በአፍሪካ የኤድስ መስፋፋት ለዓለም ማስጠንቀቂያ ነው!
“ለ6 ዓመታት በየዓመቱ 1 ፍቅረኛ ቢይዙና እነርሱም እንደዚሁ እያንዳንዳቸው ለ6 ዓመታት አንድ አንድ ፍቅረኛ ቢይዙ በመጨረሻው ከ45,000 ሰዎች ጋር የጾታ ንክኪ ይኖርዎታል ማለት ነው።” ኮንቲኒዊንግ ሜዲካል ኤጁኬሽን በተባለው የደቡብ አፍሪካ መጽሔት ላይ የተጠቀሰውና በዶክተር ኬ ኢ ሳፒር የተቀመረው ይህ ቀላል ስሌት ሴሰኛ የሆኑ ሰዎች ኤድስ ምን ያህል በቀላሉ ሊይዛቸው እንደሚችል የሚያሳይ ነው።
አፍሪካ የተተኮረባት ለምንድን ነው?
በአፍሪካ ውስጥ እየደረሰ ያለው ሁኔታ ለዓለም ማስጠንቀቂያ ስለሆነ ነው። ልቅ የጾታ ብልግና የተስፋፋው በአፍሪካ ብቻ አይደለም። በዓለም ዙሪያ ያለ ነገር ነው። “ውሎ አድሮ” ይላሉ የኤድስ ኤክስፐርት የሆኑት ዴኒስ ሲፍሪስ፤ “ከበርካታ ሰዎች ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈጽም ማንኛውም በዓለም ላይ ያለ ሰው ለበሽታው በእጅጉ የተጋለጠ ይሆናል።” በተመሳሳይም ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት የተባለው መጽሔት በገለጸው መሠረት በአሁኑ ጊዜ ካለው የሥነ ምግባር ዝቅጠት አኳያ ሌላው ቀርቶ “አንድ ሰው ትዳር ያለው መሆኑ ከተመሳሳይ ጾታ ጋርም ሆነ ከትዳር ጓደኛው ውጪ የጾታ ግንኙነት ከመፈጸም አያግደውም፤ በመሆኑም ኤድስን ሙሉ በሙሉ ሊመክት የሚችል ነገር የለም።”
ስለዚህ አፍሪካን አፌርስ የተባለው መጽሔት “ወረርሽኙ በየትኛውም ቦታ ሊዛመት ይችላል” የሚል ማስጠንቀቂያ የሰጠበት ጥሩ ምክንያት አለው። ሁኔታዎቹ በሚጠቁሙት መሠረት በአፍሪካ ላይ የደረሰው ቀውስ በሌሎች የዓለም ክፍሎችም ላይ የሚከሰት በሂደት ላይ ያለ ነገር ነው።
ለምሳሌ ያህል በብራዚል “ከተቃራኒ ጾታ ጋር ብቻ የጾታ ግንኙነት የሚፈጽሙ ቁጥራቸው ከፍ እያለ የመጣ ብዙ ሰዎች በበሽታው ከተለከፉ ፍቅረኞቻቸው ኤድስ ተላልፎባቸዋል” በማለት ኒውስዊክ መጽሔት ዘግቧል። የዚህች አገር የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ ግማሽ ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች በኤች አይ ቪ እንደተለከፉ ገምቷል። “ምንም ነገር ማድረግ ካልተቻለ በሕዝቡ ጤንነት ላይ መዓት ይወርዳል” በማለት በሪዮ ዲ ጃኔሮ በሚገኘው ጋፍሬ ኢ ጉንል ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ውስጥ የኤድስ ምርምር ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ካርሎስ አልቤርቶ ሞሬስ ዲ ሳ ተናግረዋል።
ዩናይትድ ስቴትስም አደጋ ላይ ወድቃለች። “ከተቃራኒ ጾታ ጋር ብቻ የጾታ ግንኙነት በሚፈጽሙ ሰዎች ላይ በሽታው የተከሰተው በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ ቢሆንም [በ1990] በአንድ ጊዜ 40 በመቶ እድገት አሳይቷል። ይህም ከሌሎቹ መተላለፊያ መንገዶች በበለጠ ፍጥነት አድጓል ማለት ነው” በማለት ታይም መጽሔት ዘግቧል። ዝነኛው አትሌት ማጂክ ጆንሰን ከተቃራኒ ጾታ ጋር በተፈጸመ የግብረ ሥጋ ግንኙነት በኤድስ እንደተያዘ ይፋ ከወጣ በኋላ በተከታዩ ሳምንት የሕክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከሎች የስልክ መስመሮቻቸው ስለ በሽታው ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው በሚወተውቱና በሁኔታው እጅግ በተሸበሩ ሰዎች ተይዘው ነበር።
እስያም በቅርቡ መዓት እንደሚወርድባት የሚጠቁሙ አስደንጋጭ ምልክቶችን እየሰጠች ነው። በዚህኛው የዓለም ክፍልም በ1988 ምንም የኤድስ በሽተኛ የለም ይባል ከነበረበት ሁኔታ ተነስቶ በአሁኑ ጊዜ በኤች አይ ቪ የተለከፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣት ከአንድ ሚልዮን በላይ ደርሰዋል! ዶክተር ጂም ማክደርሞት ስለ ሁኔታው በቂ መረጃ ለማሰባሰብ ወደ ስፍራው በመሄድ ተልዕኳቸውን አጠናቀው ከተመለሱ በኋላ ባቀረቡት ሪፖርት “በእስያ ካለው ሁኔታ ጋር ስናነጻጽረው በአፍሪካ የበሽታው ስርጭት አነስተኛ ነው ለማለት ያስደፍራል” ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም “ዓለም አቀፉ የኤድስ ወረርሽኝ በስፋት ስሩን ሰዶ የሚገኘው ለችግሩ ገና ባልነቃችው በእስያ ውስጥ እንደሆነ በሚገባ ማረጋገጥ ችያለሁ” ብለዋል።
ኤድስ የተነሳውና የተሰራጨው ከዚህ ነው ብሎ በየትኛውም አህጉር ወይም ብሔር ላይ ጣትን መቀሰሩ ፋይዳ ቢስና ትርጉም የሌለው ነው። ሚሺጋን ዩ ኤስ ኤ ውስጥ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ጤና ትምህርት ቤት ዲን የሆኑት ዶክተር ጁን ኦስቦርን “ቁም ነገሩ የአንተ ማንነት ሳይሆን የምታደርገው ነገር ነው” ሲሉ በግልጽ ተናግረዋል።
ኤድስ በየትኛውም ቦታ ሰውን እንደ ቅጠል እያረገፈ ይኖራልን? መፍትሔ ይገኝለት ይሆን? ወይስ በመጨረሻ የአፍሪካን አህጉር ሰፋፊ ቦታዎችና የተቀሩትን የዓለም ክፍሎች ሰው አልባ ያደርጋቸዋል?
[ምንጭ]
WHO photo by H. Anenden; background: NASA photo