የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 5/8 ገጽ 21-23
  • የአምላክ ሕዝቦችና የማንበብና የመጻፍ ችሎታ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአምላክ ሕዝቦችና የማንበብና የመጻፍ ችሎታ
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በዘመናችን የሚኖሩት የአምላክ ሕዝቦች
  • ማንበብ መቻል
  • ልጄን ትምህርት ቤት ማስገባት ይኖርብኛል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ መጠቀም
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ለማንበብ ትጋ
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማንበብና መጻፍ መማርን ያበረታታል
    ንቁ!—2015
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 5/8 ገጽ 21-23

የአምላክ ሕዝቦችና የማንበብና የመጻፍ ችሎታ

በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩ የአምላክ ሕዝቦች በአብዛኛው ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ነበሩ። ከ3,500 ዓመታት በፊት ገደማ ሙሴ የመጀመሪያዎቹን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ጻፈ። በሙሴ እግር የተተካው ኢያሱ አምላክ የሰጠውን ሥራ በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን እንዲችል ቅዱሳን ጽሑፎችን “በቀንና በሌሊት” እንዲያነብ ታዟል። በተጨማሪም የእስራኤል ነገሥታት ዙፋን ላይ በሚቀመጡበት ጊዜ ሕጉን እንዲገለብጡና በየቀኑ እንዲያነቡት ታዘዋል።—ኢያሱ 1:8፤ ዘዳግም 17:18, 19

የማንበብና የመጻፍ ችሎታ በሕዝቡ መሪዎች አካባቢ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። እስራኤላውያን የአምላክን ትእዛዛት በቤቶቻቸው መቃን ላይ ‘እንዲጽፉ’ የተሰጠው ትእዛዝ ምሳሌያዊ ትርጉም ያለው እንደሆነ ግልጽ ቢሆንም ሕዝቡ በአብዛኛው ማንበብና መጻፍ የሚችል መሆኑን ያመለክታል። አሞጽ የበግ እረኛ፣ ሚክያስ ደግሞ በገጠር አካባቢ ያደገ ነቢይ ቢሆንም ሁለቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑ መጻሕፍት ጽፈዋል።—ዘዳግም 6:8, 9፤ አሞጽ 1:1፤ ሚክያስ 1:1

ኢየሱስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጥቅልሎች በምኩራቦች አግኝቶ ማንበብ ይችል ነበር። በአንድ ወቅት በምኩራብ በተሰበሰቡ ሰዎች ፊት አንድ ጥቅስ አውጥቶ በማንበብ ይህ ጥቅስ በእርሱ ላይ እንደተፈጸመ ገልጿል። ሐዋርያቱም ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ሲሆኑ በጻፏቸው ጽሑፎች ውስጥ በመቶ በሚቆጠሩ ጊዜያት ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ጠቅሰዋል።—ሉቃስ 4:16-21፤ ሥራ 17:11

በዘመናችን የሚኖሩት የአምላክ ሕዝቦች

ኢየሱስ ለተከታዮቹ “አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚል ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። በተጨማሪም “የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” የሚል ትንቢት ተናግሯል።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20

የይሖዋ ምሥክሮች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ እንደነበሩት ክርስቲያኖች በቅንዓት በአንደበታቸው በመስበክና በማስተማር ይህን የተሰጣቸውን ሥራ ፈጽመዋል። በተጨማሪም የመንግሥቱን ምሥራች በጽሑፎች አማካኝነት አሰራጭተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ከ1920 ወዲህ ከዘጠኝ ቢልዮን የሚበልጡ መጽሐፍ ቅዱሶችን፣ መጻሕፍትን፣ መጽሔቶችንና በራሪ ጽሑፎችን ከ200 በሚበልጡ ቋንቋዎች አዘጋጅተው አሰራጭተዋል።

በመላው ዓለም የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምሥራቹን ተቀብለው የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሆነዋል። ከእነዚህ መካከል ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ወንዶችና ሴቶች ይገኙበታል። እነዚህ መሃይማን በክርስቲያንነታቸው ከሌሎች ያነሱ አይደሉም። ብዙዎቹ አምላክን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በታማኝነት አገልግለዋል፣ ሃይማኖታዊ ስደቶችን ተቋቁመዋል፣ ትእዛዞቹንም በመጠበቅ ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር አሳይተዋል።—1 ዮሐንስ 5:3

ብዙዎቹ ማንበብና መጻፍ መቻል ለአምላክ የሚያቀርቡትን አምልኮ የሚያበለጽግላቸውን በር የሚከፍትላቸው ቁልፍ መሆኑን በመገንዘብ ማንበብና መጻፍ ለመቻል ከልባቸው ይጓጓሉ። በስብሰባዎች ላይ የሚነበቡትን የመጽሐፍ ቅዱስና የክርስቲያናዊ ጽሑፎች ክፍል ለመከታተል፣ ከመንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር አብረው ለመዘመር ሲሉ የሚዘምሯቸውን መዝሙሮች ስንኞች ለማንበብ ይፈልጋሉ። በቤታቸው መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ለማነጽ ይመኛሉ። በአገልግሎት በንባብ የሚረዳቸው ሰው ሳያስፈልጋቸው የአምላክን ቃል እውነት ለሌሎች ለማስተማር ይናፍቃሉ።

ማንበብ መቻል

የይሖዋ ምሥክሮች ይህን የወንድሞቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ መሃይማንን በማስተማር የጉባኤዎቻቸው አባላት በሙሉ መጻፍና ማንበብ የሚችሉ እንዲሆኑ ጥረት ያደርጋሉ። በመላው ዓለም ያስተማሯቸው ሰዎች ቁጥር እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው። በናይጄርያ ብቻ የይሖዋ ምሥክሮች ከ23,000 የሚበልጡ ሰዎችን ማንበብና መጻፍ አስተምረዋል። ከእነዚህ መካከል ኤፎር ይገኝበታል። እንዲህ በማለት ይናገራል:-

“ማንበብና መጻፍ የጀመርኩት በ1950 የ16 ዓመት ወጣት ሳለሁ ነበር። መሠረተ ትምህርቱን የሚሰጡት የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ለማስተማሪያነት የምንጠቀምበት በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የተዘጋጀውን ጽሑፍ ሲሆን እቤታችን ሆነን የምናነበው የቤት ሥራ ይሰጠን ነበር።

“መሃይምነቴን እንደ አንድ በሽታ እመለከተው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ለወንድሞቼና ለጓደኞቼ ማስረዳት እፈልጋለሁ። ይሁን እንጂ ማንበብና መጻፍ ስለማልችል ግን ይህን እንደሚገባ ማድረግ አልችልም። እንድማር ያነሳሳኝ ሌሎች ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን እንዲችሉ ለመርዳት የነበረኝ የመስበክና የማስተማር ፍላጎት ነው። ባገኘሁት ነገር ሁሉ ላይ፣ በሙዝ ቅጠል ላይ እንኳን ሳይቀር እጽፍ ነበር። ማንበብና መጻፍ ለመቻል የነበረኝ ፍላጎት በጣም ከፍተኛ በመሆኑ በሕልሜ ሳይቀር መጻፍና ማንበብ እለማመድ ነበር። ሌሎች ሰዎች እንዲረዱኝ እጠይቃለሁ፣ በመጠየቄም አላፍርም። ለጓደኞቼ የጻፍኩትን ደብዳቤ የተማሩ ሰዎች እንዲያርሙልኝ አሳያቸው እንደ ነበረ አስታውሳለሁ።

“ጉባኤው ማንበብና መጻፍ ለማስተማር ያወጣውን ፕሮግራም ለመከታተል አንድ ዓመት ያህል ፈጀብኝ። ከዚያ በኋላ በዚሁ ክፍል እንዳስተምር ተመደብኩ። ይህም ብዙዎችን እንድረዳ የሚያስችለኝ አጋጣሚ አስገኘልኝ።

“ይህ ትምህርት ቤት ያደረገልኝ እርዳታ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ባለፉት በርካታ ዓመታት የማኅበሩን ድራማዎች ከእንግሊዝኛ ቋንቋ የራሴ ቋንቋ ወደሆነው ወደ ኢሶኮ የመተርጎም መብት አግኝቻለሁ። ከዚህም ሌላ ከ1960ዎቹ ዓመታት ወዲህ የጉባኤ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገልግያለሁ። በ1980ዎቹ ዓመታት ተተኪ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገልግያለሁ። በተጨማሪም የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት [ለሙሉ አገልጋዮች የሚሰጥ ትምህርት ቤት ነው] የመምራትና ሁለት ጊዜ በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት [ለክርስቲያን ሽማግሌዎች ስልጠና የሚሰጥ ትምህርት ቤት ነው] የማስተማር መብት አግኝቻለሁ። መሃይም እንደሆንኩ ብኖር ኖሮ እነዚህን መብቶች በሙሉ ላገኝ እንደማልችል አውቃለሁ።

“ትሁታን የሆኑ ሰዎችን ማንበብና መጻፍ ለማስተማር የተደረገውን ይህን ዝግጅት ከልብ አደንቃለሁ! አንዳንዴ ሌሊት በመኝታዬ ላይ እያለሁ በዚህ ዘመናዊ በሆነ ዓለም ውስጥ መሃይም ሆኜ ባለመቅረቴ ይሖዋን የማመሰግንበት ጊዜ አለ።”

ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ ለሰው ልጆች ማንበብና መጻፍ የመቻልን ስጦታ በልግስና ሰጥቷል። ይሁን እንጂ ይህ ችሎታ አለ ድካምና ጥረት እንዲሁ የሚገኝ አይደለም። ማንበብና መጻፍ መማር ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች ትልቁ የአምላክን ቃል “ቀንና ሌሊት በተመስጦ አንብበው” የሚለውን መለኮታዊ ትእዛዝ ለመፈጸም መቻል ነው።—ኢያሱ 1:8 NW

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ልጆቻችሁ የማንበብ ፍቅር እንዲያድርባቸው ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው?

● እናንተ ራሳችሁ አዘውታሪ አንባቢዎች በመሆን ጥሩ አርዓያ ሁኗቸው። አንባቢ ወላጆች አንባቢ ልጆች ይኖሯቸዋል።

● ልጆቻችሁን ከጨቅላነታቸው ጀምራችሁ አነጋግሯቸው። ሕፃናት ትርጉም ያለው ቋንቋ መስማታቸው ወደፊት በቀላሉ ማንበብ እንዲችሉ የሚረዷቸውን ቃላትና ሐሳቦች እንዲያውቁ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።

● ለልጆቻችሁ አዘውትራችሁ አንብቡ። ሕፃናትን ጭናችሁ ላይ አድርጋችሁ ስታነቡላቸው የሚነበብላቸውን ታሪክ ለመረዳት በሚችሉበት ዕድሜ ላይ ባይደርሱም እንኳን ሲነበብ የሚሰሟቸው ቃላትና መጻሕፍት ጥሩ ነገር መሆናቸውን ያስተውላሉ። ራሳቸው ማንበብ ከቻሉ በኋላ እንኳን ቢሆን ለልጆቻችሁ አንብቡላቸው። ልጆች ከትምህርት ቤት አስተማሪዎቻቸው እንዴት ማንበብ እንደሚችሉ ሊማሩ ቢችሉም በንባብ መደሰት የሚማሩት ከወላጆቻቸው ነው። የሚወዷቸውን ታሪኮች ከወላጆቻቸው ደጋግመው መስማት ያስደስታቸዋል።

● ልጆች እቤት ውስጥ የሚያነቧቸው መጻሕፍት አዘጋጁላቸው።

● ልጆቻችሁ እንዲጽፉ አበረታቷቸው። መጻፍ የሚወድ ልጅ አብዛኛውን ጊዜ ማንበብም ይወዳል።

● ቤተሰቡ አንድ ላይ ሆኖ በየቀኑ የሚያነብበት ጊዜ መድቡ። በየተራ ካነበባችሁ በኋላ ባነበባችሁት ላይ ተወያዩ። እነዚህ የንባብ ጊዜያት የሚያስደስቱና የሚያንጹ መሆን አለባቸው።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ሰዎች ማንበብና መጻፍ ይችሉ ነበር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ