የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ijwhf ርዕስ 28
  • ጥሩ አባት መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥሩ አባት መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?
  • ለቤተሰብ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአባት ሚና ምንድን ነው?
  • የአባት ድርሻ የተለየ የሆነው እንዴት ነው?
  • አባቶችና ሴት ልጆቻቸው
  • ልጅ መውለድ በትዳር ላይ የሚያመጣው ለውጥ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • እንደምትወጂያቸው ንገሪያቸው
    የይሖዋ ምሥክሮች ተሞክሮዎች
  • ከኃላፊነት የሚሸሹ አባቶች—በእርግጥ ከኃላፊነት ያመልጡ ይሆን?
    ንቁ!—2000
  • ጥሩ አባት መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2013
ለተጨማሪ መረጃ
ለቤተሰብ
ijwhf ርዕስ 28
አንድ አባትና በአሥራዎቹ ዕድሜ ያለች ልጁ በደስታ አብረው ሲጓዙ።

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ጥሩ አባት መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

በዚህ ርዕስ ውስጥ

  • የአባት ሚና ምንድን ነው?

  • የአባት ድርሻ የተለየ የሆነው እንዴት ነው?

  • አባቶችና ሴት ልጆቻቸው

  • ለአባቶች የተሰጠ ምክር

የአባት ሚና ምንድን ነው?

  • ልጁ ከመወለዱ በፊት። አሁን የባልነት ድርሻህን የምትወጣበት መንገድ ወደፊት የአባትነት ድርሻህን ስለምትወጣበት መንገድ ፍንጭ ይሰጣል። ዱ ፋዘርስ ማተር? የሚለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦

    “ነፍሰ ጡር የሆነች አጋሩ ቁሳቁሶችን ስትገዛ የሚረዳት፣ የሕክምና ክትትል ስታደርግ ሆስፒታል የሚወስዳት እንዲሁም ፅንሱን በአልትራሳውንድ የሚያይ ወይም የልብ ምቱን የሚያዳምጥ አባት፣ ልጁ ከተወለደ በኋላ ከአጋሩም ሆነ ከሕፃኑ ጋር መቀራረቡ አይቀርም።”

    “ባለቤቴ ነፍሰ ጡር በነበረችበት ወቅት ብቻዋን እንደሆነች እንዲሰማት ስላልፈለግኩ በቻልኩት መንገድ ሁሉ እረዳት ነበር። የሕፃኑን ክፍልም ያዘጋጀነው አብረን ነው። ሕፃኑን ለመቀበል በመዘጋጀት ያሳለፍነው ጊዜ ለሁለታችንም ልዩ ነበር።”—ጄምስ

    የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵስዩስ 2:4

  • ልጁ ከተወለደ በኋላ። ከሕፃን ልጅህ ጋር በመጫወትና ልጁን በማቀፍ ልዩ ቅርርብ መፍጠር ትችላለህ። ሕፃኑን በመንከባከቡ ሥራም ተካፈል። የአባትነት ድርሻህን የምትወጣበት መንገድ በልጁ እድገት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል። ከልጅህ ጋር ትስስር መፍጠርህ ልጁን ውድ አድርገህ እንደምትመለከተው ያሳያል።

    “እንደ ልጅህ ወደ መሬት ውረድ። ተጫወት። ቀልደኛ ሁን። በራስህ ለመሳቅ ፈቃደኛ ሁን። ልጃችሁ መጀመሪያ ስለ ፍቅር የሚማረው ከወላጆቹ እንደሆነ አስታውስ።”—ሪቻርድ

    አንድ አዲስ አባት ሕፃን ልጁን አቅፎ።

    የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ልጆች ከይሖዋ የተገኙ ውርሻ ናቸው፤ የማህፀንም ፍሬ ከእሱ የሚገኝ ስጦታ ነው።”—መዝሙር 127:3

  • ልጁ እያደገ ሲሄድ። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከአባቶቻቸው ጋር የሚቀራረቡ ልጆች የትምህርት ውጤታቸው ከፍተኛ ነው፤ እንዲሁም ለሥነ ልቦና ቀውስና ለዕፅ ሱሰኝነት የመጋለጣቸው ወይም በወንጀል ድርጊት የመካፈላቸው አጋጣሚ ጠባብ ነው። ጊዜ መድበህ ከልጅህ ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት ጥረት አድርግ።

    “ልጄ ራሱን ችሎ ከቤት ሲወጣ በጣም የሚናፍቀው ነገር በመኪና ስንጓዝ ወይም ራት ስንበላ እናደርግ የነበረው ጭውውት እንደሆነ ነግሮኛል። ወሳኝ ስለሆኑ አንዳንድ ጉዳዮች የተነጋገርነው ባልጠበቅኩት ጊዜ ነው። ስለ እነዚህ ጉዳዮች ማውራት የቻልነው አብረን ብዙ ጊዜ እናሳልፍ ስለነበር ነው።”—ዴኒስ

    አንድ አባትና በአሥራዎቹ ዕድሜ ያለ ልጁ ጀልባ ውስጥ ሆነው በደስታ ሲያወሩ።

    የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ . . . ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።”—ኤፌሶን 5:15, 16

የአባት ድርሻ የተለየ የሆነው እንዴት ነው?

በብዙ ባሕሎች ውስጥ አባቶች ቤተሰባቸውን የማስተዳደርና ከጉዳት የመጠበቅ፣ እናቶች ደግሞ የቤተሰቡን ስሜታዊ ፍላጎት የማሟላት ኃላፊነት እንዳለባቸው ተደርጎ ይቆጠራል። (ዘዳግም 1:31፤ ኢሳይያስ 49:15) እርግጥ በአንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ የአባትና የእናት ድርሻ በተወሰነ መጠን ሊቀያየር ይችላል። ያም ቢሆን አባትም ሆነ እናት በቤተሰቡ ውስጥ የራሳቸው የሆነ ልዩ ሚና እንዳላቸው ተመራማሪዎች ይገልጻሉ።a

የቤተሰብ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት ጁዲት ዋለርስታይን ይህን የሚያሳይ ገጠመኝ እንዳላቸው ተናግረዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “የአሥራ ሁለት ዓመት ልጄ የመኪና አደጋ ባጋጠማት ወቅት አምቡላንስ ውስጥ አባቷ አብሯት እንዲሄድ ፈልጋ ነበር፤ ምክንያቱም ይረዳኛል ብላ የተማመነችው በእሱ ነው። ሆስፒታል ከደረሰች በኋላ ደግሞ ቀኑን ሙሉ ከአልጋዋ አጠገብ ቁጭ ብዬ እንዳጽናናት የፈለገችው እኔን ነው።”b

“አባቶች ቤተሰባቸው የተረጋጋና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ይችላሉ፤ እናቶች ብቻቸውን ይህን ማድረግ ሊያስቸግራቸው ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ እናቶች የልጆቻቸውን ስሜት ስለሚረዱና ስለሚያዳምጧቸው በቤቱ ውስጥ ፍቅር እንዲሰፍን ያደርጋሉ። ሁለቱም እንደ አንድ ቡድን ተባብረው ይሠራሉ።”—ዳንኤል

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ተግሣጽ አዳምጥ፤ የእናትህንም መመሪያ አትተው።”—ምሳሌ 1:8

አባቶችና ሴት ልጆቻቸው

አባት እንደመሆንህ መጠን ልጅህ ሌሎች ወንዶች እንዴት እንዲይዟት መጠበቅ እንዳለባት የምታስተምራት አንተ ነህ። ልጅህ ይህን የምትማረው በሚከተሉት ሁለት መንገዶች ነው፦

  • እናቷን የምትይዝበትን መንገድ በማየት። ሚስትህን በፍቅርና በአክብሮት የምትይዝ ከሆነ ልጅህ ወደፊት ባል በምትመርጥበት ጊዜ ለየትኞቹ ባሕርያት ትኩረት መስጠት እንዳለባት ትማራለች።—1 ጴጥሮስ 3:7

    በአሥራዎቹ ዕድሜ ያለች ልጅ ከወላጆቿ ጋር ራት እየበላች በፈገግታ ስታያቸው። አባቷ የእናቷን እጅ ይዞ አብረው እየሳቁ ነው።
  • እሷን የምትይዝበትን መንገድ በማየት። ልጅህን በአክብሮት የምትይዛት ከሆነ እሷም ራሷን ማክበር እንዳለባት ትማራለች። በተጨማሪም ሌሎች ወንዶች በአክብሮት እንዲይዟት መጠበቅ እንዳለባት ትማራለች።

    በሌላ በኩል ግን አንድ አባት ልጁን ነጋ ጠባ የሚተቻት ከሆነ ለራሷ ያላት ግምት ሊቀንስና የሌሎች ወንዶችን አድናቆት ለማትረፍ መጣጣር ልትጀምር ትችላለች፤ እነዚህ ወንዶች ደግሞ ስውር ዓላማ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ።

    “የአባቷን ፍቅርና ድጋፍ አግኝታ ያደገች ልጅ ከጥሩ ባል የሚጠበቁትን ብቃቶች በማያሟላ ሰው የመማረኳ አጋጣሚ ጠባብ ነው።”—ዌይን

a በርካታ እናቶች ያለባል እርዳታ ልጆቻቸውን ጥሩ አድርገው ማሳደግ ችለዋል።

b ዚ አንኤክስፔክትድ ሌጋሲ ኦቭ ዲቮርስ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።

ለአባቶች የተሰጠ ምክር

ግሪጎሪ፣ ልጁ ኦሊቪያ እና ባለቤቱ ኦድሪ።

“ልጅህ ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ ስትገባ ይበልጥ አብረሃት ጊዜ አሳልፍ፤ እንዲሁም ልክ እንደ በፊቱ እንደምትወዳት ንገራት። እንዲህ ማድረግህ የመተማመን ስሜት እንዲኖራት እንዲሁም ስለ ማንኛውም ጉዳይ ልታዋራህ እንደምትችል እንዲሰማት ያደርጋል። ለእሷ የሚሆን ጊዜ ከሌለህ ይህን ማስተዋሏ አይቀርም፤ በመሆኑም ትኩረት የሚሰጣት ሰው ፍለጋ ልትሄድ ትችላለች።”—ግሪጎሪ ከልጁ ከኦሊቪያ እና ከባለቤቱ ከኦድሪ ጋር

ክለሳ፦ ጥሩ አባት መሆን የምችለው እንዴት ነው?

  • ልጁ ከመወለዱ በፊት የአባትነት ድርሻህን ተወጣ። ሚስትህ ነፍሰ ጡር ሳለች የባልነት ኃላፊነትህን የምትወጣበት መንገድ ልጁ ከተወለደ በኋላ የአባትነት ድርሻህን ስለምትወጣበት መንገድ ፍንጭ ይሰጣል።

  • ልጁ እያደገ ሲሄድ ከእሱ ጋር ጥሩ ቅርርብ ለመመሥረት ጥረት አድርግ። ከአባቶቻቸው ጋር የሚቀራረቡ ልጆች የትምህርት ውጤታቸው ከፍተኛ ነው፤ በተጨማሪም ለሥነ ልቦና ቀውስ እንዲሁም ለዕፅና ለአልኮል ሱሰኝነት የመጋለጣቸው አጋጣሚ ጠባብ ነው።

  • ጥሩ ባል ሁን። ሚስትህን በፍቅርና በአክብሮት የምትይዝ ከሆነ ልጅህ ሌሎች ወንዶች እንዴት እንዲይዟት መጠበቅ እንዳለባት ትማራለች።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ