የሃይማኖት የወደፊቱ ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንጻር ሲታይ
ክፍል 10:- ከ537 ከዘአበ ጀምሮ አሁንም መሲሕን ይጠብቃሉ
“የወደፊቱ ጊዜ ምንም ዓይነት የተስፋ ፍንጭ ካላሳየ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት መፈክር ብቻ ሆኖ ይቀራል”—ጆን ኤፍ ኬኔዲ 35ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዘዳንት
የሰባ ዓመት የባቢሎን ግዞት ዘመን አብቅቷል። ባቢሎንን ድል ያደረገው የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ አይሁዳውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ፈቅዷል። ወደ ተስፋይቱ ምድር ከተመለሱ በኋላ ግን (537 ከዘአበ) ነፃ ሕዝብ ሆነው የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት አላገኙም። ንጉሥ አልነበራቸውም። ገዥዎቻቸው የነበራቸው የፖለቲካ መብትም ቢሆን ብዙ ሳይቆይ የአገሪቱ መሪዎች ሆነው መታየት በጀመሩት ሊቃነ ካህናት ሃይማኖታዊ ሥልጣን መዳከም ጀመረ።
መሲሐዊውን ተስፋ መከታተል
ዘ ኮንሳይስ ጁዊሽ ኢንሳይክሎፔድያ እንደሚለው “የተቀባ ገዥ ብቻ ሳይሆን የእስራኤልን ጠላቶች አጥፍቶ ፍጹም የሆነ የሰላምና የፍጽምና ዘመን የሚያመጣ ንጉሥ ይነሣል” የሚለው መሲሐዊ ጽንሰ ሐሳብ የተወለደው በዚህ ጊዜ ነበር።
ታላቁ እስክንድር በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት አይሁዳውያንን ድል አድርጎ በመዳፉ ውስጥ አስገባቸው። ይሁን እንጂ የታላቁ እስክንድር አፄያዊ ግዛት በአይሁዳውያን ምድር፣ ባሕልና ሃይማኖት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ ቢሆንም ይጠብቁት የነበረው መሲሕ አልሆነላቸውም።
እስክንድር ከሞተ በኋላም ቢሆን ፓለስቲና ከግሪካውያን እጅ አልወጣችም። በመጀመሪያ በግብጽ ፐቶሎሚዎች ስትገዛ ቆይታ በኋላ ደግሞ በሶሪያ ሰልዩሲዶች መገዛት ጀመረች። ሁለቱም ሥርወ መንግሥቶች ከእስክንድር ወራሾች የተገኙ ናቸው። የግሪካውያን ተጽዕኖ እየጨመረ በሄደ መጠን ታዋቂና ባላባታዊ ዝርያ የነበራቸው አይሁዶች የአይሁዳውያንን ባሕልና ወግ ዘመን እንዳለፈበት አሮጌ ባሕልና ወግ መመልከት ጀመሩ። በዚህ ረገድ ግንባር ቀደም የነበሩት የጦቢያ ቤተሰቦች ነበሩ። እነዚህ የጦቢያ ቤተሰቦች የሰልዩሲድ ሥርወ መንግሥት አባል በነበረው በንጉሥ አንቲዮከስ አራተኛ ኤፒፋነስ ዘመን (175–164 ከዘአበ) ዘመዳቸው ለነበረው መንላወስ የተባለ ሰው የሊቀ ካህንነት ሹመት ሰጡ። ይህን ያደረጉት መንላወስ በሰለሞን ቤተ መቅደስ ሊቀ ካህናት የነበረው የሳዶቅ ዝርያ አለመሆኑን እያወቁ ነው። የግሪካውያን ተጽዕኖ በጣም አይሎ ስለነበረ የአይሁዳውያን ሃይማኖታዊ በዓሎች እንዳይከበሩ ተከለከሉ። ቤተ መቅደሱም የግሪካውያን ጸሎት ቤት ሆነ።
በ167 ከዘአበ መታትያስ የተባለው የአይሁዳውያን ካህንና ብዙ ጊዜ መቃባውያን ወይም ሃስሞናውያን ተብለው የሚጠሩት አምስት ልጆቹ ዓመፅ አካሄዱ። የመቃባውያን ዓመፅ በመጀመሪያ ላይ ሃይማኖታዊ ባሕርይ የነበረው ቢሆንም ቆየት ብሎ ግን ለአይሁዳውያን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የሚታገል ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሆነ። በ165 ከዘአበ ቤተ መቅደሱ በቁጥጥራቸው ሥር እንዲሆንና በድጋሚ እንዲመረቅ አደረጉ። በዛሬው ጊዜ በመላው ዓለም የሚኖሩ አይሁዳውያን ይህ የሆነበትን ጊዜ ሃኑካ በሚባለው የስምንት ቀን የብርሃን ድግስ ያከብሩታል። ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜም ቢሆን መሲሕ ብቅ አላለም።
ቸልተኛ እረኞችና ሃይማኖታዊ ልዩነት
ፒክቶሪያል ቢብሊካል ኢንሳይክሎፔድያ በዚህ ጊዜ “በካህናት አመራር ሥር ወድቆ የነበረው የሕዝቡ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሕይወት ብቻ አልነበረም። ካህናቱ በኢየሩሳሌም በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ የበላይነት ያላቸው በጣም ባለጠጋና ኃይለኛ የሆነ መደብ አባላት ሆኑ” ይላል። ካህናቱ አምባገነኖችና የእረኝነት ተግባራቸውን ለመፈጸም ቸልተኞች በመሆናቸው ካህናት ያልሆኑ ሰዎች በምትካቸው ሕጉን የመተርጎምና ሕግ የማስፈጸም ሥራ ማከናወን ጀመሩ። እነዚህ ጸሐፍት ተብለው የተጠሩት ሰዎች ሕጉን ለማጣመም የሚያስችል ሰበብ ይፈልጉ ነበር።
በዚሁ ዘመን የአይሁዳውያን ሃይማኖት እርስ በርሳቸው በሚፎካከሩ ኑፋቄዎች ተከፋፍሎ ነበር። ፈሪሳውያን አምላክ ለእስራኤላውያን ሁለት ዓይነት ሕጎችን፣ ማለትም የተጻፈና በአፍ የሚተላለፍ ሕግ ሰጥቷል ብለው ያስተምሩ ነበር። ከጥንት ዘመን ሲወርድ ሲዋርድ የመጣው የሊቀ ክህነት የዘር ግንድ ከተቋረጠ በኋላ የተቋቋመው ሊቀ ክህነት ሕጋዊ ስለመሆኑ የሚሰጡት ምክንያት በዚህ በአፍ የሚተላለፍ ሕግ ላይ የተመሠረተ ነው። ሰዱቃውያን ግን በአፍ የሚተላለፍ ሕግ መኖሩን ፈጽሞ አይቀበሉም። ሊቀ ካህናት ሆኖ ሊያገለግል የሚችለው ከሳዶቅ የዘር ግንድ የተወለደ ሰው ብቻ ነው ይሉ ነበር።
“ፈሪሳዊ” የሚለው ቃል “የተለየ” ወይም “ልዩ ሆኖ የሚታይ” የሚል ትርጉም ካለው ቃል የተገኘ ነው። አንዳንዶች ፈሪሳውያንን ይቃወሙ የነበሩ ሰዎች መናፍቃን መሆናቸውን ለማመልከት የሰጧቸው ስያሜ ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ እንደ ርኩስ ከሚቆጥሩአቸው አምሃሪቶች (የምድር ሰዎች) ራሳቸውን በመለየት የወሰዱትን “የተለየ” አቋም ለማመልከት የተሰጠ ስያሜ ነው ይላሉ። ፈሪሳውያን የተጻፈውንም ሆነ በአፍ የሚተላለፈውን ሕግ በመጠበቅ ረገድ ከመጠን በላይ ራሳቸውን የሚያመጻድቁ ሰዎች ነበሩ። ጋንያሁ ኮርንፌልድ የተባሉት አይሁዳዊ ደራሲ ሰዱቃውያን ከዚህ ባላነሰ ሁኔታ ለተጻፈው ሕግ ግትር አቋም የወሰዱት “ልዩ የሆነ ሃይማኖታዊ ስሜት ስለኖራቸው ሳይሆን ፈሪሳውያን የነበራቸውን የሕግ አውጪነት ሥልጣን ለመቃወም እንዲችሉ በፖለቲካ መሣሪያነት ስለሚያገለግላቸው ነው” ብለዋል።
ኢሴንስ የተባለውም ሃይማኖታዊ ቡድን በዚህ ጊዜ አካባቢ የተፈጠረ ይመስላል። እነዚህ ሰዎች በይፋ ይታወቅ ከነበረው ክህነት ተገንጥለው በቤተ መቅደሱ ይከናወን ከነበረው ሃይማኖታዊ ሥርዓትና መሥዋዕት ምንም ዓይነት ተካፋይነት እንዲኖራቸው ያልፈለጉ ናቸው። ሕጉን ግን አጥብቀው ይከተሉ ነበር። ኢሰንስ ከፈሪሳውያን ባልተለየ ሁኔታ በብዙ መንገዶች በሄለናውያን ወይም በግሪኮች ተጽዕኖ ተሸንፈው ነበር። በነፍስ ዘላለማዊነት ያምኑ ነበር።
ይህ ቡድን ከ4, 000 የማይበልጡ ወንዶች አባላት የነበሩት ሲሆን ሁሉም መነኮሳት ነበሩ። በፓለስቲና ምድር በሚገኙ ገለልተኛ የሆኑ ቦታዎች አንድ ላይ ተሰባስበው ይኖሩ ነበር። ኢንሳይክሎፔድያ ጁዳይካ ሰላማውያን ነን ስለሚሉት አቋማቸው ሲናገር “በዘመናችን እንዳሉት የይሖዋ ምሥክሮች ሳይሆኑ አይቀሩም” ይላል። ይሁን እንጂ ኢሰንስ በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚወስዱትን ጥብቅ የሆነ የገለልተኝነት አቋም እንዳልተከተሉ በቂ ማስረጃ አለ። የአይሁዳውያን ፒክቶሪያል ቢብሊካል ኢንሳይክሎፔድያ ኢሰንስ “በሮማ ላይ በተነሳው ዓመፅ በጀግንነት ተዋግተዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ የጦር መሪዎች ኢሰንስ ነበሩ” ይላል። ጆሴፈስ የተባለው አይሁዳዊ ታሪክ ጸሐፊ በ66 እዘአ በተነሣው ዓመፅ አይሁዳዊ ጄኔራል ሆኖ ስላገለገለ “ጆን ዘ ኢሰን” የተባለ ሰው ጠቅሷል።
በ1947 በተገኙት የሙት ባሕር ጥቅልሎች ውስጥ ስለ ኩምራን ሃይማኖታዊ ቡድን የሚገልጽ መረጃ ተገኝቷል። አንዳንድ ምሁራን ይህ ሃይማኖታዊ ቡድን ከኢሰን ጋር አንድ እንደሆነ ያምናሉ። አጥማቂው ዮሐንስና ኢየሱስ የኢሰን ሃይማኖታዊ ቡድን አባሎች ነበሩ ወይም ቢያንስ ይህ ሃይማኖታዊ ቡድን በአስተሳሰባቸውና በአመለካከታቸው ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር ስለሚሉት አባባል ግን ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ “ይህ ግምታዊ አስተሳሰብ ስህተት መሆኑን የሚያረጋግጡ . . . ታላላቅ ምክንያቶች አሉ” ይላል። “በኩምራን ሃይማኖታዊ ቡድንና በመጥምቁ ዮሐንስ መካከል መሠረታዊ ልዩነቶች አሉ። . . . እንዲሁም የኢየሱስ አገልግሎት፣ የደህንነት መልእክቱ፣ ስለ አምላክ ፈቃድ የነበረው ግንዛቤ . . . በተለይ ደግሞ ስለ ፍቅር የሰጠው ሥር ነቀል ትእዛዝና ከኃጢአተኞችና ማኅበረሰቡ ይንቃቸው ከነበሩ ሰዎች ጋር አብሮ መዋሉ ከዚህ ሃይማኖታዊ ቡድን አመለካከት ጋር ፈጽሞ የሚጻረር ነው።”
እንደ እውነቱ ከሆነ ሁሉም የአይሁድ ሃይማኖታዊ ኑፋቄዎች አጥማቂውን ዮሐንስንም ሆነ ዮሐንስ መሲሕ ነው ብሎ ያስተዋወቀውን ኢየሱስን ተቃውመው ነበር። ብዙዎቹ ካህናት የዮሐንስን መልእክት ከመቀበል ይልቅ ዚለትስ ይባሉ የነበሩትንና ለአይሁዳውያን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ለማስገኘት ይታገሉ የነበሩትን አብዮተኞች ወደ መከተል አዘንብለው እንደነበር ጆሴፈስ ጽፏል። በ63 ከዘአበ በግሪካውያን አገዛዝ እግር የተተካውን የሮማውያን አገዛዝ ይቃወሙ የነበሩት እነዚህን የመሰሉ ቡድኖች በርከት ላሉ ዓመታት የሽብር ፈጠራ እንቅስቃሴ አድርገው ነበር። በመጨረሻም በ66 እዘአ ግልጽ የሆነ ዓመፅ አካሄዱ። በዚህም ምክንያት የአይሁድ ቤተ መቅደስና ክህነት ጠፋ። መሲሐዊው ተስፋ ፈጽሞ ጨለመ።
ቤተ መቅደስና የክህነት ሥርዓት የሌለው ይሁዲነት
ይህ ከመሆኑ ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ማለትም በባቢሎን ምርኮ ዘመን ወይም ከባቢሎን ምርኮ በኋላ የሕጉን እውቀት ለማስፋፋት ሥራ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ ነበር። በየስፍራው ምኩራብ የሚባሉ የማስተማሪያ ማዕከሎች ተሠሩ። ከዚያ በኋላ ልዩ በሆኑ ወቅቶችና መሥዋዕት ለማቅረብ ካልሆነ በስተቀር ወደ ቤተ መቅደሱ መሄድ ቀረ። በዚህም ምክንያት በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ በየምኩራቦቹ ማምለክ የተለመደ ነገር ሆኖ ነበር። ቤተ መቅደሱ በ70 እዘአ ከጠፋ በኋላ ደግሞ ምኩራቦች የቤተ መቅደስ ምትክ ሆነው መታየት ጀመሩ።
በዚህ ጊዜ ከሕልውና ውጭ ከሆነው የክህነት ሥርዓት ይልቅ ረቢ ለሚባሉ መምህራን ትልቅ ግምት መሰጠት ጀመረ። ሰዱቃውያን በቡድን ደረጃ አሉ ሊባሉ በማይችሉበት ሁኔታ ላይ ስለነበሩና ኢሰኖችም ፈጽመው ጠፍተው ስለነበረ ፈሪሳውያን አለአንዳች ተቀናቃኝ የመሪነቱን ቦታ ያዙ። የሂብሩ ዩኒየን ኮሌጅ ባልደረባ የሆኑት ኤሊስ ሪቭኪን እንደሚከተለው በማለት ፈሪሳውያን ያሳደሩትን ተጽዕኖ ገልጸዋል። “የፈሪሳውያን ያልተጻፈ የቃል ሕግ ለሚሽና፣ ለፓለስቲናውያንና ለባቢሎናውያን ታልሙድ፣ ለጥንታዊው፣ ለመካከለኛውና ለዘመናዊው ዘመን ሪስፖንሳ (የአይሁዳውያን የሕግ መጽሐፍ)፣ እንዲሁም ለተለያዩ የአይሁድ የሕግ መጻሕፍት መገኘት ምክንያት ሆኗል።” በተጨማሪም ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “ዛሬም እንኳን ቢሆን የተለያዩት የአይሁዳውያን ቡድኖች፣ አክራሪዎችም ሆኑ ወግ አጥባቂዎች ወይም የተሐድሶ አራማጆች ሁሉም ቡድናቸው ከፈሪሳውያን ወይም ከሊቃውንት ረቢዎች በቀጥታ የመጣ እንደሆነ ይናገራሉ።”
በዲያስፖራ ዘመን የነበሩ መሲሐዊ ተስፋዎች
ከ70 እዘአ በፊትም እንኳን ቢሆን በሚልዮን የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ከፓለስቲና ምድር ውጭ፣ በሶሪያ፣ በታናሽቱ እስያ፣ በባቢሎንና በግብጽ ይኖሩ ነበር። ከ70 እዘአ በኋላ ግን ከእልቂት የተረፉት አይሁዶች ከመሠረታቸው ስለተነቀሉ ኑሯቸውን በዲያስፖራ ለመግፋት ተገደዋል። ዲያስፖራ ማለት በግሪክኛ “መበተን” ማለት ነው። እንዲህ ባለ ሁኔታ እየኖሩ እንኳን ብዙዎቹ ወደፊት በሚመጣው መሲሕ አማካኝነት የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት እንደሚያገኙ ተስፋ ያደርጉ ነበር። ባር ኮክባ የተባለው የአይሁዳውያን መሪ በ132 እዘአ በሮማ መንግሥት ላይ ያልተሳካለት ዓመፅ በማስነሣት ሐሳዌ መሲሕ ሆኗል። ዘ ጁዊሽ ኢንሳይክሎፔድያ እንደሚለው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ 1744 እዘአ ድረስ 28 የሚያክሉ ባር ኮክባን የመሰሉ ሐሳዌ መሲሖች ተነሥተዋል።
መሲሐዊው ተስፋ በዚህ መንገድ እርስ በርሱ የተሳከረ ሆነ። ኢንሳይክሎፔድያ ጁዳይካ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “በመካከለኛው ዘመን የነበረው የአይሁድ ንድፈ ሐሳብ ከጥንቱ ዘመን ስለ መሲሑ አንድ ወጥ የሆነና የተያያዘ ጽንሰ ሐሳብ አላገኘም። በታልሙድ ጽሑፎች ውስጥ፣ የተለያዩትን የሚድራሺም ጽሑፎች ጨምሮ፣ ብዙ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ሐሳቦች አሉ።” በ12ኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው ሞሰስ ማይሞኒደስ የተባለ አይሁዳዊ ፈላስፋ እንኳን የመሲሑ ግዛት አንድ ከፍተኛ ደረጃ ያለውን ማኅበረሰብ የሚያመለክት ምሳሌያዊ የሆነ ግዛት ሳይሆን አይቀርም ብሏል። በ19ኛው መቶ ዘመን የተሐድሶ አራማጅ የሆኑ አይሁዶች “በመሲሐዊ ዘመን የነበረው እምነት በግላዊ መሲሕ ተተካ። . . . መሲሐዊው ተስፋ ግዞተኞች ወደ ጽዮን ከመመለሳቸው ጋር የነበረውን የጥንት ዝምድና አጣ።”
ከዚህ ጥቂት ቀደም ብሎ በአውሮፓ የተካሄደው የሃስካላ (የእውቀት ብርሃን) እንቅስቃሴ ለተጨማሪ መሳከር ምክንያት ሆኗል። ይህ እንቅስቃሴ ከምዕራቡ አኗኗር ጋር የሚስማማ የአይሁድ ሃይማኖት እንዲስፋፋ አድርጓል። አይሁዳውያን በመሲሕ መሪነት ዳግመኛ በምትቋቋም የአይሁድ ምድር የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት አግኝቶ መኖር ከሁሉም ይበልጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ነው ብለው በሚያምኑና በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር ከተወለዱበት አገር የኑሮ ሁኔታ ጋር ለመስማማት መቻል ነው በሚሉ ሁለት ቡድኖች እንዲከፈሉ አድርጓል።
የእነዚህ ሁኔታዎች መፈጠርና የፀረ ሴማዊነት ስሜት እየተጠናከረ መሄድ በ19ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ በቲዎዶር ኸርዘል ለተወለደው ለዘመናዊው ጽዮናዊ እንቅስቃሴ መገኘት ምክንያት ሆኗል። ይህ የዛሬ 46 ዓመት በግንቦት ወር የተጀመረው እንቅስቃሴ አይሁዳውያን በገዛ አገራቸው የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት አግኝተው እንዲኖሩ አስችሏል። ይሁን እንጂ መሲሐዊው ተስፋ ተፈጽሞላቸዋልን?
ከተፈጸመላቸውስ አንዳንድ አይሁዶች የለንደን ታይምስ እንዳለው “ጽዮናዊነት በእስራኤል መፈጠር እውን የሆነ ታላቅ ርኩሰት ነው” የሚሉት ለምንድን ነው? ሟቹ ታሪክ ጸሐፊ፣ ቲዎዶር ኤች ዋይት ራሳቸው አይሁድ ሆነው ሳሉ በፍጹም ግልጽነት “የፕሮቴስታንቶችን ያህል እርስ በርሳቸው የሚጣሉ ብዙ የአይሁዳውያን ኑፋቄዎች አሉ” ያሉት ለምንድን ነው? ታይም መጽሔት በ1987 ክኔሴት በተባለው 120 አባላት ያሉት የፖለቲካ አካል ውስጥ ስለሚታየው ሃይማኖታዊ መለያየት ሲጽፍ “እስራኤል እርስ በርሱ የተከፋፈለ ቤት እንዳትሆን ከተፈለገ አንድ ዓይነት መፍትሔ መገኘት ይኖርበታል” ያለው ለምንድን ነው?
የዘመናችን የአይሁዳውያን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚሰጠው ምንም ተስፋ የለውም። ዘመናዊው የአይሁድ እምነት መሲሐዊውን ተስፋ ለማግኘት በሰብአውያን ፖለቲከኞች ስለሚታመን በራሱ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈውን “በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል” የሚለውን ቃል ችላ ብሏል።—መዝሙር 118:8፤ 146:3
በዘመናችን የሚኖሩ ብዙ አይሁዶች መሲሐዊ ተስፋቸውን ለይተው ለማወቅ ባልቻሉበት እንዲህ ያለ ግራ መጋባት የሚኖሩ ይሁኑ እንጂ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ቅድመ አያቶቻቸው ግን መሲሑን ለይተው ለማወቅ አልተቸገሩም። (ዮሐንስ 1:41 ተመልከት።) ያመኑትን መሲሕ በመከተል “የእምነት፣ የተስፋና የፍቅር” ሃይማኖት ነው ብለን ልንጠራ ለምንችለው ሃይማኖት ጠንካራ ጠበቆች ሆነዋል። የሚቀጥለው እትማችን ይህንን ያብራራል።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አይሁዳውያን በ70 እዘአ ከጠፋው ቤተ መቅደሳቸው የቀረው በተለምዶ ዘ ዌይሊንግ ዎል እየተባለ የሚጠራው የምዕራብ ግድግዳ ብቻ ነው