የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • lfs ርዕስ 18
  • “ያለቃል” ባለቤቴን መለወጥ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ያለቃል” ባለቤቴን መለወጥ
  • የይሖዋ ምሥክሮች የሕይወት ታሪኮች
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • እንቢ ማለት የማልችለው ግብዣ
  • ተቃውሞው ተባባሰ
  • ትልቅ ለውጥ አጋጠመን
  • ይሖዋ ላደረገልኝ ያልተቋረጠ ድጋፍ አመስጋኝ ነኝ
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • “ይሖዋ እንደገና አገኘኸኝ!”
    ንቁ!—2004
  • ከኤድስ የከፋ ነገር
    ንቁ!—1993
  • ‘እንደ ሚዳቋ የምዘልበት’ ጊዜ ይመጣል
    ንቁ!—2006
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋ ምሥክሮች የሕይወት ታሪኮች
lfs ርዕስ 18
ኢባያ ባታ።

ኢባያ ባታ | የሕይወት ታሪክ

“ያለቃል” ባለቤቴን መለወጥ

ይሖዋን እንድወደው ያደረጉኝ ብዙ ምክንያቶች አሉ። የእሱ ሕዝቦች የሚያሳዩት ፍቅርና ወዳጃዊ ስሜት እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እውነትን ማስተማራቸው ልቤን በጥልቅ ነክቶታል። አምላክ ለሰዎች እንደሚያስብና ለወደፊቱ ጊዜ አስደናቂ ተስፋ እንደሰጠ መማሬም አስደስቶኛል። ሆኖም ባለቤቴ የምማረውን ነገር አልወደደውም፤ ይህም ብዙ ችግሮች አስከትሎብኛል።

ኢባያ እና ኢሽቫን በሠርጋቸው ቀን።

በሠርጋችን ቀን

የተወለድኩት በ1952 ሩማንያ ውስጥ ነው። እናቴ የተጠመቀች የይሖዋ ምሥክር ብትሆንም በወቅቱ ቀዝቅዛ ነበር፤ ስለዚህ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚወስደኝ ሰው አልነበረም። በዚያ ላይ ደግሞ በወቅቱ ሩማንያ በኮሚኒስት አገዛዝ ሥር ስለነበረች የይሖዋ ምሥክሮች የሕትመትና የስብከት እንቅስቃሴ ታግዶ ነበር። ስለዚህ 36 ዓመት እስኪሆነኝ ድረስ ስለ ይሖዋም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያስተምረው ትምህርት የማውቀው ነገር አልነበረም። ሆኖም በ1988 ከባለቤቴ ከኢሽቫን ጋር ሳቱ ማሬ በተባለች ከተማ ስንኖር ያጋጠመኝ ነገር ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ ቀየረው።

እንቢ ማለት የማልችለው ግብዣ

አንድ ቀን እናቴ ልትጠይቀኝ መጣች። ከዚያም እንዲህ አለችኝ፦ “አክስትሽን ለመጠየቅ ልሄድ ነው። ለምን አብረሽኝ አትሄጂም? ከዚያ በኋላ አንዳንድ ነገሮችን እንገዛዛለን።” ሌላ ጉዳይ ስላልነበረኝ በሐሳቧ ተስማማሁ።

አክስቴ ቤት ስንደርስ በዚያ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ እየተካሄደ ነበር፤ በስብሰባው ላይ ከእሷ ውጭ ወደ ዘጠኝ የሚያህሉ ሰዎች ተገኝተው ነበር። ለካስ እናቴ መልሳ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክር ሆና ነበር። ያን ዕለት ማለዳ የሰማሁት ነገር ልቤን በጥልቅ ነካው።

ፕሮግራሙ ሲያልቅ ስብሰባውን ይመራ የነበረው ወንድም መጥቶ ተዋወቀኝ። “ያኖሽ እባላለሁ” አለኝ። ከዚያም “ስብሰባውን በትኩረት ስትከታተዪ እንደነበር አስተውያለሁ። ትምህርቱን ወደድሽው?” አለኝ። እኔም እንዲህ ባለ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ እንደማላውቅና ድጋሚ መምጣት እንደምፈልግ ነገርኩት። እሱም “መጽሐፍ ቅዱስን መማር ትፈልጊያለሽ?” በማለት ጠየቀኝ። ይህ እንቢ ማለት የማልችለው ግብዣ ነበር። ወደ እነዚህ ሰዎች የመራኝ አምላክ እንደሆነ አልተጠራጠርኩም።

በቀጣዩ ቀን ያኖሽ ከኢዳ ጋር አስተዋወቀኝ፤ እሷም መጽሐፍ ቅዱስን ታስተምረኝ ጀመር። ሆኖም ኢሽቫን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናሁ እንደሆነ ቢያውቅ ምን ይል ይሆን ብዬ ፈርቼ ነበር። በተደጋጋሚ ላዋራው ብሞክርም ጉዳዩን በቁም ነገር አልተመለከተውም። እያደረግኩ ባለሁት ነገር ደስተኛ እንዳልሆነ ገብቶኝ ነበር።

ያም ሆኖ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴን ቀጥዬ ነሐሴ 1989 ተጠመቅኩ። ከአራት ወር በኋላ በሩማንያ የነበረው የኮሚኒስት አገዛዝ የወደቀ ከመሆኑም ሌላ መሪው ተገደለ።

ተቃውሞው ተባባሰ

የአገዛዙን መውደቅ ተከትሎ ብዙ ነፃነት አገኘን። የይሖዋ ምሥክሮች በይፋ መሰብሰብና መስበክ ቻሉ። ሆኖም ይህ ነፃነት ለእኔ ተጨማሪ ተቃውሞ አመጣብኝ። ኢሽቫን “የፈለግሽውን ማመን ትችያለሽ፤ ከቤት ወደ ቤት እየሄድሽ እንድትሰብኪ ግን አልፈልግም” አለኝ።

መቼም፣ መስበኬን እንደማላቆም የታወቀ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 4:20) ስለዚህ በተቻለኝ መጠን በዘዴ ለመስበክ እሞክር ነበር። አንድ ቀን ግን የኢሽቫን ጓደኞች ከቤት ወደ ቤት ሳገለግል አዩኝና ለኢሽቫን ነገሩት። ቤት ስገባ “እኔንም ሆነ ቤተሰባችንን እያሰደብሽ ነው!” በማለት ጮኸብኝ። ቢላ ወደ ጉሮሮዬ አስጠግቶ፣ መስበኬን ካላቆምኩ እንደሚገድለኝ ዛተብኝ።

እኔ ግን ተረጋግቼ ሁኔታውን ያስረዳሁት ከመሆኑም ሌላ እንደምወደው ነገርኩት። ይህም ለጊዜው ትንሽ አረጋጋው። ሆኖም በሌላ አጋጣሚ፣ ሃይማኖታዊ ይዘት ባለው በአንድ የቅርብ ዘመድ ሠርግ ላይ ለመገኘት ፈቃደኛ አለመሆኔ በድጋሚ አስቆጣው። ከዚያ በኋላ ስሜት የሚጎዱ ነገሮችን መናገሩን ገፋበት።

የሚያሳዝነው ይህ ሁኔታ ለ13 ዓመት ቀጠለ። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ኢሽቫን እንደሚፈታኝ በመግለጽ ያስፈራራኝ ነበር። በሩን ቆልፎ ወደ ቤት አላስገባ የሚለኝ ጊዜም ነበር። አንዳንዴ ደግሞ ሻንጣዬን ጠቅልዬ ከቤት እንድወጣ ይነግረኛል።

እነዚህን ከባድ ሁኔታዎች ለመቋቋም የረዳኝ ምንድን ነው? ወደ ይሖዋ በመጸለይ ለመረጋጋት እንዲረዳኝ እጠይቀው ነበር፤ ደግሞም እሱ ደግፎ እንደያዘኝ ይሰማኝ ነበር። (መዝሙር 55:22) ጉባኤውም ትልቅ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል። ሽማግሌዎችና አንዳንድ የጎለመሱ እህቶች ተስፋ ቆርጬ አገልግሎቴን እንዳላቆም አበረታተውኛል። ሚስቶች በመጽናትና ለይሖዋ ታማኝ ሆነው በመቀጠል ባሎቻቸውን “ያለቃል” መማረክ እንደሚችሉ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ያስታውሱኝ ነበር። (1 ጴጥሮስ 3:1) ከጊዜ በኋላ ይህ ሐሳብ በእኔ ሕይወት ውስጥ ሲፈጸም አይቻለሁ።

ትልቅ ለውጥ አጋጠመን

በ2001 ኢሽቫን አንጎሉ ውስጥ ደም ስለፈሰሰ መራመድ አቃተው። ለአንድ ወር ሆስፒታል ከተኛ በኋላ ለተወሰኑ ሳምንታት ማገገሚያ ውስጥ ቆየ። በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ከጎኑ አልተለየሁም። ምግብ አበላውና አዋራው እንዲሁም የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማሟላት እጥር ነበር።

ወንድሞችና እህቶችም ሊጠይቁት ይመጡ ነበር። ይህም ፍቅራቸውንና አሳቢነታቸውን በቅርበት እንዲመለከት አስችሎታል። ብዙዎቹ የቤት ውስጥ ሥራ ሊያግዙን ፈቃደኛ ነበሩ። ሽማግሌዎችም እኛን ለማጽናናትና ለመደገፍ ምንጊዜም ዝግጁ ነበሩ።

ወንድሞች ባደረጉልን ነገር ኢሽቫን ልቡ ተነካ፤ ላደረሰብኝ በደልም ይጸጸት ጀመር። በተጨማሪም ከጓደኞቹ መካከል አንዳቸውም ሊጠይቁት እንዳልመጡ አስተዋለ። ስለዚህ ኢሽቫን ከሆስፒታል ሲወጣ “መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና የይሖዋ ምሥክር መሆን እፈልጋለሁ” አለ። ከደስታዬ የተነሳ እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም!

ግንቦት 2005 ኢሽቫን ተጠመቀ። መራመድ ስለማይችል ወንድሞች በዊልቼር እስከ መጠመቂያ ገንዳው ከወሰዱት በኋላ በቀስታ ተሸክመው ውኃ ውስጥ በማስገባት አጠመቁት። ኢሽቫን ቀናተኛ የመንግሥቱ ሰባኪ ሆነ። በመስክ አገልግሎት ከእሱ ጋር ያሳለፍኳቸው ጥሩ ትዝታዎች አሉኝ። ሁኔታውን ሳስበው በጣም ይገርመኛል! እስቲ አስቡት—በአንድ ወቅት የአምላክን ቃል እውነት በመስበኬ ይቃወመኝ የነበረ ሰው አሁን ከጎኔ ሆኖ ምሥራቹን በደስታ ለሌሎች እያካፈለ ነው!

ኢሽቫን ለይሖዋ ያለው ፍቅር እያደገ የሄደ ሲሆን ጊዜውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ለማጥናትና በቃሉ ለመያዝ ይጠቀምበት ነበር። በጉባኤያችን ካሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር በእነዚህ ጥቅሶች ላይ መወያየት ያስደስተዋል። እነዚህን አጋጣሚዎች እነሱን ለማበረታታት ይጠቀምባቸዋል።

ኢባያ እና ዊልቼር ላይ የተቀመጠው ኢሽቫን ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር የተነሱት ፎቶግራፍ።

በክልል ስብሰባ ላይ ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር

የኢሽቫን ጤንነት እያሽቆለቆለ ሄደ። በተደጋጋሚ በአንጎሉ ውስጥ ደም ከፈሰሰ በኋላ የመናገር ችሎታውን አጣ፤ ከጊዜ በኋላም የአልጋ ቁራኛ ሆነ። ይህ ሁኔታ በመንፈሳዊ እንዲቀዘቅዝ ያደረገው ይመስላችኋል? በፍጹም! አቅሙ በፈቀደለት መጠን ማንበቡንና ማጥናቱን ቀጥሎ ነበር። ወንድሞችና እህቶች ሊጠይቁት ሲመጡ ስክሪን ያለው የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ተጠቅሞ ያነጋግራቸውና ያበረታታቸው ነበር። አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ኢሽቫንን መጠየቅ በጣም ያስደስተኛል። ሁሌም ወደ ቤት የምመለሰው ኃይሌ ታድሶና ተበረታትቼ ነው።”

የሚያሳዝነው ታኅሣሥ 2015 ኢሽቫን አረፈ። እሱን ማጣቴ ከባድ ሐዘን አስከትሎብኛል። በሌላ በኩል ግን በውስጤ ሰላም ይሰማኛል። ምክንያቱም ኢሽቫን ከመሞቱ ከረጅም ጊዜ በፊት የይሖዋ ወዳጅ መሆን ችሏል። ይህ በጣም ከሚያስደስቱኝ ነገሮች መካከል አንዱ ነው። በአሁኑ ጊዜ ኢሽቫን እና እናቴ በይሖዋ መታሰቢያ ውስጥ ናቸው። በድጋሚ ከእነሱ ጋር የምተቃቀፍበትንና ጽድቅ በሰፈነበት የይሖዋ አዲስ ዓለም ውስጥ እነሱን የምቀበልበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ።

ከ35 ዓመት ገደማ በፊት እኔና እናቴ አክስቴን ልንጠይቅ የሄድንበትን ያን ቀን መቼም አልረሳውም። አሁን 70 ዓመት አልፎኛል፤ በዘወትር አቅኚነት እያገለገልኩ ነው። ላደረገልኝ ነገር ሁሉ ይሖዋን ላመሰግን የምችልበት ከዚህ የተሻለ መንገድ የለም። (መዝሙር 116:12) ይሖዋ ተቃውሞ ባጋጠመኝ ወቅት ታማኝ ሆኜና ተረጋግቼ እንድቀጥል ረድቶኛል። ደግሞም ተቃውሞ ቢኖርም ሁኔታዎች ሊለወጡ እንደሚችሉ ተምሬያለሁ። ፈጽሞ ባልጠበቅኩት መንገድ ባለቤቴን ያለቃል ወደ እውነት ማምጣት ችያለሁ።

ኢባያ እና ሌላ እህት ከምሥክርነት መስጫ ጋሪ አጠገብ ቆመው። ኢባያ “ለዘላለም በደስታ ኑር!” የተባለውን ብሮሹር ተጠቅማ ለአንዲት ሴት ስትመሠክር።
    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ