የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 5/8 ገጽ 25-29
  • ብቸኛ ብሆንም ሕይወቴ ከንቱ አልነበረም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ብቸኛ ብሆንም ሕይወቴ ከንቱ አልነበረም
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ስለ ይሖዋ መማር
  • በስፔይን በኩል ወደ ታይላንድ
  • ወደ አውስትራሊያ
  • ወደ ቡገንቪል
  • ወደ አፍሪካ
  • በደቡብ አሜሪካ
  • ወደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ
  • ከጉባኤ ጋር መሥራት
  • ይሖዋን ማገልገል የዕድሜ ልክ ሥራዬ እንዲሆን መረጥኩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
  • በይሖዋ ማዕድ ላይ መቀመጥ በጣም ያስደስታል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • “እነሆኝ! እኛን ላኩን!”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
  • ትክክለኛውን የሕይወት ጎዳና በመምረጤ ደስተኛ ነኝ
    የይሖዋ ምሥክሮች የሕይወት ታሪኮች
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 5/8 ገጽ 25-29

ብቸኛ ብሆንም ሕይወቴ ከንቱ አልነበረም

የተወለድኩት በጥር ወር 1927፣ በስፔይን አገር በማላጋ ሲሆን ድሃ ለሆኑት ካቶሊክ ወላጆቼ ከሰባት ልጆቻቸው ስድስተኛዋ ነበርኩ። ከ1936 እስከ 1939 ባሉት ዓመታት አገራችን በእርስ በርስ ጦርነት ፈራርሳ ነበር። ከፈንጂዎች እየሸሸንና በራሽን ይሰጠን የነበረውን ምግብ ብቻ እየተቃመስን እንኖር ነበር። ቢሆንም መዝፈንና ከሰዎች ጋር መጫወት የምወድ ደስተኛ ልጅ ነበርኩ።

ይሁን እንጂ አንድ ነገር በጣም ያስፈራኝ ነበር። እርሱም በሲኦል እሳት መቃጠል ነው። ይህ ፍርሃቴ ጋብ እንዲልልኝ ገና በ12 ዓመት ዕድሜዬ ገዳም ገባሁ። በዚህ ገዳም ሦስት ዓመት ለሚያህል ጊዜ የደረጃውን ዕብነ በረድ በተደጋጋሚ እየወለወልኩና እየጸለይኩ ብቆይም አንድ የጎደለኝ ነገር እንዳለ ይሰማኝ ነበር። በ1941 ከገዳም ለመውጣት በመቻሌ ደስ አለኝ።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከአንዲት ዘፋኝ ጋር ወዳጅነት መሠረትኩ፤ ይህች ጓደኛዬ ድምፄ ገንዘብ ሊያስገኝልኝ እንደሚችል ስላሰበች ፒያኖና የአዘፋፈን ስልት አስተማረችኝ። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1945 እንዳለቀ ወደ ሞሮኮ ሄድኩና በካዛብላንካና በታንጅር ከተሞች በሚገኙ የምሽት ክበቦች መዝፈን ጀመርኩ። ይህ ዓይነቱ ሕይወት ለአንዲት ወጣት ሴት በጣም የሚያስደስት ነበር። ሆኖም ትርዒት ባሳየሁ ቁጥር ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄጄ ድንግል ማርያም ይቅር እንድትለኝና ከሲኦል እሳት እንድታድነኝ እጸልይ ነበር።

ለዘጠኝ ዓመታት ያህል በምሽት ክበቦች ከሠራሁ በኋላ ጃክ አበርናቲ ከሚባል አሜሪካዊ ጋር ተገናኘሁ። በዚያ ጊዜ በሞሮኮ ለአንድ የአሜሪካ የግንባታ ኩባንያ ይሠራ ነበር። በዚያው ዓመት ተጋባንና የዘፋኝነት ሥራዬን አቆምኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ወደ ስፔይን፣ ሴቪል ተዛወርንና እስከ 1960 ድረስ በዚያ ኖርን። ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ሎዲ፣ ካሊፎርንያ፣ ዩ ኤስ ኤ ተዛወርን። ይህ ዝውውር በሕይወቴ ላጋጠመኝ ትልቅ ለውጥ መንገድ ጠራጊ ሆነ።

ስለ ይሖዋ መማር

በ1961 ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን መጥተው መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ትተውልን ሄዱ። በኋላም አብሬያቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንዳጠና ጠየቁኝና ፈቃደኛ ሆንኩ። በዚህ መንገድ እውነተኛ አምላክ ስለሆነው ስለ አፍቃሪው የሰማዩ አባታችን ስለ ይሖዋ ለመማር ቻልኩ። (መዝሙር 83:18) እሳታማ ሲኦል አለመኖሩንና ይልቁንም ገነት በምትሆን ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዳለን ማወቅ መቻል እንዴት ያለ እፎይታ ነው!—መዝሙር 37:9-11, 29፤ ራእይ 21:3, 4

በአቅራቢያችን ትኖር የነበረችው እህቴ ፓኪታም ጥናት ጀመረች። ከዚህ ቀደም ትንባሆ አጨስ የነበረ ከመሆኑም በላይ ወደ ፓርቲዎች መሄድ እወድ ነበር። ከመጠን በላይ ብስጩና ግልፍተኛ ነበርኩ። ይሁን እንጂ ለውጥ ማድረግ ጀመርኩና ጥቅምት 17 ቀን 1962 እኔና ፓኪታ በሳክራሜንቶ፣ ካሊፎርንያ ራሳችንን ለይሖዋ አገልግሎት መወሰናችንን ለማሳየት ተጠመቅን።

በስፔይን በኩል ወደ ታይላንድ

ከዚህ ብዙም ሳይቆይ ባለቤቴን የሚሠራበት የግንባታ ኩባንያ ወደ ታይላንድ ስላዛወረው አብሬው ሄድኩ። እግረ መንገዴን ወደ ስፔይን ሄድኩና እምነቴን ለሌሎች የቤተሰቤ አባሎች ለማካፈል ቻልኩ። የወንድሜ ባለቤት የሆነችው ፑራ ምሥራቹን ተቀበለችና ምሥክር ሆነች።

በዚያ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በስፔይን ታግዶ ነበር። ቢሆንም አንድ ጠረጴዛ ብቻ ባለበትና አንዳችም ወንበር በሌለበት ትንሽ ክፍል በድብቅ እንሰበሰብ ነበር። ሃያዎቻችንም እንቆም ነበር። በካሊፎርኒያ እናደርጋቸው ከነበሩት ስብሰባዎች በጣም የተለየ ነበር። ወገኖቼ ለመሰብሰብ ሲሉ እንዴት ራሳቸውን ለእስራት እንደሚያጋልጡ መመልከቴ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ አረጋገጠልኝ። ባንኮክ፣ ታይላንድ ከመድረሴ በፊት ይህን ትምህርት ማግኘቴ በጣም ወቅታዊ ነበር።

ባንኮክ በደረስንበት ቀን ጃክ “ከዛሬ ጀምሮ ስትሰብኪ ባገኝሽ እንለያያለን” አለኝ። በማግስቱ በገጠር አካባቢ ይከናወን የነበረውን የግንባታ ሥራ ለመቆጣጠር ስለሄደ ግርግር በሚበዛበት የባንኮክ ከተማ ላነጋግራት ከማልችል አንዲት የቤት ሠራተኛ ጋር ብቻዬን ቀረሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎቼን ደግሜ፣ ደጋግሜ በማጥናት ራሴን በሥራ ለማስጠመድ ሞከርኩ።

አንድ ቀን በመስከረም ወር 1963 ወደ ቤቴ ስመለስ በሬ ላይ ከዚህ በፊት አይቼ የማላውቀው ጥንድ ጫማ አየሁ። አንዲት ወርቅማ ፀጉር ያላት ሴት ትጠብቀኝ ነበር። “ምን ልርዳሽ?” ስል ጠየቅኳት።

“የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ወኪል ነኝ” አለችኝ።

በጣም ከመደሰቴ የተነሳ ዘልዬ እቅፍ አድርጌ ሳምኳት። ኢቫ ሂበርት ከካናዳ የመጣች ሚሲዮናዊ ናት። ከዚያ ቀን ጀምሮ ኢቫ ሁለትና ሦስት አውቶቡስ ቀያይራ እየመጣች ትጠይቀኝ ጀመር። እኔ ግን ሰዎች እንደ ሰርዲን ታጭቀው በሚሄዱበት አውቶቡስ ላይ መውጣት ያስፈራኝ ነበር። ይሁን እንጂ ከቦታ ወደ ቦታ ልጓጓዝ የምችልበት ሌላ መንገድ አልነበረም። ኢቫ “በእነዚህ አውቶቡሶች እስካልተጠቀምሽ ድረስ ፈጽሞ ይሖዋን ልታገለግይ አትችይም” አለችኝ። ወደ ስብሰባ ቦታ የሚወስደኝን አውቶቡስ እንዴት እንደምሳፈር ተለማመድን።

ቋንቋውን ስለማላውቅ መስበክ ያስፈራኝ ነበር። የኢቫን እጅ፣ ቅርጫትና ቀሚስ ሙጭጭ አድርጌ ይዤ እከተላታለሁ። “እንዲህ ሆነሽ ይሖዋን ልታገለግይ አትችይም” አለችኝ።

“ቋንቋውን ስለማልችል እኮ ነው” ስል መለስኩላት።

ኢቫ አሥር መጽሔቶች ሰጠችኝና ገበያ መሐል ጥላኝ ጠፋች። በፍርሃት እየተንቀጠቀጥኩ ወደ አንዲት ቻይናዊት ሴት ጠጋ አልኩና መጽሔቶቹን አሳየኋት፣ ተቀበለች።

ኢቫን ሳገኛት “አሥሩንም መጽሔቶች አበረከትኩ” ስል ደስታዬን ገለጽኩላት። “ይሖዋ እንዳንቺ ያሉትን ሰዎች ይወዳል፤ ብቻ ቀጥይ” አለችኝ። በዚሁ ቀጠልኩና በታይ ቋንቋ ሰላምታ መስጠትና በአካባቢው ባሕል መሠረት ወለል ላይ መቀመጥ ተማርኩ። በተጨማሪም ከቦታ ቦታ መዘዋወር ቻልኩ። ታዲያ ባለቤቴ ምን ተሰማው? ስለ እምነቴ የለሰለሰ አቋም ይዞ የነበረው ባለቤቴ አንድ ቀን እንግዶች ሲመጡበት “ከፔፒታ ጋር ሆናችሁ አገሩን ጎብኙ። ስለምትሰብክ መውጫ መግቢያውን ሁሉ ታውቃለች” አላቸው።

ወደ አውስትራሊያ

ኢቫ የሰጠችኝ ጠንካራና ፍቅራዊ ሥልጠና ባለቤቴ ቀጥሎ በተዛወረበት በሰሜን ምዕራብ አውስትራሊያ በይሖዋ አገልግሎት ንቁ ሆኜ እንድቀጥል ረድቶኛል። እዚያ የደረስነው በ1965 አጋማሽ ላይ ሲሆን የጃክ ኩባንያ የባቡር ሐዲድ ጥርጊያ ያዘጋጅ በነበረበት በረሐ ውስጥ በሚገኝ የሥራ ካምፕ መኖር ጀመርኩ። ምግብ የሚመጣልን በአውሮፕላን ሲሆን ሙቀቱ እስከ 43 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል። በካምፑ ውስጥ 21 የሚያክሉ የሰሜን አሜሪካ ቤተሰቦች ስለነበሩ የመንግሥቱን ምሥራች ለእነዚህ ቤተሰቦች መናገር ጀመርኩ። በኋላም የሐዲዱ ጥርጊያ ሥራ እየቀጠለ ሲሄድ ሰው ወደሌለበት ይበልጥ በረሃማ ወደሆነ አካባቢ ተዛወርን።

ቀደም ሲል በአውስትራሊያ ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ደብዳቤ ጽፌ ስለነበር “ሞቅ ያለ ፍቅራችንና ሰላምታችን ይድረስሽ . . . በሚቀጥሉት ወራት በሙሉ በአሳባችንና በጸሎታችን እናስታውስሻለን” የሚል ደብዳቤ ሲደርሰኝ ምን ያህል ደስ እንዳለኝ ልትገምቱ ትችላላችሁ! ባለቤቴ ለሥራ በተመደበባቸው ራቅ ያሉ የምድር ክፍሎች በተዘዋወርኩባቸው ጊዜያት ሁሉ እንደነዚህ ባሉት ከይሖዋ ድርጅት የሚላኩልኝ ደብዳቤዎች በጣም ተጽናንቻለሁ። አነዚህን ደብዳቤዎች ማንበቤ አልፎ አልፎ የሚሰማኝን የብቸኝነት ስሜት እንድቋቋምና በአጠገቤ አንድም ምሥክር ባይኖርም በስብከቱ ሥራ እንድሰማራ አበረታቶኛል።

የአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ ምሥክሮች የሆኑ አንድ ባልና ሚስት ካምፑ ድረስ መጥተው ለአንድ ሳምንት ያህል ጉብኝት እንዲያደርጉልኝ ዝግጅት አደረገልኝ። በአገልግሎታችን ወቅት በጣም ሩቅ በሆነ አካባቢ የምትኖር ፍላጎት ያላት ሴት አገኘን። በሳምንት ሁለት ቀን እባቦችና እንሽላሊቶች በሚርመሰመሱበት አካባቢ በእግር እየተጓዝኩ ወደዚህች ሴት እሄድ ነበር። በእግሬ በምጓዝበት ጊዜ ጮክ ብዬ “ከይሖዋ ጎን ቁም፣ በሱም ተደሰት። ከቶ አይተውህም በጎዳናው ሂድ” የሚለውን የመንግሥት መዝሙር እዘምር ነበር። ከዚህች ሴት ጋር ለ11 ወራት አጠናን።

ከዚያም አንድ ዓመት ለሚያክል ጊዜ ሜልቦርን ከቆየን በኋላ ከባለቤቴ ጋር አሁንም በአውስትራሊያ ሰሜናዊ ምዕራብ ወደሚገኝ ፖርት ሄድላንድ የሚባል የማዕድን ከተማ ተዛወርን። ከአምስት ቀናት በኋላ የሚጎበኙን ሰዎች መጡ። ቅርንጫፍ ቢሮው ወደዚያ መዛወሬን ነግሯቸው ነበር። ከሄዱ በኋላ ብቻዬን ስብሰባዎችን ማካሄድ ቀጠልኩ። የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት፣ የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት፣ የአገልግሎት ስብሰባና የመጠበቂያ ግንብ ጥናት እመራለሁ። መዝሙር ከዘመርኩና በጸሎት ከከፈትኩ በኋላ ጥያቄዎቹን መልሼ ስጨርስ በመዝሙርና በጸሎት እደመድማለሁ። ተሰብሳቢዎቹን መቁጠር አይቸግረኝም ነበር። ምክንያቱም ሁልጊዜ የሚኖረው አንድ ተሰብሳቢ ብቻ ነው። ቢሆንም ይህ የሳምንታዊ ስብሰባዎች ፕሮግራም ይሖዋን ብቻዬን ባገለገልኩባቸው በርካታ ዓመታት ሁሉ ጠንክሬ እንድቆም አስችሎኛል።

ወደ ቡገንቪል

ለአምስት ዓመታት በአውስትራሊያ በረሐ ስንቃጠል ከቆየን በኋላ በ1969 ባለቤቴ በቡገንቪል ደሴት እርጥበት አዘል አየር ባለባቸው ተራሮች ወደ መዳብ ማዕድን ማውጫ የሚወስድ የአንድ መንገድ ሥራ ፕሮጀክት ፎርማን ሆኖ ተመደበ። አንድ ቀን ምሽት የቤታችን በር ተንኳኳ። ጃክ ከፈተ። “አንድ ምሥክር ከሚስቱና ከአራት ልጆቹ ጋር መጥቷል” አለኝ። በባሕሩ ዳርቻ አካባቢ የሚኖሩ ናቸው። በሳምንት አንድ ጊዜ እየሄድኩ እጠይቃቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ በአካባቢው በሚገኝ ትምህርት ቤት በሚደረግ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ እገኝ ነበር።

በሌላ ወቅት ደግሞ በፓፑዋ ኒው ጊኒ የሚኖሩ ሦስት ምሥክሮች ጎበኙኝ። ባለቤቴ ኩራት እየተሰማው “ባለቤቴ የትም አገር ብትሄድ የይሖዋ ምሥክር ወዳጆቿ ይጠብቋታል” ሲል ለሥራ ባልደረቦቹ ተናገረ።

ወደ አፍሪካ

በ1972 የጃክ ኩባንያ የመስኖ ፕሮጀክት ሥራ ወደ ጀመረበት ወደ ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ወደ አልጀርያ በረሃማ ቦታ ተቀየርን። ለአራት ዓመት የሚቆይ ፕሮጀክት ነበር። በፈረንሣይ አገር ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ስለ ስብከቱ ሥራ ደብዳቤ ጻፍኩና ‘በጣም ጥንቃቄ ማድረግ አለብሽ፣ ሥራችን በዚህ አገር ታግዷል’ ሲሉ ጻፉልኝ። ማኅበሩ አገልግሎት ካቆሙ ሁለት ምሥክሮች ጋር እንድገናኝ አስቻለኝና የጥናት ቡድን አቋቋምን።

በዚህ ጊዜ በካምፓችን ውስጥ ከሚኖሩት ጎረቤቶቼ አንዷ የሆነችው ሲሲልያ ታመመች። በየቀኑ ወደ ሆስፒታል ሾርባ እየወሰድኩ እጠይቃትና አልጋዋን አነጥፍላት ነበር። ወደ ቤትዋ ከተመለሰች በኋላም እላላካትና የመንግሥቱን ተስፋ እነግራት ጀመር። በዚህ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርኩላት። ከስምንት ወራት በኋላ ሲሲልያ “መጠመቅ እፈልጋለሁ” አለች። ግን የትና በማን ትጠመቅ?

ፍራንስዋ የሚባል ምሥክር ለአጭር እረፍት ወደ አልጀርያ እንደሚመጣ የሚገልጽ ደብዳቤ ፈረንሣይ ከሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ደረሰን። በረሃ ውስጥ ወደሚገኘው መንደራችን ልናመጣውና ወደ አውሮፕላን ማረፊያው በሰዓቱ ልንመልሰው ከቻልን የጥምቀቱን ሥርዓት እንደሚያከናውንልን ተነገረን። ከ24 ሰዓት በላይ ግን ሊቆይ አይችልም።

ፍራንስዋ እንደ ደረሰ ወዲያው ወደነበርንበት በረሃ በመኪና እንዲመጣ ተደረገ። በዚያው ምሽት በሲሲልያ ቤት ከሸሚዙ ኪስ ውስጥ ትንሽ የማስታወሻ ወረቀት አውጥቶ በጣም ግሩም የሆነ ንግግር ሰጠ። ግንቦት 18, 1974 ማለዳ ላይ በእኔ ቤት በሚገኘው የመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ሲሲልያን ካጠመቃት በኋላ ተመልሶ ሄደ።

በ1975 መጨረሻ ላይ በአልጀርያ ጦርነት ስለተጀመረ እኔና ጃክ በድንገት ለቀን ለመውጣት ተገደድን። በስፔይን የሚገኙትን ዘመዶቼን ጠየቅኩ። በ1976 ጃክ ወደ ተመደበበት በደቡብ አሜሪካ በሱሪናም ጥቅጥቅ ያለ ደን ውስጥ ወደሚገኘው የሥራ ካምፕ ለመጓዝ ጓዜን ጠቅልዬ ተነሳሁ።

በደቡብ አሜሪካ

በሱሪናም ደቡባዊ ምዕራብ የሚገኘው የሠራተኞች ሠፈር ጥቅጥቅ ባለ ደን የተከበበ ነበር። ጯሂ ፓሮቶችና ተጠራጣሪ ዝንጀሮዎች ከዛፎች ላይ ሆነው 15 የምንሆነውን እንግዳ ቤተሰቦች ይመለከቱናል። ከእነዚህ ቤተሰቦች አብዛኞቹ ከዚህ ቀደም አንድ ላይ የነበርን በመሆናችን የማውቃቸው ናቸው። ከስድስት ወር በኋላ በአልጀርያ የተጠመቀችውን ሲሲልያን ጨምሮ ሌሎች ተጨማሪ የሠራተኞች ቤተሰቦች መጡ። የአገልግሎት ጓደኛ አገኘሁ ማለት ነው!

መጋቢት 23, 1978 እየቀረበ ሲመጣ የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ እንዴት እንደምናከብር ማሰብ ጀመርን። ወደ ዋና ከተማው ወደ ፓራማሪቦ የሚወስድ መጓጓዣ ስለሌለን እኔው ቤት ውስጥ ለማክበር አሰብን። የካምፑ ሥራ አስኪያጅ የመታሰቢያው ቀን ማስታወቂያ የወጣበትን መጠበቂያ ግንብ የመጨረሻ ገጽ ፎቶ ኮፒ እንድናነሳ ፈቅዶልን በካምፑ ውስጥ ከቤት ወደ ቤት እየሄድን አሰራጨነው። ሀያ አንድ ሰዎች ተገኙ! ንግግሩን ያቀረበችው ሲሲልያ ስትሆን እኔ ደግሞ ጥቅሶቹን አነበብኩ። በዚያች ምሽት ብቻችንን ብንሆንም ዓለም አቀፋዊ ከሆነው የይሖዋ ድርጅት ጋር አንድ እንደሆንን ተሰማን።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሱሪናም የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እርዳታ ላከልን። ሚስዮናውያን የሆኑ ወጣት ባልና ሚስት በአንድ አሮጌ ላንድ ሮቨር መጡ። ከመምጣታቸው በፊት ምንም ዋጋ የሌለኝ ሰው እንደሆንኩ ሊሰማኝ ጀምሮ ነበር። ሚስዮናውያኑ ግን “ፔፒታ፣ እዚህ የመጣሽው ለአንድ ዓላማ ነው” ሲሉ አረጋገጡልኝ። በወቅቱ አባባላቸውን ባላምንም በኋላ ግን ትክክል መሆናቸውን ተረዳሁ።

ከዕለታት አንድ ቀን በሚስዮናውያኑ ጉብኝት ወቅት አዲስ የተጠረገ የአፈር መንገድ አገኘን። ከካምፓችን 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የአሜሪካ ሕንዶች መንደር መኖሩን ስንመለከት በጣም ደስ አለን። በእነዚህ ሰው ወዳድ የሆኑ የአራዋክ ሕንዶች መካከል ያከናወንነው የጥቂት ቀናት ስብከት በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አስገኘልን። ስለዚህም ሚስዮናውያኑ ከተመለሱ በኋላ ሲሲልያና እኔ በሳምንት ሁለት ቀን ወደነዚህ ሰዎች መሄድ ጀመርን።

ማለዳ በአሥር ሰዓት እንወጣና አንድ ሰዓት ሲሆን የመጀመሪያ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን እንጀምራለን። ከሰዓት በኋላ 11 ሰዓት ገደማ ላይ ቤታችን እንመለሳለን። ለሁለት ዓመታት ያህል በየሳምንቱ 30 ጥናቶች መራን። ብዙም ሳይቆይ የመንደሩ ሕፃናት አክስቴ መጽሐፍ ቅዱስ እያሉ ይጠሩኝ ጀመር! ከጊዜ በኋላ ብዙዎቹ የተጠመቁ ሲሆን ከዓመታት በኋላ በዚያው መንደር በተደረገ የወረዳ ስብሰባ ላይ 182 ሰዎች ተገኝተዋል። በእርግጥም ውድ ሚስዮናውያን ጓደኞቼ እንዳሉት በዚያ ጫካ ውስጥ የኖርነው ለአንድ ዓላማ ነበር!

ወደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ

በ1980 ሱሪናምን ለቅቀን በሚቀጥለው ዓመት ወደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ተላክን። በዋና ከተማይቱ በፖርት ሞረስቢ ከምሥክሮች ጋር አስደሳች የሆኑ ስድስት ወራት ካሳለፍን በኋላ በሄሊኮፕተር ተሳፍሬ የጃክ ኩባንያ የወርቅ ማዕድን ሥራ ወደሚያከናውንበት ተራራማ አካባቢ ሄድኩ። መንገድ የሚባል አልነበረም። ሰዎች፣ መሣሪያና ምግብ የሚጓጓዙት በአየር ነበር። በእንዲህ ያለ ፍጹም ገለልተኛ በሆነ አካባቢ ኖሬ አላውቅም። አሁንም እንደገና የማነጋግራቸው ሰዎች የት ላገኝ እችላለሁ? ብዬ አሰብኩ።

በካምፑ ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ቀደም ብለው የሚያውቁኝ ስለሆኑ ሊያዳምጡኝ አይፈልጉም። ይሁን እንጂ በዚሁ ጊዜ አካባቢ ኩባንያው አንድ ግሮሰሪ ከፈተ። ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶች እየመጡ ዕቃዎችን ይሸምቱ ነበር። ወዲያው ሱቁን ከሚያዘወትሩ ሰዎች አንዷ ሆንኩ። ታዲያ ተሳካልኝ?

አንድ ቀን ከአንዲት የፓፑዋ ሴት ጋር ውይይት ጀመርኩ። አስተማሪ እንደሆነች ነገረችኝ። “እኔም እኮ አስተማሪ ነኝ” አልኳት።

“ኧረ! ነሽ እንዴ?” ስትል ጠየቀችኝ።

“አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምራለሁ” አልኳት። ወዲያው መጽሐፍ ቅዱስ ላስጠናት እንደምችል ያቀረብኩላትን ጥያቄ ተቀበለች። ቆየት ብሎም ወደ ግሮሰሪው የሚመጡ ሌሎች ተጨማሪ ሴቶች መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማሙ። ይህ በወርቅ ማዕድን ማውጫ አጠገብ የተመሠረተው መንደር ሰባት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አስገኝቷል። በእርግጥም ጥሩ የመንፈሳዊ ወርቅ ማዕድን ማውጫ ነበር!

በዚህች የፓስፊክ ደሴት ሦስት ዓመታት ካሳለፍን በኋላ ለአዲስ ሥራ የካሪብያን ደሴት ወደ ሆነችው ወደ ግሬናዳ ተላክን። ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ግን ባለቤቴ በጤንነት ችግር ምክንያት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመመለስ ተገደደ። በዚህም ምክንያት በ1986 በቧስ፣ አይዳሆ መኖር ጀመርን።

ከጉባኤ ጋር መሥራት

እነዚህን ሁሉ ዓመታት ከክርስቲያን ወንድሞቼና እህቶቼ ተነጥዬ ስለኖርኩ አሁን ከሌሎች ጋር እንዴት እንደምሠራ መማር አስፈልጎኝ ነበር። ይሁን እንጂ ክርስቲያን ሽማግሌዎችና ሌሎች በትዕግሥት ረድተውኛል። በአሁኑ ጊዜ ባለሁበት በዚህ የምድር ክፍል በስብሰባዎች ላይ በመገኘትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በመምራት ላይ ነኝ።

ይሁን እንጂ ብቻዬን ቁጭ ብዬ በማስብበት ጊዜ ግርግር በሚበዛበት በባንኮክ ከተማ ከኢቫ ኋላ ኋላ ስሮጥ ወይም በአውስትራሊያ በሚገኘው የበረሐ መንገድ የመንግሥቱን መዝሙር ጮክ ብዬ ስዘምር ወይም ደግሞ በሱሪናም ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች ውስጥ ትሁታን ለሆኑት የአሜሪካ ሕንዶች ስሰብክ በድጋሚ ይታየኝና ይሖዋን በብቸኝነት ባገለገልኩባቸው በርካታ ዓመታት ለተደረገልኝ እንክብካቤ ልቤ በምሥጋና ተሞልቶ ዓይኖቼ የደስታ እንባ ያቀርራሉ።—ዦሴፋ ‘ፔፒታ’ አበርናቲ እንደተናገረችው

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሜልቦርን ከስፓኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቼ ጋር ስዘምር

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በፓፑዋ ኒው ጊኒ ብዙዎች ይሖዋን እንዲያውቁ ረድቻለሁ

በሱሪናም የአምላክን ቃል ማስተማር

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ በአይዳሆ ከሚገኝ ጉባኤ ጋር በማገልገል ላይ ነኝ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ