የጥናት ርዕስ 49
መዝሙር 44 የተቸገረ ሰው ጸሎት
የኢዮብ መጽሐፍ ምክር ስትሰጥ ይረዳሃል
“አሁን ግን ኢዮብ፣ እባክህ ቃሌን ስማ።”—ኢዮብ 33:1
ዓላማ
የኢዮብ መጽሐፍ ጠቃሚ ምክር ለመስጠት የሚረዳን እንዴት ነው?
1-2. ሦስቱ የኢዮብ ጓደኞችና ኤሊሁ ምን ማድረግ ነበረባቸው? ይህን ማድረግ ተፈታታኝ የሚሆነውስ ለምንድን ነው?
ወሬው በምሥራቅ ባሉት ሰዎች ዘንድ በስፋት ተሰራጨ። በብልጽግናው የሚታወቀው ኢዮብ ያለውን ነገር ሁሉ አጥቷል። ሦስቱ የኢዮብ ጓደኞች ኤሊፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር በኢዮብ ላይ የደረሰውን ነገር ሲሰሙ እሱን ለማጽናናት ወደ ዑጽ መጡ። ሆኖም እዚያ ሲደርሱ የተመለከቱት ነገር አስደንግጧቸዋል።
2 ሁኔታውን በምናብህ ለመሣል ሞክር። ኢዮብ ያለውን ነገር ሁሉ አጥቷል። የበግ፣ የከብት፣ የግመልና የአህያ መንጋዎቹ አሁን የሉም። ልጆቹ ሞተዋል፤ አብዛኞቹ አገልጋዮቹም ተገድለዋል። የኢዮብ ልጆች የሞቱበት ቤት የፍርስራሽ ክምር ሆኗል። ይህ አልበቃ ብሎ ኢዮብ በከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ ነው። እጅግ የሚያሠቃይ እባጭ ሰውነቱን ወርሶታል። ሦስቱ ሰዎች ኢዮብ በሐዘን ተውጦና አመድ ላይ ተቀምጦ ከሩቅ ተመለከቱት። ታዲያ ምን ያደርጉ ይሆን? በከባድ ሥቃይ ውስጥ የነበረውን ኢዮብን ለሰባት ቀን ያህል አንድም ቃል አልተናገሩትም። (ኢዮብ 2:12, 13) ኤሊሁ የተባለ ወጣትም መጥቶ በአቅራቢያቸው ተቀመጠ። በመጨረሻም ኢዮብ የተወለደበትን ቀን በመርገምና ሞቱን በመመኘት ንግግሩን ጀመረ። (ኢዮብ 3:1-3, 11) በእርግጥም ኢዮብ ማጽናኛ ያስፈልገዋል! ታዲያ ምን ይሉት ይሆን? እነዚህ ሰዎች የሚናገሩት ነገርና የሚናገሩበት መንገድ ለእሱ የሚያስቡ እውነተኛ ወዳጆቹ መሆን አለመሆናቸውን ያሳያል።
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
3 ይሖዋ ሦስቱ የኢዮብ ጓደኞችና ኤሊሁ የተናገሩትንና ያደረጉትን ነገር ሙሴ እንዲጽፍ አድርጓል። ኤሊፋዝ አንዳንድ ነገሮችን የተናገረው ክፉ መንፈስ ገፋፍቶት ሳይሆን አይቀርም። ኤሊሁ ግን የተናገረው በይሖዋ መንፈስ ተመርቶ ነው። (ኢዮብ 4:12-16፤ 33:24, 25) በመሆኑም የኢዮብ መጽሐፍ ጥሩ ምክር የሚባለው ምን እንደሆነ እንዲሁም መጥፎ ምክር የሚባለው ምን እንደሆነ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ይዟል። የኢዮብን መጽሐፍ ስንመረምር ለሌሎች ምክር መስጠት ስለምንችልበት መንገድ እንማራለን። በመጀመሪያ፣ የኢዮብ ሦስት ጓደኞች የተዉትን መጥፎ ምሳሌ እንመረምራለን። ከዚያም ኤሊሁ የተወውን ጥሩ ምሳሌ እንመለከታለን። እያንዳንዱን ነጥብ ስንመረምር፣ እስራኤላውያን ከኢዮብ መጽሐፍ ምን ትምህርት ማግኘት ይችሉ እንደነበር እንዲሁም እኛ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመለከታለን።
የኢዮብ ሦስት ጓደኞች ምክር የሰጡት እንዴት ነው?
4. የኢዮብ ሦስት ጓደኞች ዓላማቸውን ማሳካት ያልቻሉት ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
4 መጽሐፍ ቅዱስ፣ የኢዮብ ሦስት ጓደኞች ኢዮብ የደረሰበትን ነገር ሲሰሙ “እሱን ለማስተዛዘንና ለማጽናናት” እንደሄዱ ይናገራል። (ኢዮብ 2:11) ሆኖም ይህን ዓላማቸውን ማሳካት አልቻሉም። ለምን? ቢያንስ ሦስት ምክንያቶችን መጥቀስ እንችላለን። አንደኛ፣ በችኮላ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ለምሳሌ ኢዮብ በሠራቸው ኃጢአቶች የተነሳ እየተቀጣ እንደሆነ አስበው ነበር።a (ኢዮብ 4:7፤ 11:14) ሁለተኛ፣ እነዚህ ሰዎች የሰጧቸው አብዛኞቹ ምክሮች ኢዮብን የማይጠቅሙ፣ ደግነት የጎደላቸው ይባስ ብሎም ስሜቱን የሚያቆስሉ ነበሩ። ለምሳሌ ሦስቱም ሰዎች ከላይ ሲታዩ ጥሩ የሚመስሉ ሆኖም ምንም እርባና የሌላቸው ሐሳቦችን ተናግረዋል። (ኢዮብ 13:12) በልዳዶስ ኢዮብን ‘ብዙ ታወራለህ’ በማለት ደግነት በጎደለው መንገድ ተናግሮታል። (ኢዮብ 8:2) ሶፋር ደግሞ ኢዮብን ‘አእምሮ ከሌለው ሰው’ ጋር አመሳስሎታል። (ኢዮብ 11:12) ሦስተኛ፣ ኢዮብን ያነጋገሩት በጩኸት ላይሆን ቢችልም የተናገሩበት መንገድ ንቀት፣ አሽሙርና ውንጀላ የሚንጸባረቅበት ነበር። (ኢዮብ 15:7-11) ኢዮብን ለማጽናናት ወይም እምነቱን ለማጠናከር ከመሞከር ይልቅ ጥፋተኛ መሆኑን በማሳየት ላይ አተኩረዋል።
ምክር ስትሰጥ ግለሰቡን እንደምትንቅ በሚያስመስል መንገድ አትናገር። ዓላማህ ግለሰቡን መርዳት ሊሆን ይገባል (አንቀጽ 4ን ተመልከት)
5. የኢዮብ ጓደኞች የሰጡት ምክር ምን ውጤት አምጥቷል?
5 የኢዮብ ጓደኞች የሰጡት ምክር ጥሩ ውጤት አለማምጣቱ የሚያስገርም አይደለም። ኢዮብ በተናገሩት ነገር ስሜቱ ተደቁሷል። (ኢዮብ 19:2) በተጨማሪም ውንጀላቸው ‘ጻድቅ ነኝ’ ብሎ እንዲሟገት ይበልጥ አነሳስቶታል። ይህም ሚዛኑን እንዲስትና ጥበብ በጎደለው መንገድ እንዲናገር አድርጎታል። (ኢዮብ 6:3, 26) የኢዮብ ጓደኞች ንግግር ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር የሚስማማ አልነበረም፤ ለኢዮብም ቢሆን ርኅራኄ አላሳዩትም። በውጤቱም ሳይታወቃቸው የሰይጣን መሣሪያዎች ሆኑ። (ኢዮብ 2:4, 6) ይህ ዘገባ እስራኤላውያንን ሊጠቅማቸው ይችል የነበረው እንዴት ነው? እኛንስ የሚጠቅመን እንዴት ነው?
6. የእስራኤል ሽማግሌዎች የኢዮብ ሦስት ጓደኞች ከተዉት መጥፎ ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ይችሉ ነበር?
6 ይህ ታሪክ እስራኤላውያንን ሊጠቅማቸው ይችል የነበረው እንዴት ነው? ይሖዋ የእስራኤል ብሔር እንዲቋቋም ካደረገ በኋላ በእሱ የጽድቅ መሥፈርቶች ላይ ተመሥርተው ፍርድ የሚሰጡ ብቃት ያላቸውን ሽማግሌዎች ሾመላቸው። (ዘዳ. 1:15-18፤ 27:1) እነዚህ ወንዶች ምክር ከመስጠታቸውም ሆነ ፍርድ ከማስተላለፋቸው በፊት በጥሞና ማዳመጥ ነበረባቸው። (2 ዜና 19:6) በተጨማሪም ሁሉንም ነገር እንደሚያውቁ ከማሰብ ይልቅ ጥያቄዎችን መጠየቅ ነበረባቸው። (ዘዳ. 19:18) እነዚህ ሽማግሌዎች፣ እርዳታ ፈልገው ወደ እነሱ የሚመጡ ሰዎችን በኃይለ ቃል ከመናገር መቆጠብ ነበረባቸው። ለምን? ምክንያቱም በቁጣ ካነጋገሯቸው ስሜታቸውን ለመግለጽ ሊፈሩ ይችላሉ። (ዘፀ. 22:22-24) የእስራኤል ሽማግሌዎች ከኢዮብ ታሪክ እነዚህን ትምህርቶች ማግኘት ይችሉ ነበር።
7. እስራኤል ውስጥ ከሽማግሌዎች በተጨማሪ እነማን ምክር መስጠት ይችሉ ነበር? የኢዮብ ታሪክ ሊጠቅማቸው የሚችለውስ እንዴት ነው? (ምሳሌ 27:9)
7 እርግጥ ነው፣ እስራኤል ውስጥ ምክር መስጠት የሚችሉት ሽማግሌዎች ብቻ አልነበሩም። ወጣት፣ አረጋዊ፣ ወንድ፣ ሴት ሳይል ማንኛውም እስራኤላዊ በአምልኮ ወይም በባሕርይ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ ለሚያስፈልገው ሰው ምክር መስጠት ይችል ነበር። (መዝ. 141:5) እንዲህ ያለው ልባዊ ምክር የእውነተኛ ጓደኝነት መገለጫ ነው። (ምሳሌ 27:9ን አንብብ።) የኢዮብ ሦስት ጓደኞች የተዉት መጥፎ ምሳሌ እስራኤላውያን ምክር በሚሰጡበት ጊዜ ምን ማለት እንደሌለባቸውና ምን ማድረግ እንደሌለባቸው የሚያሳይ ሕያው ምሳሌ ነው።
8. ምክር ስንሰጥ ምን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
8 እኛስ ምን ጥቅም እናገኛለን? ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መከራ ሲደርስባቸው እነሱን መርዳት እንፈልጋለን። ሆኖም እንዲህ ስናደርግ የኢዮብ ሦስት ጓደኞች የሠሩትን ስህተት ከመሥራት መቆጠብ ይኖርብናል። በመጀመሪያ፣ ቸኩለን መደምደሚያ ላይ ከመድረስ መቆጠብ ይኖርብናል፤ እንዲሁም ከመናገራችን በፊት የተሟላ መረጃ ሊኖረን ይገባል። ሁለተኛ፣ ኤሊፋዝ በተደጋጋሚ እንዳደረገው ምክራችን በዋነኝነት የተመሠረተው በራሳችን የሕይወት ተሞክሮ ላይ ሊሆን አይገባም፤ ከዚህ ይልቅ ምክራችን አስተማማኝ በሆነው የአምላክ ቃል ላይ መመሥረት ይኖርበታል። (ኢዮብ 4:8፤ 5:3, 27) ሦስተኛ፣ ደግነት የጎደለውና ትችት የሚንጸባረቅበት ንግግር ከመናገር መቆጠብ አለብን። ኤሊፋዝና ጓደኞቹ የተናገሯቸው አንዳንድ ነገሮች እውነትነት እንደነበራቸው ልብ በል፤ እንዲያውም ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ፣ ኤሊፋዝ የተናገረውን አንድ ሐሳብ ጠቅሷል። (ኢዮብ 5:13ን ከ1 ቆሮንቶስ 3:19 ጋር አወዳድር።) ሆኖም ከተናገሯቸው ነገሮች አብዛኞቹ የአምላክን ስም የሚያጠፉና ኢዮብን የሚጎዱ ነበሩ። በመሆኑም ይሖዋ የተናገሩት ነገር ውሸት እንደሆነ ገልጿል። (ኢዮብ 42:7, 8) ምክር ስንሰጥ ይሖዋ ምክንያታዊ እንዳልሆነ የሚያስመስል ወይም አገልጋዮቹን እንደማይወዳቸው እንዲሰማቸው የሚያደርግ ምንም ነገር መናገር የለብንም። አሁን ደግሞ ኤሊሁ ከተወልን ምሳሌ የምናገኘውን ትምህርት እንመልከት።
ምክር ስትሰጥ (1) የተሟላ መረጃ ለማግኘት ጥረት አድርግ፤ (2) የአምላክን ቃል ተጠቀም፤ እንዲሁም (3) ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ተናገር (አንቀጽ 8ን ተመልከት)
ኤሊሁ ለኢዮብ ምክር የሰጠው እንዴት ነው?
9. ኢዮብ ጓደኞቹ መናገር ካቆሙ በኋላ እርዳታ ያስፈለገው ለምንድን ነው? ይሖዋስ የሚያስፈልገውን እርዳታ የሰጠው እንዴት ነው?
9 ኢዮብና ጓደኞቹ ክርክራቸውን ባቆሙበት ወቅት ሁኔታው ውጥረት የነገሠበት እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም። እነዚህ ሰዎች 28 የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎችን ለመሙላት የሚበቃ ንግግር ተናግረዋል፤ አብዛኛውን ነገር የተናገሩት ደግሞ በቁጣና በብስጭት ተሞልተው ነው። በእርግጥም ኢዮብ ተስፋ የቆረጠ መሆኑ አያስገርምም። አሁንም ቢሆን ማጽናኛና እርማት ያስፈልገዋል። ታዲያ ይሖዋ ኢዮብን የረዳው እንዴት ነው? ኤሊሁን ተጠቅሞ ምክር ሰጥቶታል። ኤሊሁ እስካሁን ያልተናገረው ለምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “እኔ በዕድሜ ትንሽ ነኝ፤ እናንተ ግን ትላልቆች ናችሁ። ለእናንተ ካለኝ አክብሮት የተነሳ ከመናገር ዝም አልኩ።” (ኢዮብ 32:6, 7) ወጣቱ ኤሊሁ አንድ ሐቅ ተረድቶ ነበር፤ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ከወጣቶች ይበልጥ ብዙ ዕድሜ ስለኖሩና ተሞክሮ ስላካበቱ በአብዛኛው ጥበበኛ እንደሚሆኑ አስተውሏል። ሆኖም ኢዮብንም ሆነ ጓደኞቹን በትዕግሥት ሲያዳምጥ ከቆየ በኋላ ከዚህ በላይ ዝም ማለት አልቻለም። እንዲህ ብሏል፦ “ዕድሜ በራሱ ሰውን ጥበበኛ አያደርገውም፤ ትክክለኛውን ነገር የሚያስተውሉትም በዕድሜ የገፉ ሰዎች ብቻ አይደሉም።” (ኢዮብ 32:9) ኤሊሁ ቀጥሎ ምን ይናገር ይሆን? የተናገረበት መንገድስ ምን ይመስላል?
10. ኤሊሁ ለኢዮብ ምክር ከመስጠቱ በፊት ምን አድርጓል? (ኢዮብ 33:6, 7)
10 ኤሊሁ ለኢዮብ ምክር ከመስጠቱ በፊት ተስማሚ ድባብ ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። እንዴት? በመጀመሪያ ስሜቱን ተቆጣጥሯል። ይህን እንዴት እናውቃለን? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኤሊሁ መጀመሪያ ላይ እጅግ ተቆጥቶ እንደነበር ስለሚናገር ነው። (ኢዮብ 32:2-5) ሆኖም በንዴት ተነሳስቶ ኢዮብን ኃይለ ቃል አልተናገረውም። ከዚህ ይልቅ ያነጋገረው በሚያጽናና መንገድ ነው። ለምሳሌ ኢዮብን “እነሆ፣ በእውነተኛው አምላክ ፊት እኔም እንደ አንተው ነኝ” ብሎታል። (ኢዮብ 33:6, 7ን አንብብ።) ከዚያም ኤሊሁ ኢዮብን በጥሞና እንዳዳመጠው አሳይቷል። እንዲያውም ኢዮብ በስድስቱ ንግግሮቹ ላይ የተናገራቸውን አንኳር ነጥቦች ጠቅለል አድርጎ ገልጿል። (ኢዮብ 32:11፤ 33:8-11) ኤሊሁ ንግግሩን በቀጠለ ጊዜም ኢዮብ የተናገራቸውን ሐሳቦች በድጋሚ ጠቅሷል፤ ይህም ኢዮብን እንዳዳመጠው ያሳያል።—ኢዮብ 34:5, 6, 9፤ 35:1-4
11. ኤሊሁ ለኢዮብ ምክር የሰጠው እንዴት ነው? (ኢዮብ 33:1)
11 ኤሊሁ ለኢዮብ ምክር የሰጠው ለዚህ ታማኝ ሰው አክብሮት እንዳለው በሚያሳይ መንገድ ነው። ለምሳሌ ኤሊሁ ኢዮብን በስሙ ይጠራው ነበር፤ ሦስቱ ጓደኞቹ ግን እንዲህ ያደረጉ አይመስልም። (ኢዮብ 33:1ን አንብብ።) በተጨማሪም ኤሊሁ፣ ኢዮብ በምክሩ መሃል ምላሽ እንዲሰጥ አጋጣሚውን ሰጥቶታል። ምናልባትም ይህን ያደረገው የራሱን ስሜት አስታውሶ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ኢዮብና ጓደኞቹ ሲከራከሩ ምላሽ መስጠት ፈልጎ ነበር። (ኢዮብ 32:4፤ 33:32) ኤሊሁ የኢዮብ አስተሳሰብ አደገኛ እንደሆነ በመግለጽ አስጠንቅቆታል። እንዲሁም የይሖዋን ጥበብ፣ ኃይል፣ ፍትሕና ታማኝ ፍቅር እንዲያስታውስ በደግነት ረድቶታል። (ኢዮብ 36:18, 21-26፤ 37:23, 24) ኤሊሁ ለኢዮብ የሰጠው ጥሩ ምክር ይሖዋ ቀጥሎ የሚሰጠውን ምክር ለመቀበል አእምሮውን አዘጋጅቶለት መሆን አለበት። (ኢዮብ 38:1-3) ኤሊሁ የተወው ምሳሌ እስራኤላውያንን ሊጠቅማቸው ይችል የነበረው እንዴት ነው? እኛንስ የሚጠቅመን እንዴት ነው?
12. ይሖዋ ሕዝቡን ለመርዳት ሲል ነቢያትን የተጠቀመው እንዴት ነው? እስራኤላውያን ከኤሊሁ ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ይችሉ ነበር?
12 ይህ ታሪክ እስራኤላውያንን ሊጠቅማቸው ይችል የነበረው እንዴት ነው? በእስራኤል የታሪክ ዘመን በሙሉ ይሖዋ ዓላማውን ለሕዝቡ ለማሳወቅ ሲል ነቢያትን ሾሞላቸው ነበር። ለምሳሌ በመሳፍንት ዘመን ዲቦራ ለብሔሩ እንደ እናት በመሆን መንፈሳዊ መመሪያ ትሰጣቸው ነበር፤ እንዲሁም ሳሙኤል ከልጅነቱ ጀምሮ የይሖዋ ቃል አቀባይ በመሆን በትጋት አገልግሏል። (መሳ. 4:4-7፤ 5:7፤ 1 ሳሙ. 3:19, 20) ከዚያም በነገሥታት ዘመን ይሖዋ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ለማጠናከርና ከንጹሕ አምልኮ ለራቁት ሰዎች ምክር ለመስጠት ሲል ነቢያትን ያለማቋረጥ ይልክላቸው ነበር። (2 ሳሙ. 12:1-4፤ ሥራ 3:24) በኢዮብ መጽሐፍ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው የኤሊሁ ምሳሌ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ምክር በሚሰጡበት ጊዜ ምን መናገርና እንዴት መናገር እንዳለባቸው ጥሩ ትምህርት ይሰጣቸዋል።
13. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች የእምነት አጋሮቻቸውን ማበረታታት የሚችሉት እንዴት ነው?
13 እኛስ ምን ጥቅም እናገኛለን? ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ሐሳብ በማወጅ ሌሎች የአምላክን ፈቃድ እንዲያውቁ እንረዳለን። ከዚህም በተጨማሪ፣ በምንናገረው ነገር የእምነት አጋሮቻችንን ማነጽና ማበረታታት ይጠበቅብናል። (1 ቆሮ. 14:3) በተለይ ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ‘ማጽናናት’ ይጠበቅባቸዋል፤ ይህም በቀላሉ የሚበሳጩትን ወይም በጭንቀት በመዋጣቸው የተነሳ ‘እንዳመጣላቸው የሚናገሩትን’ ይጨምራል።—1 ተሰ. 5:14፤ ኢዮብ 6:3
14-15. የጉባኤ ሽማግሌዎች ምክር ሲሰጡ የኤሊሁን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።
14 አንድ የጉባኤ ሽማግሌ በጉባኤው ውስጥ ያለች አንዲት እህት ከተስፋ መቁረጥ ስሜት ጋር እየታገለች እንደሆነ ሰማ እንበል። ከዚያም እሷን ለማበረታታት ሲል ከአንድ ወንድም ጋር ሊጠይቃት ሄደ። እህትን ሲያነጋግሯት፣ በጉባኤ ስብሰባና በአገልግሎት ብትካፈልም ደስታዋን እንዳጣች ገለጸችላቸው። ታዲያ የጉባኤ ሽማግሌው ለዚህ ሁኔታ ምን ምላሽ ይሰጥ ይሆን?
15 በመጀመሪያ፣ እህት እንዲህ ሊሰማት የቻለው ለምን እንደሆነ ለማጣራት ይሞክር ይሆናል። ይህን ለማወቅ በጥሞና ማዳመጥ ይጠበቅበታል። ይሖዋ ሊወዳት እንደማይችል ተሰምቷት ይሆን? ወይም ‘የኑሮ ጭንቀት’ መንፈሷን ደቁሶት ይሆን? (ሉቃስ 21:34) ሁለተኛ፣ የጉባኤ ሽማግሌው እህትን ለማመስገን አጋጣሚዎችን ይፈልጋል። ከዚህ ስሜት ጋር እየታገለችም በጉባኤ ስብሰባና በአገልግሎት በመካፈሏ ሊያመሰግናት ይችላል። ሦስተኛ ደግሞ የጉባኤ ሽማግሌው፣ እህት ያለችበትን ሁኔታና እንዲህ እንዲሰማት ያደረገውን ምክንያት ይበልጥ ከተረዳ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም ይሖዋ እንደሚወዳት ያረጋግጥላታል።—ገላ. 2:20
ከኢዮብ መጽሐፍ ጥቅም ማግኘትህን ቀጥል
16. ከኢዮብ መጽሐፍ ጥቅም ማግኘታችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?
16 በእርግጥም የኢዮብን መጽሐፍ በመመርመር ግሩም ትምህርቶችን ማግኘት እንችላለን! ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው፣ የኢዮብ መጽሐፍ አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ብቻ ሳይሆን መከራ ሲደርስብን መጽናት የምንችለው እንዴት እንደሆነም ጭምር ያስተምረናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ ደግሞ ሁላችንም የኢዮብ ሦስት ጓደኞች የተዉትን መጥፎ ምሳሌ ከመከተል ይልቅ ኤሊሁ የተወውን ግሩም ምሳሌ በመከተል ጥሩ ምክር መስጠት እንደምንችል ተምረናል። ወደፊት ለሌሎች ምክር ከመስጠትህ በፊት ከኢዮብ መጽሐፍ ያገኘሃቸውን ትምህርቶች ለምን አትከልስም? የኢዮብን መጽሐፍ በቅርቡ ካላነበብከው ደግሞ ይህን ግሩም መጽሐፍ በድጋሚ ለማንበብ ግብ አውጣ። በተጻፈበት ዘመን የነበረውን ያህል ዛሬም በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ትገነዘባለህ።
መዝሙር 125 “መሐሪዎች ደስተኞች ናቸው”
a ኤሊፋዝ ማንም ሰው በይሖዋ ፊት እንደ ጻድቅ ሊቆጠርና እሱን ሊያስደስተው እንደማይችል እንዲደመድም ያደረገው አንድ ክፉ መንፈስ ሳይሆን አይቀርም። ኤሊፋዝ ይህን የተሳሳተ ሐሳብ አምኖበት ነበር። በሦስቱም ንግግሮቹ ላይ ይህን ሐሳብ ደግሞታል።—ኢዮብ 4:17፤ 15:15, 16፤ 22:2