በደቡብ ምሥራቅ እስያ የእውነት ብርሃን ፋና ወጊ የሆነችው ላይትቤረር
በ1930ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የይሖዋ ምሥክሮች በማሌዥያ፣ በኢንዶኔዥያና በአሁኗ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ምንም አልሰበኩም ነበር ማለት ይቻላል። ታዲያ ምሥራቹ ወደነዚህ አገሮች እንዲደርስ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? የአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ (አሁን የአውስትራሌዢያ ቅርንጫፍ ቢሮ ተብሏል) ለዚህ እልባት ለማስገኘት ሲል 16 ሜትር ርዝመት ያላት ባለ ሁለት ሸራ በሞተር የምትሠራ ጀልባ ገዛ። ጀልባዋ ላይትቤረር (ብርሃን አብሪ) የሚል ስያሜ ተሰጣት፤ እንዲህ የተባለችው ሁሉም አቅኚዎችa የሆኑት የጀልባዋ አባላት ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች መንፈሳዊ ብርሃን ለማድረስ ጀልባዋን እንዲጠቀሙባት ስለታሰበ ነው።—ማቴዎስ 5:14-16
በኒው ጊኒ መስበክ
የካቲት 1935 ሰባት ሰዎችን የያዘችው ጀልባ በአውስትራሊያ ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻ ላይ ከምትገኘው ከሲድኒ ተነስታ ጉዞ ጀመረች፤ መዳረሻቸው በስተ ሰሜን በኒው ጊኒ የምትገኘው ፖርት ሞርዝቢ ነበረች። በጉዟቸው ላይ ዓሣ ያጠምዱ የነበረ ሲሆን ነዳጅና ተጨማሪ ምግብ ለመግዛት እንዲሁም ለጥገና ሲሉ በተለያዩ ወደቦች ላይ ቆመዋል። ሚያዝያ 10, 1935 ከኩክታውን፣ ኩዊንስላንድ ተነስተው ባሕሩን ማቋረጥ ጀመሩ። አደገኛ የሆነውን ግሬት ባሪየር ሪፍ ወደሚያቋርጡበት የባሕር መስመር ሲያመሩ በጀልባዋ ሞተር ለመጠቀም መረጡ። ሆኖም ሞተሩ እንግዳ የሆነ ድምፅ ማሰማት ስለጀመረ ሞተሩን ለማጥፋት ተገደዱ። ታዲያ ወደ ኋላ ቢመለሱ ይሻላል ወይስ ሸራቸውን ዘርግተው በነፋሱ እየተነዱ ወደ ኒው ጊኒ ቢሄዱ? የጀልባዋ ካፒቴን የሆነው ኤሪክ ኤዊንስ “ወደ ኋላ መመለስ ጨርሶ አልፈለግንም” ብሏል። ስለዚህ ላይትቤረር ጉዞዋን የቀጠለች ሲሆን ሚያዝያ 28, 1935 በሰላም ፖርት ሞርዝቢ ደረሰች።
በላይትቤረር ላይ የነበሩት አቅኚዎች ከግራ ወደ ቀኝ፦ ዊልያም ሀንተር፣ ቻርልስ ሐሪስ፣ አለን በክኔል (ፊት ለፊት የሚታየው)፣ አልፍሬድ ሮው፣ ፍራንክ ዴዋር፣ ኤሪክ ኤዊንስ፣ ሪቻርድ ነትሊ
ጀልባዋ ጥገና እየተደረገላት ሳለ ከፍራንክ ዴዋር በስተቀር ሁሉም የጀልባዋ አባላት በፖርት ሞርዝቢ ምሥራቹን መስበክ ጀመሩ። አንደኛው ወንድም “ጀግና አቅኚ” እንደሆነ የተናገረለት ፍራንክ ግን እንዲህ ብሏል፦ ‘ብዙ መጽሐፎች ያዝኩና 32 ኪሎ ሜትር ወይም ከዚያ በላይ ወደ መሃል አገር በእግሬ ዘልቄ ገባሁ፤ ከዚያም ለነዋሪዎቹ መስበክ ጀመርኩ።’ ፍራንክ ሲመለስ በሌላ መንገድ የተጠቀመ ሲሆን አዞዎች የሚኖሩበትን አነስተኛ ወንዝ ማቋረጥ ነበረበት። ሆኖም በጥንቃቄ በመሻገር በሰላም ወደ ወደቡ ደረሰ። እነዚህ ወንድሞች ያከናወኑት ስብከት ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። በዚያ ወቅት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የወሰዱ አንዳንድ ሰዎች ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።
በጃቫ መስበክ
የጀልባዋ ሞተር ከተጠገነ በኋላ ላይትቤረር ከፖርት ሞርዝቢ ተነስታ በደች ኢስት ኢንዲስ (አሁን ያለውን ኢንዶኔዥያ ያጠቃልላል) ወደምትገኘው የጃቫ ደሴት አቀናች። የተለያዩ ነገሮችን ለመግዛት አንዳንድ ቦታዎች ላይ የቆሙ ሲሆን በመጨረሻም ሐምሌ 15, 1935 በባታቪያ (የአሁኗ ጃካርታ) መልሕቃቸውን ጣሉ።
በዚህ ጊዜ ቻርልስ ሐሪስ የተባለው የጀልባዋ ተሳፋሪ ላይትቤረርን ትቶ በጃቫ ለመቆየት ወሰነ፤ በዚያም ምሥራቹን በቅንዓት መስበኩን ቀጠለ።b እንዲህ ብሏል፦ “ያን ጊዜ በዋነኝነት አገልግሎታችንን የምናከናውነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለሰዎች እየሰጠን ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው ከተማ በመሄድ ነበር። እኔም በቻይንኛ፣ በአረብኛ፣ በኢንዶኔዥያኛ፣ በእንግሊዝኛና በደች የተዘጋጁ ጽሑፎችን ይዤ ነበር። ሰዎች ጽሑፎቻችንን በደስታ ይቀበሉ ስለነበር በአንድ ዓመት ውስጥ 17,000 የሚያህሉ ጽሑፎችን አበረከትኩ።”
ላይትቤረር ሸራዋን ዘርግታ ስትጓዝ
ቻርልስ በቅንዓት ያከናወነው አገልግሎት የደች ባለሥልጣናትን ትኩረት ስቦ ነበር። በአንድ ወቅት አንድ ባለሥልጣን በጃቫ ያገለግል የነበረ አንድ የይሖዋ ምሥክርን ጠርቶ ቻርልስ በነበረበት በኢስት ጃቫ ምን ያህል የይሖዋ ምሥክሮች እንዳሉ ጠየቀው። ወንድም “አንድ ብቻ” ሲል መለሰለት። ባለሥልጣኑም “ያምነኛል ብለህ ነው?” ብሎ ጮኸ። “በየቦታው ካሰራጫችኋቸው ጽሑፎች መገመት እንደሚቻለው በጣም ትልቅ ሠራዊት ሳይኖራችሁ አይቀርም!” አለ።
በሲንጋፖርና በማሌዥያ መስበክ
ላይትቤረር ከኢንዶኔዥያ ተነስታ ወደ ሲንጋፖር ያቀናች ሲሆን እዚያም ነሐሴ 7 ደረሰች። ወንድሞች በቆሙባቸው ቦታዎች ሁሉ የጀልባዋን ኃይለኛ ድምፅ ማጉያ በመጠቀም የተቀዱ ንግግሮችን ያጫውቱ ነበር። ይህ የስብከት ዘዴ ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ ትኩረት ይስብ ነበር። እንዲያውም ሲንጋፖር ፍሬ ፕሬስ የተባለው ጋዜጣ ‘ረቡዕ ምሽት ላይ ጎላ ያለ ድምፅ ከባሕሩ ላይ ይሰማ ነበር’ በማለት ዘግቧል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ ‘ላይትቤረር የሚል ስያሜ ከተሰጣት ጀልባ አንድ ለየት ያለ ንግግር እየተላለፈ ነበር፤ ከአውስትራሊያ የተነሳችው ይህች ጀልባ ሲንጋፖር ከደረሰችበት ጊዜ አንስቶ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሮግራሞችን ስታስተላልፍ ቆይታለች።’ ዘገባው እንደገለጸው ‘የአየሩ ሁኔታ ጥሩ ከሆነ እንዲህ ያሉት ፕሮግራሞች እስከ ሦስት ወይም አራት ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ጥርት ብለው ይሰማሉ።’
ላይትቤረር ሲንጋፖር እያለች ፍራንክ ዴዋር ጀልባዋን ትቶ አዲስ የአገልግሎት ምድብ ጀመረ። ከሌሎቹ ጋር ስለተለያየበት መንገድ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ጀልባዋ ላይ እየኖርን ሲንጋፖር ውስጥ ማገልገል ጀመርን። ላይትቤረር ጉዞዋን የምትቀጥልበት ጊዜ ሲደርስ ኤሪክ ኤዊንስ የነገረኝ ነገር አስደንግጦኝ ነበር። ‘እንግዲህ ፍራንክ ለማገልገል ያሰብከው በሳያም (የአሁኗ ታይላንድ) እንደሆነ ተናግረሃል። ልንሸኝህ የምንችለው እስከዚህ ድረስ ብቻ ነው። ከዚህ በኋላ መንገድህን ትቀጥላለህ!’ አለኝ። እኔም ምን እንደምል ቃላት አጥሮኝ ‘እንዴ ከዚህ ተነስቼ ወደ ሳያም እንዴት እንደምሄድ እኮ አላውቅም!’ አልኩት።” ኤሪክ፣ ከክዋላ ላምፑር (በአሁኗ ማሌዥያ ውስጥ ትገኛለች) ተነስቶ በባቡር ወደ ሳያም መጓዝ እንደሚችል ለፍራንክ ነገረው። ፍራንክም እንደተባለው ወደ ክዋላ ላምፑር ጉዞ ጀመረ፤ ከዚያም ከወራት በኋላ ታይላንድ ደረሰ።c
ላይትቤረር የማሌዥያን ምዕራባዊ ዳርቻ ይዛ ባደረገችው ጉዞ በጀሆር ባሩ፣ በምዋር፣ በማላካ፣ በክላንግ፣ በፖርት ስዌተናም (የአሁኗ ፖርት ክላንግ) እና በፔናንግ ቆማ ነበር። በእያንዳንዱ ወደብ ላይ አቅኚዎቹ፣ የተቀዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን በጀልባዋ የድምፅ ማጉያ ተጠቅመው ያሰሙ ነበር። በወቅቱ በኢንዶኔዥያ ታገለግል የነበረች ጂን ዴሻ የተባለች የይሖዋ ምሥክር፣ ሰዎች አንድ ባዕድ ነገር ያዩ ያህል ትኩረታቸው እንደተሳበ ተናግራለች። አቅኚዎቹ ንግግሮቹን ካሰሙ በኋላ ከጀልባዋ ወርደው፣ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ጽሑፎችን ይሰጡ ነበር።
በሱማትራ መስበክ
በጀልባዋ ላይ ያሉት አቅኚዎች ከፔናንግ ተነስተው የማላካ የባሕር ወሽመጥን በማቋረጥ በሱማትራ (አሁን የኢንዶኔዥያ ክፍል ናት) ወደምትገኘው ወደ ሜዳን ሄዱ። ኤሪክ ኤዊንስ ሁኔታውን አስታውሶ ሲናገር “በሜዳን አውራጃ ደስ የሚል ጊዜ አሳልፈናል፤ ብዙ ሰዎችም ምሥራቹን ለመስማት ፈቃደኞች ነበሩ” ብሏል። ወንድሞች በዚያ አካባቢ ወደ 3,000 ገደማ ጽሑፎችን ሰጥተዋል።
ላይትቤረር ወደ ደቡብ ጉዞዋን ስትቀጥል አቅኚዎቹ በሱማትራ ምሥራቃዊ ዳርቻ በሚገኙ ዋና ዋና ወደቦች ላይ ሰብከዋል። ኅዳር 1936 ላይትቤረር ወደ ሲንጋፖር የተመለሰች ሲሆን በዚያም ኤሪክ ኤዊንስ ተለያቸው። ከጥቂት ሳምንታት በኋላም በሲንጋፖር ትኖር የነበረች አይሪን ስትሮውስ የተባለች የይሖዋ ምሥክር አገባ። ከዚያም ኤሪክና አይሪን በሱማትራ አቅኚ ሆነው ማገልገላቸውን ቀጠሉ። ላይትቤረር ደግሞ አዲስ ካፒቴን አስፈለጋት።
በቦርንዮ መስበክ
አዲሱ ካፒቴን ኖርማን ሲኒየር የተባለ የሠለጠነ መርከበኛ ነበር። ከሲድኒ ተነስቶ ጥር 1937 ጀልባዋ ወዳለችበት ቦታ ደረሰ። ከዚያም ጀልባዋ ከሲንጋፖር ተነስታ ወደ ቦርንዮ እና ሰለቢስ (የአሁኗ ሱላዌሲ) ጉዞዋን ቀጠለች፤ በእነዚህ አካባቢዎች አቅኚዎቹ እስከ 480 ኪሎ ሜትር ድረስ ወደ መሃል አገር ዘልቀው በመግባት በስፋት ሰብከዋል።
ላይትቤረር በቦርንዮ ወደሚገኝ ሳማሪንዳ የተባለ ወደብ ላይ ስትደርስ የወደቡ ባለሥልጣን አቅኚዎቹን ለአካባቢው ሕዝብ እንዳይሰብኩ ከለከላቸው። ሆኖም ኖርማን ስለ ስብከቱ ሥራችን ካብራራለት በኋላ ሰውየው የተባበራቸው ሲሆን እንዲያውም ጽሑፎችን ወሰደ።
በሌላ ጊዜ ደግሞ አንድ ቄስ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ እንዲሰብክ ኖርማንን ጋበዘው። ኖርማን ግን ራሱ ንግግር ከመስጠት ይልቅ በድምፅ የተቀዱ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን በሸክላ ማጫወቻ አጫወተ፤ ቄሱም ንግግሮቹን ወደዳቸው። እንዲያውም ለጓደኞቹ የሚሰጣቸው አንዳንድ ጽሑፎች ወሰደ። እንዲህ ዓይነት ምላሽ የሰጠው ቄስ ግን እሱ ብቻ ነበር። በጥቅሉ ሲታይ ቀሳውስቱ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያከናውኑት ሥራ ደስተኞች አልነበሩም። እንዲያውም አቅኚዎቹ በድፍረት በሚሰጡት ምሥክርነት በጣም ስለተበሳጩ ላይትቤረር ሌሎች ወደቦች ላይ እንዳትቆም እገዳ እንዲጥሉ በባለሥልጣናቱ ላይ ጫና ማሳደር ጀመሩ።
ላይትቤረር የተጓዘችባቸው ቦታዎች፤ እነዚህ ቦታዎች በወቅቱ መጠሪያቸው ይህ ነበር
ወደ አውስትራሊያ መመለስ
ቀሳውስቱ ባነሳሱት እገዳ የተነሳ ታኅሣሥ 1937 ላይትቤረር ወደ አውስትራሊያ ለመመለስ ተገደደች። አቅኚዎቹ ወደ ሲድኒ የተመለሱ ሲሆን ሚያዝያ 1938 ለተካሄደው የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ልክ በወቅቱ ደረሱ። ላይትቤረር የተመለሰችው ከሲድኒ ከተነሳች ከሦስት ዓመት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ነው። በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ በአውስትራሊያ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ እንደታገደ አካባቢ ጀልባዋ ተሸጠች። ወንድም ኤዊንስ “የተገዛችበትን ዓላማ ሙሉ በሙሉ ተወጥታለች” ብሏል፤ ይህ ወንድም በላይትቤረር ላይ ያሳለፈውን ጊዜ “በሕይወቴ በጣም የተደሰትኩባቸው ዓመታት” በማለት ገልጿቸዋል።
ላይትቤረር ትታ ያለፈችው ቅርስ
በላይትቤረር ላይ የነበሩት አቅኚዎች ብዙ ሕዝብ በሚኖርበት ሰፊ ክልል ውስጥ የመንግሥቱን ዘር ዘርተዋል። ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም ያከናወኑት ሥራ ውሎ አድሮ ፍሬ አፍርቷል። (ሉቃስ 8:11, 15) እነዚያ አቅኚዎች በዚያ ወቅት በሰበኩባቸው አገሮች ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ከ40,000 የሚበልጡ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ይገኛሉ። በጣት የሚቆጠሩት እነዚያ ደፋር ወንድሞች እና እንደ ስሟ ሆና የተገኘችው ጀልባቸው በእርግጥም አስደናቂ ቅርስ ትተው አልፈዋል!
a አቅኚዎች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።
b የቻርልስ ሐሪስ የሕይወት ታሪክ በሰኔ 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጥቷል።