የወጣቶች ጥያቄ
ሐዘንን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
በቅርቡ የቤተሰብህን አባል ወይም ጓደኛህን በሞት አጥተሃል? ከሆነ ይህ ርዕስ ሐዘንህን ለመቋቋም ሊረዳህ ይችላል።
በዚህ ርዕስ ውስጥ
ሐዘኔ ከልክ ያለፈ ነው?
ብዙዎች የሚወዱትን ሰው ሲያጡ የሚሰማቸው ሐዘን በጣም ከባድ ነው፤ ደግሞም ለረጅም ጊዜ ይዘልቃል።
“ስለ አያቴ ሳላስብ አንድም ቀን አያልፍም። ከሞተ ሁለት ዓመት ቢያልፈውም አሁንም ስለ እሱ ባወራሁ ቁጥር እንባዬን መቆጣጠር ያቅተኛል።”—ኦሊቪያ
“አያቴ ግቦቼ ላይ እንድደርስ በጣም ትደግፈኝ ነበር፤ ሆኖም አንዱም ግቤ ላይ ስደርስ አላየችም። በሕይወቴ ውስጥ አንድ ግብ ላይ በደረስኩ ቁጥር አያቴ ይህን ለማየት ባለመብቃቷ በሐዘን እዋጣለሁ።”—አሊሰን
ሐዘን የተለያዩ ስሜቶችን ሊፈጥርብህ ይችላል። ለምሳሌ፦
“አጎቴ ሲሞት በጣም ደነገጥኩ፤ ድንጋጤው ለረጅም ጊዜ አልለቀቀኝም። የቅርብ ሰው ሲሞትብኝ ያ የመጀመሪያ ጊዜ ነበር፤ ባቡር ላዬ ላይ እንደሄደብኝ ተሰማኝ።”—ናዲን
“አያቴ ሲሞት ተበሳጭቼበት ነበር። ምክንያቱም ጤንነቱን እንዲንከባከብ ብንወተውተውም እንደዚያ አያደርግም ነበር።”—ካርሎስ
“አያቴ በሞተበት ወቅት ከቤተሰባችን መካከል በቦታው ያልነበርነው እኔና እህቴ ብቻ ነን። አያቴን በሥርዓት እንዳልተሰናበትኩት ስለተሰማኝ በጥፋተኝነት ስሜት ተዋጥኩ።”—አድሪያና
“ከቤተሰባችን ጋር የሚቀራረቡ አንድ ባልና ሚስት በመኪና አደጋ ሞቱ። ከዚያ በኋላ ቤተሰቦቼ ከቤት በወጡ ቁጥር እነሱም ሊሞቱ እንደሚችሉ በማሰብ ፍርሃት ይሰማኝ ነበር።”—ጃሬድ
“አያቴ ከሦስት ዓመት በፊት ስትሞት፣ በሕይወት በነበረችበት ወቅት አብሬያት ብዙ ጊዜ ባለማሳለፌ ቆጨኝ።”—ጁሊያና
ድንጋጤ፣ ብስጭት፣ የጥፋተኝነት ስሜት፣ ፍርሃትና ቁጭት የተለመዱ የሐዘን ገጽታዎች ናቸው። እነዚህ ስሜቶች ከተፈጠሩብህ አይዞህ። በጊዜ ሂደት እየቀለሉ መሄዳቸው አይቀርም። እስከዚያው ድረስ ግን ሐዘንህን መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?
ሐዘንን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
ለጓደኛህ ስሜትህን አውጥተህ ተናገር። መጽሐፍ ቅዱስ፣ እውነተኛ ወዳጅ “ለመከራ ቀን” እንደሚወለድ ይናገራል። (ምሳሌ 17:17) ስሜትህን አውጥተህ ለሌላ ሰው መናገርህ የሚያስፈልግህን ድጋፍ እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል።
“ማዘን ተፈጥሯዊ ነገር ነው። በምናዝንበት ጊዜ ብቻችንን መሆን ልንፈልግ እንችላለን፤ ሆኖም ይህ ሁሉ ነገር እንዲጨላልምብን ሊያደርግ ይችላል። ስሜታችንን ለሌላ ሰው መናገር ጠቃሚ የሆነው ለዚህ ነው።”—ኢቬት
ስለሞተብህ ሰው አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጥሩ ሰው በልቡ መልካም ነገር እንደሚያከማች’ ይናገራል። (ሉቃስ 6:45) ከግለሰቡ ጋር ስላሳለፋችሁት ጥሩ ትዝታ ልትጽፍ ወይም የፎቶ አልበም ልታዘጋጅ ትችላለህ።
“ጓደኛዬ ከመሞቱ በፊት ያስተማረኝን ነገሮች በሙሉ ለመጻፍ ወሰንኩ፤ በዚህ መንገድ ከእሱ ምሳሌ መጠቀሜን መቀጠል ችያለሁ። ይህን መጻፌ ሐዘኔን ለመቋቋም ረድቶኛል።”—ጄፍሪ
ጤንነትህን ተንከባከብ። መጽሐፍ ቅዱስ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ጥቅም እንዳለው ይገልጻል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) የተመጣጠነ ምግብ ተመገብ፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርግ፤ እንዲሁም በቂ እረፍት አድርግ።
“ሐዘን የማመዛዘን ችሎታችንን ሊያዛባብን ይችላል፤ ስለዚህ ጤንነታችንን ለመንከባከብ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። በደንብ መመገብና በቂ እንቅልፍ ማግኘት እንዳለብን መዘንጋት አይኖርብንም።”—ማሪያ
ሌሎችን እርዳ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ይላል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35
“ሌሎች ሰዎችን በተለይም እንደ እናንተ ሐዘን ያጋጠማቸውን ሰዎች ለመርዳት ጥረት አድርጉ። እንዲህ ማድረጋችሁ በሐዘን እየተሠቃዩ ያሉ ሌሎችም እንዳሉ እንድታስታውሱ ይረዳችኋል።”—ካርሎስ
ስሜትህን አውጥተህ ጸልይ። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አምላክን “ጸሎት ሰሚ” በማለት ይጠራዋል። (መዝሙር 65:2) በተጨማሪም “[ይሖዋ] የተሰበረ ልብ ያላቸውን ይጠግናል፤ ቁስላቸውን ይፈውሳል” ይላል።—መዝሙር 147:3
“ይሖዋ የሚያስፈልጋችሁን ድጋፍና ማበረታቻ እንዲሰጣችሁ ጠይቁት። ሥቃዩ የሚከብድብን ጊዜ ሊኖር ይችላል፤ ሆኖም ይሖዋ ሁልጊዜም ከጎናችን ነው።”—ጃኔት
በምትጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ሁን። እያንዳንዱ ሰው ሐዘንን የሚያስተናግድበት መንገድ የተለያየ እንደሆነ አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ያዕቆብ ልጁ እንደሞተ ባሰበበት ወቅት ‘ፈጽሞ ሊጽናና እንዳልቻለ’ ይናገራል። (ዘፍጥረት 37:35) ስለዚህ ሐዘኑ ረጅም ጊዜ ቢቆይብህ የሚያስገርም ነገር አይደለም።
“የአያቴ እህት ከሞተች 15 ዓመት ቢያልፋትም አንዳንድ ነገሮችን ሳይ ትዝታዋ ይቀሰቀስብኛል።”—ቴይለር
አጥንትህ ከተሰበረ ሥቃዩ ከባድ እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም፤ ለመዳንም ጊዜ ይወስዳል። እስከዚያው ድረስ ግን ሐኪምህ ሰውነትህ ቶሎ እንዲያገግም የሚረዱ ምክሮችን ሊሰጥህ ይችላል።
የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ከሚያስከትለው “ቁስል” ከማገገም ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ከከባድ ሐዘን ለማገገም ጊዜ ይወስዳል። ስለዚህ ታጋሽ ሁን። በዚህ ርዕስ ውስጥ የተሰጡትን ሐሳቦች ልብ በል፤ ምናልባት አንዳንዶቹ ለአንተም ይጠቅሙህ ይሆናል።