ቤተሰቤ በመንፈሳዊ ባለጸጋ እንዲሆን መርዳት
ጆሰፋት ቡሳን እንደተናገረው
በጥር 1941 ወደ ጆሃንስበርግ፣ ደቡብ አፍሪካ ያደረግኩትን የባቡር ጉዞ ፈጽሞ አልዘነጋም። አብሮ አደጌ የሆነው ኤልያስ ኩኔንና እኔ የእረፍት ጊዜያችንን በዙሉላንድ ካሳለፍን በኋላ ወደ ሥራ ቦታችን መመለሳችን ነበር።
ባቡሩ ላይ ከተሳፈሩት ሰዎች መካከል ምትሐታዊ ኃይል አለው የሚባልና አብዛኛውን ጊዜ በጠንቋይ የሚዘጋጅ ሙቲ የሚባል መድኃኒት የያዘ ወጣት ሰው ነበር። ሰውዬው፣ ነጭ አሠሪው በተለየ ሞገስ እንዲመለከተው የሚያደርግ ኃይል እንዳለው ያመነበትን ሙቲ ሽፋሽፍቱ ላይ ቀባ። ከባቡሩ በመውረድ ላይ እንዳለን ኤልያስ “አምላኩ ሙቲ ነው” አለ። እነዚህ ቃሎች ልቤን ልክ እንደ ጩቤ ወጉት። ምክንያቱም እኔም በሻንጣዬ ውስጥ አንድ ጠንቋይ በሰጠኝ መመሪያ መሠረት ያዘጋጀሁት ሙቲ ነበረኝ።
ኤልያስና እኔ መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስናጠና የቆየን ቢሆንም ከእኔ ይልቅ እሱ መንፈሳዊ እድገት በማድረግ በኩል በጣም ቀድሞኝ እንደሄደ ተገነዘብኩ። ወዲያውኑ ሙቲዬን ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ወረወርኩና ከኤልያስ ጋር የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ።
እኔም ሆንኩ ኤልያስ ባለ ትዳሮች ነበርን። ታዲያ ከቤታችን 400 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ከተማ የምንሠራው ለምንድን ነው? የከተማው ኑሮ በዙሉላንድ ከሚገኘው የገጠር ኑሮ በምን ይለያል? ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘታችንስ በገጠር ለተውናቸው ቤተሰቦቻችን ጥቅም አስገኝቶላቸዋል?
የዙሉላንድ ኑሮ
በ1908 በዙሉላንድ፣ ደቡብ አፍሪካ ተወለድኩ። ቤተሰባችን ይኖር የነበረው በለምለም ሣር በተሸፈኑ ሜዳዎች፣ ኮረብታዎችና እሾሃማ ቁጥቋጦዎች በሚበዙበት በምሲንጋ አውራጃ ነበር። ይህ አካባቢ በበልግ ወራት ሹል ጫፍ ያላቸው የእሬት አበቦች ስለሚበዙበት ቀይ ሆኖ ይታያል። ከብቶችና ፍየሎች በኮረብቶች ላይ በሚገኙ ዛፎች መካከል የሚበቅለውን ሣር ይግጣሉ። በሜዳዎቹ ላይ ጎጆ ቤቶችና የበቆሎ ማሳዎች ዘርዘር ብለው ይታያሉ። በቆሎ የዙሉዎች ዋነኛ ምግብ ነው።
መኖሪያችን እንደ ሌሎቹ ዙሉዎች አንድ የወላጆቻችን ጎጆ፣ አንድ የእህቴና አንድ የእኔና የወንድሜ ጎጆ የሚገኝበት ነው። በወጥ ቤትነት የሚያገለግል አንድ ጎጆ ሲኖር ለዕቃ ማስቀመጫነት የሚያገለግል ሌላ ጎጆ አለ። እያንዳንዱ ጎጆ እንደ ንብ ቀፎ በክብ ቅርጽ የተሠራ ሲሆን ግማሽ ሜትር የሚያክል ከፍታ ያለው የጭቃ ግድግዳና ከሣር የተሠራ ጣሪያ አለው። በጎጆዎቹ ዙሪያ ዶሮዎች መሬቱን እየጫሩ ምግባቸውን ይፈላልጋሉ። ከጎጆዎቹ አጠገብ የከብቶች በረት አለ። ቤተሰባችን በዚህ ቀላል የሆነ የግብርና ኑሮ ረክቶ ይኖር ነበር። ምግብና መጠለያ ስላለን አባቴ ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ መሥራት አላስፈለገውም።
ይሁን እንጂ የዙሉላንድ ፀጥታና የተረጋጋ ኑሮ የተናጋባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው። አስደሳች የሆኑት ኮረብታዎችና ወንዞች በሰው ደም ተጥለቅለቀዋል። በ19ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ዙሉላንድ በተለያዩ ነፃ በሆኑ ነገዶች ተወርራለች። በኋላም ሻካ የሚባል አንድ የዙሉ ጦረኛ ሰው ተነሳ። የሻካ ሠራዊት የአካባቢውን ነገዶች በሙሉ ወረረ። ከጦርነቱ የተረፉት ወደ ሌላ አካባቢ ለመሸሽ ወይም ከዙሉ ብሔር ጋር ተቀላቅለው ለመኖር ተገደዱ።
በኋለኞቹ ዓመታት ደግሞ በዙሉዎችና በዳች ሰፋሪዎች መካከል ጦርነት ተደርጓል። አንደኛው ጦርነት የተደረገው ከእኛ አካባቢ ብዙም በማይርቅ ወንዝ አጠገብ ነበር። በጣም ብዙ ደም በመፍሰሱ ምክንያት ወንዙ ቀልቶ ስለነበረ የደም ወንዝ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር። ከዚያ በኋላ ደግሞ የብሪታንያ ሠራዊት መጣ። ከእኔ አካባቢ ብዙም በማይርቅ ኢሳንድልዋና በሚባል ኮረብታ ላይ በእንግሊዛውያንና በዙሉ ወታደሮች መካከል በተደረጉ በርካታና ከባድ ጦርነቶች በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። ይህ በእኛ አካባቢ የሚገኘው የዙሉላንድ ክፍል ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ሰላም አለማግኘቱ የሚያሳዝን ነው። በየጊዜው ለዘመናት ተዳፍነው የቆዩ የጎሣ ግጭቶች መፈንዳታቸው አልቀረም።
ቁሳዊ ሀብት ለማግኘት ያደረግኩት ሙከራ
ገና አምስት ዓመት እንደሆነኝ እናቴ ሞተች። አባቴና ታላቅ እህቴ በርቲና ስድስተኛ ክፍል እስክደርስ ድረስ እየተንከባከቡ አሳደጉኝ። ከዚያም 19 ዓመት ሲሞላኝ አቅራቢያችን በሚገኘው ደንዲ በሚባል ከተማ የአንድ ባለ ሱቅ ረዳት ሆኜ ተቀጠርኩ።
ብዙ ወጣቶች የደቡብ አፍሪካ የወርቅ ማዕድን ኢንዱስትሪ ማዕከል በሆነችው በጆሃንስበርግ ብዙ ገንዘብ እንደሚያገኙ ሰማሁ። በዚህም ምክንያት በሚቀጥለው ዓመት ወደ ጆሃንስበርግ ሄድኩና የማስታወቂያ ጽሑፎችን በመለጠፍ ሥራ ብዙ ዓመት ሠራሁ።
ጆሃንስበርግ የሚገኙ ማራኪ ነገሮችና ክፍት የሥራ ቦታዎች ቢያስደንቁኝም የከተማው ኑሮ የወገኖቼን ባሕላዊ ሥነ ምግባር የሚሸረሽር እንደሆነ ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ አልወሰደብኝም። ቢሆንም ብዙ ወጣቶች በገጠር የሚኖሩትን ቤተሰቦቻቸውን ፈጽሞ ሲረሷቸው እኔ ግን ዘወትር ገንዘብ እልክላቸው ነበር።
አባቴ በ1938 ሞተ። ትልቁ ወንድ ልጅ እኔ በመሆኔ በዙሉ ባሕል መሠረት ተመልሼ የቤተሰባችንን መንደር “ለማንቀሳቀስ” ተገደድኩ። በዚህም ምክንያት በቀጣዩ ዓመት ከዙሉላንድ ክላውዲና ማዶንዶ የምትባል ልጃገረድ አገባሁ። ትዳር ብመሠርትም 400 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በጆሃንስበርግ መሥራቴን አልተውኩም። ከእኩዮቼ መካከል አብዛኞቹ ያደረጉት ይህንኑ ነበር። ለረዥም ጊዜያት ከቤተሰቤ መለየቴ በጣም የሚሰማኝ ቢሆንም የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ የማስቻል ግዴታ እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር።
ቁሳዊ ወይስ መንፈሳዊ ሀብት?
በቤታችን ውስጥ ቤተ ክርስቲያን የመሄድ ልማድ የነበራት እናታችን ብቻ ስትሆን ከእርሷ መጽሐፍ ቅዱስ ሌላ ምንም ዓይነት መጽሐፍ አልነበረንም። እርሷ ከሞተች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ማንበብ ቻልኩና ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ጀመርኩ። ይሁን እንጂ የአብያተ ክርስቲያናት መሠረተ ትምህርቶችና ተግባሮች ይረብሹኝ ጀመር። ለምሳሌ ያህል የቤተ ክርስቲያን አባሎች ዝሙት እየፈጸሙ ምንም ዓይነት እርምጃ አይወሰድባቸውም። እንደነዚህ ስላሉት ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር የማይጣጣሙ ድርጊቶች ሰባኪዎች እንዲያስረዱኝ ብጠይቅም አጥጋቢ ማብራሪያ አላገኘሁም።
ጆሃንስበርግ እያለን ኤልያስ ኩነን እና እኔ እውነተኛውን ሃይማኖት ለመፈለግ ወሰንን። በአካባቢያችን ያሉትን ቤተ ክርስቲያኖች በሙሉ እየተዘዋወርን ብናይም አንዳቸውም ቢሆኑ አላረኩንም። ከዚያም ኤልያስ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘ። ከእነርሱ የተማራቸውን ነገሮች ሊያስረዳኝ ሲሞክር ፈጽሞ ተታልለሃል አልኩት። ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር ያደረገውን ውይይት ካዳመጥኩና ስህተት መሆኑን ሊያረጋግጡ አለመቻላቸውን ከተመለከትኩ በኋላ ኤልያስ የሰጠኝን የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማንበብ ጀመርኩ። ኤልያስ በሙቲ መታመን አደገኛ መሆኑን እንድረዳ ያደረገኝና ሊረሳ የማይችል የባቡር ጉዞ ያደረግኩት በዚህ ጊዜ ነበር።—ዘዳግም 18:10-12፤ ምሳሌ 3:5, 6
ከዚያ በኋላ ከኤልያስ ጋር በጆሃንስበርግ በተቋቋመው የመጀመሪያ የጥቁር የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ መገኘት ጀመርኩ። በ1942 ሕይወቴን ለይሖዋ ከወሰንኩ በኋላ በኦርላንዶ፣ ሶዌቶ ተጠመቅኩ። ወደ ዙሉላንድ በምመለስባቸው ጊዜያት ሁሉ እምነቴን ለክላውዲና ለማካፈል እጥር ነበር። እርሷ ግን በቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች ተጠምዳ ነበር።
ይሁን እንጂ ጽሑፎቻችንን ከመጽሐፍ ቅዱሷ ጋር ማነጻጸር ስለ ጀመረች ቀስ በቀስ የአምላክ ቃል እውነት ልቧን መንካት ጀመረ። በ1945 ተጠመቀች። ለጎረቤቶቿ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የምታካፍል ቀናተኛ ክርስቲያን አገልጋይ ከመሆኗም በላይ በልጆቻችን ልብ ውስጥ እውነትን መትከል ጀመረች።
በዚሁ ጊዜ በጆሃንስበርግ አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያውቁ ለመርዳት ችያለሁ። በ1945 በጆሃንስበርግ የሚገኙ የጥቁሮች ጉባኤዎች አራት የደረሱ ሲሆን የስሞል ማርኬት ጉባኤ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገለግል ነበር። ከጊዜ በኋላ ከቤተሰባቸው ተለይተው የሚሠሩ ባለ ትዳር ወንዶች ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱና የቤተሰብ ራስነት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ ተሰጠ።—ኤፌሶን 5:28-31፤ 6:4
ከጆሃንስበርግ ለመመለስ የመጀመሪያ የሆነው ኤልያስ ሲሆን ከዚያ በኋላ ከቤተሰቡ ተነጥሎ አያውቅም። በዚህ ምክንያት ሚስቱና አምስት ልጆቹ የይሖዋ ምሥክሮች ለመሆን በቅተዋል። በተጨማሪም ኤልያስ ያሳድጋቸው የነበሩት የሟች ወንድሙ ልጆች ራሳቸውን የወሰኑ ምሥክሮች ሆነዋል። ይሖዋ በቃሉና በምድራዊ ድርጅቱ በኩል የሚሰጣቸውን መመሪያዎች በታማኝነት በመከተል ረገድ ጥሩ ምሳሌ ከተወ በኋላ በ1983 ሞተ።
በ1949 በጆሃንስበርግ የነበረኝን ሥራ ትቼ ቤተሰቤን በይሖዋ መንገድ ለመንከባከብ ወደ ገጠር ተመለስኩ። ከአንድ የእንስሳት ሐኪም ጋር ከብቶችን ገንዳ ውስጥ በማጥለቅ ሥራ ረዳት ሆኜ ተቀጠርኩ። በማገኛት አነስተኛ ደመወዝ ስድስት ልጆቼን ማስተዳደር ቀላል አልነበረም። ወጪዎቼን ለመሸፈን የምናመርታቸውን አትክልቶችና በቆሎ እሸጥ ነበር።
የበለጠ ዋጋ ያላቸው በረከቶች
ቤተሰባችን በቁሳዊ ነገሮች ሀብታም ባይሆንም ኢየሱስ “ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቈፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቈፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ” በማለት የሰጠውን መመሪያ በመከተላችን መንፈሳዊ ሀብት ለማግኘት ችለናል።—ማቴዎስ 6:19, 20
እነዚህን መንፈሳዊ ሀብቶች ለማግኘት በጆሃንስበርግ አካባቢ በሚገኙት የወርቅ ማዕድኖች ከሚደረገው ቁፋሮ የማይተናነስ ድካምና ጥረት ጠይቆብናል። በየምሽቱ ለልጆቼ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ካነበብኩ በኋላ ከጥቅሱ ምን እንደተማሩ እንዲነግሩኝ እያንዳንዳቸውን እጠይቃለሁ። ቅዳሜና እሑድ ሁሉንም በየተራ እየያዝኩ ወደ ስብከቱ ሥራ እሄዳለሁ። ከአንዱ መንደር ወደ ሌላው በምንጓዝበት ጊዜ ቅዱስ ጽሑፋዊ ጉዳዮችን አንስተን እንወያይና የመጽሐፍ ቅዱስን ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደንቦች በልባቸው ውስጥ ለመትከል እጥራለሁ።—ዘዳግም 6:6, 7
ለምሳሌ ያህል ልጆቻችን እንደማይሰርቁ ለማረጋገጥ ወደ ቤት የሚያመጧቸውን ነገሮች በሙሉ ከየት እንዳመጡ አረጋግጣለሁ። (ኤፌሶን 4:28) በተመሳሳይም አንዳቸው ውሸት ቢናገር በበትር ከመቅጣት ወደኋላ አልልም። (ምሳሌ 22:15) በተጨማሪም ለሸመገሉ ሰዎች ተገቢውን አክብሮት እንዲያሳዩ አዝዛቸዋለሁ።—ዘሌዋውያን 19:32
የቤተሰብ ራስ እንደመሆኔ ከስብሰባዎች ባለመቅረት ጥሩ ምሳሌ እሆናቸዋለሁ። ልጆቼም ከስብሰባ እንዳይቀሩ አደርጋለሁ። እያንዳንዱ ልጅ የየራሱን መዝሙር መጽሐፍ፣ መጽሐፍ ቅዱስና በስብሰባው ላይ የሚጠናው ጽሑፍ እንዲኖረው አደርጋለሁ። በተጨማሪም አንድ ላይ ሆነን ለስብሰባዎች እንዘጋጃለን። በስብሰባ ላይ ሐሳብ ያልሰጠ ልጅ ካለ በሚቀጥለው ሐሳብ እንዲሰጥ ለመርዳት እሞክራለሁ።
ለበርካታ ዓመታት ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾች መስተንግዶ የማቅረብ አቅም የነበረው የእኛ ቤተሰብ ብቻ ነበር። እነዚህ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ወኪሎች በልጆቻችን ላይ በጎ ተጽእኖ ለማሳደር ከመቻላቸውም በላይ አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን የመሆን ፍላጎት እንዲያድርባቸው ረድተዋል። የበኩር ልጃችን አፍሪካ የአሥረኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቅቆ የአቅኚነት ሥራ ሲጀምር እኔና ባለቤቴ በጣም ተደስተን ነበር። በኋላም ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ሲያገለግል ቆይቶ በደቡብ አፍሪካ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ተርጓሚ ሆኖ እንዲሠራ ተጋበዘ። በአሁኑ ጊዜ ሚስት አግብቶ ልጆች ወልዷል። በዙሉላንድ በሚገኝ ጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ በማገልገል ላይ ሲሆን የደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ በንጹሕ አምልኮ ምክንያት በየጊዜው በሚያጋጥሙት ሕግ ነክ ጉዳዮች የመርዳት መብት አግኝቷል።
በጠቅላላው አምስት ወንድ ልጆችና አንድ ሴት ልጅ አለን። ስድስቱም ልጆቻችን በአሁኑ ጊዜ ያደጉ ሲሆን በመንፈሳዊም ጠንካሮች ናቸው። ይህም ልባችን በደስታና በቁሳዊ ሀብት ሊገዛ በማይችል ጥልቅ እርካታ እንዲሞላ አድርጎልናል። ከወንድ ልጆቼ መካከል አራቱ በየሚገኙባቸው ጉባኤዎች ሽማግሌዎች ሆነው ያገለግላሉ። ከመካከላቸው ቴዎፍሎስ የሚባለው በአሁኑ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ በቤቴል የማገልገል መብት አግኝቷል።
በዙሉላንድ እውነትን ማሠራጨት
ከቤተሰቤ ጋር ለመኖር ወደ ዙሉላንድ በተመለስኩበት በ1949 በኮሌሲ ጉባኤ የነበሩት የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ሦስት ብቻ ነበሩ። ከጊዜ በኋላ ጉባኤው አድጎ 30 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው የፖሜሮይ መንደር ሁለተኛ ጉባኤ ተቋቁሟል።
የስብከት ሥራችን በተለያዩ ጎሣዎች መካከል በሚፈጠር አምባጓሮ ምክንያት ችግር ላይ የወደቀባቸው ጊዜያት ነበሩ። የአብያተ ክርስቲያናት አባሎች በእነዚህ የጎሣ ግጭቶች ይካፈላሉ። በገለልተኝነታቸው የሚታወቁት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው። አንድ ጊዜ ከብቶችን የማጥለቅ ሥራዬን አከናውን በነበረበት አካባቢ የማባሶና የማቦምቩ ጎሣዎች ተጋጭተው ነበር። በዚህ አካባቢ የሚኖሩት ሰዎች የማባሶ ጎሣዎች ሲሆኑ እኔ ደግሞ የማቦምቩ ጎሣ አባል መሆኔን ስለሚያውቁ ሊገድሉኝ ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ጭምር ያውቁ ስለነበረ ምንም ዓይነት ጉዳት አላደረሱብኝም።
በ1970ዎቹ ዓመታት በጎሣዎች መካከል የሚደረገው ውጊያ በጣም ተባብሶ ስለነበረ የምሲንጋ አውራጃ ለኑሮ በጣም አደገኛ ሆኖ ነበር። ከሌሎች ጋር ሆኜ ቤተሰቤን ሻል ያለ ሰላም ወደነበረበት የዙሉላንድ ክፍል ለማዛወር ወሰንኩ። በ1978 በኖንጎማ ከተማ መኖር ጀመርንና ከሊንዲዝዌ ጉባኤ ጋር መተባበር ጀመርን። በቀጣዩ ዓመት ውዷ ባለቤቴ ክላውዲና ሞተች። እርሷን ማጣቴ ድንገተኛ ዱብ ዕዳ ስለሆነብኝ ጤንነቴ ታወከ።
ሆኖም ይሖዋ ባደረገልኝ የማይገባ ቸርነት ከሁለት ዓመት በኋላ አገግሜ የአቅኚነት አገልግሎት ለመጀመር ቻልኩ። የስብከት እንቅስቃሴዬን መጨመሬ ጤንነቴ ይበልጥ እንዲሻሻል በማስቻሉ ይሖዋን ከልብ አመሰግነዋለሁ። እድሜዬ 85 ዓመት ሲሆን አሁንም በየወሩ በስብከቱ ሥራ በአማካኝ 90 ሰዓት ለማሳለፍ እችላለሁ። በጥር ወር 1992 ከልጄ ኒኮላስ ጋር ተጨማሪ የመንግሥት አስፋፊዎች ወደሚያስፈልጉበት የዙሉላንድ ክፍል ወደ ሙደን ተዛወርኩ።
እንደኔ ያሉ ሰዎች ለቤተሰቦቻቸው መንፈሳዊ ፍላጎት የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡ ከይሖዋ ድርጅት ለተሰጠው መመሪያ ምንኛ አመስጋኝ ነኝ! በዚህ ምክንያት ያገኘኋቸው በረከቶች ገንዘብ ሊገዛ ከሚችለው ማንኛውም ነገር ይበልጣሉ። (ምሳሌ 10:22) ይሖዋን ለዚህ ሁሉ አወድሰዋለሁ። የእርሱ መንግሥት ይህችን ምድር ወደ ገነትነት የሚለውጥበት ጊዜ እንዲመጣ እጸልያለሁ። ከዚያ በኋላ ውብ በሆኑት የዙሉላንድ ኮረብቶችና ሸለቆዎች የሚኖረው ሕይወት ጸጥታና ሰላም የሰፈነበት ይሆናል። እያንዳንዱ ሰው ‘የሚያስፈራው ሳይኖር በወይኑና በበለሱ ሥር ተዘልሎ ይቀመጣል።’—ሚክያስ 4:4