የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g93 4/8 ገጽ 10-13
  • በብዙ ቅጂዎች የተሰራጩ ሃይማኖታዊ መጽሐፎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በብዙ ቅጂዎች የተሰራጩ ሃይማኖታዊ መጽሐፎች
  • ንቁ!—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ትክክለኛ የሆነ የቅዱሳን ጽሑፎች ስብስብ ማዘጋጀት
  • “ቫት ሽክሪፍት፣ ብሊፍት”
  • የማን ቃል ነው? ለምን ያህል ሰዎችስ?
  • ሃይማኖቶች በመጽሐፎቻቸው ሲመዘኑ
  • መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ሁሉንም ነገር በትክክል ይነግረናል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
  • መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዋነኛው መማሪያ መጽሐፋችን
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ክፍል 7:- 1500 ከዘአበ ገደማ ጀምሮ​—ሂንዱይዝም —​ስምህ ችሎ መኖር ነው
    ንቁ!—1993
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1993
g93 4/8 ገጽ 10-13

የሃይማኖት የወደፊቱ ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንጻር ሲታይ

ክፍል 6​—ከ1513 ከዘአበ ጀምሮ​—በብዙ ቅጂዎች የተሰራጩ ሃይማኖታዊ መጽሐፎች

“ ሃይማኖታችን የሚገኘው በመጽሐፍ ውስጥ ነው።” የ18ኛው መቶ ዘመን እንግሊዛዊ የሥነ ጽሑፍ ሰውና ባለቅኔ፣ ሳሙኤል ጆንሰን

ትልልቅ ሃይማኖቶች ሁሉ የራሳቸው መጽሐፍ ወይም መጻሕፍት አሏቸው። “በቅርጽ፣ በመጠን፣ በዕድሜና በሚሰጣቸው የቅድስና ደረጃ በእጅጉ ሊለያዩ” ቢችሉም ይላል ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ “የሁሉም የጋራ ባህርይ የመጻሕፍቱ ቃል በአማኞቻቸው ዘንድ እንደ ቅዱስ ነገር ተደርጎ መታየቱ ነው።” ቅዱሳን ተደርገው የሚታዩ በጣም ብዙ መጻሕፍት መኖራቸው ራሱ የሰው ልጅ በተፈጥሮው ሃይማኖታዊ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ (የክርስትና)፤ ቁራን (የእስልምና)፣ ታልሙድ (የይሁዲነት)፣ ቬዳስና (የሂንዱይዝም) ትሪፒታካ (የቡድሂዝም) በሠፊው የታወቁ የትልልቅ ሃይማኖቶች ቅዱሳን ጹሑፎች ናቸው።a

ሌሎች መጻሕፍት ደግሞ በየትኛውም የሃይማኖት ድርጅት የቅድስና ደረጃ ባይሰጣቸውም ሃይማኖታዊ ባሕርይ ያላቸው ናቸው። እንደነዚህ ካሉት መጻሕፍት መካከል በሺንቶ እምነትና በጃፓናውያን ሕይወት ላይ ለብዙ ዘመናት ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ ያሳደሩትን ኮጂኪ እና ኒሆንጂ የተባሉትን መጻሕፍት መጥቀስ ይቻላል። 13ቱ የጥንት የኮንፊሺየስ ጹሑፎችም እንደዚሁ በቻይናውያን ሕይወት ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል። እነዚኞቹ ጹሑፎች በ539 ከዘአበ ባቢሎን በሜዶ ፋርስ እጅ በወደቀችበት ጊዜ በአሥራዎቹ ዕድሜ ይገኝ ነበር በሚባልለት በቻይናዊው ጥበበኛ በኮንፊሽየስ ትምህርቶች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ከየዓይነቱ ተመርጠው የተሰባሰቡ ምንባቦችን የያዘው የኮንፊሺያኒዝም ዋነኛ መጽሐፍ (ሉን ዩ ) በ496 ምዕራፎቹ ውስጥ የኮንፊሽየስ ቃሎች እንደሠፈሩ ይነገራል።

በቅርብ ጊዜ የተጻፉ ሃይማኖታዊ ጽሑፎችም የቅድስና ደረጃ ተሰጥቷቸዋል። አንዳንዶቹ ቀደም ሲል ተቀባይነት ባገኘው ቅዱስ ጽሑፍ ላይ መጨመር የሚገባቸው ናቸው ይባላል። ለምሳሌ የኋለኞቹ ዘመን ቅዱሳን የሆኑት የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አባላት የሞርሞን መጽሐፍ ሞርሞን በተባለ ነቢይ በወርቅ ሳህኖች ላይ የተጻፈ ጽሑፍ እንደሆነ፣ በኋላም ሞሮኒ የተባለው ልጁ እንደቀበረውና ይህ ከሆነ ከ1,400 ዓመታት በኋላ በ19ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አጋማሽ ላይ አንድ መልአክ አግኝቶ መጽሐፉን ለተረጎመው ለጆሴፍ ስሚዝ እንደሰጠው ያምናሉ።

በመጀመሪያ ሳይንስ ኤንድ ሄልዝ በሚል ስያሜ በ1875 ታትሞ የወጣውን በሜሪ ቤከር ኤዲ የተጻፈውን ሳይንስ ኤንድ ሄልዝ ዊዝ ኪ ቱ ዘ ስክሪፕቸርስ የተባለውንም መጽሐፍ የሚመለከቱት በዚሁ መንገድ ነው። እኚህ ሴት ለበርካታ ዓመታት መጽሐፋቸው ወደ ሌሎች ቋንቋዎች እንዳይተረጎም አግደው ቢቆዩም በመጨረሻ አንዳንድ ገደቦችን በማውጣት ይህን አቋማቸውን ለውጠዋል። “ይህ አዲስ እትም የእንግሊዝኛውን ቅጂና ጀርመንኛውን ትርጉም ጎን ለጎን ይዞ ይወጣል፤ በአንደኛው ጎን በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈው የእንግሊዝኛ ቅጂ ሲሰፍር በሌላኛው ጎን ደግሞ የተተረጎመው የጀርመንኛ ቅጂ ይሠፍራል። የእንግሊዝኛው ግልባጭ ለትርጉም ትክክለኛነት ማመሳከሪያ ይሆናል።”​—ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

ሃይማኖታዊ ያልሆኑ መጽሐፎች እንኳ የቅዱስነት ደረጃ አግኝተዋል። ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል የዝግመተ ለውጥንና የኮሚኒዝምን ጽንሰ ሃሳቦች የያዙት በ19ኛውና በ20ኛው መቶ ዘመን እንደ ቻርልስ ዳርዊን፣ ካርል ማርክስና ማኦ ሴቱንግ ባሉ ሰዎች የተጻፉት መጻሕፍት ይገኙበታል። እነዚህ መጻሕፍት በሚልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ዘንድ ከሃይማኖት ጋር የሚተካከል ድጋፍ አግኝተዋል።

ትክክለኛ የሆነ የቅዱሳን ጽሑፎች ስብስብ ማዘጋጀት

አንዳንዶቹ ቅዱሳን ጽሑፎች በቃል እየተነገሩ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የቆዩ ናቸው። በኋላ ግን አንድ የተወሰነ ሃይማኖት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ከተላለፉት ትምህርቶች መካከል ትክክለኛውን ቅዱስ ጽሑፍ (ካኖን) ለይቶ ማውጣት አስፈላጊ እንደሆነ ታመነበት። “ካኖን” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “ቅዱስ መሆናቸው ተቀባይነት ያገኘ መጻሕፍት ስብስብ ወይም ብዙ እውቀትን ያዘሉ ጽሑፎች ዝርዝር” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል።

ቋሚ የሆነና የማይለዋወጥ ካኖን ወይም የቅዱሳን መጻሕፍት ስብስብ ማዘጋጀት በጣም ከባድ እንዲያውም አንዳንዴ ፈጽሞ የማይቻል ሆኗል። ለምሳሌ ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን የቡድሂስት ጽሑፎች በዓለም ላይ ካሉት ሃይማኖታዊ ጽሑፎች ሁሉ የተለየ ባህርይ እንዳላቸው ይገልጻል። ምክንያቱም የትክክለኞቹ ቅዱሳን ጽሑፎች ዝርዝር ወይም ስብስብ የተለያየ ነው። ኢንሳይክሎፒዲያው እንዲህ ይላል:- “እነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ስብስቦች አንዳቸው ከሌላው በእጅጉ ይለያያሉ፤ በሁሉም ኅብረተሰብ ወግና ልማድ ውስጥ የሚገኙት ጽሑፎችም በጣም ጥቂት ናቸው።” በዚህ የተምታታ ሁኔታ የተነሳ ታሪክ “አሥራ ስምንቱ ክፍሎች” ብሎ የሚጠራቸው የቡድሂስት ትምህርቶችና የተለያዩ የእምነት ቡድኖች ተፈጠሩ።

በሌላ በኩል ደግሞ ሂንዱይዝም የራሱን ጽሑፎች ትክክለኛ የቅዱስ ጽሑፍ ክፍል ተደርገው የሚቆጠሩና የተሟላ የቅድስና ደረጃ የማይሰጣቸው ጽሑፎች በማለት ለሁለት ይከፍላቸዋል። የሂንዱ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል ስሩቲ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ትርጓሜውም “በመስማት መማር” ማለት ነው። ይህም ዋነኛ የሆነውን ራእይ፣ ቬዳስንና አፓኒሼድስን የሚያካትት ነው። “ጠለቅ ያለ ሃይማኖታዊ ጥናት” የሚል ትርጉም ያለው ስምርቲ ስሩቲን የሚያብራራና የሚገልጽ ተጨማሪ መጽሐፍ ነው። ሂንዱዎች ስለ ሃይማኖታቸው የሚያውቋቸው አብዛኛዎቹ ነገሮች የተገኙት ከስምርቲ ቢሆንም ለዚህ ጽሑፍ የሚሰጠው ግምት አነስተኛ ነው። ሙሉ በሙሉ ትክክለኛ የቅዱስ ጽሑፉ ክፍል እንደሆነ ተደርጎ አይታይም።

ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎችም የትኞቹ ጽሑፎች ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ተደርገው ሊቆጠሩ እንደሚችሉ መወሰን ተስኗቸዋል። የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና አብዛኛዎቹ በምሥራቅና በሩቅ ምሥራቅ አገሮች ውስጥ ያሉ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያኖች 13 ተጨማሪ ጽሑፎችን በሙሉ ወይም ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ “ዴኦትሮካኖኒካል” ናቸው ብለው ያስባሉ። “ዴኦትሮካኖኒካል” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “ሁለተኛው (ወይም የኋለኛው) ተቀባይነት ያለው ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል” ማለት ነው። ፕሮቴስታንቶች አፖክራይፋ (አዋልድ) ብለው ይጠሯቸዋል። የዚህ ቃል መሠረታዊ ትርጉም “በድብቅ የተያዘ” ማለት ነው። ምክንያቱም በሕዝብ ፊት አይነበቡም ነበር። በዚህም ምክንያት በዛሬው ጊዜ እውነተኝነታቸው አጠራጣሪ ሆኗል። የፕሪንስተን መንፈሳዊ ትምህርት ቤት አስተማሪ ጀምስ ኤች ቻርልስ ዎርዝ እንዲህ ብለዋል:- “ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ተደርገው የሚቆጠሩት ቅዱሳን ጽሑፎች መጀመሪያ በአይሁዶች በኋላም ሥልጣን በነበራቸው ክርስቲያኖች ተሰብስበው አንድ ላይ በተጠቃለሉበት ጊዜ እነዚህ ጽሑፎች አልተካተቱም ነበር። በሰዎች ላይ ያሳድሩት የነበረው ተጽዕኖና የነበራቸው ጠቀሜታ ወዲያውኑ መክሰም ጀመረ።” የትሬንት ምክር ቤት በ1546 ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ናቸው ብሎ እስከ አወጀበት ጊዜ ድረስ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አልነበሩም።

“ቫት ሽክሪፍት፣ ብሊፍት”

“በአፍ ያለ ይረሳል፣ በጽሑፍ ያለ ይወረሳል” ተብሎ ሊተረጎም የሚችለው ይህ የጀርመናውያን ምሳሌ አንድን ሐሳብ በቃል ማስተላለፍ የኋላ ኋላ ችግር እንደሚያመጣ ጎላ አድርጎ ያሳያል። በጣም አስፈላጊ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች ከናካቴው ሊረሱ ይችላሉ። ጥቃቅን ለውጦች በመጀመሪያ ያልነበሩና ያልታሰቡ ሐሳቦችን ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ስለዚህ በጽሑፍ ከሠፈሩት ቅዱሳን ጽሑፎች መካከል መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ መሆኑ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው። እንዲያውም ሙሴ የመጀመሪያውን ክፍል ጽፎ የጨረሰው በ1513 ከዘአበ ነበር።

በአንጻሩ ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን እንደሚለው የቬዳስ ተጨማሪ ክፍል የሆነው፣ ከስምንተኛው እስከ አራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ባለው ጊዜ ውስጥ የተገኘ ነው የሚባለውና በሳንስክሪት ቋንቋ የተዘጋጀው አፓኒሼድስ “በመጀመሪያ በጽሑፍ መልክ የተዘጋጀው በ1656 እዘአ” ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ጽሑፍ ይህን ያህል ዘግይቶ ሊጻፍ የቻለው በቸልተኝነት የተነሣ አይደለም። ሆን ተብሎና ታስቦ የተደረገ ነው። ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- “ቬዳስና ጀግንነትን የሚያወሱ ግጥሞች ከሚያዜሟቸው ትውልዶች ጋር አብረው ያደጉ መዝሙሮች ናቸው፤ ለንባብ እንዲውሉ ሳይሆን በድምፅ እንዲያቀነቅኗቸው የተዘጋጁ ነበሩ።”

እስከ አሁንም ድረስ አንዳንድ ሂንዱዎችና ቡዲስቶች ቅዱስ ጽሑፉ ትልቅ ትርጉም የሚኖረውና ከፍተኛ ጠቀሜታ ሊያስገኝ የሚችለው በቃል ሲነገር ብቻ ነው በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ። ማንትራ ብለው የሚጠሯቸውንና የማዳን ኃይል አላቸው ተብሎ የሚነገርላቸውን ድግምቶች ወይም የሚነበነቡ ቃላት አክብደው ይመለከቷቸዋል። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “አንድ ሰው ማንትራን በትክክለኛው መንገድ በመድገም አማልክቱ በአማኙ ላይ አስማታዊና መንፈሳዊ ኃይል እንዲያፈሱ ማነሣሣት አልፎ ተርፎም ማስገደድ ይችላል፤ እንዲህ ካላደረገ ግን ይህን ኃይል ማግኘት አይችልም።”

የማን ቃል ነው? ለምን ያህል ሰዎችስ?

በመለኮታዊ መንፈስ አመራር እንደተጻፉ የሚናገሩት ወይም በስፋት እንዲሰራጩና በሁሉም ሰው እጅ እንዲገቡ የሚሹት ሁሉም ቅዱሳን ጽሑፎች አይደሉም። ለምሳሌ የሂንዱዎች መጽሐፍ የሆነው አፓኒሼድስ (“በአጠገብ የሚቀመጥ” ማለት ነው) ይህን መጠሪያውን ሊያገኝ የቻለው የሃይማኖት አስተማሪዎች ምሥጢራዊ መሠረተ ትምህርቶችን ‘በአጠገባቸው ለሚቀመጡ’ ማለትም በጣም ለሚቀርቧቸውና ወዳጃቸው ለሆኑ ተማሪዎች ብቻ ይገልጡ ስለነበረ ነው። “አፓኒሼድስ የሚለው ቃል አንድ በምሥጢር የተያዘን ነገር ያመለክታል፤” በማለት ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን ይገልጻል። አክሎም “እንዲያውም እነዚህ ትምህርቶች ለጠቅላላው ሕዝብ ታስበው የተዘጋጁ አይደሉም ሲል አፓኒሼድስ በግልጽ ይናገራል። . . . [ከዚህ ይልቅ] ወደ ተወሰኑ ሰዎች ጆሮ እንዲደርሱ ብቻ የተዘጋጁ ናቸው” ብሏል።

የአረብኛውም ቁርዓን እንደዚሁ ለአረቦች ብቻ ታስቦ በመሐመድ የተዘጋጀ መጽሐፍ ነው። በመጽሐፉ ውስጥ የሚናገረው የሕዝቦች ሁሉ ፈጣሪ የሆነው አምላክ ብቻ ሆኖ ሳለ ለአረቦች ብቻ የተዘጋጀ መጽሐፍ መሆኑ የሚያስገርም ነው። ቁርዓንን ወደ ሌሎች ቋንቋዎች መተርጎም ተገቢ አይደለም ይባላል። በዚህም ምክንያት በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ መጠቀምና በሕዝብ ፊት ማንበብ የሚቻለው በአረብኛ የተጻፈውን ብቻ ነው። ይህም በ1960ዎቹ ዓመታት ከተደረገው ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባዔ በፊት በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሥነ ሥርዓቶች ላይ መጠቀም የሚቻለው በላቲን በተጻፈው ቅዱስ ጽሑፍ ብቻ እንደነበረ ያስታውሰናል።

በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ መልእክቱ ለየትኛውም ሕዝብ የተወሰነ እንዳልሆነ በግልጽ ይናገራል። ይህም ‘የእግዚአብሔር ቃል እንጂ የሰው ቃል’ አይደለም ከሚለው አባባል ጋር ይስማማል። (1 ተሰሎንቄ 2:13) መጽሐፍ ቅዱስን የሚደግፉ ሰዎች እያንዳንዱ ሰው ከፈጣሪው የጥበብ ቃላት ጥቅም የማግኘት እኩል መብት እንዳለው በማመን በስፋት ለማሰራጨት ጥረት አድርገዋል። ስለዚህም በ1987 ማብቂያ ላይ ቢያንስ በከፊል በ1,884 ቋንቋዎች ወይም ቀበልኛ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። ዘ ቡክ ኦቭ ሊስትስ የተባለው መጽሐፍ በ1977 በግምት 2,458 ሚልዮን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች እንደተሰራጩና 3,000 ሚልዮን ቅጂዎች ተሰራጭተዋል ማለቱ ይበልጥ ትክክል እንደሚሆን ገልጿል።

ሃይማኖቶች በመጽሐፎቻቸው ሲመዘኑ

በ1933 እንግሊዛዊው ፈላስፋ አልፍረድ ዋይትሄድ “የትኛውም ሃይማኖት ከተከታዮቹ ተነጥሎ ሊታይ አይችልም” በማለት ጽፈዋል። አንድ ሃይማኖት የሚያፈራቸውን ሰዎች በመመልከት እውነተኛ ነው ወይም የሐሰት ሃይማኖት ነው፣ ጥሩ ወይም መጥፎ ሃይማኖት ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። የአንድ ሃይማኖት ተከታዮች ባሕርይ የሚያምኑባቸውን መጻሕፍት ሥራ ላይ በማዋላቸው የሚመካ ቢሆንም የሚያምኑበት መጽሐፍ ባሕርያቸውን በመቅረጽ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አያጠራጥርም።

ቅዱሳን ጽሑፎች ተገቢውን መመሪያ መስጠት ይኖርባቸዋል። ልክ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ሰው ሁሉ “ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ . . . ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” የሚጠቅሙ መሆን ይኖርባቸዋል።​—2 ጢሞቴዎስ 3:16,17

በብዙ ቅጂ የተሰራጩት ሃይማኖታዊ መጻሕፍት እንዴት ናቸው? ለምሳሌ የሂንዱና የቡድሂስት መጽሐፎች አንባቢዎቻቸው የሕይወትን ውጣ ውረድ መቋቋም እንዲችሉ ምን ያህል አስታጥቀዋቸዋል? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት እንድንችል ታሪክ ጸሐፊው ዱራንት የዚህችን አገር ያህል “ሃይማኖት ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረበት ወይም እጅግ አስፈላጊ የሆነበት አንድም ሌላ አገር የለም” በማለት ወደ ተናገሩላት ወደ ሕንድ ፊታችንን ማቅናት ይኖርብናል። በሚቀጥሉት እትሞቻችን ላይ የሚወጡት ሁለት ርዕሶች ትኩረት የሚስበውን ይህን ርዕሰ ጉዳይ የሚያብራሩ ትምህርቶችን ይዘው ይወጣሉ፤ የመጀመሪያው አርዕስት “ሂንዱይዝም—ስምህ ችሎ መኖር ነው” የሚል ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ይህ ርዕስ የሚያብራራው ራሳቸውን መጻሕፍቱን ሲሆን ወደፊት የሚወጡት ርዕሶች በመጽሐፎቹ ስለሚጠቀሙት ሃይማኖቶች ጠለቅ ያለ ማብራሪያ ይሰጣሉ።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የስማቸው ትርጉም

ቡድሂዝም:- ትሪፒታካ፤ “ሦስት ቅርጫቶች [ስብስቦች]” የሚል ትርጉም ካለው የሳንስክሪት ቃል የመጣ

ክርስትና:- መጽሐፍ ቅዱስ፤ በእንግሊዝኛ “ትንንሽ መጽሐፎች” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል የመጣ

ኮንፊሺያኒዝም:- ሉን ዩ፤ “የሐሳብ ልውውጥ” የሚል ትርጉም ያለው የቻይና ቃል

ሂንዱይዝም:- ቬዳ፤ “እውቀት” የሚል ትርጉም ካለው የሳንስክሪት ቃል የመጣ

እስልምና:- ቁርዓን፤ “ማንበብ፣ መድገም” የሚል ትርጉም ካለው የአረብኛ ቃል የመጣ

ይሁዲነት:- ታልሙድ፤ “ማጥናት፣ መማር” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ

ሺንቶ:- ኮጂኪ እና ኒሆንጊ፤ “የጥንታዊ ጉዳዮች መዝገብ” እና “የጃፓን መዋዕለ ዜናዎች” የሚሉ ትርጉሞች ያሏቸው የጃፓናውያን ቃሎች

ታኦይዝም:- ታኦ–ቴ ቺንግ፤ “የኃይልን አካሄድ የሚገልጽ ጽሑፍ” የሚል ትርጉም ያለው የቻይና ቃል

ዞራስተራኒዝም:- አቬስታ፤ አቬስታን በተባለው መጽሐፉ በተጻፈበት የኢራን የጠፋ ቋንቋ የተሰየመ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ያላቸው መጠን ሲወዳደር

በብዙ ቅጂዎች ከተሰራጩት ሃይማኖታዊ መጽሐፎች መካከል አንዳንዶቹ በጣም ትልልቅ ናቸው። ከዚህ የሚለየው ቁርዓን ብቻ ሲሆን መጠኑ የመጽሐፍ ቅዱስን አንድ አራተኛ ያህላል። ሳማሂታስ ተብሎ የሚጠራው አንዱ የሂንዱ ቅዱሳን ጽሑፎች ስብስብ ብቻ እንኳን ከአንድ ሚልዮን ስንኞች በላይ እንደያዘ ይገመታል። ከዚህ ጋር ሲነጻጸር ኪንግ ጀምስ ቨርሽን የያዘው 31,102 ጥቅሶችን ብቻ ነው። ኪንግ ጀምስ 773,746 ቃላትን የያዘ ሲሆን የባቢሎናውያን ታልሙድ ግን 2.5 ሚልዮን የሚሆኑ ቃላትን ይዟል። ትክክለኛ የቅዱሳን ጽሑፎች ስብስብ ነው የሚባለው የቻይናው የቡድሂስት መጽሐፍ ከዚህ በጣም የሚበልጥ መጠን ያለው ሲሆን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ገጾች አሉት።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በብዙ ቅጂዎች ከተሰራጩ ሃይማኖታዊ ጽሑፎች መካከል መጽሐፍ ቅዱስና ቁርዓን ይገኙበታል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ