የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g95 10/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የተሻለ የማንበብና የመጻፍ ችሎታ ያላቸው ልጆች
  • ከዋክብትን መቁጠር
  • የሰውነትን አካል መብሳት የሚያደርሰው የጤና ችግር
  • ደም መውሰድ የሚያስከትላቸው አደጋዎች
  • “ገና ያልታወቀችው ፕላኔት”
  • በዩናይትድ ስቴትስ
  • በጨው ውስጥ የሚገኘው አዮዲን
  • የሚያደነቁር ድምፅ
  • ‘የመጨረሻው ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት’
  • ከሳንባ ነቀርሳ ጋር በሚደረገው ውጊያ መሸነፍ
  • በ40 ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ80,000 የሚበልጡ የመሬት ነውጦች
  • ጦርነት መልኩን ቀይሯል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
ንቁ!—1995
g95 10/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

የተሻለ የማንበብና የመጻፍ ችሎታ ያላቸው ልጆች

ግሎብ ኤንድ ሜይል የተባለው የካናዳ ጋዜጣ “ለትናንሽ ልጆች ማንበብ የመጻፍ ችሎታቸውን ያዳብርላቸዋል” በማለት ሪፖርት አድርጓል። የኦንታሪዮ ካናዳ ትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ባደረገው ጥናት ትናንሾች ሳሉ የተለያየ ተረት ይነበብልን ነበር ያሉ ልጆች ምንም ዓይነት መጽሐፍ ካልተነበበላቸው ወይም አልፎ አልፎ ብቻ ከተነበበላቸው ልጆች የተሻለ ውጤት ሊያገኙ እንደቻሉ አረጋግጧል። በተጨማሪም ግሎብ “ጥሩ የንባብ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች ጥሩ የመጻፍ ችሎታም እንዳላቸው” ከገለጸ በኋላ “ከትምህርት ጊዜያቸው ውጭ የሚያነቡ ተማሪዎች ከሌሎች የተሻለ የማንበብም ሆነ የመጻፍ ችሎታ እንዳላቸው” ዘግቧል። የኦንታሪዮ መምህራን ፌዴረሽን ፕሬዚደንት እንደተናገሩት “14 ዓመት ዕድሜ ላይ ከመድረሳቸው በፊት የማንበብ ልማድ ያልነበራቸው ወይም ሳይነበብላቸው ያደጉ ተማሪዎች ከዚያ በኋላም ቢሆን አንባቢዎች” እንደማይሆኑ ጥናቱ አረጋግጧል።

ከዋክብትን መቁጠር

ሰማዩ በከዋክብት በሚሞላበት ምሽት ቀና ብለህ እየተመለከትህ ምን ያህል ከዋክብት ለማየት እችል ይሆን? ብለህ ራስህን ጠይቀህ ታውቃለህን? በቅርቡ ስካይ ኤንድ ቴሌስኮፕ የተባለው መጽሔት ለዚህ የበርካታ ዘመናት ጥያቄ መልስ ለማግኘት ሞክሮ ነበር፤ መልሱ ግን የሚታሰበውን ያህል ቀላል አይደለም። መጽሔቱ የአስትሮኖሚ ጽሑፎች እንደሚያመለክቱት አንድ በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ በሚገኝ ጨለም ያለ የገጠር አካባቢ ቆሞ የሚመለከት ሰው በአማካይ 2,862 ከዋክብት ለማየት ይችላል ሲል ገልጿል። ይሁን እንጂ እነዚህ ከዋክብት በሙሉ በማንኛውም ጊዜ ከአድማስ በላይ ሆነው የሚታዩ አይደሉም፤ ብዙዎቹ ብቅ ጥልቅ የሚሉ ናቸው። ከዚህም በላይ አናት ላይ ሲሆኑ በቀላሉ የሚታዩ ከዋክብት ወደ አድማስ ሲጠጉ አይታዩም። ይህ የሚሆነው ከዋክብቱ ይህን ያህል ዝቅ በሚሉበት ጊዜ ብርሃናቸው ወደ ተመልካቹ ዓይን ለመድረስ የሚያቋርጠው የምድር ከባቢ አየር ውፍረት ስለሚጨምር ነው። ስካይ ኤንድ ቴሌስኮፕ ሲደመድም በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ በ40 ዲግሪ መስመር ላይ የሚገኝ ተመልካች በማንኛውም የዓመቱ ክፍል 1,809 ከዋክብት ለማየት ይችላል ብሏል።

የሰውነትን አካል መብሳት የሚያደርሰው የጤና ችግር

በካናዳ የካልገሪ ጤና አገልግሎት ድርጅት የአካባቢ ጤና ዲሬክተር የሆኑት ጆን ፔልተን “ሰዎች ከዚህ በፊት ተበስተው የማያውቁ የአካል ክፍሎችን መብሳት ጀምረዋል” ይላሉ። የቅንድባቸውን ቆዳ፣ ከንፈራቸውን፣ ምላሳቸውንና እንብርታቸውን እንደሚበሱ ዘ ቫንኩቨር ሳን ዘግቧል። የአልበርታ የአካባቢ ጤና አገልግሎት መሥሪያ ቤት ይህ እየተስፋፋ የመጣ ወረት ኤድስ፣ ሄፓታይትስ ቢ እና ሲ ሊያስተላልፍ ይችላል ብሎ በመስጋቱ የሰውነት አካል መብሳትን የሚቆጣጠር መመሪያ ለማውጣት ተገዷል። “ከጊዜ በኋላ ደግሞ የሰውነት አካልን መተኮስ፣ ማቃጠል፣ መንቀስና ነርቮችን ማደንዘዝ የመሰሉትን ቁጥጥር የማይደረግባቸውን አገልግሎቶች የሚቆጣጠር ደንብ ይወጣል።” የእነዚህ ደንቦች ረቂቅ በሕዝብ ጤና አጠባበቅ ባለ ሥልጣኖች እንደሚመረመር ዘገባው አክሎ ይገልጻል። ለጆሮ መብሻ የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን ለሰውነት መብሻ በመጠቀም ረገድ በዚህ ሞያ የተሰለፈ አንድ ሰው “ኢንፌክሽን ይዟቸው ሆስፒታል የገቡ ሰዎች እናውቃለን። በእውነትም በጣም የሚያሰጋ ነገር ነው” ብሏል።

ደም መውሰድ የሚያስከትላቸው አደጋዎች

ዘ ቶሮንቶ ስታር “የካናዳ የደም ባንኮች ለሺህ ዓመታት ጥብቅ የሆነ ምርመራ ቢደረግባቸው እንኳን ደም መውሰድ አደጋ ማስከተሉ አይቀርም” ሲል ዘግቧል። የሴይንት ማይክል ሆስፒታል ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ዊልያም ኖብል የካናዳን የደም ባንኮች አስተማማኝነት ለመመርመር በተቋቋመው ኮሚሽን ፊት ቀርበው በሰጡት የምሥክርነት ቃል “አሁንም አደገኛ ነው፣ ወደፊትም ቢሆን አደገኛ እንደሆነ ይኖራል” ብለዋል። ስታር ደም መውሰድ የሚያስከትላቸው አደጋዎች “ከአለርጂ አንስቶ በኤድስ እስከ መለከፍ ድረስ ያሉትን ሁሉ” የሚያካትቱ ናቸው ይላል። ደም ለበሽተኞች በመስጠት ሥራ የተሰማሩ ጠበብት በዛሬው ጊዜ በሚወስዱት ደም ምክንያት ኤድስ እንዳይዛቸው የሚፈሩ ሰዎች ቁጥር እየበዛ እንደመጣ ይናገራሉ። ዶክተር ኖብል “‘ደም ልስጥ ወይስ አልስጥ?’ ብለን ያልተወያየንበት አንድም ቀን የለም” ብለዋል።

“ገና ያልታወቀችው ፕላኔት”

በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ በአማዞን ደን ውስጥ ከዚህ በፊት የማይታወቁ ሦስት ዓይነት የዝንጀሮ ዝርያዎች ተገኝተዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በአማካይ በየዓመቱ ሦስት ዓይነት አዳዲስ የአእዋፍ ዝርያዎች ይገኛሉ። በፓናማ በ19 ዛፎች ላይ በተደረገ ጥናት 1,200 የሚያክሉ የጥንዚዛ ዝርያዎች ተገኝተዋል። 80 በመቶ የሚያክሉት ከዚህ በፊት የማይታወቁ ዝርያዎች ናቸው። ዩኔስኮ ሶርስስ የተባለው መጽሔት “ገና ያላወቅናቸው በጣም በርካታ የሆኑ ሕያዋን ፍጥረታት አሉ” ብሏል። ለምሳሌ ያህል “በደቡብ አሜሪካ ጨዋማ ባልሆኑ ወንዞችና ሐይቆች ከሚገኙት ዓሣዎች መካከል 40 በመቶ የሚያክሉት ጥናት ተደርጎባቸው እንደየዝርያቸው ያልተመደቡ ናቸው። . . . እምብዛም ጥናት ባልተደረገበት የውቅያኖሶች ጥልቀት ውስጥ ምን ያህል በርካታ ሕያዋን ፍጥረታትን እናገኝ ይሆን?” እንደ ባክተሪያ፣ ፈንገስ፣ ኔማቶድ፣ አራክኒድና ኢንሴክት በመባል የሚታወቁትን ጥቃቅን ፍጥረታት እንዲሁም ገና ምንነታቸው ያልታወቁትን በርካታ ዕፀዋት ስንመለከት ችግሩ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ልንገምት እንችላለን። “በሐሩር ክልል ውስጥ በሚገኝ አንድ ግራም አፈር ውስጥ ብቻ 90 ሚልዮን የሚያክሉ ባክተሪያዎችና ሚክሮቦች ይኖራሉ።” አንዳንዶች እንደሚገምቱት በምድር ላይ “200 ሚልዮን የሚያክሉ ዝርያዎች ይኖራሉ” በማለት ዩኔስኮ ሶርስስ ገልጿል። መጠነ ሰፊ ምርምር የተካሄደ ቢሆንም አሁንም ምድር “ገና ያልታወቀች ፕላኔት” ነች።

በዩናይትድ ስቴትስ

ዋነኞቹ የሞት ምክንያቶች

በዩናይትድ ስቴትስ ዋነኞቹ የሞት ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ዘ ጆርናል ኦቭ ዘ አሜሪካን መዲካል አሶሲዬሽን ላይ በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ዋነኞቹን ውጪያዊ የሆኑ ወይም ከዘር ውርሻ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው የሞት ምክንያቶች ለማወቅ ሞክሮ ነበር። ሰፋ ያለ ስታትስቲካዊ ጥናት ከተደረገ በኋላ በ1990 በዩናይትድ ስቴትስ ከሞቱት 2,148,000 ሰዎች መካከል 400,000 የሚሆኑት በትንባሆ፣ 300,000 የሚሆኑት በአመጋገብና በአካላዊ እንቅስቃሴ ልማዶች፣ 100,000 የሚያክሉት በአልኮል፣ 90,000ዎቹ በሚክሮቦች፣ 60,000 የሚያክሉት በምግብና በውኃ ውስጥ በሚገኙ መርዛማ ቅመሞች፣ 35,000ዎቹ በጦር መሣሪያ፣ 30,000ዎቹ በወሲባዊ ልማድ፣ 25,000ዎቹ በተሽከርካሪ አደጋ፣ 20,000ዎቹ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ መድኃኒቶች በመውሰድ ምክንያት እንደሆነ ደምድሟል። ጥናቱ በአጠቃላይ በአንድ ዓመት ውስጥ ከሞቱት ሰዎች መካከል ግማሽ የሚሆኑት የሞቱት በእነዚህ ውጪያዊ ምክንያቶች እንደሆነ አረጋግጧል።

በጨው ውስጥ የሚገኘው አዮዲን

የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እንደገመተው በሚመገቡት ምግብ ውስጥ አዮዲን የተባለውን ማዕድን በማጣታቸው ምክንያት ጤንነታቸው የተቃወሰባቸው ሰዎች ብዛት 600 ሚልዮን ይደርሳል። ከእነዚህ ተጎጂዎች መካከል በየዓመቱ 100,000 የሚያክሉ ጨቅላ ሕፃናት በደረሰባቸው በጣም ከባድ የሆነ የአዮዲን እጦት ምክንያት አካለ ስንኩል ሆነውና ያልዳበረ አእምሮ ይዘው ይወለዳሉ። 50 ሚልዮን የሚያክሉ ሌሎች ሕፃናት ደግሞ በአዮዲን እጦት ምክንያት የአእምሮአቸውና የአካላቸው እድገት አዝጋሚ ይሆናል። በተጨማሪም እንቅርት የሚመጣው በአዮዲን ጉድለት ምክንያት ነው። የአዮዲን እጦት እንዳይደርስ በቀላሉ መከላከል የሚቻል ሲሆን ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ነገርም አይደለም። አዮዲን ያለበት ጨው መመገብ ብቻ ነው። በ1995 የዓለም ሕዝብ የሚመገበው ጨው በሙሉ አዮዲን ያለበት እንዲሆን ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ከመሆኑም በላይ እስከ 2000 ዓመት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በአዮዲን እጦት ምክንያት የሚደርሰውን የጤና ቀውስ ጨርሶ ለማጥፋት ይሞከራል።

የሚያደነቁር ድምፅ

ከዓለም ሕዝብ መካከል ቢያንስ ቢያንስ 10 በመቶው መጠኑ ይብዛም ይነስ የመስማት ችግር አለበት። በብራዚል እየታተመ የሚወጣው ግሎቦ ሴንሲያ የተባለው መጽሔት “የሰው ልጅ ጆሮ ዘመናዊ መሣሪያዎች የሚፈጥሯቸውን ኃይለኛ ድምፆች መቋቋም እንዲችል ተደርጎ አልተሠራም” ሲል ገልጿል። በተጨማሪም አንድ ሰው በየዕለቱ ጆሮ ለሚያደነቁሩ ድምፆች የተጋለጠ ከሆነ በአንድ ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ ሊቸግረው፣ ምርታማነቱ ሊቀንስ፣ ሊበሳጭ እንዲሁም በሥራው ላይ አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል።

‘የመጨረሻው ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት’

የሮማ ዕለታዊ ጋዜጣ የሆነው ላ ሪፑብሊካ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በቅርቡ 30 የሚያክሉ አዳዲስ ካርዲናሎችን ከሾሙ በኋላ በጻፈው ዘገባ “በጀርመን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቫቲካን ወግ አጥባቂነት ላይ የሚሰማው ቅሬታ እየጨመረ ሄዷል” ብሏል። ተቃዋሚ የሆኑት ዝነኛው የሃይማኖት ምሁር ሃንስ ኩንግ የሚቀጥለውን ጳጳስ ለመምረጥ “መላይቱን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በትክክል የሚወክሉ የመራጮች አካል መመሥረት ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው” ይላሉ። ኩንግ “ሊቀ ጳጳሱ የበርካታ አማኞችን አመኔታ” እንዳጡ ያምናሉ። ኩንግ ሐሳባቸውን በመቀጠል “ስታሊንዝም ከተንኮታኮተ ወዲህ በምዕራቡ ዓለም የቀረው የመጨረሻ ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት የሮማ ካቶሊክ ሥርዓት መሆኑን ችላ ማለት አይቻልም” ብለዋል።

ከሳንባ ነቀርሳ ጋር በሚደረገው ውጊያ መሸነፍ

በፓሪስ የሚገኘው የላ ፒትዬ ሳልፔትርየር ሆስፒታል የባክተሪዮሎጂና ቫይሮሎጂ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ዣክ ግሮሴ በአጠቃላይ ከበሽታ ጋር ያደረግነው ጦርነት በተለይም ከሳንባ ነቀርሳ ጋር ያደረግነው ውጊያ “በመላው ዓለም ከሽፏል” ብለዋል። በበሽታው ከሚለከፉት ሰዎች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት ምንም ሕክምና ባይደረግላቸው ይሞታሉ። በበሽታው ከሚሰቃዩት የዓለም ሰዎች መካከል ግማሽ የሚሆኑት ምርመራም ሆነ ሕክምና ለማግኘት የማይችሉ ሲሆኑ በጣም አሳሳቢ የሆነው ግን በቴክኖሎጂ በተራመዱና አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች እንደ ልብ በሚገኙባቸው አገሮች ከሚኖሩ በሽተኞች ሙሉ በሙሉ እስኪድኑ ድረስ መድኃኒት የሚወስዱት ግማሽ የሚሆኑት ብቻ መሆናቸው እንደሆነ ፕሮፌሰር ግሮሴ ገልጸዋል። “ግማሽ የሚሆኑት ሕክምናቸውን ጨርሶ አይወስዱም ወይም የሚወስዱት አልፎ አልፎ ብቻ ነው። በዚህ ምክንያት የሟቾች ቁጥር ይጨምራል፣ (ሕክምና ከተሰጣቸው ሰዎች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ይሞታሉ) እንዲሁም አንቲባዮቲክ የማያሸንፋቸው የቱበርክል ባሲለስ ዝርያዎች እንዲገኙ ያደርጋል።”

በ40 ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ80,000 የሚበልጡ የመሬት ነውጦች

ፍራንክፉርተር አልገማይነ ሳይቱንግ “በኮሎኝ አካባቢ [ጀርመን] የሚገኘው የበንስበርግ የመሬት ነውጥ መቆጣጠሪያ ማዕከል በመላው ዓለም ከ80,000 በላይ የሚሆኑ የመሬት ነውጦችን መዝግቧል” በማለት ዘግቧል። ይህን ያስታወቁት ለ40 ዓመታት የመሬት ነውጦችን ሲመዘግብ የቆየው የዚህ ጣቢያ ኃላፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ሉድቪግ አሆነር ናቸው። ጣቢያው በሌሎች የዓለም ክፍሎች የደረሱትን የመሬት ነውጦች ሊመዘግብ የሚችለው እንዴት ነው? 200 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በሚገኘው የሰሜን ባሕር ጠረፍ የባሕር ሞገድ ከመሬት ጋር በመላተሙ ምክንያት የሚደርሰውን የመሬት መርገብገብ እንኳን ሊለኩ የሚችሉ በጣም የተራቀቁ መሣሪያዎችን በመጠቀም ነው። ጣቢያው ከመዘገባቸው በጀርመን አገር ከደረሱት የመሬት ነውጦች መካከል ከፍተኛው በሚያዝያ ወር 1992 የደረሰው ነው። ነውጡ በሪክተር መለኪያ 5.9 የደረሰ ነበር።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ