ጠብ ቤተሰብን ሲያናጋ
“ጥፊም ሆነ መገፍተር፣ በጩቤ መውጋትም ሆነ ተኩሶ መግደል በኅብረተሰባችን ውስጥ ከማንኛውም አካባቢ ይበልጥ ጠብ የሚታይበት ቦታ የቤተሰብ ክልል ነው።”—ቢሃይንድ ክሎዝድ ዶርስ
በአሜሪካ በማንኛውም አካባቢ ከሁለት ቤቶች መካከል በአንዱ ቢያንስ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ጠብ አይጠፋም። ከአራት ቤቶች መካከል በአንዱ ደግሞ በተደጋጋሚ ጠብ ይከሰታል። ከጨለመ በኋላ በጎዳና ላይ መጓዝ የሚፈሩ በርካታ ሰዎች ከጎዳና ላይ ይልቅ የከፋ አደጋ የሚጠብቃቸው እገዛ ቤታቸው ውስጥ መሆኑ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው።
ይሁን እንጂ በቤተሰብ ክልል ውስጥ የሚነሳ ጠብ በአሜሪካ ብቻ የተወሰነ አይደለም። በመላው ዓለም ያለ ነገር ነው። ለምሳሌ ያህል በዴንማርክ ከ3 ግድያዎች መካከል ሁለቱ የሚፈጸሙት በቤተሰብ ውስጥ ነው። በአፍሪካ ውስጥ የተደረገ ጥናት እንደሚጠቁመው ከጠቅላላ ነፍስ ግድያዎች መካከል፣ መጠኑ ከአገር ወደ አገር የተለያየ ቢሆንም፣ ከ22 እስከ 63 በመቶ የሚሆኑት ግድያዎች የሚፈጸሙት በቤተሰብ ውስጥ ነው። በላቲን አሜሪካም ብዙ ሰዎች፣ በተለይም ሴቶች ትምክህተኛ በሆኑ ወንዶች ዝቅ ተደርገው ይታያሉ፣ ይደበደባሉ እንዲሁም ይገደላሉ።
በካናዳ በየዓመቱ አንድ መቶ የሚያክሉ ሴቶች በባሎቻቸው ወይም አለ ሕጋዊ ጋብቻ አብረዋቸው በሚኖሩ ወንዶች እጅ ሕይወታቸው ያልፋል። ከካናዳ በአሥር እጥፍ የሚበልጥ የሕዝብ ብዛት ባላት ዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ 4,000 የሚያክሉ ሴቶች ጠበኛ በሆኑ ባሎቻቸው ወይም በወንድ ጓደኞቻቸው ይገደላሉ። ከዚህም በላይ በየዓመቱ 2,000 የሚያክሉ ልጆች በወላጆቻቸው የሚገደሉ ሲሆን ያንኑ የሚያክል ቁጥር ያላቸው ወላጆች ደግሞ በልጆቻቸው ይገደላሉ።
አዎን፣ በመላው ዓለም ባሎች ሚስቶቻቸውን ይደበድባሉ፣ ሚስቶች ባሎቻቸውን ይማታሉ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ይደበድባሉ፣ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ እንዲሁም ልጆች እርስ በርሳቸው ይደባደባሉ። ዌን ፋሚሊስ ፋይት የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “ሙሉ ዕድሜ ላይ የደረሱ ሰዎች በመላ ሕይወታቸው በጣም የሚያናድድ ነገርና አምባጓሮ የገጠማቸው ከሥጋ ዘመዶቻቸው ነው። በዚህ ጊዜ የተሰማቸው ንዴት በማንኛውም ሌላ ግንኙነት ካጋጠሟቸው ሁሉ የከፋ ነው።”
እርስ በርስ የሚፋጅ ቤተሰብ
በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈጸም በደል:- ብዙ ጊዜ ባሎች የጋብቻ የምሥክር ወረቀታቸውን ሚስቶቻቸውን ለመደብደብ እንደሚያስችላቸው የፈቃድ ወረቀት አድርገው ይቆጥሩታል። ወንዶችን የሚማቱ ሴቶች ቢኖሩም በወንዶቹ ላይ የሚደርሰው ጉዳት አብዛኛውን ጊዜ ወንዶች ሚስቶቻቸውን በሚደበድቡበት ጊዜ የሚደርሰውን ያህል የከፋ አይሆንም። ፓረንትስ የተባለው መጽሔት እንደዘገበው “በትዳር ጓደኞች ላይ እንደ ደረሱ ሪፖርት ከተደረጉት ከባድ ጥቃቶች መካከል 95 በመቶ የሚሆነው ወንዶች ሴቶችን በመደብደባቸው ምክንያት የደረሰ ነው።”
የኒው ዮርክ ክፍለ ሐገር አቃቤ ሕግ ሹም “በሴቶች ላይ የሚፈጸም የኃይል ድርጊት በአሜሪካውያን ኅብረተሰብ ውስጥ እንደ ወረርሽኝ ተስፋፍቷል። . . . በየዓመቱ 6 ሚልዮን የሚደርሱ ሴቶች እንደሚደበደቡ ኤፍ ቢ አይ ገምቷል” ብለዋል። መጠኑ ከአገር ወደ አገር ይለያይ እንጂ፣ ወንዶች በሴቶች ላይ የሚሰነዝሩት ዱላ፣ በሁሉም አገሮች ለማለት ባይቻልም በአብዛኛዎቹ አገሮች እንደ ወረርሽኝ እየተዛመተ ነው።
በዩናይትድ ስቴትስ “ከ10 ሴቶች መካከል አንዷ በጋብቻዋ ዘመን ውስጥ ከባሏ ከባድ ጥቃት (ዱላ፣ ጥፊ፣ እርግጫ ወይም ከዚያ የከፋ) እንደሚደርስባት” ይገመታል። ቀለል ያሉት ጥቃቶች ከታከሉ “በዩናይትድ ስቴትስ ከሁለት ሴቶች መካከል በአንዷ ላይ የኃይል ድርጊት ይፈጸማል” በማለት ፋሚሊ ሪሌሽንስ የተባለው መጽሔት ዘግቧል።
እንዲያውም አንድ የኒው ዮርክ አቃቤ ሕግ ሹም “በባሎቻቸው በመደብደባቸው ምክንያት ሆስፒታል እስከመግባት የሚያደርስ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች ቁጥር ተገድደው በመደፈር፣ በዘረፋና በመኪና አደጋ ምክንያት ጉዳት ከሚደርስባቸው እንደሚበልጥ” ተናግረዋል።
ዶክተር ሎይስ ጂ ሊቭዚ “በሴቶችና በቤተሰብ አባሎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት በጣም የተስፋፋ ከመሆኑም በላይ ይህን ወንጀል የሚፈጽሙት . . . ተራ የሆኑ ሰዎች ናቸው። . . . መደብና ዘር የማይለይ መላውን ሕዝብ ያጠቃለለ ችግር ነው።”
የኃይል ድርጊት የተፈጸመባቸው ሰዎች ለተፈጸመው ድርጊት ራሳቸው ምክንያት እንደሆኑ ስለሚቆጥሩ ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅተኛ ይሆናል። ፓረንትስ የተባለው መጽሔት እንደሚያብራራው “በራሷ የማትተማመንና ራሷን ዝቅ አድርጋ የምትመለከት ሴት ራሷን ለጥቃት ዒላማ አድርጋ ታቀርባለች። . . . የጉልበት ጥቃት የሚፈጸምባት ሴት ለራሷ የሚበጅ እቅድ ማውጣትና መሥራት ያስፈራታል።”
በባልና ሚስት መካከል የሚፈጠር አምባጓሮ በልጆችም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል። በኃይል ተጠቅሞ ሌሎችን እንደፈለጉ መቆጣጠር እንደሚቻል ይማራሉ። እንዲያውም ልጆቻቸው እንዲህ ካላደረግሽልኝ “አባዬ እንዲመታሽ አደርጋለሁ” ብለው እንደሚያስፈራሯቸው የሚናገሩ እናቶች አሉ።
በልጆች ላይ የሚፈጸም በደል:- በየዓመቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ልጆች ከባድ ጉዳት፣ የአካል ጉድለት ወይም ሞት የሚያስከትል ኃይለኛ ቅጣት ይፈጸምባቸዋል። ከሚፈጸሙት 200 ጥቃቶች መካከል ሪፖርት የሚደረገው አንድ ብቻ እንደሆነ ይገመታል። ሶሺኦሎጂ ኦቭ ማሬጅ ኤንድ ዘ ፋሚሊ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ከሆነ “ብዙውን ጊዜ ለልጆች ከማንኛውም ቦታ ይበልጥ አደገኛ የሚሆንባቸው የገዛ ቤታቸው ነው።”
የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆን ኢ ቤትስ አንድ ልጅ በወደፊት ሕይወቱ በሚያሳየው ባሕርይ ላይ ኃይለኛ ተጽእኖ ከሚያሳድሩ የቤተሰብ ሁኔታዎች አንዱ በልጅነቱ የሚፈጸምበት በደል እንደሆነ” ተናግረዋል። ዶክተር ሱዛን ፎርዋርድ ደግሞ “ልጆች አድገው ትልቅ ሰው ሲሆኑ ለራሳቸው በሚኖራቸው ግምት ላይ በቀላሉ የማይሽር ጠባሳ የሚተውና የስሜት ቀውስም የሚያስከትል እንደዚህ የከፋ የሕይወት ገጠመኝ የለም” ብለዋል። ከአራት እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ላይ በሚገኙ በአስቸጋሪ ሁኔታ ያደጉ ልጆች ላይ እንኳን የጠበኝነት ባሕርያት ሊታዩ ችለዋል። እንደነዚህ ያሉት ልጆች ሲያድጉ ዕፅ ወሳጆች፣ ሰካራሞች፣ ወንጀለኞች፣ ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ያለባቸው የመሆንና አዝጋሚ እድገት የማሳየት ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ ይሆናል።
በደል የሚፈጸምባቸው ልጆች በደል በፈጸመባቸው ወላጅ ላይ ቂም መያዛቸው የሚጠበቅ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ በደሉ ሲፈጸም ዝም ብሎ በመመልከቱ በደል ባልፈጸመባቸው ወላጅ ላይም ቂም ይይዛሉ። ድርጊቱን በዝምታ የተመለከተው ወላጅ በሕፃኑ አእምሮ ውስጥ የድርጊቱ ተባባሪ ሆኖ ይታያል።
በአረጋውያን ላይ የሚፈጸም በደል:- በካናዳ 15 በመቶ የሚሆኑ አረጋውያን በዕድሜ ትልልቅ የሆኑ ልጆቻቸው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት እንደሚፈጽሙባቸው ይገመታል። አንድ ዶክተር እንደተነበዩት “ይህ ሁኔታ የአረጋውያን ቁጥር እየጨመረና በልጆቻቸው ላይ የሚወድቀው የገንዘብና የስሜት ሸክም እየከበደ በሄደ መጠን እየተባባሰ መሄዱ የማይቀር ነው።” ይህ ዓይነቱ ሥጋት በመላው ዓለም እየጨመረ ሄዷል።
ብዙውን ጊዜ አረጋውያን የሚፈጸምባቸውን በደል ለመናገር አይፈልጉም። በደል የሚፈጽምባቸው የሚያስተዳድራቸው ሰው ሊሆን ስለሚችል የሚደርስባቸውን ግፍ ችለው ይኖራሉ። አንዲት አሮጊት ልጅዋንና ምራትዋን ለባለ ሥልጣኖች የምታጋልጠው መቼ እንደሆነ ስትጠየቅ “ሌላ ጊዜ” የሚል መልስ ሰጥታለች። በጣም ስለ ደበደቧት ለአንድ ወር ያህል ሆስፒታል ለመቆየት ተገድዳ ነበር።
በወንድማማቾችና በእህትማማቾች መካከል የሚፈጸም ጥቃት:- ይህ በጣም ተስፋፍቶ የሚገኝ በቤተሰብ መሃል የሚከሰት ጠብ ነው። አንዳንዶች “ወንዶች ምንጊዜም ወንዶች ናቸው” በማለት ሁኔታውን ያቃልላሉ። ይሁን እንጂ በአንድ ጥናት በተገኘ መረጃ መሠረት ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ልጆች በወንድማቸው ወይም በእህታቸው ላይ የፈጸሙት ወንጀል ከቤተሰባቸው ውጪ በሆነ ሰው ላይ ቢፈጽሙ ኖሮ በወንጀል ሊያስከስሳቸው የሚችል ድርጊት ነበር።
ብዙዎች በወንድም ወይም በእህት ላይ የሚፈጸም በደል ካደጉም በኋላ የማይለቅ ጠባይ እንደሚሆን ያምናሉ። በአንዳንዶች ላይ እንደታየው በትዳር ጓደኛቸው ላይ በደል እንዲፈጽሙ የበለጠ ምክንያት የሆናቸው በወላጆቻቸው መካከል የሚፈጸመውን ጠብ መመልከታቸው ሳይሆን ከወንድማቸው ወይም ከእህታቸው ጋር ሲደባደቡ ያደጉ መሆናቸው ነው።
አደገኛ የሆነ የጦርነት አውድማ
አንድ የሕግ ነክ ጉዳዮች ተመራማሪ የቤተሰብ ግጭት ፖሊሶች ለገላጋይነት ከሚጠሩባቸው ሌሎች የግጭት ዓይነቶች ሁሉ እንደሚበልጥ ገምተዋል። በተጨማሪም ሌላ አይነት ግጭቶችን ሲገላግሉ ከተገደሉት ፖሊሶች ይልቅ በቤተሰብ መካከል የተነሳውን ጠብ ሲገላግሉ የተገደሉት ፖሊሶች እንደሚበልጡ ተናግረዋል። አንድ ፖሊስ “ዘረፋ ከሆነ ቢያንስ ተዘጋጅተህ መሄድህ አይቀርም። አንድ ሰው ቤት ስትገባ ግን ምን ሊያጋጥምህ እንደሚችል ፈጽሞ አታውቅም” ብሏል።
አንድ የምርምር ቡድን በቤተሰብ መሃል ስለሚፈጸም ጠብ ሰፊ ጥናት ካደረገ በኋላ ከውጊያ አውድማ ሌላ የቤተሰብን ያህል የኃይል ድርጊት የሚፈጸምበት የማኅበረሰብ ክልል እንደሌለ ደምድሟል።
በቤተሰብ ውስጥ ጠብ እንዲኖር የሚያደርገው ምንድን ነው? እንዲህ ያለው ድርጊት የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? የኃይል ድርጊት ተገቢ ሊሆን የሚችልበት ምክንያት ይኖር ይሆን? የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች ይመረምራል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“በሴቶች ላይ የሚፈጸም የኃይል ድርጊት በአሜሪካውያን ኅብረተሰብ ውስጥ እንደ ወረርሽኝ ተስፋፍቷል።”—የክፍለ ሐገር አቃቤ ሕግ ሹም
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ብዙውን ጊዜ ለልጆች ከማንኛውም ቦታ ይበልጥ አደገኛ የሚሆንባቸው የገዛ ቤታቸው ነው።”—ሶሺኦሎጂ ኦቭ ማሬጅ ኤንድ ዘ ፋምሊ