በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ—ክራይሚያ
የሩሲያ ባለሥልጣናት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚያደርሱት ከባድ ተቃውሞ ወደ ክራይሚያም ተዛምቷል። የሩሲያ መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮችን ሕጋዊ ማኅበራት በማገድ ብቻ አልተወሰነም፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚያከናውኑትን አምልኮ ለማደናቀፍ ቆርጦ እንደተነሳም በግልጽ አሳይቷል። ሚያዝያ 2017 ከተጣለው እገዳ አንስቶ የሩሲያ ባለሥልጣናት፣ በሩሲያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ በርካታ ድንገተኛ ብርበራዎች አድርገዋል፤ ይህን ተከትሎም ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በቁጥጥር ሥር ውለዋል እንዲሁም ታስረዋል። በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተፋፋመው ይህ ዘመቻ በክራይሚያም ቀጥሏል።
ክራይሚያ ውስጥ የመጀመሪያው የብርበራ ዘመቻ የተካሄደው ኅዳር 15, 2018 በጃንኮይ ከተማ ነው፤ በወቅቱ ወደ 200 የሚጠጉ ፖሊሶችና ልዩ ኃይሎች በስምንት የይሖዋ ምሥክሮች መኖሪያ ቤቶች ላይ ድንገተኛ ብርበራ አደረጉ፤ በወቅቱ በእነዚህ ቤቶች ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በትናንሽ ቡድኖች ሆነው መጽሐፍ ቅዱስን እያነበቡና እየተወያዩ ነበር። ቢያንስ 35 የሚሆኑ መሣሪያ የታጠቁና ጭንብል ያጠለቁ ፖሊሶች የሰርጌ ፊላቶቭን ቤት ሰብረው ገቡ፤ ስድስት የይሖዋ ምሥክሮች በዚያ ተሰብስበው ነበር። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በፖሊሶቹ የኃይል እርምጃ ተደናግጠው ነበር። ፖሊሶቹ አንድን የ78 ዓመት አረጋዊ ከግድግዳ ጋር ካጣበቁት በኋላ መሬት ላይ አስተኝተው በካቴና አሰሩት፤ በጣም ስለደበደቡት በአስቸኳይ ወደ ሆስፒታል መሄድ አስፈለገው። ሌሎች ሁለት በዕድሜ የገፉ ወንዶችም በሁኔታው በጣም ተደናግጠው ደማቸው ከፍ ስላለ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። የሚያሳዝነው፣ ቤቷ የተበረበረባት አንዲት ወጣት ፅንስ ተጨናግፎባታል።
ብርበራውን ተከትሎ ሰርጌ የሩሲያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 282.2(1)ን መሠረት በማድረግ ‘የጽንፈኛ ድርጅትን እንቅስቃሴ አስተባብሯል’ የሚል ክስ ቀረበበት። መጋቢት 5, 2020 በክራይሚያ የሚገኘው የአውራጃ ፍርድ ቤት በሰርጌ ላይ የስድስት ዓመት እስራት አስተላለፈ። ፍርዱ ከተላለፈ በኋላ ወዲያውኑ ወደ እስር ቤት ተወሰደ።
በ2018 በጃንኮይ ከተካሄደው ብርበራ በኋላ ባሉት ዓመታት የልዩ ኃይል አባላት፣ በጽንፈኝነት እንቅስቃሴዎች በመካፈል የተጠረጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ሰብረው መግባታቸውን ቀጠሉ። በቅርቡ ብርበራ የተካሄደው ነሐሴ 7, 2024 ሲሆን መሣሪያ የታጠቁና ጭንብል ያጠለቁ በርካታ ፖሊሶች የአምስት የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ፈተሹ፤ ፍተሻ ከተካሄደባቸው መካከል በራዝዶልኖዬ መንደር የምትኖረው የ68 ዓመቷ ታማራ ብራትሴቫ ትገኝበታለች። የጽንፈኛ ድርጅት እንቅስቃሴዎችን በማስተባበር ወንጀል የተከሰሰችው ታማራ ጉዳይዋ በፍርድ ቤት እየታየ ነው። ጥቅምት 2024 ደግሞ ዩሪ ጌራሽቼንኮ እና ሰርጌ ፓርፌኖቪች የተባሉ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች የስድስት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል። ከዚህ ቀደም የገደብ እስራት ተፈርዶባቸው የነበረ ቢሆንም አቃቤ ሕጉ ጠንከር ያለ ቅጣት ሊበየንባቸው እንደሚገባ ተከራከረ፤ ፍርድ ቤቱም በዚህ በመስማማት እስራት በይኖባቸዋል። ሁለቱም ችሎት ላይ በቁጥጥር ሥር ውለው ወዲያውኑ ወደ ወህኒ ተወስደዋል።
ቤታቸው በተፈተሸባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የወንጀል ክሶች የተመሠረቱ ሲሆን ጥፋተኛ ናቸው ተብለው የተፈረደባቸውም አሉ፤ በአሁኑ ወቅት 14 የይሖዋ ምሥክር ወንዶች እስከ ስድስት ዓመት ተኩል የሚደርስ እስራት ተፈርዶባቸው ወህኒ ቤት ወርደዋል። ሁሉም የተከሰሱት የጽንፈኛ ድርጅትን እንቅስቃሴ አስተባብራችኋል በሚል ነው።
የጊዜ ሰሌዳ
ሰኔ 17, 2025
በክራይሚያ የሚኖሩ 14 የይሖዋ ምሥክሮች በአሁኑ ወቅት ታስረዋል።
ጥቅምት 3, 2024
ዩሪ ጌራሽቼንኮ እና ሰርጌ ፓርፌኖቪች የስድስት ዓመት እስራት ተፈረደባቸው።
ነሐሴ 7, 2024
ፖሊሶች በአሉሽታ፣ በራዝዶልኖዬ እና በሴኖኮስኖዬ የሚኖሩ አምስት የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ፈተሹ። ታማራ ብራትሴቫ የወንጀል ክስ ተመሠረተባት።
ነሐሴ 5, 2021
ስምንት የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ተፈተሹ። አሌክሳንደር ዱቦቬንኮ እና አሌክሳንደር ሊትቪንዩክ በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
ጥቅምት 1, 2020
በሴቫስቶፖል ያሉ ዘጠኝ ቤቶች ተበረበሩ። ኢጎር ሽሚድት በቁጥጥር ሥር ውሎ ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ተደረገ።
ሰኔ 4, 2019
የልዩ ኃይል አባላት በሴቫስቶፖል የሚኖሩ አሥር የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ፈተሹ። በኋላም፣ ቪክቶር ስታሺቭስኪ የጽንፈኝነት እንቅስቃሴዎችን አደራጅቷል የሚል ክስ ተመሠረተበት።
መጋቢት 20, 2019
የልዩ ኃይል አባላት በአሉፕካ እና በያልታ የሚገኙ ስምንት ቤቶችን በረበሩ። አርተም ገራሲሞቭ ምርመራ ከተደረገበት በኋላ ‘ጽንፈኛ እንቅስቃሴዎችን አደራጅቷል’ በሚል ተከሰሰ።
ኅዳር 15, 2018
ከ200 የሚበልጡ ፖሊሶችና ልዩ ኃይሎች የሰርጌ ፊላቶቭን ጨምሮ በጃንኮይ የሚገኙ ስምንት ቤቶችን በረበሩ።