የሃይማኖት የወደፊቱ ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንጻር ሲታይ
ክፍል 7:- 1500 ከዘአበ ገደማ ጀምሮ—ሂንዱይዝም —ስምህ ችሎ መኖር ነው
“ ማንኛውም ሰው የራሱን ሃይማኖት መከተል ይኖርበታል።”—ራማክሪሽና፣ የ19ኛው መቶ ዘመን የሂንዱ ለውጥ አራማጅ
ሌላውን ሳይቃወሙ ተቻችሎ መኖር እንደ በጎ ባሕርይ ተደርጎ ይታያል። ያም ሆነ ይህ ቃሉ ሂንዱይዝም ተብሎ የሚጠራውን ግዙፉን የዓለም ሃይማኖት በደንብ ይገልጸዋል። በ1985 በዓለም ላይ ካለው ሕዝብ መካከል 13.5 በመቶዎቹ ይኸውም ወደ 650,000,000 የሚጠጉ ሰዎች ሂንዱዎች ነን ብለው እንደተናገሩ ተዘግቧል።
ሂንዱይዝም “ብዙ የተለያዩ ክፍሎችን ያቀፈ የተወሳሰበ ብሔራዊ ሃይማኖት” እና “በህንድ ውስጥ የሚገኙ ሃይማኖቶች ሁሉ የጋራ መጠሪያ” ተብሎ ሲጠራ ቆይቷል። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ነገሩን ለማብራራት በትንሹም ቢሆን የሚለው ነገር ይኖረዋል። እንዲህ ይላል:- “በዚህም ሆነ በዚያ ለሂንዱይዝም አንድ የተወሰነ ፍቺ ለመስጠት የተደረገው ሙከራ በአብዛኛው አጥጋቢ ሆኖ አልተገኘም። ምክንያቱም ሂንዱ የሆኑትን ጨምሮ የህንድ ታላላቅ የሂንዱይዝም ምሁራን ጎላ አድርገው የገለጹት የሃይማኖቱን የተለያዩ ክፍሎች ነው።”
ያም ሆነ ይህ ሂንዱይዝም የቆየ ሃይማኖት ነው። ይህ ሃይማኖት የተጀመረው በአሁኑ ጊዜ ፓኪስታን ውስጥ በሚገኘው በኢንደስ ወንዝ ሸለቆ ነው። አርያን በመባል የሚታወቁት የህንድና የአውሮፓ ቅልቅል ህዝቦች በ1500 ከዘአበ ገደማ ወደዚህ ስፍራ መጡ። አንዳንድ ጽሑፎችን እንደ ቅዱስ እውቀት (ቬዳ ) አድርገው ይመለከቱ ስለነበረ ሃይማኖታቸው ቬዲዝም ተባለ። ይህ ሃይማኖት ለአሁኖቹ ኢራናውያን የቀድሞ አባቶች ከነበሩት ሰዎች ሃይማኖት የመነጩ አንዳንድ ትምህርቶችን ያቀፈ ነው። ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን ኤንድ ኤቲክስ “በባቢሎናውያንና በጥንቶቹ ሂንዱዎች ባህል መካከል ስላሉት ብዙ ዓይነት አንድነቶች” እንደሚናገረው ከሆነ የባቢሎናውያን ሃይማኖትም ተጽዕኖ ያሳደረበት ሁኔታ አለ። የመጀመሪያዎቹ ሰፋሪዎች ሌሎች ሃይማኖቶች ተጽዕኖ ባሳደሩባቸው ቁጥር እምነቶችንና ልማዶችን እየተቀበሉም ሆነ እየተዉ ሃይማኖታቸውን ከሌሎች ሃይማኖቶች በመነጩት በእነዚህ ትምህርቶች ላይ አነጹ። ስለዚህም ሂንዱይዝም ከሌሎች ምንጮች የተገኙ ብዙ ትምህርቶችን በየጊዜው በማከል እያደገና እየሰፋ የመጣ ሃይማኖት ነው።
ትምህርቶቹና ልማዶቹ
ለሂንዱ ህብረተሰባዊ ክፍሎች ሥርዓት መሠረት ለመጣል አሪያኖች ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የመጀመሪያዎቹ አራቱ ህብረተሰባዊ ክፍሎች ተበራክተው ከጊዜ በኋላ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ንዑሳን ክፍሎችን ያቀፉ ሆኑ። እነዚህ አራት የሂንዱ ህብረተሰባዊ ክፍሎች ከመጀመሪያው የሰው ዘሮች አባት ከፑሩሳ የተለያዩ የአካል ክፍሎች የተገኙ ናቸው ተብሎ ይነገራል፤ ይህም የሳንስክሪት ቃል ሲሆን ትርጓሜውም “ሰው” ወይም “ወንድ” ማለት ነው።
ከአፉ የተወለዱ ናቸው የሚባሉት ብራህማዎች ሃይማኖታዊ መሪዎች ነበሩ። ከክንዶቹ የተወለዱት ክሻትሪያዎች የውትድርናና የፖለቲካ መሪዎች ናቸው። ከጭኑ የተወለዱት ቬሲያስ ገበሬዎች፣ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ነጋዴዎች ናቸው። ከእግሩ የተወለዱት ሱድራዎች ደግሞ ባሪያዎች ናቸው። “ተራ ሰዎች” የሚባሉት ደግሞ ሥራቸውና የአኗኗር ዘይቤያቸው በሃይማኖታዊ ዓይን ሲታይ ንጹህ ካልሆኑ ድርጊቶች ጋር የተጠላለፈ ዝቅተኛ ደረጃ የሚሰጣቸው የህብረተሰቡ ክፍሎች ናቸው። ምንም እንኳን ህንድና ፓኪስታን ከሂንዱ ህብረተሰባዊ ክፍሎች ሥርዓት መካከል በጣም ጎጂ የሆኑትን ከ40 ዓመታት በፊት በሕግ ቢያግዱም ርዝራዦቻቸው አሁንም ገና አልጠፉም።
በጊዜው የእንስሳት መሥዋዕት በአምልኮው ውስጥ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። ቄሶች የሚያስፈልጉትን ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ለማከናወን እንዲችሉ እነዚህ መሥዋዕቶች ያስፈልጉ ነበር። ብራህማዎች እያየሉ ስለመጡ ብራህማኒዝም የሚባል የሃይማኖቱ ቅርንጫፍ ብቅ አለ። “ቄሶቹ ከአማልክቱ የበለጠ ይፈሩና ይከበሩ ነበር” በማለት ቲ ደብሊው ኦርጋን ይናገራሉ፤ “ምክንያቱም ቄሶቹ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በመለወጥ ብቻ ጠላቶቻቸውን ሊያጠፉ ስለሚችሉ ነው።” መሥዋዕት የማቅረቡ ሥርዓት ይበልጥ እየተወሳሰበ ሲመጣ የብህትውናን ኑሮ ወይም ሥጋን እየበደሉ መኖርን የሚያጠናክር ዝንባሌ መንሰራፋት ጀመረ።
ሳምሳራ መሠረታዊ የሆነ እምነት ነበር። የዚህ እምነት ፅንሰ ሐሳብ የቀረበው የሂንዱ ቅዱስ ጽሑፍ ስብስብ በሆነው በአፓኒሼድስ ውስጥ ነው፤ ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በመጀመሪያው ሺህ ዓመት አጋማሽ ከዘአበ ሳይሆን አይቀርም። ከሞትና በሲኦል ወይም በመንግሥተ ሰማያት ውስጥ ከሚደረግ የመሸጋገሪያ ወቅት ቆይታ በኋላ ሰዎች ቀድሞ ከነበራቸው ሰብአዊ አካል የላቀ ወይም ያነሰ አካል ይዘው እንስሳ ወይም ሰው ሆነው ይወለዳሉ ብለው ያስተምራሉ፤ ይህም በካራማ ሕግ ላይ የተመሠረተ ነው። የሕይወት ዓላማ የሞክሻን ግብ ዳር ማድረስ ነው፤ ይህም ከማያቋርጠው የመወለድ፣ የመሞትና እንደገና መወለድ የሕይወት ዑደት ነፃ መሆን እንዲሁም ብራህማ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ዋነኛው የሥርዓቱ ምንጭ መጠቃለል ማለት ነው።
ቬዲዝም ብዙ አማልክት አሉት። ኮንሰፕትስ ኦቭ ኢንዲያን ፊሎዞፊ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ከሆነ ግን ተከታዮቹ ይህን አጥጋቢ ሆኖ አላገኙትም። ስለዚህም “ራስ የሆነ አንድ አምላክ አለ ወደሚለው ፅንሰ ሐሳብ ቀስ በቀስ አዘነበሉ። . . . ሃሳባዊ የሆነ አምላክ በአእምሮ ውስጥ [ለ]መፍጠር . . . አንዱ መንገድ የቀድሞቹን አማልክት በሙሉ በአንድ መጠቅለል ነው።” በዚህ ምክንያት ብራህማ በተለያዩ አማልክት የተወከለ ነገር ግን ምንም ዓይነት ባህሪያት የሌሉት አንድ አካል ያልሆነ አምላክ ሆነ።
የሞክሻን ግብ ዳር ለማድረስ ያለው ፍላጎት ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት “በሁሉም የሂንዱ ትምህርቶች ውስጥ ግልጽ ባልሆነ መንገድ የሚሽከረከረው . . . የሕይወት ጥላቻ” ብለው በገለጹት ነገር ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ ግልጽ ያልሆነና አፍራሽ የሆነ አመለካከት የሚከተሉትን ጥያቄዎች በሚያቀርበው በሜትሪ አፓኒሼድስ ላይ በደንብ ተገልጿል:- “በዚህ አካል ውስጥ በፍላጎት፣ በቁጣ፣ በመጎምጀት፣ በከንቱ ስሜት፣ በፍርሃት፣ በትካዜ፣ በቅናት፣ ጠቃሚ ከሆነው ነገር በመራቅ፣ ጠቃሚ ወዳልሆነው ነገር በመቅረብ፣ በረሃብ፣ በጥማት፣ በእርጅና፣ በሞት፣ በበሽታ፣ በሐዘንና በመሳሰሉት ነገሮች የሚጠቃው አካል የትኛው ነው? ፍላጎቶችን ማርካት ጥሩነቱ ምን ላይ ነው?”
ይህን የማያስደስት ሁኔታ ማስወገድ የሚቻልበት መንገድ በፑራናስ ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል። እነዚህ ተከታታይ ጽሑፎች በአንድ ላይ የተቀነባበሩት በመጀመሪያዎቹ መቶ ዓመታት እዘአ ሳይሆን አይቀርም። “ጥንታዊ ታሪኮች” የሚል ትርጉም ያላቸው እነዚህ ጽሑፎች በሰፊው ጥቅም ላይ ውለው ነበር። የተራ ሰው ቅዱሳን ጽሑፎች የሚል መጠሪያም አግኝተዋል። ጋሩዳ ፑራና እንዲህ ሲል ይናገራል:- “እውነተኛ ደስታ ማግኘት ሁሉም ስሜቶች በመጥፋታቸው ላይ የተመካ ነው። . . . የመውደድ ስሜት እስካለ ድረስ ኀዘን ይኖራል። . . . የመውደድን ስሜት ካስወገድክ ደስተኛ ትሆናለህ።” የሚያሳዝነው ግን ይህ መፍትሄ የደስታ ማጣትን ያህል የሚቀፍ መሆኑ ነው። እንዲሁ ለማጽናኛ ይሆናል ተብሎ የታለመ ነው።
ከዚህ በፊት የነበረውና “የጌታ መዝሙር” የሚል ትርጉም ያለው አንዳንዴም “በህንድ ውስጥ ከተጻፉት መጽሐፎች ሁሉ የላቀ ጠቀሜታ አለው” ተብሎ የሚጠራው ባጋቫድ ጊታ ነፃነት የሚገኝባቸውን ሦስት መንገዶች ይጠቁማል። ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችንና ማኅበራዊ ግዴታዎችን ማከናወንን ጠበቅ አድርጎ የሚገልጸው “የሥራ መንገድ”፣ ማሰላሰልንና ዮጋን የሚያጠቃልለው “የእውቀት መንገድ” እና ለየግል አምላካቸው ያደሩ መሆንን የሚያካትተው “ራስን የመወሰን መንገድ” ናቸው። ባጋቫድ ጊታ ከሕዝበ ክርስትና “አዲስ ኪዳን” ጋር ሲመሳሰል ቆይቷል። አብዛኛዎቹ ህንዶች አንዳንዶቹን ጥቅሶች በቃላቸው ያውቋቸዋል። ብዙዎቹ በቃል የሚያውቋቸውን ክፍሎች በየቀኑ ያዜሟቸዋል።
እርግጥ ባጋቫድ ጊታ ማሃባራታ ተብሎ የሚጠራው የጀግንነት ግጥም አነስተኛ ክፍል ብቻ ነው። ይህ ጽሑፍ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ጥቅሶችን የያዘ ነው። ይህም በዓለም ላይ ከሚገኙት ግጥሞች ሁሉ በርዝመቱ የላቀ እንዲሆን አስችሎታል። በመጨረሻም ባጋቫድ ጊታን በማሃባራታ ውስጥ በማካተት (በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ሳይሆን አይቀርም) ሂንዱይዝም ከቬዲዝምና ከብራህማኒዝም ተለይቶ ራሱን የቻለ ሃይማኖት ሆነ።
የማያቋርጥ ተሃድሶ
ከመጀመሪያው ጀምሮ ሂንዱይዝም ያለማቋረጥ በሚካሄድ የተሃድሶ እንቅስቃሴ ተለይቶ የታወቀ ሆነ። ከተሃድሶ አራማጆቹ መካከል የቡድሂዝም መሥራች የሆነው ሲድሃርታ ጉታማና የጃኒዝም መሥራች የሆነው ቫርዳሃማና ማሃቪራ ዋነኞቹ ነበሩ።
ማሃቪራ በጂናዎች (ድል አድራጊዎች) መሥመር 24ኛው ሰው እሱ እንደሆነ አድርጎ ራሱን ይቆጥር ነበር። ጃኒዝም የተመሠረተው በእነዚህ ሰዎች ሕይወት ላይ ነው። ይህ ሃይማኖት ከሂንዱይዝም የሚለየው ፈጣሪን የማይቀበል በመሆኑ ነው። ዓለም ሁልጊዜ እንዳለ ይኖራል ሲል ያስተምራል። ለአሂምሳ መሠረተ ትምህርት ለየት ያለ ትኩረት ይሰጣል። በ20ኛው መቶ ዘመን የህንድ መሪ የነበሩት ሞሃንዳስ ጋንዲ ህንድ ከቅኝ አገዛዝ እንድትወጣ በሰላማዊ ሁኔታ በታገሉበት ወቅት ይህን ሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርት በፖለቲካዊ መንገድ ተጠቅመውበታል።
ጃኒዝም እንደሚለው ከሆነ ትክክለኛ እምነት፣ ትክክለኛ እውቀትና ትክክለኛ ሥነ ምግባር ዮጋን በተግባር ከማዋል ጋር ሲጣመሩ ወደ ነጻነት ይመራሉ። የዚያኑ ያህል ደግሞ ማንኛውም ነገር የአመለካከት ጉዳይ ነው ሲል አበክሮ ይገልጻል። በመሆኑም ትክክል የሆነውንና ስህተት የሆነውን ለይተው ለሚያሳውቁና ቋሚ ለሆኑ መመሪያዎች ቦታ አይሰጥም። ይህም ከጃኒዝም የመነጨውን ሁሉንም ዓይነት እምነትና አመለካከት ሳይቃወሙ የማለፍን የሂንዱይዝም ዝንባሌ ጎላ አድርጎ ያሳያል።
ወደ 2,000 የሚጠጉ ዓመታት ካለፉ በኋላ በ15ኛው መቶ ዘመን ሌላ የለውጥ አራማጅ ተነሳ። ይህ ሰው ናናክ የሚባል ሲሆን በሂንዱዎችም ሆነ በእስላሞች ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሃይማኖት ለማቀናበር ሞክሯል። በውጤቱም ሲኪዝም የተባለ ሃይማኖት ተመሠረተ። “ሲክ” “ደቀ መዝሙር” የሚል ትርጉም ካለው የሳንስክሪት ቃል የመጣ ነው። ናናክ ከአሥሩ የሂንዱይዝም የሃይማኖት መሪዎች አንዱ ነው፤ ካሃልሳ (ንጹህ ሰዎች) ተብሎ የሚታወቀው በ1699 የተቋቋመውና ለአንድ ዓላማ የቆመው ቡድን አሥረኛ አባል ነበር። የሂንዱ ህብረተሰባዊ ክፍሎችን ልዩነት ለማጥፋትና የእምነታቸው ወታደሮች መሆናቸውን ለማጉላት አባላቱ ሲንግ (አንበሳ) የሚል እንደ ቤተሰብ ስም ሆኖ የሚያገለግል የጋራ መጠሪያ ይሰጣቸው ነበር። አምስቱን በከ የሚጀምሩ መመሪያዎች በሥራ እንዲያውሉ ይጠበቅባቸው ነበር:- ጸጉራቸውንና ጺማቸውን አለመቆረጥ (ኬሽ )፤ በጨርቅ የሚጠመጥሙትን ጸጉራቸውን በትልቅ የጸጉር ማስያዣ እንዲያስይዙት (ካንጋ )፤ ቁምጣ እንዲለብሱ (ካችስ )፣ ይህን የሚያደርጉት ከረጃጅም ሱሪዎች ሥር ሊሆን ይችላል፤ ሻምላ እንዲይዙ (ኪርፓን )፤ እና የብረት አንባር እንዲያደርጉ (ካራ )። የቡድሂዝም የሃይማኖት መሪዎች መስመር አሥር ላይ ሲደርስ አብቅቷል። የሲኪዝም ቅዱስ መጽሐፍ የሆነው ጉሩ ግራንት ሳሂብ ቦታውን ወስዷል። የተዘጋጀው በ1604 ሲሆን እንደገና ተሻሽሎ የታተመው አንድ መቶ ዘመን ካለፈ በኋላ ነበር።a
በ19ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ራማክሪሽና የሚባል የካልካታ ቄስ የተሻሉ ናቸው ብሎ የሚያስባቸውን የምዕራባውያን ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ከሂንዱይዝም ትምህርቶች ጋር ለመቀላቀል ሞክሯል። ውኃ እንኳን በተለያዩ ቋንቋዎች የተለያዩ ስሞች አሉት፤ ልክ እንደዚሁም “ሳት–ቺታናንዳን፣ የማሰብ ችሎታ ያለውን ዘላለማዊውንና ደስተኛውን አካል አንዳንዶች አምላክ፣ አንዳንዶች አላህ፣ አንዳንዶች ይሖዋ፣ አንዳንዶች ሃሪ ሌሎች ደግሞ ብራህማን ብለው ይጠሩታል” በማለት ይከራከራል። ሌላው ቀርቶ “አንድ ሰው በመሰላል ወይም በሸምበቆ ወይም በደረጃዎች ወይም በገመድ ተጠቅሞ ወደ አንድ ቤት ጣራ መውጣት እንደሚችል ሁሉ አምላክም የሚቀረብባቸው መንገዶች እንደዚሁ የተለያዩ ናቸው። . . . የተለያዩ እምነቶች አሉ፤ ነገር ግን ሁሉም ሁሉን ቻይ ወደሆነው አካል የሚያደርሱ የተለያዩ መንገዶች ናቸው።”
ይህን የመሰለው ማንኛውንም ዓይነት እምነትና አመለካከት የመቀበል ዝንባሌ በሂንዱ አምልኮ ውስጥ የተለያዩ ለውጦች ማድረግ እንዲቻል ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ይህም አንዳንድ የእምነት ክፍሎች የአምልኮ ሥርዓታቸውን በአብዛኛው ወደ ብራህማ (ብራህማኒዝም)፣ ሌሎች ወደ ቪሽኑ (ቬሽናቪዝም)፣ ሌሎች ደግሞ ወደ ሲቫ (ሴቪዝም) እንዲለውጡ በር ከፍቶላቸዋል። እያንዳንዳቸው በራሳቸው ዘይቤ ሂንዱይዝምን እንዲሰብኩ ባህላዊ ሂንዱይዝምን፣ ሻክቲዝምንና ታንተሪዝምን ፈቅዷል። ለምሳሌ ታንተሪዝም የጎሳና ባህላዊ ልማዶችን የሚያካትት ሲሆን በጥንቱ የሂንዱይዝም ታሪክ ውስጥ ይካሄድ የነበረውን የእንስት አምላክ አምልኮን ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ህንዶች አገራቸውን “ህንድ እናታችን” ብለው ይጠሯታል፤ ይህም ባራት ማ በተባለችው አምላክ የተወከለ ነው።
ሁሉንም እምነቶችና አመለካከቶች መቀበል ጥሩ ነው ወይስ መጥፎ?
“ሂንዱይዝም አዳዲስ ትምህርቶችን መቀበል የሚችል መሆኑን ያለማቋረጥ አረጋግጧል” በማለት የሃይማኖት ሊቅና ሃይማኖትን በማነጻጸር ለሚካሄድ ጥናት የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ የሆኑት ብሪታኒያዊው ጄኦፍሬይ ፓሪንደር ጽፈዋል። አክለውም “ይህ የተለያዩ እምነቶችን አንድ ላይ የመቀላቀል ወይም የመደባለቅ ልማድ በዛሬው የሂንዱ ትምህርት ውስጥ የተለመደ ነገር ሳይሆን አይቀርም” ብለዋል። ብዙ ሰዎች ‘ለአንተ ትክክል መስሎ በታየህ መንገድ አምላክን አገልግለው’ ከሚለው ሁሉንም እምነትና አመለካከት ከሚቀበለው የሂንዱ ፍልስፍና ጋር የሚስማሙ ይመስላል።
ይሁን እንጂ “ሁሉንም እምነቶች በአንድ ዓይን ማየት ጥሩውንና መጥፎውን መለየት እንዲሳን” ሊያደርግ እንደሚችል ፓሪንደር ጠቁመዋል። ሃይማኖት ጥሩም ሆነ መጥፎ ሊሆን እንደሚችል ይበልጥ ግልጽ እየሆነ አልመጣምን? የአንድን መጥፎ ሃይማኖት ትምህርቶች ወደ ራስ ሃይማኖት መቀላቀሉ ጥሩነቱ ምኑ ላይ ነው?
ዛሬ ብዙ ሰዎች በሃይማኖታቸው ላይ ቅሬታ አላቸው። ሁለት ሺህ ዓመታት ተኩል ከሚያክሉ ጊዜያት በፊት ይኖር የነበረውና ክሻትሪያ የሚባለው የሂንዱ ህብረተሰባዊ አመራር ክፍል አካል የነበረ አንድ ሰው የነበረው ሁኔታም ከዚህ የተለየ አልነበረም። ሂንዱይዝም የዚህን ሰው ጥያቄዎች መመለስ አልቻለም። ለጥያቄዎቹ መልስ የሚሆኑ ማብራሪያዎችን ይፈልግ ነበር። በሚቀጥለው እትማችን የሚወጣው “ነጻነትን ያስገኛል ተብሎ ተስፋ የተደረገበት የእውቀት ጮራ” የሚለው ርዕስ ይበልጥ የሚነግረን ነገር ይኖረዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በ1985 በ5 የተለያዩ አገሮች ውስጥ 3,300,300 የጃኒዝም ተከታዮች ይኖሩ እንደነበረ ታውቋል። በ19 አገሮች ውስጥ ደግሞ 16,000,000 የሲኪዝም ተከታዮች ይኖሩ ነበር።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ተገርመህ ይሆናል
ሂንዱዎች ሳምሳራን ምን ብለው ይገልጹታል? ባጋቫድ ጊታ እንዲህ ይላል:- “አንድ ሰው ያረጀ ልብሱን ጥሎ አዲስ ልብስ እንደሚለብስ ሁሉ በአካል ውስጥ የምትኖረዋ የማትሞተዋ ነፍስም እንደዚሁ ያረጁ አካሎችን ትታ አዲስ በሆኑ አካሎች ውስጥ መኖር ትጀምራለች።” ጋሩዳ ፑራና እንዲህ ሲል ያብራራል:- “ይህ ክንውን አንድ አካል ወደ ሕይወት ከመምጣቱ በፊት በቀጣዩ ሕይወት ውስጥ የሚኖረውን ተፈጥሯዊ ሁኔታ የሚወስን ሥራ ነው . . . አንድ ሰው በሕይወቱ ሊያገኘው የሚችለው ነገር አስቀድሞ የተወሰነለትን ነገር ነው፤ አምላክ እንኳን ሊለውጠው የሚችለው ነገር አይደለም።” ማርካንዴያ ፑራና :- “ብራህማና፣ ክሻትሪያ፣ ቬስያና ሱድራ ሆኜ ተወልጃለሁ፤ አውሬ፣ ትል፣ አጋዘንና ወፍ ሆኜም ተወልጃለሁ” ብሎ የሚናገርን ሰው በመጥቀስ ሁኔታውን በምሳሌ ያስረዳል።
ሂንዱዎች ላሞች ቅዱስ ናቸው ብለው ያምናሉን? ሪግ–ቬዳም ሆነ አቬስታ ላሞች “መገደል የሌለባቸው እንስሳት” ናቸው ይላሉ። ይሁን እንጂ ይህ ሃሳብ አንድ ሕይወት ያለው አካል ከሞተ በኋላ እንደገና ሕያው ይሆናል በሚለው እምነት ላይ ሳይሆን ቋሚ መመሪያ በሆነው በአሂምሳ ላይ የተመረኮዘ ይመስላል። ይሁን እንጂ ማርካንዴያ ፑራና ይህን ሕግ አለመጠበቅ የሚያስከትለው መዘዝ ቀላል አለመሆኑን ሲያመለክት “አንድ ላም የገደለ ሰው ለሦስት ተከታታይ ጊዜያት በተወለደ ቁጥር ወደ ሲኦል ይወርዳል” ይላል።
ሂንዱዎች ስለ ጋንጂዝ ወንዝ ምን ይላሉ? “በዚህ ወንዝ ውኃ በመታጠብ የነጹ ቅዱሳን ሰዎችና በሙሉ ነፍሳቸው ለኬሳቫ [ቪሽኑ] ያደሩ ሰዎች የመጨረሻውን ነጻነት ያገኛሉ። ሰዎች ሁሉ የቅዱሱን ወንዝ ፈሳሽ ድምፅ ሲሰሙ፣ ሲመኙት፣ ሲያዩት፣ ሲነኩት፣ ሲታጠቡበት ወይም የውዳሴ መዝሙር ሲያዜሙለት ከዕለት ወደ ዕለት እየነጹ ይሄዳሉ። ሌላው ቀርቶ በአንድ መቶ ዮያናዎች [1,440 ኪሎ ሜትሮች] ርቀት ላይ የሚኖሩ ‘ጋንጋና ጋንጋ’ እያሉ የሚጮኹ ሰዎች እንኳን ቀደም ሲል ሦስት ጊዜ ተወልደው ባሳለፉዋቸው የሕይወት ዘመኖች ከሠሯቸው ኃጢአቶች ነጻ ይሆናሉ።”—ዘ ቪሽኑ ፑራና
ለሂንዱ አምላክ ለክሪሽና ራሳቸውን የወሰኑ ሰዎች እነማን ናቸው? የክሪሽና አስተሳሰብ ዓለም አቀፋዊ ማኅበር አባላት ናቸው። የሚስዮናዊነት መልክ ያለው የሂንዱይዝም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ነው። የእምነት መሥራች ሟቹ ኤ ሲ ባክቲቭዳንታ ስዋሚ ፕራቡፓዳ መልእክቱን በ1965 ለዩናይትድ ስቴትስ አድርሷል። ከሂንዱይዝም የብህትውና ኑሮ እምነት ውስጥ አንዳንድ ትምህርቶችን የያዘ ሲሆን ክሪሽና በተባለው አምላክ አምልኮ ላይ ያተኮረ ነው። ሄር ክሪሽና ማንትራን መድገም እንደሚገባ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ባክቲቭዳንታ የአምላክን ስም መጥራቱ ብቻ ለመዳን በቂ ነው የሚል እምነት ነበረው።