በካናዳ “ስለ ተበከለ ደም” የተደረገ ምርመራ
ካናዳ በሚገኘው የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ የተጠናቀረ
ካናዳ ውስጥ የተበከለ ደም ወስደው በኤድስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ለምን ጨመረ? በ1980ዎቹ ዓመታት ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ካናዳውያን “በተበከለ ደም” እና በደም ተዋጽኦዎች ምክንያት በኤድስ ቫይረስ ተለክፈዋል። እነዚህ የሚያስደነግጡ ክስተቶች ፌዴራላዊው መንግሥት በካናዳ ያለውን የደም ባንክ አሠራር የሚመረምር ኮሚሽን እንዲያቋቁም አስገድደዋል። መንግሥታዊው ምርመራ በካናዳ ያለው የደም ባንክ ምን ያህል አስተማማኝ እንደሆነ ለማወቅ ያስችላል።
የምርመራ ቡድኑ ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት በአገሪቱ ከፍተኛ ክብር ከሚሰጣቸው ታላላቅ ዳኞች አንዱ ናቸው። ኮሚሽኑ በመላው ካናዳ የሚሰጡትን የምሥክርነት ቃሎች ያዳምጣል። ማዳመጥ የጀመረው የካቲት 14, 1994 በቶሮንቶ ከተማ ሲሆን የኦንታሪዮ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ክቡር ሆሬስ ክሬቨር የደረሱበትን ሁኔታና መሻሻል ያለበትን ነገር በየጊዜው ሪፖርት እንዲያደርጉ ታዘዋል።
በተበከለ ደም አማካኝነት በያዘው ኤድስ ልጅዋ የሞተባት አንዲት እናት ለዳኛው “ልጄን ገድለውታል፤ ያገኘሁት ካሳ ቢኖር ይህ ምርመራ ብቻ ነው። እባካችሁ ለዚህ ምርመራ ከፍተኛ ቦታ ስጡት” በማለት አቤቱታዋን አሰምታለች። ደም ከመስጠት ጋር የተያያዙ አደጋዎችን ለማስወገድ የሚረዱ አስፈላጊ እርምጃዎች ለመውሰድ የሚያስችል ጥልቅ ምርመራ እንዲደረግ ብርቱ ፍላጎት ነበራት። በተበከለ ደም ምክንያት ልጅዋን በሞት ያጣች እናት እርሷ ብቻ አልነበረችም። ኮሚሽኑ የብዙ ካናዳውያንን ሕይወት ያበላሸውን ይህን አሳዛኝ ሁኔታ የሚመለከቱ አንጀት የሚበሉ በርካታ የምሥክርነት ቃሎች ሰምቷል።
የቶሮንቶው ግሎብ ኤንድ ሜል ጋዜጣ እንደሚከተሉት ያሉ ርዕሰ አንቀጾች አውጥቷል። “ደም በመውሰድ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እንባና የቁጣ ሲቃ እየተናነቃቸው የምሥክርነት ቃል ሰጥተዋል፣” “ስለ ደም ምርመራ እንዲያደርግ የተቋቋመው ኮሚሽን አስደንጋጭ ምሥክርነቶችን እየሰማ ነው፣” “የሕክምና ባለሙያዎች አላዋቂነት ይፋ ወጣ” እንዲሁም “ስለ ደም ምርመራ እንዲያደርግ የተቋቋመው ኮሚሽን ኤድስ የሚያስከትለውን ጉዳት ባለ ሥልጣኖች አቅልለው ይመለከታሉ በማለት አስታወቀ።”
ደም ወስደው በኤች አይ ቪ የተለከፉ ሰዎች ደም መውሰድ ስለመሚያስከትለው አደጋ ምንም የተነገረን ነገር አልነበረም ብለዋል። አብዛኞቹ ደም መውሰዳቸውን ያወቁት በኤድስ ቫይረስ መለከፋቸውን ካወቁ በኋላ ነበር።
የኤድስ በሽተኛ የሆነ አንድ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኝ ልጅ በኤች አይ ቪ ቫይረስ የተለከፈው የሦስት ዓመት ልጅ ሳለ የልብ ቀዶ ሕክምና ሲደረግለት በተሰጠው ደም አማካኝነት ነበር። ቀለል ያለ ሄሞፊሊያ የተባለ በሽታ ያለበትና በኤች አይ ቪ የተለከፈ አንድ ሰው ከ1984 በፊት የደም ተዋጽኦዎችን ይጠቀም የነበረ ሲሆን በዚያን ጊዜ ሆኪ ይጫወት ነበር። የደም ተዋጽኦዎችን መውሰዱ የሚያስከትልበትን አደጋ ቢያውቅ ኖሮ አኗኗሩን ይቀይር ነበር። አንዲት እናት በ1985 በኤች አይ ቪ የተለከፈ ደም ወስዳ ነበር። በአሁኑ ጊዜ እርሷ፣ ባሏና የአራት ዓመት ሴት ልጃቸው ኤድስ ይዟቸዋል።
አንድ ወይም ሁለት ዩኒት ደም ብቻ ወስደው በኤድስ ስለ ተያዙ ሰዎችም በጣም አሳዛኝ ሪፖርት ተሰምቷል። ባለቤቷ ደም በመውሰዱ ምክንያት በኤች አይ ቪ የተለከፈባት አንዲት ሴት ደም የተሰጠው “ፊቱን ለማሳመር ተብሎ” እንደነበረ በምሬት ተናግራለች። አሁን እርሷም በቫይረሱ ተለክፋለች።
የብዙ ምሥክሮች ቃል እየተሰማ ሲሄድ በጣም ከባድ የሆነ ሌላ አሳዛኝ ነገር ሊስተዋል ችሏል። እርሱም በደም አማካኝነት የሚተላለፈው ሄፓታይተስ የተባለው በሽታ ነው። ግሎብ ኤንድ ሜል በተባለው ጋዜጣ መሠረት “በየዓመቱ ከ1,000 የሚበልጡ ካናዳውያን ሄፓታይተስ ሲ በተባለው በሽታ ይሞታሉ” ተብሎ ይገመታል። ጋዜጣው አክሎ ሲናገር “ከእነዚህ መካከል ግማሽ የሚያክሉት በበሽታው የተለከፉት ደም በመውሰድ ሊሆን ይችላል” ብሏል።
አንድ ሰው ሄፓታይተስ ሲ የያዘው በ1961 ጀርባው ላይ ቀዶ ሕክምና ሲደረግለት በተሰጠው ደም እንደሆነ ተናግሯል። ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ሳያቋርጥ ደም ሲለግስ ቆይቷል። በ1993 ሲሮሲስ የተባለ የጉበት በሽታ እንዳለበት አወቀ። “ይህ በሽታ እንዳለብኝ ከማወቄ በፊት ያን ሁሉ ዓመት የለገስኩትን ደም የወሰዱ ሰዎች ምን ሊሆኑ ነው?” በማለት ለመርማሪው ኮሚሽን ጥያቄ አቅርቧል።
ዳኛው ክሬቨር በኤች አይ ቪ እና በተበከለ ደም አማካኝነት በሚመጡ ሌሎች በሽታዎች ሕይወታቸው የጨለመባቸውን ከአንድ መቶ የሚበልጡ ካናዳውያን በጥሞና አዳምጠዋል። የሕክምና ባለሙያዎች የደም አቅርቦትን ሙሉ በሙሉ ከተላላፊ በሽታ ወይም ከሌሎች አደጋዎች ነፃ ማድረግ እንደማይቻል አረጋግጠዋል። ደም ከአግባብ ውጭ ለሆነ ግልጋሎትና ለአደገኛ ሁኔታዎች የተጋለጠ መሆኑን አምነዋል። የአካባቢ ደም የመስጠት አገልግሎት ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ጄ ብርያን ማክሺፍሬ ትምህርት በሚሰጡበት ጊዜ “ደም መስጠት ካለብህ ወይ ትክክለኛ ምርመራ አላደረግክም አለዚያም ትክክለኛ ሕክምና አላደረግክም” በማለት ችግሩን እንደሚያስገነዝቡ መስክረዋል።
መንግሥታዊው ኮሚቴ በካናዳ 250 ሚልዮን ዶላር ዓመታዊ ባጀት የተመደበለት የደም ሥርጭት ሥርዓት “ዋንኛ ባለቤቶች” ናቸው በሚላቸው ድርጅቶች መካከል ፖለቲካዊ መናቆርና ፉክክር መኖሩን አጋልጧል። በቀይ መስቀልና በሌሎች መንግሥታዊ ድርጅቶች ላይ ብዙ ክስ ቀርቧል። ይሁን እንጂ በአገሪቱ የደም ባንክ ላይ ለተፈጠረው ችግር ኃላፊ የሚሆን ያለ አይመስልም።
ከዚህ የተለየ አስደሳች ሁኔታ
ግንቦት 25, 1994 ዳኛ ክሬቨር በሪጃይና ሲስካቹዋን ውስጥ ከእነዚህ ተስፋ አስቆራጭ የምስክርነት ቃሎች የተለየ ጥሩ ሪፖርት አዳምጠዋል። ከባድ ሄሞፊሊያ (የደም አለመርጋት በሽታ) ያለበት የ75 ዓመቱ ዊልያም ጄ ሆል በደም ተዋጽኦዎች ፋንታ በሌሎች አማራጮች በመጠቀም እንዴት በተሳካ ሁኔታ ጤንነቱን እንደሚንከባከብ ተናገረ። በዚህ የተነሳ ኤድስ አልያዘውም። ሚስተር ሆል የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኑ መጠን በሃይማኖታዊ ኅሊናው የተነሳ ከደምና ከደም ተዋጽኦዎች ርቋል።— ገጽ 27 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።
ገና የሚደመጡ በርካታ ማስረጃዎች አሉ። መንግሥት ምርመራው እስከ 1995 ማብቂያ እንዲቀጥል አድርጓል። ኮሚሽኑ በሺህ በሚቆጠሩ አዋቂና ሕፃናት የይሖዋ ምሥክሮች ላይ አለ ደም የተደረጉትን የተሳኩ ሕክምናዎች ለመመርመር በቂ ጊዜ ለማግኘት ይችላል። እነዚህ አማራጭ ሕክምናዎች የይሖዋ ምሥክር ላልሆኑ በሽተኞችም ያገለግላሉ።
በእነዚህ አማራጭ ሕክምናዎች የተጠቀሙ ዶክተሮች ለኮሚሽኑ ሊያካፍሉት የሚችሉት ጠለቅ ያለ እውቀት አግኝተዋል። በማክጊል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሠሩት ዶክተር ማርክ ቦይድ በ1993 ዘ ሜዲካል ፖስት ለተባለው ጋዜጣ ሲናገሩ “የይሖዋ ምሥክሮችን በጣም ማመስገን አለብን። ምክንያቱም ደም ሳይሰጥ የተሳካ ሕክምና እንዴት ማድረግ እንደምንችል አሳይተውናል” ብለዋል። በ1988 የዩ ኤስ ፕሬዘዳንታዊ ኮሚሽን “ደም በመስጠት ምክንያት የሚደርሱትን ችግሮች አስተማማኝ በሆነ መንገድ ማስወገድ የሚቻለው በተቻለ መጠን ማንኛውም በሽተኛ ከሌላ ሰው ደም ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖረው በማድረግ ነው” በማለት አስታውቆ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ‘ከደም ራቁ’ የሚለውን የአምላክ ሕግ በመታዘዝ ከተበከለ ደምም ሆነ ደም መውሰድ ከሚያስከትላቸው ሌሎች አደጋዎች ‘አስተማማኝ በሆነ መንገድ ራሳቸውን ሊጠብቁ’ ችለዋል።— ሥራ 15:20, 28, 29
ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል
የሚያሳዝነው ግን አብዛኞቹ የተበከለ ደም በመውሰዳቸው ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ከዚህ አሳዛኝ ገጠመኛቸው ሊጠብቋቸው የሚችሉ በደም ፋንታ የሚሰጡ ሕክምናዎች እንዳሉ አልተነገራቸውም ነበር። በሽተኞች የሚሰጣቸው ሕክምና የሚያመጣው ጉዳትና ጥቅም ተነግሯቸው ደም መውሰድ የሚያስከትላቸውን አደጋዎች እንዲቀበሉ አለዚያም አስተማማኝ የሆኑ አማራጮችን እንዲጠቀሙ ምርጫ አልተሰጣቸውም።
ለኮሚሽኑ የቀረቡት ማስረጃዎች በደም ፋንታ ስለሚሰጡ ሕክምናዎች ዶክተሮችንና ሕዝቡን ማስተማር እንደሚያስፈልግ አሳይተዋል። ይህ በከፍተኛ ደረጃ የተካሄደ መንግሥታዊ ምርመራ ከፍተኛ ውጤት እንደሚኖረው ይታመናል። ዳኛ ክሬቨር የሚሰጡት አስተያየት ካናዳ ውስጥ የሚሰጡትን ከደም ጋር የተያያዙ ሕክምናዎች በተመለከተ የአመለካከትና የትምህርት አሰጣጥ ለውጥ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ይፈጥራል። ምርመራውን ያደረገው ኮሚሽን የሚደርስባቸው ውሳኔዎች ደም ከመውሰድ ጋር ተያይዘው የሚመጡ አደጋዎችን ለማስወገድ የሚጥሩትን ሁሉ ያስደስታሉ።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሄሞፊሊያ የተባለውን የደም አለመርጋት በሽታ ያለ ደም መቆጣጠር ተቻለ
በኒፕዊን ሲስካቹዋን የሚኖረው ዊሊያም ጄ ሆል ያለበትን ከባድ የሆነ የሄሞፊሊያ በሽታ ያለ ደም ተዋጽኦዎች እንዴት እንደተቆጣጠረና ይህንንም ለምን እንዳደረገ ለኮሚሽኑ ተናግሮ ነበር። የሚከተለው ፍርድ ቤቱ በጽሑፍ ካሰፈረው የምሥክርነት ቃል የተወሰደ ነው:-
◻ “ሰውነቴ ከእግር ጣቴ ጀምሮ እስከ ወገቤ ድረስ ሲያብጥ ወላጆቼ ሄሞፊሊያ እንዳለብኝ አወቁ። ዶክተሮች መርምረው በሽታዬ ሄሞፊሊያ እንደሆነ አረጋገጡ። . . . በዚያን ጊዜ የአንድ ዓመት ልጅ ሳልሆን አልቀርም።”
◻ “ደም ወይም ማንኛውንም ዓይነት የደም ተዋጽኦ ወስጄ አላውቅም። . . . ደምን ቅዱስ አድርጌ ስለምመለከት ደም መውሰድ ከሃይማኖታዊ እምነቶቼ ጋር ይጋጫል።”
◻ ሄሞፊሊያ ስለነበረበት ወንድሙ ሲናገር:- “ከእኔ የተለየ እምነት [ሃይማኖት] ስለነበረው ደም ወሰደና በሄፓታይተስ በሽታ ሞተ” ብሏል።
◻ በ1962 ስለደረሰበት የአንጀት መቁሰል በሽታ ሲናገር:- “ዶክተሩ ደም ካልወሰድኩ እንደምሞት ነግሮኝ ነበር። . . . ሆስፒታሉ [ያለ ደም] ጥሩ ሕክምና አደረገልኝ” ብሏል። የሚፈስሰውን ደም ለማቆም ተችሎ ነበር።
◻ የተሰበረ ዳሌውን ለመጠገን በ1971 ስለተደረገለት ሕክምና ሲናገር:- “ጥንቃቄ የተሞላበት ያለ ደም የተደረገ ቀዶ ሕክምና ነበር። . . . ቀዶ ሕክምናው የተሳካ ነበር” ብሏል። በጊዜው የተደረገለት ተደጋጋሚ የደም ምርመራ በደሙ ውስጥ ፋክተር VIII (ደም እንዲረጋ የሚያደርግ) የተባለ ንጥረ ነገር እንደሌለ አሳይቷል።
◻ በሽታውን እንዴት ተቋቁሞ ሊኖር እንደቻለ ሲናገር:- “በአኗኗሬ ጥንቁቅ ስለሆንኩ ነው” ብሏል። አመጋገቡን ይቆጣጠራል፣ ያርፋል፣ የሰውነት እንቅስቃሴ ያደርጋል እንዲሁም ሰውነቱ ሲያብጥ፣ ሲቆስልና ሲደማ በጥንቃቄ ይታከማል።
◻ “ራስን ማዝናናት፣ አምላካችን ያደረገልንን ጥሩ ነገሮች ማሰላሰልና የሚያስጨንቁንን ነገሮች መርሳት ጥሩ እንደሆነ አምናለሁ። ይህ በጣም የረዳኝ ይመስለኛል።”
ዊልያም ሆል ዕድሜው 76 ዓመት ሲሆን የይሖዋ ምሥክር ነው።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር የሆኑት ዳኛ ሆሬስ ክሬቨር
[ምንጭ]
CANPRESS PHOTO SERVICE (RYAN REMIROZ)
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዊልያምና ማርጋሬት ሆል በምርመራ ኮሚሽኑ ፊት ለመቅረብ 370 ኪሎ ሜትር በመኪና ተጉዘው ነበር