ኤድስ የያዛቸውን ሰዎች መርዳት
“ቄሱ በኤድስ በመለከፋቸው ምክንያት በር ተዘጋባቸው” ይላል ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ የወጣ የአንድ ጽሑፍ ርዕስ። ጋዜጣው አንድ ሚስታቸውና ሁለት ልጆቻቸው በኤድስ ስለተያዙባቸው የባፕቲስት ቄስ ይተርካል። ሚስታቸው በበሽታው የተያዙት በ1982 በወሰዱት ደም ምክንያት ሲሆን ልጆቹ ግን የተለከፉት ማኅፀን ውስጥ እንደነበሩ ነው። እርሳቸውም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው በተለያዩ የባፕቲስት አብያተ ክርስቲያናት ለመገኘት ጥረት ቢያደርጉም በበሽታው ምክንያት ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በመጨረሻም ተስፋ በመቁረጥ ጥረታቸውንም ሆነ የባፕቲስት አገልጋይነት ሥራቸውን አቁመዋል።
እኚህ ሰው ቤተ ክርስቲያናቸው ተገቢውን እንክብካቤ ሳያደርግላቸው በመቅረቱ ምክንያት የደረሰባቸው ብስጭት በርካታ ጥያቄዎችን ያስነሳል:- አምላክ ለታመሙ ሰዎች፣ ኤድስ ለያዛቸው ሰዎች ጭምር ያስባልን? እነዚህስ ሕሙማን በምን መንገድ እርዳታ ሊሰጣቸው ይችላል? ኤድስ ለያዛቸው ሰዎች ክርስቲያናዊ ማጽናኛ በሚሰጥበት ጊዜ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል?
አምላክ ለሕሙማን ያለው ፍቅር
ሁሉን የሚችለው አምላክ መከራ ለሚደርስባቸው ሰዎች በጥልቅ እንደሚያስብ መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። ኢየሱስም በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ለታመሙ ሰዎች ልባዊ አዘኔታ አሳይቷል። አምላክም ከሕመማቸው ሁሉ እንዲፈውሳቸው የሚያስችል ኃይል ሰጥቶታል። መጽሐፍ ቅዱስ “ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፣ ዕውሮችንም፣ ዲዳዎችንም፣ ጉንድሾችንም፣ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ ቀረቡ፣ በኢየሱስም እግር አጠገብ ጣሉአቸው፣ ፈወሳቸውም” በማለት ይተርክልናል።— ማቴዎስ 15:30
እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ አምላክ ለኢየሱስ እንዳደረገው ሰዎችን በተአምር ለመፈወስ የሚያስችል ኃይል የሰጠው ሰው በምድር ላይ አይገኝም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ በሚቋቋመው የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ‘ታምሜአለሁ የሚል ሰው እንደማይኖር’ ይናገራል። (ኢሳይያስ 33:24) መጽሐፍ ቅዱስ “[አምላክ] እንባዎችን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” የሚል ተስፋ ይሰጠናል። (ራእይ 21:4) አምላክ ለሰው ልጆች ባለው ታላቅ ፍቅር ተነሳስቶ ሁሉንም በሽታዎች ኤድስን ጨምሮ፣ የሚያስወግድበትን ዘላቂ መፍትሔ አዘጋጅቷል።
መዝሙር 22:24 (የ1980 ትርጉም ) ስለ አምላክ እንዲህ ይላል:- “እርሱ ድኾችን አይንቅም፤ ሥቃያቸውንም ቸል አይልም፤ ከእነርሱ አይርቅም፤ ወደ እርሱ በሚጮኹበትም ጊዜ ይሰማቸዋል።” የአምላክ ፍቅር ከልባቸው ወደ እርሱ ለሚጮኹ ሁሉ ክፍት ነው።
በኤድስ ቫይረስ የሚለከፉት እንዴት ያሉ ሰዎች ናቸው?
ኤድስ በአብዛኛው ሰዎች በሚከተሉት የተሳሳተ የአኗኗር መንገድ ምክንያት የሚመጣ በሽታ ነው። በዚህ በሽታ ከተለከፉት ሰዎች አብዛኞቹ “ከኃጢአታቸውና ከበደላቸው ብዛት የተነሣ ሥቃይ ደረሰባቸው፣ እንደሞኞችም ተቆጠሩ” የሚለው የመዝሙር 107:17 (የ1980 ትርጉም ) ቃል እንደደረሰባቸው ያምናሉ።
አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን ሕግጋት ተላልፎ አምላክ ከፈቀደው የጋብቻ ዝግጅት ውጭ የጾታ ግንኙነት ሲፈጽም በኤድስ በሽታ ለመለከፍ ወይም በሽታውን ወደ ሌሎች ለማስተላለፍ አደጋ ይጋለጣል። በተጨማሪም ግለሰቦች በአንድ መርፌ ተጠቅመው አደንዛዥ ዕፆችን በደም ሥራቸው ሲወጉ በኤድስ በሽታ ሊለከፉ ወይም በሽታውን ለሌሎች ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ከዚህም በላይ ብዙዎች በኤድስ የተለከፉ ሰዎች ከለገሱት ደም በበሽታው ተይዘዋል።
ይሁን እንጂ ቁጥራቸው በቀላሉ የማይገመት ንጹሐን ሰዎች በተለያዩ መንገዶች በኤድስ ቫይረስ በመለከፍ ላይ መሆናቸው በጣም የሚያሳዝን ነው። ለምሳሌ ያህል ብዙ ታማኝ ባለ ትዳሮች ምንም ጥፋት ሳይሠሩ በኤድስ ከተለከፉ የትዳር ጓደኞቻቸው ጋር የጾታ ግንኙነት በመፈጸማቸው ብቻ በበሽታው በመያዝ ላይ ናቸው። በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ቁጥራቸው በአስደንጋጭ ደረጃ እየጨመረ የሄደ ጨቅላ ሕፃናት የኤድስ ቫይረሶችን ከእናቶቻቸው በመውረስ ላይ ናቸው። በዚህም ምክንያት ጨቅላ ሕፃናት ከኤድስ ሰለባዎች መካከል በጣም አሳዛኞቹ ተጠቂዎች ሆነዋል። በተጨማሪም የሕክምና ሠራተኞችና ሌሎች ሳያስቡት በድንገት በበሽታው ከተለከፈ ደም ጋር በመነካካታቸው ምክንያት በበሽታው ተይዘዋል።
ማንም ሰው በምንም ዓይነት መንገድ በበሽታው ቢለከፍ ለዚህ ቀሳፊ በሽታ መተላለፍና መዛመት አምላክ በኃላፊነት ሊጠየቅ እንደማይችል ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ ያመለክታሉ። በዛሬው ጊዜ በኤድስ በሽታ ከተለከፉት ሰዎች አብዛኞቹ በሽታውን በራሳቸው ላይ ያመጡና ከመጽሐፍ ቅዱስ ሕግጋት በሚቃረኑ ድርጊቶቻቸው ሌሎች ሰዎችን የመረዙ ቢሆንም ከራሳቸው ጥፋት ውጭ በሆኑ ምክንያቶች የሚለከፉት ንጹሐን ሕፃናትና ታማኝ ባለትዳሮች ቁጥር እያደር እየጨመረ መጥቷል።
የዓለም ጤና ድርጅት በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም የሚኖሩ ሴቶች ከወንዶች ባላነሰ መጠን በኤድስ ቫይረስ በመያዝ ላይ እንደሆኑና በ2000 ዓመት አብዛኞቹ አዳዲስ የኤድስ ተጠቂዎች ሴቶች እንደሚሆኑ ተናግሯል። በአፍሪካ የሚገኙ የጤና ባለሞያዎች በዚህች አሕጉር በኤድስ ከሚያዙት ሰዎች 80 በመቶ የሚያክሉት “ከተቃራኒ ጾታ ጋር በተፈጸመ ሩካቤ ሥጋ የተጋባባቸው ሲሆኑ የቀሩት በሙሉ ማለት ይቻላል፣ በእርግዝና ወይም በመውለድ ወቅት ከእናት ወደ ልጅ የተጋባባቸው” እንደሆኑ ይገልጻሉ።
ይሁን እንጂ አምላክ መጣሳቸው እንደነዚህ ያሉትን ሥቃዮች የሚያስከትሉትን ሕጎች ጨምሮ፣ ሕጎቹ በሙሉ እንዳይጣሱ የሚከለክል ቢሆንም በዚህ ምክንያት ችግር ላይ ለወደቁ ሁሉ የምሕረት እጁን ለመዘርጋት ዝግጁ ነው። በራሳቸው የተሳሳተ ድርጊት ምክንያት በኤድስ የተያዙ ሰዎች እንኳን ንስሐ በመግባትና ክፉ የሆነውን ነገር ማድረጋቸውን በማቆም ከአምላክ ምሕረት ሊጠቀሙ ይችላሉ።— ኢሳይያስ 1:18፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9–11
በአሁኑ ጊዜ የሚታወቀው ነገር ምንድን ነው?
ኤድስ መላውን ምድር ያዳረሰ የጤና ችግር ነው። ሳይንቲስቶች “ኤች አይ ቪ በቀላሉ የማይዛመት ቫይረስ” መሆኑን ደጋግመው ቢያረጋግጡም ይህ አባባላቸው በአሁኑ ጊዜ በበሽታው ተይዘው ለሚገኙት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም ሆነ በመጪዎቹ ዓመታት ለሚያዙት ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሰዎች ምንም ዓይነት ፋይዳ ሊኖረው አይችልም። በመላው ምድር ላይ በሽታው እንዳይዛመት መግታት አልተቻለም።
አንድ ባለ ሥልጣን በሽታው የሚዛመትባቸውን የተለመዱ መንገዶች ሲገልጹ “አብዛኛውን ጊዜ የኤች አይ ቪ ኢንፌክሽኖች የሚተላለፉት በወሲባዊ ንኪኪ ወይም ለተመረዘ ደም በመጋለጥ ነው” ብለዋል። አንድ ሪፖርት ደግሞ አብዛኞቹ የጤና ባለሞያዎች የደረሱበትን ድምዳሜ በማንጸባረቅ “ኢንፌክሽን የሚኖረው በበሽታው ከተመረዘ ሰው የሚወጣ ፈሳሽ (ሁልጊዜ ደም ወይም የዘር ፈሳሽ ማለት ይቻላል) ገና በበሽታው ወዳልተለከፈ ውስጣዊ አካል ሲገባ ነው” ይላል።
ይሁን እንጂ “አብዛኛውን ጊዜ” እና “ማለት ይቻላል” የሚሉት ሐረጎች ከዚህ የሚለዩ ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያመለክታል። ስለዚህ የኤድስ በሽታ ከሚተላለፍባቸው መንገዶች አብዛኞቹ በአሁኑ ጊዜ በሕክምና ዘርፍ በተሰማሩ ባለሞያዎች የታወቁ ቢሆኑም በጣም አነስተኛ የሆኑ ገና ያልታወቁ የመዛመቻ መንገዶች ሊኖሩ ይችላሉ። ስለዚህ አሁንም ጠንቃቃ መሆን አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።
እንዴት ይሰማችኋል?
እስከ አሁን ድረስ በመላው ዓለም ላይ ከ12 ሚልዮን እስከ 14 ሚልዮን የሚደርሱ ሰዎች በኤድስ ቫይረስ ተለክፈዋል። እስከዚህ መቶ ዘመን መጨረሻ ድረስ ሌሎች በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚለከፉም ይገመታል። ስለዚህ አሁንም ሆነ ወደፊት በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር መገናኘታችሁ አይቀርም። ለምሳሌ ያህል፣ በማንኛውም ትልቅ ከተማ የሚኖር ሰው በሥራ ቦታ፣ በምግብ ቤቶች፣ በቲያትር ቤቶች፣ በስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ በአውቶቡሶች፣ ከምድር በታች መጓጓዣዎች፣ በአውሮፕላኖችና በባቡሮች እንዲሁም በሌሎች የሕዝብ መሰብሰቢያዎች ኤድስ ከያዘው ሰው ጋር መገናኘቱ አይቀርም።
ስለዚህ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለመገኘትና ራሳቸውን ለአምላክ እስከ መወሰን የሚያደርስ መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ከሚፈልጉ የኤድስ ሕሙማን ጋር የመገናኘታቸውና እነርሱንም ለመርዳት የመገፋፋታቸው አጋጣሚ እየጨመረ መሄዱ አይቀርም። ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ ፍላጎት ያላቸው የኤድስ ሕሙማን ሲያጋጥሟቸው ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ለበሽተኛውም ሆነ ለክርስቲያን ጉባኤ አባሎች ጥቅም ሊያስገኙ የሚችሉና ተግባራዊ የሆኑ ጥንቃቄዎች ይኖራሉን?
እስከ አሁን ድረስ በተደረሰው ግንዛቤ መሠረት ተራ የሆነ ንኪኪ የኤድስን በሽታ አያስተላልፍም። ስለዚህ ማንም ቢሆን ኤድስ በያዛቸው ሰዎች አካባቢ መገኘት ሊያስፈራው አይገባም ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ይመስላል። በተጨማሪም የኤድስ በሽተኞች በሽታ የመከላከል ኃይላቸው በጣም የተዳከመ ስለሆነ ምናልባት እኛ ያሉብንን የተለመዱት የቫይረስ በሽታዎች እንዳናጋባባቸው መጠንቀቅ ይገባናል። እንደነዚህ ያሉት የተለመዱ በሽታዎች በሰውነታቸው ላይ ትልቅ ጉዳት ሊያስከትሉባቸው ይችላል።
ኤድስ በባሕርዩ ሕይወት አጥፊ በመሆኑ ምክንያት ከአንድ የኤድስ በሽተኛ ጋር በምንቀራረብበት ወይም ግለሰቡን በክርስቲያን ጉባኤ በምንቀበልበት ጊዜ አንዳንድ ምክንያታዊ ጥንቃቄዎችን ማድረግ ጥበብ ይሆናል። በመጀመሪያ ደረጃ ለመላው ጉባኤ ማስታወቂያ መናገር አስፈላጊ ባይሆንም ስለ ሁኔታው ለሚጠይቁ ሁሉ ተገቢውን መልስ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት እንዲደረግ በጉባኤው ውስጥ ለሚገኝ ሽማግሌ ለማሳወቅ እንፈልግ ይሆናል።
ቫይረሱ በበሽታው በተመረዘ ደም አማካኝነት ሊተላለፍ ስለሚችል ጉባኤዎች የማረፊያ ክፍሎችንና ከሰውነት የወጡ ፈሳሾችን፣ በተለይ ደም የተቀላቀለባቸውን ፈሳሾች በሚያጸዱበት ጊዜ አጠቃላይ የሆነ የሐይጂን ጥንቃቄ ቢያደርጉ ምክንያታዊ ይሆናል። “አጠቃላይ የሆነ የሐይጂን ጥንቃቄ” የሚለው ቃል የሕክምናው ዓለም የማንም ሰው ደም አደገኛና በበሽታ የተለከፈ እንደሆነ ተቆጥሮ በተለየ ሁኔታ እንዲያዝ የሚያዘውን ሕግ ለማመልከት የሚጠቀምበት ቃል ነው። የመንግሥት አዳራሽ የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታ በመሆኑ አደጋ ቢፈጠር ተገቢውን ጽዳትና ጥንቃቄ ለማድረግ እንዲቻል ንጹሕ የእጅ ጓንትና የንጽሕና ቁሳቁሶችን አዘጋጅቶ ማስቀመጥ ጥበብ ይሆናል። የተንጠባጠበ ደም ለማጽዳት 10 በመቶ ኃይል ያለው በረኪና (ክሎሮክስ) በቂ ይሆናል።
ክርስቲያኖች ከማንኛውም ሰው ጋር፣ ከኤድስ ሕመምተኛ ጋር ጭምር በሚኖረን ግንኙነት ሁሉ የኢየሱስን አርዓያ እንድንከተል ተመክረናል። ኢየሱስ አምላክን ለማስደሰት ልባዊ ፍላጎት ለነበራቸው ሕመምተኞች ያሳየውን ርህራሄ መቅዳት ይኖርብናል። (ከማቴዎስ 9:35–38ና ከማርቆስ 1:40, 41 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ኤድስ ምንም ዓይነት መድኃኒት ያልተገኘለት በሽታ በመሆኑ አንድ ክርስቲያን በበሽታው የተያዘ ሰው በአዛኝነት በሚረዳበት ጊዜ ምክንያታዊ የሆነ ጥንቃቄ ቢያደርግ ተገቢ ነው።— ምሳሌ 14:15
የኤድስ ሕሙማንም የበኩላቸውን እርዳታ ሊያበረክቱ ይችላሉ
አንድ አስተዋይ የሆነ የኤድስ ታማሚ ሌሎች ሰዎች ለዚህ በሽታ ከፍተኛ ፍራቻ እንዳላቸው ይገነዘባል። በዚህም ምክንያት አንድ የኤድስ ታማሚ ሊረዱት የሚፈልጉትን ሰዎች ስሜት በማክበር እንደ ማቀፍና መሳም ከመሰሉት የአደባባይ ፍቅር መግለጫዎች ቢጠበቅ ጥሩ ይሆናል። እንደነዚህ ያሉት አድራጎቶች ኤድስን የሚያስፋፉበት መንገድ በጣም አነስተኛ ወይም ፈጽሞ የሌለ ቢሆንም በሽተኛው በዚህ ረገድ ራሱን መግታቱ ለሌሎች አሳቢነት እንዳለው ያሳያል። ይህ ደግሞ ሌሎችም ተመሳሳይ አሳቢነት እንዲያሳዩት ይገፋፋቸዋል።a
አንድ በኤድስ የተያዘ ሰው ሌሎች ወደ ግል ቤታቸው እንደማይጋብዙት ወይም ወላጆች ልጆቻቸው እንዳይቀርቡት እንደሚከለክሉ ቢገነዘብ ብዙዎች ስለ በሽታው ገና ያልታወቁት ነገሮች እንደሚያስፈሯቸው ተገንዝቦ እነርሱን ከመቀየም መጠበቅ ይኖርበታል። በተጨማሪም በመንግሥት አዳራሹ የሚደረግ የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ከኖረ የኤድስ ሕመምተኛው ከቤቱ ባለቤት ጋር ስለሁኔታው ካልተነጋገረ በስተቀር በግል ቤት ከሚደረጉት ይልቅ በዚህ በመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው መጽሐፍ ጥናት ቢገኝ ጥሩ ይሆናል።
የኤድስ ቫይረስ ተሸካሚዎችም ቢሆኑ ለምሳሌ ያህል አክታ በሚኖራቸውና የሳንባ ነቀርሳ እንደያዛቸው በሚታወቅበት ጊዜ ለሌሎች አሳቢነት ማሳየት ይገባቸዋል። በዚህ ጊዜ እንደነዚህ ባሉ በሽታዎች የተያዙ ሰዎች መከተል የሚገባቸውን ራስን የማግለል የጤና ሕጎች መጠበቅ ይኖርባቸዋል።
አንድ ንጹሕ ሰው በበሽታው ሊለከፍ የሚችልበት ሌላ ሁኔታ ደግሞ በኤድስ ቫይረስ እንደተለከፈ ከማያውቅ ሰው ጋር መጋባት ነው። በተለይ ከሁለቱ ተጋቢዎች መካከል አንዱ ወይም ሁለቱ ትክክለኛውን የአምላክ ቃል እውቀት ከማግኘታቸው በፊት የዝሙት ኑሮ ይኖሩ ከነበረ ወይም በመርፌ በመጠቀም አደንዛዥ ዕፅ ይወስዱ ከነበረ በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ይሆናል። የኤድስ በሽታ ምልክቶች ገና ያልታዩባቸው የኤች አይ ቪ ተሸካሚዎች ቁጥር በጣም እየበዛ በመምጣቱ አንድ ግለሰብ ወይም አሳቢ የሆኑ ወላጆች ከጋብቻ ወይም ከመተጫጨት በፊት የኤድስ ምርመራ እንዲደረግ ቢጠይቁ ከአግባብ ውጭ አይሆንም። ይህ በሽታ ቀሳፊ በመሆኑ ምክንያት የትዳር ጓደኛ እንዲሆን የታጨው ሰው የኤድስ ምርመራ እንዲያደርግ በመጠየቁ ምክንያት መቀየም አይኖርበትም።
ምርመራው በበሽታው የተለከፈ መሆኑን የሚያረጋግጥ ከሆነና ጤነኛው ወገን መተጫጨቱ ወይም መጠናናቱ በዚሁ እንዲያበቃ ከወሰነ በበሽታው የተመረዘው ወገን እንዲቀጥል ተጽእኖ ማድረግ አይገባውም። እንዲያውም ከዚህ በፊት በዝሙት አኗኗሩ ወይም አደንዛዥ ዕፆችን በደም ሥር በመውሰዱ ምክንያት ራሱን ለዚህ አደጋ አጋልጦ የቆየ ከሆነ መጠናናት ከመጀመራቸው በፊት በራሱ ፈቃድ ተነሳስቶ ምርመራ ቢያደርግ ጥሩ ይሆናል። በዚህ ምክንያት የሚፈጠረውንም የስሜት መጎዳት ማስወገድ ይቻላል።
ስለዚህ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በኤድስ ለተያዙ ሰዎች ርህራሄ እናሳያለን እንጂ ፈጽሞ አንሸሻቸውም፤ ይሁን እንጂ የተለያዩ ግለሰቦች በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኖራቸው ስሜት ሊለያይ እንደሚችል መገንዘብ ይኖርብናል። (ገላትያ 6:5) ሰዎች እንደ ኤድስ ከመሰለው ገና ብዙ ነገር ያልታወቀለትና አሠቃቂ የሆነ በሽታ ለመሸሽ መፈለጋቸው የሚጠበቅ ነገር ነው። በዚህ ረገድ ሊኖረን የሚገባው ሚዛናዊ አመለካከት የኤድስ ሕሙማንን በጉባኤዎቻችን በመቀበልና ለእነርሱም ፍቅርና ሞቅ ያለ መንፈስ በማሳየት መቀጠል መሆን ይኖርበታል። እንዲህም ሲባል ራሳችንንም ሆነ ቤተሰቦቻችንን ከበሽታው ለመጠበቅ ምክንያታዊ የሆኑ ጥንቃቄዎች ማድረጋችንን መተው አይኖርብንም።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በኤድስ እንደተያዘ የሚያውቅ አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር ለመሆንና ለመጠመቅ በሚፈልግበት ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርበታል? ኤድስ የመዋኛ ገንዳዎችን በጋራ በመጠቀም እንደተጋባ የሚያመለክት ማስረጃ እስከ አሁን ያልተገኘ ቢሆንም ለሌሎች ስሜት በማሰብ ብቻውን እንዲጠመቅ ቢጠይቅ ጥሩ ይሆናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ብዙ ክርስቲያኖች ሕዝብ በተሰበሰበባቸው ቦታዎች የተጠመቁ ቢሆንም በተለያዩ ሁኔታዎች ምክንያት ብቻቸውን የተጠመቁም ነበሩ። (ሥራ 2:38–41፤ 8:34–38፤ 9:17, 18) ሌላው አማራጭ ደግሞ በኤድስ የተያዘው ሰው መጨረሻ ላይ እንዲጠመቅ ማድረግ ይሆናል።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከልቤ አዘንኩላት
አንድ ቀን ሕዝባዊ አገልግሎቴን በማከናውንበት ጊዜ 20 ዓመት የሚሆናት ወጣት ሴት አነጋገርኩ። ትላልቅ ቡናማ ዓይኖቿ እንባ አቅርረው ነበር። ስለ አምላክ መንግሥት ውይይት ለመክፈት አስቤ በእጄ ከያዝኳቸው ትራክቶች አንዱን ሰጠኋት። አለምንም ማመንታት ለተጨነቁ ሰዎች የሚሆን መጽናኛ የተባለውን ትራክት መረጠች። ትራክቱን ከተመለከተች በኋላ ወደ እኔ ዞር ብላ ደከም ባለ ድምፅ “በቅርቡ እህቴ በኤድስ በሽታ ሞተች” አለችኝ። የሚያሳዝን ነገር መሆኑን ተናግሬ ሳልጨርስ “እኔም በኤድስ የምሞትበት ቀን ቀርቧል። ሁለት ትናንሽ ልጆች አሉኝ” አለች።
ከልቤ አዘንኩላትና አምላክ ለሰው ልጅ ቃል ስለገባው የወደፊት ተስፋ ከመጽሐፍ ቅዱስ አነበብኩላት። “አምላክ አንድም ቀን እንኳን አስቤው ለማላውቀው ለእኔ ለምን ያስባል?” አለችኝ። መጽሐፍ ቅዱስን ብታጠና አምላክ ከልቡ የሚጸጸተውንና በእርሱና በልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚታመነውን ማንኛውም ሰው በደስታ እንደሚቀበል ልትረዳ እንደምትችል ነገርኳት። “እናንተ እነማን እንደሆናችሁ አውቃለሁ። ከመንገዱ በታች ባለው የመንግሥት አዳራሽ የምትሰበሰቡት ሰዎች ናችሁ። እንደ እኔ ያለውን ሰው በመንግሥት አዳራሻችሁ ትቀበላላችሁ?” ስትል መለሰችልኝ። በደስታ እንደምንቀበላት አረጋገጥኩላት።
በመጨረሻም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን መጽሐፍና ትራክትዋን ይዛ መንገድዋን ስትቀጥል ‘ከአምላክ ብቻ ሊገኝ የሚችለውን መጽናኛ ታገኛለች’ ብዬ አሰብኩ።