የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g95 1/8 ገጽ 9-11
  • ሴቶች፣ በሥራ ቦታቸው ይከበራሉን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሴቶች፣ በሥራ ቦታቸው ይከበራሉን?
  • ንቁ!—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • እብሪተኛ ወንድ
  • ሴቶችና ሕግ
  • ሴቶች፣ በቤታቸው ውስጥ ይከበራሉን?
    ንቁ!—1995
  • ጾታዊ ትንኮላን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2000
  • ሴቶች በአሁኑ ጊዜ ይከበራሉን?
    ንቁ!—1995
  • በሁሉም ዕለታዊ የኑሮ ክፍሎች ሴቶችን ማክበር
    ንቁ!—1995
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1995
g95 1/8 ገጽ 9-11

ሴቶች፣ በሥራ ቦታቸው ይከበራሉን?

“አብዛኞቹ ወንዶች፣ ያገቡም ሆኑ ያላገቡ፣ ሴቶችን እንደ መደሰቻ ይቆጥሯቸዋል።”— ጄኒ የሕግ ጸሐፊ የነበረች

“በሆስፒታል አካባቢዎች ሴቶችን መዳፈርና ማስፈራራት በጣም ተስፋፍቷል።”— ሣራ፣ ነርስ

“በሥራ ቦታዬ ሁልጊዜ በብልግና ድርጊት እንድካፈል ጥያቄ ይቀርብልኛል።”— ጄን፣ ነርስ

እነዚህ ሁኔታዎች አብዛኛውን ጊዜ ከሚያጋጥሙት ሁኔታዎች የተለዩና ያልተለመዱ ናቸው ወይስ በጣም የተስፋፉ? ንቁ! መጽሔት በሥራ ቦታ ለሚውሉ በርካታ ሴቶች ቃለ መጠይቅ አድርጎ ነበር። እነዚህ ሴቶች ከወንዶች ባልደረቦቻቸው የአክብሮት አያያዝ ያገኛሉን? ሴቶቹ ከሰጧቸው አስተያየቶች የሚከተሉት ይገኛሉ:-

በኒው ጀርሲ ዩ ኤስ ኤ የምትኖረውና ለዘጠኝ ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል የሠራችው ሣራ እንዲህ ብላለች:- “በሳን አንቶኒዮ፣ ቴክሳስ ስሠራ የነበረበት ጊዜ ትዝ ይለኛል። በኩላሊት ሕክምና ክፍል ውስጥ አንድ ክፍት የሥራ ቦታ ነበር። ይህን ቦታ ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገኝ በርካታ ዶክተሮችን አማከርኩ። አንደኛው ዶክተር ‘ከኃላፊው ዶክተር ጋር ተኚ’ አለኝ። ‘ይህን ካላደረግኩ ቦታውን የማላገኝ ከሆነ ሥራውንም አልፈልግም’ አልኩ። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ እድገትና ሥራ የሚገኘው በዚህ መንገድ ነው። ሴቶች ለወንዶቹ ልቅ ፍትወት መንበርከክ ይኖርባቸዋል።

“በሌላ ጊዜ ደግሞ ለበሽተኞች ከፍተኛ ክትትል በሚደረግበት ክፍል ውስጥ ለአንድ በሽተኛ በደም ሥር የሚሰጠውን መድኃኒት ሳስተካክል አንድ ዶክተር ከኋላዬ መጥቶ መቀመጫዬን ቆነጠጠኝ። በጣም ተናድጄ ወደሚቀጥለው ክፍል ሮጥኩ። ተከትሎኝ መጣና የብልግና ቃል ተናገረኝ። ገፍትሬ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት ውስጥ ወረወርኩት! ከዚያም ወደ በሽተኛው ተመለስኩ። ከዚያ በኋላ አልደረሰብኝም!”

በካይሮ የጸሐፊነት ሥራ ትሠራ የነበረችው ሚርያም የተባለች ባለ ትዳር ግብጻዊት ሴት እስልምና በተስፋፋበት በግብጽ አገር የሚሠሩ ሴቶች የሚያጋጥማቸውን ሁኔታ እንዲህ ስትል ገልጻለች። “በዚህ አገር ሴቶች በምዕራባውያን ማኅበረሰብ ከሚኖሩ ሴቶች ይበልጥ ልከኛ ልብስ ይለብሳሉ። በሥራ ቦታዬ ወንዶች ሴቶችን በጾታ ሲዳፈሩ አልተመለከትኩም። ከምድር በታች በሚንቀሳቀሱ መጓጓዣዎች ግን በጾታ መዳፈር በጣም በመብዛቱ በመጀመሪያው ተሽከርካሪ ሴቶች ብቻ እንዲሳፈሩ ተደርጓል።”

በነርስነት ሞያ የ20 ዓመት ተሞክሮ ያላት፣ ዝምተኛና ቆራጥ የሆነችው ጄን እንዲህ ብላለች:- “በሥራ ቦታዬ ካሉት ወንዶች ከአንዱም ጋር ላለመቀጣጠር ቁርጥ ውሳኔ አደረግኩ። ቢሆንም ወንዶች ሐኪሞችም ሆኑ አስታማሚዎች እኔን ለመዳፈር መቃጣታቸው አልቀረም። ሁሉም በእኔ ላይ የሥነ ልቦና የበላይነት እንዳላቸው ያስቡ ነበር። እኛ ነርሶች ፍትወታቸውን እንዲያረኩ ‘ካልተባበርናቸው’ በሽተኛን አልጋ ላይ ማውጣትን የመሰሉ ጉልበት የሚጠይቁ ሥራዎችን በምንሠራበት ጊዜ ወንዶቹ አስታማሚዎች ብቅ አይሉልንም።”

ጄኒ ለሰባት ዓመታት የሕግ ጸሐፊ ሆና ሠርታለች። ከጠበቆች ጋር በምትሠራበት ጊዜ ያጋጠማትን ሁኔታ እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “አብዛኞቹ ወንዶች፣ ያገቡም ሆኑ ያላገቡ፣ ሴቶችን የሚመለከቱት እንደ መደሰቻ ነው። ‘ጠበቆች በመሆናችን በሴቶች መደሰት ልናገኝ ከሚገቡን መብቶች አንዱ ነው’ የሚል ዝንባሌ አላቸው።” ሌሎች የሞያ ሰዎችም ቢሆኑ ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አስተሳሰብ እንዳላቸው የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ። ይሁን እንጂ አንዲት ሴት ወንዶች እንዳይዳፈሯት ምን ልታደርግ ትችላለች?

በጸሐፊነትና በምግብ ቤት አስተናጋጅነት የምትሠራው ጥቁር አሜሪካዊቷ ዳርሊን እንዲህ ብላለች:- “በራሳችሁ ጠባይና አካሄድ ላይ ቁርጥ ያለ ድንበር ካላበጃችሁ ችግር ላይ መውደቃችሁ አይቀርም። አንድ ወንድ ሊቀልድባችሁ ቢጀምርና እናንተም ቀልዱን በቀልድ ብትመልሱ ሁኔታው በቀላሉ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይችላል። በተለያዩ ወቅቶች አቋሜን ግልጽ አድርጌ ለማሳወቅ ተገድጄአለሁ። ‘እንደነዚህ ባሉ ቃላት ባትናገረኝ ደስ ይለኛል’ እንደሚሉ ባሉ አነጋገሮች ተጠቅሜያለሁ። አንድ ጊዜ ‘ያገባሁ ሴት እንደመሆኔ ይህ የተናገርከው ቃል በጣም ያስቀይመኛል፣ ባለቤቴም ቢሆን የሚደሰትበት አይመስለኝም’ ብያለሁ።

“ዋናው ቁም ነገር መከበር ከፈለጋችሁ ክብር የሚገባችሁ ሆናችሁ መገኘት የሚኖርባችሁ መሆኑ ነው። ከወንዶች ጋር በአስነዋሪ ቀልዶችና በብልግና አነጋገሮች ለመተካከል የምትሞክር ሴት የወንዶችን አክብሮት ልታገኝ የምትችልበት መንገድ አይታየኝም። ተቀባይነት ባለውና በሌለው አነጋገርና ጠባይ መካከል ያለው ድንበር እንዲድበሰበስና በግልጽ እንዳይታይ ካደረጋችሁ ይህን ድንበር ለመተላለፍ የሚሞክር ሰው መኖሩ አይቀርም።”

እብሪተኛ ወንድ

የ14 ዓመት የሥራ ልምድ ያላት ኮኒ የተባለች ነርስ በማንኛውም የሥራ አካባቢ ሊያጋጥም ስለሚችል ጥቃት ትገልጻለች። “ከአንድ ዶክተር ጋር ለአንድ በሽተኛ የቁስል ፋሻ እቀይር ነበር። ዘወትር ከምሠራው ሥራ ምንም የተለየ ነገር አልነበረውም። የተማርኳቸውን የአሠራር ስልቶች በሙሉ በትክክል ተከትያለሁ። በሽታ እንዳይዛመት የሚደረጉትን የንጽሕና መንገዶችንና ሌሎችንም ጥንቃቄዎች በሙሉ አድርጌአለሁ። ይሁን እንጂ ለዚያ ሐኪም የማደርገው ሁሉ ሊጥመው አልቻለም። በጣም እየጮኸና እየተቆጣ እያንዳንዱን እንቅስቃሴዬን አጥላላብኝ። ይህ ዓይነቱ ሴቶችን የማቃለል ድርጊት በጣም የተለመደ ነው። አንዳንድ ወንዶች የበላይነት ስሜት ስለሚሰማቸው አብረዋቸው በሚሠሩ ሴቶች ላይ የበላይነታቸውንና ሥልጣናቸውን ለማሳየት የሚፈልጉ ይመስላል።”

ቀደም ብላ የተጠቀሰችው ሣራ በዚህ ረገድ ያጋጠማትንም ተሞክሮ አክላለች። “አንድን በሽተኛ ለኦፕራሲዮን በማዘጋጅበት ጊዜ የበሽተኛውን ሁኔታ የሚገልጹትን መዝገቦች ተመለከትኩ። የኢ ኬ ጄው [ኤሌክትሮካርዲዮግራም] ምርመራ ውጤት ኦፕራሲዮን ሊደረግለት በሚያስችል ሁኔታ ላይ የማይገኝ በሽተኛ መሆኑን በግልጽ ያመለክት ነበር። ይህንንም ኦፕራሲዮን ለሚያደርገው ሐኪም አስታወቅኩ። በጣም ተቆጥቶ ‘ነርሶች የሽንት ዕቃ መድፋት ነው እንጂ ስለ ኢ ኬ ጂ የሚያገባችሁ ነገር የለም’ አለኝ። በዚህ ጊዜ ለዋናው አኔስቴዝዮሎጂስት ሁኔታውን አስረዳሁ። እርሱም በሽተኛው በዚህ ሁኔታ እያለ ኦፕራሲዮን ከሚያደርገው ሐኪም ጋር እርሱም ሆነ የሥራ ባልደረቦቹ አብረውት እንደማይሠሩ ነገረው። ከዚህ በኋላ ኦፕራሲዮን የሚያደርገው ሐኪም ወደ በሽተኛው ሚስት ሄዶ የባልዋ ኦፕራሲዮን የዘገየው በእኔ ምክንያት እንደሆነ ነገራት! እንዲህ ባለው ሁኔታ አንዲት ሴት ልታሸንፍ የምትችልበት መንገድ የለም። ለምን? ምክንያቱም ሳታስቡት የወንዱን የበላይነት ስሜት ነክታችኋል።”

ሴቶች በሥራ ቦታቸው አዋራጅ ሁኔታና ጥቃት እንደሚደርስባቸው ግልጽ ነው። በሕግ ረገድስ የሚያጋጥማቸው ሁኔታ እንዴት ያለ ነው?

ሴቶችና ሕግ

በአንዳንድ አገሮች ሴቶች በተግባር ያልተገለጸ፣ በወረቀት ላይ ብቻ የሰፈረ እኩልነት ለማግኘት እንኳን የበርካታ መቶ ዘመናት ትግል ጠይቆባቸዋል። ወንድና ሴት እኩል መሆናቸውን የሚደነግጉ ሕግጋት ባሉባቸው አገሮች እንኳን በተጻፈው ሕግና ተግባር ላይ በማዋል መካከል ትልቅ ክፍተት ይታያል።

ዘ ወርልድስ ዉሜን— 1970–1990 የተባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ይህ ክፍተት [የመንግሥታት የፖሊሲ ክፍተት] በአብዛኛው የሚታየው ሴቶች የመሬት ባለቤት ለመሆን፣ ገንዘብ ለመበደርና ውል ለመዋዋል ባላቸው መብት ረገድ ከወንዶች ጋር እኩል እንዳይሆኑ በሚያግዱ ሕጎች ነው።” አንዲት ኡጋንዳዊት ሴት እንዲህ ብላለች:- “ሁለተኛ ደረጃ ዜጎች፣ እንዲያውም ወንዶች ልጆቻችን ስለሚበልጡን ሦስተኛ ደረጃ ዜጎች ሆነን እንኖራለን። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ አህዮችና ትራክተሮች ከእኛ የተሻለ አያያዝ ያገኛሉ።”

ሜን ኤንድ ዉሜን የተባለው የታይም–ላይፍ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “በ1920 የሴቶች የመምረጥ መብት በ19ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተረጋገጠ። ይህ የሆነው በብዙ የአውሮፓ አገሮች የሴቶች የመምረጥ መብት ከተረጋገጠ በኋላ ብዙ ቆይቶ ነው። በብሪታንያ ግን እስከ 1928 ድረስ (በጃፓን ደግሞ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በፊት) ይህ መብት ለሴቶች አልተሰጠም።” ኤሚሊ ዋይልዲንግ ዴቪሰን የተባሉት እንግሊዛዊት የሴቶች የመምረጥ መብት ተሟጋች በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ፖለቲካዊ አድልዎ ለመቃወም በ1913 በተደረገው የፈረስ ጉግስ ውድድር በንጉሡ ፈረስ ፊት ዘለው በመውደቅ ራሳቸውን ገድለዋል። ለሴቶች የመብት እኩልነት ራሳቸውን ሰማዕት አድርገዋል።

“ቫዮለንስ አጌንስት ዉሜን አክት” የተባለው ሕግ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የታየው በ1990 መሆኑ በወንዶች የበላይነት የሚመራው ሕግ ምን ያህል የሴቶችን ችግር ለመፍታት ዝግተኛ እንደሆነ ያሳያል።

ይህ በመላው ዓለም በሴቶች ላይ የሚደርሰውን መጥፎ ሁኔታ በአጭሩ ለመመልከት የቀረበው መግለጫ፣ ታዲያ ይህ ሁኔታ የሚሻሻልበት ጊዜ ይኖር ይሆንን? ሁኔታው እንዲለወጥ ምን ማድረግ ያስፈልጋል? ወደሚሉ ጥያቄዎች ይመራናል። የሚከተሉት ሁለት ርዕሶች እነዚህን ጥያቄዎች ያብራራሉ።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ከሁሉ የሚብሱት ችግረኞች እነማን ናቸው?

“የዓለምን ሁለት ሦስተኛ ሥራ የሚያከናውኑት ሴቶች ናቸው። ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን የአፍሪካና የእስያ እንዲሁም 40 በመቶ የሚሆነውን የላቲን አሜሪካ ቀለብ የሚያመርቱት ሴቶች ናቸው። ሆኖም ከጠቅላላው የዓለም ገቢ የሚያገኙት አንድ አሥረኛውን ብቻ ሲሆን የባለቤትነት መብት ያላቸው ከአንድ በመቶ ለሚያንሰው የዓለም ንብረት ነው። ከዓለም ድሆች የመጨረሻዎቹ ድሆች እነርሱ ናቸው።”— ሜይ ዩ ቢ ዘ ማዘር ኦቭ ኤ ሃንድረድ ሳንስ፣ በኤልዛቤት ቡሚለር

“[በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች] ንጹሕ የመጠጥ ውኃ በቅርብ ስለማይገኝ ትናንሽ ልጃገረዶች ትምህርት ቤት አይገቡም። . . . ለአቅመ ሔዋን የደረሱ ልጃገረዶች ከሃያ አንዳንዴም ከሠላሳ ኪሎ ሜትር ርቀት ውኃ ቀድተው ሲመጡ ተመልክቼአለሁ። ሙሉ ቀን የሚፈጅ ሥራ ነው። እነዚህ ልጃገረዶች ትምህርት ቤት ሳይገቡና ምንም ነገር ለመማር ሳይችሉ . . . አሥራ አራትና አሥራ አምስት ዓመት ዕድሜ ላይ ይደርሳሉ።”— ዣክ ኢቭ ኩስቶ፣ ዘ ዩኔስኮ ኩርየር፣ ኅዳር 1991

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጾታዊ ጥቃቶችን ታግሦ ማሳለፍ አይገባም

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ