የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g94 10/8 ገጽ 26-29
  • ንጹሕ ለመሆን ያለውን ትግል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ንጹሕ ለመሆን ያለውን ትግል
  • ንቁ!—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የንጽሕና ጥቅሞች
  • የቤተሰብ ትብብር
  • የመከላከያ እርምጃዎች
  • ትክክለኛ አመለካከት
  • በትግሉ አሸናፊዎች ልትሆኑ ትችላላችሁን?
  • ንጽሕና አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ቤተሰባችሁን ማስተዳደር የምትችሉት እንዴት ነው?
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
  • ጤንነትህን ለመጠበቅ የሚረዱ ስድስት መንገዶች
    ንቁ!—2003
  • ንጹሕ ቤት እያንዳንዳችን የምናበረክተው አስተዋጽኦ
    ንቁ!—2005
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1994
g94 10/8 ገጽ 26-29

ንጹሕ ለመሆን ያለውን ትግል ማሸነፍ

ኬንያ የሚገኘው የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

“ማማ፣ ናኩፋ!” ብሎ ጮኸ ልጁ። ትርጉሙ “እማማ መሞቴ ነው!” ማለት ነው። አንድ ሰው ሊገድለው ሞክሮ ይሆን? አይደለም፤ ትንሹ ልጅ ሳፋ ውስጥ ቆሞ እናቱ ፍትግ አድርጋ እያጠበችው ናት። ልጁ እናቱን ለማስቆም በጣም ቢታገልም እናትዬዋ አጥባ ጨረሰች!

በአፍሪካ ውስጥ በጣም ድህነት ያለበት ነው በሚባለው አካባቢ እንኳ ሳይቀር ይህን የመሰለ ሁኔታ ማየት የተለመደ ነው። ያም ሆኖ ግን ንጽሕናን መጠበቅ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። በጣም ሞቃት የሆነው የአፍሪካ የአየር ጠባይ የጽዳት ሥራን የበለጠ ያከብደዋል። ነፋሱ አቧራውን እያነሳ ቤት ውስጥ እያንዳንዱን ስንጥቅ ደቃቅ ቡናማ ዱቄት ያለብሰዋል። ኢኮኖሚው እያሽቆለቆለ በመሄዱ ምክንያት የንጽሕና ዕቃዎች፣ የማሳደሻዎች፣ ሌላው ቀርቶ የውኃ ዋጋ ጭምር በመናሩ ብዙ ሰው በቀላሉ ሊያገኛቸው አይችልም። ሴቶች ውኃ ለመቅዳት በየቀኑ ረጅም ርቀት በሚጓዙባቸው ቦታዎች ይህን እንዲህ ውድ የሆነ ነገር ለማጠብ እንደማይጠቀሙበት የታወቀ ነው።

በከተማዎችና በአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የሄደው የሕዝብ ብዛት ለጤና አደገኛ የሆነ ሁኔታ ፈጥሯል። ክፍት የፍሳሽ ማውረጃ ቦዮች፣ በተገቢው ቦታ ተወስደው ያልተጣሉ የቆሻሻ ክምችቶች፣ የቆሸሹ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች፣ በሽታ አስተላላፊ የሆኑ አይጦች፣ በረሮዎችና ዝንቦች በየቦታው የሚታዩ የተለመዱ ነገሮች ሆነዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ብዙ ሰው ተገቢ ስለሆነ ጤና አጠባበቅና ስለ ጽዳት እውቀት የለውም። ሰዎች ሞት ሊያስከትል እንደሚችል ካለመገንዘብ የተነሣ ውኃን ይበክላሉ። አይጦችና ሌሎች በሽታ አስተላላፊ እንስሳት በቸልታ ይታለፋሉ። እንዲያውም ልጆች ይጫወቱባቸዋል።

የንጽሕና ጥቅሞች

ቤተሰቦች ነገሮችን ሁሉ ለማጽዳት እንዲህ መድከምና ይህን ያህል ወጪ ማውጣት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ቆሻሻ በሆኑ አካባቢዎች ባክቴሪያዎችና በሽታ አስተላላፊ ጥገኛ ተዋስያን በብዛት ይራባሉ። ስለዚህ ማጠብ ወይም መታጠብ ቀላል ነገር ቢሆንም ለልጃችሁ ሞት ወይም ሕይወት ማለት ሊሆን ይችላል! ጽዳት የቤት ወጪን እንደሚጨምር እሙን ነው። ለማጠቢያ የሚሆን ውኃ ውድ ወይም ለማግኘት የሚያስቸግር ሊሆን ይችላል። መድኃኒት ግን ከዚህ ይበልጥ ውድ ነው። ሳሙና፣ የማጠቢያ መርዝ፣ ሰም፣ የአይጥ ወጥመድና የቆሻሻ ማጠራቀሚያ መግዛት ገንዘብ ይጠይቃል፤ ሆኖም ለሐኪም ቤት የሚወጣውን ወጪ አያክ⁠ልም።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ንጹሕ”፣ “የጠራ” እና “ማጠብ” ከሚሉት ቃላት ጋር የሚዛመዱ ቃላት ከ400 ጊዜ በላይ ተጠቅሰው ይገኛሉ። ለእስራኤላውያን ተሰጥቷቸው የነበረው የአምላክ ሕግ የሰውነትን ንጽሕና መጠበቅንና ጥሩ የመጸዳዳት ልማድን የሚያበረታቱ ተለይተው የተጠቀሱ መመሪያዎች ነበሩበት። (ዘጸአት 30:​18–21፤ ዘዳግም 23:​11–14) ‘ባልንጀራህን ውደድ’ የሚለው ትእዛዝም ክርስቲያኖች የራሳቸውንም ሆነ የቤታቸውን ንጽሕና እንዲጠብቁ ይገፋፋቸዋል። — ማቴዎስ 22:​39

በገጽ 10 ላይ ያለው ሣጥን በቤት አካባቢ ሊደረጉ የሚችሉ ንጽሕና ለመቆጣጠር የሚረዱ ጠቃሚ ነጥቦችን ይጠቁማል። መመሪያዎቹ በማንኛውም አገር ሊሠሩ የሚችሉ ናቸው። ከተሰጡት ሐሳቦች ውስጥ አንዳንዶቹ ለምሳሌ ወለሉን በሰም መወልወል (በዚያውም ትንንሽ ስንጥቆችን መድፈን) እንዲሁም ቆሻሻን ክዳን ባለው ማጠራቀሚያ ውስጥ ማስቀመጥ ነፍሳትና ሌሎች በሽታ አስተላላፊ እንስሳት ወደ ቤታችሁ ተስበው ለመግባት ያላቸውን አጋጣሚ በእጅጉ ይቀንሰዋል። የበርና የመስኮት ቀዳዳዎችን መድፈንም አቧራ እንዳይገባ ከመከላከሉም በላይ ትንንሽ ነፍሳት ሾልከው እንዳይገቡ ያደርጋል። ስለዚህ ንጽሕና ሌላው ቢቀር ቤታችሁን የሚያምር መኖሪያ ያደርገ⁠ዋል!

የቤተሰብ ትብብር

አንዲት የቤት እመቤት እነዚህን የንጽሕና መቆጣጠሪያ ዘዴዎች ካጠናች በኋላ ቋሚ የጽዳት ፕሮግራም ታወጣ ይሆናል። የቤተሰቡ አባላት በሙሉ ከተባበሩ ፕሮግራሙ አድካሚ ሸክም አይሆንም።

ለምሳሌ ያህል በምሥራቅ አፍሪካ በሚገኝ አንድ ከተማ ውስጥ በጠባብ ቤት ውስጥ የምትኖረውንና የስምንት ልጆች እናት የሆነችውን ጄሲንታን እንውሰድ። ቤቷን እንዴት ማራኪ አድርጋ ልትይዝ እንደቻለች በተጠየቀች ጊዜ “ሁሉም የየራሳቸውን ድርሻ መሥራት ለምደዋል። አንድ ሰው የሆነ ነገር ቢደፋበት መወልወያ ጨርቅ ወይም ሌላ ነገር ይሰጠውና ያጸዳል። ሳያዝረከረኩ መብላትም ተምረዋል” ብላለች። አባትም ከሚስቱ ጋር ሊተባበርና በምታደርገው ጥረት ሊደግፋት ይችላል። እሱም ልጆቹን ገና ከሕፃንነታቸው ንጹሕና ጽዱ እንዲሆኑ በማሠልጠኑ ሥራ ሊካፈል ይችላል።

የመከላከያ እርምጃዎች

አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው የመከላከያ እርምጃዎችን በመውሰድ የጽዳት ሥራን ለማቅለል ይችላል። ለምሳሌ አቧራን ለመቀነስ በቤታችሁ አካባቢ ሣርና ዛፎች ለምን አትተክሉም? ወይም በቤታችሁ አቅራቢያ የተወሰነ አካባቢ በማጠር ልጆቻችሁ የሚጫወቱበት ንጹሕ ቦታ እንዲኖራቸው ሞክሩ። ሰፈራችሁ ጭንቅንቅ ያለ ከሆነ ብዙም ያልተጨናነቀ ሰፈር መኖሪያ ቤት ለመፈለግ ትችሉ ይሆን? የምታገኙት ቤት ከምትሠሩበት ቦታ ራቅ ያለ ሊሆን ስለሚችል መንገድ ይጨምርባችሁ ይሆናል፤ ቢሆንም የሚቆጭ አይደለም።

እንዲሁም ያስቀመጣችኋቸውን የማይጠቅሙ ዕቃዎች ለማስወገድ ሞክሩ። እንዲህ ማድረግ ቤታችሁ ሳያስፈልግ እንዳይዝረከረክ ያደርጋል። ወደቤታችሁ የሚያስገባው መንገድ በዝናብ ጊዜ የሚጨቀይ ከሆነ መግቢያችሁ ላይ ጠጠር ለማፍሰስ ለምን አትሞክሩም? የመጸዳጃ ቤታችሁ ከቤት ውጭ ከሆነ ሌሎች ገብተው እንዳያቆሽሹባችሁ ለምን አትቆልፉትም?

ትክክለኛ አመለካከት

ሰው የሚያየው ነገር ብቻ ቢጸዳ ይበቃል የሚል አመለካከት አትያዙ። አንዳንዶች በፊት በኩል ያለው ግቢ ንጹሕ ከሆነ ጓሮው ቢዝረከረክም ምንም አይደለም፤ ሳሎኑ ከጸዳ መኝታ ቤቱ ቢዝረከረክ ወይም የወጥ ቤቱ ግድግዳ በእጅ ምልክትና በጭስ ቢጠቁርም ምንም አይደለም የሚል ስሜት አላቸው። ይህ ዓይነቱ አንድ መሥመር ያልተከተለ ሁኔታ ኢየሱስ ለፈሪሳውያን የተናገረውን ያስታውሰናል:- “በውስጡ ቅሚያ . . . ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ [ታጠራላችሁ።] . . . ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ።” (ማቴዎስ 23:​25, 26) እያንዳንዱን ክፍል ሁልጊዜ አንድም ቆሻሻ የሌለበት እንዲሆን ማድረግ እንደማይቻል የታመነ ነው። ይሁን እንጂ የተወሰኑ ክፍሎች ብቻ ሳይሆን ቤቱ በጠቅላላ ንጹሕ እንዲሆን ቢያንስ ግብ ማውጣቱ ጠቃሚ አይደለምን?

ቤቱን ያላጸዳው አከራዩ ነው ብሎ ማሳበብም ትክክል አይሆንም። እውነት ነው ቤቱ ለረጅም ጊዜ ቀለም ሳይቀባ ቆይቶ ሊሆን ይችላል፤ ቢያንስ ቢያንስ ግን ግድግዳው መታጠብ ይችላል። ምናልባትም ቤቱን እናንተ እንድታሳድሱ፣ የቤቱ ባለቤት ደግሞ ኪራዩን እንዲቀንስላችሁ ልትዋዋሉ ትችሉ ይሆናል።

በትግሉ አሸናፊዎች ልትሆኑ ትችላላችሁን?

“በመጀመሪያ ላይ ማመን አቅቶኝ ነበር” ይላል ጆሴፍ የተባለ አንድ አፍሪካዊ የቤተሰብ ኃላፊ። ከአሁን በፊት የሰማውን ንጽሕናን በተመለከተ የተሰጠ አንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር ጠቀሰ። ቤተሰቡ የሚኖረው ብዙ ቤቶች ባሉበት የተጨናነቀ ሰፈር በምትገኝ ከእንጨት በተሠራች አንዲት ትንሽ ቤት ውስጥ ነው። መጸዳጃ ቤቱ የጋራ ሲሆን መንገዱም ያልተስተካከለ ነው። ያም ሆኖ ግን ጆሴፍና ቤተሰቡ እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በቤታቸው ተግባራዊ ለማድረግ ሞከሩ። “አሁን ልጆቼ ሰንደል ጫማ ያደርጋሉ፤ እግራችንን እንጠርጋለን፤ እጃችንን በሳሙናና በውኃ እንታጠባለን፤ እንዲሁም ንጽሕናችንን ለመጠበቅ ሌሎች ነገሮች እናደርጋለን” ይላል ጆሴፍ። ምን ውጤት አገኙ? “በጣም ነው የገረመኝ። ልጆቹ እንደ በፊቱ ቶሎ ቶሎ አይታመሙም፤ ስለዚህ ለሐኪም ቤት እናወጣ የነበረው ያ ሁሉ ወጪ ቀርቶልናል።”

እንግዲያው በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የሚኖሩ ወላጆች ከሌላው ነገር ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ በሆነ ወጪና ጥረት ቤታቸው ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው የማያሰጋና ንጹሕ መኖሪያ እንዲሆን ሊያደርጉት ይችላሉ። ይሁን እንጂ በማደግ ላይ ባለው ዓለም የሚኖረውን ሕዝብ የጤና ችግሮች ለመቅረፍ ከዚህ የበለጡ ብዙ ነገሮች ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑ ግልጽ ነው።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሳሙና፣ የማጠቢያ መርዝ፣ ሰም፣ የአይጥ ወጥመድና የቆሻሻ ማጠራቀሚያ መግዛት ገንዘብ ይጠይቃል፤ ሆኖም ለሐኪም ቤት የሚወጣውን ወጪ አያክልም

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የቤትን ንጽሕና መቆጣጠሪያ

መጸዳጃ ቤት:-

ከተጸዳዱ በኋላ ውኃ መድፋት

ባለ መቀመጫ ላልሆኑ ወይም ከቤት ውጭ ነጠል ብለው ለሚገኙ መጸዳጃ ቤቶች ፀረ ነፍሳት መርዝ መርጨት

ከተጸዳዱ በኋላ እጅን በሳሙናና በውኃ መታጠብ

የመጸዳጃውን ቤት መቀመጫ፣ ክዳን፣ እጅ መታጠቢያና ሌሎቹንም የመጸዳጃ ቤት ዕቃዎች በየጊዜው በማጠቢያ መርዝ ማጠብ

ወጥ ቤት:-

ምግብ ከማዘጋጀትም ሆነ ከማቅረብ በፊት እጅን በሳሙናና በውኃ መታጠብ

ቆሻሻን ክዳን ባለው መያዣ ውስጥ ማስቀመጥና ቶሎ ቶሎ መድፋት

የቆሸሹ የወጥ ቤት ዕቃዎችን ሳያጥቡ አለማሳደር

አትክልትና ፍራፍሬ ከመመገብ በፊት በደንብ ማጠብ

ምግብ የሚሠራው ውጪ ከሆነ ሳህኖችንና የወጥ ቤት ዕቃዎችን መሬት ላይ አለማስቀመጥ። ምግብ ላይ አቧራ እንዳያርፍ መከላከል

በየማዕዘኑ ላይ ያሉ ቦታዎችንና ቁም ሳጥኖች በየሳምንቱ ማጽዳት

ጡጦን በፈላ ውኃ ማጠብ

ውኃው የተበከለ ከሆነ አፍልቶ መጠጣት

ቤት ውስጥ:-

የቆሸሹና የሚታጠቡ ልብሶችን በቅርጫት ወይም በሌላ ዕቃ ውስጥ ማስቀመጥ

ልብስን በንጹሕ የልብስ ማጠቢያ ውኃ ቶሎ ቶሎ ማጠብ

የእንጨት በሮችን፣ የጣውላ ወለልንና፣ ሌሎች የእንጨት ዕቃዎችን በየጊዜው በሰም መወልወል

ግድግዳ፣ በርና የመብራት ማጥፊያና ማብሪያ ላይ ያሉትን ቆሻሻዎች ማጽዳት

መስኮት መወልወል

አይጦችን በወጥመድ ይዞ መግደል፤ በረሮዎችንና ሌሎች ነፍሳትንም መግደል

ትኋንና ሌሎች ነፍሳት እንዳይኖሩ በየጊዜው መኝታን መፈተሽ

መግቢያ በር ላይ የእግር መጥረጊያ ምንጣፍ ወይም እርጥብ ጨርቅ ማስቀመጥ

በግድግዳዎችና በበሮች ላይ ያሉ ቀዳዳዎችንና የተሰነጠቁ ወለሎችን መድፈን

የተሰበሩ የመስኮት መስታወቶችን መቀየር

የተቀደዱ ፍራሾችንና የስፖንጅ ልባስ ያላቸውን ዕቃዎች ማደስ

ከቤት ውጭ:-

ቆሻሻን መቅበር ወይም ማቃጠል

የሰውንም ሆነ የእንስሳትን ዓይነ ምድር ማስወገድ ወይም መቅበር

ፍሳሾች በግቢ ውስጥ እንዳያልፉ ቦይ ቆፍሮ መስመር ማስያዝ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቤተሰባችሁን አስተምሩ​—የአካባቢን ንጽሕና ለመጠበቅ ማድረግ ያሉብንና የሌሉብን ነገሮች

ወደ ቤት ሲገቡ እግርን መጥረግ

ሽፍን ወይም ክፍት ጫማ ማድረግ

ከተጸዳዱ በኋላ ውኃ መድፋት

ከተጸዳዱ በኋላ እንዲሁም ምግብ ከመመገብ በፊት እጅን በሳሙናና በውኃ መታጠብ

አፍንጫን ማጽዳት

ወለል ላይ የሚቀመጡ ከሆነ ሸሚዝ፣ ሱሪ ወይም ቀሚስ መልበስ

የሚከተሉትን ነገሮች በእጅ አለመንካት:-

 ዓይነ ምድርን

 አይጦችን

 በረሮዎችን

 ቆሻሻን

 ባለቤት የሌላቸውን ውሾች

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ