የወጣቶች ጥያቄ . . .
የማዳምጠው ሙዚቃ በእርግጥ ሊጎዳኝ ይችላልን?
ቶም ሙሉ ጤና ያለው የ14 ዓመት ልጅ ነበር። ጎረቤቶቹን መርዳት ደስ የሚለው ጎበዝ ተማሪም ነበር። በጣም ውድ የሆነ የስቴሪዮ ማጫወቻ ከገዛ በኋላ ግን የሄቪ ሜታል ዘፈኖችን ማዳመጥ ጀመረ።
ቶም በመኝታ ክፍሉ ውስጥ ተዘግቶ ዘፈን ሲያዳምጥ የሚውል ልጅ ሆነ። አባቱ “ሁልጊዜ እዚያ ተወሽቀህ ስቴሪዮህን ስታዳምጥ መዋል አትችልም” ይለው እንደነበረ ያስታውሳል። ይሁን እንጂ ቶም ዘፈኖቹን ማዳመጡን ቀጠለ። ከዚያም በክረምት ወራት አንድ ቀን እናቱን በጩቤ ወግቶ ከገደላት በኋላ ራሱን ደግሞ ገደለ። በኀዘን የተዋጠው የቶም አባት “ልጆቻቸው ምን ዓይነት ዘፈን እንደሚያዳምጡ እንዲከታተሏቸው ለወላጆች ንገሯቸው” በማለት ያስጠነቅቃል። ግድያውን ከመፈጸሙ በፊት ቶም በተደጋጋሚ ስለ “ደም ማፍሰስና እናት ስለ መግደል” የሚገልጽ ዘፈን ደጋግሞ ይዘፍን ነበር።
ይህ ከስንት አንድ ብቻ የሚያጋጥም ነገር ነውን? አዎን፣ ነው። ለዚህ አሠቃቂ ድርጊት አስተዋጽኦ ያደረጉ ሌሎች ነገሮች እንደነበሩ የማያጠራጥር ቢሆንም ብዙ ወጣቶች አክብደው የማይመለከቱት አንድ ነገር እውነት መሆኑን ያረጋግጣል። ሙዚቃ በባሕርይ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ምናልባት የሄቪ ሜታል ሱሰኛ ላትሆን ትችላለህ። ወይም ወንጀል ለመሥራት አትነሣሳ ይሆናል። ሆኖም ዘፈን በማታስበው መንገድ ሊነካህ ይችላል።
ሙዚቃ ያለው ኃይል
ሙዚቃ ኃይል አለው። ከኃዘንና ከርኅራኄ አንሥቶ እስከ ፍቅርና ደስታ ድረስ የተለያዩ ሰብአዊ ስሜቶችን ሊቀሰቅስ ይችላል። ሙዚቃ አንድን ሰው የተረጋጋ ስሜት ኖሮት እንዲዝናና ሊያደርገው ሲችል ለቁጣም ሊያነሣሳ ይችላል። ለአምላክ የማደር መንፈስ እንዲሰማን ወይም ጨርሰን ምግባረ ብልሹ የመሆን ዝንባሌ እንዲያድርብን ሊያደርግ ይችላል። እንግዲያው ሙዚቃ ከጥንት ጀምሮ “የዚህ ዓለም አምላክ” የሚጠቀምበት ኃይለኛ መሣሪያ ሆኖ መቆየቱ አያስገርምም። — 2 ቆሮንቶስ 4:4
ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነፃ ከወጡ በኋላ ወዲያውኑ የይሖዋን አምልኮ ትተው የወርቅ ጥጃ ያመለኩበትን ወቅት እንመልከት። አሳፋሪ ድርጊታቸውን ያጀበው ነገር ምን ነበር? ስድ የተለቀቀና አስነዋሪ ዘፈን አጅቦት ነበር። (ዘጸአት 32:1–6, 17, 18) በተጨማሪም ራስ ወዳድ የነበረው ንጉሥ ናቡከደናፆር ተገዢዎቹ አረመኔያዊ ምስል እንዲያመልኩ ባዘዘበት ወቅት የሕዝቦቹን ወኔና ሃይማኖታዊ ስሜት ለመቀስቀስ ምን አደረገ? ስሜት የሚቀሰቅስ ሙዚቃ አዘጋጀ! — ዳንኤል 3:1–7
ዛሬም ቢሆን ሰይጣን ሰዎችን ለማሳሳት በሙዚቃ እንደሚጠቀም መጠበቅ ይኖርብናል። እርሱ “በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ” ከመሆኑም በላይ “በአየር ላይ ሥልጣን” አለው። (ኤፌሶን 2:2) ዛሬ የሚሰሙት አብዛኛዎቹ ሙዚቃዎች የሰይጣንን የዓመፀኝነት መንፈስ የሚያንጸባርቁ ናቸው። ይህም የሚያስደንቅ ነገር አይደለም። ምክንያቱም የሙዚቃዎቹ ደራሲዎች በአብዛኛው መጽሐፍ ቅዱስ ‘በአእምሮአቸው ከንቱነት የሚመላለሱ፣ በልባቸው ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው የጨለመና ከአምላክ ሕይወት የራቁ ናቸው’ ብሎ የሚጠራቸው ዓይነት ሰዎች ናቸው። በእውነትም በጣም ዝነኛ ዘፋኞች፣ ሙዚቀኞችና የዘፈን አቀነባባሪዎች “ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው” የሰጡ መሆናቸውን ከአኗኗራቸው መረዳት ይቻላል። — ኤፌሶን 4:17–19
ስለሆነም የእነርሱን ሙዚቃ ማዳመጥ በክርስቲያን ወጣቶች ላይ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። ሁሉም ዘመናዊ ሙዚቃዎች መጥፎ ናቸው ወይም መጠንቀቅ የሚገባው ከሮክ ሙዚቃዎች ብቻ ነው ማለት አይደለም።a ጤናማ ያልሆኑ የክላሲካልና የኦፔራ ሙዚቃዎችም አሉ። ቀደም ባሉት ጊዜያት ብልግናን በስውር አነጋገር ጠቀስ የሚያደርጉ ዘፈኖች ቢኖሩም በአሁኑ ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ ሙዚቃዎች ግን ብልግናን ሐፍረተ ቢስ በሆነ መንገድ የሚናገሩ ናቸው።
ለጆሮና ለዓይን የሚቀፉ
በአስተሳሰብ ወይም በባሕርይ ላይ ጎጂ ተጽዕኖ የሚያሳድረውንና ድምፁ ጆሮ እስኪበጥስ ድረስ ከፍ ተደርጐ የሚደመጠውን ሄቪ ሜታል የተባለ ሙዚቃ እንውሰድ። የሄቪ ሜታል ባንዶች እንደ መርዝ፣ መሸታ ቤት፣ ጠብመንጃና ጽጌረዳ እንዲሁም ገዳይ በመሰሉ ስሞች ይጠራሉ። ታይም መጽሔት “የባንዶቹ ስሞች ራሳቸው የብጥብጥ፣ ሌሎችን የማሠቃየትና የመግደል መንፈስ የሚያነሣሱ ናቸው” ብሏል። በካሴቶቻቸው ሽፋን ላይ የሚታዩት አስፈሪና አብዛኛውን ጊዜ ሰይጣናዊ ምልክቶች የሚገኙባቸው ሥዕሎችም ከዚህ የተለዩ አይደሉም።
ስለ ሙዚቃውስ ቢሆን ምን ሊባል ይቻላል? እንደ “ሥጋና ደም”፣ “ማውደም የጠማው” የመሰሉ ርዕሶች ያሏቸው ሲሆኑ ግጥሞቹም በራስ ወይም በሌላ ሰው ሥቃይ መደሰትን፣ ሴት አስገድዶ ማስነወርንና ነፍስ መግደልን የሚያሞግሱ ናቸው። ስቴር ዌይ ቱ ሄል (የገሃነም መወጣጫ ደረጃ ) የተባለው የሄቪ ሜታል ዘፈን መመሪያ መጽሐፍ ሄቪ ሜታልን “የብልግና አነጋገር፣ መንቀዥቀዥ፣ ሐፍረተቢስነትና ለዓመፅ ግድየለሽ መሆን ድል የተቀዳጀበት ሙዚቃ” ብሎ መጥራቱ አያስደንቅም። የሄቪ ሜታል ሙዚቃ አድማጮች አላግባብ በዕፅ የሚጠቀሙ፣ የሰይጣን አምላኪዎችና ራሳቸውን የሚገድሉ ሰዎች ሆነው መገኘታቸው በተደጋጋሚ ታይቷል። ሆኖም በዜና ማሰራጫዎች ዘገባ መሠረት የሄቪ ሜታል ዘፈኖች በብዙ አድማጮች ዘንድ ተወዳጅ እየሆኑ መምጣታቸውን እንመለከታለን።
በተመሳሳይም አብዛኞቹ የራፕ ሙዚቃዎች (ወይም ሂፕ ሆፕ) ፈጽመው ከሥርዓት የወጡ ናቸው።b ታይም መጽሔት “የራፕ ዘፈን ደራሲዎች . . . በፖሊሶች ላይ የጦርነት እሳት እንዲወርድ ወይም የሴሰኝነት ድኝ በገሐድ እንዲዘንብ ጥሪ የሚያደርጉ ናቸው” ብሏል። በግልጽ ለመናገር፣ ከፍተኛ ተወዳጅነት ካተረፉት የራፕ ዘፈኖች የአብዛኞቹ ግጥም በብልግና የተሞላ በመሆኑ እዚህ ላይ ለመጥቀስ ያሳፍራል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ አንዲት ልጅ እንደዚህ ካሉት ዘፈኖች አንዱን በመጥቀስ “ገና የመጀመሪያውን ቃል ስሰማ ዘገነነኝ” በማለት ተናግራለች።
ይሁን እንጂ ልከኛ ናቸው ከሚባሉት የሮክ ዘፈኖች እንኳ አብዛኞቹ ለክርስቲያን ጆሮ የሚቀፉ ናቸው። በተወዳጅነታቸው አንደኛ ደረጃ ከሚሰጣቸው 40 ዘፈኖች መካከል አብዛኞቹ የራፕ ወይም ሄቪ ሜታል ዘፈኖችን ያህል ቀፋፊና የሚጮኽ ድምፅ ያላቸው ባይሆኑም ብዙዎቹ በረቀቀ መንገድ ወይም በግልጽ የጾታ ብልግናንና ሌሎች ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ድርጊቶችን ያበረታታሉ። በወጣቶች ዘንድ በጣም ተወዳጅ የሆኑት የሙዚቃ ቪዲዮዎች ከድምፁ በተጨማሪ ኃይለኛ ግፊት የሚያሳድሩ ምስሎችን ስለሚያሳዩ ሙዚቃው የሚያሳድረው ተጽዕኖ በጣም ይባባሳል። በሙዚቃ ቪዲዮዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከቪዲዮዎቹ 57 በመቶ የሚያክሉት ዓመፅ የሚታይባቸው ሲሆኑ 75 በመቶ የሚያክሉት ደግሞ በግልጽ ሊታዩ የማይገባቸው ወሲባዊ ድርጊቶች የሚታዩባቸው ሆነው ተገኝተዋል። ስሜት የሚያነሣሱ አለባበሶችና ፍትወትን የሚቀሰቅሱ ዳንሶች በአብዛኞቹ የቪዲዮ ሙዚቃዎች ላይ የሚታዩ ናቸው።
አንተን ሊጎዳህ ይችላልን?
የዚህ ዘመን ሙዚቃዎች በአብዛኛው የሚያንጹና ጤናማ ስሜት የሚያሳድሩ ሳይሆኑ “የምድር፣ የእንስሳ፣ የአጋንንት” ናቸው። (ያዕቆብ 3:15 አዓት) ይሁን እንጂ ብዙ ክርስቲያን ወጣቶች እነዚህን ዘፈኖች መስማት ወይም ቪዲዮዎቹን መመልከት ችግር የሚያመጣ መስሎ አይታያቸውም። “ስለ ራፕ ሙዚቃ ምን አስጨነቀህ? ብትፈልግ እንኳ የሚሉትን መስማት አትችልም” በማለት አንዲት ወጣት ተከራክራለች። የራፕ ዘፈኖችን ግጥም ለማዳመጥ የሞከረ ሰው ይህ አባባል በመጠኑ እውነት መሆኑን ሊቀበል ይችላል።
ወጣቶች ብዙ ጊዜ ዘመናዊ ዘፈኖች የሚያስተላልፉት የተደበቀ ትርጉም አይገባቸውም። በአንድ ጥናት ላይ ወጣቶች የአንዳንድ ዘመናዊ ዘፈኖችን ይዘት እንዲያስረዱ ተጠይቀው ነበር። አብዛኞቹ ወጣቶች ዘፈኖቹ በረቀቀ መንገድ ያቀረቡትን የጾታ፣ የዓመፅ፣ የዕፅና የሰይጣን አምልኮ መልእክት አላስተዋሉም። ዘ ጆርናል ኦቭ ዘ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲየሽን “ይህ ዓይነቱ ሙዚቃ በወጣቶቹ ባሕርይ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ለመኖሩ ምንም ማስረጃ የለም” በማለት ደምድሟል።
መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ነገር ይጠቁማል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን ዓመል ያጠፋል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) እስቲ አስበው፣ አንድ በጣም አሳፋሪና በብልግና የተሞሉ ቃላትን ከሚናገር ወይም ዕፅ እንድትወስድ ከሚወተውትህ፣ የሰይጣን አምላኪ ነኝ ከሚል ወይም የጾታ ብልግናን ግልጽ በሆነ መንገድ ከሚያወራ ሰው ጋር ተቀራርበህ ወይም እሱን እያዳመጥህ ረጅም ሰዓት ታሳልፋለህን? እንደዚህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው። ታዲያ እንደዚህ የመሰለው አነጋገር በሙዚቃ ስለቀረበ ወይም በከበሮ ስለታጀበ ብቻ አይጎዳም ተብሎ ለምን ይታሰባል? እንዲህ የመሰሉ ወራዳ መልእክት የሚያስተላልፉ ዘፈኖች ተደጋግመው ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። “በጉያው እሳትን የሚታቀፍ፣ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው?” በማለት ምሳሌ 6:27 ይጠይቃል።
በዚህ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ የብልግና ሐሳቦችን እየደጋገምን ልንሰማቸው ቀርቶ ማንሣት እንኳ እንደማይገባን አጥብቆ ይመክራል። (ኤፌሶን 5:3–5፤ ፊልጵስዩስ 4:8) ይህንን መሠረታዊ ሥርዓት ቸል የሚል ሰው “መበስበስን ያጭዳል።” (ገላትያ 6:8) ጁዲ የተባለች ወጣት “ዘፈኖቹ ሐሳባችሁን ይቀሰቅሳሉ። በአእምሮአችሁ ውስጥ ያለውን እሳት ያቀጣጥላሉ” በማለት ተናግራለች። አንድ ወጣት የጾታ ብልግናን ሥዕላዊ በሆነ መንገድ የሚገልጽ አንድ የራፕ ዘፈን ካዳመጠ በኋላ “ከአእምሮዬ ሊወጣልኝ አልቻለም” በማለት ተናግሯል።
ስለ ሞት፣ ስለ ዕፅ ወይም ስለ ሰይጣን አምልኮ የሚናገሩ የሄቪ ሜታል ዘፈኖችስ? አንድ ክርስቲያን ወጣት የሄቪ ሜታል ዘፈኖችን ማዳመጥ ከጀመረ በኋላ ስለ ሞት ብቻ ማሰብ ጀመረ። በወላጆቹ ያልተቆጠበ ጥረትና በአንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ወዳጅ እርዳታ ከመንፈሳዊና ከአካላዊ አደጋ ሊያመልጥ ችሏል።
አንዳንድ ጊዜ የምናስባቸው ነገሮች ወደ ተግባር ይለወጣሉ። (ያዕቆብ 1:14, 15) በዛሬው ጊዜ የሚገኙት አብዛኞቹ ዘፈኖች ደግሞ አእምሮ በክፉ ሐሳቦች እንዲሞላ ለማድረግ በብልሃት የተቀነባበሩ ናቸው። እውነት ነው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች መሠረት ተኰትኩተህ አድገህ ከሆነ ዘፈን ስለሰማህ ብቻ ሰው አትገድል ወይም የጾታ ብልግና አትፈጽም ይሆናል። ይሁን እንጂ በሌላ መንገድ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድርብህ ይችላል። አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች የሮክና የራፕ ዘፋኞችን ቅጥ የለሽ አለባበስና ፀጉር አበጣጠር ቀድተዋል። የእነዚህ ወጣቶች አነጋገር፣ የሰውነት እንቅስቃሴና ዝንባሌ በሚሰሙት ሙዚቃ የተለወጠ መሆኑን በግልጽ ያሳያል።
አንድ በደቡብ አፍሪካ የሚኖር ወጣት “ወጣቶች የማዳምጠው ሙዚቃ እኔን አይጎዳኝም ይላሉ። ነገር ግን ሰይጣን ሕይወታችሁን እንዲቆጣጠር መንገድ ይከፍትለታል” በማለት ተናግሯል። ይህንን ለመናገር የበቃው በራሱ ላይ ከደረሰው ነገር በመነሣት ነው። “አዳምጥ የነበረው ዘፈን ስለ መናፍስትነት፣ ስለ ዕፅና ስለ ጾታ የሚናገር ነበር” አለ። ታዲያ ወራዳ ሙዚቃ ከሚያስከትለው ጉዳት እንዴት ሊላቀቅ ቻለ?
“የሙዚቃ ካሴቶችን በሙሉ አውጥቼ ጣልኳቸው። ጭር ባለ ክፍል ውስጥ መቀመጥ ለእኔ አዲስ ነገር ቢሆንብኝም በጣም የተሻልኩ ሰው እንድሆን አስችሎኛል።” አንተስ ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ ያስፈልግሃልን? ያሉህን የሙዚቃ ካሴቶች በሙሉ አውጥተህ መጣል ባይኖርብህም በግልጽ ወራዳ የሆኑትን አውጥተህ መጣል ያስፈልግሃልን? — ከሥራ 19:19 ጋር አወዳድር።
ይህም ሁለተኛ ዘፈን አልሰማም ብለህ መማል አለብህ ማለት ሳይሆን መራጭ መሆንን መማር አለብህ ማለት ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “የሮክ ሙዚቃ” የሚለው አባባል እዚህ ላይ የተሠራበት በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፉትን የተለያዩ የሙዚቃ ዓይነቶች ለማመልከት ነው።
b የእንግሊዥኛውን ንቁ! መጽሔት የካቲት 8, 1993 እትም “የወጣቶች ጥያቄ . . . የማዳምጠው ሙዚቃ ምን መጥፎነት አለው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አእምሮህን በሞት፣ በጥፋትና ወራዳ በሆኑ የጾታ ብልግና መልእክቶች መሙላት ይጠቅምሃል ወይስ ይጎዳሃል?