የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 6/8 ገጽ 21-23
  • ሕይወቴን ላስተካክል የምችለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሕይወቴን ላስተካክል የምችለው እንዴት ነው?
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አንድ ዓመፀኛ ልጅ ቤቱን ጥሎ ወጣ
  • “ወደ ልቡ ተመለሰ”
  • ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ማስተካከል
  • ለእግራችሁ ቅን መንገድ አድርጉ
  • “ይሖዋ፣ መሐሪና ሞገስ ያለው አምላክ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • አንድን “አባካኝ” ልጅ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ለሚመለሱት የሚደረግ የሞቀ አቀባበል
    በሕይወት ተርፎ ወደ አዲስ ምድር መግባት
  • የጠፋው ልጅ ታሪክ
    እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 6/8 ገጽ 21-23

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .

ሕይወቴን ላስተካክል የምችለው እንዴት ነው?

“ፈጽሞ ወደ ውስጥ ልገባ አልቻልኩም” በማለት ጆን ይናገራል። ወደ ይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ከሄደ በኋላ ከውጭ ቆሞ ቀረ። በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ሲደርስ የክርስትናን ሕይወት ትቶ የወንጀል ኑሮ፣ አደገኛ ዕፅ መውሰድና የዝሙት ኑሮ ማሳደድ ጀመረ። ለበርካታ ዓመታት በዚህ ዓይነት አኗኗር ከቀጠለ በኋላም መጽሐፍ ቅዱስ ጨርሶ ከአእምሮው ሊወጣ አልቻለም። በዚህ ምክንያት ወደ አንድ መንግሥት አዳራሽ ቢሄድም ወደ ውስጥ መግባት ግን አስፈራው። ወደ ውስጥ እንዲገባ ላደፋፈረው አንድ ሰው “ፈጽሞ ሊገባህ አይችልም። እጅግ በጣም ብዙ መጥፎ ነገሮች ሠርቼአለሁ። ይሖዋ እኔን ይቅር ሊል የሚችልበት መንገድ ይኖራል ብዬ ፈጽሞ አላስብም” አለው።

በርካታ ወጣቶች ወላጆቻቸው በሚያወጧቸው መመሪያዎች፣ በሃይማኖታቸውና በሥነ ምግባር ደንቦቻቸው ላይ ያምጻሉ። በተለይ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች ተንከባክበው ያሳደጓቸው ወጣቶች በዚህ ዓይነት መንገድ ሲጓዙ በጣም ያስደነግጣል። በዚህ ዓይነቱ ጎዳና ለመመላለስ የመረጡ ወጣቶች ጥቂቶች ናቸው ባይባሉም አንዳንዶቹ የፈንጠዝያ አኗኗራቸው ሊሸፍንላቸው ያልቻለ የባዶነት ስሜት ሊሰማቸው ይጀምራል። (ምሳሌ 14:13) አንዳንድ ወጣቶች ይህ ክፉ ዓለም እንደፈለገ ከተጠቀመባቸው በኋላ ሕይወታቸውን ለማስተካከልና ልጆች ሳሉ ወደ ተማሯቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ለመመለስ ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ በእርግጥ ለመመለስ ይችላሉ?

አንድ ዓመፀኛ ልጅ ቤቱን ጥሎ ወጣ

በሉቃስ 15:11-32 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ የተናገረው ምሳሌ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥሩ ግንዛቤ ይሰጣል። ታሪኩ እንዲህ ይነበባል:- “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ አባቱን:- አባቴ ሆይ፣ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው። ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ።”

ይህ ወጣት የዓመፅ መንገድ ለመከተል የመረጠው አባቱ ጨካኝ፣ ተሳዳቢ ወይም ከልክ በላይ ጨቋኝ ስለሆነበት እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። በሙሴ ሕግ መሠረት አንድ ልጅ አብዛኛውን ጊዜ አባቱ ከመሞቱ በፊት የውርስ ጥያቄ የማያቀርብ ቢሆንም ከአባቱ ንብረት የመካፈል መብት ነበረው። (ዘዳግም 21:15-17) አባቱ ገና ሳይሞት ድርሻው እንዲሰጠው መጠየቁ ምንኛ ደንታ ቢስ ቢሆን ነው! ሆኖም አባቱ የጠየቀውን ሁሉ ሰጠው። (ከዘፍጥረት 25:5, 6 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ የተሳሳተ ዝንባሌ የነበረው ልጅዬው እንጂ አባትዬው እንዳልነበረ ግልጽ ነው። አልፍሬድ ኤደርስሃይም የተባሉት ምሁር እንዳሉት “በቤቱ ውስጥ የነበረው ሥርዓትና ጥብቅ ደንብ” አስጠልቶት “ነጻነትና ፈንጠዝያ የሞላበት ኑሮ” ፈልጎ ይሆናል።

ቀደም ሲል በዚህ መጽሔት ላይ እንደተጠቆመው ደግነትና አሳቢነት የሚጎድላቸው ወላጆች ሊኖሩ እንደሚችሉ የታወቀ ነው።a ይሁን እንጂ አንድ ወላጅ ጨካኝ ወይም ምክንያተ ቢስ በሚሆንበት ጊዜ ማመፅ መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ዓመፅ በመጨረሻ ላይ ጥፋት ማስከተሉ አይቀርም። የኢየሱስን ምሳሌ ደግመን እንመልከት። ወጣቱ ይኖር ከነበረበት አካባቢ ርቆ ከሄደ በኋላ “እያባከነ ገንዘቡን በተነ። ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፣ እርሱም ይጨነቅ ጀመር።” በዚህ ጊዜ እንኳን ወደ ልቦናው አልተመለሰም። አሁንም በራሱ በመታመን “ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፣ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው። እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፣ የሚሰጠውም አልነበረም።”

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ኸርበርት ሎክየር “ኢየሱስን ያዳምጡ የነበሩት አይሁዶች እነዚህን ቃላት ሲሰሙ ሳይዘገንናቸው አይቀርም። ለአንድ አይሁዳዊ የእሪያዎች ቀላቢ ከመሆን የበለጠ ውርደት ሊኖር አይችልም።” ዛሬም በተመሳሳይ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ጥለው የሚወጡ ሰዎች ብዙ ጊዜ በጣም አስቸጋሪ፣ እንዲያውም በጣም ወራዳ በሆነ ሁኔታ ላይ ይወድቃሉ። አንዲት ቤቷን ጥላ የወጣች ክርስቲያን ወጣት “ገንዘቤን በሙሉ ለዕፅ ስለ ጨረስኩ ለሌሎች ነገሮች የቀረኝ ምንም ገንዘብ አልነበረኝም። በዚህ ምክንያት ሱሴን ለመወጣት ወደ ሱቆች እየገባሁ መስረቅ ጀመርኩ” ስትል ተናዛለች።

“ወደ ልቡ ተመለሰ”

ይሁን እንጂ አባካኙ ልጅ እንዲህ ባለ ችግር ላይ በወደቀ ጊዜ ምን አደረገ? ኢየሱስ ‘ወደ ልቡም ተመልሶ’ ይላል። የግሪክኛው አነጋገር “ወደ ራሱ ተመልሶ” የሚል ትርጉም አለው። በሌላ አባባል “ራሱን ስቶ” በቅዠት ዓለም ውስጥ ስለነበረ ሁኔታው ምን ያህል አስከፊ እንደነበረ ሊያስተውል አልቻለም ነበር ማለት ነው።—ከ2 ጢሞቴዎስ 2:24-26 ጋር አወዳድር።

በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ አንዳንድ ዓመፀኛ ወጣቶችም የሚገኙበትን ሁኔታ ሲገነዘቡ ድንጋጤ ይሰማቸዋል። እስር ቤት ገብተው፣ ከባድ አደጋ ደርሶባቸው ወይም የአባለ ዘር በሽታ ይዟቸው የፈንጠዝያ ኑሮ ያስከተለባቸውን መዘዝ መቅመስ ሲጀምሩ ወደ ልቦናቸው ሊመለሱ ይችላሉ። በመጨረሻ “አላዋቂዎችን ከጥበብ መራቅ ይገድላቸዋል” የሚሉት የምሳሌ 1:32 ቃላት እውነት መሆናቸውን ይገነዘባሉ።

ወላጆቿን ጥላ ከወጣች በኋላ አደገኛ ዕፅ መውሰድ የጀመረችውን ወጣቷን ኤልሳቤጥን እንውሰድ። “ፈጽሜ ስለ ይሖዋ ረሳሁ” ትላለች። ይሁን እንጂ የኒው ዮርክን ከተማ በምትጎበኝበት ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት አጠገብ አለፈች። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? “በልቤና በአእምሮዬ ውስጥ ሕመም ተሰማኝ” በማለት ታስታውሳለች። “ምን ማድረጌ ነው? ሕይወቴ እንዲህ ባለው ማጥ ውስጥ እንዲዘፈቅ ያደረግኩት ለምንድን ነው?” አለች።

አባካኙ ልጅ በመጨረሻ የሚገኝበትን እውነታ ሲረዳ ወደ ቤቱ ለመመለስና ሕይወቱን ለማስተካከል የድፍረት ውሳኔ አደረገ! ይሁን እንጂ አባቱ ያን የሚያክል ጉዳትና ክህደት ከተፈጸመበት በኋላ ይቀበለው ይሆን? ታሪኩ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል:- “እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፣ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው።” አዎን፣ ወጣቱ በጥንቃቄ የተለማመደውን የንስሐ ቃል ከመናገሩ በፊት አባቱ ቅድሚያ ወስዶ ፍቅሩንና ይቅርታውን ገለጸለት!

ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ማስተካከል

ቢሆንም አባካኙ ልጅ ለአባቱ “አባቴ ሆይ፣ በሰማይና በፊትህ በደልሁ” ብሏል። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ከአምላክ መንገድ ኮብልለው የነበሩ ወጣቶች ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ‘ካላስተካከሉ’ ሕይወታቸውን ሊያስተካክሉ አይችሉም! (ኢሳይያስ 1:18) ይሖዋ አምላክ ከእርሱ ጋር ልንታረቅ የምንችልበትን መንገድ ክፍት በማድረጉ አመስጋኞች መሆን ይገባናል። አዎን፣ በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው አባት የይሖዋ አምላክ ምሳሌ ነው። አምላክም ንሥሐ ለገቡ ኃጢአተኞች “ወደ እኔ ተመለሱ፣ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” በማለት ከዚህ አባት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ይቅርታ የማድረግ ዝንባሌ አሳይቷል። (ሚልክያስ 3:7፤ ከመዝሙር 103:13, 14 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ እነዚህ ንስሐ የገቡ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንደነበሩት በደለኛ አይሁድ “መንገዳችንን እንመርምርና እንፈትን፣ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ” በማለት ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል።—ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:40

የተጓዙበትን የኃጢአት መንገድ በጥሞና መመልከት አለባቸው ማለት ነው። አንድ በደለኛ ወጣት ይህን በሚያደርግበት ጊዜ በይሖዋ አምላክ ፊት የሠራውን ኃጢአት ለመናዘዝ መገፋፋት ይኖርበታል። መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል:- “ዝም ባልሁ ጊዜ አጥንቶቼ ተበላሹ፣ . . . ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፣ በደሌንም አልሸፈንሁም። . . . አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ።”—መዝሙር 32:3-5

አንድ ወጣት ወይም አንዲት ወጣት ምናልባት እንደ ማስወረድ፣ ዝሙት መፈጸም፣ አደገኛ ዕፅ መውሰድ ያለ ከባድ ኃጢአት ወይም ከባድ ወንጀል ፈጽሞ/ፈጽማ ከነበረስ? እንዲህ ያደረገ ወጣት ይቅርታ ሊደረግለት የማይገባ እንደሆነ ቢሰማው አያስደንቅም። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ጆን እንዲህ ተሰምቶት ነበር። አንድ ደግ የጉባኤ ሽማግሌ፣ የጥንት የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ንጉሥ ምናሴም ግድያን ጨምሮ ከባድ ኃጢአቶች ሠርቶ እንደነበረ እስኪያስታውሰው ድረስ ከመንግሥት አዳራሹ ውጭ ተገትሮ ቆሞ ነበር። ቢሆንም ይሖዋ ይቅር ብሎታል። (2 ዜና መዋዕል 33:1-13) ጆን “ሕይወቴን ያዳነልኝ ያ ሽማግሌ ነበር” በማለት ይናገራል። ጆን ይቅርታ ሊያገኝ እንደሚችል ካወቀ በኋላ ወደ መንግሥት አዳራሹ ለመግባትና እርዳታ ለመጠየቅ የሚያስችለው ድፍረት አገኘ።b

እንዲህ በመሰሉ ሁኔታዎች ውስጥ ከወደቁ ብዙ ወጣቶች መካከል አብዛኞቹ ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ዝምድና እንዲያስተካክሉ ተመሳሳይ እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። በዚህ ረገድ የጉባኤ ሽማግሌዎች ብዙ መልካም እርዳታ ሊያበረክቱ ይችላሉ። ወጣቱ ‘ኃጢአቱን በግልጽ በሚናዘዝበት’ ጊዜ ራሳቸውን በእርሱ ቦታ አድርገው በመመልከት ሊያዳምጡትና ችግሩን ሊረዱለት ይችላሉ። በተጨማሪም ዲስፕሊንና ተግባራዊ እርዳታ ሊሰጡት ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው የአምላክን ቃል መሠረታዊ ነገሮች ከመጀመሪያ ጀምሮ በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት እንዲያስተምረው ዝግጅት ሊያደርጉ ይችላሉ። በደለኛው የመጸለይ ችግር ካለበት ደግሞ አንድ ሽማግሌ አብሮት ወይም አብሯት ሊጸልይ ይችላል። “የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል።—ያዕቆብ 5:14-16፤ ዕብራውያን 5:12

ለእግራችሁ ቅን መንገድ አድርጉ

እርግጥ ነው፣ ከአምላክ ጋር የነበረንን ዝምድና ማስተካከል የመጀመሪያው እርምጃ ብቻ ነው። አባካኙ ልጅ አባቱን ይቅርታ እንደጠየቀ ሁሉ በደል የፈጸሙ ወጣቶችም ወላጆቻቸውን ለመካስ መሞከር ይኖርባቸዋል። ከልባቸው ይቅርታ ቢጠይቁ ወላጆቻቸው የተሰማቸው ቅሬታ ሊቀነስላቸው ስለሚችል እርዳታቸውን ለማግኘት ይችላሉ። ከወላጆቿ ኮብልላ የነበረችና ዲቃላ ይዛ የተመለሰች አንዲት ወጣት “አባባና እማማ በጣም ከፍተኛ የሆነ ፍቅር አሳይተውኛል” ብላለች።

አምላክን ለማስደሰት የሚፈልግ ወጣት ‘ለእግሩ ቅን መንገድ ማድረግ’ ይኖርበታል። (ዕብራውያን 12:13) ይህም የቀድሞ አኗኗሩን፣ ልማዶቹንና ጓደኞቹን እንዲለውጥ ሊጠይቅበት ይችላል። (መዝሙር 25:9፤ ምሳሌ 9:6) በተጨማሪም የግል ጥናት ልማድ ማዳበር በጣም አስፈላጊ ነው። ከዚህ ቀደም ዓመፀኛ የነበረች አንዲት ልጃገረድ እንዲህ ትላለች:- “መጽሐፍ ቅዱስና በይሖዋ ምሥክሮች የሚታተሙትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በሙሉ አነባለሁ። አምላክ ሌላ ዕድል ስለሰጠኝ አመሰግነዋለሁ።”

ጆን እንደሚከተለው በማለት በጥሩ ሁኔታ አጠቃሎታል:- “ያባከንኩትን ጊዜ መለስ ብዬ እመለከታለሁ። ምን ማድረግ ይገባኝ እንደነበረ አስባለሁ። ይሁን እንጂ የሆነውን ነገር እንዳልሆነ ላደርግ የምችልበት መንገድ የለም።” ጥለውት የሄዱትን ሁሉ ሞቅ ባለ ስሜት እንዲመለሱ የሚጋብዝ መሐሪ አምላክ የምናመልክ መሆናችን በጣም ያስደስተናል። ታዲያ ግብዣውን ለምን አትቀበልም?

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በሐምሌ—መስከረም 1995 ንቁ! “የወጣቶች ጥያቄ . . . ወላጆቼን መታዘዝ ያለብኝ ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

b በክርስትና መንገድ ያላደግህ ብትሆንም ሕይወትህን ለመለወጥ የምትፈልግ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮችን የመንግሥት አዳራሽ መጎብኘት ጥሩ ጅምር ሊሆንልህ ይችላል። ነጻ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግልህ ጠይቅ። በዚህ መንገድ ሕይወትህን ለማስተካከል የሚያስችል እርዳታ በግል ለማግኘት ትችላለህ።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጎለመሱ ክርስቲያኖች ሕይወትህን እንድታስተካክል ሊረዱህ ይችላሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ