የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g96 7/8 ገጽ 27-29
  • ስርቆት ተገቢ ያልሆነው ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ስርቆት ተገቢ ያልሆነው ለምንድን ነው?
  • ንቁ!—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሚሰርቁበት ምክንያት
  • ስሜታዊ ሥቃይን ለመደበቅ ያስችላልን?
  • እኩዮችና የሚያሳድሩት ተጽዕኖ
  • የአምላክን አመለካከት መያዝ
  • ፈተናውን መዋጋት
  • ድህነት ለስርቆት ማሳበቢያ ሊሆን ይችላልን?
    ንቁ!—1998
  • ስርቆት እየጨመረ ያለው ለምንድን ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ሌባ እንዳትሆን ተጠንቀቅ!
    ከታላቁ አስተማሪ ተማር
  • በእርግጥ ስርቆት ነውን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1996
g96 7/8 ገጽ 27-29

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ስርቆት ተገቢ ያልሆነው ለምንድን ነው?

“ዕድሜዬ 16 ዓመት ነው፤ አንድ ትልቅ ችግር አለብኝ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ መስረቅ ጀምሬአለሁ። አሁን እንኳ ወደ ገበያ ማዕከሉ ሄጄ ሰባት ጥንድ የጆሮ ጉትቻዎችን ሰርቄያለሁ። ስለ ችግሬ ለሰው እንዳልናገር እፈራለሁ። እባካችሁ እርዱኝ!”

አንዲት በጣም የተጨነቀች በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ ወጣት ለአንድ መጽሔት የምክር አምድ የጻፈችው ከላይ እንዳለው በማለት ነበር። አንድ ጸሐፊ የሚከተለውን ሪፖርት አቅርበዋል:- “[በዩናይትድ ስቴትስ] ውስጥ በየዓመቱ በግምት አሥር ቢልዮን ዶላር የሚያወጡ ለሽያጭ የሚቀርቡ ዕቃዎች . . . ከችርቻሮ ንግድ ሱቆች ይዘረፋሉ፣ አለዚያም በማጭበርበር ወይም ደግሞ በሌላ መንገድ ይሰረቃሉ። ሱቅ ውስጥ ሲሰርቁ ከሚያዙት መካከል ግማሽ የሚያህሉት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።”

በቅርቡ በተደረገ በሕዝብ አስተያየት ላይ በተመሠረተ አንድ ጥናት መሠረት ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሆኑት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከሱቅ እንደሚሰርቁ አምነዋል። በተጨማሪም ጃን ኖርማንና ማይረን ሃሪስ በተባሉ ተመራማሪዎች የተካሄደ በሌላ የሕዝብ አስተያየት ላይ የተመሠረተ ጥናት እንዳመለከተው “ሁሉም [ወጣቶች] ማለት ይቻላል ምንም ሳይከፍሉ ዕቃ የወሰዱበት ጊዜ እንዳለ አምነዋል።”

የሚሰርቁበት ምክንያት

ሌባ የአንድ ግለሰብ ንብረት የሆነውን ነገር ሆን ብሎ ሳያስፈቅድ የሚወስድ ሰው ነው። አንዳንድ ጊዜ በግል ችግር ምክንያት ስርቆት ተገቢ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ድህነት ያጠቃው አንድ ወጣት እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነበርኩ። [ፈጣን ምግብ ወደሚዘጋጅበት ሬስቶራንት] ውስጥ በጀርባ በኩል በሩን ሰብሬ እገባና ጥቂት የተጠበሰ የዶሮ ሥጋ እወስዳለሁ። ሆኖም ከዚህ ሌላ ምንም የማደርገው ነገር አልነበረም። ይህንንም የማደርገው ይርበኝ ስለነበረ ነው።”

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ሌባ በተራበ ጊዜ ነፍሱን ሊያጠግብ ቢሰርቅ ሰዎች አይንቁትም” ይላል። ሆኖም መስረቅ በሥነ ምግባር ደረጃ ስሕተት ነው። ስለዚህ የሚቀጥለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሌባው የሰረቀው ርቦት ቢሆንም እንኳ ከባድ ቅጣት በመክፈል ‘መተካት’ እንደሚኖርበት ይገልጻል።— ምሳሌ 6:30, 31

የሚያስገርመው ግን በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ከሚገኙት ሌቦች መካከል በችግር ምክንያት የሚሰርቁት ጥቂቶች ናቸው። እንዲህ በማለት የተናገረችው ወጣቷ ሜሪ ጄን ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ነች:- “አዎን፣ ከሱቅ እሰርቅ ነበር፤ ይህን የማደርገው ለምን እንደሆነ ስለማላውቅ ሁኔታው ግራ የሚያጋባ ነበር። ወላጆቼ ለማንኛውም ነገር የሚያስፈልግ ገንዘብ ይሰጡኝ ነበር። ምንም ነገር አልተቸገርኩም ነበር።”a ሰቨንቲን የተባለው መጽሔት የሚከተለውን ተመሳሳይ ሪፖርት አቅርቧል:- “በብሔራዊ የወንጀል መከላከያ ኮሚቴ የተካሄደ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ጥፋተኞቹ የሚያቀርቡት የተለመደ ምክንያት አንድን ነገር በነፃ ማግኘት ስለምንፈልግ ነው የሚል ነው።” እንዲያውም አንዳንድ ወጣቶች ሱቆቹ ‘ከመጠን በላይ የሆነ ዋጋ ይጠይቃሉ’ በማለት ለማይጾም እጃቸው ሰበብ ያቀርባሉ!

ብዙ ወጣቶች የሚሰርቁት ከስልቹነት ለመዳን ነው። ቀደም ሲል ሌባ የነበረው ጄርሚ የተባለ አንድ ወጣት “ከትምህርት ሰዓት በኋላ እንዲሁ ጊዜ የማሳልፍበት ነገር ነበር” በማለት ገልጿል። በተጨማሪም ስርቆት አደገኛ ቢሆንም እንኳ እንደ ጨዋታ ተደርጎ የሚታይ ይመስላል፤ አንዳንዶች ሸሚዝ ወይም ኮምፓክት ዲስክ ሰርቀው ቦርሳቸው ውስጥ ሲከቱ ፍርሃቱ በውስጣቸው በሚፈጥረው ስሜት ይደሰታሉ።

ስሜታዊ ሥቃይን ለመደበቅ ያስችላልን?

እርግጥ ራስን በእስር አደጋ ላይ ሳይጥሉ የስልቹነትን ስሜት ለመዋጋት የሚያስችሉ አደገኛ ያልሆኑ ዘዴዎች አሉ። ታዲያ ትንሽ ለመጫወት ከመፈለግ በስተጀርባ እንዲህ ዓይነቱን ደስታ ለመሻት የሚያነሣሱ ሌሎች ምክንያቶች ይኖሩ ይሆን? ብዙ ጠበብቶች ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ ያምናሉ። ሌዲስ ሆም ጆርናል የተባለው መጽሔት አንዳንድ ወጣቶችን አስመልክቶ የሚከተለውን ገልጿል:- “ወደ ጉልምስና ማደግ የሚያስከትላቸውን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ መቋቋም ይቸግራቸዋል። ከወላጆቻቸው ጋር መጣላታቸው፣ ከጓደኛቸው መለያየታቸውና በፈተና ዝቅተኛ ውጤት ማምጣታቸው ሕይወታቸውን መምራት እንደተሳናቸው እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል፤ ሕጎችን ሲጥሱ ኃይል እንዳላቸው ይሰማቸዋል።”

አዎን፣ አንድ ሌባ ላይ ላዩን ከሚያሳየው ድፍረት በስተጀርባ ብዙ ጉዳትና ሥቃይ ሊኖርበት ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “በሳቅ ጊዜም ልብ በሐዘን ሊዋጥ ይችላል።” (ምሳሌ 14:13 አዓት) በተደጋጋሚ ጊዜያት ከሱቅ መስረቅ የመንፈስ ጭንቀት ምልክት ሊሆን እንደሚችል ማስረጃዎች ያሳያሉ። እንዲያውም አንዳንድ ወጣት ሌቦች በልጅነታቸው የተለያየ በደል የደረሰባቸው እንደሆኑ ተደርሶበታል። የሥቃዩ መንስኤ ምንም ይሁን ምን በስርቆት የሚያገኙት ደስታ ቢያንስ ለጊዜው ያህል ሥሜታዊ ስቃይን የሚያስታግሥ ሊመስል ይችላል።b ለምሳሌ ያህል መኪናዎችን ሰርቆ በከፍተኛ ፍጥነት እየነዳ ለመዝናናት የሚጠቀምባቸውን አንድ አሜሪካዊ ወጣት እንውሰድ። እንዲህ አለ:- “ደስ ይላል። በምትፈራበትና ዕፅ በምትወስድበት ወቅት እንደሚያድርብህ ዓይነት ስሜት ይሰማሃል።”

እኩዮችና የሚያሳድሩት ተጽዕኖ

መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ይህ እውነት በሰፊው ተቀባይነት አግኝቷል። ዴኒዝ ቪ ላንግ የተባሉ ጸሐፊ “አንድ ወጣት በራሱ ተነሣስቶ ችግር ውስጥ የሚገባው አልፎ አልፎ ብቻ ነው” የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። ብዙውን ጊዜ እኩያሞች “እስቲ ልብ ካለህ . . .” በሚል አነጋገር አንዱ ሌላውን ለስርቆት ይገፋፋዋል። ብዙ ወጣቶች ለዚህ ተጽዕኖ መንበርከካቸው ያሳዝናል።

ወጣቷ ካቲ “በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከሚገኝ አንድ የወጣት ሴቶች ቡድን ጋር ተቀላቀልኩ” ብላለች። የቡድናቸው አባል ለመሆን ምን መክፈል ያስፈልግ ነበር? አንድ ውድ የሆነ ሹራብ ሰርቆ መክፈል ያስፈልግ ነበር። “እዚህ ቡድን ውስጥ መግባት ስለፈለግሁ ወደ አንድ ሱቅ ሄድኩና ሹራቡን ሰረቅሁ” በማለት የፈጸመችውን ነገር ገልጻለች።

የአምላክን አመለካከት መያዝ

ልትገዛው የማትችለውን ነገር የራስህ ንብረት ለማድረግ መቻል፣ አጉል ጀብዱ በመሥራት መደሰት ወይም በእኩዮች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ስርቆትን አጓጊ እንደሆነ ነገር ተደርጎ እንዲታይ ሊያደርጉት ይችላሉ። ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት አሥርቱ ትእዛዛት አንዱ “አትስረቅ” ይላል። (ዘጸአት 20:15) ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ሌቦች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም’ በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 6:10) በተለይ ክርስቲያን ሆነው ያደጉ ወጣቶች የአምላክ አመለካከት ሊያሳስባቸው ይገባል። ጻድቅ መስሎ በድብቅ የሌብነት ተግባር ማከናወን ምንኛ ግብዝነት ነው! ሐዋርያው ጳውሎስ ጉዳዩን እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል:- “አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን?”— ሮሜ 2:21

ሲሰርቁ መያዝ የሚያስከትለው ውርደት መጥፎ ምግባር ከሆነው ስርቆት ለመራቅ በቂ ምክንያት ይሆናል። አንድ ወጣት ሌባ ከተያዘ በኋላ “ሞት ተመኝቼ ነበር” ብሏል። ይሖዋ ‘ስርቆትን እንደሚጠላ’ ማወቅ ለስርቆት የሚገፋፋንን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያስችል ከሁሉ የተሻለ ጠንካራ ምክንያት ነው። (ኢሳይያስ 61:8) አንድ ሰው መስረቁን ከሱቅ ሠራተኞች፣ ከፖሊስና ከወላጆች ሊደብቅ ቢችልም ከይሖዋ ሊሸሽግ አይችልም። መጋለጡ የማይቀር ነው።— ኢሳይያስ 29:15

በተጨማሪም ኃጢአት መሥራት የአንድን ግለሰብ ልብ እንደሚያደነድን አትርሳ። (ዕብራውያን 3:13) ትንሽ ነገር መስረቅ እንኳ የኋላ ኋላ ኀፍረተ ቢስ ወደ መሆንና አጓጉል የሆኑ ተግባራትን ወደ መፈጸም ይመራል። ለምሳሌ ያህል ወጣቱ ሮጀር የወንጀል ድርጊቶች መፈጸም የጀመረው ከእናቱ ቦርሳ ገንዘብ በመስረቅ ነበር። ከጊዜ በኋላ አረጋውያን ሴቶችን ገፍትሮ እየጣለ ቦርሳቸውን መስረቁን ቀጠለ።

ፈተናውን መዋጋት

አንድ ሰው በድብቅ መስረቅ ከጀመረ ስርቆትን ማቆም ቀላል ላይሆንለት እንደሚችል እሙን ነው። አንድ ወጣት “እንደ ሱስ ያለ ነገር ነው ማለት ይቻላል” በማለት ተናግሯል። አንድን ወጣት አካሄዱን እንዲለውጥ ሊረዳው የሚችለው ነገር ምንድን ነው?

ኃጢአትህን ለአምላክ ተናዘዝ። አምላክ ከኃጢአታቸው ንስሐ የሚገቡና ለእርሱ በግልጽ የሚናዘዙ ሰዎችን ‘ይቅር ይላቸዋል።’— ኢሳይያስ 55:7

እርዳታ ጠይቅ። ብዙዎቹ የዚህ መጽሔት አንባብያን በአካባቢያቸው ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የክርስቲያን ጉባኤ ጋር ይተዋወቃሉ። እነዚህ ግለሰቦች ወደ ጉባኤው ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ሄደው መንፈሳዊ እርዳታና እርማት ሊጠይቁ ይችላሉ። (ያዕቆብ 5:14, 15) ጥሩ የሥነ ምግባር መመሪያ የሚሰጡ ወላጆችም የእርዳታና የድጋፍ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህን እኩይ ተግባር እንዲፈጽሙ የሚገፋፋቸው የደረሰባቸው በደል፣ ሥቃይ ወይም የስልቹነት ስሜት ከሆነ በርኅራኄ ለሚያዳምጣቸው ሰው ጉዳዩን ማዋየት በጣም ሊጠቅም ይችላል።— ምሳሌ 12:25

ካሳ ክፈል። በሙሴ ሕግ ሌቦች የሰረቋቸውን ነገሮች ከወለድ ጋር የመክፈል ግዴታ ነበረባቸው። (ዘሌዋውያን 6:4, 5) ተመሳሳይ ነገር ማድረግ የግለሰቡን ሕሊና ንጹሕ እንዲሆን የሚረዳ ከመሆኑም በላይ ስርቆት በሌሎች ሰዎች ላይ የሚያስከትለውን ችግር እንዲገነዘብ ያስችለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ግለሰብ “የነጠቀውንም ቢመልስ በሕይወትም ትእዛዝ ቢሄድ . . . በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም” የሚል ተስፋ ይሰጣል።— ሕዝቅኤል 33:15

የቅናት ስሜትንና ስግብግብነትን አስወግድ። የአሥርቱ ትእዛዛት የመጨረሻው ትእዛዝ “ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ” የሚል ነው። (ዘጸአት 20:17) እጅግ የተቸገርክበት ወይም የምትፈልገው ነገር ካለና ልትገዛው የማትችለው ከሆነ ዕቃውን ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ ሠርተህ የምታገኝበትን መንገድ ልትፈልግ ትችል ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፣ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጐደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም” የሚል ምክር ሰጥቷል።— ኤፌሶን 4:28

አብረሃቸው የምትውላቸውን ሰዎች በጥንቃቄ ምረጥ። ዴኒዝ ላንድ የተባሉት ጸሐፊ “አንድ መጥፎ ነገር ከሚሠራ ጓደኛህ ወይም ጓደኞችህ ጋር ከሆንህ ከእነርሱ ጋር በመገኘትህ ብቻ አንተም ጭምር እንደ ጥፋተኛ ወይም ወንጀል እንደፈጸምክ ተደርገህ ትታያለህ” ብለዋል። እኩዮችህ አንድ ሕገ ወጥ የሆነ ተግባር እንድትፈጽም ሲጠይቁህ እምቢ ለማለት የሚያስችል ብርታት ይኑርህ።— ምሳሌ 1:10-19

ስርቆት በሌሎች ሰዎች ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት አስብ። ሌባ የሚያስበው ስለ ራሱ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” በማለት መክሮናል። (ማቴዎስ 7:12) አንድ ሰው ለሌሎች ሰዎች ማሰብን ሲማር በሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት የሚያስከትል ነገር የመፈጸም ዝንባሌው በጣም ይቀንሳል።

በአንተ ላይ የሚያመጣቸውን መዘዞች አስብ። (ገላትያ 6:7) ልትገዛቸው የማትችላቸውን የሚያብረቀርቁ ጌጣ ጌጦች ወይም መሣሪያዎች መውሰድ በጣም እንደሚያስደስት ከማሰብ ይልቅ ተይዞ ሕግ ፊት መቅረብ ምን ያህል አሳፋሪ እንደሆነ አስብ፤ በወላጆችህና በአምላክ ላይ የምታመጣውን ነቀፋ አስብ! መስረቅ ጥሩ አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ እንደምትደርስ አያጠራጥርም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።

b እዚህ ላይ በእንግሊዝኛ ክሌፕቶማኒያ በመባል የሚታወቀውን ለመስረቅ የሚገፋፋ ኃይለኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር የአእምሮ በሽታ መጥቀሳችን አይደለም። ዶክተሮች ክሌፕቶማኒያ እምብዛም እንደማይከሰትና ከሱቅ ሌቦች መካከል በዚህ ችግር የተጠቁት ከ5 በመቶ በታች እንደሚሆኑ ይናገራሉ። ይህ በሽታ ብዙውን ጊዜ በሕክምና ሊድን ይችላል።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሱቅ ሌቦች ብዙውን ጊዜ ተይዘው ውርደት ይከናነባሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ