመረጠው፣ የመጀመሪያ ተአምሩን ያከናወነው እንዲሁም ከትንሣኤው በኋላ ከ500 ለሚበልጡ ተከታዮቹ የታየው በገሊላ ነበር። (ማቴዎስ 5:1–7:27፤ 28:16-20፤ ማርቆስ 3:13, 14፤ ዮሐንስ 2:8-11፤ 1 ቆሮንቶስ 15:6) በዚህ መንገድ ኢየሱስ ‘የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር በማክበር’ የኢሳይያስን ትንቢት ፈጽሟል። እርግጥ የኢየሱስ አገልግሎት ለገሊላ ሰዎች ብቻ የተወሰነ ነበር ማለት አይደለም። ኢየሱስ በምድሪቱ በሞላ ተዘዋውሮ ምሥራቹን በመስበክ ይሁዳን ጨምሮ መላው የእስራኤል ብሔር ‘እንዲከበር አድርጓል።’
17 ማቴዎስ በገሊላ እንደሚወጣ ስለተናገረለት ‘ታላቅ ብርሃንስ’ ምን ማለት ይቻላል? ይህም ቢሆን ከኢሳይያስ መጽሐፍ የተወሰደ ሐሳብ ነው። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በጨለማ የሄደ ሕዝብ [“ታላቅ፣” NW ] ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው።” (ኢሳይያስ 9:2) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የእውነት ብርሃን በአረማዊ የሐሰት ትምህርቶች ተቀብሮ ነበር። የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ደግሞ ‘የእግዚአብሔርን ቃል ሽረው’ ሃይማኖታዊ ወጋቸውን የሙጥኝ በማለት ችግሩን አባብሰውት ነበር። (ማቴዎስ 15:6) ከታች ያሉት ሰዎች ‘እውር የሆኑ መሪዎችን’ እየተከተሉ ለጭቆናና ግራ መጋባት ተዳርገው ነበር። (ማቴዎስ 23:2-4, 16) መሲሑ ኢየሱስ በተገለጠ ጊዜ ከሥር የነበሩት የብዙዎቹ ሰዎች ዓይን አስገራሚ በሆነ መንገድ ተከፈተ። (ዮሐንስ 1:9, 12) ኢየሱስ በምድር ላይ ያከናወነው ሥራና በመሥዋዕቱ አማካኝነት የተገኙት በረከቶች በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ እንደ “ታላቅ ብርሃን” ተደርገው መገለጻቸው ትክክል ነው።—ዮሐንስ 8:12
የሰላም መስፍን እንደሚነሳ የተሰጠ ተስፋ
18 ለዚህ ብርሃን ምላሽ የሰጡ ሰዎች የሚደሰቱበት ብዙ ምክንያት ነበራቸው። ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “ሕዝብን አብዝተሃል፣ ደስታንም ጨምረህላቸዋል፤ በመከር ደስ እንደሚላቸው፣ ሰዎችም ምርኮን ሲካፈሉ ደስ እንደሚላቸው በፊትህ ደስ ይላቸዋል።” (ኢሳይያስ 9:3 ) ኢየሱስና ተከታዮቹ ባከናወኑት የስብከት እንቅስቃሴ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ይሖዋን በመንፈስና በእውነት የማምለክ ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል። (ዮሐንስ 4:24) ከአራት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ክርስትናን ተቀበሉ። በ33 እዘአ በዋለው ጰንጠቆስጤ ዕለት ሦስት ሺህ ሰዎች ተጠመቁ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ‘የወንዶቹ ቊጥር አምስት ሺህ ሆኗል።’ (ሥራ 2:41፤ 4:4) ደቀ መዛሙርቱ በቅንዓት ይህን ብርሃን በማንጸባረቃቸው “በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቊጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ።”—ሥራ 6:7
19 በተትረፈረፈ የመከር አዝመራ ደስ እንደሚላቸው ወይም ከታላቅ ወታደራዊ ድል በኋላ ከፍ ያለ ዋጋ ያለውን ብዝበዛ በመከፋፈል እንደሚደሰቱ ሰዎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በተገኘው ጭማሪ ፈንድቀዋል። (ሥራ 2:46, 47) ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ይህ ብርሃን ለአሕዛብ እንዲበራ አድርጓል። (ሥራ 14:27) ወደ ይሖዋ ለመቅረብ የሚያስችለው መንገድ ለእነርሱም ስለተከፈተላቸው ከየብሔራቱ የተውጣጡ ሰዎች እጅግ ደስ ብሏቸዋል።—ሥራ 13:48
የሰላም መስፍን እንደሚነሳ የተሰጠ ተስፋ
20 ኢሳይያስ ቀጥሎ ከተናገራቸው ቃላት መረዳት እንደምንችለው የመሲሁ እንቅስቃሴ ያስገኛቸው ውጤቶች ዘላቂ ናቸው፦ “በምድያም ጊዜ እንደ ሆነ የሸክሙን ቀንበር የጫንቃውንም በትር የአስጨናቂውንም ዘንግ ሰብረሃል።” (ኢሳይያስ 9:4) ከኢሳይያስ ዘመን ብዙ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ ምድያማውያን እስራኤላውያንን በኃጢአት ወጥመድ ውስጥ ለማስገባት ከሞዓባውያን ጋር አሲረውባቸው ነበር። (ዘኍልቁ 25:1-9, 14-18፤ 31:15, 16) በኋላም ምድያማውያን እስራኤላውያንን በመውረር እንዲሁም መንደሮቻቸውንና እርሻዎቻቸውን በመዝረፍ ለሰባት ዓመታት ሲያሸብሯቸው ቆይተዋል። (መሳፍንት 6:1-6) ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ ይሖዋ በአገልጋዩ በጌዴዎን አማካኝነት የምድያማውያንን ሠራዊት አሳደደላቸው። ከዚያ ‘የምድያም ጊዜ’ አንስቶ የይሖዋ ሕዝቦች በምድያማውያን እጅ እንደተቸገሩ የሚገልጽ ምንም መረጃ የለም። (መሳፍንት 6:7-16፤ 8:28) በቅርቡም ታላቁ ጌዴዎን ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬው ጊዜ ባሉት የይሖዋ ጠላቶች ላይ በማያዳግም ሁኔታ ክንዱን ያሳርፍባቸዋል። (ራእይ 17:14፤ 19:11-21) በዚህ ጊዜ በሰዎች ልዩ ችሎታ ሳይሆን በይሖዋ ኃይል ‘እንደ ምድያም ጊዜ’ የተሟላና ዘላቂ ድል ይገኛል። (መሳፍንት 7:2-22) ከዚህ በኋላ የአምላክ ሕዝብ ዳግም በጭቆና ቀንበር አይማቅቅም!
21 የመለኮታዊው ኃይል መግለጫዎች መታየታቸው ጦርነትን እንደማወደስ ሊቆጠር አይገባም። ከሞት የተነሣውና የሰላም መስፍን የሆነው ኢየሱስ ጠላቶቹን በማጥፋት ለዘላለም የሚዘልቅ ሰላም ያሰፍናል። ቀጥሎ ኢሳይያስ ወታደራዊ ቁሶች ሙሉ በሙሉ በእሳት እንደሚበሉ ይገልጻል፦ “የሚረግጡ የሰልፈኞች ጫማ ሁሉ፣ በደምም የተለወሰ ልብስ ለቃጠሎ ይሆናል፣ እንደ እሳት ማቃጠያም ሆኖ ይቃጠላል።” (ኢሳይያስ 9:5) ሰልፈኛ ወታደሮች የሚያሰሙት የእርግጫ ድምፅ ዳግመኛ አይሰማም። በውጊያ የደነደኑት ጦረኞች በደም የተነከረ ልብስ ከእንግዲህ በኋላ አይታይም። ጦርነት ፈጽሞ አይኖርም!—መዝሙር 46:9
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የሰላም መስፍን እንደሚነሳ የተሰጠ ተስፋ
23 መካር ማለት ምክር ወይም ሐሳብ የሚያካፍል ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር በነበረበት ወቅት ድንቅ ምክሮችን ለግሷል። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ሕዝቡ በትምህርቱ እንደተገረሙ’ እናነባለን። (ማቴዎስ 7:28) የሰውን ተፈጥሮ አብጠርጥሮ የሚያውቅ ጥበበኛና የሰው ችግር የሚገባው መካሪ ነው። ምክሩ ተግሳጽና ወቀሳ ብቻ አልነበረም። ብዙውን ጊዜ በትምህርትና በፍቅራዊ መመሪያ መልክ የሚቀርብ ነበር። የኢየሱስ ምክር ሁል ጊዜም ጥበብ የሞላበት፣ ፍጹምና የማይሻር በመሆኑ ድንቅ ነው። ምክሩን ከተከተልነው ወደ ዘላለም ሕይወት ይመራናል።—ዮሐንስ 6:68
24 የኢየሱስ ምክር እንዲሁ ከራሱ ብልህ አእምሮው አፍልቆ የሚናገረው አይደለም። ከዚህ ይልቅ “ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 7:16) እንደ ሰሎሞን ሁሉ የኢየሱስም የጥበብ ምንጭ ይሖዋ አምላክ ነበር። (1 ነገሥት 3:7-14፤ ማቴዎስ 12:42) ይህ የኢየሱስ ምሳሌ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ አስተማሪዎችና መካሪዎች የሚሰጡት ትምህርት ዘወትር በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ሊያነሳሳቸው ይገባል።—ምሳሌ 21:30
ከታኅሣሥ 22-28
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 11–13
ስለ መሲሑ የተነገሩ ትንቢቶች
በመሲሑ ግዛት የሚገኝ መዳንና ደስታ
4 ከኢሳይያስ ዘመን ብዙ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ ሌሎች ዕብራውያን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችም ስለ መሲሑ ማለትም ይሖዋ ወደ እስራኤል ስለሚልከው እውነተኛ መሪ መምጣት ተናግረው ነበር። (ዘፍጥረት 49:10፤ ዘዳግም 18:18፤ መዝሙር 118:22, 26) አሁን ደግሞ ይሖዋ በኢሳይያስ አማካኝነት ተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዮችን ይገልጻል። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፣ ከሥሩም ቁጥቋጥ ያፈራል። ” (ኢሳይያስ 11:1፤ ከመዝሙር 132:11 ጋር አወዳድር።) “በትር” እና “ቁጥቋጥ” የሚሉት ሁለቱም መግለጫዎች መሲሑ የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ በዘይት በተቀባው በእሴይ ልጅ በዳዊት በኩል የሚመጣ የእሴይ ዘር እንደሆነ የሚያመለክቱ ናቸው። (1 ሳሙኤል 16:13፤ ኤርምያስ 23:5፤ ራእይ 22:16) እውነተኛው መሲሕ ማለትም ከዳዊት ቤት የሚወጣው ይህ “ቁጥቋጥ” ሲመጣ መልካም ፍሬዎችን ያፈራል።
5 ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ ኢየሱስ ነው። የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ማቴዎስ ኢየሱስ “ናዝራዊ” ተብሎ መጠራቱ የነቢያት ቃል ፍጻሜ ነው ብሎ ሲጽፍ በተዘዋዋሪ መንገድ ኢሳይያስ 11:1ን መጥቀሱ ነበር። ኢየሱስ ያደገው በናዝሬት ከተማ በመሆኑ ናዝራዊ ተብሎ ተጠርቷል። ይህ ስም በኢሳይያስ 11:1 ላይ ከተጠቀሰው “ቁጥቋጥ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር የሚዛመድ ነው።—ማቴዎስ 2:23፣ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ፤ ሉቃስ 2:39, 40
በመሲሑ ግዛት የሚገኝ መዳንና ደስታ
6 መሲሑ ምን ዓይነት ገዥ ይወጣው ይሆን? አሥሩን ነገድ ሰሜናዊ የእስራኤል መንግሥት እንዳጠፉት አሦራውያን ጨካኝና ያሻውን የሚያደርግ ንጉሥ ይሆናልን? በፍጹም አይሆንም። መሲሑን በተመለከተ ኢሳይያስ እንዲህ ይላል፦ “የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ፣ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። እግዚአብሔርን በመፍራት ደስታውን ያያል። ” (ኢሳይያስ 11:2, 3ሀ) መሲሑ የተቀባው በዘይት ሳይሆን በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ነው። ይህ የሆነው ኢየሱስ ሲጠመቅ ዮሐንስ እያየ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በእርግብ አምሳል በወረደበት ጊዜ ነበር። (ሉቃስ 3:22) ኢየሱስ የይሖዋ መንፈስ ‘አርፎበታል።’ በጥበብ፣ በማስተዋል፣ በምክር፣ በኃይልና በእውቀት ያከናወናቸው ነገሮች ይህንኑ የሚያንጸባርቁ ናቸው። እነዚህ አንድ ገዥ ሊኖረው የሚገቡ እንዴት ያሉ ግሩም ባሕርያት ናቸው!
በመሲሑ ግዛት የሚገኝ መዳንና ደስታ
8 በመሲሑ ላይ የሚንጸባረቀው የይሖዋ ፍርሃት ምንድን ነው? ኢየሱስ የአምላክን ኩነኔ በመፍራት ይሸበራል ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ መሲሑ ለአምላክ ያለው ፍርሃት በፍቅርና በአክብሮት ላይ የተመሠረተ ነው። አምላክን የሚፈራ አንድ ሰው እንደ ኢየሱስ ሁልጊዜ አምላክን “ደስ የሚያሰኘውን” ለማድረግ ይጥራል። (ዮሐንስ 8:29) ኢየሱስ በየዕለቱ ጤናማ በሆነ መንገድ ይሖዋን በመፍራት ከመመላለስ የበለጠ ደስታ እንደሌለ በቃልም ሆነ በድርጊት አስተምሯል።
በመሲሑ ግዛት የሚገኝ መዳንና ደስታ
9 ኢሳይያስ ስለ መሲሑ ባሕርይ ተጨማሪ ነገርም ተንብዮአል፦ “ዓይኑም እንደምታይ አይፈርድም፣ ጆሮውም እንደምትሰማ አይበይንም።” (ኢሳይያስ 11:3ለ) ችሎት ፊት መቅረብ ቢኖርብህና እንዲህ ዓይነት ዳኛ ብታገኝ ደስ አይልህም? መሲሑ የሰው ዘር ሁሉ ፈራጅ ሆኖ ሲሠራ በሐሰት የመከራከሪያ ነጥቦች፣ ችሎትን ለማደናገር በሚሰነዘሩ መሠሪ ሐሳቦች፣ በወሬ ወይም እንደ ሀብት ባሉ ውጫዊ ነገሮች አይታለልም። ማታለያዎችን ለይቶ ያውቃል እንዲሁም እምብዛም ከማይማርኩ ውጫዊ ሁኔታዎች በስተጀርባ ያለውን ይመለከታል። ‘የተሰወረውን የልብ ሰው’ ማለትም ‘ስውር የሆነውን ማንነት’ ያስተውላል። (1 ጴጥሮስ 3:4፣ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ይህ ወደር የማይገኝለት የኢየሱስ ምሳሌ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የመፍረድ ሥልጣን ላላቸው ሁሉ ግሩም አርዓያ ነው።—1 ቆሮንቶስ 6:1-4
በመሲሑ ግዛት የሚገኝ መዳንና ደስታ
11 ኢየሱስ ተከታዮቹ እርማት ባስፈለጋቸው ጊዜ እርማቱን የሚሰጠው ሙሉ ጥቅም ማግኘት በሚያስችላቸው መንገድ ነበር። ይህም ለክርስቲያን ሽማግሌዎች ግሩም ምሳሌ ነው። በአንጻሩ ደግሞ ክፋትን ልማዳቸው ያደረጉ ሰዎች ጠንከር ያለ ፍርድ እንደሚያገኛቸው ሊጠብቁ ይችላሉ። አምላክ ይህን የነገሮች ሥርዓት ወደ ፍርድ በሚያመጣበት ጊዜ መሲሑ በክፉዎች ሁሉ ላይ የጥፋት ፍርድ በማስተላለፍ ከአፉ በሚወጣው የማይሻር ቃሉ “ምድርን ይመታል።” (መዝሙር 2:9፤ ከራእይ 19:15 ጋር አወዳድር።) በመጨረሻ የሰውን ዘር ሰላም የሚያደፈርስ ኃጢአተኛ ፈጽሞ አይኖርም። (መዝሙር 37:10, 11) ጽድቅን በወገቡ የታጠቀውና ታማኝነትን የጎኑ መቀነት ያደረገው ኢየሱስ ይህን ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል አለው።—መዝሙር 45:3-7
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
በመሲሑ ግዛት የሚገኝ መዳንና ደስታ
16 ለመጀመሪያ ጊዜ በንጹሕ አምልኮ ላይ ጥቃት የተሰነዘረው ሰይጣን በተሳካ ሁኔታ አዳምና ሔዋንን ኤድን ገነት ውስጥ በይሖዋ ላይ እንዲያምፁ ባነሳሳበት ጊዜ ነው። እስከዛሬም ድረስ ሰይጣን የተቻለውን ያህል ብዙ ሰዎችን ከአምላክ የማራቅ ግቡን ገፍቶበታል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ከምድር ገጽ እንዲጠፋ በፍጹም አይፈቅድም። ይህ ከስሙ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው። ደግሞም እርሱን ስለሚያገለግሉት ሰዎች ያስባል። ከዚህ የተነሳ በኢሳይያስ በኩል አንድ ትልቅ ተስፋ ሰጥቷል፦ “በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ለአሕዛብ ምልክት ሊሆን የቆመውን የእሴይን ሥር አሕዛብ ይፈልጉታል፤ ማረፊያውም የተከበረ ይሆናል። ” (ኢሳይያስ 11:10) ዳዊት የአገሪቱ መዲና አድርጓት የነበረችው ኢየሩሳሌም በ537 ከዘአበ የተበታተኑት አይሁዳውያን ታማኝ ቀሪዎች ተመልሰው ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የተሰባሰቡባት ምልክት ሆናለች።
17 ይሁን እንጂ ትንቢቱ ከዚህ የበለጠ ትርጉም አለው። ቀደም ሲልም እንደተገለጸው ይህ ትንቢት ከአሕዛብ ሁሉ ለተውጣጡ ሰዎች እውነተኛ አለቃ ስለሚሆነው ስለ መሲሑ አገዛዝ የሚጠቁም ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በእርሱ ዘመን አሕዛብ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ቦታ እንደሚኖራቸው ለማመልከት ከሰፕቱጀንት ትርጉም ኢሳይያስ 11:10ን በመጥቀስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ኢሳይያስ፦ የእሴይ ሥር አሕዛብንም ሊገዛ የሚነሣው ይሆናል፤ በእርሱ አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ ይላል።” (ሮሜ 15:12) ይሁን እንጂ ትንቢቱ በዚህ ብቻ አይወሰንም። በዘመናችንም ከአሕዛብ የተውጣጡ ሰዎች የመሲሑን ቅቡዓን ወንድሞች በመደገፍ ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር እንደሚያሳዩ የሚያረጋግጥ ነው።—ኢሳይያስ 61:5-9፤ ማቴዎስ 25:31-40
18 ትንቢቱ በዚህ ዘመን በሚኖረው ፍጻሜ ውስጥ “በዚያም ቀን” ሲል ኢሳይያስ የተናገረለት ጊዜ የጀመረው መሲሑ የአምላክ ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ ዙፋን ላይ በተቀመጠበት በ1914 ነው። (ሉቃስ 21:10፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ራእይ 12:10) ከዚያ ጊዜ ወዲህ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመንፈሳዊ እስራኤልና የጽድቅ መስተዳድር እንዲሰፍን ለሚናፍቁ አሕዛብ ሁሉ ግልጽ ምልክት ሆኗል። ኢየሱስ አስቀድሞ በትንቢት እንደተናገረው የመንግሥቱ ምሥራች በመሲሑ አመራር ለሁሉም ብሔራት ሲዳረስ ቆይቷል። (ማቴዎስ 24:14፤ ማርቆስ 13:10) ይህ ምሥራች ያስገኘው ውጤት በቀላሉ የሚገመት አይደለም። “አንድ እንኳ ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብ . . . ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” ራሳቸውን ለመሲሑ በማስገዛት ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር በንጹሕ አምልኮ እየተባበሩ ነው። (ራእይ 7:9) ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በይሖዋ መንፈሳዊ “የጸሎት ቤት” ከቅቡዓኑ ጋር ለመተባበር መጉረፋቸው ለመሲሑ ‘ማረፊያ’ ማለትም ለአምላክ ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ክብር የሚጨምር ነው።—ኢሳይያስ 56:7፤ ሐጌ 2:7
ከታኅሣሥ 29–ጥር 4
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 14–16
የአምላክ ሕዝብ ጠላቶች ከቅጣት አያመልጡም
ይሖዋ ኩሩዋን ከተማ ያዋርዳል
16 ይህ ወዲያው በ539 ከዘአበ አልተፈጸመም። ያም ሆኖ ግን ኢሳይያስ ባቢሎንን አስመልክቶ የተናገረው ነገር አንድም ሳይቀር እንደተፈጸመ ዛሬ በግልጽ የሚታይ ሐቅ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ባቢሎንን በሚመለከት እንዲህ ብለዋል፦ “ዛሬም ሆነ ባለፉት ብዙ መቶ ዘመናት ባድማ መሬትና የፍርስራሽ ክምር ነች። ይህንን ትዕይንት ተመልክቶ የኢሳይያስና የኤርምያስ ትንበያዎች እንዴት በትክክል ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ለማስተዋል የሚቸገር ሰው አይኖርም።” በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው በኢሳይያስ ዘመን ባቢሎን እንደምትወድቅና በመጨረሻም ባድማ እንደምትሆን ሊተነብይ የሚችል አንድም ሰው አልነበረም። ደግሞም ባቢሎን በሜዶንና በፋርስ እጅ የወደቀችው ኢሳይያስ መጽሐፉን ከጻፈ ከ200 ዓመት በኋላ ነው! ሙሉ በሙሉ የወደመችው ደግሞ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ነው። ታዲያ ይህ ነገር መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ስለመሆኑ ያለንን እምነት የሚያጠናክር አይደለምን? (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ከዚህም በላይ ይሖዋ ጥንት ትንቢቶች እንዲፈጸሙ እንዳደረገ ሁሉ እስካሁን ፍጻሜያቸውን ያላገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችም አምላክ በፈቀደው ጊዜ እንደሚፈጸሙ ትምክህት ሊኖረን ይችላል።
ይሖዋ ኩሩዋን ከተማ ያዋርዳል
24 በዳዊት የንግሥና መስመር የተነሱት ነገሥታት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት እንደ ከዋክብት ተደርገው ነው። (ዘኍልቁ 24:17) ከዳዊት አንስቶ እነዚያ ‘ከዋክብት’ መቀመጫቸውን በጽዮን ተራራ አድርገው ገዝተዋል። ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን በኢየሩሳሌም ከገነባ በኋላ ደግሞ ጽዮን የሚለው ስም መላዋን ከተማ የሚያመለክት ሆኗል። በሕጉ ቃል ኪዳን መሠረት እስራኤላውያን ወንዶች በሙሉ በዓመት ሦስት ጊዜ ወደ ጽዮን የመጓዝ ግዴታ ነበረባቸው። ከዚህ የተነሣ ‘መሰብሰቢያ ተራራ’ ሆኖ ነበር። ናቡከደነፆር የይሁዳን ነገሥታት በቁጥጥሩ ሥር አስገብቶ ከዚያ ተራራ ለማስወገድ ቆርጦ መነሳቱ ራሱን ከእነዚያ ‘ከዋክብት’ በላይ ለማድረግ መፈለጉን የሚያሳይ ነው። በእነርሱ ላይ ድል በመቀዳጀቱ ለይሖዋ ክብር አይሰጥም። እንዲያውም በእብሪት ራሱን በይሖዋ ቦታ ያስቀመጠ ያህል ሆኖ ነበር።
ይሖዋ በብሔራት ላይ የመከረው ምክር
ይሖዋ ሕዝቡን ስለ ክፋታቸው ለመቅጣት በሌሎች ብሔራት ሊጠቀም ይችላል። ሆኖም እነዚያ ብሔራት የሚያሳዩትን ከልክ ያለፈ ጭካኔና ኩራት እንዲሁም ለእውነተኛ አምልኮ ያላቸውን ጥላቻ ቸል ብሎ ያልፋል ማለት አይደለም። ከዚህም የተነሣ ይሖዋ ከረጅም ጊዜ በፊት ኢሳይያስ ‘ስለ ባቢሎን የተነገረውን ሸክም’ እንዲጽፍ በመንፈሱ አነሳስቶታል። (ኢሳይያስ 13:1) ይሁን እንጂ ወደፊት ባቢሎን ትልቅ ስጋት መፍጠሯ አይቀርም። በኢሳይያስ ዘመን አሦር የአምላክን የቃል ኪዳን ሕዝብ በመጨቆን ላይ ነበር። አሦር ሰሜናዊውን የእስራኤል መንግሥት አጥፍቶና በአብዛኛው የይሁዳ ክልል ላይ ውድመት አድርሶ ነበር። ነገር ግን የአሦራውያኑ ድል ውስን ነበር። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሎአል፦ እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፣ . . . አሦርን በምድሬ ላይ እሰብረዋለሁ፣ በተራራዬም ላይ እረግጠዋለሁ፤ ቀንበሩም ከእነርሱ ላይ ይነሣል፣ ሸክሙም ከጫንቃቸው ላይ ይወገዳል።” (ኢሳይያስ 14:24, 25) ኢሳይያስ ይህን ትንቢት ከተናገረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አሦራውያን በይሁዳ ላይ እንዲያንዣብብ አድርገውት የነበረው የስጋት ደመና ተገፍፏል።
ይሖዋ በብሔራት ላይ የመከረው ምክር
12 ይህ ትንቢት ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ ነው? በቅርቡ ነው። “እግዚአብሔር በሞዓብ ላይ በድሮ ዘመን የተናገረው ነገር ይህ ነው። አሁን ግን እግዚአብሔር፦ በሦስት ዓመት ውስጥ እንደ ምንደኛ ዓመት የሞዓብ ክብርና የሕዝቡ ሁሉ ብዛት ይዋረዳል፣ ቅሬታውም እጅግ ያነሰና የተጠቃ ይሆናል ይላል።” (ኢሳይያስ 16:13, 14) ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ሞዓብ አሳዛኝ መከራ እንደደረሰባትና ብዙዎቹ ቦታዎቿ ሰው አልባ እንደሆኑ የሚያሳይ አርኬኦሎጂያዊ ማስረጃ አለ። ሳልሳዊ ቴልጌልቴልፌልሶር ለእርሱ ይገብሩ ከነበሩት ገዥዎች መካከል የሞዓቡ ሳላማኑ እንደሚገኝበት ጠቅሷል። የሞዓቡ ንጉሥ ካሙሱንዳቢ ለሰናክሬም ገብሯል። የአሦር ንጉሠ ነገሥታት አስራዶንና አሸርባኒፓል የሞዓባውያኑ ነገሥታት ሙሱሪ እና ካማሻልቱ የእነርሱ ተገዥዎች እንደነበሩ ጠቅሰዋል። ሞዓባውያን በሕዝብ ደረጃ የነበራቸውን ሕልውና ጭራሽ ካጡ ብዙ መቶ ዓመታት ተቆጥረዋል። የሞዓባውያን ከተሞች ነበሩ ተብለው የሚታሰቡ አንዳንድ ፍርስራሾች በቁፋሮ ተገኝተዋል። ይሁን እንጂ በአንድ ወቅት ኃያል ስለነበረችው ስለዚህች የእስራኤል ጠላት እስካሁን ድረስ በቁፋሮ የተገኘው ግዑዝ ማስረጃ እጅግ በጣም ጥቂት ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የኢሳይያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1
14:1, 2—የይሖዋ ሕዝቦች ‘የማረኳቸውን የሚማርኩት፤ የጨቈኗቸውንም የሚገዟቸው’ እንዴት ነው? እንዲህ ያለ ሁኔታ የተፈጸመበት ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ዳንኤል በሜዶንና ፋርስ መንግሥት ሥር የባቢሎን ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ሆኖ ተሾሟል፤ እንዲሁም አስቴር የፋርስ ንግሥት ሆናለች። በተጨማሪም መርዶክዮስ በመላው የፋርስ ግዛት ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ሆኖ ነበር።