የሃይማኖት የወደፊቱ ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንጻር ሲታይ
ክፍል 16:- ከ9ኛው-16ኛው መቶ ዘመን እዘአ ከፍተኛ ተሐድሶ የሚያስፈልገው ሃይማኖት
“የተበላሸ ነገር ሁሉ መታደስ አለበት።”—በ18ኛው መቶ ዘመን የነበረው ፈረንሳዊው ደራሲና ታሪክ ጸሐፊ፣ ቮልቴር
የጥንት ክርስቲያኖች መንጽሔ አለ ብለው አላስተማሩም፣ ማንኛውንም ምስል አላመለኩም፣ “ቅዱሳን” የሚባሉ ሰዎችን አላከበሩም እንዲሁም የተለያዩ ቅርሶችን እንደ ቅዱስ ነገር አድርገው አላመለኩም። በፖለቲካ ውስጥ ካለመሳተፋቸውም በተጨማሪ በጦር መሣሪያዎች አይጠቀሙም ነበር። በ15ኛው መቶ ዘመን ግን የጥንት ክርስቲያኖችን እንከተላለን ይሉ የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች በሙሉ ይፈጽሙ ነበር።
“መናፍቃን” ተሐድሶ እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ
ዘ ኮሊንስ አትላስ ኦቭ ወርልድስ ሂስትሪ “[በሮም ካቶሊክ ሃይማኖት ላይ] የመጀመሪያው ኑፋቄ ብቅ ያለው በ1000 እዘአ አካባቢ በፈረንሳይና በሰሜናዊ ኢጣሊያ ውስጥ ነበር” ይላል። ቀደም ሲል መናፍቃን ይባሉ ከነበሩት መካከል አንዳንዶቹ መናፍቅ የሆኑት በቤተ ክርስቲያኒቱ አመለካከት ብቻ ነበር። መናፍቃን ይባሉ የነበሩት ግለሰቦች የጥንቱን ክርስትና የቱን ያህል አጥብቀው ይከተሉ እንደነበር በአሁኑ ጊዜ በትክክል ማወቅ ያስቸግራል። ሆኖም ቢያንስ አንዳንዶቹ የሞከሩ ይመስላል።
በዘጠነኛው መቶ ዘመን፣ መጀመሪያ የልዮንስ ከተማ ሊቀ ጳጳስ አጎባርድ የምስል አምልኮንና ወደ “ቅዱሳን” የሚቀርቡ ጸሎቶችን አወገዙ። በ11ኛው መቶ ዘመን የታወርስ ከተማ ነዋሪና የሊቀ ጳጳስ ረዳት የነበረው ቤረንጋር በካቶሊክ የቅዳሴ ሥርዓት ላይ የሚቀርበው ቂጣና ወይን ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደም እንደሚለወጥ በሚነገርለት የምሥጢረ ቁርባን ትምህርት ላይ ጥያቄ በማስነሣቱ ተወገዘ። ከአንድ መቶ ዘመን በኋላ ፒተር ደ ብራይስና የሉዛን መንደር ነዋሪ የነበረው ሔንሪ የሕፃናት ጥምቀትንና የመስቀል አምልኮን ተቃወሙ። በዚሁ ሳቢያ ሔንሪ ነፃነቱን ሲያጣ ፒተር ተገደለ።
ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት “በአሥራ ሁለተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ የምዕራብ አውሮፓ ከተሞች በመናፍቃን ቡድኖች ተሞልተው ነበር” በማለት ዘግበዋል። ከእነዚህ ቡድኖች ውስጥ በይበልጥ ጎላ ብለው ይታዩ የነበሩት ዎልደንሳውያን ነበሩ። ዎልደንሳውያን በ12ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ፒየር ቫልደስ (ፒተር ዎልዶ) በተባለ አንድ ፈረንሳዊ ነጋዴ መሪነት በስፋት ሊታወቁ ችለዋል። ዎልደንሳውያን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር ከማይስማሙባቸው ነገሮች መካከል የማርያም አምልኮ፣ ለቄሶች መናዘዝ፣ ፍታት፣ ሊቀ ጳጳሳት ገንዘብ በመክፈል የኃጢአት ስርየት ለማግኘት ትችላላችሁ ማለታቸው፣ የቀሳውስት ብሕትውናና በጦር መሣሪያ መዋጋት ይገኙበት ነበር። ይህ እንቅስቃሴ በፍጥነት በመላው ፈረንሳይና በሰሜናዊ ኢጣሊያ ከተስፋፋ በኋላ ወደ ፍላንደርስ፣ ጀርመን፣ ኦስትርያና ቦህምያ (ቺኮዝላቫኪያ) ጭምር ተዛመተ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ “የእንግሊዝ ተሐድሶ አጥቢያ ኮከብ” በመባል የሚታወቀው የኦክስፎርዱ ምሁር ጆን ዊክሊፍ በ14ኛው መቶ ዘመን በእንግሊዝ ውስጥ ‘የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የጨበጡትን ሥልጣን’ ማውገዝ ጀምሮ ነበር። ጆን ዊክሊፍ ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ በመተርጎሙ እርሱና ደጋፊዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ለተራው ሕዝብ በስፋት እንዲዳረስ አድርገዋል። የዊክሊፍ ተከታዮች ሎላርዳውያን በመባል ይጠሩ ነበር። ሎላርዳውያን ለሕዝብ በይፋ ከመስበካቸውም በተጨማሪ ትራክቶችንና የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ያሰራጩ ነበር። እንዲህ ዓይነቱ “መናፍቃዊ” ባሕርይ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የጎን ውጋት ሆኖባት ነበር።
የዊክሊፍ ትምህርት በባሕር ማዶም ተሰራጨ። በቦህምያ የሚገኘው የፕራግ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ባለ ሥልጣን የነበረውን የጃን ሁስን (ጆን ሁስ) ትኩረት ሳበ። ሁስ የሊቀ ጳጳሱ ሥልጣን ተገቢ ስለ መሆኑ ጥያቄ ከማስነሣቱም በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያኒቱ በጴጥሮስ መሠረት ላይ ተመሥርታለች የሚባለው ነገር ትክክል እንዳልሆነ ገልጿል። የኃጢአትን ስርየት በገንዘብ ለመሸጥ ይደረግ በነበረው ሩጫ ላይ ውዝግብ ከተነሣ በኋላ ሁስ ኑፋቄ አራማጅ ነው ተብሎ ፍርድ ቤት ቀረበና በ1415 በእንጨት ላይ ተሰቅሎ በእሳት ተቃጠለ። በካቶሊክ ትምህርት መሠረት ኢንደልጀንስ የኃጢአት ቅጣት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ምሕረት ተደርጎ ግለሰቡ ሰማይ ከመግባቱ በፊት በመንጽሔ ውስጥ እየተሠቃየ ለጊዜው የሚቀጣበት ወይም የሚነጻበት ጊዜ የሚያጥርበት አሊያም ጨርሶ የሚሰረዝበት ዝግጅት ነው።
ተሐድሶ እንዲደረግ የሚቀርበው ጥሪ ቀጠለ። የ15ኛው መቶ ዘመን የዶሚኒካን እምነት ሰባኪ የነበረው ጂሮላሞ ሳቮናሮላ እንዲህ በማለት የተሰማውን ቅሬታ ገልጿል:- ‘ሊቀ ጳጳሳትና ከፍተኛ የሃይማኖት መሪዎች ኩራትንና የሥልጣን ጥማትን ቢያወግዙም ራሳቸው በእነዚህ ነገሮች ተነክረዋል። ስለ ድንግልና እየሰበኩ ቁባቶችን ይይዛሉ። የሚያስቡት ስለ ዓለምና ስለ ዓለማዊ ነገሮች ብቻ ነው፤ ለነፍሳት ደንታ የላቸውም።’ የካቶሊክ ካርዲናሎች እንኳ ችግሩን ተገንዝበውታል። በ1538 ለሊቀ ጳጳስ ጳውሎስ ሣልሳዊ በጻፉት ማስታወሻ ላይ ቤተ ክህነትን፣ ገንዘብን፣ የፍርድ ጉዳዮችንና የሥነ ምግባር ብልግናዎችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋቸው ነበር። ሆኖም ሊቀ ጳጳሱ አስፈላጊውን ተሐድሶ ሳያደርጉ መቅረታቸው የፕሮቴስታንት ተሐድሶ አስከተለ። ከመጀመሪያዎቹ የተሐድሶ መሪዎች መካከል ማርቲን ሉተር፣ ሁልድሪክ ዝዊንግሊ እና ጆን ካልቪን ይገኙበታል።
ሉተርና “የ16ኛው መቶ ዘመን ቢንጎ”
ጥቅምት 31, 1517 ሉተር የኢንደልጀንስ ሽያጭን ለመቃወም በዊተንበርግ በሚገኘው የቤተ ክርስቲያኑ በር ላይ 95 የተቃውሞ ነጥቦችን ጽፎ በለጠፈበት ወቅት በሃይማኖታዊው ዓለም ላይ እሳት ለኩሶበታል።
ኢንደልጀንስ መሸጥ የተጀመረው በመስቀል ጦርነቶች ወቅት “ቅዱስ” ጦርነት ለማካሄድ ሲሉ ሕይወታቸውን የሚሠዉ ሰዎች ሥርየት እንደሚያገኙ ለማግባባት ነበር። በኋላም ለቤተ ክርስቲያኒቱ የገንዘብ ድጋፍ ለሚያደርጉ ሰዎች መሰጠት ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ ኢንደልጀንስ ቤተ ክርስቲያኖችን፣ ገዳማትን ወይም ሆስፒታሎችን ለመሥራት የሚያስችል ገንዘብ ለመሰብሰብ አመቺ ዘዴ ሆነ። የሃይማኖት ታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ሮናልድ ቤይንተን “በመካከለኛው ዘመን የታነጹት በጣም ዝነኛ የሆኑ ታሪካዊ ሕንፃዎች የተሠሩበት ገንዘብ የተገኘው በዚህ መንገድ ነበር” ብለዋል። በተጨማሪም ኢንደልጀንስን “የ16ኛው መቶ ዘመን ቢንጎ” ብለውታል።
ሉተር ታዋቂ በሆነበት ኃይለኛ አንደበቱ “ሊቀ ጳጳሱ [በኢንደልጀንስ ተጠቅሞ] ማንኛውንም ሰው ከመንጽሔ የማውጣት ሥልጣን ካለው በፍቅር ተነሣስቶ እያንዳንዱን ሰው ከመንጽሔ ቅጣት ለምን ነፃ አያደርገውም?” በማለት ጥያቄ አቅርቧል። ሉተር ለአንድ የሮማውያን የሕንፃ ፕሮጄክት ገንዘብ እንዲያዋጣ ሲጠየቅ ሊቀ ጳጳሱ “ቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያንን ሸጦ ገንዘቡን በኢንደልጀንስ ለተዘረፉት ድሆች ቢሰጣቸው ይሻላል” በማለት በንዴት መልሷል።
በተጨማሪም ሉተር “ከአይሁዳውያን ጋር ባለን ግንኙነት የሊቀ ጳጳሱን ሐሳብ ሳይሆን የክርስቶስን የፍቅር ሕግ መከተል ይኖርብናል” የሚል ምክር በመስጠት ካቶሊክ የነበራትን ፀረ አይሁዳውያን አቋም ተቃውሟል። የተለያዩ ጥንታዊ ቅርሶችን እንደ ቅዱስ ነገር አድርጎ ማክበርን በተመለከተም እንዲህ ብሎ ተችቷል:- “አንዱ ሰው የመልአኩ ገብርኤል ክንፍ ላባ ተሰጥቶኛል ሲል የሜይንዙ ጳጳስ የሙሴ ቁጥቋጦ ነበልባል አለኝ ይላል። የኢየሱስ ሐዋርያት አሥራ ሁለት ብቻ ሆነው ሳለ አሥራ ስምንት ሐዋርያት በጀርመን ውስጥ ተቀብረዋል እንዴት ሊባል ይችላል?”
ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሉተር ተቃውሞ ምላሸ የሰጠችው እርሱን ከቤተ ክርስቲያን አባልነት በመሰረዝ ነበር። የሮሙ ቅዱስ ንጉሠ ነገሥት የነበረው ቻርልስ አምስተኛ ለሊቀ ጳጳሱ ተጽዕኖ በመንበርከክ ሉተርን አገደው። ይህ ሁኔታ ከፍተኛ ውዝግብ በማስከተሉ በ1530 ስለ ጉዳዩ ለመወያየት የኦግስበርግ ጉባኤ ተጠራ። ስምምነት ላይ ለመድረስ የተደረጉት ጥረቶች ሁሉ ሊሳኩ ስላልቻሉ የሉተር መሠረተ ትምህርቶችን በተመለከተ ስለ ነበረው እምነት መግለጫ ወጣ። ይህ የኦግስበርግ የእምነት ቃል በመባል የሚታወቀው ይፋዊ መግለጫ የመጀመሪያው የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን መመሥረቱን የማወጅ ያህል ነበር።
ዝዊንግሊና ሉተር አልተስማሙም
ዝዊንግሊ መጽሐፍ ቅዱስ የቤተ ክርስቲያን የመጨረሻውና ብቸኛው ባለ ሥልጣን እንደሆነ አጥብቆ ይናገር ነበር። የሉተር ምሳሌነት ያበረታታው ቢሆንም የክርስቶስን ትምህርቶች የተማረው ከአምላክ ቃል እንጂ ከሉተር እንዳልሆነ በመግለጽ የሉተር ተከታይ ተብሎ መጠራትን ይቃወም ነበር። እንዲያውም በአንዳንድ የጌታ ራት በዓል አከባበር ሥርዓቶች ላይም ሆነ ክርስቲያኖች ከመንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ሊኖራቸው በሚገባው ግንኙነት ረገድ ከሉተር ጋር አይስማማም ነበር።
ሁለቱ ተሐድሶ አራማጆች የተገናኙት በ1529 አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ዘ ሪፎርሜሽን ክራይስዝ የተባለው መጽሐፍ ይህን ሁኔታ “የሃይማኖት መሪዎች ስብሰባ ይመስል ነበር” በማለት ጠርቶታል። መጽሐፉ “ሁለቱ ሰዎች ወዳጅ ሆነው ባይለያዩም . . . በስብሰባው ማብቂያ ላይ በሁሉም የስብሰባው ተካፋዮች የተፈረመው የጋራ መግለጫ በመካከላቸው የነበረውን ልዩነት በዘዴ ሸፋፍኖታል።”
ዝዊንግሊ ከተከታዮቹም ጋር ያልተግባባባቸው ጉዳዮች ነበሩት። በ1525 መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ላይ ስላለው ሥልጣን በተነሣው አከራካሪ ጉዳይ ከእነርሱ ጋር ሳይግባባ ቀረና አንድ ቡድን ተገነጠለ። እርሱ መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ላይ ሥልጣን አለው ሲል እነርሱ ግን ይህን ሐሳብ አይደግፉም ነበር። አናባፕቲስትስ (“እንደገና አጥማቂዎች”) በመባል የሚጠራው ይህ ቡድን መጠመቅ ያለባቸው አዋቂ የሆኑ አማኞች ብቻ እንደሆኑ በመናገር የሕፃናት ጥምቀትን ምንም ጥቅም እንደሌለው አድርጎ ይመለከት ነበር። በተጨማሪም ትክክለኛ በተባሉት ጦርነቶች እንኳ ቢሆን በጦር መሣሪያ መዋጋትን ይቃወም ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ የቡድኑ አባላት በእምነታቸው ምክንያት ተገድለዋል።
ካልቪን በተሐድሶ ሂደት ላይ የተጫወተው ሚና
ብዙ ምሁራን ካልቪንን ከሁሉ የበለጠ ተሐድሶ አራማጅ እንደነበረ አድርገው ይመለከቱታል። ቤተ ክርስቲያን ወደ ክርስትና የመጀመሪያ መሠረታዊ ትምህርቶች እንድትመለስ አጥብቆ ተከራክሯል። ሆኖም ከዋና ዋና ትምህርቶቹ አንዱ የሆነው የሰው ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው ትምህርት ኢስጦኢኮች ሁሉንም ነገር የሚወስነው ዚየስ ስለሆነ ሰዎች የማይቀርላቸውን ዕጣ ክፍላቸውን አሜን ብለው መቀበል አለባቸው ከሚለው የጥንት ግሪክ ትምህርቶች የተወሰደ ነው። ይህ መሠረተ ትምህርት ክርስቲያናዊ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
በካልቪን ዘመን የፈረንሳይ ፕሮቴስታንቶች ሁጉኖታውያን በመባል ይጠሩ ነበር። በዚህ ወቅት ከፍተኛ ስደት ደርሶባቸው ነበር። ነሐሴ 24, 1572 ከዋለው ከቅዱስ በርተሎሜዎስ ቀን ጀምሮ በፈረንሳይ በደረሰው እልቂት የካቶሊክ ኃይሎች በመጀመሪያ በፓሪስ ቀጥሎም በጠቅላላው አገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ፕሮቴስታንቶችን ገድለዋል። ሆኖም ሁጉኖታውያንም ጭምር በ16ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ በተካሄዱት ደም መፋሰስ የሞላባቸው ጦርነቶች ሰይፍ መዝዘው ብዙ ሰዎችን ፈጅተዋል። በዚህ መንገድ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ . . . ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ” በማለት ኢየሱስ የሰጠውን መመሪያ ላለመከተል መርጠዋል።— ማቴዎስ 5:44
ሟቹ የፕሮቴስታንት ቄስ ሃሪ ኢመርሰን ፎስዲክ ጭካኔ የተሞላበትና ዘግናኝ በማለት የገለጹት ካልቪን ሃይማኖታዊ እምነቶቹን ለማስፋፋት የተጠቀመባቸው ዘዴዎች መጥፎ ምሳሌ ሆነዋል። ካልቪን ለጄኔቫ ባስተማረው የቤተ ክርስቲያን ሕግ መሠረት በአራት ዓመታት ውስጥ ብቻ 58 ሰዎች በሞት ሲቀጡ 76ቱ ደግሞ በአራት ዓመት ውስጥ ከአገር እንዲባረሩ ተደርጓል፤ በ16ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ወደ 150 የሚገመቱ ሰዎች በእንጨት ላይ ተሰቅለው በእሳት ተቃጥለዋል። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ የስፔይኑ ተወላጅ ሐኪምና የሃይማኖት ምሁር የነበረው በተጨማሪም የሥላሴን ትምህርት ባለመቀበሉ ምክንያት ሰዎች ሁሉ “መናፍቅ” ነው ያሉት ማይክል ሴርቬተስ ነበር። የካቶሊክ ባለ ሥልጣናት የማይክል ሴርቬተስን ምስል ሠርተው በእሳት አቃጠሉ፤ ፕሮቴስታንቶች ደግሞ ከዚህ የከፋ እርምጃ በመውሰድ በእንጨት ላይ ሰቅለው አቃጥለውታል።
በመጨረሻ ‘አንድ አስፈሪ እውነታ ገሀድ ወጣ’
አንዳንድ ተሐድሶ አራማጆች ነን ባዮች በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ ከሉተር ጋር ቢስማሙም የእርሱን አቋም አልደገፉም። ከእነዚህ አንዱ የደች ምሁር የነበረው ዴስዴሪየስ ኢራስመስ ነበር። በ1516 “አዲስ ኪዳንን” በመጀመሪያው የግሪክ ቋንቋ ለማሳተም የመጀመሪያው ሰው ሆነ። ኢድንበርግ ሪቪው ‘ተሐድሶው አስፈሪ እውነታ እስኪሆን ድረስ ተሐድሶ አራማጅ ነበር’ ይላል።
ሆኖም ሌሎች ተሐድሶውን ማራመዳቸውን ቀጠሉና በጀርመንና በስካንዲኔቪያ የሉተር እምነት በፍጥነት ተስፋፋ። በ1534 እንግሊዝ ከሊቀ ጳጳሱ ሥልጣን ራሷን ነፃ አደረገች። ብዙም ሳይቆይ በተሐድሶ አራማጁ በጆን ኖክስ መሪነት ስኮትላንድ ተከተለች። ከ16ኛ መቶ ዘመን ማብቂያ በፊት የፕሮቴስታንት ሃይማኖት በፈረንሳይና በፖላንድ ሕጋዊ እውቅና አገኘ።
አዎን፣ ቮልቴር “የተበላሸ ነገር ሁሉ መታደስ አለበት” በማለት የተናገረው ትክክል ነው። ሆኖም ቮልቴር “የተበላሸ ነገር መታደስ ያለበት ተሐድሶው ከተበላሸው ነገር የበለጠ አደገኛ ካልሆነ ነው” ሲል ለዚህ አባባሉ ማብራሪያ የሆነውን ነገር አክሏል። የእነዚህን ቃላት እውነተኝነት በተሻለ ሁኔታ ለመገንዘብ “የፕሮቴስታንት እምነት— በእርግጥ ተሐድሶ ነበርን?” የሚለውን በሚቀጥለው እትማችን ላይ የሚወጣውን ርዕስ እንዲያነቡ ተጋብዘዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
እነዚህ መሠረተ ትምህርቶችና ልማዶች በጥንት ክርስቲያኖች ዘንድ ይታወቁ እንዳልነበረ ለማረጋገጥ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር አማካኝነት የታተመው ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር የተባለው መጽሐፍ ላይ የሚገኙትን “ሐዋርያዊ ተተኪነት፣” “ጥምቀት፣” “መናዘዝ፣” “መስቀል፣” “ዕድል፣” “ምስሎች፣” “ማርያም፣” “ቁርባን፣” “ገለልተኝነት” እና “ቅዱሳን” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።
“ፕሮቴስታንት” የሚለው መጠሪያ ለካቶሊኮች የበለጠ ሃይማኖታዊ ነፃነት የሰጠውን ድንጋጌ ለተቃወሙት የሉተር ተከታዮች ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው በ1529 በተካሄደው የስፒየር ጉባኤ ላይ ነበር።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማርቲን ሉተር፣ በ1483 በጀርመን ተወለደ፣ በ23 ዓመቱ በቅስና ማዕረግ ተሾመ፤ በዊትንበርግ ዩኒቨርሲቲ ሃይማኖታዊ ትምህርት አጥንቶ በ1512 የቅዱሳን ጽሑፎች ፕሮፌሰር ሆነ፣ በ62 ዓመቱ ሞተ
ሁልደሪክ ዝዊንግሊ፣ ሉተር ከተወለደ ከሁለት ወራት ያህል በኋላ በስዊዘርላንድ ተወለደ፤ በ1506 በቅስና ማዕረግ ተሾመ፣ በ47 ዓመቱ የፕሮቴስታንቶች አዝማች ሆኖ በጦር ሜዳ ሞተ
[ምንጭ]
Kunstmuseum, Winterthur
ጆን ካልቪን፣ ሉተርና ዝዊንግሊ ከተወለዱ ከ25 ዓመታት በኋላ ተወለደ፤ በወጣትነቱ ከፈረንሳይ ወደ ስዊዘርላድ ሄደና ጄኔቫ ውስጥ በቤተ ክርስቲያን የሚተዳደር መንግሥት ካቋቋመ በኋላ በ54 ዓመቱ ሞተ