የወጣቶች ጥያቄ . . .
የቤት ሥራ ይበዛል ምን ባደርግ ይሻላል?
ለብዙ ወጣት ተማሪዎች ጭንቀት መንስኤ ከሆኑት ከዋነኞቹ ነገሮች አንዱ “የቤት ሥራና የጥናት ብዛት” እንደሆነ ይጠቀሳል
“በሚገባ ካልተደራጀህ ቀጥሎ ምን እንደምትሠራ ለመወሰን ብዙ ጊዜ ታጠፋለህ”
‘በቂ ጊዜ የለንም!’ እንዲህ ሲል በማማረር የተናገረው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሚገኙበት አንድ ቡድን ነው። የችግሩ መንስኤ ምንድን ነው? ወጣቶች ትምህርት ቤትም ሆነ ቤታቸው ሄደው እንዲያከናውኗቸው የሚፈለግባቸው ብዙ ሥራ ስላለባቸው ነው። ወጣቱ ቬሮኒክ እንዲህ ብሏል:- “ትምህርት ከጠዋቱ 2 ሰዓት ይጀምርና በ11 ሰዓት ተኩል ያበቃል። እቤት የምደርሰው በ12 ሰዓት ተኩል ነው። አስቸጋሪ ነው። ወላጆች ተማሪ መሆን ማለት በጣም አስደሳች ሕይወት እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ትምህርት ቤት አድካሚና አስጨናቂ መሆኑ አይገባቸውም። እቤት ከሄድን በኋላም የቤት ሥራ አለ።” የአሥራ ሰባት ዓመቷ ሶንድሪንም “የቤት ሥራ ለመሥራት ማታ ማታ ከሁለት እስከ ሦስት ሰዓት አጠፋለሁ፤ ከዚያም በላይ ቅዳሜና እሁድም እሠራለሁ” ብላለች።
ቬሮኒክ እና ሶንድሪን የሚኖሩት ተማሪዎች ለረጅም ሰዓት ከሚማሩባቸው የአውሮፓ አገሮች አንዷ በሆነችው በፈረንሳይ ነው። በሌሎች ብዙ አገሮች ያሉ ተማሪዎችም እንደዚሁ ጭንቀትና ብስጭት ይሰማቸዋል፤ እንዲሁም ጊዜያቸው በጣም ብዙ ሥራ በመሥራት እንደተያዘ ሆኖ ይታያቸዋል። ለወጣቶች ጭንቀት መንስኤ ናቸው ተብለው ዘወትር ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ “ብዙ ማጥናት” እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል።
በአብዛኞቹ አገሮች ሥራ ማግኘት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስቸጋሪ ስለሆነ፣ ብዙ ወጣቶች በደንብ መማር ወደፊት ወደ ሥራው ዓለም መግባት ይችሉ ዘንድ ወሳኝነት እንዳለው ይሰማቸዋል። ቫዮሊን የተባለች አንዲት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ “ጥሩ ሥራ የማግኘቱ አጋጣሚ በጣም እየጠበበ መጥቷል። ዛሬ ያሉት ሕፃናት ሥራ ለማግኘት ያላቸው አማራጭ አንድ ብቻ እርሱም ማጥናት! መሆኑን መገንዘብ አለባቸው” በማለት ተናግራለች።
እውነት በቂ ጊዜ የለም?
ሆኖም ትምህርታቸውን ደህና አድርገው የሚያጠኑ ተማሪዎች ይህ ጊዜና ጉልበት የሚጠይቅ እንደሆነ ያውቃሉ። ክርስቲያን ወጣት ከሆንክ ደግሞ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና እምነትህን ለሌሎች ማካፈል ተጨማሪ ጊዜ ይጠይቅብሃል። (ዮሐንስ 17:3፤ ሮሜ 10:10፤ ዕብራውያን 10:24, 25) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ “ለመሳቅ” እና ለመዝናናት “ጊዜ” አለው ይላል። (መክብብ 3:1, 4፤ 11:9) እንደ ብዙዎቹ ወጣቶች ሁሉ አንተም ለመዝናናትና ለማረፍ ቢያንስ ጥቂት ጊዜ እንዲኖርህ ትፈልግ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከትምህርት ቤትህ እንድትሠራው የተሰጠህ ሥራ ጊዜህን ስለሚያጣብብብህ የምትፈልጋቸውን ነገሮች ለማድረግ የሚኖርህ ጊዜ በጣም አነስተኛ ነው።
ሆኖም ብዙውን ጊዜ ችግሩ ጊዜ የማጣት ጉዳይ ብቻ አይደለም። በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጥሩ ውጤት የማያመጡባቸው ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች “ጊዜን በአግባቡ አለመጠቀም” እና “ቅንጅት የጎደለው አሠራር” መሆናቸውን ገልጧል። አንድ ሰው ቅንጅት የጎደለው አሠራሩ ከፈተና ውጤት የበለጡ ነገሮችን የሚነካበት መሆኑን ኦሊቨር የተባለ አንድ ወጣት ተገንዝቧል። “በደንብ ካልተደራጀህ ቀጥሎ ምን መሥራት እንዳለብህ ለመወሰን ብዙ ጊዜ ታጠፋለህ” ሲል ተናግሯል። ታዲያ ራስህን ማደራጀት የምትችለው እንዴት ነው?
ለጥናት ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት መያዝ
ከሁሉ በፊት የትምህርት ቤት ጥናትህን በተገቢው ቦታ ማስቀመጥ አለብህ። መጽሐፍ ቅዱስ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ለይተን እንድናውቅ” ይነግረናል። (ፊልጵስዩስ 1:10 አዓት) ስታስበው በሕይወትህ ውስጥ ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ መሆን የሚገባው ነገር የትኛው ነው? መንፈሳዊ ግዴታህ መሆን አይገባውምን? እንዲያውም ኢየሱስ ለተከታዮቹ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 6:33) ይህም ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች፣ ለጸሎት፣ ለጥናትና ለሌሎች ለመስበኩ ሥራ ቅድሚያ መስጠት ማለት ነው።
ታዲያ ይህ ማለት ትምህርትን ማጥናት አስፈላጊ አይደለም ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም። ነገር ግን ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን የምትማርበት ዓላማ ሥራ መያዝ እንዲያስችልህ ብቻ መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ ለአምላክ በምታቀርበው አገልግሎት የሚጠቅምህ ጥሩ ችሎታ ለማዳበር ጭምር መሆን አለበት። ይህም ራስህን ምናልባትም አንድ ወቅት ላይ ቤተሰብ ሲኖርህ ቤተሰብህንም ለመርዳት የሚያስችል ሥራ ለመያዝ ያዘጋጅሃል። (1 ተሰሎንቄ 4:11, 12፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8) ይህን ማወቅህ የምትችለውን ያህል ትምህርትህን ተግተህ ለማጥናት እንድትጥር ያደርግሃል። የዚያንኑ ያህል ደግሞ በመንፈሳዊ ጠንካራ ለመሆን ጥረት ማድረግ አለብህ።
በእርግጥ ለመንፈሳዊ ግዴታዎችህ፣ ዘወትር ለምታከናውናቸው ተግባሮች፣ ለመዝናኛና ትምህርትህን ለማጥናት ‘ጊዜ መዋጀት’ አስቸጋሪ ሊሆን ይቻላል፤ ቢሆንም እነዚህን ጉዳዮችህን ለማከናወን ጊዜ ማግኘት ይቻላል። — ኤፌሶን 5:15, 16
ቋሚ የጥናት ፕሮግራም ማውጣት ያለው ጥቅም
ጊዜ የሚዋጅበት አንደኛው መንገድ ውጤታማ በሆነ መንገድ ማጥናት ነው። የወጣቶች ጥያቄና ሊሠሩ የሚችሉ መልሶቻቸው የተባለው መጽሐፍ በምዕራፍ 18 ላይ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ብዙ ጠቃሚ ምክሮችን ይሰጣል።a ለምሳሌ ትምህርትህን የምታጠናበት ቋሚ የሆነ ፕሮግራም ለማውጣት ሞክረህ ታውቃለህ? — ከፊልጵስዩስ 3:16 ጋር አወዳድር።
ሃሪ ማዶክስ ሃው ቱ ስተዲ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “ጥናትን በተመለከተ የሚያጋጥመው ዋናው ችግር ቋሚ ፕሮግራም አውጥቶ ሐሳብን በማሰባሰብ ለማጥናት አለመቻል ነው” ሲሉ ጽፈዋል። አንተስ እንዴት ነህ? አጥና አጥና እስኪልህ ወይም አመቺ የሚመስልህ ጊዜ እስክታገኝ ድረስ የተሰጠህን የቤት ሥራ ሳትሠራ ትቆያለህን? መክብብ 11:4 “ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፣ ደመናትንም የሚመለከት አያጭድም” ሲል ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።
በተጨማሪም ሃሪ ማዶክስ የሚከተለውን ታዝበዋል:- “ጥቂት በጥቂት ጊዜን ማባከን ቀላል ነው። ራስህን በራስህ አስገድደህ ጊዜ ካልመደብህ በስተቀር ማጥናት በሚኖርብህ ሰዓት ቴሌቪዥን በማየት፣ መጽሔት በማንበብ . . . ወይም ሰነፍ ተማሪዎች ከማጥናት ይልቅ መሥራት የሚወድዷቸውን የሆኑ ያልሆኑ ነገሮች በመሥራት ብዙ ጊዜ ልታጠፋ ትችላለህ። የማጥኛ ፕሮግራም ካወጣህና እሱን ለመከተል ቁርጥ ሐሳብ ካለህ ፕሮግራሙን መከበር ያለበት ሕግ አድርገህ ታየዋለህ። ውሎ አድሮ በፕሮግራምህ መሠረት መሥራት ጥረት የማይጠይቅ እየሆነ ይመጣል፤ አንተም ፕሮግራሙን የሕይወትህ ተፈጥሮአዊ ክፍል አድርገህ መመልከት ትጀምራለህ።”
በደንብ በተደራጀና ሥርዓት ባለው መንገድ ትምህርትህን ካጠናህ ትርፍ ጊዜ ልታገኝ ትችላለህ። በተጨማሪም ጥሩ እቅድ ማውጣትህ እንድትሠራ የተሰጡህን የትምህርት ቤት ሥራዎች በማጠናቀቅና በጉባኤ ስብሰባዎች እንደመገኘት ባሉ ክርስቲያናዊ ግዴታዎችህ መካከል የፕሮግራም አለመስማማት እንዳይኖር ይከላከላል።
ጊዜህን ተቆጣጠር
በቤት ውስጥ ለመሥራት የምትፈልጋቸውና የግዴታ ማከናወን ያለብህ የዕለት ተዕለት ጉዳዮች ይኖራሉ። ለእነዚህስ ጊዜ የምታገኘው እንዴት ነው? ለዚህም ቢሆን ቁልፉ መደራጀት ነው። ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች በሥራ ላይ ለማዋል ሞክር:-
የምትሠራቸውን ነገሮች በዝርዝር ጽፈህ ያዝ። የጊዜ አጠቃቀም አማካሪ የሆኑት ስቴፋኒ ዊንስተን ሁልጊዜ የማስታወሻ ደብተር በኪስ መያዝ ጥሩ እንደሆነ ይናገራሉ። “ማንኛውንም ጉዳይ፣ የቤት ወይም የትምህርት ቤት ሥራ፣ የስልክ ጥሪ፣ ልትሠራው ያቀድከውን ነገር ወይም መልእክት ትልቅ ይሁን ትንሽ፣ በጣም አስፈላጊ ይሁን አነስተኛ ወዲያውኑ ጻፈው።” መጀመሪያ ስትመለከተው የጻፍከው ዝርዝር በጣም ብዙ ሆኖ ይታይህ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የሚከተሉትን ሐሳቦች በመጠቀም ለአፈጻጸም አመቺ ወደሆነ መጠን ልትቀንሰው ትችላለህ።
ነገሮችን ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጀምረህ በቅደም ተከተል አስቀምጣቸው። ይህን ማድረግህ ልትሠራቸው በሚገቡ ነገሮች ላይ ይበልጥ እንድታተኩር ይረዳሃል። ሊቆዩ የሚችሉ ወይም ያለህ ጊዜ እንድትሠራቸው የማይፈቅድልህን ነገሮች ልትሰርዛቸው ትችላለህ።
ፕሮግራም አውጣ። የጻፍከውን ዝርዝር የሥራ እቅድህን ወደሚገልጽ ፕሮግራም ለውጠህ ጻፈው። በኪስ የምትያዝ አነስተኛ የቀን መቁጠሪያ ወይም የየቀኑን ጉዳይ መመዝገቢያ ማስታወሻ መያዝ ይህን ለማድረግ ሊረዳህ ይችላል። ሚዛናዊ የሆነ ፕሮግራም ማውጣት ነፃነት ከማሳጣት ይልቅ ጊዜህን የበለጠ ለመቆጣጠር ያስችልሃል።
ከእውነታው ያልወጣህ ሁን። የተለያዩ ዘዴዎችን በመሞከር አንዳንድ ነገሮች መቼ ቢሠሩ እንደሚሻል እወቅ። ለምሳሌ የቤት ሥራህን አእምሮህ ገና ንቁ እያለ ቀኑ ሳይመሽ ለመሥራት ማቀድ ጠቃሚ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ።
ሆኖም ለእያንዳንዱ ደቂቃ ሁሉ እቅድ ማውጣት እንደማያስፈልግህ መገንዘብ ይኖርብሃል። ፕሮግራምህ ሳይጠበቁና ድንገት ለሚከሰቱ ነገሮች ጊዜ የሚሰጥና እንደሁኔታው ሊለወጥ የሚችል አድርገው። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ማስተካከያዎችን አድርግ። በታቸለ መጠን ግን ፕሮግራምህን አጥብቀህ ተከተል። በአብዛኛው አንድን የተወሰነ ሥራ ለማከናወን በዛ ያለ ጊዜ መመደቡ ጥሩ መሆኑን ልታስተውል ይገባሃል። ካሰብከው ጊዜ ቀድመህ ከጨረስክ ማስተካከያ ልታደርግ ትችላለህ።
የራስህ የሆነ ቀነ ገደብ አብጅ። ይህ አንድን ነገር ለመሥራት እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ የመጠበቅን ዝንባሌ እንድታስወግድ ይረዳሃል። እንድትሠራው የተሰጠህ የትምህርት ቤት ሥራ ካለ ማስረከብ ከሚገባህ ቀን ቀድመህ ለመጨረስ የሚያስችል ግብ ለማውጣት ሞክር።
ፕሮግራምህን አጥብቀህ ለመከተል ራስህን ገሥጽ። በዓመቱ መጨረሻ ለሚሰጠው ፈተና እቤትህ ሆነህ ማጥናት ሲኖርብህ ወደ ጓደኛህ ቤት ለመሄድ ብታስብ ፈታኝ ሊሆንብህ ይችላል። ሆኖም ጥናትህን በተመለከተ በጥቂቱ መዝራትህ ፈተናውን ለማለፍ የማያስችል ውጤት እንድታጭድ ያደርግሃል። (ከ2 ቆሮንቶስ 9:6 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በላይ ብዙውን ጊዜ ይበልጥ ደስ የሚልህ ሥራህን ጨርሰህ ትርፍ ጊዜ ስታገኝ ነው። በዚህ በኩል ጠቃሚ የሆነው መሠረታዊ ሥርዓት ይበልጥ አስፈላጊ ለሆነው ነገር ቅድሚያ ሰጥቶ ለጨዋታ ወይም ለቀልድ ሁለተኛ ደረጃ መስጠት ነው።
ፕሮግራም ማውጣትና ራስህን ማደራጀት ጊዜ፣ ትዕግሥትና በከፍተኛ ደረጃ ራስን መግዛት ይጠይቃል። ክርስቲያኖች ደግሞ በሁሉም ነገሮች ራሳቸውን እንዲገዙ ተመክረዋል። (1 ቆሮንቶስ 9:25) በፕሮግራም መመራትን መልመድ ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ለማዋል የሚረዳ ጥሩ መንገድ ነው። የዚህም ውጤት አንድን ሥራ በማከናወን እርካታ ማግኘት፣ ሕይወትህን ይበልጥ ለመቆጣጠር መቻልና መሥራት የምትፈልጋቸውንና መሥራት ያለብህን ነገሮች ማከናወን መቻል ናቸው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጥናት ፕሮግራም አውጣና ፕሮግራምህን አጥብቀህ ተከተል